Friday, January 3, 2014

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ልዩ ጉባኤው የአቋም መግለጫ


January 3/2014

ዛሬ በደረስንበት 21ኛው ክፍለዘመን በአለማችን የሚገኘው ሕዝብ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ በተከበሩበት ሁኔታ መመራት ይሻል፡፡ በዚህ ዘመን አምባገነን መሪዎችና መንግስታት በየትኛውም መስፈርት ስልጣን ላይ የመቆየት እድል የላቸውም፡፡ በዚህ ረገድ በቅርብ አመታት ውስጥ የማይደፈሩና እንደ ፈርኦን ይመለኩ የነበሩ አምባገነን መንግስታት በህዝባዊ ማዕበል ተጥለቅልቀውና ተንጠው መቀመቅ ሲወርዱ የአለም ህዝብ ሁሉ አስተውሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዲሞክራሲና የነፃነት ጥየቄ ከዳቦ ጥያቄ ይበልጥ አንገብጋቢ እየሆነ መጥቷል፡፡

የአለማችን አንድ አካል የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ የዘመናት የስልጣኔ ጉዞዋ የምድራችን ቁንጮ የታሪክ ባለቤት ያደርጋታል፡፡ በየዘመናቱ የተነሱ ገዢዎቻችን ሲጭኑብን የቆዩት የአገዛዝ ቀንበር ወገባችንን ቢያጎብጠውም የኢትዮጵያ አንድነትና ሉኣላዊነት ፍፁም ሳይሸራረፍ ተጠብቆ ዘመን እንዲሻገርና ለትውልድ እንዲተላለፍ የማይሻ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡

ወታደራዊው ደርግ ከሥልጣን በተወገደ ማግስት ዲሞክራሲና ነፃነት የሰፈነበት የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩባትን ኢትዮጵያ ለማየት ያልጓጓ ኢትዮጵያዊ አልነበረም፡፡ ህልማችን በእውነት ሳይፈታ ቀረ፣ ተስፋ ያደረግነው ነገር ከዓመት ዓመት እየጨለመ መጣ፡፡ ኢህአዴግ ባለፉት 23 ዓመታት የምኒሊክን ቤተመንግስት ቢቆጣጠርም የአገርን ህልውና ከመጠበቅና የህዝብ እንባን ከማበስ ይልቅ ዜጎችን መውጪያ መግቢያእያሳጣና የመከራን ገፈት እያስጨለጠ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ ስደቱ፣ እንግልቱ፣ ግርፋቱ፣ እስራቱ፣ ግድያው፣ አፈናው፣ ስቃዩ ከመቀነስ ይልቅ በየጊዜው እየከፋ ይገኛል፡፡

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ይህን ቀንበር ለመስበር እንደ መርፌ ቀዳዳ በጠበበው የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እየተንቀሳቀሰ በመላው አገሪቱ ህዝብን ለትግል እያሰለፈ ይገኛል፡፡

ይህን እልህ አስጨራሽ ትግል ለመምራት ትልቁ የስልጣን አካል የሆነው ይህ ጠቅላላ ጉባኤ ታህሳስ 19 እና 20 / 2006 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ባደረገው ከፍተኛ ስብሰባ አያሌ አገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ተወያይቷል፡፡ የፓርቲውን ምክር ቤት ፣ የሥራ አስፈፃሚና የኦዲት ኮሚሽንን ሪፖርት በማድመጥ ጠንካራ ውይይት አካሂዷል፡፡

በመጨረሻም የአገልግሎት ዘመናቸውን ባጠናቀቁት የፓርቲው ፕሬዚደንት የተከበሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ምትክ የተከበሩ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውን ፍፁም ግልፅና ዲሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ተክቷል፡፡ የፓርቲውን ብሔራዊ ምክር ቤት እና የኦዲት ኮሚሽን አባላትንም በመምረጥ ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

አባላቱ በጉባኤው ማጠናቀቂያ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚከተለውን የአቋም መግለጫና ውሳኔ በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡
1ኛ. ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በአገሪቱ የሚደረገውን የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ለማኮላሸት ነጋ ጠባ የሚያጠነጠነው እኩይ ሴራ የህዝቡን ስሜት ወደ ሌላ አቅጣጫ እና ጥግ እየገፋው ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲያችን አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በጀመረው የሰላማዊ ትግል ጉዞ የኢትዮጵያን ህዝብ የስልጣን ባለመብት ለማድረግ እስከመጨረሻው እንጥፍጣፊ በጥብቅ መታገል እንደሚኖርበት ይታመናል፡፡ በመሆኑም እኛ ከመላው አገሪቱ በዚህ ጉባኤ ላይ የታደምን የፓርቲ አባላትና አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ለሰላማዊ ትግሉ ቁርጠኛ መሆናችንን እናረጋግጣለን፡፡

2ኛ. አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት የፓርቲያችንን እንቅስቃሴዎች እግር በእግር እየተከታተለና በሀሰት ውንጀላ በማጠልሸት በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳናገኝ ጠቅልሎ በያዘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሰፊ የሆነ አፍራሽ ተልዕኮን እያስተጋባ ይገኛል፡፡ይህ ጉዳይ ህገ መንግስቱ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ያመቻቸውን መንገድ ሙሉ ለሙሉ የሚጠቅም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አገር እየመራሁኝ ነው የሚለው ኢህአዴግ ፓርቲያችንን ከሽብር ድርጊት ከአሸባሪዎች ጋር ለማቆራኘት የሚያደርገውን እኩይ ሴራ አጥብቀን እናወግዛለን፡፡

3ኛ. በዚህ ልዩ ጉባኤ ወቅት በአካል በመቅረብ በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ካድሬዎችና ታጣቂዎች በሰሜን ጎንደር ዳባት ወረዳ አርቡር ቀበሌ ነዋሪ የሆነችው የ 8 ዓመቷ ህፃን ስለእናት ማስረሻ ጥላሁን የደረሰባትን እጅግ ዘግናኝና ሰቅጣጭ የአካል ጉዳትአሳይታለች፣ ሁኔታው የጉባኤውን አባላት ክፉኛ ያስቆጣ ሆኗል፡፡ አባቷን እና የቤት እንስሳትን በጥይት ገድለው ህፃን ስለእናትን በጥይት አረር እጇን የቆረጡ እኝህ እኩያን ወንጀለኞች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፡፡

4ኛ. የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የአመራር ዘመን አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ እጅግ የተዋረደችበትና ሉኣላዊነቷ የተደፈረበት ወቅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዜጎች የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይደርስባቸዋል፣ይታሰራሉ፣ ይደበደባሉ፣ ይገደላሉ፣ ይሰደዳሉ ወዘተርፈ፡፡
ለስደት በተዳረጉባቸው አገራትም ዜጎቻችን በግፍ ሲገደሉና ሲደበደቡ እያን ነው፡፡ በቅርቡ በሳውዲ አረቢያና ሰሞኑን ደግሞ በደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰው ሞትና ስቃይ የእያንዳንዳችንን ልብ የሰበረ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው፡፡
በመሆኑም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በመላው ዓለም እንደ ወንዝ ዳር አሸዋ ተበትነው ለሚንገላቱ ዜጎች ጉዳይ በአፅንኦት እየተከታተለ እንዲታደግና የመንግስትነት ግዴታውን ባግባቡ እንዲወጣ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

5ኛ. በአሁኑ ወቅት የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጥቂት ሹማምንት እጆቻቸውን እያስረዘሙ የአገርን ሀብት እየዘረፉ ናቸው፣ ሥርዓቱ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ በሙስና የተጨማለቀ መሆኑን እየተጋለጠ ነው፡፡ ዜጎች ዛሬ የዕለት ጉርሳቸውን አጥተው ሲራቡና ሲጠሙ፣ወጣቶች የሥራ ዕድል ተነፍጓቸው በአሳፋሪ ሁኔታ ከአገር ሲሰደዱ፣ የኑሮ ውድነቱ ትውልዱን ግራ እያጋባ ነው፣ ህዝቡ ፍትህና መልካም አስተዳደር በማጣት ነጋ ጠባ የዜግነቱ ጉዳይ ጥያቄ በፈጠረበት ሁኔታ የነገዋን ኃያልና የበለፀገች ኢትዮጵያን አይደለም ማየት ይቅርና የህልውናዋ ጉዳይም አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ሰዓት ላይ ደርሰናል፡፡ በአገሪቱም አስከፊ ብሔራዊ ቀውስ ይፈጠራል ብለን እንሰጋለን፡፡

ከዚህ አንፃር ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብሔራዊ መግባባትን የሚያሰፍን መድረክ እንዲያዘጋጅ አበክረን እንጠይቃለን፡፡
6ኛ. ኢቴቪ የኢትዮጵያ ሕዝብ ልሳንነቱን እርግፍ አድርጎ በመተው የገዢው ፓርቲ አገልጋይ መሆኑን የትኛውም ኢትዮጵዊ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ፕሮግራም ላይ በመላው አገሪቱ ሰላማዊ ሰልፍ እና ስብሰባዎችን በጠራበት ወቅት ኢቴቪ ጅሃዳዊ ሃረካት ፊልምን አቀናብሮ ፓርቲያችንን ከአሸባሪዎች ተርታ ሲፈርጀው ቆይቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ ጉባኤያችንን ባከናወንበት ታህሳስ 19 ምሽት ኢቴቪ ያንኑ ፊልም በድጋሚ በማቅረብ አንድነት ፓርቲ በደሴ፣ በጎንደር፣ በአርባምንጭ፣ በጂንካ፣ በባህርዳር ወዘተ ካደረጋቸው ሰላማዊ ሰልፎችና በፓርላማ የፓርቲያችን ብቸኛው ተወካይ ስለ ፀረ ሽብር ህጉ አፋኝነት ያነሱትን ሀሳብ ከሽብር ጋር በማያያዝ ከንቱ ዲስኩር ሲያቀርብ ተመልክተናል፡፡ ኢቴቪ የአንድ ድርጅት መሆኑ አብቅቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዋይታና ብሶት የሚያስተጋባ ግዙፍ የብዙሃን መገናኛ ድርጅት እንዲሆን አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

7ኛ. ፓርቲያችን አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከተመሠረተበት ዕለት ጀምሮ ከኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ጋር በብርቱ እየተናነቀ መሪዎቹ እየታሰሩበትና እየተደበደቡበት መዋቅሩን በመላው አገሪቱ ዘርግቶ አመርቂ የትግል ውጤት እያመጣ ቢሆንም የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚቀረው ጉዞ እጅግ ረጅም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ፓርቲያችን ይህ ታላቅ ጉባኤ የወሰናቸውን ውሳኔዎችና መርሃ ግብሮች በአግባቡ እየተወጣ ታሪክ ይሰራ ዘንድ አጥብቀን እናስገነዝባለን፡፡

በቀጣይ ዓመታት ፓርቲውን በበላይነት እንዲመሩ የተመረጡ አመራሮች ከመቼውም ግዜ በበለጠ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከአደራ ጭምር እናሳስባለን፡፡

ጄነራል ሳሞራ የኑስ የወጠኑት ሴራ የጄነራል አበባ ታደሰን ህልውና አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል።


ከተወሰኑት ወራት በፊት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከፍተኛ አዛዦች የሆኑት ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ ጄኔራል ሞላ ሃይለማርያምና ጄ/ል ሰአረ መኮንን ማእረጋቸው ሳይነካ ከተወሰኑ የሀላፊነት ቦታቸው ዝቅ ብለው እንዲሰሩ መወሰኑ የጦሩ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በሶስቱ ጎምቱ አዛዦች እና ውሳኔውን ባስተላለፉት በኢታማጆር ሹሙ በጄኔራል ሳሞራ የኑስ የተፈጠረው አለመግባባት መንስኤ ለብዙዎቹ ግልጽ አልነበረም። እነሆ ከወራት በሁዋላ ኢሳት የተወሰኑ የመከላከያ ሰራዊት አዛዦችን በማነጋገር ያጠናከረውን ሪፖርት ያቀርባል። የመረጃ ምንጮቻችን በኮሎኔልነት ማእረግ ደረጃ ያሉ ናቸው። ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እና ድምጻቸው እንዲካተት ፈቃደኛ አልሆኑም፣ ጊዜው ሲፈቅድ አዛዦቹ እራሳቸው ታሪኩን ይፋ እንደሚያወጡት ቃል በመግባታቸው እስከዛው በእነሱ በኩል ያለውን እይታ እንደሚከተለው እናቀርበዋልን።

ዊክሊክስ ከ2 አመታት በፊት ይፋ ባደረገው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መረጃ በህወሀት ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ ወግ አጥባቂና ለዘብተኛ የሚባሉ መሪዎች እንዳሉ ገልጿል። ወግ አጥባቂ የሚባሉት አመራሮች የህወሀት ወይም የትግራይ የበላይነት ተጠብቆ እንዲቆይ የሚፈልጉ ሲሆኑ ለዘብተኞች ደግሞ ይህ አካሄድ ለህወሀትም ሆነ ለኢትዮጵያ ህልውና አደገኛ በመሆኑ በፌደራል ደረጃ የህወሀት ሰዎች ከጀርባ ሆነው ስራዎችን ቢሰሩ ይሻላል ብለው የሚያምኑ ናቸው። 
ሟቹ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መከላከያው ከህወሀት እጅ እስካልወጣ ድረስ በሌሎች ቦታዎች ላይ የሌሎች ብሄር ሰዎች ፊት ሆነው ቢታዩና የህወሀት ሰዎች ከጀርባ ሆነው አመራር ቢሰጡ ይሻላል ከሚሉት ወገኖች መካከል ነበሩ። በዚህም እምነታቸው እርሳቸውን እንዲተኩ የደህኢህዴጉን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ለምክትል ጠ/ሚኒስትር አጩዋቸው፣ እርሳቸውም ሲያርፉ አቶ ሃይለማርያም ጠ/ሚኒስትር ሆኑ። 

የአቶ ሃይለማርያም ጠ/ሚ ሆኖ መሾም አክራሪ የሚባሉትን ወታደራዊ አዛዦችና የደህንነት ሰራተኞችን እንዲሁም በህወሀት ውስጥ ያሉ ጠንካራ ካድሬዎችን አላስደሰተም ። በብአዴን እና በሌሎች ኢህአዴግን በመሰረቱ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ አንዳንድ አመራሮች በመከላከያ ውስጥም የመተካካት ስራ ይጀመር በሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ መከላከያ ከፖለቲካው ውጭ ነው በሚል ሰሚ ሳያገኙ ቆይተዋል። ይሁን እንጅ መከላከያን በበላይነት የሚመሩት ጄኔራል ሳሞራ ከእድሜ እና ከጤና ጋር በተያያዘ ሃላፊነታቸውን የሚያስረክቡበት ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ፣ ህወሃቶች እርሳቸውን ሊተካ የሚችል ሰው ማፈላለግ ነበረባቸው። የመከላከያ አዛዦች እንደሚሉት በአግልግሎትም በብቃትም ሳሞራን ሊተኩ የሚችሉት ጄኔራል አበባው ታደሰ ናቸው። 

ጄኔራል አበባው የብአዴን ነባር ታጋይ ቢሆኑም፣ በብአዴን ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ አዛዦች ተገቢ የአዛዥነት ቦታ እንዲሰጣቸውና የህወሀት የበላይነት እንዲያበቃና ሁሉም በችሎታው የሚሾምበት አሰራር እንዲመጣ ሲጠይቁ ጄኔራሉ ከህወሀት አዛዦች ጎን በመቆም ከፍተኛ ውለታ እንደሰሩ ይቅርብ ሰዎች ይናገራሉ። ምንም እንኳ በዚህ አገልግሎታቸው በህወሀቶች ዘንድ እንደታማኝ መኮንን ቢታዩም ፣ የጄነራል ሳሞራን ቦታ የመውሰዱን ሃሰብ ግን አክራሪዎቹ የህወሀቶች መሪዎች የሚቀበሉት አይደለም። ወታደራዊ አዞዦቹ አራት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ። በቅድሚያ መለስ ህወሀት ያልሆነ ሰው በጠ/ሚንስትር መሾማቸው ስህተት ሰርቷል ብለው ያምናሉ። ሁለተኛ ጄኔራል አበባው ለብአዴን ያላቸው ታማኝነት የህወሀትን የበላይነት ሊያጠፋውና ብአዴንን ወደ ላይ ሊያመጣው ይችላል ብለው ይሰጋሉ። ሶስተኛው ደግሞ 98 በመቶ የሚሆነውን የወታደራዊ አዛዥነት ቦታዎች የተቆጣጠሩት ህወሀቶች በመሆናቸው፣ ጄ/ል አበባው ይህን ለማስተካከል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ብለው ይሰጋሉ። በአራተኛ ደረጃና ዋናው ምክንያት ብለው የሚያስቀምጡት ደግሞ በመከላከያ ውስጥ ለተንሰራፋው ተስፋ ማጣትና መዳከም ዋናው መንስኤ ሙስና ነው በሚል ጄኔራል አበባው በሙስና ላይ እርምጃ ከወሰዱ ከብዙ የህወሀት አመራሮች ጋር ሊያላትማቸው ይችላል የሚል ነው። በተለይም በብዙ ቢሊዮን ብር በተገናባው ብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ( ብኢኮ) እየተባለ በሚጠራው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ውስጥ የሚታየው ከፍተኛ ሙስና በጄ/ል ሳሞራ እውቅና የሚካሄድ መሆኑና በዚህም ሙስና ውስጥ የተዘፈቁት ጥቂት የህወሀት ከፍተኛ አመራሮች በመሆናቸው፣ ጄ/ል አበባው እርምጃ ለመውሰድ ሊነሳሱና ይህን የሙስና ሰንሰለት ሊበጥሱት ይችላሉ የሚል ነው። 

ጄኔራል ሳሞራ የኑስ የመከላከያ አዛዥነቱን ቦታ ከህወሀት ውጭ ለሆነ ሰው በመስጠት ህወሀትን ማዳከምና ያልታሰበ ጣጣ ማምጣት አልፈለጉም፣ በሌላ በኩል ደግሞ የስልጣን ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት ጄ/ል አበባው ታደሰን የብአዴን አባላት በማይከፉበት፣ የእርሳቸው ደጋፊዎች ተቃውሞ በማያነሱበት እንዲሁም ምንም የዘር ፖለቲካ ባህሪ በሌለው መልኩ ማከናወን አለባቸው። የህወሀት አመራሮች ምንም ነገር ኮሽ ሳይል የወጠኑት እቅድ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ጄ/ል ሞላ ሐይለማርያምንና ጄ/ል ሳእረ መኮንንን ለመጠቀም መወሰናቸውን ወታደራዊ ምንጮቻችን ይገልጻሉ።

በመጀመሪያ ጄኔራል ሞላ ጄኔራል አበባውን በመቅረብ፣ " ጄኔራል ሳሞራ የኑስ በኢንጂነሪንግና ብረታብረት ኮርፖሬሽን ( ብኢኮ) ውስጥ የሚታየውን ከፍተኛ ሙስና ለመዋጋት ባለመቻሉ መከላከያ የተገነባበት ዋና መሰረት እየተናጋ ነው። ይህንን ጉዳይ ቶሎ ካላስቆምነው መከላከያ ውስጥ ችግር ከመፈጠሩ አይቀሬ ነው " በሚል ሀሳባቸውን አካፈሉዋቸው። ጄ/ል አበባውም ሀሳቡ ትክክል መሆኑን በመቀበል ከጄኔራል ሞላ ጋር ለወደፊት ስለሚወስዱት እርምጃ ተወያዩ። በዚህ ሂደት ጄል ሳእረ እንዲገባበት ጄል ሞላ ሀይለማርያም ሃሳብ ያቀርባሉ። ጄ/ል ሳእረም በሀሳቡ በመስማማት ከሶስቱ ጄኔራሎች ጋር ምክክር ማድረግ ጀመሩ። ሶስቱ ጄኔራሎች ሌሎች ጄኔራሎችንና አንዳንድ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦችን ለማሳተፍ ወስነው እንቅስቃሴ ጀመሩ። የእንቅስቀሴው አላማ ጄ/ል ሳሞራ ስራቸውን በተገቢው አልተወጡም በሚል ግምገማ ከማካሄድ እንዳያልፍ ተስማምተዋል። በዚህም መሰረት ጄኔራሎቹ ብዙ ደጋፊዎችን አገኙ። 

በቂ ምስክሮች መገኘታቸው ሲታወቅ፣ ከመካሪዎች መካከል አንዱ መረጃውን አሾልኮ አወጣ። በዚህን ጊዜ መረጃውን የሚያጣራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደረገ። ሶስቱ ጄኔራሎች ቀደም ብለው ያማከሩዋቸው ሰዎች ምስክርነታቸው ለኮሚቴው አባላት ሰጡ። የኮሚቴዎቹ የምርመራ ውጤት ሶስቱም ጄኔራሎች የመከላከያ ሰራዊት አባላት በጄል ሳሞራ የኑስ ላይ ተቃውሞ እንዲያሰሙ አድማ ማድረጋቸውን አመላከተ። ጄ/ል ሳሞራ የኮሚቴውን ሪፖርት አንድ በአንድ ለሶስቱም ጄኔራሎች አነበቡላቸው። ሶስቱም ጄኔራሎች በሃላፊነት ቦታቸው ላይ እንዲቆዩ ቢደረጉም ከእድገት እንደታገዱና ከአንዳንድ ሃላፊነት ቦታቸው እንደተነሱ ተነገራቸው።

ጄ/ል አበባው የጄ/ል ሳሞራ የኑስን ቦታ የመውሰድ ህልም ተጨናገፈ። ድራማው ምንም የዘር ፖለቲካ ያለበት ሳይመስል በድል ተጠናቀቀ። ጄ/ል ሞላ ሀይለማርያምና ጄ/ል ሳእረ መኮንንም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የቀየሱት መንገድ ተሳካ። ቀጣዩ ኢታማዦር ሹም የህወሀቱ ሌ/ት ጄ/ል ዮሀንስ ገብረመስቀል ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሶስቱንም ጄኔራሎች አስተያየት ለማከተት ላለፉት ሁለት ወራት ከፍተኛ ጥረት ስናደርግ ብንቆይም ሊሳካልን አልቻልም። መረጃውን በማካፈል በኩል የተባበሩንን ወታደራዊ አዛዦች ለማስገን እንወዳለን።

ምንጭ ኢሳት 

በደቡብ ክልል የይርጋ ጨፌ መምህራን የስራ ማቆም አድማ አደረጉ




ታህሳስ ፳፫( ሃያ ሦስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና መምህራኑ አድማውን የጀመሩት ያለፍላጎታችን ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ደሞዛችን እየተቆረጠብን ነው በሚል ነው። መምህራኑ ለይርጋ ጨፌ ከተማ አስተዳደር፣ ለጌዲዮ ዞንና ልክልሉ ትምህርት ቢሮ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ” ከ ሀምሌ 2005 ዓም ጀምሮ ለህዳሴ ግድብ የሚቆረጠው ገንዘባችን እኛ ያለፈቀድነውና ያልተስማማንበት በመሆኑ ጥቅምት 28፣ 2006 ጀምሮ ስራችንን በአግባቡ እየሰራን የመብት ጥያቄያችንን ለሚመለከተው ሁሉ ስናቀርብ በመቆየታችን ታህሳስ አንድ በዞን መምህራን ማህበር ሰብሳቢነት የከተማው ከንቲባ ፣ የከተማው ትምህርት ዩኒት ሃላፊ በተገኙበት አቆራረጡ አግባብነት የሌለውና የመምህራንን መብት የጣሰ መሆኑን በውይይቱ ተረጋግጦ ከታህሳስ ጀምሮ የሚቆረጠው ገንዘብ እንዲቆም፣ መወሰኑን” አስታውሷል። ድብዳቤው “ነገር ግን የከተማው አመራር እንደተለመደው በመዋሸት እንዲቆም የተወሰነው ገንዘባችን እንዲቆረጥብን አድርጓል” ይላል።


ድብዳቤው አያይዞም ” የታህሳስ ወር የተቆረጠበን ተስተካክሎ እንዲከፈለን፣ ከሀምሌ 30 ፣ 2005 ዓም ጀምሮ ለተከታታይ 5 ወራት የተቆረጠብን ገንዘብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲመለስልን፣ ከዚህ ቀደምም ያለፈቃዳችን እየተቆረጠብን ያለው የኢች አይ ቪ መዋጮ እንዲቆም እየጠየቅን ከዛሬ ማለትም ከታህሳስ 22 ቀን 2006 ዓም ጀምሮ ስራ ማቆማችንን እንገልጻለን፤ የታህሳስ ወር የሚመለስልን ከሆነ ግን ወደ ስራ ገበታችን ተመልሰን እየሰራን ከዚህ ቀደም የተቆረጠውን የ5 ወር ገንዘባችንን ደግሞ እስከ ታህሳስ 25 2006ዓም በትእግስት የምንጠብቅ ሲሆን ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን አሁንም ስራችንን ለማቆም የምንገደድ እና ለሚመለከተው የበላይ አካል የምንሄድ መሆናችንን ከወዲሁ እናሳውቃለን” ብሎአል። በትምህርት ቤቱም ይሁን ከትምህርት ቤት ውጭ ለሚፈጠሩ ችግሮች መምህራኑ ተጠያቂዎች ያለመሆናቸውን ገልጸዋል።
ደብዳቤውን ተከትሎ መምህራኑ ያስራ ማቆም አድማውን ተማሪዎችን በማሰናበት መጀመራቸውን ተከትሎ መስተዳድሩ ዛሬ የታህሳስን ወር ለመክፈል መገደዱን ዘግይቶ የደረሰን ዜና ያመለክታል።
በደቡብ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን ያለፈቃዳቸው የሚቆረጥባቸውን ገንዘብ በመቃወም የስራ ማቆም አድማ ሲያደርጉ ሰንብተዋል።

ሰበር ዜና፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በአቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ ላይ ውሳኔ አስተላለፈ


- አቶ መላኩ የሞገቱበት የአዋጅ አንቀጽ እንዲስተካከል ተወሰነ
በሙስና ወንጀል የተከሰሱት አቶ መላኩ ፈንታን ክስ መመልከት ያለበትን ፍርድ ቤት በሚመለከት ዛሬ የተወያየው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክሱ መታየት ያለበት በጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑን ለማሳየት ተከሳሹ የጠቀሱት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች
አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 8 ንኡስ አንቀጽ 1 ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረስ በመሆኑ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንዲጣጣም ሆኖ እንዲስተካከል በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ ውሳኔው ስምንት ተቃውሞና ሁለት ድምፀ ተአቅቦ ተመዝግቦበታል፡፡
የአዋጁ ንኡስ አንቀጾች እንደሚያስረዱት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሥልጣን ላይ ሳሉ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ በሚያጠፉት ጥፋት የሚጠየቁት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያደረገው ውይይት ባለሥልጣናቱ በዚህ መልኩ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚጠየቁ ከሆነ ጥፋተኛ ወይም ነፃ ቢባሉ እነሱ ወይም መንግሥት ይግባኝ የሚሉበት ዕድል አይኖርም፡፡ ይህ ደግሞ ሁለቱንም ወገን የሚጎዳና የይግባኝ መብትን የሚፃረር ነው፡፡ 
ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት የአቶ መላኩ ክስ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የመታየት ዕድል አይኖረውም
POSTED BY TAMRAT YDEGO

አዲስ አበባ በቤት ኪራይ ንረት እየተናጠች ነው

ዜና ትንታኔ ከብርሃኑ ፈቃደ

(ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው)
የመኪና ራዲያተር ጥገና ባለሙያ ነው፡፡ በኪራይ ምክንያት በሚሠራበት ሰባተኛ አካባቢ የተደረገበት ጭማሪ አስደንጋጭ ሆኖበት ሲበሳጭ ከርሟል፡፡ አንድ ሺሕ ብር ይከፍልበት የነበረው ቤት፣ ‹‹ብዙ ግብር መጥቶብኛል፤ ስለዚህ ሁለት ሺሕ ብር ተጨማሪ ክፍያ መደረጉንና የኪራዩ ዋጋ ሦስት ሺሕ ብር መሆኑን እንድታውቀው፤›› የሚል ቀጭን መልዕክት ደርሶት ከአከራዩ ጋር ተጨቃጭቆ መክረሙን የሚናገረው ወጣቱ ሰው፣ አልታይ ዘለቀ (ስሙ ተቀይሯል) ነው፡፡
appartment in addis
ለጭማሪው በአከራዩ የቀረበውን ምክንያት የማይቀበለው አልታይ፣ ‹‹እንዴትም ተብሎ ግብር ቢጨምር፣ ከመንገድ ዳር ርቆ የትኛውም ደንበኛ ቤቱን አይቶ ለመምጣት በማያስችለው አካበቢ ላይ ለሚገኝ ቤት፣ ሥራው በተባራሪ እየተሠራ፣ ሥራውን ለሚያመጡ ደላሎች ኮሚሽን እየከፈልኩ ለምሠራው ሥራ በአንድ ጊዜ ይሄን ያህል ጭማሪ ማድረግ ወዴት እየወሰደን እንደሆነ ግራ ገብቶኛል፤›› ሲል ይኮንናል፡፡ የአንድ ልጅ አባት የሆነው አልታይ፣ የራሱንና የባለቤቱን ቤተሰቦች ጨምሮ ሦስት ቤተሰብ የሚያስተዳድርበት ይህ ሙያው ከዚህ ሁሉ ቤተሰብ ቀለብና ወጪ ተርፎ በአንድ ጊዜ ጭማሪ በተደረገበት ልክ የሚበቃ ገቢ ካላገኘበት፣ ወደ ክፍለ አገር አለያም ወደ ዓረብ አገር ለመሰደድ ማሰቡን ተናግሯል፡፡

የአልታይ ጓደኛ የሆነው ሌላው አስተያየት ሰጪ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ትምህርት ቤት ከፍቶ መሥራት ከጀመረ ሦስት ዓመታት መቆጠራቸውን ይገልጻል፡፡ ያለቻቸውን ገንዘብ አሟጥጠው፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ገንዘብ ተቋማት ተበድረው የሚያንቀሳቅሱትን ትምህርት ቤት የከፈቱት ሕንፃ ከግለሰብ ተከራይተው ነው፡፡ ለኪራይ በዓመት ከአምስት መቶ ሺሕ ብር በላይ ይከፍላሉ፡፡ ማስፋፊያ ለማድረግ ሌላ ተጨማሪ የግለሰብ ሕንፃ መከራየት ግድ ሆኖባቸው መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ ከአንደኛ ክፍል እስከ 12ኛ ለማስተማር የሚያስችሉ ክፍሎችን ለማሟላት የግለሰብ ሕንፃ በውድ ዋጋ መከራየትና መሥራት አማራጭ የለውም ይላሉ፡፡ ሥራው እንዲህ ያለው አላስፈላጊ ጫና ባይኖርበት ኖሮ የበለጠ ጥሩ ሥራ ለመሥራት ያመቻቸው እንደነበርና ይበልጥ የሰው ኃይል ቀጥረው፣ በርካታ ተማሪዎችን ማፍራት የሚያስችላቸውን መንገድ የቤት ኪራይ ዋጋ እንዳራቀባቸው ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ለትምህርት ዘርፍ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ቢያስታውቅም፣ በደህናው ጊዜ ቦታ በርካሽ አግኝተው ሕንፃ የሠሩ ሰዎች በኪራይ ከሚያግበሰብሱት ገቢ የማያገኘውን ታክስ፣ እኒህ ተከራዮች ከሚሰጡት የትምህርት አገልግሎት ከፍተኛ ታክስ ይሰበስባል፡፡ ሆኖም ትህምርት ቤት መሥሪያ ቦታ ማግኘት የማይታሰብ እንደሆነባቸው የሚገልጹት አስተያየት ሰጪ፣ የሊዝ ግዥ ለማድረግ የሚቀርበው መነሻ ዋጋ በአስገራሚ ሁኔታ በካሬ ሜትር እስከ አሥር ሺሕና በዚያም በላይ በመድረሱ መቸገራቸውን ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት ለትምህርት ዘርፉ እንደቆዳና ሌሎች ፋብሪካዎች የሰጠውን ማበረታቻ ሲሰጥ ማየትም አልቻንም ይላሉ፡፡ በሊዝ ጨረታ መነሻ ዋጋ መሬት እንደልብ ከተማው ላይ ለእነዚህ ዘርፎች ሲሰጥ ይታያል፡፡
ከቻይናና ከሌላውም አገር ለመጡ ‹‹የውጭ ባለሀብቶች›› የሚሰጠው ድጋፍ በትምህርቱ ዘርፍ አገልግሎት ሰጥተው፣ ብዙ ሠራተኛ ቀጥረው ለሚያሠሩትና ከፍተኛ ግብር በመክፈል አስተዋጽኦ ለሚያበረክቱት ሰዎች ምንም ዓይነት ድጋፍ ከመንግሥት እያገኙ እንዳልሆነ በመግለጽ መቸገራቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሕንፃ አከራይ እንዲያገኝ የተመቻቸለትን ጥቅም፣ ለብዙ ሰው የሥራ ዕድል አስገኝተውና አገልግሎት ለሕዝቡ ሰጥተው የሚሠሩ ሰዎች እንደአስቷጽኦዋቸው የሚጠቀሙበትን ዕድል አለማግኘታቸውን ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት ለአከራይ እንጂ ለሠርቶ አሠሪና በኢኮኖሚው ውስጥ እሴት ጨማሪ ለሆኑ አካላት በመሬት አቅርቦት የሚያድርገው ድጋፍ ከወለል በታች መሆኑን በመግለጽ ይተቻሉ፡፡
‹‹የመንግሥት የመደብ ጨቋኝነት ሚና››
በአዲስ አበባ ሕንፃ የገነቡ አብዛኞቹ ከመንግሥት የ70 ከመቶ ብድር አግኝተው፣ መሬት ተመርተው ወይም በርካሽ ተጫርተው በሊዝም ሆነ በይዞታ ከገዙ በኋላ ያለምንም ድካምና ውጣውረድ በመንግሥት ገንዘብ በገነቡት ሕንፃ ያለሐሳብ ሀብታሞች እንዲሆኑ በመንግሥት ዕድሉ የተሰጣቸው ናቸው፡፡ መኪና ገጣጥመው፣ ትምህርት ቤት መሥርተው፣ በፋብሪካ አምርተው ለመሥራት የሚጣጣሩ ሰዎች የማያገኙትን የገቢ ዝቆሽ፣ ሕንፃ አከራዮች በመንግሥት ተባባሪነት የሚያገኙትን ጥቅምና የዳጎሰ ገቢ በመመልከት፣ አንድ ሕንፃ በባንክ ብድር በመሥራትና ሕንፃውን ለብድር ማስያዣነት በመዋል ገርበብ ባለው የብልጽግና በር በኩል ሾልከው የተመነደጉ ጥቂት አይደሉም፡፡
በአገሪቱም ሆነ በአዲስ አበባ መዲናም መንግሥት የሚፈልገውን ያህል የማኑፋክቸሪንግ ወይም የኢንዱስትሪ መስኮች አለመስፋፋት ችግሮች መንስዔ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል እነዚህ አቋራጭና በቀላሉ የዕድሜ ልክ ባለሀብት መሆን የሚቻልባቸው መንገዶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ አንድ ባለፋብሪካ ወይም ባለትምህርት ቤቱ ባለጉዳይ እንደሚጠቅሱት ሥራቸው በበርካታ ሰዎች ትከሻ ላይ የወደቀ ነው፡፡ ብዙ ሠራተኛ ተቀጥሮና እሴት ተጨምሮ የሚሠራው ሥራ ትርፍ ማስገኘት የሚጀምረው ከፕሮጀክቱ ትግበራ አራት ወይም አምስት ዓመታት በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡ በአንፃሩ ሕንፃ ሠርተውና ሸንሽነው የሚያከራዩ ግን ቦታ አጥቶ የተቸገረ ነጋዴ ወይም ሌላው አካል በካሬ ከ500 እስከ 5,000 ብርና ከዚያም በላይ እየከፈለ ለመሥራት የሚገደድ ጭሰኛ ሆኗል ይላሉ፡፡ አከራዮች ከኪራይ በሚሰበስቡት ገንዘብ የባንክ ዕዳ ከፍለው ሀብታቸው የማይነጥፍ ቱባ ሀብታሞች ይሆናሉ፡፡
ስለዚህ ፋብሪካ ከመገንባትና ለኢኮኖሚው እሴት የሚጨምሩ ዘርፎች ላይ ከመሠማራት ይልቅ በአቋራጭና በአጭር መንገድ ሀብታም የሚያደርጉ አማራጮች በመንግሥት በኩል ስለተመቻቹ፣ ለምን ብለው ይደክማሉ፤ ለነገሩ የደከሙትስ ምን አተረፉና የሚል መከራከሪያ በከተማው በሰፊው የሚደመጥ ሙግት ሆኗል፡፡
መምህር በቀለ የተባሉ በጡረታ ላይ የሚገኙ መምህር በአንድ ወቅት በኅብረተሰብ ሳይንስ ትምህርት ወቅት ስለመንግሥት ሥርዓትና አወቃቀር ሲያስትምሩ ‹‹መንግሥት የመደብ መጨቆኛ መሳሪያ ነው፤›› በማለት ይገልጹ ነበር፡፡ ይህም ሲባል የበላይ መደብ ያላቸው፣ በካፒታልና በገንዘብ አቅማቸው የተነሳ የመንግሥትን አገልግሎት በቀላሉ ለማግኘት የሚቻላቸው መሆናቸውን ለማመልከት የሚጠቀሙበት አገላለጽም ነው፡፡
ቤት መግዛት ባትችል ትከራያለህ፣ መከራየት ባትችል ግን?
በአሜሪካ የኪራይ ቤቶችን በማስመልከት ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንድ ጥናት ይፋ ተደርጎ ነበር፡፡ በኪራይ ቤቶች ዙሪያ በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲና በአጋሮቹ የተደረገው የጋራ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ የቤት ኪራይ ዋጋ እ.ኤ.አ. ከ1980ዎቹ ጀምሮ እየጨመረ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ የዜጎች ገቢ በየጊዜው እየቀነሰና እያነሰ መምጣቱን ተመልክቷል፡፡ የሀርቫርድ የኪራይ ቤቶች ጥናት እንደሚያረጋግጠው፣ ከሆነ ከ11.3 ሚሊዮን ያላነሱ አሜሪካውያን የራሳቸው ቤት ሊኖራቸው የሚችልበት አቅም የላቸውም፡፡ የኪራይ ቤት ጥገኛ ናቸው፡፡ በዚህ ሳቢያ ከግማሽ በላይ ገቢያቸውን ለኪራይ በመክፈል ለአስከፊ ወጪ የተዳረጉና ልፋታቸውን ለኪራይ የሚገብሩ መሆናቸውን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ ከእነዚህ ትንሽ ዝቅ ያለ ገቢ ያላቸው ግለሰቦች ዝቅተኛ የሚባለው የኪራይ ወጪያቸው፣ የገቢያቸውን 30 ከመቶ ለኪራይ የሚከፍሉ ናቸው፡፡
ከሁለት አሜሪካውያን አንዱ በቤት ኪራይ ወጪ ናላው የሚናውዝ መሆኑን የሚጠቁመው ጥናት፣ በአሁኑ ወቅት ለከፍተኛ የኪራይ ጫና ከተዳረጉት 12 ሚሊዮን አሜሪካውያን ባሻገር 21.1 ሚሊዮን አሜሪካውያን ለቤት ኪራይ ወጪ መሸፈኛነት ገቢያቸውን በማሟጠጥ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
ጥናቱ ሰፊና አስገራሚ ዕውነታዎችን ማስነበቡን ይቀጥላል፡፡ አሜሪካውያን በፌደራል መንግሥታቸው ደረጃ በሰዓት በአማካይ የሚያገኙት ገቢ 7.5 ዶላር (በወቅቱ ምንዛሪ ቢመታ 150 ብር መሆኑ) ነው፡፡ ሆኖም ባለሁለት መኝታ ክፍል ደህና መኖሪያ ቤት መከራየት የሚፈልግ አሜሪካዊ፣ በየትኛውም የአሜሪካ ግዛቶች ይህን መሰል ቤት መከራየት የሚችለው በሰዓት ቢያንስ 20 ዶላር (በሰዓት 400 ብር ያህል) ገቢ ማግኘት የቻለ እንደሆነ ነው ሲል ጥናቱ ማረጋገጫውን አስፍሯል፡፡ ከሁለት መኝታ ቤት ያነሰ ግን ደግሞ ደህና ሊባል የሚችል ቤት መከራየት የሚፈልግ ሰው የሰዓት ገቢው 12 ዶላር መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህ በየትኛውም የአሜሪካ ግዛት በሰዓት 7.5 ዶላር ዝቅተኛውን ገቢ የሚያገኝ አንድ ዜጋ ደህና የሚባለውን ቤት ተከራይቶ መኖር አይችልም፡፡
ኪራይ የሚያንረው ባለንብረቱ ነው
የኢትዮጵያ በተለይ የአዲስ አበባ ሁኔታ ይህንን ይመስላል፡፡ ኮንዶሚኒየም ተከራይቶ ለመኖር የሚችለው ሰው ወርኃዊ ገቢው ቢያንስ ከአምስት ሺሕ ብርና ከዚያም በላይ መሆን እንዳለበት ጥናት ማድረግ ሳያስፈልገው የሚታወቅ ነው፡፡ በከተማው ትልቁን የገቢ ምንጭ የሚበዘብዘው የኪራይ ዋጋ እንደሆነ ተራ አባወራ ብቻም ሳይሆን ሕንፃ ተከራይተው ቅርንጫፎቻቸውን የሚስፋፉ ባንኮች ሳይቀር የሚገነዘቡት ነው፡፡ የባንክ አገልግሎት እምብዛም በማይፈለግባቸው የአዲስ አበባ ጠረፍ አካካቢ የተከፈቱ የባንክ ቅርንጫፎች ሲናገሩት የሚደመጥ ነው፡፡
በአንፃሩ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቢሮ ለመከራየት ሁለት ጉዳዮች ቦታ እንዳላቸው የሚገልጹት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ደምስ ጫንያለው ናቸው፡፡ አንደኛው ቤቱ የሚገኝበት ቦታ ለኪራይ ዋጋው ከፍተኛ መሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ‹‹ዓይን ቦታ›› ተብሎ በልማድ የሚጠቀሰው አገላለጽ በተለይ በንግድ ሥራ ለተሰማሩ ሰዎች የተለመደ ሲሆን፣ ገበያ እስካለውና ወጪያቸውን ሸፍኖ ትርፍ እስካስገኘ ድረስ፣ ለትራንስፖርትና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች ያለው ምቹነት እየታየ ዋጋው እንደሚለያይ ከምሁሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ሌላኛው ዋጋውን ውድና ተገቢ ሊያደርገው የሚችለው ምክንያት የቤቱ ወይም የንብረቱ ባለቤትነት ነው፡፡ በግለሰቦች ይዞታና በተቋማት መካከል ባለው ልዩነት መካከል የዋጋው ከፍተኛነትና ዝቅተኛነት ሊንፀባረቅ እንደሚችልም ዶክተር ደምስ ይገልጻሉ፡፡
በኢኮኖሚ ሙያቸው የማማከርና የጥናት ሥራዎችን የሚያካሂዱት ዶክተር ደምስ፣ የኪራይ ዋጋ ከውል ውጭ ያለአግባብ ተጨምሮባቸው የተከራዩትን የግለሰብ ቤት ለመልቀቅ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከግለሰብ ተከራይተን ነበር የምንሠራው፡፡ ስድስት ወር እንኳ ሳንቆይ በአንድ ጊዜ 35 ከመቶ ያህል ጨምረውብናል፤›› ያሉት ዶክተር ደምስ፣ አብዛኞቹ ግለሰቦች ሀብቱ ስላላቸው ዋጋ እንዳሻቸው ይጨምራሉ እንጂ ገበያው ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አይተውና ጥናት አድረገው የሚጨምሩ እንዳይማስላቸውም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ለአንድ ዓመት በውል ተዋውለውና ቅድሚያ መክፈል የሚጠበቅባቸውን ከፍለው ሥራ ቢጀምሩም፣ ከውል ውጭ በተደረገው ጭማሪ ቅር ተሰኝተው ሌላ አካባቢ ፈልገው ለመግባት ተገድደዋል፡፡
የአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ለአብዛኛው ሰው የሚቀመስ አለመሆኑን ምሁሩ ብቻም ሳይሆን ነዋሪዎችና ነጋዴዎች የሚስማሙበት ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል አንዳንድ ሰዎች ‹‹ከፒያሳና ከቦሌ ዕቃ መግዛት ለነጋዴው የቤት ኪራይ እንደመክፈል ይቆጠራል፤›› ሲሉ የሚደመጡት፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚሸጡት ዕቃዎች መርካቶና ሌላው አካባቢ ከሚሸጡት የተለዩ ሆነው ሳይሆን በዋጋቸው የማይቀመሱ ሆነው ስለሚገኙ የሚነገር አገላለጽ ነው፡፡ በከተማው ለሱቅ ኪራይ በካሬ የሚከፈለው ክፍያ በአስገራሚ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በቦሌ አካባቢ ከሚገኙ ሕንፃዎች መከራየት የሚፈልግ ነጋዴ፣ በአማካይ በካሬ ከሁለት ሺሕ እስከ ሦስት ሺሕ ብር ይጠየቃል፡፡ አምስት መቶ ብርና ከዚያ ያነሰ ዋጋ በካሬ የሚከፈልባቸው ሕንፃዎች ቢኖሩም፣ አዳዲስ የተሠሩት ግን በዚህ ዋጋ የሚደፈሩ አይደሉም፡፡ አካባቢ የቤት ኪራይ ዋጋን በዚህ መልኩ ሊወስን ቢችልም፣ የግል አከራዮች የሚያደርጉት ጭማሪ ባለንብረትነታቸው ላይ ያጋድላል፡፡
በአንፃሩ አከራዮች የየራሳቸውን አካሄድ እንደሚከተሉና በርካታ ወጪዎችን በማውጣት፣ ጥሪታቸውን አሟጠው ለገነቡት ሕንፃ ተመጣጣኝና ተከራዮችንም የማይጎዳ የኪራይ ዋጋ እንደሚጠይቁ ይሟገታሉ፡፡ በተለይ ከመገናኛ እስከ ሃያ ሁለት ባለው መስመር ሕንፃዎቻቸውን የሚያከራዩ ባለንብረቶች፣ በመንገድና በባቡር መስመር ግንባታ ምክንያት ሥራ በመጥፋቱ ምክንያት ኪራይ በግማሽ የቀነሱ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንም በመንገድ ሥራው ምክንያት ሥራ ቀንሶባቸዋል ባላቸው ድርጅቶችና አነስተኛ ነጋዴዎች ላይ የሚጥለው ታክስ ላይ አስተያየት ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡
በአዲስ አበባ ኬሻ በጠረባ ከሚተኛባቸው የጎጃም በረንዳ፣ የአሜሪካ ግቢ፣ የሰባተኛ ሰፈሮች አንስቶ እስከ ቦሌ፣ ገርጂ፣ ቤቴል የመሳሰሉት አካባቢዎች ቤት የሚከራይባቸው ናቸው፡፡ ኬሻ በጠረባዎቹ ቤት ለአዳር ያከራያሉ፡፡ ኬሻ በጠረባ እየተባሉ የሚታወቁት ቤቶች፣ ድሮ ድሮ ኬሻ፣ አሁን አሁን ካርቶን ተነጥፎ ለአንድ አዳር ሰው እንደጣውላ ተደርድሮ የሚታደርባቸው ቤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ቤቶች ድሮ ከነበራቸው ማደሪያ የለሽ ደንበኛ ባሻገር፣ ከየክፍለ አገሩ ይጎርፉ የነበሩ የዓረብ አገር መንገደኞች የሚያገኙት ገቢ አስተማማኝ ሆኖላቸው ቆይቷል፡፡ ዓረብ አገር የሚሄዱ ሴቶች እንደከተማው ማደሪያ ቢስ ሰካራም ሳይሆን እጥፍ ከፍለው ያድሩ እንደነበር ሪፖርተር ያነጋገራት የጎጃም በረንዳ ኬሻ በጠረባ አከራይ ሺመታ አሕመድ ታስታውሳለች፡፡ አሁን ግን በጎጃም በረንዳ ኬሻ በጠረባ እያበቃለት መምጣቱን የሚጠቁም አካሄድ በባቡሩ መስመር ግንባታ እየታየ ነው ትላለች፡፡ ከፊት ለፊት የነበሩት ሱቆች አብዛኞቹ በመፍረሳቸው፣ አልጋ ያከራዩ ከነበሩት ቤቶች አንዳንዶቹ ለሱቆች ዕቃ ማከማቻነት እየዋሉ መምጣታቸውን ትገልጻለች፡፡ አብዛኞቹ ግን ለአዳር ከሚያከራዩዋቸው ቤቶች ውስጥ አብረው የሚኖሩ በመሆናቸው፣ ቤቶቹ ሲፈርሱባቸው ዕድል ከቀናቸው ኮንዶሚኒየም ቤት የሚቀየርላቸው በመሆኑ የገቢ ምንጫቸው ላይ አደጋ እንደተጋረጠበት ሥጋት የገባቸው ናቸው፡፡
ከእነዚህ ባሻገር ያሉት የገርጂና የቦሌ ቤቶች ቅንጡ ናቸው፡፡ የሚከራዩት በድረ ገጽ በሚለቀቁ ማስታወቂያዎች ሲሆን፣ ከ800 (16,000 ብር) እስከ 4,000 ዶላር (80,000 ብር) ድረስ የኪራይ ዋጋ የሚጠየቅባቸው ቤቶችም በአዲስ አበባ ጥቂት አይደሉም፡፡ አብዛኞቹ ቦሌ፣ ኦሎምፒያ፣ ገርጂ (በይበልጥ ሰንሻይን አፓርታማዎች)፣ ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኙ ቤቶች ባለአንድ፣ ባለሁለትና ባለሦስት መኝታ መሆናቸው እየተገለጸና ዘመናዊ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ እንደተሟላላቸው የሚገልጹ ማስታወቂዎች የሚያጅቧቸው ናቸው፡፡
ኪራይ የሚቆልሉት ደላሎች ናቸው
ከፍና ዝቅ ያለውን የአዲስ አበባ የኑሮ ቅኝት እንዲህ የሚመሰክሩት የአዲስ አበባ የኪራይ ቤቶች፣ በመካከሉ ላለው ነዋሪ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና የሚፈጥሩ ሆነው ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ሌላው ጥልቅ ችግር ለመሆኑ በመንግሥትም በሕዝቡም ስምምነት የሚደረግበት ትልቅ ችግር የደላሎች ሚና ነው፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር በተለያዩ አጋጣሚዎች የደላሎችን ተግባር በማስመልከት ከፍተኛ ቅሬታ ሲያሰማ ማድመጥ የተለመደ ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ስለብርቱካን ዋጋ መወደድ ለማሳሰብ በተጠራው የንግድ ሚኒስቴር ስብሰባ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ደላሎች ከሚችለው በላይ ሆነውበት መቸገሩን አስታውቋል፡፡
ጥቂት ቢቆይም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ‹‹ጉዳይ እናስፈጽማለን›› በሚሉ ደላሎች መቸገሩን አስታውቆ ነበር፡፡ ዋናው መሥሪያ ቤት ድረስ ሰተት ብሎ የረዘመው የደላሎች እጅ፣ በተለይ ከሦስት ዓመት በፊት ጡዘት ላይ ደርሶ የነበረውን የአነስተኛ ግብር ከፋዮች ጉዳይ መነሻ በማድረግ በባለሥልጣኑ ጉዳያቸውን ሊያይ የሚችል አካል እንደሚያውቁና እንደሚያስጨርሱላቸውና ውክልና ሳይቀር እንዳላቸው በመግለጽ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ሳይቀር ማስቸገራቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡
ይህ መሆኑ ደግሞ በየትኛውም የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ላይ ደላሎች አይነኬና የማይፈነቀል ሚና ይዘው ለመቆየታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ ከቤት ሠራተኛ ቅጥር ጀምሮ በቤት ሽያጭና ግዥ፣ አሁን በግልጽ አይሁን እንጂ በድብቅ የመሬት ሽያጭና ግዥ በማካሄድ፣ ከውጭ ዕቃ በማስመጣትና ደንበኛ በማፈላለግ ላይና በየትኛውም የኢኮኖሚ አውታር ላይ የደላሎች ሚና ከደም ሥር በላይ ሆኖ ይታያል፡፡
በቤት ኪራይ ላይ የሚታየው የደላሎች ጣልቃ ገብነት ደግሞ አብዛኛውን የከተማ ነዋሪ ከማንገሽገሽ አልፎ አንዳንዶችን ለጠብ ሲጋብዝ ማየት እየተለመደ ነው፡፡ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ለሚከናወኑ የኪራይ ድርድሮች ደላሎች ማዕከላዊውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ ያለደላሎች ጣልቃ ገብነት የትኛውም ቤት አይከራይም፣ አይሸጥም ሲባል መስማት የተለመደ ነው፡፡ በመካኒሳ ባቱ አራት ባለሁለት መኝታ ቤት ለመከራየት ፈልጋ ዘበኞችን የጠየቀችው እመቤት ጌታቸው የተባለች ወጣት፣ አከራዩን በስልክም በአካልም ማግኘት እንደማትችል ይልቁንም የቤቱን ቁልፍ ከያዘው ደላላ ጋር ተነጋግራ ከተስማማች መከራየት እንደምትችል እንደተነገራት ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡
በገዥና ሻጭ መካከል በቀጥታ የሚደረጉ ስምምነቶችን በዚህ ምክንያት ማድረግ አደጋች ሆኖ ይታያል፡፡ አንዳንድ የኮንዶሚኒየም ኮሚቴዎች ግን ይህንን አጥር በመስበር፣ በአከራይና ተከራይ መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ ሲጣጣሩ ይታያሉ፡፡ ደላሎች ለአከራዩ የቅድሚያ ክፍያ ለአንድ ዓመት፣ ለስድስት ወር አለያም ለሦስት ወር የሚደረጉ የኪራይ ክፍያዎች ላይ ከሦስት እስከ አምስት በመቶ የአገልግሎት በማስከፈል እንደሚያከራዩ ሲገለጽ፣ ደላሎች በባለቤት ስም ሆነው ለሚያከራዩት ቤት እስከ አሥር በመቶ እንደሚያስከፍሉም ይታወቃል፡፡
የቤት ኪራይ ዋጋን በሚመለከት በአሜሪካ እንደሚሠራው ዓይነት ጥናት በኢትዮጵያ ይፋ ሲደረጉ ባይታም፣ ለአገሪቱ የዋጋ ንረትና ግሽበት አስተዋጽኦ እንዳለው የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ በየወሩ ይፋ የሚያደርገው የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ አሃዝ ያመለክታል፡፡ የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ (ሸማቾች ለተወሰኑ ዕቃዎችና አገልግሎቶች የከፈሉትን አማካይ የዋጋ ለውጥ ለመለካት የሚያገልገግል ጠቋሚ አሃዝ ነው ሲል ኤጀንሲው ይገልጸዋል) ሲተነትን፣ ምግብ ነክ የሆኑና ምግብ ነክ ያልሆኑ የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ብሎ ባስቀመጣቸው መለኪያዎች መሠረት፣ ምግብ ነክ ካልሆኑት መመዘኛ አሃዞች መካከል፣ የሸማቾች የችርቻሮ መመዘኛ ዋጋን በዘንድሮውና በዓምናው መካከል ያለውን ልዩነት በማነፃፀር ያቀርባል፡፡ በዚህ መሠረት ከቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ ከውኃና ኢነርጂ ወጪዎች ጋር የተደለደለው የቤት ኪራይ አንድ ላይ 7.8 ከመቶ ጭማሪ በማሳየት፣ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ከነበረው አገር አቀፍ ጠቅላላ የችርቻሮ ኢንዴክስ ጋር ሲነፃፀር የ7.9 ከመቶ ጭምሪ እንዲሳይ ምክንያት ለመሆን መቻሉን የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ አድርጓል፡፡ እስካሁን ባለው አካሄድም የቤት ኪራይ ወጪ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ ሆኖም ይህ ጠቋሚ አሃዝ የቤት ኪራይ ዋጋን በተናጠል ካለማመልከቱም በላይ፣ ምን ያህል የቤት ተከራዮች እንዳሉ (የመኖሪያና የሥራ ቦታ) አያሳይም፡፡ ምን ያህል ተጨማሪ ተከራይ ሊኖር እንደሚችል፣ የኪራይ ዋጋ በቀጣዩ ወር ወይም ዓመት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ወዘተ. ያለውን ትንታኔም የሸማቾች ዋጋ መመዘኛው አይጠቁምም፡
posted by TAMRAT YDEGO 

ከሙስና ጋር በተያያዘ ሲፈለጉ የነበሩት አቶ ጌቱ ገለቱ እንግሊዝ አንደሚገኙ የቅርብ ሰዎች አረጋገጡ።(እየሩሳሌም አረአያ)


ሼህ አላሙዲ ከምክትላቸው አቶ አብነት እንዲሁም አበበ ባልቻ (የሰውለሰው አስናቀ) ጨምሮ በበርካታ የቅርብ ሰዎቻቸው ታጅበው ዋሽንግተን ዲሲ ከመጡ 15 ቀን አለፋቸው። ከአገር ቤት ዘፋኞችን ጭምር አስመጥተዋል። ዲሲ በሚገኝ አንድ የምሽት መዝናኛ አዲሱን የፈረንጆች አመት በተለየ ግብዣና ፈንጠዝያ አሳልፈዋል። በዚህ ምሽት እዚህ ያሉት የገዢው አምባሰደርና ተከታዮቻቸው ያሳዩት የነበረው እጅግ ራስን የሚያዋርድ ተግባር በአንዳንድ ታዳሚዎች ግርምትን ፈጥሯል። ባለሃብቱና ተከታዮቻቸው አሜሪካ ከመጡ ዛሬ 18 ቀን ሆናቸው። ይህ ያልተለመደ በመሆኑ የተለያዩ ወሬዎች መናፈሳቸው አልቀረም። 

ለመሆኑ “ምክትላቸው ከጉምሩክ ጋር በተያያዘ ስለሚፈለጉ ነው” የሚባለው ወሬ ነው ወይስ…?…አንድ ለባለሃብቶቹ ቅርብ የሆነ ሰው እንደነገረኝ ሁለት ነገሮች እንደሚወሩና አንደኛው ከላይ የተገለፀው ሲሆን ሌላኛውና እርሱ የሚያውቀው ምክትሉ ቦርጭ (ፋት) ለመቀነስ ሲሉ 7 አሜሪካዊያን እንደቀጠሩ እንደሚያውቅ ነግሮኛል። ሌሎች መረጃዎች ቢኖሩም… አሁን ማለፍን መረጥኩ። …ከሙስና ጋር በተያያዘ ሲፈለጉ የነበሩት አቶ ጌቱ ገለቱ እንግሊዝ አንደሚገኙ የቅርብ ሰዎች አረጋግጠዋል። ግን ጌቱ ብቻ ለምን?…ሲሉ ጠይቀዋል።…እስር ቤት የተወረወሩት የኬኬ ባለቤት የደርጉን ባለስልጣን ሻ/ል ፍቅረስላሴ ወግደረስን በየሳምንቱ እየሄዱ ይጠይቁትና ከተፈታም በኋላ ቤትና መኪና ገዝተው እንደሰጡት ተነግሯል። እስሩን ከዚህ ጋር የሚያያይዙት አሉ። 

እውነቱ የቱ ነው?…ሌላው ረቡዕ ማታ የፈረንጆቹ አዲስ አመት የሚገባበት ቀን ነበር። የፌስቡክ ወዳጄ ቢኒያም ታምራት “ለፈረንጆቹ 2014ኒው ይር እኔና እናንተን ምን አገባን? ” ያለው እውነት ነው። ረቡዕ ማታ በዲሲ ሃበሻ በሚበዛበት መንደር 20 ሃበሾች በስካር ተነሳስተው ከመደባደብ ባለፈ በድንጋይ እስከመፈነካከት ደርሰዋል። የሚገርመው ድንጋዩን ከየት እንዳመጡት ነው፤ በዚሁ ድብድብ ሶስት ሴቶች በስለት ተወግተው ጉዳት ደርሶባቸዋል። ፖሊስ ደርሶ ሁሉንም ወደ እስር ቤት መውሰዱ ታውቋል። ሽጉጥ የተተኮሰ ሲሆን ከማን ወገን እንደተተኮሰ ግን አልታወቀም። ..የተፈፀመው ነገር አሳፋሪ ነው። ብዙዎች ተጎድተዋል። በጩቤ ሴትን ልጅ መውጋት (ያውም አሜሪካ) ምን አይነት የጭካኔ ድንቁርና ይሆን?….ጥፋተኞቹ ከታሰሩ በኋላ ከአሜሪካ እስከመባረር የሚደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል። የሚያሳዝነው አንዳንዶች ትንሽ ሲቀምሱ .መደባብደብን እንደትልቅ ጀብድ መቁጠራቸው ነው። በአሉ የነጮች ሆኖ ሳለ የሚፈነጥዙት፣ ስለት እስከመማዘዝ የሚደርሱት የእኛው ጉዶች። ይህን ምን ይሉታል?

posted by TAMRAT YDEGO 

Wednesday, January 1, 2014

የከተማ አብዮት! (ተመስገን ደሳለኝ)

የከተማ አብዮት! (ተመስገን ደሳለኝ)

ከሩሲያውያኑ ቦልሼቪክና ሜንሼቪክ አንስቶ፣ የእኛዎቹ ኢህአፓና መኢሶን በፊት-አውራሪነት እስከ ተሳተፉበት ድረስ ያሉ በደም የጨቀዩ አብዮቶች በሙሉ በከተሞች የተካሄዱ ሲሆን፣ አብዛኛው አጋፋሪዎቻቸው
ደግሞ ልሂቃኖች እንደነበሩ በጉዳዩ ዙሪያ የተፃፉ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ይሁንና እነዚህ አብዮቶች (የተሳኩትም ሆነ የከሸፉት) ሰላማዊውንና ህጋዊውን መንገድ የተከተሉ ባለመሆናቸው ዛሬም ይዘገንናሉ፤ ለወደፊቱም ባልተደገሙ ያሰኛሉ፡፡ ስለምን ቢሉ? ግድግዳው ላይ የተቸከቸከው ፅሁፍ እንዲህ የሚል ምላሽ ያስነብባልና፡- በጭቁን ሕዝብ ስም የብዙሀኑን ቤት አፍርሰዋል፤ ሀገርና ታሪክ ለመቀየር የማይሳናቸው አፍላ ወጣቶችን እርስ በእርስ አጫርሰዋል፤ ‹አንቱ› ሊባሉ የሚችሉ ምሁራንን በአንድ ጀንበር ወደ ትንታግ ነፍሰ-ገዳይነት ቀይረዋል፤ ክስረቱም ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ጠባሳ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሷል…

በርግጥም ያ ወቅት መደማመጥ፣ መነጋገር፣ መወያየት፣ መቻቻልን… የመሳሰሉ ምክንያታዊ እሴቶች ህቡዕ ገብተው፤ መጯጯኽ፣ መነቋቆር፣ መፈራረጅ፣ መገዳደል… የገነኑበት ነበር፤ ለዚህም ይመስለኛል ሀገር ሊረከብ የተዘጋጀ አንድ ትውልድ፣ በተኮረጀ ርዕዮተ-ዓለም፣ ባልጠራ ፕሮግራም እቅሉን ስቶ ‹ማርክስ እንደፃፈው›፣ ‹ሌኒን እንዳብራራው›፣ ‹ማኦ እንዳስተማረው›፣ ‹ሆጃ እንደመከረው›… በሚል ጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ስቶ-በማሳት፣ ሀገር ምድሩን የጦር አውድማ አድርጎ ማለፉ የትላንት የቁጭት ትዝታ የሆነብን፡፡ በአናቱም ዛሬ ‹‹ነፃ አወጣናችሁ›› እያሉ ጃሎታ የሚመቱት የኢህአዴግ መሪዎች ከዚሁ ምንጭ የተቀዱ፣ ግና በቃላት ስንጠቃና በጎሳ ጠባብ አስተሳሰብ የተለዩ የትውልዱና የመንፈሱ ተጋሪ በመሆናቸው፣ የሁነቱ ‹ታሪክ›ነት ለተሰዉት እንጂ፣ ለእነርሱ ‹ሀገር እየመራንበት ነው› የሚሉበት ‹ፖለቲካ› ነውና፣ የነገይቷ የምንወዳት ኢትዮጵያችን መፃኢ ዕድል ገና ከእርስ በእርስ ግጭት ስጋት አለመላቀቁን ያመላክታል፡፡ በዚህ ፅሁፍም የምንዘመርለት የ‹አትነሳም ወይ?› ድምፅ አደገኛውን ስርዓት የመቀየሪያው ጊዜ አሁን በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ግን እነኢህአፓ ተቸንፈው የተሰናበቱበትም ሆነ ኢህአዴግ ድል አድርጎ የመጣበት መንገድ ለዘመኑ መልካም ተሞክሮ ሊሆን ይችላል እንደማለት አይደለም፤ ምክንያቱም በእኔ እምነት የእነርሱ ‹ፋኖተሰማራ…› ጊዜው በበየነበት ሙዚየምና የታሪክ ትምህርት ክፍል ውስጥ ብቻ ካልተገደበ ጉዳቱ በቀላሉ የሚጠገን ካለመሆኑም ባለፈ፣ የምንመኘውን ለውጥ ሊያመጣ አይችልምና ነው፡፡
የሆነው ሆኖ ለትውልዱ ክቡድ ጥያቄ ስኬታማነት መንገድ መሪ አብርሆት መሆን የሚችሉ የደም ግብር ያልጠየቁ፣ ፍፁም ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ በከተሞች ተካሂደው ሀገርና ህዝብ ያለ ብዙ ኪሳራ በአሸናፊነት የወጡባቸው በርካታ አብነታዊ አብዮቶች (እንደ አረቡ ፀደይም ሆነ እንደ አውሮፓውያኑ ጆርጂያና ዩክሬን ብርቱካናማ-አብዮቶች) መኖራቸው እውነት ነው፤ እንዲሁም በእነርሱ መንፈስ መቀደስ፣ በእነርሱ ፀበል መጠመቅ የአምባገነኑንና የበደለኛውን ሥርዓት እድሜ ለማሳጠር የሚያበረታ ኃይል ማስረፁ እውነት ነው፡፡
ከተማን እንደ ጠላት
የ‹ያ ትውልድ› የጠብ-መንጃ ትንቅንቅን በድል የተሻገረው ኢህአዴግ (ከልቡ አምኖበት ባይሆንም) ይህንን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለው በተለይም ለአርሶ አደሩ ጥቅም መሆኑን በአገኘው አጋጣሚ ሳይናገር አያልፍም፡፡ በግልባጩ ደግሞ የከተማ ነዋሪዎችን ‹ጠላት› አድርጎ በመፈረጅ ሲገነግን ተደጋግሞ ተስተውሏል፤ በርግጥ የዚህ መግፍኤ በብሔር እና በሀይማኖት የከፋፈለውን ሕዝብ፣ በመደብም ለያይቶ የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ ለማድረግ እና በየአምስት ዓመቱ በሚያካሄደው የይስሙላ ‹ምርጫ› ኮረጆ ገልብጦ ሲያበቃ የፈረደበት ምስኪን አርሶ አደር ‹መርጦኛል› ለሚለው የተለመደ ሰበቡ ‹ይጠቅመኛል› በሚል ለማመቻቸት ‹አዛኝ ቅቤ…› ተቆርቋሪ በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ይህም ሆኖ ድርጅቱ ይህንን የማጭበርበሪያ ስልት በደደቢት በረሃ ራሱ የቀመረው ነው ብሎ ለመከራከር የሚያስችል ገፊ ጭብጥ ይኖራል ብዬ አላስብም፤ ምክንያቱም በአንዳንድ የዓለማችን ሀገራት የፖለቲካውን ኃይል ከጨበጡ በኋላ በሕዝባቸው ላይ ነጋሪት ጎስመው ሞትን ከነዙ፣ ስቃይን ከረጩ እርኩሳን መሪዎች (ፓርቲዎች) ድርሳናት ቃል-በቃል የተገለበጠ መሆኑን የሚያስረግጡ (በስነ-አመክንዮ) የተቀኙ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላልና፤ እንደምሳሌም አንዱን በአዲስ መስመር እንምዘዘው፡-
የ‹ኬመር ሩዥ› መንገድ
በተለምዶ ‹ኬመር ሩዥ› (Khmer Rouge) በመባል የሚታወቀውና አክራሪ ኮምኒስታዊ የገበሬዎች ድርጅት እንደሆነ የሚነገርለት ‹‹Communist Party of Kampuchea /CPK/›› እ.ኤ.አ ከ1975-1979 ዓ.ም ድረስ፣ በወጣት የገበሬ ሠራዊት ታግዞ በካምቦዲያ መንግስታዊ ሥልጣን ተቆናጥጦ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ጨካኝና አፍቃሪ ቻይና የሆነው የፓርቲው ሊቀ-መንበር ፖል ፖትም (Pol Pot)፣ ማኦ ዜዱንግ ‹‹የሀገሬን ኢኮኖሚ ያሳድግልኛል›› በማለት ያረቀቀውንና በግብርና ላይ የሚያተኩረውን ‹‹Great Leap Forward›› ፕሮግራም፣ ‹‹Super Great Leap Forward›› በሚል ተቀጥላ እንደወረደ በመኮረጅ ‹‹ሙሉ የካምቦዲያን ሕዝብ ወደ ‹እርሻ መር-ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ› (Agrarian Society) እቀይራለሁ›› ብሎ ያደረገው ሙከራ ወጪ-ኪሳራን ያወራረደው ሁለት ሚሊዮን ዜጎቹንለህልፈት በመዳረግ እንደ ነበር የታሪክ መፃህፍት ያትታሉ፡፡
ከሁሉም የከፋው ግን ፖል ፖትና ጓዶቹ ‹‹እውነተኛ ዜጋ ገበሬ ብቻ ነው›› በማለት የከተማ ነዋሪዎችን በጠላትነት ከፈረጁ በኋላ ‹‹ማህበረሰባችንን ለማንፃት›› በሚል የቁም-ቅዠት ምዕራባዊ አስተሳሰብ የተንፀባረቀበትን ማንኛውንም ጉዳይ፣ የከተማ ሕይወትን፣ ኃይማኖትን፣ ትምህርትን፣ አንድ ብርም ቢሆን በግል መያዝን… በአዋጅ ማገዳቸው ነበር፤ እንዲሁም ኢምባሴዎችን፣ ጋዜጣና ቴሌቪዥን ጣቢያን ዘግተዋል፤ በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች የሚኖሩ ዜጎችን በማፈናቀል ወደ ገጠር አግዘው፣ በግዳጅ የእርሻ ሥራ ላይ አሰማርተዋል፤ ከዋና ከተማዋ ‹ፈኖሞ ፔንህ› (Phnom Penh) ብቻ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች ወደገጠር በእግር እንዲጓዙ በመገደዳቸው ሃያ ሺህ የሚሆኑት በጉዞ ላይ ወድቀው እንደወጡ ቀርተዋል፤ ገጠር የደረሱትንም ቢሆን ‹የግድያ ወረዳዎች› እያሉ በሚጠሯቸው የእርሻ ሥራ ላይ አሰማርተው ለአንድ ሰው በነፍስ ወከፍ በየሁለት ቀኑ አንዴ 180 ግራም ሩዝ ብቻ በመስጠት በረሀብ፣ በበሽታ፣ ብስቅየት እና በግድያ እንዲያልቁ አድርጓል፡፡ በመጨረሻም አገዛዙ በቬትናም ጣልቃ ገብነት እ.ኤ.አ በ1979 ዓ.ም በኃይል በመወገዱ፣ ፖል ፖት ከእነተከታዮቹ ሀገሩ ከታይላንድ ወደምትዋሰንበት ጠረፍ አካባቢ በመሸሽ፣ የትጥቅ ትግል እንደአዲስ ጀምሮ ለረዥም ዓመታት ከታገለ በኋላ፣ እ.ኤ.አ በ1997 ዓ.ም እርጅና ተጭኖት በህግ ቁጥጥር ስር በዋለ፣ በዓመቱ ከልብ ጋር በተያያዘ ህመም ምክንያት ህይወቱ ማለፉ ይታወቃል (በነገራችን ላይ ይህ ድርጅት የሽምቅ ውጊያ ከመጀመሩ በፊትም ሆነ በኋላ የተጠናከረበትን ምስጢራዊ መንገድ ጨምሮ የተከተለው ስልት ከሞላ ጎደል ከኢህአፓና ህወሓት አፈጣጠር ትርክት ጋር ተመሳሳይነት አለው)
ኢህአዴግ እንደ ‹ኬመር ሩዥ›
ከሁለት አስርተ ዓመታት የሥልጣን ቆይታም በኋላ፣ የከተማ ነዋሪዎችን በጠላትነት ካሰፈረበት ጥቁር መዝገቡ ላይ መሰረዙ ያልሆነለት ኢህአዴግ ‹እንደ ኬመር ሩዥ ሁሉንም የጭካኔ ተግባራት በአደባባይ ፈፅሟል› ተብሎ ባይወነጀልም፣ ተመሳሳይ ስልቶችን በመኮረጅ በረቀቀ መንገድ አለዝቦ መተግበሩን ግን መካድ አይቻልም፡፡ እንዲሁም የሁለቱ ድርጅቶች ዋነኛ ልዩነት ወደ እንዲህ አይነቱ የጥላቻ ጠርዝ
የተገፉበት ምክንያት ይመስለኛል፤ ይኸውም ፈላጭ ቆራጩ ፖል ፖት በከተሜው ላይ የከፋ ቂም የቋጠረበት መነሾ፣ ከገበሬ ቤተሰብ መገኘቱን ጨምሮ፣ ከአስተዳደጉ ጋር በሚያያዙ ‹ህመማቸው-ህመሜ› በሚል ሲባጎ የተቋጠረ ሲሆን፣ መለስና ጓዶቹ ደግሞ የሥልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም በማስላት ብቻ መሆኑ ነው፤ መቼም መሬት የረገጠውን እውነታ ተመልክቶ የሀገሬ አርሶ አደር ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በዘለለ፣ ከከተሜው የተለየ የመልካም አስተዳደርም ሆነ የመሰረተ-ልማት ተጠቃሚ አለመሆኑን መረዳቱ አዳጋች አይደለም፡፡ የሆነው ሆኖ የኢህአዴግ ‹ፀረ-ከተሜነት› እንዲህ በግላጭ አፍጥጦ የወጣው ከምርጫ 97 በኋላ ነው፤ በወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትሩ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ፣ ድርጅቱ በከተሞች መሸነፉን ከገለፀ በኋላ፣ በገጠር ሙሉ በሙሉ ስለተሳካለት መንግስት ለመመስረት የሚያስችል የመራጭ ድምፅ ማግኘቱን አውጇል፤ ይህንንም ተከትሎ ግንባሩን ያልመረጡ የከተማ ነዋሪዎች በተቀነባበረ ሴራ የጥቃት ዒላማ መሆናቸውን የሚያመላክቱ በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በተለይም በድህረ-ምርጫው ከተሜውን ዒላማ ያደረጉ በስራ ላይ የዋሉ አፋኝ ህጎች እና ፖሊሲዎችን ጨምሮ በደባ የተፈፀሙ መንግስታዊ ጥፋቶችን ዘርዘር አድርገን እንያቸው፡፡

መሬትን በተመለከተ የወጣውን የሊዝ አዋጅ በቀዳሚ ምሳሌነት እናንሳው፤ ፓርቲው በ1987 ዓ.ም ባፀደቀው ህገ-መንግስት የመሬት ፖሊሲውን አንዱ ዕማድ አድርጎ በማካተቱ፣ የመንግስት ጭሰኝነትን (Tenants of the state) በገጠሩ ክፍል ሲያሰፍን፣ የመሬት ከፊል ባለቤትነትን ደግሞ ለከተሞች እንዲፈቅድ አድርጎት ነበር፡፡ እናም የግል ይዞታን መሸጥ (መንግስት ለሚፈልጋቸው ‹‹ልማቶች››ም ሆነ
በሊዝ ለመቸብቸብ ዜጎችን የማፈናቀል መብት ከማግኘቱ ውጪ) እስከ 97ቱ ድህረ-ምርጫ ድረስ ተፈቅዶ የዘለቀበት ሂደት፣ በዚህ የሊዝ አዋጅ በመሻሩ የተነሳ፣ ነዋሪው መሬት በመሸጥ ሊያገኝ ይችል የነበረው ገቢ ተጨምቆ ወደ መንግስት ካዝና እንዲሻገር ሆኗል፡፡ የዚህን አዋጅ ‹ፖለቲካዊ ንባብ› ውስጥ የምናገኘው ጭብጥ፣ በከፊልም ቢሆን መሬት ላይ የቆመውን የሀብት መሰረት በመናድ፣ የተቃውሞ ኃይሉ የድጋፍ መዕከል እንደሆነ ያመነውን የማህበረሰብ ክፍል ክፉኛ ማድቀቁን ስንረዳ ነው፡፡ አዋጁን እንለጥጠው ካልን ደግሞ ግንባሩ በገጠሩ ያነበረውን የዜጎች የመንግስት ጭሰኝነት በጠመዝማዛ መንገድ፣ በተለይም በአዲስ አበባ የመፈጸም ዕቅዱ አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡

የኢህአዴግ ከተማንና ከተሜዎችን የመፍራት አባዜ ከጫካ ትግሉ ጋርም በረዥሙ የሚተሳሰር ነው፡፡ በወቅቱ በጥላቻ ከመተያየት አልፎ ደም የተቃባቸው ኢህአፓን መሰል ኃይሎች መሰረታቸው ከተሞች ላይ እንደነበረ ይታወቃል፤ በአናቱም በትግሉ መጠናቀቂያ ዋዜማ እና ማግስት ሊገዛለት ያልቻለው (ማማለሉ ያልተሳካለት) ልብ በተለይ የአዲስ አበቤዎችን ነበር፤ በ1980ዎቹ መጀመሪያም ፓርቲው አንገት ላይ ታንቆ ሊደፋው የነበረው ዋነኛ ጉዳይ፣ ብሔር ተኮር ስርዓቱ ህገ-መንግስታዊ ድጋፍ ሲያገኝና የብሄር ፖለቲካ ብቸኛው የድጋፍም የተቃውሞም ተዋስኦ እንዲሆን መደረጉ ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ በኢትዮጵያዊብሔርተኝነት መንፈስ ከተገራው የአዲስ አበቤ ብሔር ዘለል ማንነት ጋር እንዲህ በፊት ለፊት መጋጨቱ፣ ከተማይቱን በወረራ የያዛት እስኪመስል ድረስ በጥላቻ እንዲዘምቱበት አነሳስቷል፡፡
ሁለተኛው ምዕራፍ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ የመጣው የአሰብ ወደብን ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንዲካለል የመፈለግ የከተሜዎቹ ግፊት ነው፡፡ ጦርነቱ ሲያበቃና የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ሲገደዱ የነዋሪው ቁጣ ብርቱ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ይህ እውነትም ሌላኛው ፓርቲውን ቂም ያስቋጠረ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ በድህረ-ምርጫ 97 የፀደቀውና አፋኝነቱ በተግባር የተረጋገጠው የሲቪል ማህበረሰቡን የሚመለከተው አዋጅም ‹የብዙዎች ተቋማት ዋናመቀመጫ አዲስ አበባ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የወጣ ነው› በማለት ከየአቅጣጫው ይነሳ የነበረውን የተቃውሞ ውግዘት አጣጥሎ፣ በሥራላይ ባዋለበት ዓመት በርካታ ተቋማትን ከማፈራረሱ አኳያ፣ መጀመሪያውንም ለእንዲህ አይነቱ ክፉ እርምጃ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ወደሚል ጥርዝ ይገፋል፡፡ በተጨማሪም ያለፉትን ሃያ ሁለት ዓመታት ሙሉ በአይኑ መዓት የሚያያቸው ምሁራን፣ የነፃው ፕሬስ አባላት እና በየዘመኑ ከባድ ተግዳሮት የፈጠሩበት የተቃውሞ ስብስቦች ጠንካራ መሰረት በከተማይቱ ውስጥ መሆኑ ጥላቻ እና የጭካኔ እርምጃዎቹን አብዝቶታል፡፡
ሌላው አገዛዙ በከተሜዎች (በሸማቾች) ላይ ያለውን ስር የሰደደ ጥላቻ የሚያሳዩት፡- ከምርጫው በኋላ ጤናማ ያልሆነ የዋጋ ንረት በከፋ ደረጃ ማሻቀቡ፣ ፍትሃዊ ያልሆኑ የተለያዩ የግብር ህጎች በእንጀራ እና ሽንኩርት ቸርቻሪዎች ላይ ሳይቀር መተግበራቸው ነው፡፡ በተለይም ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ የተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ዋነኛ አባባሽ ኃይል የምግብ ዋጋ መናር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ
የምግብ ዋጋ መናር በዋነኝነት ቋሚ ደሞዝ ተከፋዩ የከተማ ነዋሪው ተጎጂ መሆኑን የስርዓቱ ባለስልጣናትም ይቀበላሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ከሁለት ወራት በፊት በ‹‹አዲስ ዘመን›› መፅሄት የተጠየቀው የፋይናስና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ ‹‹በ2006 ዓ.ም የሚጨመር ደሞዝ አይኖርም›› ከማለቱ ባለፈ ‹‹ነገ ይችን አገር ወደተሻለ የሚያደርስ በጎ መስዋዕትነት ነው›› ሲል በከተሜው መከራ ላይ አላግጧል፡፡ በርግጥ ይህ ሁሉ መዓት ከመውረዱ በፊት በ1998 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ራሱ አቶ መለስ በደቡብ ክልል ወደምትገኘው ይርጋለም ከተማ ድረስ ሄዶ የሙዝ አምራች አርሶ አደሮችን ሰብስቦ ካነጋገረ በኋላ፣ እንዲህ ለፍተው የሚያገኙትን ምርት ለከተሜው በርካሽ መሸጣቸው አግባብ አለመሆኑን ቀስቅሶ ዋጋውን በአራት እጥፍ እንዲጨምሩ በማድረጉ የተፈጠረው የገበያ እጥረት፣ ምንም እንኳ መልሶ አምራቾቹን ሰለባ ቢያደርግም፣ ኩነቱ የጠቅላይ ሚንስትሩን ቀጣይ ዕቅድ የሚያመላከት ነበር፡፡

በከተሞች ውስጥ እየተደረገ ያለው ‹‹የሰፈራ ፕሮግራም››ም (Urban Resettlement) አንዱ ሊነሳ የሚገባው ነጥብ ነው፡፡ በእርግጥ በዚህ ዕቅድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተሻለ የመኖሪያ ቤቶች ተጠቃሚ እንደሆኑ ማየት እንችል ይሆናል፡፡ ጥያቄው የሚነሳው ግን፣ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎችን ከሌሎች የፈረሱ የከተማዎቹ ክፍሎች ከሚመጡት ጋር በአንድ አዳብሎ በኮንዶሙኒየም ቤቶች አጥሮ የማስቀመጡ አንደምታ ላይ ነው፡፡ የዚህ ዕቅድ ክፉ ገፅ የሚገባን በረዥም የአብሮነት መስተጋብር (ሶስት መንግስታትን መሻገር የቻለ የአንድ አካባቢ ነዋሪነት) የተገነባው የጋርዮሽ ፖለቲካው አረዳድ እና የእርስ በእርስ ፍፁም መተማመን፣ 97ን ጨምሮ በተለያዩ ወቅቶች በተነሱ ተቃውሞዎች ወጥ ምላሽ እንዲሰጡ ማደፋፈሩን (አራት ኪሎን የመሳሰሉ አካባቢዎች) አስታውሰን፣ በመልሶ ማስፈሩ ደግሞ የአንዱን አካባቢ ነዋሪ በታትኖ ወደተለያዩ ሳይቶች መውሰዱን ስንመለከት ነው፤ ይህ መራራ እውነታም የገዥዎቻችን ጥላቻ ስር የሰደደ መሆኑን እና የአምባገነናዊ ስርዓቱን ዕድሜ ለማራዘም ያለመ እንደሆነ ይጠቁመናል፡፡
(ስርዓቱ በከተሜዎች ላይ የሰረፀበትን ጥልቅ የጥላቻ ፅንፍ እንዲህ ከተመለከትን፣ የከተማ አብዮት፣ ማኦኢዝም ከሚያዘው ከገጠር ከሚነሳው ብረታዊ ትግል ጋር ያለውን ልዩነት፣ በአረቡ ፀደይ ተሞክሮ በመንተራስ መፈተሹን፤ እንዲሁም የኢህአዴግ ግድፈቶች (Achilles’ heel) የከተማ አብዮትን ለማስነሳት ያላቸውን አስተዋፅኦ፣ በአደባባይ ሊያሰባስቡ የሚችሉ ጥያቄዎች ምን ቢሆኑ የተሻለ ነባራዊውን እውነት ያንፀባርቃሉ… የሚሉትን ጉዳዮች እና መንገዱን ስለሚመሩ የሚችሉትን መልከአ-ቡድኖች ማንነት ሳምንት እመለስበታለሁ)
ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com
posted by ታምራት ይደጎ