Wednesday, February 5, 2014

ትምህርት ቤታችን እና ኮሚኒቲውን የከበበው አደጋ …!




የመምህራን ማስጠንቀቂያ …
ሰሞነኛው የጅዳዎች ጉዳይ የመኖሪያ ፈቃድን በማስተካከል ዙሪያ ቢሆንም ከ 3000 (ከሶስት ሽህ) በላይ ታዳጊዎችን የሚያስተናግደው የጅዳው አለም አቀፍ ት/ቤት አሁንም አደጋ ላይ መሆኑን እየሰማን ዝም ብለናል!  ከሳምንታት በፊት መምህራን አመጽ አድርገው ነበር። ከቀናት በፊትም  25 መምህራን ስብሰባ ተቀምጠው፣ በአንድ አቋም ጸንተው ጠንከር ያለ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል። ላለፉት 8 ወራት በትምህርት ቤቱ ባለቤት በኮሚኒቲው ጉዳያቸው ቢያዝም እስካሁን ከወሬ ያላለፈ አርምጃ አለማየታቸውን ገልጸዋል።  25 ቱ school letterመምህራን ለትምህርት ቤቱ አስተዳደር፣ ለኮሚኒቲው፣ ለጅዳ ቆንስልና ለወላጅ መምህራን ህብረት ባስገቡት ደብዳቤ እስከ ቀጣዩ ሳምንት የሁለተኛው የትምህት አጋማሽ መጀመሪያ የመኖሪያና የስራ ፈቃዳቸው ተስተካክሎ ካልተሰጣቸው  በማስተማር መደበኛ ስራቸው እንደማይገኙ በላኩት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ማስጠንቀቃቸውን በእጀ የገባው ሰነድ ያመላክታል!
የወላጅ መምህራን ህብረት ስብሰባ ጥሪ …
“ወላጅና መምህራን ህብረት” በሚል ካች አምና በመንግስት ትዕዛዝ የወላጅ ኮሚቴን የተካው ኮሚቴ በትምህርት ቤቱ ዙሪያ ለመምከር ለወላጅ ስብሰባ ጠርቷል። ኮሚቴው የሳውዲን የምህረት አዋጅ ማለቅ ተከትሎ የጅዳ አለም አቀፍ ትምህርት ቤት ለሳምንት ሲዘጋ የሚወክለውን ወላጅም ሆነ መምህራኑን ብሎ ድምጹን አላሰማም። ትምህርት ቤቱ ካንድም ሁለት ሶስቴ በመምህራን ስራ ማቆም አድማ ሲናጥ፣ ከፍተኛ የማህበረሰቡ መዋዕለ ንዋይ ከመጋረጃ ጀርባ ለሚደረጉ የመምህራን እና ሰራተኛ ዝውውር መባከኑ ሲሰማ የዝሆን ጀሮ ስጠኝ ማለቱ አይደንቅ ይሆናል። የመንግስት ሃላፊዎች ትኩረትና ጥበቃ የማይደረግለትን  የትምህርት ማዕከል ህልውና ለማስጠበቅ ስብሰባ መጥራትና ወላጁን ባለማማከሩ ተወቃሽ ከመሆን ግን አላመለጠም። ለሚታየው እንግዳ፣ ለሚሰማው ባዳ መሆናቸው ያስከፋው ወላጅ ከትናንትም ዛሬ ተስፋ ቆርጧል።
ዛሬ የወላጅ መምህራን ህብረት ተብየውን ምን እንዳሰናከለው፣ ምን እንዳሽመደመደው መስማት ባያጓጓም የወደፊት የወላጁን፣ የመምህራንንና የታዳጊዎችን ትምህርት ቤት አደጋ ላይ መውደቅ  እያየ ስለያዘው አቋም መስማት ጓጉተናል። ማስታወቂያ ባወጣ በሳምንቱ፣ ስብሰባውን ሊያደርግ ቀናት ሲቀሩት ደግሞ ዛሬ ምሽት የህብረቱ አመራሮች በጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት ሃላፊዎች ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርተዋል። አሁንም ኮሚቴው በዚህ ስብሰባ ምን በል ሊባልም ሆነ ከወላጅ መምህራን ጋር በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንዳይነካ የሚፈለገውን ቦታና  እንዳይታለፍ የሚፈለገው የቀይ መስመር ገደብ ምን ሊሆን እንደሚችል አንገምትም።  ብቻ ሁነኛ ባለቤት አጥቶ አንደ ስደተኛው ተገፊ ወገን ለሚከላተመው የ3000 ታዳጊዎች ትምህርት ቤት መጻኢ ህይዎት ወላጁ በስብሰባው በመሳተፍ መምከር ይኖርበታል።sch letter
በመግስት ሊደራጅ ያታቀደው ኮሚኒቲ …
ዛሬ ያለው ኮሚኒቲ በአዲስ የመተኪያው የምርጫ ጊዜ በቆንስል መስሪያ ቤቱ ትዕዛዝ ተላልፏል። የሚተካው ኮሚቴ ደግሞ የሚደራጀው በመንግስት እንደሆነ እየተነገረን ነው። የምርጫው መዘግየትም ዋናው ምክንያት ይህ እውነት መሆኑ ቆንስል መስሪያ ቤቱ ከመካከለኛው ምስራቅ አገኘሁ ያለውን ሞዴል የኮሚኒቲ ህግና ደንብ ረቂቅ ጊዜውን ለጨረሰው ኮሚኒቲ ይፋ አድርጎታል። ቅንነት በሌለበት መንደር በወረቀት ላይ በሰፈረ ህግና መመሪያ ለወጥ ያመጣ ይመስል የማይገባ ስራ መሰራት ተጀመሯል። የሚጠፋውን ጊዜና የሚባክነውን የማህበረሰብ ንብረት ብክነት ነዋሪው ህብረት ፈጥሮና ማህበሩን ከፖለቲካና ከድርጅት አደረጃጀት ጣለቃ ገብ ሂደት በማስቆም ነጻ ካላወጣው አደጋው የከፋ እንደሚሆን ጥርጣሬው ያየለብኝ ለእኔ ብቻ ቢሆን መልካም ነበር ። ግን አይደለም። ብዙ ነዋሪ አዲሱን አካሄድ አልወደደውም!
ኮሚኒቲውን በአንድ ባንዴራ ስር ከማደራጀት ተወጥቶ በብሔር ብሔረሰብ ስብጥርና የፖለቲካ ድርጅት ሰወች በኮሚኒቲው በማሰግሰግ የሰራነው ስራ እንዳላዋጣን እናስተውለው። ወላጁም ሆነ አብዛኛው የጅዳና አካባቢው ነዋሪ ለአመታት የራቀው ኮሚኒቲ የጥቂቶች መፈንጫ ከሆነ ወዲህ የሆነውን ቆም ብለን እናስብ! እናም ቢያንስ በልጆቻችን ትምህርት ቤትን ህልውና ለማስጠበቅ ኮሚኒቲውን ሊውጠው ከተዘጋጀ ክፉ አውሬ አፍ ለማዳን እንረባረብ!  በኮሚኒቲውና በትምህርት ቤቱ ዙሪያ በሚደረጉ ስብሰባዎች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የልጆቻችን ትምህርት ቤት ለመታደግና ለህልናው ወሳኝ የሆነውን ኮሚኒቲ ከወደቀበት አዘቅት አውጥተን ለብሩህ ተስፋ ሂደቱ እንታደገው፣ እናጎልብተው!  ወላጅና መምህራን ህብረት በጠሩት ስብሰባ ተሳታፊ እንሁን፣ በነጻነት ሃሳባችን እናንሸራሽር! የልጆቻችን ትምህር ቤተችን ከአደጋ እንታደገው!  ይህ ማንም የማይገሰው መብታችን ነውና!
ጀሮ ያለው ይስማ!
ነቢዩ ሲራክ

ምሁራኑ ሠልጣኝ፣ ሹመኞች አሰልጣኝ የሆኑበት ዩኒቨርሲቲ ሆኗል – ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ


addis ababa university
መጽሔታችን የአገራችን የትምህርት ሁኔታበከፍተኛ ደረጃ ችግር ላይ የወደቀ መሆኑን በመገንዘብ፣ የችግሩን ጥልቀት ለማወቅና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማስቀመጥ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ካደረጉ ምሁራን ጋር ተከታታይ ውይይቶችንስታደርግ ቆይታለች፡፡ በዚህ ዕትማችንም ውይይቱን በመቀጠል ከዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጋር ስለትምህርት ፍልስፍና፣ ስለዩኒቨርሲቲ ተልዕኮና ስለሌሎቸ ተያያዥ ጉዳዮች ቆይታ አድርገናል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው ለአብዛኛው የመገናኛ ብዙኃን ተከታታይ እንግዳ ስላልሆኑ ማስተዋወቅ ያለብን አይመስለንም፡፡ ውይይቱን እነሆ፡-
ዕንቁ፡-ውይይታችን በዩኒቨርሲቲባህሪና ትርጉም እንጀምር፡፡ ለመሆኑ ዩኒቨርሲቲ ምን ማለት ነው?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-ከሁሉ አስቀድሞ ይኼ ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ መልስ የሚሰጠው ሳይሆን በተለያየ ጊዜና በተለያየ የባህልና የአመለካከት አውድ ውስጥ ተፈትሾ ለመግለጽ የሚሞከር ጉዳይ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ በባህሪው የሕዝብ (‘ፐብሊክ’) እና የግል (‘ፕራይቬት’) የሆነ ልዩ ተቋም መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እንደሕዝብ ተቋምነቱ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ተሰማርቶ ለማኅበረሰቡ ይውላሉ ወይም አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን ነገሮች በማበርከት አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ እንደግል ተቋምነቱ ደግሞ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ የራሱ የሆነ ግብና ዕቅድ አንግቦ ለሰው ልጅ መንፈሳዊና አዕምሯዊ ብልጽግናንናበአጠቃላይ ዕውቀትን ለማጎናጸፍ የተቋቋመማዕከል ነው፡፡
አሁን የበላይነት ወደያዘው የአገራችን የትምህርት ፍልስፍና ስንገባ፣የዩኒቨርሲቲዎች ሕልውና የተመሰረተበትን የግል ጥሪና ፍላጎት ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ተቋማቱን የሕዝብ አገልግሎት አቅራቢ ብቻ ለማድረግመንግሥትና የዩኒቨርሲቲዎቹ የበላይ አስተዳዳሪዎች ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ በመሆኑም ለማኅበረሰቡ “ቀጥተኛ ጥቅም” አይሰጡም ያሏቸውን እንደፍልስፍና፣ ታሪክ፣ ሥነ-ጽሁፍ፣ ቋንቋና ሌሎች የሥነ-ሰብዕ ትምህርቶች እንዲቀጭጩ መደረግ ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች አልመረጡም በሚል ፈሊጥ የቅድመ-ምረቃ ፕሮግራሙ ወደመዘጋት እየደረሰ ነው፡፡
ዕንቁ፡-የዩኒቨርሲቲን ተፈጥሮና ጠባይ ከሞላ ጎደል ለመመልከት ትንሽ ወደታሪክ መመለስ ይኖርብናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለመሆኑዩኒቨርሲቲ እንደ ተቋም እንዴት ተጀመረ?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-ይኼ ጥያቄ ማንም ሰው እንደሚረዳው ሰፋ ያለ ትንታኔና ገለጻ የሚያስፈልገው ነው፡፡ ሆኖም ግን ጥቂት ነገሮች ለመግለጽ ያህል፣ በዚህ መስክጥናት ያደረጉትምሁራንእንደሚነግሩን ዩኒቨርሲቲ አውሮፓበ13ኛው እና በ14ኛው ክፍለ ዘመን ከደረሰችበት የመንፈስ፣ የባህል፣ የፍልስፍና… ወዘተ ሥልጣኔ የመነጨ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ታሪክ ዙሪያ ከጻፉት ምሁራን መካከል እውቅናን ያገኙትና በሰፊው የሚጠቀሱት ‘ቻርልስ ሆሜር ሀስኪንስ’ (Charles Homer Haskins) ናቸው፡፡ እንደሳቸው አቀራረብ ዩኒቨርሲቲ ከጥንታዊ ግሪኮችና ከሮማውያን ሥልጣኔ ጋር ግንኙነት ቢኖረውም በይዘቱና በጠባዩ የመካከለኛው ዘመን ውጤት ነው፡፡
ከአዕምሯዊ ይዘቱ አካላዊ ወደሆነው ቅርጹናአደረጃጀቱስንመጣ፣ ‘ሀስኪንስ’ በታሪክ ድርሳናቸው ላይእንዳብራሩትለዩኒቨርሲቲ (ግቢ) መፈጠር ምክንያት ከሆኑት ውጫዊ ሁኔታዎች መካከል በወቅቱ ተማሪዎችን የገጠማቸውየቤት ኪራይ ዋጋ መናር አንዱ ምክንያት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜብዙ ተማሪዎች ትምህርት ለመቅሰም ወደከተማ ይጎርፉ ነበር፡፡ የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የቤት ኪራይ ዋጋም በጣም እየናረ ሄዶ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ተማሪዎች የሚከፍሉትን የቤት ኪራይ ወጪ ለመቀነስ በአንድ ላይ መሰባሰብና በጋራ በመሆንተደራድረው የቤት ኪራይ ማስቀነስ ጀመሩ፡፡ ይሄ አንዱ ምክንያት ነው፡፡
ሌላው ምክንያት ደግሞ ከአስተማሪዎች የሚመጣው ችግር ነበር፡፡ ይኸውም በአንድ በኩል ገንዘብ እየተቀበሉ ከማስተማር ሥራቸው የሚጠፉ መምህራን ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይኼ ነው የሚባል የትምህርት ዝግጅት ወይም የማስተማር ችሎታ ሳይኖራቸው “መምህራን ነን” የሚሉም ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት ተማሪዎች ተሰብስበውና ተቋም ፈጥረው አስተማሪዎችንሕጋዊ ግዴታ ያስገቧቸው ጀመር፡፡ የትምህርት ዝግጅታቸውን የሚያሳይ ሰርተፊኬት መጠየቅምተጀመረ፡፡ ይህ ሰርትፊኬት ቀስ በቀስ ለዲፕሎማና ለዲግሪ መፈጠር አስኳል ሆነ፡፡
ዕንቁ፡- አንደኛው የዩኒቨርሲቲ ተልዕኮ ዕውቀት ማመንጨት ነው ካልን፣ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የዕውቀት ድርሻ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-የዩኒቨርሲቲን ተልዕኮና የእውቀትን ድርሻ በሚመለከት ሁለት አበይት የሆኑ ክርክሮችና አመለካከቶችአሉ፡፡ አንደኛው፣ ከ300 ዓመት በፊት በአጠቃላይ ስለ ትምህርትና ስለዕውቀት ጠቃሚነት የጻፉት (የሳይንስ አብዮት ጀማሪዎች ከሚባሉት አንዱ)እንግሊዛዊው ሮጀር ቤከን እንዳስተማሩት ዕውቀት ከተግባር ተለይቶ ሊታይ የማይችል፣ ለሰው ልጅ የኑሮ ደረጃ (በጤና፣በእርሻ …ወዘተ)አስተዋጽኦ ማድረግ ያለበት ነገር ነው፡፡በቤከን እምነት ዕውቀት የዕድገት ወይምየኑሮ ማሻሻያ መሳሪያ ነው፡፡ እንዲያውም ብዙ ጊዜ የሚጠቀስላቸው አባባል እንደሚነግረን ለእርሳቸው ‹‹ዕውቀት ማለት ሀይል ነው››፡፡
ወደ ሁለተኛው አመለካከት ስንመጣ ደግሞ ከመቶ ዓመታት በፊት “The idea of the University” በሚል ርዕስ ወሳኝ ድርሳን የጻፉትን ካርዲናል ኒውማንን እናገኛለን፡፡ እንደ እርሳቸው አመለካከት ዕውቀት የራሱ ተልዕኮ አለው፡፡ እንደ መገልገያ መሳሪያ ብቻ ሊታይ አይገባውም፡፡ ዕውቀት የሰውን ልጅ አዕምሮ የሚኮተኩትና ሰውን የተሟላ ፍጡር የሚያደርግ ነው፡፡
እነኝህን ሁለት የአመለካከት ዘይቤዎች መሰረት አድርጎ አሁንም አልፎ አልፎ ክርክሩ ቢቀሰቀስም፣ ባለንበት ዘመን አንድ ዩኒቨርሲቲ የተሟላ ነው የሚባለው ቢያንስ ቢያንስ የሚከተሉትን ሦስትዕቅዶች አንግቦ ሲንቀሳቀስ ነው፡፡ ይኸውምየመማር ማስተማር ሂደት የሚከናወንበት፣ ዕውነት ላይ ለመድረስ ጥናትና ምርምር የሚደረግበትና በልዩ ልዩ መስክለማኅበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጥበትተቋም ነው፡፡ በመሆኑም ምርጫው የሮጀር ቤከን “ጥቅማዊ” መንገድ ብቻ ወይም የካርዲናል ኒውማን“አዕምሮን ማበልጸግ” የተናጠል አስተሳሰብ አይደለም፡፡
dagnachew assefa
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
አሁን በአገራችንመንግሥት እየተከተለ ያለውንየትምህርት ፍልስፍና ስንመለከት፣ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ችግር-ፈቺና ቁሳዊ ጥቅምን ማምጣት የሚችሉመሆን አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ ይኼም ማለት፣ ትምህርት ራሱ በራሱ በጎና አስፈላጊ ነገር ሳይሆን መንግሥት ላቀደው የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት አጋርና አካል መሆን አለበት ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲውን በሚመለከት አንድ ትልቅ እንደ ደንቀራ ሆኖ የገጠመን ችግር ይኼ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ወደፊት በሚቀጥለው ዕትም በሰፊው እንመጣበታለን፡፡ ከወዲሁ ግን ከችግሩ አኳያ አንድ ሁለት ነገሮች ብቻተናግሬ ልለፍ፡፡ በሌላ ጉዳይም ላይ ተደጋግሞ እንደሚታየው ሁልጊዜም በባህላችን መካከለኛ መንገድ ከመምረጥ ይልቅ ነገሮችን ከአንድ ወይም ከሌላ ጥግ ብቻ የማየት ግድፈት አለብን፡፡
ሁለተኛ፣ ገዥው ግንባር በሌሎች ጥያቄዎችም ላይ እንደሚያደርገውችግር ብሎ ለሚያነሳቸው ጉዳዮች በሙሉ አንድ ብቸኛ መፍትሄ እንዳለ አድርጎ የማቅረብ አባዜ አለበት፡፡ እስከሚገባኝ ድረስ ‹‹ከቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ ውጪ የተለየ አቀራረብ ሊኖር አይችልም›› የሚለው ወይም ደግሞ ‹‹አማራጭ የለም››የሚለው አመለካከት ምርጫ የሚያሳጣ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ ነጻነትን በእጅጉየሚጋፋም ነው፡፡ እንዲያውም በሕግ የሰው ልጆችን አስተሳሰብ ከመገደብ የበለጠ ጫና የሚፈጥረውና ነጻነት ገፋፊ የሚሆነው በተወሰነ ጥያቄ ዙሪያ አማራጮችን ዘግቶ ልክ አንድ ብቸኛ መፍትሄ እንዳለ አድርጎ የማቅረብ አካሄድ ነው፡፡ ይኼ ‹‹እኔ ካቀረብኩት የመፍትሄ አማራጭ ውጪ ሌላ መንገድ ሊኖር አይችልም›› የሚለው አካሄድ ዩኒቨርሲቲዎችን አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲከተሉ እያደረጋቸው ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲ የሰው ልጅ በረዥም ታሪኩ ያከማቻቸው የአዕምሮ ውጤቶች ተጠብቀው የሚቀመጡበት፣ ለአዲሱ ትውልድ የሚተላለፉበትና በታሪክ ውስጥ የተነሱ ጥያቄዎች የሚፈተሹበት፣ የሚመለሱበት… ወዘተ ማዕከል ነው እንጂ የፖለቲካ አስተዳደሩ ወሳኝ ናቸው የሚላቸውን ጉዳዮች ብቻ እንግቦ የሚንቀሳቀስ ተቋም አይደለም፡፡ አንድ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ተልዕኮዬ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት መስጠት ብቻ ነው›› የሚል ከሆነ ሕልውናውን እንደዩኒቨርሲቲ ያጣል፡፡ዩኒቨርሲቲ ዕውቀት ፈልገው የሚመጡት ተማሪዎች ማኅበረሰቡ ሊያቀርብላቸው ወይም ሊያስተምራቸው የማይችለውን ትምህርትና ተሞክሮ የሚቀስሙበት አምባም ነው፡፡
ዕንቁ፡-በዘመናችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ወይም የበላይነት የያዘው ትምህርት ፍልስፍና ምንድን ነው?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-ወደ አሁኑ ዘመን የትምህርት ፍልስፍና በምንገባበት ጊዜ ብዙ ጸሐፍት አራት ዋና ዋና ንድፈ-ሃሳቦችን ያቀርባሉ፡፡ የመጀመሪያው መሠረታዊነት ወይም ‘ፐረኒያሊዝም’ የሚባለው አስተሳሰብ ነው፡፡ ይኼን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ምሁራን እንደሚሉት የሰው ልጅ ተፈጥሮ (በየትኛውም ቦታ ቢኖር) ተመሳሳይ ነው፤ ዕውቀት የትም ቦታ አንድ አይነት ነው፡፡ ስለሆነም የሚሰጠው ትምህርትም አንደ አይነት ወይም ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡ የሰው ልጅ ምክንያታዊ እንስሳት ነው፤ ይህ ምክንያታዊነቱ ግን መኮትኮት አለበት፡፡ የአስተማሪው ተቀዳሚ ሥራ ደግሞየሰውን ልጅ ምክንያታዊነት መኮትኮት ነው፡፡ ትምህርት ዘለዓለማዊ የሆነ ዕውነትን የሚያስተምር ነው፤ ለኑሮ የሚያዘጋጀ መሳሪያምነው፤የሰው ልጅ ወሳኝ ወይም መሠረታዊ የሆኑ እንደሥነ-ጽሁፍ፣ ታሪክ፣ ሒሳብ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ፍልስፍና፣ ሥነ-ጥበብ … ወዘተ ትምህርቶችን መማር አለበት፡፡ እንዲሁምተማሪዎች ያለፈውን (ሊቃውንትትተውት ያለፉትን) ዕውቀት መማርና መመርመር አለባቸው፡፡
ሁለተኛው፣ አመለካከት ደግሞ ‘ፕሮግረሲቪዝም’ የሚባለው ነው፡፡ ይኼን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ምሁራን እንደሚገልጹት፣ ትምህርት በየጊዜው እየጎለበተ የሚሄድ ነገር በመሆኑ መምህራን ራሳቸውን በዕውቀትና በማስተማር ዘዴ በየጊዜው ማሻሻል አለባቸው፤ትምህርት ራሱ ሕይወት ነው እንጂ ለሕይወት የሚደረግ ዝግጅት አይደለም፤ማወቅ ማለት መተንተንና የሕይወት ተሞክሯችንን መረዳት ማለት ነው፤ ትምህርት ከተማሪው ፍላጎት ጋር መዛመድ አለበት፤ ተማሪው ሌላ ሰው “ይህን ተማር” ስላለው ሳይሆን የሚፈልገውንና ለእርሱ አስፈላጊ የሆነውን ትምህርት ነው መማር ያለበት፤ዕውቀት ተፈላጊ የሚሆነውአንድ ነገር ልናደርግበት ስንችል ብቻ ነው፤ የመምህሩ ሚና ማማከር እንጂ አቅጣጫ ማስያዝ አይደለም፤ ትምህርት ቤት ውድድር ሳይሆን ትብብርና መደጋገፍ የሚፈጠርበት ቦታ ነው፤ ነጻ የሆነ የሃሳብ ልውውጥ ሊፈጠር የሚችለው በዴሞክራሲ ብቻ ነው፡፡
ሦስተኛው፣ አመለካከት ‘ኢሴንሻሊዝም’ የሚባለው ሲሆን፣ አመለካከቱን የሚያራምዱ ምሁራን እንደሚሉት የሰው ልጅ ተምሯል የሚባለው መሠረታዊ የሆኑ ትምህርቶችን ሲያውቅ ነው፡፡ መማር ከፍተኛ ጥንካሬ የሚጠይቅ ነገር ነው፤ መማር የማንፈልገውን የትምህርት ዓይነት መማርን ጭምር የሚያካትት ሲሆን ለመማር ደግሞ ‘ዲሲፕሊን’ በጣም አስፈላጊ ነው፤ትምህርት የሚሰጠው “ተማሪው ምን ይፈልጋል?” የሚለውን መሠረት አድርጎ ሳይሆን “ለተማሪው ምን ያስፈልገዋል?” የሚለውን ተከትሎ መሆን አለበት፡፡ ተማሪው የሚማረው የማይፈልገውን ትምህርት እንኳን ቢሆን በሂደት እየተማረ ሲሄድ ይወደዋል ብለው ያምናሉ፡፡ የመማር ማስተማሩ ሂደት የሚያርፈው በአስተማሪው ላይ ነው፤ ስለዚህ አስተማሪው ወሳኝ ነው፡፡ ትምህርት ሰዎች የውስጥ አቅማቸውን እንዲያወጡ የሚረዳ መሳሪያ ነው፡፡
አራተኛው፣ አመለካከት ‘ሪኮንስትራክሽኒዝም’ይሰኛል፡፡ ትምህርት አዲስ የኅብረተሰብ ሥርዓት (social order) ለመፍጠር ማገልገል አለበት፤ ትምህርት ማኅበረሰቡን ለመለወጥና ለመሻሻልመዋል አለበት፤ ትምህርት የተሻለ የኑሮ ግብ የምንመታበት መሳሪያ ነው፤… ወዘተ የሚሉትን ሃሳቦች የሚያራምድ አመለካከት ነው፡፡
ዕንቁ፡-ከላይ የተመለከትናቸው የትምህርት ንድፈ-ሃሳቦች ከጥንታዊው እና ከአሁኑ ዘመን የኢትዮጵያ የትምህርት ፍልስፍና ጋር እንዴት ይዛመዳሉ?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-ከሁሉ አስቀድሞ ይኼ ጥያቄ በጣም ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ለጥያቄው መልስ ለመስጠት ሦስት በዚሁ ጉዳይ ላይ የተጻፉ ድርሳናትን መመልከቱ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አንደኛ የዛሬ 45 ዓመት ገደማ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ዳኜ በ“ውይይት” መጽሔት ላይ “የኢትዮጵያ የትምህርት ፍልስፍና” በሚል ርዕስ የጻፉት ጽሑፍ፣ ሁለተኛ፣ የዶ/ር ሀይሉ ፉላስ “Knowledge and Its Attainment in the Ethiopian context” (The Ethiopian Journal of Education June 1974 vol.7 no.1) የሚለው ጽሑፍና ሦስተኛ፣ ዶ/ር ተሾመ ዋጋው የጻፉት “The Development of Higher Education and Social Change an Ethiopian Experience” (1990) የሚለው መጽሐፍ በጣም ጠቃሚ ድርሳናት ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
addis-ababa-police
ፌዴራል ፖሊስ ኬኔዲ ቤተመጻህፍት አካባቢ (ቆየት ካሉ ፎቶዎች)
እነኝህን ሦስቱን ድርሳናት በምናይበት ጊዜ፣ጥንታዊው የኢትዮጵያ የትምህርት ፍልስፍና ከላይ ‘ፐረኒያሊዝም’ ብለን ከጠቀስነው የትምህርት ፍልስፍና ጋር በእጅጉ የተዛመደ መሆኑንእንረዳለን፡፡ የጥንታዊ ኢትዮጵያ የትምህርት ፍልስፍና በመሠረታዊነት በክርስትና ወይም በእስልምና አስተምህሮት ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ ስለ እግዚአብሔር ጠባይ፣ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋራ ስላለው ግንኙነት፣ ስለዓለም አፈጣጠር …. ወዘተ ያለቀለት ወይም ዳግመኛ ምርምር የማይጠይቅና በቅዱሳን መጽሐፍት ላይ ተመርኩዞ የሚጠና ነው፡፡ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ከሃይማኖት አበው ጠቅሰው እንደጻፉት ‹‹ነአምን ዘእንበለ ተኅሥሦ›› (ሳንመረምር ሚስጥራቸውን እንቀበላለን) የሚለው አባባል ይኼንን ነጥብ በሚገባ ያብራራዋል፡፡ ይኼ አንደኛው አስተምህሮት ነው፡፡
ሁለተኛው፣ አስተምህሮት ዓለም በሁለት ነገሮች እንደተከፈለችው ሁሉሰውም በሁለት ነገሮች የተከፈለ ነው የሚለው ነው፡፡ የዓለም አከፋፈል ሰማያዊና ምድራዊ ሲሆን የሰው ልጅ አከፋፈል ደግሞ ነብስና ሥጋ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ሰማያዊ ዓለሙ ምድራዊ ዓለሙን እንደሚመራ ነብስ ደግሞ ሥጋን እንድትመራ ይጠበቃል፡፡ የቀለም ትምህርት ዓላማው ቅዱሳት መጽሐፍትን እያስተማረ ለሚመጣው ዘለዓለማዊ ዓለም ማዘጋጀት ነው፡፡
ሦስተኛ፣ አስተምህሮት ደግሞ ይህች ዓለም አላፊና ጠፊ በመሆኗ ከንቱ ናት፤ ሰማያዊው ዓለም ግን ዘለዓለማዊ ደስታን ይሰጣል የሚለው ነው፡፡ይኼ እንግዲህ ቁሳዊ ብልጽግናንና ዕድገትን አያበረታታም፡፡ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ይኼን አስተሳሰብ በሚመለከትሲጽፉ ‹‹ባህላችን ቀለም ለተማረ ሰው ከእጅ ሠራተኛና ከገበሬ የበለጠ ደረጃ ሰጥቶታል›› ይላሉ፡፡
በኔ እምነት በአክሱም ዘመነ መንግሥት ትልቅ ቦታ የነበራቸው በቴክኒክ፣ በግንባታ/ምህንድስና፣ በልዩ ልዩየእደ-ጥበብ ሥራዎች … ወዘተ የተሰማሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ክርስትናና እስልምና ከሙጡ በኋላ ቀደም ሲል ትልቅ ቦታ ይሰጣቸው የነበሩት ተሽረው ካህናትና ኡለማዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ እንዲይዙ ተደርጓል፡፡ ምናልባት የአገሪቱ የቁሳዊ ሥልጣኔና ብልጽግና ከአክሱም በኋላ ወደታች እየወረደ የመጣው ከዚህ የዕሴት ለውጥ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡
ለማጠቃለል፣ የአገራችንም ሆነ የምዕራቡን ዓለም የ‘ፐረኒያል’ አመለካከት ስንመለከት አንደኛ፣ ሁለቱም ማለትም የኢትዮጵያው ቁዱሳን መጽሐፍትን፣ የምዕራቡ ዓለም ደግሞጥንታዊ የግሪክና የሮማውያን ድርሳናትን አይሻሩም፣ አይለወጡም፣ አይጠየቁም የሚሉ ናቸው፡፡ሁለቱም በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይየአስተማሪው ድርሻ ትልቅ እንደሆነናአካላዊ ቅጣት ዋና የማስተማሪያ መሳሪያ እንደሆነም ይቀበላሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ትምህርት ማለት መንፈሳዊና አዕምሯዊ ብቃትን ማዳበርነው፤ ከሃይማኖትና ከባህል የተረከብነውን እውቀት እናጠናዋለን እንጂ ወደፊት ሌላ የዕውቀት ግኝት እናመጣለን በሚል ተስፋ ምርምር የምናካሄድበት ዘርፍ አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡
አሁን ወዳለንበት የትምህርት ፍልስፍና በምንሄድበት ጊዜ ደግሞ፣ ከ‘ኮንስታረክሽኒዝም’ና ከ‘ፕሮግረሲቪዝም’ አስተሳሰቦች ጋራ የተዛመደ አመለካከት አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ትምህርት በይዘቱ ማኅበራዊ የኑሮ ደረጃን የሚለውጥ መሳሪያ ነው፤ማኅበረሰብን ከመለወጥ ውጪ ሌላ ፋይዳ የለውም፤በተጨማሪም የትምህርት ተቀዳሚ ትኩረት መሆን ያለበት በትምህርቱ ይዘት ላይ ሳይሆን ችግር ፈቺ ነው ወይስ አይደለም በሚለው ጥያቄ ላይ ነው፤ በመሆኑም የሚመረጠው የትምህርት ዓይነት የሚወሰነው የማኅበረሰቡን ችግር ይፈታል ወይስ አይፈታም ከሚል አስተሳሰብ በመነሳት ነው፡፡ ትምህርት ተማሪውን ያማከለና የተማሪውን አጠቃላይ ፍላጎት የሚያሟላ መሆን አለበት፤ የትምህርት ሥርዓቱ በየጊዜው እንዳስፈላጊነቱ መሻሻልና መለወጥ አለበት…ወዘተ የሚሉት አመለካከቶች ከወቅቱ የአገራችን የትምህርት ፍልስፍና ጋር በእጅጉ ይዛመዳሉ፡፡ ወደአገራችንሁኔታ በምንመጣበት ጊዜ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ ትምህርት የልማት አጋር በመሆን መንግሥት ያቀደውን የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ አስፈጻሚ መሆን አለበት የሚል አቋም ተይዟል፡፡
ዕንቁ፡-እስካሁን የተነጋገርንበትን ጉዳይ ማለትም ስለ ትምህርት ፍልስፍና ስለጥንታዊውና አሁን ስላለው የትምህርት ይዞታ በሚቀጥሉት ዕትሞቻችን ላይ በሰፊው እንቀጥላለን፡፡ ለአሁኑ የዛሬ ስድስት ወር ገደማ ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ዩኒቨርሲቲ መጥተው ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ስለደሞዝ ጭማሪ የተናገሩት አስካሁን ድረስ በማነጋገር ላይ ያለ ጉዳይ ስለሆነየእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? የሚለውን ይግለጹልን፡፡
ዶ/ርዳኛቸው፡-ዩኒቨርሲቲ ከሕዝብም ሆነ ከፖለቲካ አመራሩ ክፍል የሚመጣ ሃሳብ የሚፈትሽበት፤ለማኅበረሰቡም ሆነ ለአስተዳደር ክፍሉ ገንቢ አስተያየቶችንና አመለካከቶችን የሚቀርቡበት ተቋም ነው፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ በተገላቢጦሹ ሃሳብና ምክር ይፈልቅበታል በሚባለው ተቋም ሹመኞች በተለያየ ምክንያት እየመጡ አስተማሪዎችን እየሰበሰቡ የሃሳብና የምክር አቅራቢነት ሚና መጫወታቸው በጣም ያስገርማል፡፡ በተለያየ ጊዜ የዩኒቨርሲቲውን መምህራን እየሰበሰቡ ከኃይማኖት እስከ ልማት፣ ከዕድገት እስከ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ … ወዘተ “አሰልጣኞች” ተመድበው “ሥልጠና” ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ይህን ጉዳይ ይበልጥ ለማብራራት በቅርቡ አቶ ብርሃኑ አስረስ ከጻፉት መጽሐፍ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከታህሳሱ ግርግር በኋላ ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ ተይዘው ፍርድቤት በቀረበቡበት ወቅት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲጠየቁ “የተናቀ መንደር ‘በምንትስ’ ይወረራል” ብለው የተረቱት ተረት ሁኔታውን በሚገባ የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ሠልጣኝ የመንግሥት ሹመኞች አሰልጣኝ የሆኑበት ግቢ ሆኗል፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን የደሞዝ አንሶናል ጥያቄውን ሲመልሱ ‹‹እናንተ እውቀትና ክህሎት ያላችሁ በመሆናችሁ ከዩኒቨርሲቲው ውጪ ተንቀሳቅሳችሁ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ትላላችሁ›› ብለው ነበር፡፡ መምህራንን ከተመደቡበት የማስተማር ውጪ ሌላ ተፎካካሪ ሥራ “ሥሩ” ብለው መምከራቸውና በመማር ማስተማርሂደቱ ላይ ጫና እንደሚፈጥር አለመገንዘባቸው አስገሞኛል፡፡ መቼም ይኼ “ምክር” ለአብዛኞቹ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች አዲስ ነገር ሆኖ እንደማይገኝ ጥርጥርየለኝም፡፡ እኔ እስከምረዳው ድረስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን “ከማስተማር ውጪ በኮንሰልታንሲም ሆነ በልዩ ልዩ መንገድ ገንዘብ ይገኛል” ብሎ መንገር ለነብር “ሚዳቋ ወይም ጥንቸል ትበላላች” ብሎ እንደመምከር ይሆናል፡፡
ደሞዝን በሚመለከት ከመምህራኑ ይበልጥ በጣም እየተጎዱ ያሉት የጥበቃ፣ የጽዳት፣ የካፍቴሪያና የአትክልተኛነት ሥራዎችን የሚሰሩት ሠራተኞች ናቸው፡፡ እነኚህ ሠራተኞች የሚሰሩት ሥራ ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቅ ሆነ ሳለ የሚከፈላቸው ደሞዝ ግን እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ ሰባት እና ስምንት ዓመታት ያህል ያገለገሉ ሠራተኞች ደሞዝ ይጨመርልናል ብለው ሲጠብቁ “ቋሚ አድርገናችኋል” በሚል ፈሊጥ የደሞዝ ቅነሳ ተደርጎባቸዋል፡፡ ይኼ በእጅጉ የሚያሳዝንና ፍትሃዊነት የጎደለው እርምጃ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በበኩሌ ዩኒቨርሲቲው አንጋፋና ትልቅ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ስሙንና ክብሩን በጠበቀ መልኩ ለእነኝህ ሰዎች ደህንነት አስቦ የደሞዝ ማስተካከያ ማድረግ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደጽዳት ሠራተኞች በምንሄድበት ጊዜ ደግሞ ያለው ችግር ተገቢ ደሞዝ ያለማግኘት ብቻ ሳይሆን ከጤንነትምጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በቅርቡ ሰፋ ያለ ጽሁፍ ስለማቀርብ ለጊዜው በዚሁ ይብቃን፡፡(ምንጭ: ዕንቁ መጽሄት)

Tuesday, February 4, 2014

ከሳኡዲ የተለመሱ ተቃዉሞ ሊኦያሰሙ ሲሉ በፖሊስ ተበተኑ !



በሳዉዲ መንግስት በግፍና ጭካኔ ተባረው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉ ኢትዮጵያዊያን በአዲስ አበባ፣ በዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ፣ «መንግስት ትኩረት አልሰጠንም» በሚል ድምጻቸውን ለማሰማት የተሰባሰቡ ወደ 400 መቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያዉያን በፖሊሲ እንዲበተኑ መደረጉን የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነው የፍኖት ጋዜጣ ዘገበ።

«ቦሌ አካባቢ ከሚገኘው ጊዜያዊ ማረፊያቸው፣ ከ400 በላይ ሆነው ቅሬታቸውን ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለማሰማት ያቀዱትን ቅሬታ አቅራቢዎች ፖሊስ በትኗቸዋል፡፡ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መሀከል ከ20 የማይበልጡት ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አቅራቢያ ቢሰባሰቡም ፖሊሶች አከባቢውን ለቀው እንዲሄዱ እያስገዷቸው መሆኑን በስፍራው ያለው የፍኖተ ነፃነት ሪፖርተር ዘግቧል» ሲል ነበር ፍኖት የዘገበዉ።
የሳዉዲ ስደተኞች ወደ አገራቸው ተመልሰው በነበረ ጊዜ፣ ባለስልጣናቱ ከነርሱ ጋር ፎቶ በመነሳት፣ ለስደተኞች የሚያስፈልገው እንክብካቤ እንደሚደረግ ሲገጽሉ እንደነበረ ይታወቃል። ኢቲቪ ስደተኞችን በአይሮፕላን ማረፊያ ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ ብነስደተንጮ የተሰጡ የምስጋና መልእክቶችን በማስተላለፍ፣ የስደተኞችን ጉዳይ ለፖለቲካ መጠቀሚያ አድርጎት እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነዉ።

‹‹ከአገር እንድወጣ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል›› አቶ አስመላሽ ሀዲሽ ወልዱ

ዋና ዜና
‹‹ከአገር እንድወጣ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል››  አቶ አስመላሽ ሀዲሽ ወልዱ
የዛሬው ‹‹ምን እየሠሩ ነው?›› ዓምድ እንግዳችን አቶ አስመላሽ ሀዲሽ ወልዱ ይባላሉ፡፡ ተወልደው ያደጉት በትግራይ ክልል አጋሜ አውራጃ አዲግራት ከተማ ውስጥ ነው፡፡
ትምህርታቸውን እስከ ዘጠነኛ ክፍል በተወለዱበት አዲግራት ከተማ ተከታትለው፣ ወደ አሰብ ራስ ገዝ በመጓዝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ የደርግ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ በ1983 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ከተማ መምጣታቸውን የሚናገሩት አቶ አስመላሽ በንግድ ሥራ ተሰማርተው ስኬታማ ሥራ እየሠሩ የነበሩ ቢሆንም፣ ባልታሰበ ድንገተኛ ገጠመኝ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ስለገጠማቸው አስቸጋሪ የሕይወት ፈተናና አሁን ስላሉበት ሁኔታ ታምሩ ጽጌአነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ አዲስ አበባ የመጡት መቼ ነው?
አቶ አስመላሽ፡- በ1983 ዓ.ም. ነው የመጣሁት፡፡ 
ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ የተሰማሩበት የሥራ መስክ ምን ነበር?
አቶ አስመላሽ፡- አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ የአስመጭና ላኪነት ፈቃድ በማውጣት በንግድ ሥራ ተሰማራሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት የንግድ ሥራዎችን ነበር የሚያስመጡትና የሚልኩት?
አቶ አስመላሽ፡- የማስመጣው ጨርቃ ጨርቆችንና የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን ነበር፡፡ ይኸንን የንግድ ሥራ ስሠራ በመንግሥት በኩል የሚጠበቅብኝን ግብርም ሆነ ሌሎች የንግድ ሥራው የሚጠይቀውን ግዴታዎች እየተወጣሁ ነበር፡፡ 
ሪፖርተር፡- በዚህ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት እስከመቼ ነበር?
አቶ አስመላሽ፡- ከ1984 ዓ.ም. እስከ 1991 ዓ.ም. ድረስ ሠርቻለሁ፡፡ ከ1991 ዓ.ም. በኋላ ወደሌላ ሥራ ተዘዋወርኩ፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ሥራ ለወጡ?
አቶ አስመላሽ፡- ሥራ የመለወጥ ሳይሆን ፣ ያው የንግድ ሥራ ሆኖ ሙሉ በሙሉ በላኪነት ብቻ መሥራት ጀመርኩ፡፡ በኢትዮጵያ የሚመረቱ ሸቀጣ ሸቀጦችን ብቻ መላክ ጀመርኩ፡፡ የግብርና ውጤቶችንና ማዕድን መላክ ጀመርኩኝ፡፡ 
ሪፖርተር፡- የግብርና ውጤቶችን ሲሉ ምን ዓይነት የሰብል ምርቶችንና ማዕድን መላክ የጀመሩ?
አቶ አስመላሽ፡- ከማዕድን እጣን፣ ከጥራጥሬ ዘሮች ሁሉንም ዓይነትና እንጨት እልክ ነበር፡፡ 
ሪፖርተር፡- እንጨት እንዴት ነው የሚልኩት?
አቶ አስመላሽ፡- የባሕር ዛፍ እንጨት ነው የምንልከው፡፡ በአንድ አካባቢ ለልማት ተብሎ የሚቆረጥን ባሕር ዛፍ ወይም አልምቶ ከሚሸጥ እገዛና፣ ወደ ውጭ እልካለሁ፡፡ 
ሪፖርተር፡- እንጨቱ በምን ዓይነት ሁኔታ ተዘጋጅቶ ነው የሚላከው? የትኞቹስ አገሮች ናቸው የሚገዙት?
አቶ አስመላሽ፡- ዋና ገዢ አገር የመን ነች፡፡ እንጨቱን አድርቀን በቁመቱ ሳይቆራረጥ አዘጋጅተን እንልከዋለን፡፡ እነሱም የሚጠቀሙበት በአብዛኛው ለወይን እርሻ ነው፡፡ ማለትም፤ የወይን ተክላቸው በመሬት ላይ ሲተኛ በተለያዩ ነገሮች ይበላሽባቸዋል፡፡ ይኸንን ለመከላከል ከእኛ በሚገዙት እንጨት እንደ ዳስ በመጠቀም ከብዙ ነገር ይከላከሉበታል፡፡ ከእጣንና እንጨት በተጨማሪ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የዱባ ፍሬ ወደ ውጭ አገር መላክ የጀመርኩት እኔ ነኝ፡፡ የዱባ ፍሬ ለዘመናት የሚጣል እንጂ ወደ ውጭ አገር ተልኮ የውጭ ምንዛሪ የሚያመጣ አልነበረም፡፡
ሪፖርተር፡- የዱባ ፍሬ የሚልኩት የት ነበር?
አቶ አስመላሽ፡- ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ዮርዳኖስ፣ የመንና ሌሎች የዓረብ አገሮች ነበር፡፡ ይኸንን ሥራዬን በወቅቱ አብሬያቸው (በመበደርና በማበደር) የምሠራው፣ አዋሽ፣ ወጋገን፣ ንብ እና ዳሽን ባንኮች ያውቃሉ፡፡ 
ሪፖርተር፡- ንግድ ሲጀምሩ መነሻ ካፒታልዎ ስንት ነበር?
አቶ አስመላሽ፡- በወቅቱ የነበረው የገንዘብ ዋጋ ከፍተኛ ስለነበር እንጂ መነሻ ካፒታሌ የተጋነነ አልነበረም፡፡ በ100 ሺሕ ብር ካፒታል ነው ወደ ንግዱ ዓለም የተቀላቀልኩት፡፡ ከትንሽ ነው የተነሳሁት፡፡ ከውጭ አልባሳትና የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን በማስመጣት ጀምሬ፣ እያደግኩኝ ስመጣ ወደ ላኪነት ሥራ አደግኩኝ፡፡ በላኪነት ንግድ ለመሰማራት በዋናነት ያነሳሳኝ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የአገሬን ምርት ለውጭው ዓለም በመላኬ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት በተጨማሪ፣ አገርንና ምርቷን ማስተዋወቅ ነው፡፡ ሁለተኛ እኔም ተጠቅሜ የአገሬን አርሶ አደር ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ አበዳሪዎቼ ባንኮችም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በተለይ ወጋገን ባንክና ንብ ባንክ ዋና አበዳሪዎቼ ስለነበሩ፣ ሥራውን አብረን እየሠራን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ ባንኮቹ ብድር ሲሰጡኝ ለምበደረው የገንዘብ መጠን ኮላተራል ይዘው ቢሆንም፤ በቀናነትና በተባባሪነት መንፈስ ተግባብተን ስንሠራ ቆይተናል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ከጥራጥሬ እህሎች በዋናነት የምትልኳቸው የትኞቹን ዓይነት ነው? የምትልኩላቸው አገሮች የትኞቹ ናቸው?
አቶ አስመላሽ፡- የምልከው አውሮፓ፣ ዓረብ አገሮች በሙሉ፣ ወደ አፍሪካና አሜሪካ ነው፡፡ ጥራጥሬዎች፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞችን ነበር የምልከው፡፡ 
ሪፖርተር፡- በላኪነት የንግድ ሥራ ላይ ምን ያህል ጊዜ ሠርተዋል?
አቶ አስመላሽ፡- ለስድስት ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ እኔ ወደ ላኪነት ሥራ ስገባ ዝም ብዬ በድፍረት አልገባሁም፡፡ የላኪነት ሥራ እንዴት እንደሚሠራ፣ ውጤታማ ለመሆን ምን መደረግ አለበት? ከነማንና በምን ሁኔታ ይሠራል? እኔ ለራሴና ለሀገሬ ማድረግ ያለብኝ ምንድን ነው? የሚለውን ጭምር ለማወቅ በአገሬና በውጭ አገር ሥልጠና ወስጄ ነው ወደ ዘርፉ የተቀላቀልኩት፤ ከሥልጠና በኋላም፣ የላኪነት ሥራ ላይ ከተሰማሩ ነጋዴዎች ጋር በመሆን ሥራውን ተለማምጄ ነው በራሴ መሥራት የጀመርኩት፡፡ በአሁኑ ጊዜ በጣም ብዙ በላኪነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ የንግድ ዘርፍ ጥሩ የውጭ ምንዛሪ እያገናኘ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን እኔ በዚህ የሥራ ዘርፍ በተሰማራሁበት ጊዜ በላኪነት የንግድ ዘርፍ ተሰማርተው የነበሩት በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ 
ሪፖርተር፡- የግብርና ውጤቶችን ወደ ውጭ የምትልኩት በምን ዓይነት ሁኔታ ነበር?
አቶ አስመላሽ፡- እኔ መላክ የጀመርኩት መጀመርያ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አማኑኤል አካባቢ የማበጠሪያና ማሸጊያ ማሽን በማዘጋጀት ሁሉንም የምልካቸውን ምርቶች በልዩ ሁኔታ በማሸግና የሚፈለገውን የአላላክ ሁኔታ በማሟላት ነበር፡፡ የሚላከው ዝም ብሎ አበጥሮና አሽጐ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀና በአገራችንም የደረጃዎች መዳቢ ባለሥልጣን ባስቀመጣቸው መስፈርቶች አማካይነት ነው፡፡ በመሆኑም ያንን ሁሉ ነገር አሟልቼ ነበር የምልከው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው የኤክስፖርት ንግድ አሠራር መመሪያ መሠረት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር (በወቅቱ) በሰጠው ፈቃድ መሠረትና ኢትዮጵያ የንግድ ሕግን በሚመለከት ያስቀመጠችውን ሕጋዊ አካሄድ ሁሉ በማሟላት እሠራ ነበር፡፡ በመንግሥት ደረጃ ጥሩ ተቀባይነትም ነበረኝ፡፡ የመላክ ሥራ በአዲስ አበባ አማኑኤል አካባቢ በደቂቃ አንድ ኩንታል የሚያዘጋጅ ሁለት ማበጠሪያና ማሸጊያ ማሽን በመታገዝ ጀምሬ፣ ሥራው እየተስፋፋና የውጭ አገር ደንበኞች እየበዙ ሲሄዱ ቡራዩ፣ ናዝሬት፣ ጐንደርና ሁመራ ላይ በድምሩ ዘጠኝ የማበጠሪያና ማሸጊያ ማሽኖችን በመትከል ሥራውን በሰፊው መሥራት ጀመርኩ፡፡ የማበጠሪያና ማሸጊያ ማሽኖችን በተለያዩ ቦታዎች ለመትከል ያስገደደኝ፣ ምርቱን የሚያቀርቡ ነጋዴዎችና አርሶ አደሮች ባሉበት አካባቢ በቀላሉ መገበያየት እንድንችል ነው፡፡ ሌላው በየአካባቢው የሚሰበሰቡ ምርቶች ባሉበት አካባቢ ተዘጋጅተው በዚያው ለመላክ አመች በመሆኑና የትራንስፖርት ወጪን ለሁላችንም ለመቀነስም ጭምር ነው፡፡ ሥራው በየክልሉ እየተስፋፋ ሲሄድ ዜጐችም ሥራ የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ ብዙም ሠራተኞች ነበሩኝ፡፡    
ሪፖርተር፡- የድርጅትዎ ስያሜ ምንድነው?
አቶ አስመላሽ፡- አንደኛው ኤቨር ግሪን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፡፡ ሁለተኛው ሥረዋት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ሦስተኛው ድርጅቴ ኦል ግሪን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የሚባሉ ሲሆኑ የላኪነት ሥራው ይሠራ የነበረው በእነዚህ ድርጅቶች ነበር፡፡ የላኪነት ሥራው ጥሩ እየሆነ በመሄዱ ተጨማሪ የላኪነት ሥራውን የሚያግዙ ሌሎች ኩባንያዎችን እንዳቋቁም ሥራው እራሱ አስገደደኝ፡፡ በመሆኑም በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ አካባቢ የእርሻ መሬት በመውሰድ ከባልደረቦቼ ጋር በመሆን ኦል ግሪን አግሮ ኢንዱስትሪ የሚባል ድርጅት አቋቋምን፡፡ ከአርሶ አደሮች ከምንገዛው የሚላኩ ምርቶች በተጨማሪ ራሳችንም አምርተን ለመላክ በማሰብ ነው ወደ እርሻው ኢንቨስትመንት የገባነው፡፡ ቃሊቲ አካባቢም የምግብ ማደራጃ አቋቋምኩ፡፡ ይኸንን ደግሞ ለማቋቋም ያስገደደኝ ነገር፣ ወደ ውጭ አገር የምንልካቸው የግብርና ውጤቶች በውጭ አገር ወደ ሌላ የምግብ ዓይነት ተቀይረው ወደ አገራችን ሲገቡ በማየቴ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ለምን እዚሁ አገራችን ላይ አናመርታቸውም?›› በማለት የምግብ ማደራጃ ፋብሪካ ለማቋቋም ወሰንኩ፡፡ በውጭ ምንዛሪ የላክናቸውን ሸቀጣ ሸቀጦች ዓይነትና መልካቸውን ቀይረው ሲላኩልን፣ በውጭ ምንዛሪ መግዛታችን ያለማወቅ ስለነበር፣ ያንን በማጥናት አስፈላጊነቱ ጐልቶ ስለታየን ፋብሪካ ለማቋቋም ችዬ ነበር፡፡ በሥራ አማካይነት ከማውቃቸው አንድ የየመን ዜጋ ጋር በመሆን በሽርክና የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመሥራት ተስማምተን በአማራ ክልል ደጀን ከተማ አካባቢ ቦታ ወስደን ነበር፡፡ ቦታውን ከተረከብን በኋላ፣ የማምረቻ ማሽን ለማስገባት አዘዝን፡፡ ይኸንን ሁሉ የምናደርገው ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ተገቢውን ሕጋዊ ፈቃድ በመውሰድ ነው፡፡ ለአገር መጠቀሚያና ወደ ውጭ ለመላክ ከፍተኛ ዕቅድ ይዘን ነበር የተነሳነው፡፡ የውጭ ብድር ከአውሮፓ አግኝቼ የማሽኑን መግቢያ ቀን እየተጠባበቅሁ ነበር፡፡ የሁሉም ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስኪያጅ እኔ ብሆንም፣ ለቅርንጫፍ ድርጅቶቼ ግን፣ የማምናቸውና ሙሉ በሙሉ ኩባንያዎቹን በኃላፊነት ተቆጣጥረው ይሠራሉ ያልኳቸው በተለይ ሁለት ምክትል ሥራ አስኪያጆች ነበሩኝ፡፡ በወቅቱም ጥሩ ሠራተኞቼ ነበሩ፡፡ ታማኞችና ለአገር ለወገን ተቆርቋሪ፣ ዕድገት ፈላጊና ብሩህ ተስፋ የነበራቸው መልካም ዜጐች ነበሩ፡፡ ጥሩ ደመወዝተኞችና ከሥራቸው ያሉ ሠራተኞችን በጥሩ ሁኔታ እየተቀጣጠሩ ይሠሩ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ መጀመሪያ የላኪነትም ሆነ ሌሎች የንግድ ድርጅቶቼን የመሠረትኩት ከእህቶቼ ጋር እንደነበር ለመጥቀስ እወዳለሁ፡፡ ሌሎች ሸሪኮች የመጡት በኋላ ላይ ነው፡፡    
ሪፖርተር፡- ምን ያህል ሠራተኞች ነበሩዎት? በቋሚነትና በጊዜያዊነት የሚሠሩ?
አቶ አስመላሽ፡- በወቅቱ ቋሚ ሆነው የሚሠሩት ከ50 በላይ ሠራተኞች ነበሩ፤ በጊዜያዊ ወይም በቀን ሠራተኛነት እስከ አሥር ሺሕ ይደርሱ ነበር፡፡ 
ሪፖርተር፡- የጊዜያዊ ሠራተኞቹ ቁጥር አልተጋነነም?
አቶ አስመላሽ፡- አልተጋነነም፡፡ ቦሎቄ፣ ጥቁር አዝሙድ ጤፍና፣ ሌሎቹም የእህል ዘሮች በማሽን ከተበጠሩ በኋላ፣ አንዳንድ ከማሽኑ የሚያልፉ አሉ፡፡ እነዚህ ከማሽንና ከወንፊት ያለፉት የሚለቀሙት በእጅ ነው፡፡ በተለይ ቦሎቄ በእጅ የተለቀመ ቢሆን በገዥም ስለሚፈለግ፣ የሚሠራው በሰው ኃይል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የቀን ሠራተኛ ቁጥር ተጋኖ ሳይሆን የሥራው ባሕሪ የፈጠረው ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- ከውጭ ነጋዴዎች ጋር የምትገናኙት ወይም ገበያ የምታፈላልጉት እንዴት ነው?
አቶ አስመላሽ፡- አገር ውስጥ ያለውን ሥራ የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ በጥሩ ደመወዝ የቀጠርኳቸው ምክትል ሥራ አስኪያጆች አሉ፡፡ እነሱ ልክ እንደኔ ሆነው ይሠራሉ፡፡ በተለይ ሰብሎች በሚሰበስቡበት ወቅት እኔ አለሁ፡፡ ግዢ ካጠናቀቅን በኋላ፣ ምክትሎቼ የማስበጠርና የማሳሸግ ቁጥጥር ሥራውን እንዲሠሩ መመሪያ ሰጥቼ ወደ ውጭ እሄዳለሁ፡፡ ምርቶቹን በምልክባቸው አገሮችም ወኪሎች አሉኝ፡፡ እነሱ ገዥዎችን አመቻችተው ይጠብቁኛል፡፡ ካለወኪልም በቀጥታ ግዥ የሚፈጽሙ ደንበኞች አሉን፡፡ በአጠቃላይ የእኔ ምክትል የሆኑ ሦስት ሰዎች በኃላፊነት እየሠሩ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የቁም ከብትና ሥጋም እንልክ ነበር፡፡ 
ሪፖርተር፡- በአማራ ክልል ደጀን ከተማ አካባቢ ሲሚንቶ ፋብሪካ ለመትከል ፈቃድ ወስዳችሁና መሬት ተረክባችሁ ማሽን አዛችሁ እንደነበር ገልጸውልኛል፡፡ ፋብሪካውም አልተተከለም፤ ማሽኑም አልመጣም፡፡ ለምን?
አቶ አስመላሽ፡- ማሽንና ፋብሪካ ብቻ አይደለም ተግባራዊ ሳይሆን የቀረው፣ ሌሎችም ብዙ ጅምሮች ነበሩ፡፡ ሆለታ ላይ የአበባ እርሻ ከአንድ የመናዊና ጣሊያናዊ ጋር መሬት ወስደን በጅምር የቀረ አለ፡፡ ሞጆ ላይ ደግሞ የማድለቢያና የቄራ መሬት ወስደን ሥራው በጅምር ቀርቷል፡፡ ሌሎችም ብዙ ዕቅዶችና ጥናቶች ነበሩኝ፡፡ 
ሪፖርተር፡- ተግባራዊ ያልሆነበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ አስመላሽ፡- ምክንያቱ እኔ በ1997 ዓ.ም. ለሥራ ወደ የመን ሄጀ ነበር፡፡ ነገር ግን የመን ውስጥ ከአንድ የንግድ ድርጅት ጋር ስለሥራ ሁኔታ ተነጋግሬ ተፈራርሜ ከምሽቱ 4 ሰዓት ስወጣ በታጣቂዎች ታፈንኩኝ፡፡ ሰነዐ ከተማ ላይ፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ታዋቂ ነጋዴና በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩ መሆኑን ነግረውኛል፡፡ በቀን መፈራረም ሲቻል በምሽት መፈራረሙ ለምን አስፈለገ?
አቶ አስመላሽ፡- ዓረብ አገሮች በተለምዶ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ይሠራሉ፡፡ ዋና የድርጅት ኃላፊዎች የሚገኙት ከሰዓት በኋላና ግማሽ ሌሊት ድረስ ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- እነማን እንዳፈንዎትና ወዴት እንደወሰድዎት ታውቋል? ያደረሱብዎት ጉዳትስ?
አቶ አስመላሽ፡-  አፍነው ወዴት እንደወሰዱኝ አላወቅኩኝም፡፡ እነሱ ጋ ከሁለት ወራት በላይ አቆይተውኛል፡፡ በወቅቱ የጠየቁኝ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ያገኙት ነገር የለም፡፡
ሪፖርተር፡- ወራቱን የቆዩት በእስር ቤት ነው ወይስ በግለሰብ ቤት ውስጥ?
አቶ አስመላሽ፡- በግለሰብ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ዶላር እንድሰጣቸው ደጋግመው ጠየቁኝ፣ ወደ ቤተሰብና የመን አገር ደንበኞች ጋ ቢደውሉም ቢያስደውሉም ግን ምንም ያገኙት ነገር አልነበረም፡፡ መታፈኔንና በማላውቀው ቦታ መታሰሬን እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅነት ለቀጠርኩትና በወቅቱ ፍፁም ታማኝ ለነበረው ግለሰብ (ለጊዜው ስሙን መጥቀስ አልፈልግም) አሳውቄዋለሁ፡፡ አፋኞቼም የሚፈልጉት ዶላር መሆኑን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያውቅልኝና በኢትዮጵያ የየመን ኤምባሲ በኩል ክትትል እንዲያደርጉልኝ እንዲነግርልኝም ነግሬው ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ግለሰቡ ‹‹አይለቀቅም አብቅቶለታል›› ብሎ አስቦ ይሁን ወይም በወቅቱ ምን እንዳሰበ ባላውቅም፣ ለኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ለሚመለከታቸው ወገኖች አላሳወቀልኝም፡፡ በመሆኑም ማንም ያስታወሰኝ የለም፡፡ ከተወሰነ በኋላ ‹‹አመሲያንሴ›› የሚሉት የፖለቲከኞች እስር ቤት አስረከቡኝ፡፡ ‹‹ይኸ ማንነቱ ያልታወቀ እስረኛ ነው›› በማለት አስረከቡኝ፡፡ አፋኞቼ ከዛቻና ማስፈራራት ያለፈ ምንም ዓይነት ድብደባም ሆነ መንገላታት አላደረሱብኝም፡፡ እንዲያውም ያበሉኝ ያጠጡኝ ነበር፡፡ ፖለቲከኞች እስር ቤት ግን ‹‹ማነህ? እንዴት ልትገባ ቻልክ? ከየት ነህ›› በማለት ድብደባ ደርሶብኛል፡፡ አንድ ወር አካባቢ እንደቆየሁ ‹‹በእኛ በኩል አጣርተናል፣ አንፈልግህም፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ በማጭበርበር ወንጀል እንደምትፈለግ ተገልፆልናል፡፡ እንድንመረምርህና እንድናጣራ ነግረውናል በማለት የአካል መጉደል እስከሚደርስብኝ ማለትም በመታፈኔ እንደልብ እንዳልተነፍስ የሚያደርግ ሕመምተኛ ሆኛለሁ፡፡ ከፖለቲከኞች እስር ቤት ሰነዐ ወደሚገኘው ወህኒ ቤት ‹‹ኢንተርፓል ነን›› በሚሉ ፖሊሶች ተወሰድኩ፡፡ በተደጋጋሚ ‹‹ወደ አገርህ ብንልክህ የፖለቲካ ችግር ይገጥምሀል?›› በማለት ስጠየቅ፣ ምንም ችግር እንደሌለብኝ በመግለጽ እንዲልኩኝ ተማፀንኳቸው፡፡ ሰላማዊ፣ ነጋዴና አገሬን ጠቅሜ እራሴን የምጠቅም ሰው መሆኔን ስነግራቸው፤ ‹‹በምን እንደተፈለክ እስከምናጣራ ምግብና ሕክምና ባለበት ወህኒ ቤት መቆየት አለብህ›› አሉኝ፡፡ ሁለት ወር ወህኒ ቤት ከቆየሁ በኋላ ‹‹ኢመነልጐ›› ወደሚባል እስር ቤት ወስደውኝ ከምድር በታች (Underground) አስገብተውኝ ለሁለት ሳምንታት ገረፉኝ፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላ ‹‹ምርመራውን ጨርሰናል ተፈላጊ ሰው ነህ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አጭበርብረሀል፡፡ የባንኮች ብር ዘርፈህ የመጣህ መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ አሁን ልናስረክብህ ነው›› አሉኝ፡፡ በቃል፡፡ ሊያስረክቡኝ ነው ብዬ ደስ ሲለኝ ዘገዩብኝ፡፡ ለምን እንደዘገዩ ስጠይቃቸው ‹‹የአገርህ ፖሊስ ሲመጣ ነው የምናስረክብህ›› አሉኝ፡፡ ሳያስረክቡኝ ባጠቃላይ ሰባት ዓመታት ከአራት ወር እዚያው ታስሬ ከረምኩኝ፡፡ ከሰባት ዓመታት በኋላ በድንገት ከምሽቱ አራት ሰዓት ‹‹ትፈለጋለህ›› ተብዬ በፖሊስ ታጅቤ ወደ የመን ሰነዓ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወሰዱኝ፡፡ ከኢትዮጵያ ለመጡ ሁለት ፖሊሶች ሲያስረክቡኝ የነበረኝ ደስታ ወሰን አልነበረውም፡፡ አመሰገንኳቸው፡፡ የአገሬን መንግሥትም አመሰገንኩ፡፡ አለመረሳቴም ገረመኝ፡፡ ሐምሌ 2 ቀን 2005 ዓ.ም. አገሬ ገባሁ፡፡   
ሪፖርተር፡- ከየመን ያመጡዎትን ፖሊሶች ለምን ይኸንን ያህል ዓመታት እንዳቆዩዎት አልጠየቋቸውም?
አቶ አስመላሽ፡- ‹‹ይኸ የእኛ ችግር አይደለም፡፡ የየመን ችግር ነው፡፡ እነሱ ካላስረከቡን እኛ ማምጣት አንችልም፡፡ አሁንም የመጣነው ለማስረከብ ፈቃደኛ ስለሆኑ ነው›› አሉኝ፡፡ 
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ሲገቡ ምን ገጠመዎት?
አቶ አስመላሽ፡- ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ስደርስ መጀመሪያ በቴሌቪዥን ተቀረጽኩኝ፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ፕሮግራም አዘጋጆች እየቀረጹኝ ‹‹የምትናገረው ካለ›› ብለው ጠየቁኝ፡፡ ‹‹ለምንድነው የምትቀርጹኝ›› በማለት እንዳይቀርጹኝ ጠይቄ ነበር፡፡ ግን የሰማኝ አልነበረም፡፡ ‹‹የምንቀርጽህ ለዶክመንት ነው›› አሉኝ፡፡ እኔ ወንጀለኛ ልባል የሚገባኝ በፖሊስ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጐብኝ፣ በዓቃቤ ሕግ ክስ ከተመሠረተብኝና ፍርድ ቤት ወንጀለኛ መሆኔን ሲያረጋግጥ ብቻ ቢሆንም፣ የፖሊስ ፕሮግራም አዘጋጆች ወይም የሚመለከተው አካል ሐምሌ 2 ቀን 2005 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከገባሁበትና ከቀረፁኝ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ሙሉ ቀን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በየሰዓቱ ‹‹ለሰባት ዓመታት ስንከታተለው የነበረው፣ ከወጋገን ባንክና ከንብ ባንክ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተበድሮ ተሰውሮ የነበረውን ግለሰብ ከተወሰረበት ቦታ በቁጥጥር ሥር ውሎ በኢንተርፖል አማካይነት ወደ አገር ውስጥ ተይዞ ገባ›› የሚል ዘገባ ተላለፈ፡፡ የሚያሳዝነውና የሚገርመው ነገር እኔ ሰባት ዓመታት የት እንደቆየሁ ያውቃሉ፡፡ ሌላው አስገራሚና እንኳን የንግድ ወይም የባንክ ዕውቀት ላለው ቀርቶ ለሌለው ሰው ግልጽ የሆነ ነገር ቢኖር ባስተላለፉት ዜና ላይ ‹‹ከወጋገን ባንክና ንብ ባንክ ከፍተኛ ብር ተበድሮ የተሰወረው›› ማለታቸው ነው፡፡ ‹‹ለመሆኑ ባንኮቹ ብድር የሚሰጡት በእምነት ነው እንዴ? በእምነት የሚሰጥ ቢሆን አይደለም ነጋዴ ሌላው ዜጋ አይበደርም?›› ሁሉም ወገን፣ መንግሥትም፣ ዜጐችም፣ ተቋማትም ሆኑ ሌሎች አካላት ልብ ሊሉት የሚገባው ነገር፣ አንድን ዜጋ ወይም ተቋም ለማጥቃት ሲፈለግ የሚኬድበት አካሄድ ምን ያህል የተዛባና ግምት ውስጥ የሚከት መሆኑን ኢትዮጵያውያን ከእኔ ሊማሩ ይገባል፡፡ እኔ በበኩሌ፣ ስንቱ እንደኔ ያልሆነ ስም እየተሰጠው ሰለባ ሆኖ ይሆን? መልሱን ለመንግሥትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትቼዋለሁ፡፡ እኔ ምንም የፈጸምኩት ወንጀል ባለመኖሩ ሰው ብቻ ሳይሆን ፈጣሪም ያውቀዋል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በፌዴራል ፖሊስ ታስረው ነበር፡፡ እዚህ የደረሰብዎ ችግር አለ?
አቶ አስመላሽ፡- አገሬ ውስጥ ምንም የደረሰብኝ ችግር የለም፡፡ የሚፈልጉትን ምርመራ በስፋት አካሄዱ፡፡ ምርመራው ከዓቃቤ ሕግ ጋር በጋራ ነበር የተደረገው፡፡ ሐምሌ 29 ቀን 2005 ዓ.ም. ምርመራውን ያደረገው ዓቃቤ ሕግ፤ ምንም የሚያስጠይቀኝ የወንጀል ድርጊት እንደሌለብኝ በመጥቀስና ነፃ መሆኔን በመግለጽ ከእስር እንድፈታ በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል ተነገረኝ፡፡ ነገር ግን ‹‹ነፃ ነህ›› ብባልም ፖሊስ ሊለቀኝ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ 
ሪፖርተር፡- ለምን?
አቶ አስመላሽ፡- ‹‹መርማሪ ፖሊስ፣ ‹‹እኛ ገና ምርመራ ሳንጨርስ ዓቃቤ ሕግ እንዴት ይዘጋዋል?›› በማለት ‹‹አልፈታም›› በማለት ‹‹ምርመራ እንቀጥላለን›› ብሎ ቀጠለ፡፡ ፍርድ ቤት አቀረቡኝና ተጨማሪ ጊዜ ጠየቁብኝ፡፡ እኔ ደግሞ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ በጋራ መርምረውኝ ዓቃቤ ሕግ ክስ የሚያስመሠርት ምንም ዓይነት ወንጀል ያልተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ የምርመራ መዝገቡን መዝጋቱን አስረዳሁ፡፡ ፍርድ ቤቱ በሁለት ሚሊዮን ብርና ከአገር እንዳልወጣ ዕግድ ጥሎ እንድፈታ አዘዘ፡፡ ነገር ግን የዋስትና ማስያዢያው ገንዘብ ከአቅሜ በላይ ስለነበረ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አልኩኝ፡፡ ፍርድ ቤቱ ጥቅምት 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ሥራ ሲጀምር የይግባኙን መዝገብ ተመልክቶ በነፃ እንድሰናበት ውሳኔ በማስተላለፉ፤ የፍትሕ ሚኒስቴር ዓቃቤ ሕግ ‹‹ግለሰቡ ወንጀል አልፈጸመም፣ ነፃ ነው ይለቀቅ›› ባለ በ37ኛ ቀኔ ከእስር ተፈታሁ፡፡ እዚህ ጋ ልብ ሊሉ የሚገባው ‹‹የበላይ አካል ማነው? የሚለውን ነው ‹‹ዓቃቤ ሕግ ወይስ ፖሊስ? በእኔ ጉዳይ የበላይ የነበረው ፖሊስ ነበር፡፡ እንዳጠቃላይ ግን መንግሥትንና ፍርድ ቤቶችን እንዲሁም ፍትሕ ሚኒስቴርን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ምክንያቱም ንፁህ በሆነ መንገድ ጉዳዩን መርምረውና አጣርተው ትክክለኛውንና ተገቢውን ፍትሕ ስለሰጡኝ ነው፡፡ ቀደም ብለው ከየመን አስመጥተውኝ ቢሆን ኖሮ የወጣትነቴን ጊዜ በእስር ቤት ከማሳልፍ ብዙ እሠራበትና ራሴን፣ ወገኖቼንና አገሬን እጠቅም ነበር፡፡ 
ሪፖርተር፡- ከብዙ የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ወደ አገርዎ በመመለስ ፍትሕ አግኝተዋል፡፡ ከሰባት ዓመታት በፊት የጀመሯቸውና የወጠኗቸው የንግድ እንቅስቃሴዎችን በምን ሁኔታ ላይ ሆነው አገኟቸው?
አቶ አስመላሽ፡- ከእስር እንደወጣሁ ከአንድ ሳምንት ዕረፍት በኋላ በልጅነት ዕድሜ ወደጀመርኳቸው የንግድ ሥራዎችና በውጥን ላይ ወዳሉት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጄክቶቼ ነበር ያመራሁት፡፡ ምንም ነገር ላገኝ አልቻልኩም፡፡ ደብዛቸው ጠፍቷል፡፡ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በማድረግ በዋናነት የቀጠርኳቸው ሦስት ግለሰቦችን (ስማቸውን ለጊዜው መጥቀስ አልፈልግም) ላገኛቸው አልቻልኩም፡፡ በዚሀ አጋጣሚ መናገር የምፈልገው በወቅቱ በቂ ኮላተራል በማስያዝ የተበደርኳቸው ባንኮች ነበሩ፡፡ እኔን ሲያጡና ክፍያ ሲቆምባቸው በኮላተራል የያዟቸውን ንብረቶች ሸጠው እንደሚወስዱ በብድር ውሉም ላይ የተገለጸ ነገር ቢሆንም፣ የሸጡት ንብረት ሳይበቃቸው ወይም ካበደሩት ገንዘብ ጋር ያልተመጣጠነላቸው ካሉ፣ አብረውኝ ሆነውና የነበረኝን ንብረት በጋራ አስመልሰን ለመክፈል ፈቃደኛ መሆኔን ነው፡፡ ባንኮች ብቻ ሳይሆኑ፣ ምርቶቻቸውን በዱቤ ወደ መጋዘኖቼ ያስገቡና ሳይከፈላቸው የቀሩም ካሉ፣ ተባብረንና በእምነት በውክልና እንዲያስተዳድሩ የፈቀድኩላቸውን ግለሰቦች በሕግ ፊት አቁመን ንብረታችንን በማስመለስ በጋራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ መንግሥት የነበሩኝን ማሽነሪዎች፣ የንግድ መጋዘኖች አጠቃላይ ንብረቶቼን የግል መኖሪያ ቤቴን ሳይቀር በግላቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም ያዞሩት፣ በቀድሞ የእኔ ሠራተኞች (ምክትል ሥራ አስኪያጆች)፣ አሁን ደግሞ ባለሀብት የሆኑትን ግለሰቦች ተፈርዶልኝ ወደነበርኩበት ሥራ በመመለስ ራሴን፣ ቤተሰቤን፣ ወገኔንና አገሬን እየረዳሁ እንድኖር ያደርግልኝ ዘንድ እምነቴ ሙሉ ነው፡፡ የማስተምራቸው የሙት ልጆችና የራሴ ልጆች አሉኝ፡፡ ምክትል ሥራ አስኪያጆቹ እህቶቼን ‹‹ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እየፈለጓችሁ ነው›› በማለትና በማስፈራራት ብዙ ጉዳት አድርሰውብኛል፡፡ የማምነው፣ እመካበት የነበረውና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ያደረግኩት ግለሰብ፣ የመኖሪያ ቤቴን ውክልና እህቴ እንድትሰጠው በማድረግ፣ በአክስቱ ስም አዙሮት አገኘሁት፡፡ ጐንደር ላይ የነበረው የማበጠሪያና ማሸጊያ ማሽንን አንዱ ሠራተኛዬ የነበረው ግለሰብ በቀጥታ በራሱ ስም አዙሮ ትንሽ ከቆየ በኋላ በሚስቱ ስም ማዞሩን መረጃ ደርሶኛል፡፡ 
ሪፖርተር፡- እርስዎ ነፃ መሆንዎ ተረጋግጧል፡፡ ንብረትዎን በሚመለከት በሕግ አልጠየቁም?
አቶ አስመላሽ፡- ጠይቄያለሁ ‹‹ማጣራት የምትችለው አዲስ አበባ ላይ ያለውን ብቻ ነው፡፡ ሌላውን ማጣራት የሚቻለው በየክልሉ ነው አለኝ›› የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፡፡ በየክልሉ ሄደህ አመልክት ተባልኩ፡፡ ነገር ግን ያለፉት ሰባት ዓመታት ያለአግባብ ታስሬ እንደነበር መንግሥት ያውቃል፡፡ ጉዳዬ በፌዴራል መንግሥት ታይቶ የነበሩኝ ንብረቶቼ የት እንደደረሱ ተጣርቶና ተሰብስቦ ‹‹ገንዘብ አለን›› ለሚሉ ባንኮችም ሆኑ ግለሰቦች ከተሰጠ በኋላ ቀሪው ደግሞ እንደ አዲስ ‹‹ሀ›› ብዬ ድሮ በጀመርኩት ሥራ እንድሰማራ ሊደረግልኝ ይገባል የሚል ጥያቄ ለሚመለከታቸው የፍትሕ አዛዦች ጥያቄ አቅርቤያለሁ፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ‹‹የግለሰብ ጉዳይ አናይም›› ብሎኛል፡፡ ከየመን ድረስ ያመጣኝ ግን እኔን ግለሰቡን ፌዴራል ፖሊስ ነው፡፡ የግል ቤቴን በሚመለከት ለፖሊስ አመልክቼ ምርመራ ከተደረገበት በኋላ ወንጀል መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በተጠርጣሪው ላይ ክስ ቢመሠረትም ተጠርጣሪው ለጊዜው ታስሮ ወዲያው ተፈትቷል፡፡ መለቀቁ ግን ግራ አጋብቶኛል፡፡ ተመሳሳይ ወንጀል የፈጸሙ ግን ዋስትና ተከልክለው በእስር ላይ የሚገኙ ብዙ ናቸው፡፡ የእኛ ተጠርጣሪ ግን ከእስር ወጥቶ እኛ የቆጠርናቸውን ምስክሮች ከፍርድ ቤት በራፍ ላይ አሳስሯቸው በዋስ ተለቀው ጉዳያቸውን የተገላቢጦሽ እየተከታተሉ ነው፡፡ ግለሰቡን ግን ከ15 በላይ ድርጅቶች፣ በጣም ብዙ ተሽከርካሪዎች፣ ኦርጅናል የንግድ ፈቃድ፣ ውሎችና የተለያዩ የግልና መንግሥታዊ ሰነዶች፣ መኖሪያ ቤት፣ ጥሬ ገንዘብና በሌሎች ጉዳዮች መንግሥት እንዲጠይቅልኝ እየጠየቅኩኝ ነው፡፡ ‹‹ማስረጃ ስለሌለው ሊጠይቀኝ አይችልም›› በማለት የፈጸመው ቢሆንም፣ ብዙ ሐቀኛ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችና ሌሎች እማኞች ስላሉኝ፣ ከመንግሥት ድጋፍ ጋር እውነታው ላይ እደርሳለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ በታሰሩበት ዓመት የድርጅቶችዎ ካፒታል ምን ያህል ደርሶ ነበር?
አቶ አስመላሽ፡- 2.5 ቢሊዮን ብር ደርሶ ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም.፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ከተፈቱ በኋላ እየደረሰብዎ ያለ ችግር አለ?
አቶ አስመላሽ፡- በጣም ብዙ ችግር እየደረሰብኝ ነው፡፡ አንደኛ ካገር እንድወጣ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል፡፡ ሁለተኛ ከአገር የማልወጣ ከሆነ በእውነትም ይሁን በውሸት ሴራ ተጠንስሶ ወደ እስር ቤት እንደምወረወር ተነግሮኛል፡፡ ይኸንን ማድረግ ካልተቻለ ሕይወቴን እንደሚያጠፉ ጊዜ ገደብ ወስነው ነግረውኛል፡፡ ለአንድ ወር የተሰጠኝ የጊዜ ገደብ ቢያልፍም እስካሁን አለሁ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር እየተጠነቀቅሁ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲያውቅልኝ የምፈልገው ነገር፣ እኔ በሕይወቴ ከማንም ጋር ተጋጭቼና ፀብ ውስጥ ገብቼ አላውቅም፡፡ የቅርብ ወዳጆቼ የነበሩ የቀድሞ ሠራተኞቼና ኃላፊ ያደረግኳቸው ግን እያስፈራሩኝ ነውና ሕይወቴ ቢያልፍም ሆነ አንድ ጉዳት ቢደርስብኝ ከእነሱ ሌላ ተጠያቂ እንደማይኖር ሊታወቅልኝ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እያለ በጓዳ ውስጥ ተሸሽጌ አልሞትም፡፡ መጠየቅ የሚገባኝንም በሕግ ፊት የመጠየቅ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳለኝም ልገልጽ እወዳለሁ፡፡ እታሰራለሁ፣ እታፈናለሁና እገደላለሁ ብዬ መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር የከተማ ውስጥ ሽፍቶችና ትናንንሽ ‹‹መንግሥት ነን›› ባዮችን ፈርቼ የማጀት አጫዋች እንደማልሆን ሊያውቁትና ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ አንዳንዶች ማንነታቸው በግልጽ ባይታወቅም፣ ዓቃቤ ሕግ በእኔ ላይ የወንጀል ድርጊት ፈልጐ ክስ እንዲመሠርት እየገፋፉት መሆኑንም ለማወቅ ችያለሁ፡፡ ነገር ግን መንግሥትም ሆነ የፍትሕ አካሉ ማንነቴን በደንብ አብጠርጥረው ካወቁ በኋላ ነፃ መሆኔን ስላረጋገጡልኝ፣ ካሁን በኋላ ለሚመጣብኝ ‹‹በሬ ወለደ›› የክስም ሆነ የውንጀላ እንቅስቃሴ ቅንጣት ታክል የሚያስፈራኝ ነገር የሌለ መሆኑንም ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ፡፡

በዛሬውችሎት የታሪክ ምሁሩ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ከመቀመጫቸው በመነሳት ታሪካዊ እና አስደማሚ ንግግር አድርገዋል፡፡


የታሪክ ምሁሩ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ከመቀመጫቸው በመነሳት ታሪካዊ እና አስደማሚ ንግግር አድርገዋል፡፡
“እዚህ ፍርድ ቤት የተገኘነው ፍርድ ቤቱ ፍትህ ይሰጠናል ብለን አይደለም፡፡ በዚህ ፍርድ ቤት ላይ ቅንጣት ታክል አመኔታ የለንም፡፡ መከላከያ ምስክርም ሆነ ማስረጃ የምናቀርበው ለታሪክ ተመዝግቦ እንዲቀር እንጂ በዚህ ፍርድ ቤት ጉዳያችን ታይቶ ፍትህን እናገኛለን ብለን አይደለም፡፡ ትክክለኛ ፍርድ ቤት ቢሆን ህገ መንግስቱ ተጥሶ ኢቲቪ ላቀረበው ብይን ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በሰጠ ነበር” በማለት ረዘም ያለ አስደማሚ እና የፍትህ ስርአቱ የላዠቀ መሆኑን በመረጃ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ችሎቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ንግግራቸውን በየተራ ቆመው ለፍርድ ቤቱ ሲያሰሙ ዳኞቹ ደንግጠው ንግግራቸውን ከማዳመጥ የዘለለ መሃል መሃል ላይ ለማስቆም ከመሞከር በዘለለ ሌላ ምንም ሊያደርጉ አልተቻላቸውም፡፡
ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ንግግራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የኢቲቪ ጉዳይ እኔ አይመለከተኝም በማለት የመሃል ዳኛው ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
እነዚህን መሰል ጀግና ወኪሎች በመምረጣችን
እድለኞች ነን!!!

Aseged Tamene

Sunday, February 2, 2014

ኦሞት ኦባንግ – የታዳኝ አዳኝ ድራማ


ኢህአዴግም በበኩሉ እያደናቸው ነው
Wanted omot obang olum
  • “ሁሉም ከህግ አያመልጡምና ዜጎች መረጃ በመሰብሰብ የቤት ስራችሁን ስሩ” ኦባንግ ሜቶ
  • ኦሞት ኦባንግ በዓለም ዓቀፍ ተቋማት ለፍርድ እንዲቀርቡ እየታደኑ ነው
ሰሞኑን አገር ጥለው መኮብለላቸው የተደመጠው የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦሞት ኦባንግ በተለያዩ የዓለም ዓቀፍ ተቋማት ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነ ታወቀ። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ፍትህ የተዛባባቸው ዜጎች ሁሉ መረጃ በማሰባሰብና ለድርጅታቸው በመላክ የዜግነት የቤት ስራቸውን እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። አቶ ኦሞትን ፍትህ ደጅ ለማቆም ከ19 ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በኅብረት እየሰሩ መሆናቸውም አመልክተዋል። በሌላም በኩል ኢህአዴግም “ነገር ሳይበላሽ” እያደናቸው እንደሆነ ተሰምቷል፡፡
በ2003 በጅምላ ለተጨፈጨፉና በሺህ ለሚቆጠሩ የአኙዋክ ተወላጆች መሰደድ ከመለስ ቀጥሎ ግንባር ቀደም ተጠያቂ የሚባሉት አቶ ኦሞት፤ ሳምንት በፈጀ ግምገማ ከክልሉ ሊቀመንበርነታቸው መነሳታቸውና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው መመደባቸው ይታወሳል። “እውነተኛው ወያኔ” እየተባሉ የሚጠሩት አቶ ኦሞት ምንም እንኳ በሚኒስትርነት ደረጃ ቢመደቡም በሙስና ተወንጅለው እንደሚታሰሩ ጎልጉል ምንጮቹን ጠቅሶ መዘገቡ አይዘነጋም።
በሰኔ 10፤2005 ዓም (June 17, 2013) የጎልጉል ዘገባ ላይ እንደተጠቀሰው ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ አላግባብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ እንዲሁም በክልሉ የሚፈጸሙትን የተጭበረበሩ የበጀት አፈጻጸሞችንና ምዝበራዎችን የሚያጋልጡ ሰነዶችን በሚስጥር ተደራጅቶ ለኢህአዴግ የድርጅት ቢሮ ቀርቦ ነበር። የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኢሬሳ ከፍተኛ ምስጢር ያላቸውን ሰነዶች በመያዝ ከመታሰራቸው በፊት መሰወራቸውን የጠቆመው ዘገባ “የቢሮ ሃላፊው ይዘው የተሰወሩት መረጃ አቶ ኦሞት የፈረሙባቸው ከፍተኛ የገንዘብ ሰነዶችና ሙስና የተከናወነባቸው የኮንስትራክሽንና የተለያዩ መረጃዎች ይፋ የሚያደርጉ ነበሩ። በወቅቱ “መረጃዎቹ አንድ ቀን ህዝብ ፍርዱን ይሰጥ ዘንድ ይፋ ይሆናሉ” ተብሎም ነበር። የመረጃ ምንጫቸውን ባይጠቅሱም አቶ ኦባንግ “ኦሞትን በተመለከተ ከበቂ በላይ መረጃ አለን፤ ህግ ፊት እናቀርበዋለን፤ በንጹን ደም ተጨማልቆና ህዝብ ላይ ግፍ ፈጽሞ መሰወር አይቻልም” በማለት በስልክ ለጎልጉል ተናግረዋል። አቶ ተስፋዬ ኢሬሳ በድንገት ምሳ እየተመገቡ ከመርዝ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው በድንገት ማለፉ ይታወሳል።
ከታህሳስ 23 ቀን 2004 ዓ ም ጀምሮ ሟቹ አቶ መለስ በላኳቸው አስገምጋሚዎች ለሳምንት በተካሄደ አውጫጪኝ አቶ ኦሞት “የአኙዋክ ተወላጆችን አስጨፍጭፈሃል” የሚል መነሻውና ዓላማው ግልጽ ያልሆነ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። በወቅቱ ግምገማው ላይ የነበሩ እንዳሉት አቶ ኦሞት “እኔ በዚህ ጉዳይ ተጠያቂ ከሆንኩ መሳሪያና ወታደር የሰጠኝ መለስም ይታሰራል” በማለት መልስ ሰጥተው ነበር።
በወቅቱ አቶ ኦባንግ ሜቶ የሚመሩት ድርጅት /አኢጋን/ አቶ መለስን በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ችሎት ተጠያቂ ለማድረግ ያቀረበው ማመልከቻ ተቀባይነት ያገኘበትና አቶ መለስ ላይ ክስ እንዲመሰረት ውሳኔ የተደረሰበት ዜና የተሰማበት ነበር። ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የጋምቤላ ምንጮች “አቶ መለስ አቶ ኦሞትን በጭፍጨፋው ተጠያቂ በማድረግና ርምጃ በመውሰድ ራሳቸውን ጲላጦስ ለማድረግ የወጠኑት አካሄድ እንደሆነ የፌዴራል ሰዎች ነግረውናል። ኦሞትም በሙስና በዘረጋው መዋቅር እስከላይ ድረስ ዘመድና ተቆርቋሪ ስላበጀ መረጃው ደርሶት ነበር” ብለዋል። /በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የተመሰረተው ክስ መለስ ቢሞቱም እስካሁን ክፍት ነው/
Wanted omotበሌላም በኩል ወቅቱ በክልሉ ኢህአዴግ ለልማት በሚሰጠው ርዳታ ዜጎችን ለማፈንና ረግጦ ለመግዛት የሚያስችለውን ሃይል ያደራጅበታል በሚል ተቆርቋሪዎች መረጃ አስደግፈው ባቀረቡት ክስ ዓለም ባንክ አጣሪ የላከበት ነበር። ከዚሁ ጋር ተያይዞ መሬታቸውን፣ የትውልድ ቀያቸውን በአንጋቾች የተነጠቁ ምስኪን ዜጎች ድምጽ ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝቶ ኢህአዴግን ክፉኛ የተፈታተነበት ነበር። ለዚህ ይመስላል ኢህአዴግ በግምገማ በርካታ የክልሉን ሃላፊዎች ወረዳ ድረስ በመዝለቅ በሙስና ሰበብ ሲያባርርና ሲያስር፣ አቶ ኦሞትን ወደ ፌዴራል በማዛወር በቅርብ ይከታተላቸው ነበር። አቶ ኦሞት ወደ ፌዴራል ሲዛወሩ “የቤንሻንጉል ጉምዝ ፕሬዚዳንት በነበሩት አቶ ያረጋል አይሸሹ ላይ የተደረገው ይፈጸምባቸዋል” ተብሎ አስቀድሞ ተተንብዮ ነበር።
ለአብነት ከላይ በተዘረዘሩት መነሻዎችና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ሳቢያ የአቶ ኦሞትና የህወሃት ግንኙነት ማክተሙን የሚናገሩት ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ክፍሎች፣ “ቀደም ሲል ህወሃትን ሲያገለግሉ ኖረው መጨረሻቸው እስር እንደሆነው አራት የቀድሞ የክልሉ መሪዎች፣ ወይም እንደ አምስተኛው ፕሬዚዳንት አቶ ኦኬሎ አኳይ ስደት እጣ ፈንታቸው ይሆናል” የሚል ቅድመ ትንበያ ነበር።
አቶ ኦኬሎ አኳይ በአኙዋክ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ አስመልክቶ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ክልሉን ወክለው የተዛባ መረጃ እንዲሰጡ ታዘው ነበር። በአቶ አባይ ጸሃዬና ገብረአብ በርናባስ መመሪያ መሰረት ግጭቱ በጎሳ ላይ የተመረኮዘ የርስ በርስ እንደሆነ፣ በግጭቱ 59 ሰዎች ብቻ ሲሞቱ አንድ ቤት መቃጠሉን እንዲናገሩ የተሰጣቸውን መመሪያ ያልተቀበሉት አቶ ኦኬሎ ህይወታቸው አደጋ ላይ በመውደቁ አገር ጥለው መሰደዳቸው ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ በተደጋጋሚ ገልጸው ነበር። ይሁን እንጂ አቶ ኦኬሎ አኳይ በስደት ሆነው በይፋ በዚህ ጉዳይ መግለጫ ለመስጠት አለመድፈራቸው ብዙዎችን ግራ ያጋባ ጉዳይ ሆኗል።
ኦሞት የት ናቸው?
አቶ ኦሞት የክልሉ የደህንነት ሃላፊና ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ባገለገሉበት ወቅት ፍጹም ታማኝ ስለነበሩ በ2005 የተሰጣቸው የክልል መሪነት ስልጣን ለህወሃት ለሰሩት ውለታ የተከፈለ ወሮታ እንደሆነ ተደርጎ ነው የሚወሰደው። በዚሁ መነሻ ይመስላል አብዛኛው የጋምቤላ ተወላጆች ለአቶ ኦሞት የከፋ ጥላቻ እንደነበራቸው የሚናገሩ ክልሉ ተወላጆች፣ ኦሞት ከአገር ኮበለሉ መባሉ አያስገርማቸውም።
አሁን ጥያቄው ኦሞት ከኢህአዴግ አፍንጫ ስር እንዴት አመለጡ? አሁን የት ናቸው? መጪው እጣ ፈንታቸውስ? የሚለው ነው። አዲስ አድማስ ባለፈው ቅዳሜ እትሙ አቶ ኦሞትን የግምባር ዜና አድርጎ ሲያቀርብ አገር ጥለው መኮብለላቸውን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ማረጋገጣቸውን አስነብቧል። አቶ ኦባንግ ሜቶ ለጎልጉል እንደገለጹት አቶ ኦሞት ከሁለት ወር በፊት ለስልጠና አውሮፓ ሲመጡ በነበራቸው ቪዛ ከሁለት ሳምንት በፊት ዓርብ ቀን አገር ጥለው እንደወጡ መረጃው አላቸው።
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ ከ19 የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ እየሰሩ መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ ሜቶ “ኦሞት መለስ በህይወት እያለ ቢኮበልል መልካም ነበር። አሁን ከኦሞት የምንፈልገው ችሎት ፊት በወገኖቹ ላይና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ፣ ቶርቸር፣ እስር፣ ዝርፊያ፣ የመሬት ንጥቂያ፣ ወዘተ አስመልክቶ እንዲናዘዝ ነው” ብለዋል። ኮብላዩ አቶ ኦሞት የት እንደሚገኙ ተጠይቀው “አሁን እዚህ ነው የሚባልበት ደረጃ ላይ አይደለንም። ግን መሰወር የሚችል አይመስለኝም። በደም ተጨማልቆ በስደት ተበዳይ መስሎ መኖር አይቻልም። የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከመለስ ጋር በተመሰረተው ክስ ላይ ኦሞት የተካተተ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። እኛ እንኳ ዝም ብንል ፍትህ በርዋን አትዘጋም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጎልጉል ባሰባሰበው መረጃ አቶ ኦሞት አገር ጥለው የወጡት ከሁለት ሳምንት በፊት ሲሆን አንድ ሳምንት ቢዘገዩ ኖሮ እስር ቤት ይገቡ ነበር። አስቀድሞ በደረሳቸው መረጃ መሰረት አቶ ኦሞትን እስር ቤት እንዲወረወሩ የሚያዘው የአስር ማዘዣ የሚቆረጥበት ግምገማ ተዘጋጅቶ ነበር። እሳቸው አስቀድመው አገር ጥለው በመውጣታቸው ግምገማው ተስተጓጉሏል። ግምገማው የዓለም ባንክ አጣሪ ቡድንበትላንትናው ዕለት ኢትዮጵያ ሲገባ በሙስናና በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ኢህአዴግ ርምጃ በመውሰድ ዝግጅት አጠናቆ ለመጠበቅ የሚረዳው ነበር። ግን አልሆነም።
በጋምቤላ በኢቨስትመንት ስም መሬት ወስደው ከሚሰሩት መካከል 70 ከመቶ የሚሆኑት የቀድሞ የህወሃት ታጋዮችና የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው አቶ ኦሞት የሚደረግባቸውን ክትትል አልፈው አገር ሊወጡ እንደቻሉ ግምት አለ። አሁን “ባለሃብት” የሚባሉት እነዚህ ክፍሎች ባላቸው መዋቅር ሳቢያ አቶ ኦሞትን ሊታደጓቸው እንደሚችሉ ከግምት በላይ የሚናገሩ አሉ።
አቶ ኦሞት ሆላንድ ገብተዋል የሚሉም አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አውሮፓ ሊገቡ አይችሉም በማለት ግምቱን የሚያጣጥሉ አሉ። እነዚህ ክፍሎች ወደ ማሌዢያ ሄደዋል የሚለውን ምንጭ ይደግፋሉ። በስፋት እንደሚነገረው ከሆነ አቶ ኦሞት ኤዢያ እንደሚሄዱ የሚያጠናክሩ ምልክቶች አሉ። አብዛኛው የኢህአዴግ ባለስልጣኖች በማሌዢያ ባንኮች ገንዘብ አላቸው። አቶ ኦሞትም በተመሳሳይ የማሌዢያ ባንክ ተጠቃሚ ናቸው ተብሎ እንደሚገመት የሚቀርቧቸው ይናገራሉ። በተመሳሳይ በኢንቨስትመንት ስም የተወዳጇቸው ባለሃብቶች በኤዢያ ከለላ ሊሆኗቸው ስለሚችሉ የመጀመሪያ ምርጫቸው ኤዢያ እንደሚሆን ይስማማሉ።
ለጎልጉል ማንነታቸውን ሳይገልጹ መረጃ የሰጡ የኢህአዴግ ሰው እንዳሉት “ኦሞት ርቆ አልሄደም ይያዝል” በማለት ግምታቸውን ሰጥተዋል። ጉዳዩን በቅርብ እንደሚከታተሉ የገለጹት እኚህ ሰው “ኦሞት ብዙ ጉዳዮችን እንዳያበለሽ ጥንቃቄ ሲደረግ ነበር። እንዴት ለጊዜውም ቢሆን ተሰወረ?” የሚለው መነጋገሪያ መሆኑን ግን አልሸሸጉም። ኦሞት በወቅቱ የፈጸሙትን ከ400 በላይ የአኙዋኮችን ጭፍጨፋ፣ የተሳተፉበትን ሙስና፣ የመሬት ነጠቃ፣ ግድያ፣ ወዘተ የወንጀል ምስጢር በማውጣት ኢህአዴግን አሳጥተው ፍርድ እንዲቀልላቸው መደራደሪያ ከማድረጋቸው በፊት ኢህአዴግ የራሱ አደን አጠናክሮ እንደሚገኝ ተጨማሪ ዘገባዎች አሉ፡፡
አቶ ኦባንግ ሜቶ የኦሞት መሰወር አያስጨንቅም ባይ ናቸው። ኦሞትን ፍትህ አሳድዳ ትይዘዋለች የሚሉት አቶ ኦባንግ ትኩረታቸው ወንጀል የተፈጸመባቸው በሙሉ መረጃ በመሰብሰብና ወደ ጋራ ንቅናቄው በመላክ እንዲተባበሩ የመነሳሳታቸው ጉዳይ ላይ ነው። ህወሃቶች ወንጀል አሰርተው፣ መጨረሻ ላይ ፍትህ ወዳድ ለመምሰል በወንጀል ያጨማለቋቸውን ሰዎች ህግ ፊት አቅርበው እንደሚያስፈርዱባቸው ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “ሌሎች ከዚህና ከቀድሞው ተሞክሮ ተማሩ። ኦሞትን ፍትህ አደባባይ ለማውጣት የሚሰራው ስራ ወንጀለኞችን ለመፋረድ የምናደርገውን ትግል አንድ ርምጃ ያሳድገዋል። እንደ ኦሞት ያሉት ወንጀለኞች ካሉበት ይለቀማሉ። ይህንን ማድረግ አቅም አለን። በደም ተጨማልቆ በስደት መኖር አይቻልም። ሌሎችም ካሁኑ ንስሃ ግቡ፤ ህብረተሰባችሁን አስቀድሙ” ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ህወሃትም ሆነ ኢህአዴግ በራቸውን መክፈታቸው ወይም ለውጥ እንዲመጣ እንዲፈቅዱ የሚገደዱበት ዘመን መቃረቡን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “ነጻ ውጡና ህዝባችሁን ነጻ አውጡ፣ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለወንጀለኞች ቦታ የላትም፣ ትፋረዳቸዋለች” ሲሉ በድጋሚ ህዝብ በወንጀለኞች ላይ መረጃ በማሰባሰብ የቤት ስራውን በወጉ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

የቢሮ ኃላፊው በሙስና ላይ ምስክር ሳይሆኑ ተገደሉ

“ብዙ ሳይታወቅ የተገደሉ ተስፋዬዎች አሉ”
food
June 17, 2013 07:55 am By  3 Comments (Edit)
በነበራቸው የስራ ሃላፊነት በድብቅ መረጃ ሲያሰባስቡ ቆይተው ለመንግስት ካጋለጡ በኋላ ራሳቸውን ደብቀው የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኢሬሣ ምሳ እየተመገቡ ህይወታቸው ማለፉ ተሰማ። አቶ ተስፋዬ ሰኞ ለጸረ ሙስና ኮሚሽን የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ከኮሚሽነር አሊ ሱሌማን ጋር ቀጠሮ ይዘው ነበር።
በቅርቡ ወደ ፌደራል መንግስት የተዛወሩት የጋምቤላ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኡሞት ኦባንግ፣ ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ አላግባብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ እንዲሁም በክልሉ የሚፈጸሙትን የተጭበረበሩ የበጀት አፈጻጸሞችንና ምዝበራዎችን የሚያጋልጡ ሰነዶችን በሚስጥር በማደራጀት ለኢህአዴግ ያቀረቡት አቶ ተስፋዬ አሟሟታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
አቶ ተስፋዬ ኢሬሳ ከፍተኛ ምስጢር ያላቸውን ሰነዶች በመያዝ ከመታሰራቸው በፊት መሰወራቸውን፤ “የቢሮ ሃላፊው ይዘው የተሰወሩት መረጃ አቶ ኦሞት የፈረሙባቸው ከፍተኛ የገንዘብ ሰነዶችና ሙስና የተከናወነባቸው የኮንስትራክሽንና የተለያዩ መረጃዎች ናቸው። መረጃዎቹ አንድ ቀን ህዝብ ፍርዱን ይሰጥ ዘንድ ይፋ ይሆናሉ” በሚል ጎልጉል ምንጮቹን ጠቅሶ በ (ጥቅምት 19፤2005/October 29, 2012) መዘገቡ ይታወሳል።
ቀደም ሲል የጋምቤላ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ከላይ የተጠቀሰውን የሙስና ወንጀል በማጋለጣቸው ጋምቤላ መኖር ሳይችሉ ቀርተው ራሳቸውን ሸሽገው ለመኖር ተገደው እንደነበር የሚያውቋቸው ለጎልጉል አስረድተዋል።
“አቶ ተስፋዬ ሙስናን በማጋለጣቸው በፍርሃቻ ራሳቸውን ደብቀው ሊኖሩ አይገባም” በማለት ኢህአዴግ ከለላ እንደሚሰጣቸው ቃል በገባላቸው መሰረት ከተሸሸጉበት የወጡት አቶ ተስፋዬ ሰንጋተራ ትንሳዔ ሆቴል ከጋምቤላ ልጆች ጋር መገናኘት ይጀምራሉ።
ባለፈው ሳምንት ከፌዴራል የጸረ ሙስና ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ከያዙ በኋላ ኮሚሽነሩ በድንገት ለለቅሶ ወደ ጎንደር በመሄዳቸው ቀጠሮው ለሳምንት ይራዘማል። ለሰኞ (ሰኔ10፤2005) አዲስ ቀጠሮ ይይዛሉ።
በስልክ ያነጋገርናቸው ትንሳዔ ሆቴል አካባቢ እንደነበሩና ለጉዳዩ ቅርበት እንዳላቸው የሚገልጹ የጋምቤላ ተወላጅ የስራ ሃላፊ እንዳሉት አቶ ኦሞት ኦባንግ ለአቶ ተስፋዬ ስልክ ደውለው ነበር። አቶ ተስፋዬ ህይወታቸው ከማለፉ ሁለት ቀን በፊት የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኦሞት በስልክ ተማጽንዖ አቅርበው ነበር።
አቶ ኦሞት “እውነት ነው ጸረ ሙስና ኮሚሽን ቀጠሮ የያዝከው?” በማለት ይጠይቃሉ
“አዎ! እውነት ነው” በማለት አቶ ተስፋዬ መልስ ይሰጣሉ።
አቶ ኦሞት መልሰው “እንግዲያውስ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከመግባትህና ከማነጋገርህ በፊት ሁለታችን መገናኘት አለብን። የምንነጋገረው ነገር አለ” የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ። አቶ ተስፋዬ ስለ ስልክ ልውውጡ እንደነገሯቸው የተናገሩት እኚሁ ሰው፣ አቶ ኦሞት በስልክ ደጋግመው በመደወል ያቀረቡትን የ”እንነጋገር” ጥያቄ አቶ ተስፋዬ አልቀበልም ይላሉ።
ጋምቤላ ስራቸውን ለቀው ራሳቸውን ደብቀው የኖሩት በእርሳቸው ምክንያት መሆኑን፣ ፍትህ እንደሚፈልጉ፣ አሁን ለመነጋገር ጊዜው እንዳልሆነ፣ ዘርዝረው ለአቶ ኦሞት መናገራቸውን ያወሱት የጎልጉል ምንጭ፣ ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው አቶ ኦሞት በንዴት ተዛልፈው ነበር።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው እንግዲህ አቶ ተስፋዬ ትንሳዔ ሆቴል ሰዎችን በመላላክና በመታዘዝ ከሚኖር አንድ የጋምቤላ ሰው /አቶ ተስፋዬ የሚረዱት በምግባር ጉዳይ የሚታማና ጸበኛ የሚባል ሰው ነው/ አብረው ተቀምጠው ምሳ እየበሉ ሳለ አቶ ተስፋዬ አረፋ ይደፍቃቸዋል። ወዲያው ከተቀመጡበት ተንሸራተው መሬት ይወድቃሉ። ቀጥሎም ሰውነታቸው ይዝልና ኮማ ውስጥ ይገባሉ። ከአፋቸው እየተዝለገለገ የሚወጣው ፈሳሽ በመጨመሩና የተለያየ ርዳታ ቢደረግላቸውም ሊተርፉ ስላልቻሉ ሆስፒታል ተወስደው ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።
አቶ ተስፋዬ ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት እንደሞቱ የሚናገሩት የጎልጉል ምንጭ አሟሟታቸው ከመርዝ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ ተስፋዬ በሙስና ወንጀል ላይ ያሰባሱትን መረጃ ለተለያዩ አካላት የበተኑ ስለሆነ እሳቸውን በመግደል ማድበስበስ እንደማይቻል አስታውቀዋል። አቶ ተስፋዬ ሙስና ካጋለጡ በኋላ መሰወራቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው። በተያያዘ በጋምቤላ ኢንቨስትመንት ላይ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ውስጥ ከ70በመቶ በላይ የሆኑት የህወሓት የቀድሞ ታጋዮች የነበሩና የክልል አንድ ተወላጆች መሆናቸው የአቶ ተስፋዬን አሟሟት ይበልጥ ውስብስብ እንዳደረገው አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ “የአቶ ተስፋዬ ሞት አሳዛኝና አስደንጋጭ ነው። ብዙ ሳይታወቅ የተገደሉ ተስፋዬዎች አሉ” በማለት ስለ አቶ ተስፋዬ ሞትና አሟሟት መረጃ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል።
“አቶ ተስፋዬ ለእውነት ሲል ሞቷል። ኢህአዴግ ውስጥ በርካታ የወንጀል መረጃ ያላቸው ወገኖች አሉ። እንዲህ ያሉ ዜጎች በየትኛውም ዘመን አይረሱም። የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ስማቸውና ታሪካቸው ከጨዋነታቸው ጋር ተመልሶ ህያው ይሆናል። ሌቦችና ነፍሰገዳዮች ወደ ህግ ሲያመሩ፣ እንደ አቶ ተስፋዬ አይነቶቹ የመጪው ትውልድ ታላቅ ምሳሌ ሆነው እየተወደሱ ህያው ሆነው ይኖራሉ” የሚል አስተያየት የሰጡት አቶ ኦባንግ፤ አቶ ተስፋዬ ያሰባሰቧቸው የሙስናና ተመሳሳይ ወንጀሎች ማሳያ ሰነዶች እጃቸው ላይ ስላለ አቶ ተስፋዬን በመግደልና በማስገደል ወንጀል ማድበስበስ እንደማይቻል ተናግረዋል።
የአቶ ተስፋዬ የቀብር ስነስርዓት ጋምቤላ መፈጸሙን ለመረዳት ተችሏል። ቤተሰቦቻቸውን በማግኘት ሆስፒታሉ ስለ አሟሟታቸው የሰጠውን አስተያየት ጠይቀን ለመረዳት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም።


የቢሮ ኃላፊው በሙስና ላይ ምስክር ሳይሆኑ ተገደሉ


“ብዙ ሳይታወቅ የተገደሉ ተስፋዬዎች አሉ”
food
በነበራቸው የስራ ሃላፊነት በድብቅ መረጃ ሲያሰባስቡ ቆይተው ለመንግስት ካጋለጡ በኋላ ራሳቸውን ደብቀው የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኢሬሣ ምሳ እየተመገቡ ህይወታቸው ማለፉ ተሰማ። አቶ ተስፋዬ ሰኞ ለጸረ ሙስና ኮሚሽን የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ከኮሚሽነር አሊ ሱሌማን ጋር ቀጠሮ ይዘው ነበር።
በቅርቡ ወደ ፌደራል መንግስት የተዛወሩት የጋምቤላ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኡሞት ኦባንግ፣ ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ አላግባብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ እንዲሁም በክልሉ የሚፈጸሙትን የተጭበረበሩ የበጀት አፈጻጸሞችንና ምዝበራዎችን የሚያጋልጡ ሰነዶችን በሚስጥር በማደራጀት ለኢህአዴግ ያቀረቡት አቶ ተስፋዬ አሟሟታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
አቶ ተስፋዬ ኢሬሳ ከፍተኛ ምስጢር ያላቸውን ሰነዶች በመያዝ ከመታሰራቸው በፊት መሰወራቸውን፤ “የቢሮ ሃላፊው ይዘው የተሰወሩት መረጃ አቶ ኦሞት የፈረሙባቸው ከፍተኛ የገንዘብ ሰነዶችና ሙስና የተከናወነባቸው የኮንስትራክሽንና የተለያዩ መረጃዎች ናቸው። መረጃዎቹ አንድ ቀን ህዝብ ፍርዱን ይሰጥ ዘንድ ይፋ ይሆናሉ” 
ቀደም ሲል የጋምቤላ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ከላይ የተጠቀሰውን የሙስና ወንጀል በማጋለጣቸው ጋምቤላ መኖር ሳይችሉ ቀርተው ራሳቸውን ሸሽገው ለመኖር ተገደው እንደነበር የሚያውቋቸው ለጎልጉል አስረድተዋል።
“አቶ ተስፋዬ ሙስናን በማጋለጣቸው በፍርሃቻ ራሳቸውን ደብቀው ሊኖሩ አይገባም” በማለት ኢህአዴግ ከለላ እንደሚሰጣቸው ቃል በገባላቸው መሰረት ከተሸሸጉበት የወጡት አቶ ተስፋዬ ሰንጋተራ ትንሳዔ ሆቴል ከጋምቤላ ልጆች ጋር መገናኘት ይጀምራሉ።
ባለፈው ሳምንት ከፌዴራል የጸረ ሙስና ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ከያዙ በኋላ ኮሚሽነሩ በድንገት ለለቅሶ ወደ ጎንደር በመሄዳቸው ቀጠሮው ለሳምንት ይራዘማል። ለሰኞ (ሰኔ10፤2005) አዲስ ቀጠሮ ይይዛሉ።
በስልክ ያነጋገርናቸው ትንሳዔ ሆቴል አካባቢ እንደነበሩና ለጉዳዩ ቅርበት እንዳላቸው የሚገልጹ የጋምቤላ ተወላጅ የስራ ሃላፊ እንዳሉት አቶ ኦሞት ኦባንግ ለአቶ ተስፋዬ ስልክ ደውለው ነበር። አቶ ተስፋዬ ህይወታቸው ከማለፉ ሁለት ቀን በፊት የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኦሞት በስልክ ተማጽንዖ አቅርበው ነበር።
አቶ ኦሞት “እውነት ነው ጸረ ሙስና ኮሚሽን ቀጠሮ የያዝከው?” በማለት ይጠይቃሉ
“አዎ! እውነት ነው” በማለት አቶ ተስፋዬ መልስ ይሰጣሉ።
አቶ ኦሞት መልሰው “እንግዲያውስ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከመግባትህና ከማነጋገርህ በፊት ሁለታችን መገናኘት አለብን። የምንነጋገረው ነገር አለ” የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ። አቶ ተስፋዬ ስለ ስልክ ልውውጡ እንደነገሯቸው የተናገሩት እኚሁ ሰው፣ አቶ ኦሞት በስልክ ደጋግመው በመደወል ያቀረቡትን የ”እንነጋገር” ጥያቄ አቶ ተስፋዬ አልቀበልም ይላሉ።
ጋምቤላ ስራቸውን ለቀው ራሳቸውን ደብቀው የኖሩት በእርሳቸው ምክንያት መሆኑን፣ ፍትህ እንደሚፈልጉ፣ አሁን ለመነጋገር ጊዜው እንዳልሆነ፣ ዘርዝረው ለአቶ ኦሞት መናገራቸውን ያወሱት የጎልጉል ምንጭ፣ ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው አቶ ኦሞት በንዴት ተዛልፈው ነበር።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው እንግዲህ አቶ ተስፋዬ ትንሳዔ ሆቴል ሰዎችን በመላላክና በመታዘዝ ከሚኖር አንድ የጋምቤላ ሰው /አቶ ተስፋዬ የሚረዱት በምግባር ጉዳይ የሚታማና ጸበኛ የሚባል ሰው ነው/ አብረው ተቀምጠው ምሳ እየበሉ ሳለ አቶ ተስፋዬ አረፋ ይደፍቃቸዋል። ወዲያው ከተቀመጡበት ተንሸራተው መሬት ይወድቃሉ። ቀጥሎም ሰውነታቸው ይዝልና ኮማ ውስጥ ይገባሉ። ከአፋቸው እየተዝለገለገ የሚወጣው ፈሳሽ በመጨመሩና የተለያየ ርዳታ ቢደረግላቸውም ሊተርፉ ስላልቻሉ ሆስፒታል ተወስደው ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።
አቶ ተስፋዬ ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት እንደሞቱ የሚናገሩት የጎልጉል ምንጭ አሟሟታቸው ከመርዝ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ ተስፋዬ በሙስና ወንጀል ላይ ያሰባሱትን መረጃ ለተለያዩ አካላት የበተኑ ስለሆነ እሳቸውን በመግደል ማድበስበስ እንደማይቻል አስታውቀዋል። አቶ ተስፋዬ ሙስና ካጋለጡ በኋላ መሰወራቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው። በተያያዘ በጋምቤላ ኢንቨስትመንት ላይ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ውስጥ ከ70በመቶ በላይ የሆኑት የህወሓት የቀድሞ ታጋዮች የነበሩና የክልል አንድ ተወላጆች መሆናቸው የአቶ ተስፋዬን አሟሟት ይበልጥ ውስብስብ እንዳደረገው አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ “የአቶ ተስፋዬ ሞት አሳዛኝና አስደንጋጭ ነው። ብዙ ሳይታወቅ የተገደሉ ተስፋዬዎች አሉ” በማለት ስለ አቶ ተስፋዬ ሞትና አሟሟት መረጃ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል።
“አቶ ተስፋዬ ለእውነት ሲል ሞቷል። ኢህአዴግ ውስጥ በርካታ የወንጀል መረጃ ያላቸው ወገኖች አሉ። እንዲህ ያሉ ዜጎች በየትኛውም ዘመን አይረሱም። የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ስማቸውና ታሪካቸው ከጨዋነታቸው ጋር ተመልሶ ህያው ይሆናል። ሌቦችና ነፍሰገዳዮች ወደ ህግ ሲያመሩ፣ እንደ አቶ ተስፋዬ አይነቶቹ የመጪው ትውልድ ታላቅ ምሳሌ ሆነው እየተወደሱ ህያው ሆነው ይኖራሉ” የሚል አስተያየት የሰጡት አቶ ኦባንግ፤ አቶ ተስፋዬ ያሰባሰቧቸው የሙስናና ተመሳሳይ ወንጀሎች ማሳያ ሰነዶች እጃቸው ላይ ስላለ አቶ ተስፋዬን በመግደልና በማስገደል ወንጀል ማድበስበስ እንደማይቻል ተናግረዋል።
የአቶ ተስፋዬ የቀብር ስነስርዓት ጋምቤላ መፈጸሙን ለመረዳት ተችሏል። ቤተሰቦቻቸውን በማግኘት ሆስፒታሉ ስለ አሟሟታቸው የሰጠውን አስተያየት ጠይቀን ለመረዳት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም።

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡