
እንደ አስተዳደር ቦርዱ ሪፖርት የት/ቤቱ ገንዘብ ያዥ አቶ ሰለሞን የተባሉ ግለስብ ከወላጆች ይሰበስብ የነበረውን ወረሃዊ የተማሪዎች ክፍያ በቀድሞ የቦርድ አመራር ትእዛዝ ካዛና ውስጥ ያስቀምጥ እንደነበር እና ካዝናው ምንም አይነት ቁጥጥርም ሆነ ለአመታት ኦዲት ተደርጎበት እንደማያውቅ የሚያትተው ሪፖርት የቀድሞው ቦርዱ የስራ ጊዜውን ጨርሶ ከመሰናበቱ በፊት ወደ ካዛና እንዳይጠጉም ሆነ የገንዘብ ስም እንዳያነሱ የተደረጉበት ምክንያት ግራ ስላጋባቸው ገንዘብ ያዡ ለዕረፍት የሳውዲን ምደር ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ባደረጉት ክትትል የተጠቀሰውን የት/ቤት ገንዘብ ሻንጣ ውስጥ እንደ ታጨቀ ማግኘታቸውን አረጋግጠዋል።
ይህን ያህል ገንዘብ ያለምንም ዋስትና የት/ቤቱ ገንዘብ ያዥ እጅ እንዲቀመጥ የተደረገበት አግባብ እስካሁን በውል ባይታወቅም እጅ ከፍንጅ የተያዘው ጥሬ ገንዘብ ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል የሚናገሩ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ተጨማሪ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሳይዘረፍ እንዳልቀረ ይጠራጠራሉ ። በወቅቱ የት/ቤቱን ህንጻ በ 50 ሚልዮን ሪያል ለመግዛት በወላጆች ሃስብ ቀርቦ እንደነበር የሚያስታውሱ እነዚህ ውስጥ አውቂ ምንጮች ት/ቤቱ ካፒታል የለውም በሚል ሰበብ የአስተዳደር ቦርዱ ወላጆች ያቀረቡትን ሃስብ ውድቅ በማድረግ ት/ቤቱ በኪራይ እንዲቀጥል የወሰነበት ምክንያት የተጠቀሰውን ገንዘብ ለመዝረፍ ታስቦ እንደነበር ይገልጻሉ። በሪያድ አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ት/ቤት ከወላጆች እጅ ከወጣ ወዲህ ገቢና ወጪው በትክክል አይታወቅም የሚሉ ምንጮች ፤ በመቶ ሺህ ሪያል ( እስከ ሩብ ሚልዮን ብር) የሚቆጠር ጥሬ ገንዘብ በቦርድ አባላት ትእዛዝ በነጭ ወረቀት በቀላሉ ውጪ የሚደረግበት አሰራር እንዳለ ይናገራሉ።
ከ 2500 በላይ ኢትዮጵያውያን ህጻናት ተቀብሎ እንደሚያስተናገድ ስለሚነገርለት ዝነኛ የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ኮሚኒቲ ት/ቤት ከ 100 ለማይበልጡ ወላጆች ሪፖርቱን ያቀረበው አስተዳደር ቦርድ ቀደም ብሎ ሲሰራበት የነበረውን የፋይናስ ቁጥጥር በመለወጥ በአዲስ መልክ ዘረጋሁ ባለው ኔት ዎርክ ሲስተም ለት/ቤቱ ገቢ መሆን ከሚገባው ገንዘብ ውስጥ 100.000 ሪያል ወይም ( ከሩብ ሚልዮን ብር በላይ ) ጉድለት ማግኘቱን በመግለጽ ለዚህም ተጠያቂ የሆነው ግለሰብ 50.000 ሪያል ምህረት ተደርጎለት የቀረውን ገንዘብ በሂደት እንዲከፍል መወሰኑ አብዛኛውን ወላጆች አሳዝኖል። በሪያድ የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ኮሚኒቲ ት/ቤት የቦርድ አባል ሆኖ ሃገርቤት ህንጻ ያላነፀ ፡ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን ገዝቶ ያላከ ፡ አክሲዮን ያልገዛ የለም የሚሉት ምንጮች ግልጽነት እና ተጠያቂነት በሌለበት አሰራር ዛሬም ወላጆች በማያውቁት የአስተዳደር ቦርድ የሚዘወረው የት/ቤቱ ካዝናም ሆነ ት/ቤቱ ዋስትና እንደሌላቸው ይጠቁማሉ።

በሪፖርቱ ለትርፍ ሰዓትና ተለያዩ ወጪዎች 70.000 ሪያል ( 392000 ብር ) መመንዘሩን ከመግለጽ ውጭ ዝርዝር መረጃ ያላስቀመጠው የት/ቤቱ አስተዳደር ቦርድ የት/ቤቱን ፈቃድ ለማሳደስ ተጠይቆ የነበረውን እጅ መንሻ 20.000 ሪያል ( መቶ ሺህ ) ብር ማስቀረቱን ሽፋን መስጫ በማድረግ ወላጆችን ለማደናገር ሞክሯል የሚሉ ምንጮች በቀጣይ አመት የት/ቤቱ ህንጻ ካልተለወጠ እስከነ አካቴው ፈቃዱ ሊሰረዘ እነደሚችል እና የት/ቤቱ የመማር ማስተማር ሰረአት ሊስተጓጎል እንደሚችል ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት መቻሉን ገልጸዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ህልውናው አደጋ ላይ እየወደቀ የመጣውን የህዝብ ት/ቤት ለባለ ሃብቶች ለመሸጥ እቅድ እንዳለ ከአስተዳደር ቦርዱ አመራር አባላቱ ሾልኮ ከወጣ ሚስጥራዊ መረጃ ማረጋገጥ ተችሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ ለስራ ጉዳይ ሃገር ቤት የሄዱት የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አብዱል ባሴጥ አብዱል ጀማል ተመልሰው ሳውዲ እንዳይገቡ የተፈፀመው ሴራ ከ 37 ሚልዮን ሪያሉ ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው እስካሁን በውል ባይታወቅም ርዕሰ መምህሩ ላይ በላግ ( wonted )ያስደረገውን አካል ለመያዝ በሳውዲ ፖሊስ እየተጣራ መሆኑና ወደፊት በህግ እንደሚጠየቅ ርዕሰ መምህሩ የሰጡትን መረጃ ዋቢ በማድረግ ውስጥ አዋቂ ምንጮች አክለው ገልፀዋል። ኢንጂነር መሃመድ አባስ ከሪያድ