Friday, January 24, 2014

አብርሃ ደስታ አዲግራት ላይ በሕወሓት ካድሬዎች ተደበደበ


የአረና ለትግራይ ፓርቲ በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሕዝብን የማነቃቃስ ስብሰባዎችን በመጥራትና በማወያየት ላይ የሚገኝ ሲሆን በሚያደረጋቸው ሰላማዊ እንስቃሴዎች በሕወሓት ካድሬዎች ፈተና እየገጠመው ይገኛል። ዛሬ ከወደ አዲግራት የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው በፌስቡክ፣ በትዊትር እና በተለያዩ ድረገጾች ላይ “አብርሃ ደስታ ከመቀሌ” እያለ የሚዘግበው መምህር ድብደባ ተፈጽሞበታል።
Abrha Destaአረና ፓርቲ ነገ እሁድ ጁላይ 26 ቀን 2014 በአዲግራት ከተማ የጠራውን ሕዝባዊ ስብሰባ ለሕዝብ ለማስተዋወቅ በከተማዋ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በሕወሓት ካድሬዎች በተደራጁ በተባሉ ወጣቶች “ሕዝብ መቀስቅሳችሁን አቁሙ” በሚል ጥቃት የተፈጸመባቸው አሰገደ ገብረ ሥላሴ፣ አምዶም ገብረስላሴና አብርሃ ደስታ ላይ ሲሆን በአብርሃ የደረሰው ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት ባያደርስም አቶ አሰገደ እና አንዶም ወደ ሃኪም ቤት ተወስደው ህክምና እንደተደረገላቸው ለዘ-ሐበሻ የደረሱት መረጃዎች አመልክተዋል።
በተያያዘ ዜና በተጨማሪ የአዲግራቱን ስብሰባ ለማስተጓጎል ሕወሓት ወታደሮችን በማሰማራት የአረና ሰዎችን በማሳሰር ላይ እንደሚገኝ የደረሰን ዜና አመልክቶ ለማሰር የቀረበው ምክንያትም “ሕዝብ በስብሰባ እንዲሳተፍ ቀስቅሳችኋል” በሚል ነው።
ከዚህ ቀደም የአረና አባላት በተንቤይን ሕዝባዊ ስብሰባ ጠርተው የነበረ ስሂን እዚያም እስር እና እንግልት እንደደረሰባቸው ዘ-ሐበሻ በወቅቱ መዘገቧ አይዘነጋም።
(ከዚህ ቀደም የአረናን ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳይሳተፉ የተከለከሉ የሽሬ ነዋሪዎች - ፎቶ ከአብርሃ ደስታ) - ፎቶ ፋይል
(ከዚህ ቀደም የአረናን ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳይሳተፉ የተከለከሉ የሽሬ ነዋሪዎች – ፎቶ ከአብርሃ ደስታ) – ፎቶ ፋይል

ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው ግንባታ ማንኛውንም ዓይነት ሕግ የጣሰ አይደለም በማለት መንግሥት የግብፅን አቤቱታ ውድቅ አድርጓል፡፡


አል ሞኒተር የተባለ የግብፅ ሚዲያ የተለያዩ የአገሪቱ ባለሥልጣናትን በመጥቀስ፣ ግብፅ በኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን ተቃውሞ ዓለም አቀፍ ማድረግ እንደምትፈልግ ዘግቧል፡፡ 
ግብፅ የህዳሴውን ግድብ በመቃወም ለተመድ አቤት እላለሁ ማለቷን ኢትዮጵያ አጣጣለች‹‹የህዳሴው ግድብ አሁን ባለው የግንባታ ደረጃ ተገንብቶ ዕውን የሚሆን ከሆነ በግብፅ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩን ወደሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት መውሰድ እንደሚገባ፣ ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው፤›› ያሉት የአገሪቱ የመስኖና ውኃ ሀብት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ካህሊድ ዋሲፍ ናቸው፡፡ 
‹‹ግብፅ የህዳሴው ግድብ ግንባታን ፈፅሞ አትፈቅድም፡፡ ይህንን ለማሳካትም ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የውጭ ዕርዳታ ለግድቡ እንዳታገኝ ግፊት እናደርጋለን፤›› ሲሉ በይፋ ተናግረዋል፡፡ 
ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የኢትዮጵያን ግድብ በማውገዝ ከግብፅ ጐን እንዲቆም አስፈላጊው ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ በዓለም አቀፍ ሕግ የተከበረና የተረጋገጠ መብት አላት፡፡ ነገር ግን ይህ የግብፅ መብት በኢትዮጵያ እየተጣሰ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ ሕጋዊ መብት አላት የሚሉት ቃል አቀባዩ፣ ማናቸውም የተፋሰሱ አገሮች ተፋሰሱን በመጠቀም ወደ ልማት መግባት ሲፈልጉ በቅድሚያ ግብፅን የማማከርና ይሁንታ የማግኘት ግዴታ አለባቸው ሲሉ የአገራቸውን አቋም አስታውቀዋል፡፡ 
ኢትዮጵያ ይህንን ግዴታ በመጣስ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ መጀመሯ በራሱ ሕግን የጣሰ መሆኑን፣ ነገር ግን የግብፅ መንግሥት ጉዳዩን በወዳጅነት በመያዝ ሲወያይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ምንም ዓይነት ጉዳት በግብፅ ላይ እንደማያደርስ ኢትዮጵያ ለማረጋገጥ እንቢተኛ በመሆኗ ግብፅ ከውይይቱ ራሷን እንዳገለለች አስረድተዋል፡፡ 
የግብፅ የቀድሞ የመስኖና የውኃ ሀብት ሚኒስትር ሙሐሙድ ናስር አል ዲን አላም በበኩላቸው፣ ግብፅ ከዚህ በኋላ በህዳሴው ግድብ ላይ ሌላ አማራጭ የላትም ብለዋል፡፡ የቀረውና በፍጥነት ተግባራዊ መሆን የሚገባው አማራጭ ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ፣ በዋናነትም ይፋዊ ቅሬታና ተቃውሞ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማቅረብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 
‹‹ማንኛውም የዓባይ ተፋሰስ ተጋሪ አጋር በወንዙ ላይ ፕሮጀክት ከመጀመሩ በፊት የግብፅን ይሁንታ ማግኘት አለባት የሚለው ስምምነት ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያለው ነው፤›› በማለት የሚከራከሩት የቀድሞው ሚኒስትር ኢትዮጵያ ይህንን ስምምነት በመጣስ ለጀመረችው ግንባታ በተባበሩት መንግሥትት ድርጀት ልትጠየቅ ይገባታል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል አሁን ያለውን አለመግባባት በተመለከተም ዓለም አቀፍ እውነት አፈላላጊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ማጥናት ይኖርበታል በማለት ተከራክረዋል፡፡ 
የግብፅ ባለሥልጣናት እያንፀባረቁት ስላለው አዲስ አቋም የተጠየቁት የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅ አህመድ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ውል አይመለከታትም፣ ምክንያቱም አልፈረመችም፤›› ሲሉ የግብፅ ባለሥልጣናት መግለጫን አጣጥለዋል፡፡ የቅኝ ግዛት ውሉ የተፈረመው በግብፅና በእንግሊዝ መካከል መሆኑን ያስታወሱት አቶ ፈቅ፣ እንግሊዝ ቅኝ የገዛቻቸውን ኬንያ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ በመወከል ስምምነቱን ፈርማለች፡፡ ይህ ግን ኢትዮጵያን ፈፅሞ አይመለከትም ብለዋል፡፡ 
የግብፅ የቀድሞው የመስኖና የውኃ ሀብት ሚኒስትር በተደጋጋሚ ይህንን መሳይ ነገር ያነሳሉ በማለት ያስታወሱት አቶ ፈቅ፣ ‹‹ሰውዬው ከሳይንስ ውጭ ነው የሚናገሩት፣ ከእሳቸው የሚጠበቅ አይደለም፤›› ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡ 
‹‹ኢትዮጵያ የጀመረችው የህዳሴው ግድብ ግንባታ የትኛውንም ዓለም አቀፍ ሕግ የጣሰ አይደለም፡፡ ወደፈለጉበት ቢሄዱ የሚመጣ ነገር የለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ ጉዳዩን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መምራት ሊያተርፍ የሚችለው በሁለቱ አገሮች ያለውን የትብብር መንፈስ ማጥፋት ነው ሲሉ የግብፅ ባለሥልጣናትን የሰሞኑን ዘመቻ አውግዘዋል፡፡ 

ለኢሳት መረጃ አቀብሏል የተባለው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ::!


ለኢሳት መረጃ አቀብሏል የተባለው 
ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

በአሸናፊ ደምሴ

ከአሜሪካን፣ ከኔዘርላንድና ከእንግሊዝ በመላው ዓለም ለሚሰራጨው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ (ኢሳት) በኢትዮጵያ ተቋማት፣ ድርጅቶችና ዜጎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል መረጃን አቀብሏል ሲል የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተበት በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የጋምቤላ ኤርፖርቶች የጥበቃ ዋና መምሪያ ሠራተኛ የሆነው አቶ ሚኪያስ ንጋቱ በፈፀመው የስለላ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በ4 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ከትናንት በስቲያ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎበታል።
እንደዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር ከሆነ ተከሳሹ፣ ቀኑና ወሩ በውል ባልታወቀ ነገር ግን ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ በጋምቤላ ክልል በሚገኘው የኤርፖርቶች ድርጅት የጥበቃ ዋና መምሪያ ሠራተኛ ሆኖ በሚሰራበት ወቅት ስርጭቱን ከአሜሪካ፣ ከኔዘርላንድ እና ከእንግሊዝ በማድረግ የአሸባሪው የግንቦት 7 ልሳን እንደሆነ ለሚነገርለት ኢሳት በተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ውስጥ ከሚሰራው ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም ጋር ግንኙነት በመፍጠር መረጃዎችን ሲያስተላለፍ ቆይቷል ይላል። 

        ለዚህም ውለታው 4460 ብር በመቀበል፤ ለስራ ተመድቦ በሚያገለግልበት የጋምቤላ ክልል ውስጥ በተለያየ ዘርፍ ኢንቨስተሮች ሆነው ግድያ ስለተፈፀመባቸው የውጪ ዜጎችና 19 በሚደርሱ የክልሉ የግብርና ኮሌጅ ተማሪዎች ላይ ተፈፅሟል ስለተባለው ግድያ በተመለከተ በፎቶ የታገዘ መረጃን ከማቀበሉም ባሻገር፤ በክልሉ መንግስት ስር የተካሄደውን ሹምሽር በተመለከተም በምስልና በፅሁፍ አስደግፎ በኢ-ሜይል እና በስልክ መረጃዎችን በማስተላለፉ በፈፀመው የስለላ ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ በዝርዝር ያትታል። 
በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ጉዳዩ በመታየት ላይ የነበረው ተከሳሹ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበበትን ከኢ-ሜይል ሳጥኑ የተሰበሰቡ 10ገፅ የፅሁፍ ማስረጃዎችና ከስልኩ የተወሰዱ ሶስት ፎቶግራፎችን አስመልክቶ በአግባቡ መከላከል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ያለው ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል መረጃን ለአሸባሪ ቡድን አባላት ከማስተላለፉም በተጨማሪ የሙያውን ስነምግባር በሚፃረር መልኩ በፅሁፍና በፎቶ የታገዘ መረጃዎችን ሲያስተላልፍ በመያዙ እንደቅጣት ማክበጃ ይወሰድልኝ የሚል ሀሳብ አቅርቧል።

          የተከሳሹ ተከላካይ ጠበቃ በበኩላቸው ግለሰቡ ከዚህ በፊት የፈፀመው ምንም አይነት ወንጀል አለመኖሩንና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን፤ እንዲሁም በአካባቢው የወጣት ማዕከላት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበረውና የመልካም ባህሪይ ባለቤትነቱን በመጥቀስ ቅጣቱ እንዲቀልለት ጠይቀዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ፍርድ ቤቱም፤ ተከሳሽን ጥፋተኛ ነው ባለው መሰረተ በ4 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ከትናንት በስቲያ ጥር 12 ቀን 2006 ዓ.ም የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፏል።

Thursday, January 23, 2014

ልጁን አስገድዶ ለሦስት ዓመታት የደፈረው አባት በፅኑ እስራት ተቀጣ


 
-ነዋሪነቱ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 10/11 ውስጥ ነዋሪ የሆነው ሙሉጌታ ውብሸት የተባለው ግለሰብ ልጁን አስገድዶ በመድፈርና ለሦስት ዓመታት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲፈጽምባት መቆየቱ፣ በሰውና በሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ በ18 ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት፡፡
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሰባተኛ ወንጀል ችሎት  ባስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ እንደገለጸው፣ ግለሰቡ የራሱን ልጅ ከሦስት ዓመታት በፊት አስገድዶ ክብረ ንፅህናዋን ገስሷል፡፡ በወቅቱ ልጅቷ የ12 ዓመት ታዳጊ ነበረች፡፡‹‹አንች እያለሽ ሌላ ሚስት አያስፈልገኝም በማለት የራሱን ልጅ እንደ ሚስት ቆጥሮ ለሦስት ዓመታት ወንጀሉን  ፈጽሞባታል፡፡ ሕፃኗ ከሦስት ዓመታት በኋላ ለወንድሟ እኔ ምን እስከምሆን ነው የምትጠብቀኝ? አባቴ ቀለበት አድርጎ እስከሚያገባኝ ነው? በማለት በጻፈችው ደብዳቤ  የወንጀለኛው አባቷ ጉድ መጋለጡን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያመለክታል፡፡በቤት ውስጥ ወንጀለኛው አባቷ  የሚያኖራት እንደ ሚስትና ቤት ሠራተኛ በመሆኑ፣ ‹‹እኔ ልጅህ አይደለሁም›› ብላ እስከ መጠየቅ  መድረሷን ዓቃቤ ሕግ በምስክርነት አቅርቧት ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቷን የውሳኔ መዝገቡ ይገልጻል፡፡
በሥነ ልቦናዋ ላይ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰባት ለፍርድ ቤቱ በሰጠችው የምስክርነት ቃል መግለጻው የውሳኔ መዝገቡ፣ አስገድዶ መድፈርና በዘመዳሞች መካከል ግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም በወንጀል ሥር ስለሚመደብ አፈጻጸሙ ከባድ ተብሎ እንዲወሰንለት ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ቅጣት ማክበጃ ሐሳብ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ፣ በከባድ ወንጀል ወስኖታል፡፡
በመሆኑም ወንጀለኛውን አባት በአስገድዶ መድፈር ወንጀል በ15 ዓመታት ከሦስት ወራት ፅኑ እስራት፣ በዘመዳሞች መካከል በተፈጸመ ግብረ ሥጋ ግንኙነት በሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወራት ፅኑ እስራት፣ በድምሩ በ18 ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡
ወንጀለኛው ከቤተዘመድ መብቶቹና ከሕዝባዊ መብቶቹ ለሦስት ዓመታት መሻሩንም  ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ሄዶ ሰርግ ለማድረግ እየተዘጋጀ ያለውን ኢትዮጵያዊ የገደለው አሜሪካዊ ተያዘ


tulu

(ዘ-ሐበሻ) በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ሄዶ ሰርግ ለማድረግ እቅድ ነበረው ኢትዮጵያዊው ዮሴፍ ቱሉ እንደ ቴክሳሱ ፋክስ 4 ቴሌቭዥን ዘገባ። የ30 ዓመቱ ዮሴፍ በጋዝ ስቴሽን ሥራ ተግቶ የሚሰራው ሃገር ቤት ሄዶ የሚመሰርተውን ትዳር በማሰብ፤ በወግ ማዕረግ መዳርን ነበር። በተለምዶ 7/11 በሚባለው ጋዝ ስቴሽን ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ዮሴፍ ረዥም ህልም ያለው ዜጋ ነበር።
guy killed ethiopian men

እንደ ወዳጆቹ ገለጻ ከሆነ ዮሴፍ መልካም፤ ተግባቢና ረዥም ህልም የነበረው ሰው ነበር። ሆኖም ግን በሚሰራበት ጋዝ ስቴችሽን በጥይት ተመትቶ ተገድሎ ሕይወቱ አለፈ። ሃገር ቤት ሄዶ ወዳጅ ዘመዱን ሊያኮራበት የተዘጋጀው ትዳርም ህልም ሆኖ ቀረ። ይህ ነገር ብዙ ወዳጆቹን እና ዘመዶቹን የበለጠ ሃዘኑን እንዳባሰባቸው የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ጠቁመዋል።
guy with gun

የ30 ዓመቱን ኢትዮጵያዊ እዚሁ ሰሜን አሜሪዓ.ምካ የቴክሳስ ግዛት ውስጥ እንደገደለ በፖሊስ ተጠርጥሮ የተያዘው ከልተን ጃን የተባለው ወጣት የ18 ዓመቱ ሲሆን፤ በጋዝ ስቴችኑ ውስጥ የተገጠመው ካሜካ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያውን ካሸር ትናንት ማክሰኞ ጃንዋሪ 21 ቀን 2014 ሊገድል ሲገባ በቁመቱ ልክ የሆነ መሳሪያ ታጥቆ ነው። ወጣቱ ተጠርጣሪ ገዳይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቢውልም፤ ጠመንጃውን ይዞ የፈለገውን ገንዘብ ቢወስድም በቅርቡ ወደ ሃገሩ ገብቶ ሰርግ ለማድረግ ገንዘብ እያጠራቀመ የሚገኘውን ዮሴፍ ቱሉን ከመግደል አልተመለሰም።
የጋዝ ስቴሽኑ ባለቤቶች የኢትዮጵያዊውን አስከሬን ወደ ሃገር ቤት የሚመለስ ከሆነ ወጭውን ለመቻል ፈቃደኛ ሲሆኑ ገዳዩ የ1 ሚሊዮን ቦንድ ተጠይቋል።
ዘ-ሐበሻ ፎቶዎቹን ያገኘችው ከፋክስ 4 ቲቪ መሆኑን ትገልጻለች።

Wednesday, January 22, 2014

አንቶኖቭ 28 አውሮፕላን በለገዳዲ አካባቢ ተከሰከሰ


ንብረትነቱ የዩክሬን የሆነ አንቶኖቭ 28 የመንገደኞች አውሮፕላን ከኡጋንዳ ኢንቴቤ ተነስቶ ወደ ሰንዓ የመን በመብረር ላይ እንዳለ ባለፈው ሰኞ አዲስ አበባ አቅራቢያ ለገዳዲ አካባቢ መከስከሱን ሪፖርተር ጋዜጣ ከአዲስ አበባ ዘገበ። ጋዜጣው ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አገኘሁት ባለው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች ሰኞ ማለዳ ከባለሥልጣኑ ጋር ባደረጉት የሬዲዮ ግንኙነት ከኢንቴቤ ተነስተው በኢትዮጵያ በኩል ወደ የመን ለመብረር ፈቃድ ጠይቀው ነበር፡፡ ባለሥልጣኑም የበረራ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል፡፡
ሪፖርተር በዘገባው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኤር ናቪጌሽን ክፍል ለአብራሪዎቹ የሚበሩበትን ከፍታ እንደሰጣቸውና አውሮፕላኑ የኢትዮጵያን አየር ክልል አቋርጦ በማለፍ ላይ ሳለ አዲስ አበባ አካባቢ ሲደርስ የሞተር ብልሽት ሲያጋጥመው ይህንኑ ለአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ መቆጣጠሪያ ማማ አሳውቆ ‹‹ኢመርጀንሲ ላንዲንግ›› እንደሚያደርግ (በድንገተኝነት እንደሚያርፍ) ሪፖርት አድርጐ፣ ከጠዋቱ 3፡35 ሰዓት ላይ ለማረፍ ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በማምራት ላይ ሳለ ለገዳዲ አካባቢ መከስከሱን ዘግቧል።
“አደጋው እንደደረሰ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ፈልጐ ማዳን ቡድን ወደ ሥፍራው ተንቀሳቅሶ የአውሮፕላኑ አብራሪዎችን ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ሕክምና እንዲያገኙ ማድረጉን” የዘገበው ሪፖርተር በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፋሪዎች እንዳልነበሩና፣ በአደጋው አብራሪዎቹ የተጐዱ ቢሆንም፣ ሕይወቱ ያለፈ ሰው እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል ሲል ጋዜጣው ዘግቧል።
ሪፖርተር ዘገባውን ሲያጠናቅቅም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአውሮፕላን አደጋ መከላከልና ምርመራ ክፍል ባለሙያዎች የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ ምርመራ ጀምረዋል፡፡ ባለሙያዎቹ አውሮፕላኑ ወደ ወደቀበት ሥፍራ በማምራት መረጃ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ፤ ሩሲያ ሰራሽ የሆኑ አንቶኖቭ አውሮፕላኖች ከተመረቱ ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ በመሆኑ በየጊዜው እክል እየገጠማቸው በተለያዩ አገሮች በመከስከስ ይታወቃሉ፤ እነዚህ ዕድሜ ጠገብ አውሮፕላኖች ዋጋቸው ርካሽ በመሆኑ በአፍሪካ አገሮች በብዛት ይገኛሉ፤ ያረጁ በመሆኑና ተገቢ የሆነ ጥገና ስለማይደረግላቸው በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በተደጋጋሚ አደጋ እንደሚያደርሱ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ያስረዳሉ ይላል።
zehbesha

Monday, January 20, 2014

በደምና በአጥንት መስዋዕትነት ተከብሮ የቆየ የሃገራችንን ዳር ድንበር ለባዕድ አሳልፈን አንሰጥም!


ብርሃኔ አሰበ አለሁድረስ
ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የታደለች ፣መልካም የአየር ፀባይ ያላት፣ህዝቦቿ የራሳችን አኩሪባህልና ወግያለን፣የራሳችን መልካም መልክዓ ምድራዊና አሰፋፈር ያለን በጋራ ተሳስረን አብረን የኖርንባትና የምንኖርባት በየትኛውም ዘመን ሉአላዊነቷ ያልተደፈረ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች ሀገር ናት። በተለያየ ወቅት የተፈጥሮ ሃብቷን ለመቀራመትና ሉአላዊነቷን ለመዳፈር የሞከሩ ሃገራት ሁሉ፣በውድ ልጆቿ የተባበረ ክንድ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተው ኢትዮጵያን ዳግም እንዳይመኟት የተባረሩበትና የኢትዮጵያን አይበገሬነት በአፍሪካም ሆነ በአለም መድረክ ያስመሰከረች፣ አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን ጠብቃ በማቆየት በአለም ታሪካዊ ስፍራ ያላት፣ በቀደምት ውድ ልጆቿ የደም መስዋዕትነት ሀገራችን ሉአላዊነቷ ሳይደፈር ለብዙ ሺ አመታት ቆይታለች።
Ethiopian government to hand over land to Sudan
በአሁኑ ስዓት ኢህአዴግ/ህወሃት ለግልና ለግዚያዊ የፖለቲካ ጥቅም ሲል የኢትዮጵያን አንድነት በማደብዘዝ እንሆ በእኛ ዘመን ለዘመናትተደፍሮ የማያውቀውን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመጋፋት የኢትዮጵያ የሉአላዊነት ባለቤት የሆኑት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሳይወያዩበትና ሳያፀድቁት በጓሮ በር የኢትዮጵያን መሬት ለባዕድ ሃገር/ሱዳን ቆርሶ ለመስጠት ሽርጉዱን ተያይዞታል። ከአመታት በፊት በምዕራቡ የሃገራችን ክፍል /ድንበር በኩል/ በመሸራረፍ ለም የሰሊጥ ምርት የሚሰጥ መሬት ለሱዳን ሲሰጥ ዝም በማለታችን  እንሆ ዛሬ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጋፋ ፣ የኢትዮጵያን ቅርጽ የሚያጠፋ ረጅም ርዝመት ያለው ለም መሬት ለሱዳን ለመስጠት ዝግጅቱ መጠናቀቁን ሰማን።
ዛሬ ላይ ሆነን ይህንን መሰሪ ተግባር አንድነታችንን አጠናክረን መግታት ካልቻልን ነገ ደግሞ በሌላኛው የኢትዮጵያ ጫፍ በኩል የኢትዮጵያ መሬትተቆርሶ ለሌሎች አጎራባች ሀገራት ላይሰጥ ምን ዋስትና አለን?
አያቶቻችንና አባቶቻችን ደማቸውን ገብረው ፣አጥንታቸውን ከስክሰው ያስረከቡንን የሀገር ሉአላዊነት ሳይሸራረፍ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የእኛ የአሁኑ ትውልድ የታሪክ  ግዴታ ነው። ይህን የታሪክ ግዴታችንን ሳንወጣ/ችል በማለት/ በመሰሪው የህወሃት/ ኢህአዴግ አመራር የሃገራችን ሉአላዊነት እየተሸራረፈ ለባዕድ ሀገራት ሲሰጥ በምን አገባኝ ስሜትዝም ብለን ብንመለከት በ– ዚ–ያ ዘመን ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀ የውጭ ጠላትጋር የሀገሬን ሉአላዊነት አላስደፍርም በማለት በዱላ፣ በጦርና ጋሻ፣ ዘመናዊ ባልሆነ  የጦር መሳሪያ ፣በባዶ እግራቸው በመዝመት ደማቸውን አፍስሰው ፣ አጥንታቸውን ከስክሰው የኢትዮጵያን ሉአላዊነትሳያስደፍሩ ያስረከቡን የአባቶቻችን አጥንት እሾህ ሆኖ ይወጋናል።
“የኢትዮጵያ ድንበሮች በኢትዮጵያውያን ደም የራሱ፣ በኢትዮጵያውያን አጥንት የተገነቡ ሲሆኑ ድንበሮቻችንን ለማስከበር ከሁልቆ መሣፍርት፣ ተራ ዜጐች አንስቶ እስከ አንድ ታላቅ ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ አንገታቸው ሰጥተዋል፡፡ በዶጋሊ፣ በጉራዓ፣ በጉንዲት፣ በመተማ፣ በአድዋ፣ በወልወል በቅርብ ጊዜያት ደግሞ በሶማሊያና በኤርትራ የፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም የሌላውን ግዛት በመቋመጥ ሳይሆን ድንበሬን አላስነካም በሚል ነበር፡፡ እንደዛሬው መኪና ወይንም ባቡር ባልኖረበት የቀደምት ኢትዮጵያውያን ከመሃል አገር ተነስተው በእግር ለወራት በረሃውን አቋርጠው፣ ተራራውን ወጥተው፣ ንዳዱን ተቋቁመው፣ ወባውን ደፍረው ከሙስታሂል እስከ ጋምቤላ፣ ከራስ ካሣር እስከ ሞያሌ ዘልቀው ድንበሩን ሰፍረው ኢትዮጵያን ለዚህ ትውልድ አስረክበው ሄዱ፡፡ ይህ ተረካቢ ትውልድ የተረከበውን መሬት ሳይቀነስ ለቀጣዩ ትውልድ ያስተላልፋል ይሆን—-” ከያዕቆብ ኃይለማሪያም/20 July 2008/።
ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን አደራ ጠብቆ የሀገሩን ሉአላዊነት ሳይሸራረፍ በማስከበር ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ ያለበት መሆኑን ለአፍታ መዘንጋት የለበትም ። ህወሃት/ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ህዝብ እውቅና ውጭ በሚስጥር የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመጋፋት ዳር ድንበራችንን ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገውን የውል ስምምነት የፖለቲካ ልዩነት፣ ብሄር፣ ሃይማኖት፣አመለካከት ሳይለያየን  የፖለቲካፓርቲዎች ፣ ድርጅቶች፣ ሲቪክስማህበራትና ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በጋራ ተንቀሳቅሰን አሁኑኑ ማስቆም ካልቻልን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከማስደፈርም አልፎ እስከ ወዳኛው ትውልድ ድረስ ብጥብጥና ትርምስን የሚያወርስ ስውር ደባ ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉአላዊነት በመጋፋት ለም መሬታችንን ለሱዳን አሳልፎ የሚሰጠውን ስምምነት አገር ወዳድ የሆንን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በጋራ በመንቀሳቀስበደምና በአጥንት መስዋዕትነት ተከብሮ የቆየ የሃገራችንን ዳር ድንበር ለባዕድ አሳልፈን አንሰጥም!  በሚል መርህ ተግባብተን ይህንን እኩይ ተግባር ለማስቆም ግዜ ሳንወስድ በያለንበት ፈጥነን መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል።
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለባዕድ ሀገር አሳልፎ የመስጠት ታሪክ አልወረስንም!