Tuesday, September 24, 2013

ህወሓት በአባይ ወልዱና ደብረፅዮን ቡድኖች በሁለት

ህወሓት በአባይ ወልዱና ደብረፅዮን ቡድኖች በሁለት መከፈሉ ይታወቃል። ባለፈው የህወሓት የማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የህወሃት እና ትግራይ ክልል ፕሬዘዳንት አባይና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተደርጎ የተሾመው ደብረፅዮን ጠብ በጣም በመክረሩ የተነሳ ሽጉጥ መማዘዛቸው ተሰምቷል። ሃይለማርያም ደሳለኝና በረከት ስምዖን ለማስታረቅ የሞከሩ ሲሆን ዉጤቱ አልታወቅም።

ይህ በ’ንዲህ እንዳለ የአባይ ቡድንም ሰሞኑ በሁለት ተከፍሏል፤ የአባይ ወልዱና የበየነ መክሩ። ከህወሓት ስብሰባ በኋላ የስልጣን ሽግሽግ ለማድረግ የተሞከረ ቢሆንም በየነ መክሩና ኪሮስ ቢተው ከስልጣናቸው ለመውረድ (ሓላፊነት ለመቀየር) ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ከአባይ ወልዱ ጋር ከፍተኛ አምባጓሮ ተፈጥሯል።
የህወሃት ሊቀ መንበር አባይ ወልዱ እና ምክትሉ ደብረጽዮን
የህወሃት ሊቀ መንበር አባይ ወልዱ እና ምክትሉ ደብረጽዮን
ኪሮስ ቢተው የትግራይ ግብርና ቢሮ ሓላፊና የኢንተርፕራይዞች የቦርድ ሰብሳቢ ነበር። አባይ ወልዱ ወደ ሌላ ቢሮ ሊቀይረው አስቦ ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። የኢንተርፕራይዞች (ብዙ በጀት የሚመደብበት) ስልጣን ግን ቀምቶ ለአለም ገብረዋህድ ሰጥቶታል። ግብርና ቢሮም ለወዲ አዳል ታስቦ ነበር። ግን ጠብ ስለተነሳ አልተሳካም። በየነ መክሩም የንግድና ኢንዱስትሪ (የከተማ ልማት ጨምሮ) ስልጣን በእጁ ሲሆን አባይ ቢሮው ለሌላ ሊሰጠው ፈልጎ ፍቃደኛ ባለመሆኑ ግን እስካሁን ውዝግብ ላይ ናቸው። በየነ መክሩ ወደ ሀገሩ (እስራኤል) የመሄድ ሓሳብ ይዟል።
የአባይ ቡድን በሁለት መከፈሉ (አባይና በየነ የሚመሩት) ማሳያ በትግራይ ክልል የዉሃ ሃብት ቢሮ አመራር አባላት የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች ተጣልተው እንደተደባደቡና አከባቢው እስካሁን በፌደራል ፖሊስ እየተጠበቀ መሆኑ ተረጋግጧል።
ስርዓት ሲበሰብስ እንዲህ ነው። ለማንኛውም ቸር ያሰማን።

Sunday, September 22, 2013

ወላጆች ንበረቶቻቸውን ከዘራፊዎች ለማስጣል በሪያድ ከኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ጋር እያደረጉ ያለው ትንቅንቅ ዛሬ ወደ ግጭት አመራ።

ወላጆች ንበረቶቻቸውን ከዘራፊዎች ለማስጣል በሪያድ ከኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ጋር እያደረጉ ያለው ትንቅንቅ ዛሬ ወደ ግጭት አመራ።

በወላጆች እና በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያ በዲፕሎማቶች መሃከል ዛሬ ሴፕቴምበር 22 2013 ምሽት ተፈጥሮ የነበረው ግጭት ለግዜው ጋብ ቢልም መንግስት በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ የተማሪዎቹ ወላጆች በተደጋጋሚ ላቀረቡት ጥያቄ አስቸኳይ መላምት ካለፈላለገ ጉዳዩ የከፋ ሊሆን እንደሚችል የወላጆች ኮሚቴ አባላት ይገልጻሉ!
በተለይ ዛሬ ሴፕቴምበር 22/2013 ምሽት በሪያድ አለማቀፍ የኮሚኒቲ ት/ቤት ተማሪ ወላጆች ኮሚቴ የሳውዲ መንግስት በወጭ፡ሃገር ዘጎች ላይ ያወጣውን ህግ ተከትሎ በኤንባሲው የተመረጠው የት/ቤቱ ህገወጥ፡የቦርድ አስተዳደር «የመኖሪያ ፈቃድ አልተሞላም ፡ ፓስፖርት አልታደሰም ፡ ቦንድ አልገዛችሁም ፡ ወላጆቻችሁ የድምጻችን ይሰማ ደጋፊዎች ናቸው ……ወዘተ » በጣም አስዛኝ እና ግብረገብነት በጎደለው ሰንካል ምክንያት  ከ 1ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን  ከትምህርት ገበታቸው ማፈናቀሉ ይታወሳል።

በመሆኑም የአያሌ ኢትዮጵያውያን ህጻናት በሰው ሃገር ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀል የአብዛኛውን ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ያላቸው ተስፋ እንዲጨልም አድርጓ። ይህንንም የተረዳው 11 አባላት ያሉት የት/ቤቱ የወላጆች ኮሚቴ ከ1 ሺህ የሚበልጥ የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ ኤምባሲው በራሱ ስልጣን መርጦ ህገወጥ በሆነ መንገድ ያስቀመጠው የት/ቤቱ ቦርድ አዲስ የትምህርት ዘምን መጀመርን አስመክቶ ያወጣውን የአዲስ እና ነባር ተማሪዎች  መመዝገቢያ ማመዘኛዎች ትክክለኝነት በመጠራጠር  ኮሚቴው የሳውዲ ት/ሚኒስቴር መ/ቤት ድረስ በመሄድ ለማጣራት ባደረገው ሙከራ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች በእጅ አዙር እንዳይ መዘገቡ ታግደው ከነበሩ 1ሺህ ኢትዮጵያውያን ህጻናት ውስጥ 8 መቶው የሳውዲ ት/ሚ ያወጣውን ህግ የሚያሞሉ መሆናቸውን በማረጋገጥ፡ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ኮሚቴው ማስቻሉን ተከትሎ ወላጆች በተጠቀሰው ቦርድ እና ከቦርዱ ጀርባ ሆነው በሪያድ እለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኮሚኒት ት/ቤትን የመማር ማስተማር ሂደት እያመሰቃቀሉ ባሉ ወገኖች ዙሪያ ለመነጋገር ሴፕቴምበር 22 2013 የወላጅ ኮሚቴው በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ ስብሰባ ጠርቶ እንደ ነበር የወላጆች ኮሚቴ ተወካይ ይገልጻሉ ። ተወካዩም በማያያዝ  ቀደም ብለው ስብሰባ ያደርጉባቸው የነበሩ ቦታዎች ወላጆች በግል በሚከራዮቸው አካባቢያቸው በሚገኙ  የመዝናኛ ቦታዎች መሆኑንን ጠቀሰው   በሪያድ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሃላፊ የሆኑት አቶ ተመስገን ኡመር ይህ አዳራሽ እያለ ለምን ለድህነታችሁ አስተማማኝ፡ያልሆነ ቦታ ትሰበሰባላችሁ ከኤምባሲው እና ከኮሚኒቲው ርቃችሁ በድብቅ ስብሰባ ለምን ታደርጋላችሁ በሚል ቅን አስተሳሰብ ለወላጆ ኮሚቴው በሰጡት  ሞራል እና ምክር ኮሚቴው ለእሁድ ቀን ሴፕቴምበር 22 2013 ከምሽቱ 7 ስዓት  ጀምሮ ወላጆች በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ፡ እንዲገኙ የስብሰባ ጥሪ በደብዳቤ እንደበተኑ ያወጋሉ። 

እስከ ተጠቀሰው ቀን ድረስ ምንም አይነት ተቃውሞ ከኤንባሲው እንዳልነበረ የሚናገሩት የወላጅ ኮሚቴው ተወካይ በስበሰባው እለት ወላጆችን ለማስተናገድ ኮሚኒተው አካባቢ ወንበሮችን ስናስተካክል ውለን ለተለዩ ጉዳዩች ከግቢ ወጥተን ስንመለስ የግቢው በር ያለወትሮው በቁልፍ ተቆልፎ ጠበቀን።  ጉዳዩን ለማጣራት ዘበኛውን በመስኮት ስንጠይቅ በአምባሳደር መሃመድ ሃሰን በተደገፈ ፌርማ በተጻፈ የደብዳቤ ተዕዛዝ መዘጋቱን ቢገልጽም በወቅቱ ጥሪ የተደረገላቸው ወላጆች ቁጥር እየጨመረ መምጣት አካቢው ተሽከርካሪ መተላለፊያ በመሆኑ ወላጆች  ለአደጋ እንዳይዳረጉ  ጠቅሰን በገዛ ቤታችን በር እንዲከፈትልን ብንማፀንም ዘበኛው ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ ስለነበር ፈቃደኛ አልነበረም ብለዋል ። የኮሚኒቲው ሊቀመንበር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን መጥተው በቁጣ የሚጉርመረመውን  ወላጅ ለማረጋጋት ሙከራ በማድረግ የኮሚኒቲውን በር እንደሚከፍቱ እና ህዝቡ እንደሚገባ  ቃል ገብተው ዲፕሎማቱን አነጋግሬ መጣሁ በለው ህዝቡን በር ላይ አቁመው በዛው መቀረታቸው አስነዋሪ እና አንድ የኮሚኒቲ ተወካይ ከሆነ አካል የሚጠበቅ አለመሆኑን ገልጸዋል። 
ከሰአታት ቆይታ  በሃላ አልፎ አልፎ አምባሳደር መሃመድ ሃሰንን  ወክለው እንደሚሰሩ የሚነገርላቸው ዲፕሎማት አቶ ዘላለም እና ቀደም ሲል በአዳራሹ እንደ ዜጋ መገልገል « መሰብሰብ » መብታችን መሆኑንን ምክራቸውን ሲልግሱ  የነብሩ የዲያስፖራው ሃላፊ አቶ ተመስገን ኡመር በወቅቱ ህዝቡን ለማነጋገር  መጥተው እንደ ነበር ቢታወቅም የህዝቡ ስሜት ጥሩ አለምሆኑ መገድ ላይ እያሉ  መርጃ ስለደረሳቸው እና በአንዳንድ ተእግስታቸው በተሞጠጠ ወላጆች በገዛ ቤታችን እንዴት እንከለከላለን በሚል ቁጣ እና ንዴት ሊፈጸምባቸው የሚችለውን እርምጃ በመስጋት  በት/ቤቱ የጓሮ በር  ድምጻቸውን አጥፈተው በመግባት ህዝቡ ከአካባቢው እስኪበትን እዛው ባሉበት ድምጻቸውን አጥፈተው ለመቆየት መገደዳቸውን  የአይን ምስክሮች ገልጸዋል። 
በመጨረሻ የወላጆች ኮሚቴው ወደፊት ተመሳሳይ የሆነ ስብሰባ እንደሚጠራ ጠቅሷ፡ህዝቡ እልህ ውስጥ፡ሳይገባ በሰከነ መንፈስ እና ህጋዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ አይን ባልገለጹ ሃገር ተረካቢ ታዳጊ ህጻናት ልጆቹ ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት እና ንብረቱ የሆነውን በሪያድ አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኮሚኒት ት/ቤት ከዘራፊዎች ለማዳን እያደረገ ያለውን ትግል አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመገስጽ የኢትዮጵያ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ስጥቶ አስቸኳይ የሆነ መፍትሄ እስካላበጀለት ድረስ  በዲፕሎማቱ እና በተማሪ ወላጆች መሃከል የተፈጠረው  ግጭት ወደ ከፋ ደረጃ እንደሚሸጋገር አበክረው አሳስበዋል። 


Ethiopian Hagere ሳውዲ አረቢያ ጅዳ በዋዲ 

በሪያድ የኢትዮጵያው አንባሳደር የሚመሩ ዲፕሎማቶች እና ወላጆች ተጋጩ !

ሰበር ዜና 
ስውዲ አረቢያ ሪያድ ከተማ ውስጥ በኢትዮጵያ ኮሚኒት ት/ቤት ተማሪ ወላጆች እና በኢትዮጵያው አንባሳደር መሃመድ ሃሰን በሚመሩ ዲፕሎማቶች ማሀከል ግጭት ተፈጠረ !

በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ግቢ በር ላይ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ዲፕሎማት እና ከ500 የሚበልጡ በሪያድ አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ት/ቤት ወላጆች መሃከል የተፈጠረው አለመግባባት ወደ ግጭት ማምራቱን ከስፍራው የሚደርሱ መረጃዎች ይገልጻሉ። ዲፕሎማቱ የተማሪውቹ ወላጆች በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ የሚገኘው አዳራሽ፡ውስጥ፡ለመሰብሰብ ዛሬ እሁድ ቀን ሴፕቴምበር 22 2013 ፕሮግራም ይዘው እንደነበር የሚገልጹት መረጃዎች በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያው አንባሳደር መሃመድ ሃሰን ተዕዛዝ ዲፕሎማቱ የተማሪውቹን ወላጆች አሸባሪዎች በማለት ወደ ኮሚኒቲው ግቢ እንዳይገቡ የግቢውን በር ዘግተውባቸዋል። ፍጥጫው በአሁኑ ሰአት አቅጣጫ እንዳይለውጥ፡ያሰጋል ዲፕሎማቱ ለሳውዲ ፖሊስ ጥሪ ቢያደርጉም እስካሁን አካባቢው የደረሰ የጸጥታ ሃይል እንደሌለለ እይተነገረ ነው ። ሙሉ ዝርዝር መረጃውን ይጠብቁ !!!

Ethiopian Hagere ከሳውዲ አረቢያ ጅዳ በዋዲ

የኤርትራው ፕሬዝደንት «ኢሳያስ አፈወርቂ » ‹‹ወደቦች አሉን ብለን መናገር አንችልም" አሉ

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ፊታቸውን ለምን ወደ አሰብ ወደብ አዞሩ? 


አንድ ወር አልሞላውም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የሚመሩት ቡድን ነበር ለብዙ ጊዜ በጠላትነት ሲተያዩ የቆዩ ሁለት የሶማሊያ ወገኖች (የፌዴራሉ መንግሥትና የጁባላንድ ግዛት አስተዳደር) የተሳካ እርቅ እንዲፈጥሩ ያደረገው፡፡


ይኼ በአብዛኛው ለአልሸባብ ድጋፍ ይሰጣል ተብሎ የሚታማውና ኪስማዩና ሌሎች እጅግ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሥፍራዎችን የሚያጠቃልለው ግዛት አንድም ቀን የፌዴራሉ መንግሥት አካል ሆኖ አያውቅም፡፡ አንዱ ለሌላው ዕውቅና አይሰጡም ነበር፡፡ አሁን ግን በፌዴሬሽን ቅርፅ በጋራ ለመሥራት አንዱ ለሌላው ዕውቅና እንዲሰጥ ተስማምተዋል፡፡ 

ይህ ዕርቅ ዕውን በሆነበት ዕለት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተርን ጨምሮ ሁለት ጋዜጠኞች አነጋግረዋቸው ነበር፡፡ ለሶማሊያ ሕዝብ ብቻም ሳይሆን ለአካባቢው ሰላም ስምምነቱ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ሲያስረዱ፣ ‹‹ወንድማማች ሕዝቦች ናቸው፡፡ ዕርቅ መፍጠር ብቻ ነው የሚጠቅማቸው፡፡ ከጦርነትና ከጥላቻ አንድም ወገን አይጠቀምም፤›› አሉ፡፡ ታዲያ ጋዜጠኞቹ፣ ‹‹በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል መቼ ነው ሰላም የሚወርደው?›› የሚል ጥያቄ ጣል አደረጉላቸው፡፡ ውይይቱ ቀጥሏል፡፡ በነገራችን ላይ ከሌሎች የኢሕአዴግ መንግሥት ባለሥልጣናት ለየት ባለ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ በሒልተን ሆቴል በአንድ ጥግ ሆነው ሲወያዩ፣ ጋዜጠኞቹ እንደ ጋዜጠኛ እሳቸውም እንደ ባለሥልጣን ሆነው አልነበረም፡፡ ሁለቱንም እጆቻቸውን በጋዜጠኞቹ ትከሻ ላይ ጣል አድርገው በጨዋታ መልክ እንጂ እንደ ባለሥልጣን በፕሮቶኮል ተጨናንቀው አልነበረም፡፡ አጃቢዎቻቸውም ፀባያቸውን በደንብ ያወቁላቸው ይመስላል ከሩቅ ሆነው ከመጠባበቅ ውጪ ምንም የሚያደርጉት ነገር አልነበረም፡፡ ‹‹በሉ በርቱ፣ ደህና ሁኑ›› ብለው ከመለየታቸው በፊት ግን፣ ስለተነሳው የኤርትራ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹አንድ ቀን የማይቀር ነው፡፡ አንድ ሕዝብ አይደለንም? አንድ ነበርን አንድ መሆናችን ሩቅ አይደለም፡፡ የሚጠቅመንም እሱ ብቻ ነው፡፡ የእኔ ተስፋ እሱ ነው፤›› በማለት አብራሩ፡፡ ‹‹ሩቅ ሊሆን ይችላል እንጂ አንድ ቀን ይፈታል፡፡ አይቀርም፡፡ ማን ያውቃል ‘ኢስት አፍሪካ’ የሚባል አገርም እኮ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አብሮ ማደግ ነው የሚጠቅመን፡፡ የኢኮኖሚ ትብብሩ ብቻም ሳይሆን የፖለቲካ ‘ኢንተግሬሽኑ’ ሊፈጠር ይችላል፤›› ብለው ፈገግ ካሉ በኋላ ‘አይደለም?’ ካሉ በኋላ መልሰው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ 

‹‹ወደቦች አሉን ብለን መናገር አንችልም››

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኤርትራ ሕዝብ የሚከበረውን የቅዱስ ዮሐንስ በዓል ምክንያት አድርገው በሰጡት ሰፊው ቃለ ምልልሳቸው (ባለፈው ሳምንት ባቀረብነው ዘገባ) ያልነኩት ጉዳይና ያላወሩት ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ በማጠቃለያቸው ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠቀናቀቅ በኋላ የተፈጠረች አገር እንደሆነችና ኤርትራንም በቀጥታ ገዝታ የማታውቅ መሆኗን ባወሩበት አንደበታቸው፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ካልተባበረች የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ጨለማ እንደሆነ የሚያሳይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ኤርትራ ውስጥ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ወደብ፣ አውሮፕላን ማረፊያ ምንም እየፈየደ እንዳልሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ አምነዋል፡፡ ኢትዮጵያን በተመለከተ ደመነፍስ በሚመስል ስሜት ከሰጡት አስተያየት በተጨማሪ፣ ኤርትራ ውስጥ ባሉ እዚህ ግባ የማይባሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና በተለይ ወደቡን በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ‹‹ነገሩ ወዴት ነው?›› የሚያስብል ነው፡፡ ከአራቱ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ በአንፃራዊ በራስ መተማመን ጥያቄዎችን ሲያቀርብ የነበረው፣ ‹‹ኤርፖርቶቹና ወደቦቹ በአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ያላቸው ግንባር ቀደም ሚና አይዘነጋም፡፡ እናም በዚህ መሠረት እነዚህን መሠረተ ልማቶች ለማስፋፋት የተሠራ ሥራ አለ ወይ? እንዲሁም በእነዚህ መሠረተ ልማቶች የአካባቢውን ዓለም አቀፋዊ ተፈላጊነት ከፍ ለማድረግ የተያዘ ዕቅድስ አለ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ሌላውም ጋዜጠኛ፣ ‹‹ተጠቃልሎ እንዲመለስልን›› ያለውን ተጨማሪ ጥያቄ ያቀርብና ፕሬዚዳንቱ ምላሻቸውን ይቀጥላሉ፡፡ 

‹‹ወደቦች አሉን ብለን መናገር አንችልም፡፡ እንደዚያም ስለሆነ ከነፃነት ቀን ጀምሮ ያሉን ወደቦች ባፅዕና [ምፅዋ] አሰብ ተሠርተው ስለቆዩን ወይም መጠቀም ስለምንፈልግ ብቻ ሳይሆን፣ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጣቸውና ጠቀሜታቸው ምክንያት ሌላ መፍጠር ስለማይቻል ነው፡፡ እነዚህ የባህር ወደቦች ለመውጪያና ለመግቢያ ብቻ የምንጠቀምባቸው ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ አስፍተንም ካወራን ምናልባት ከአቅማችን በላይ ጉራ እንዳይመስል እንጂ፣ እነዚህ ሁለት የባህር ወደቦች ሳያድጉ የሚሰጡት (አገራዊው አገልግሎትን እርሳው) ይኼንን ጠባብ አድማስና ጥቅም ነው፡፡ የእነዚህ ወደቦችን አስፈላጊነት ከአካባቢያዊ [Regional] ጠቀሜታቸው ነው ማየት ያለብን፡፡ ወደድንም ጠላንም የምርጫ ጉዳይም አይደለም፡፡ የግድ መልማት አለባቸው፤›› አሉ፡፡ 

ፕሬዚዳንቱ በተለይ አሰብ ወደብን በተመለከተ ንግግራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ‹‹ስለ አሰብ ብዙ ነው የሚወራው፡፡ እኔ ይኼንን ፖለቲካዊ ነው የምለው፡፡ አሰብ መልማት ያለባት ወደብ ነች፡፡ ለምን እዚህ ላይ ብዙም መከራከር አልፈልግም፡፡ አሰብ ማደግ አለባት፤›› ሲሉ አነጋገራቸው ቀለል ያለ ይመስል ነበር፡፡ ድንገት ፊታቸውን ቋጥረውና ኮስተር ብለው አንድ አዲስ መልዕክት ማስተላለፍ የፈለጉ ይመስል እጆቻቸውን ግን ዘና አድርገው ወደ ግራና ቀኝ እያወራጩ፣ ‹‹ምናልባት ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ዝምድና፣ የድንበር ግጭት ጦርነት … አሰብ ከለማች የምትሰጠው አገልግሎት ለኢትዮጵያ አይደለም፡፡ የእውነት ወደብ ከሆነች ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ ጠቀሜታ አላት፡፡ ያንን አገልግሎት ለመስጠት መልማት የምትችለውን ያህል መልማት አለባት፡፡ አንዳንድ የፖለቲካና የፀጥታ ግምቶች አሉ፡፡ እንዲህ ሆነ እንዲህ ነው ተብሎ አጓጉል የምንይዝበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት ነው፡፡ እንዴት ነው የሚተገበረው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ አሁን ያለውን አሰብ ግን ወደብ ብለህ የምታወራለት አይደለም፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የነበረ ወደብ ለአሁኑ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን አይጠቅምም፡፡ ወደብ የለም፡፡ እናም እንኳን ለዓለም አቀፍ ለአገራዊ አገልግሎትም አሁን ወደብ አለን ብለህ የምታወራበት ደረጃ ላይ አይደለም፤›› አሉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ አሁን ያለው ወደብ ምንም ዓይነት ጠቀሜታ የለውም ብለው ዝም አላሉም፡፡ መንግሥታቸው የያዘው አዲስ ዕቅድ አለ፡፡ ‹‹ብንችለውም ባንችለውም፣ ጊዜ ብናገኝም ባናገኝም አንድ የተጠና ዕቅድ ሊኖረን ይገባል፡፡ አሁን መናገር እንችላለን፡፡ አንድ የውል ስምምነት አለን ብለን ማውራት እንችላለን፡፡ መቼ ነው የምንተገብረው? አብሮ የሚነሳ የውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት አለ፡፡ በእነሱ ልክ ትልቅ ኤርፖርት ያስፈልጋል፡፡ ወደብ ስለሆነ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ አስመራ ውስጥ ከምንሠራው እዚህ ላይ የምንሠራው ነገር አለ፤›› ብለዋል፡፡ 

በነገራችን ላይ ስለ አውሮፕላን ማረፊያ ቀደም ብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ የአስመራው አውሮፕላን ማረፊያ ምንም ጥቅም የለውም የሚል ምላሽ ሰጥተው፣ በምፅዋ ያለውን ማጠናከር እነደሚያስፈልግ ተናግረው ነበር፡፡ አሁንም በዚህ ላይ በወረቀት ላይ ያለውን ዕቅድ አስመልክተው ሲናገሩ፣ እነዚህን ወደቦች የመሠረተ ልማትና የመርከቦች ማመላለሻ ብቻ ሳይሆን፣ የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ እነዚህን ወደቦች ለመሥራት ያለብንን ውሱንነት እዚህ ላይ አላወራም፡፡ ነገር ግን በዕቅድ ደረጃ ቢያንስ በመካከለኛው ምሥራቅና በምሥራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ መቻል አለብን፡፡ በአገልግሎት ደረጃ ሜዳው ይኼው ፈረሱ ይኼው ብለን ነው የምንሠራው፤›› ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ወደቦቹ አሁን ያሉበትን ሁኔታና እየቀረበ ስላለው ቅሬታም ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሰብ መብራት የለውም፡፡ ብዙ ቅሬታ ነው የሚቀርበው፡፡ ስለዚህ በአጭር ጊዜ መሠራት አለበት ብለን አቅደናል፤›› ብለው የመንገድና የዓሣ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎችና ትላልቅ ኤርፖርቶችን የመሥራት የመንግሥታቸውን ዕቅድም ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሰብና ባፅዕ [ምፅዋ] በዚሁ መንገድ መልማት አለባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ ልትጠቀምበት ትችላለች፡፡ ጂቡቲ ልትጠቀምበት ትችላለች፡፡ ሜዳ ላይ መወዳደር እንችላለን፡፡ እነዚህ ፕሮግራሞች ግን ይዋል ይደር የሚባሉ አይደሉም፤›› ብለው ጉዳዩን በተመለከተ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

አሰብ የግመሎች መዋያ ሆኖ ይሆን?

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአንድ ወቅት የባህር በርን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹የአሰብ ወደብ ኢትዮጵያ ካልተጠቀመችበት የግመሎች መዋያ ከመሆን አያልፍም፤›› ብለው ነበር፡፡ ይህ ከብዙዎች ኢትዮጵያውያን የማይጠፋ ትዝታ ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ንግግር የወደብ አገልግሎት አማራጭ የማየት የገበያ ጉዳይ እንደሆነ ቀላል አድርገውት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት ከገባች ባሉት አሥራዎቹ ዓመታት የጂቡቲን ወደብ እየተጠቀመች ቢሆንም፣ ይኼኛው ወደብ እንደታሰበው አልጋ በአልጋ አልሆነም፡፡ ከአገልግሎቱ ጥራት ማነስ ጀምሮ በየቀኑ እየጨመረ የመጣው የአገልግሎት ክፍያ ለአገሪቱ ዓመታዊ ገቢ ከባድ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ቃለ ምልልስ መረዳት እንደሚቻለው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን አባባል ቃል በቃል መድገም ቢቀራቸው እንጂ፣ በተግባር ግን የአሰብም የምፅዋም ወደብ ምንም ጠቀሜታ እየሰጡ አይደሉም፡፡ ህልውናቸውም አደጋ ላይ ነው፡፡ 

ችግሩ ተጠቃሚ ማጣታቸውም ብቻም አይደለም፡፡ ኢሳያስ እንዳሉት፣ ወደብ ብሎ ለመጥራት የሚያስችል ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት አልተገነባላቸውም፡፡ በነገራችን ላይ እሳቸው በዚሁ ንግግራቸው አስመራን ዝቅ እያደረጉ ፊታቸውን ወደ አሰብ ያዞሩ ሲሆን፣ አገሪቱ የተለመቻቸውን መሠረተ ልማቶችና ፋብሪካዎች በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ምክንያት ከሥራ ውጪ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እናም በመፍትሔነት የጠቆሙት ታዳሽ የንፋስ ኃይል መጠቀምና ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛትን ጭምር ነው፡፡ 

ባለፈው ዓመት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሆኑ ጥቂት ወራት በኋላ ከአልጄዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ከኤርትራ ጋር አስመራ ድረስ በመሄድ መነጋገር እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር፡፡ ይኼው በወቅቱ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የተብጠለጠለው ንግግራቸው ግን ከአንድ ዓመት በኋላ ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ‹‹ኤርትራ በኢትዮጵያ ተገዝታ አታውቅም›› የሚለው አዲስ ፈሊጥ ከመናገራቸው ውጪ፣ እንደበፊቱ በኢትዮጵያ ላይ ያሰሙት ክስና ውርጅብኝ ቀንሷል፡፡ የለም ማለትም ይቻላል፡፡ በዚሁ ምትክ ቃል በቃል ዕርቅ እፈልጋለሁ ባይሉም፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብር የሚሰኝ ጥሪ እያደረጉ ነው፡፡ ኤርትራ ወደቦችዋን በማልማት ተወዳዳሪ አድርጋ ለኢትዮጵያ በገበያነት ለማቅረብ ዕቅድ ያላት ሲሆን፣ በምላሹ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት ትፈልጋለች፡፡ ይኼው የኢኮኖሚ ትብብር ከእርቅ በፊት ቀድሞ ይመጣል ማለት ዘበት ነው፡፡ ስለዚህ የኢሳያስ የአሁኑ ንግግር ‹‹አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ ዕርቅ መፍጠር እፈልጋለሁ›› ከማለት የሚተናነስ አይደለም፡፡ 

አሰብና ኢትዮጵያዊያን

ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ 22 ዓመቱ ሲሆን፣ የኤርትራም ዕድሜ እኩል ነው፡፡ በሕዝብ ላይ የተሠራ ጥናት ባይኖርም፣ በተለያዩ መንገዶች ሐሳባቸውን የመግለጽ ዕድል ያገኙ ኢትዮጵያውያን ልሂቃን ግን በዚሁ የኤርትራ ፍቺ ላይ ያላቸው ቅሬታ ወሰን የለውም፡፡ በራሳቸው አገላለጽ ከኢትዮጵያ ‹‹ቅኝ ግዛት›› ነፃ ለመውጣት ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ትግል ያካሄዱት ኤርትራውያን ከሕወሓት (በኋላም ከኢሕአዴግ) ጋር በመሆን ወታደራዊውን የደርግ መንግሥት ከሥልጣን ካባረሩ በኋላ ነፃነታቸውን ለማወጅ ብዙም ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ኢሕአዴግ የአራት ኪሎውን ቤተ መንግሥት ከመቆጣጠሩ ጥቂት ቀናት ቀደም ብለው ነበር የአስመራውን ቤተ መንግሥት በቁጥጥራቸው ሥር የዋለው፡፡ አዲሱ የኢሕአዴግ መንግሥት ያደረገው ነገር ቢኖር ያንን በተግባር (ዲፋክቶ) በሕዝባዊ ግንባር ኤርትራ (ሻዕቢያ) የወደቀው ግዛት ይፋዊ (ዲጁረ) ዕውቅና መስጠት ብቻ ነበር፡፡ 

የኤርትራ አዲሱ መንግሥት ለሰላሳ ዓመታት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ መስዋዕትነት ከፍሎ ኤርትራ የምትባል ነፃ ግዛት መፍጠር መቻሉ ብዙም አጠያያቂ አልነበረም፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እስካሁን ለተለያዩ የማንነት ጥያቄዎችና ጥርጣሬ የሚያስነሱ ውሳኔዎች ተደርገው ነበር የተወሰዱት፡፡ በአገር ውስጥም፣ በውጭም በኤርትራ መገንጠል የታመሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ 

ከኤርትራ መገንጠል በላይ ግን ብዙዎቹ ያነሱት ጥያቄ የፍቺውን ሕገወጥነት ነበር፡፡ ይህ አብዛኛዎቹን የ60ዎቹ የደርግ ተቃዋሚዎች ከሻዕቢያ የነጠለ አቋም በኤርትራ ላይ የነበረው ስስ አቋም ሲሆን፣ የአሰብን ወደብ በተመለከተ ደግሞ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን የሚጋሩት የኢትዮጵያ ንብረት ነው የሚል ነው፡፡ የኤርትራን መገንጠል የሚቀበሉ ሳይቀሩ አሰብ ባለቤትነቱ የኤርትራ ነው የሚለውን የማይቀበሉ አሉ፡፡ አሰብ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚም፣ የፖለቲካም እንዲሁም የደኅንነት ጉዳይ ስለሆነም አይደለም፡፡ አሁን ኤርትራ የሚባለው ግዛት አሰብን አያጠቃልልም ነበር የሚል ማከራከሪያ በማቅረብም ጭምር ነው፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት (ጆቤ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመመረቂያ ጽሑፋቸው በዚህ ላይ ሲሆን፣ ይህንን የሕግ መከራከሪያ የሚያቀርብ ሙግት አለው፡፡ በብዙዎችም ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የቅርቡን መድረክ ጨምሮ በኢትዮጵያ ብቅ የሚሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች በሙሉ ጉዳዩን የምርጫ አጀንዳ ማድረጋቸውም ከዚሁ ‹‹ሎጂክ›› የመነጨ ነው፡፡

በኢትዮ ኤርትራ መለያየት በውል እልባት ሳያገኙ በቂ ንግግርም ሳይደረግባቸው በይደር የቆዩ አራት አንኳር ጉዳዮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የዜግነት ጥያቄ፣ በኤርትራ ግዛትና በባህር ስለነበረው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ የሆነው ሀብት፣ የድንበርና የአሰብ ባለቤትነት ጥያቄ ናቸው፡፡ የድንበር ጉዳይ በሁለቱም አገሮች መካከል የነበረው በተግባር ‹‹ኮንፌዴሬሽን›› ሊሰኝ የሚችል ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ውጥንቅጡን ቢያወጣውም፣ በዚያው የ70 ሺሕ ሕይወት የበላ ጦርነት ይነሳል ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡ በዚህም የወደብ ጉዳይ ለሁለተኛ ጊዜ ዝም የተባለ ጥያቄ ነበር፡፡ በእርግጥም ከጦርነቱ በፊት ብቅ ጥልቅ ብሎ ከጦርነቱ በኋላ ሕወሓትን ለመሰንጠቅ ያበቃው ትልቁ አጀንዳ የኤርትራ ጉዳይ እንደነበር ይነገራል፡፡ በኤርትራ ላይ ጠንካራ አቋም ነበረን የሚሉ የሕወሓት ሰዎች ከፖለቲካ ውጪ መሆናቸውን ተከትሎ፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ሲያሟግት የነበረው ከኤርትራ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ጥቅም ድርሻ በሌሎች አጀንዳዎች እንዲዳፈን ተደርጓል፡፡ የሁለቱም አገሮች ግንኙነት በድንበሩ ጦርነትና ውዝግቡ ምክንያት ቢጨልምም፣ የኢትዮጵያውያን የአሰብ የባለቤትነት ጥያቄ ግን ጦርነቱ አጠቃላይ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ‹‹አጠቃላይ ጦርነት ሳይካሄድ አጠቃላይ መፍትሔ አይመጣም›› የሚል አቋም ያላቸው የፖለቲካ ተንታኞች፣ በሁለቱም አገሮች ድንበሩን መሠረት ያደረገው ውዝግብ ለመፍትሔው ይኼው የባህር ወደብ ካልታከለበት ‹‹አጠቃላይ መፍትሔ›› አይሆንም የሚል አቋም አላቸው፡፡

በቅርቡ ካታር ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማስታረቅ ስትንቀሳቀስ የነበረች ሲሆን፣ የአገሪቱ መሪ ወደ አስመራ በመሄድና ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከሁለቱም መሪዎች ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ የዕርቅ ጥረት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ግን በቂ መረጃ አልተገኘም፡፡ 

source reporter by Yemane Nagish.

Saturday, September 21, 2013

ከሰማይ ወረደ ለተባለው መስቀል የሳይንስ ምርመራ አይፈቀድም ተባለ


*በየእለቱ ከ15 ጊዜ በላይ ስለ ተከሰተው ተዓምር ገለፃ እናደርጋለን

በአቃቂ ቃሊቲ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ከሰማይ ወረደ የተባለው መስቀል ፓትርያርኩ በተገኙበት ለህዝብ እንዲታይ መግቢያ መንገድ እስኪሰራ ድረስ የተራዘመ ሲሆን፣ በመስቀሉ ላይ የሳይንስ ምርመራ እንደማይፈቀድ ተገለፀ፡፡ ከሶስት ሳምንት በፊት በፍንዳታ ድምፅና በብርሃናማ ቀስተደመና ከሰማይ ወረደ የተባለው መስቀል፣ በሚቀጥለው ሳምንት መስከረም 19 ቀን ለህዝብ ይታያል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ፓትርያርኩ የሚገኙበት ስነስርዓት ለማዘጋጀት ጊዜው እንደተራዘመ የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪዎች ተናግረዋል፡፡ መስቀሉ ለህዝብ የሚታየው ቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ በተገኙበት ስነስርዓት መሆን አለበት መባሉን አስተዳዳሪዎች ጠቅሰው፤ መንገዱ ጭቃ ስለሆነ ጠፈፍ ብሎ ለመኪና እስኪስተካከል ድረስ ቀኑ መራዘሙን ገልፀዋል፡፡ ቀኑ ገና እንዳልተወሰነና ለፓትሪያርኩ ጋር ውይይት እየተደረገበት ነው ያሉት የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪዎች፤ ስነስርዓቱን ህዳር 11 ቀን ለማካሄድ እንደታሰበ ጠቁመዋል፡፡

ከአዲስ አበባና በአቅራቢያዋ ከሚገኙ አካባቢዎች በየእለቱ ከ3ሺ በላይ ሰዎች ቦታውን እየጎበኙ መሆናቸውን የገለፁት የቤተክርስቲያኗ መጋቢ ሃዲስ ፍሰሃ፤ እኛም በየእለቱ ከ15 ጊዜ በላይ ስለ ተከሰተው ተዓምር ገለፃ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ መስቀሉ ባረፈበት ሳር ላይ እንዲሁም ወደ ቤተ መቅደሱ ከገባ በኋላ የተነሱ ፎቶዎችን የያዘ ካርድ ታትሞ ለምዕመናን በ10 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በፎቶግራፍ ላይ የሚታየው መስቀል በሰው የተሰራ የዕደ ጥበብ ውጤት እንደሚመስል በመጥቀስ ከሰማይ ወረደ መባሉን የሚጠረጥሩ መኖራቸውን በተመለከተ መጋቢ ሃዲስ ፍስሃ፣ እውነቱን የሚያውቀው ፈጣሪ ነው ብለዋል፡፡

በምድራችን የተሰራ የሚመስል መስቀል ከሰማይ ሊወርድ አይችልም የምንል ከሆነ፣ በምድራችን የምናረባው አይነት በግ ለአብርሃም ከሰማይ ወርዶለታል የሚለውን የመፅሃፍ ቅዱስ ቃል መጠራጠር ይሆናል ብለዋል መጋቢ ሃዲስ ፍስሃ፡፡ የመስቀሉን ስሪት እንዲሁም መስቀሉ አረፈበት የተባለውን ሳርና አፈር ለመመርመር ሃሳብ ተነስቶ እንደሆነ ተጠይቀው መጋቢ ሃዲስ ሲመልሱ፤ “ይህ መስቀል የቤተክርስቲያኒቱ የክብር መገለጫ ነው” በማለት ተቃውመዋል፡፡

እስካሁን በስፍራው የተፈፀመውን ተአምር ሰምተው የሚያደንቁ እንጂ በመስቀሉና በቦታው ላይ እንመራመራለን የሚሉ ምሁራን አላጋጠሙኝም ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ “እንዲህ ያለ ጥያቄ ያላቸውም ካሉም፣ የማይሞከር ነው” ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ የሃይማኖት ጉዳይ ስለሆነ ቦታውን እንፈትሻለን፣ የወረደውን መስቀል እንመረምራለን ለሚሉ የሳይንስ ባለሙያዎች ፈፅሞ አይፈቀድም ብለዋል፡፡ መስቀሉ ከሰማይ ከመውረዱ አስቀድሞ ራዕይ ታይቶኛል የሚል ሰው እስካሁን አላጋጠመን ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ ቤተክርስቲያኒቱን ያቋቋሙት አባት ግን፣ ቦታው የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ እንደሚሆን በራዕይ እንደታያቸው ተናግረው ነበር ብለዋል፡፡
source Addisadmas.

የአቶ ቡልቻ መጽሐፍ ለንባብ በቃ


“ህይወቴ እና ለኦሮሞ እና ለሌሎችም የኢትዮጵያ ህዝቦች ያለኝ ራዕይ” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀው የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ መጽሐፍ በአሜሪካ ታትሞ በውጭ አገራት ለገበያ ቀረበ፡፡ መፅሃፉ አቶ ቡልቻ ከተወለዱባት የቦጂ በርመጂ ወረዳ ጀምሮ ከኦፌዴን ሊቀመንበርነት እስከለቀቁበት ጊዜ ድረስ ያሳለፉትን የትምህርት፣ የስራ እና የፖለቲካ ህይወት ይዳስሳል፡፡ ዘመናዊ ትምህርት ለመማር ያደረጓቸውን እልህ አስጨራሽ ሙከራዎች፣ ከአሜሪካን በኢኮኖሚክስ ተመርቀው ከመጡ በኋላ በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ በምክትል ሚኒስትር ማዕረግ ባገለገሉባቸው አመታት ያጋጠሟቸውን ውጣ ውረዶች፣ በአለም ባንክ የኢትዮጵያ ተወካይ በመሆን እንዲሁም በዩኤንዲፒ ስለሠሯቸው ስራዎች በመጽሐፋቸው ተርከዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብን ጥያቄ አንስተው በፖለቲካው መስክ ስላደረጉት ተሳትፎ የፃፉት አቶ ቡልቻ፤ አዋሽ ባንክን ለመመስረት ያደረጉትን አስተዋጽኦና በባንኩ ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባትም በስፋት ዳስሰዋል፡፡ መጽሐፉ 180 ገፆች ያሉትና በ20 ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን በኦሮሚኛ እና በአማርኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለአገር ውስጥ ገበያ እንደሚቀርብ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ 


source Addisadama.

Friday, September 20, 2013

ተቃዋሚዎች በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርጉ ተከለከሉ

መስከረም ፱(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መስከረም 12 እና መስከረም 19 ሰማያዊ እና አንድነት ፓርቲዎች በተከታታይ የጠሩዋቸው ሰልፎች በመስቀል አደባባይ እንደማይካሄዱ የአዲስ አበባ መስተዳድር ህዝባዊ ስብሰባ ማስታወቂያ ክፍል አስታውቋል።
ጽህፈት ቤቱ ይህን ያስታወቀው ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት ካደረገ በሁዋላ ነው።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ” ህዝባዊ አገልግሎት የሚሰጥ ቦታ ለዜጎች ሁሉ መብት የሆነውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በህግ ለተቋቋመና ህዝባዊ ሀላፊነትን ለወሰደ የፖለቲካ ፓርቲ መከልከልና እስከዛሬም ድረስ ከገዢ ፓርቲ ጀምሮ ሌሎች አካላት በመስቀል አደባባይ በተደጋጋሚ ሰልፍ ያደረጉበት መሆኑ እየታወቀ እንደዚህ አይነት ሚዛናዊነት የጎደለው አሰራር መቀበልና በቸልታ ማለፍ ፓርቲያችን ከተመሰረተበት አላማ ጋር የሚጋጭ፣ ከሞራል ፣ከህግና ከፖለቲካ አንጻርም ተቀባይነት የሌለው” አሰራር ነው ብሎአል።
ሰማያዊ ፓርቲ የፊታችን እሁድ በመስቀል አደባባይ የሚያደርገውን የተቃውሞ ሰልፍ እንደማይለውጥ አስታውቋል። ፓርቲው ነሐሴ 26 የጠራው ሰልፍ በጸጥታ ሀይሎች እንዲደናቀፍ መደረጉ ይታወሳል።
አንድነት ፓርቲም በተመሳሳይ መልኩ መስከረም 19 ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንደማይችል እንደተገለጸለት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ ተናግረዋል
የጸጥታ ሀይሎች በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ሊስትሮዎችን፣ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችንና እና በሰልፉ ላይ ይገኛሉ ብሎ የሚጠራጠሩዋቸውን ሰዎች ዛሬም ሲይዙ ውለዋል።
የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬም ድረስ በአገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳይ ስብሰባ እያደረጉ ነው።