‹‹በመቆጠቢያ ደብተራችን ትክክል የሆነው ስማችን በኮምፒውተር ስህተት ነው ተባለ›› ተመዝጋቢዎች
‹‹መቆጠቢያ ደብተር ላይ ብቻ ተመዝግቦ መገኘት ትክክል ነኝ አያስብልም›› የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በአዲስ አበባ ከተማ ከሁለት ዓመት በላይ የኖሩና ነባር ነዋሪዎች፣ የእነሱ ስህተት ባልሆነ ምክንያት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኮንዶሚኒየም ቤት ምዝገባ ውጪ ሊያደርጋቸው መሆኑን ተናገሩ፡፡
መመዝገብና መቆጠቢያ ደብተር ይዞ መገኘት የመመዝገቢያ መሥፈርትን ማሟላት እንዳልሆነ የሚገልጸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የሚያቀርቡት መረጃ ትክክል መሆኑ ከተረጋገጠና መረጃ ሲመዘገብ የተሳሳተ ከሆነ እንደሚስተካከል አስታውቋል፡፡
በተለይ የ20/80 አዲስ ተመዝጋቢዎች በየሚኖሩበት ክፍለ ከተማና ወረዳ በአግባቡ የምዝገባ መሥፈርቶችን ካሟሉ በኋላ የቁጠባ ደብተር መውሰዳቸውን ለሪፖርተር ገልጸው፣ አንዳንዶቹ የተወሰነ ጊዜ ከቆጠቡ በኋላና አንዳንዶቹ ደግሞ ገና ምንም ሳይቆጥቡ፣ በኮምፒውተር ላይ የተመዘገበው ስማችሁና በመቆጠቢያ ደብተሩ ላይ ያለው ስም ሙሉ በሙሉ አይመሳሰልም፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ከራሳቸው፣ ከአባታቸው ወይም ከአያታቸው ስም ላይ አንድና ሁለት ፊደላት መጉደሉ እየተነገራቸው ‹‹መቆጠብ አትችሉም›› መባላቸውን አሳውቀዋል፡፡
ተመዝጋቢዎቹ በተለይ የተወሰነ ጊዜ ሲቆጥቡ የከረሙት ‹‹ይኼንን ያህል ጊዜ ከቆጠብኩ በኋላ ለምን እንደዚህ ያለ ጥያቄ ታነሳላችሁ? መጀመሪያውኑ ለምን አልነገራችሁንም?›› የሚል ጥያቄ ሲያነሱ፣ ምንም ምላሽ የሚሰጣቸው ማጣታቸውን የሚገልጹት ተመዝጋቢዎቹ፣ መጀመሪያ ወደተመዘገቡበት ቀበሌ በመሄድ ከባህር መዝገብ ጀምሮ በሙሉ የሞሏቸውን ቅጾች ሲመለከቱ ሁሉም ትክክል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ትክክለኛ ማስረጃ በመያዝ ወደ ባንክ ባለሙያዎቹ ሲቀርቡ ‹‹ችግሩ የአንድና የሁለት ሰው ሳይሆን የበርካቶች ስለሆነ፣ ጉዳዩ ለባንኩ ፕሬዚዳንት ተነግሯቸው ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ በመሆኑ ተረጋግታችሁ ጠብቁ፤›› የሚል ምላሽ እንደተነገራቸው አክለዋል፡፡
መንግሥት የመጀመሪያውን የኮንዶሚኒየም ምዝገባ ባካሄደበት ወቀት አጥተውት ሲቆጩ ከርመው ያገኙትን የምዝገባ ዕድል፣ በእነሱ ስህተት ሳይሆን በባንኩ ሠራተኞች ስህተት እንዳያጡት ሥጋት እንዳደረባቸው የሚናገሩት ተመዝጋቢዎቹ፣ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን ተከታትሎ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ተመዝጋቢዎቹ የሚያነሱትን ሥጋትና ተሳስቷል ስለሚሉት የምዝገባ ሁኔታ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሙኒዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ እንደገለጹት፣ መመዝገብና መቆጠቢያ ደብተር ይዞ መገኘት የመመዝገቢያ መሥፈርትን ማሟላት አይደለም፡፡ ቢያንስ በመንግሥት እንዲቆጠብ የተነገረውን የመጨረሻውን የቁጠባ ሒሳብ መቆጠብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ተመዝጋቢዎች ለመመዝገብ የሚያበቋቸውን መሥፈርቶች አሟልተው ስህተት የተፈጠረባቸው በባንኩ ከሆነ ተጣርቶ እንደሚስተካከል ተናግረዋል፡፡
ለምዝገባ ፕሮግራሞቹ በተሰጠው ቀነ ገደብ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተመዝጋቢዎች መመዝገባቸውን የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመመዝገባቸው አንፃር ከ99 በመቶ በላይ በአግባቡ የተመዘገቡ መሆናቸውንና የተለያዩ ችግሮች አጋጥመዋል ቢባልም እጅግ በጣም ትንሽ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ለባንኩ የተለያዩ ችግሮች መቅረባቸውን ያልካዱት ሥራ አስኪያጁ፣ ተመዝጋቢዎቹ ከተመዘገቡ በኋላ ስማቸውን በፍርድ ቤት አስቀይረው በመምጣት እንዲስተካከልላቸው የሚጠይቁ አካሄዳቸው ሕጋዊ ቢሆንም፣ በባንኩ ላይ ጫና ማሳደሩ እንዳልቀረ ተናግረዋል፡፡ መቆጠቢያ ደብተር የሚጥሉና አካውንት ቁጥራቸውን የማያውቁ እንዳሉ፣ በአስተዳደሩ በኩል ሁሉንም ቅጾች በአግባቡ ከሞሉ በኋላ በመቆጠቢያ ደብተራቸው ላይ የማይመሳሰል ስም አስመዝግበው የሚቀርቡ መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ሌላው የተመዝጋቢዎች ስህተት በውክልና ያስመዘገቡትን ሰው ስም ይተውና በመቆጠቢያ ደብተሩ ላይ የራሳቸውን ስም አስመዝግበው የሚቀርቡ እንዳሉ፣ የራሳቸው ስም ትክክል ከሆነ የአባት ወይም አያት ስም ሙሉ በሙሉ ስህተት ሆኖ የተመዘገቡ እንደሚያጋጥሙና በመጨረሻ ተመዝጋቢዎቹ የተናገሩት ከአባታቸው ወይም ከአያታቸው ስም ውስጥ ሁለት ወይም አንድ ፊደል ጎድሎ መመዝገቡ፣ በባንክ ሥራ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መሆኑን አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል፡፡
ከ1,393 በላይ ተመዝጋቢዎች ስም ተጣርቶ ማስተካከያ እንደተደረገ የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ በቀጣይም ሌሎች አቤቱታ የቀረበባቸውን ለማስተካከል በማዕከል ደረጃ እየታየ መሆኑንና ትክክለኛ ሆኖ ከተገኘ የሚስተካከል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ተመዝግበውና መቆጠቢያ ደብተር ብቻ ይዘው ሳይቆጥቡ ዝም ብለው የከረሙ ካሉ፣ መሥፈርቱን አሟልተው ከተመዘገቡትና በወቅቱ የተወሰነውን መቆጠብ ከጀመሩት ጋር እኩል ስለማይታይ እንዳልተመዘገቡ እንደሚቆጠርም አቶ ኤፍሬም አክለዋል፡፡
No comments:
Post a Comment