Thursday, June 16, 2016

ኤርትራ “200 የኢትዮጵያ ወታደሮችን ገድዬ 300 አቆስለኩ” አለች

 ቢቢሲ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን ገልጾ እንደዘገበው ኤርትራ በ2 ቀን ጦርነት 200 የኢትዮጵያ ወታደሮችን ገድላ 300 ማቁሰሏን አስታወቀች::
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባለፈው እሁድ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በጾረና በኩል ጥቃት ፈጸመብኝ ማለቱ ይታወሳል::
እንደሚኒስትሩ መግለጫ እሁድ እና ሰኞ ዕለት በተደረገው ጦርነት 200 ሰዎችን መግደሉን ይገልጽ እንጂ ከራሱ በኩል የተጎዱ ወይ የሞቱ ወታደሮች እንዳሉ የገለጸው ነገር የለም::

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ለኤርትራ መንግስት እስካሁን ለፈጸመው ትንኮሳ ተመጣጣኙን እርምጃ ሰጥተነዋል:: ወደፊትም እንደ ኤርትራ መንግስት እንቅስቃሴ ጦራችንን እናንቀሳቅሳለን ማለቱን ዘ-ሐበሻ መዘገቧ አይዘነጋም::
የመንግስት ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ በዚህ ሳምንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም ከኤርትራ ጋር ወደለየለት ጦርነት መግባት የኢትዮጵያ ምርጫ አይደለም ማለታቸው ይታወሳል::
ኢትዮጵያና ኤርትራ ከ1998 – 2000 ዓ.ም ድረስ ባደርጉት የድንበር ግጭት ከ100 ሺህ ሰዎች በላይ ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ::(ዘ-ሐበሻ) ቢቢሲን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው 

Wednesday, June 15, 2016

ሰይፉ ፋንታሁን ታሰረ – ነገ ሊፈረድበት ነው


ሰይፉ ፋንታሁን በቀረበበት ሀሰተኛ ወሬ የማሰራጨት ክስ በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ሰይፉ በመናገሻ ምድብ ችሎት ፍርድ ቤት ዛሬ በቀረበበት ወቅት ‹‹አዎ ድርጊቱን ፈፅሜያለሁ›› በማለት የእምነት ቃሉን እንደሰጠ ምንጮቻችን ገልፀውልናል፡፡ ፍርድ ቤቱም ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ መፈፀሙን በማመኑ የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ቀጠሮ ሰጥቶ ተከሳሹ በቁጥጥር ስር እንዲቆይ አዟል፡፡ በዚህ መሰረት ሰይፉ ፋንታሁን በአሁኑ ወቅት በጉለሌ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ይገኛል፡፡ በነገው ዕለት በሚውለው ችሎት የእስር ወይንም የገንዘብ ቅጣት ሊጣልበት ይችላል፡፡
ለክስ የዳረገው ጉዳይ በቴዎድሮስ ተሾመና ቴዎድሮስ ተሾመ ድርሰቴን ሰርቆኛል ብለው ክስ በመሰረቱት ግለሰብ ዙሪያ በሬዲዮ ያሰራጨው ወሬ ነው፡፡ የሁለቱ ግለሰቦች ክስ በፍትሀብሄር እየታየ በነበረበት ሰዓት ሰይፉ በችሎት ያልተባለን ነገር ተብሏል ብሎ በማውራቱ ነው የተከሰሰው፡፡
ከዚህ ቀደም ሳያት አህመድ በዚሁ ፍርድ ቤት ሰይፉ ላይ ክስ አቅርባ እንደነበርና ጉዳዩ በሽምግልና ተድበስብሶ እንዲቀር መደረጉ ይታወሳል፡፡