Thursday, January 23, 2014

ልጁን አስገድዶ ለሦስት ዓመታት የደፈረው አባት በፅኑ እስራት ተቀጣ


 
-ነዋሪነቱ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 10/11 ውስጥ ነዋሪ የሆነው ሙሉጌታ ውብሸት የተባለው ግለሰብ ልጁን አስገድዶ በመድፈርና ለሦስት ዓመታት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲፈጽምባት መቆየቱ፣ በሰውና በሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ በ18 ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት፡፡
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሰባተኛ ወንጀል ችሎት  ባስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ እንደገለጸው፣ ግለሰቡ የራሱን ልጅ ከሦስት ዓመታት በፊት አስገድዶ ክብረ ንፅህናዋን ገስሷል፡፡ በወቅቱ ልጅቷ የ12 ዓመት ታዳጊ ነበረች፡፡‹‹አንች እያለሽ ሌላ ሚስት አያስፈልገኝም በማለት የራሱን ልጅ እንደ ሚስት ቆጥሮ ለሦስት ዓመታት ወንጀሉን  ፈጽሞባታል፡፡ ሕፃኗ ከሦስት ዓመታት በኋላ ለወንድሟ እኔ ምን እስከምሆን ነው የምትጠብቀኝ? አባቴ ቀለበት አድርጎ እስከሚያገባኝ ነው? በማለት በጻፈችው ደብዳቤ  የወንጀለኛው አባቷ ጉድ መጋለጡን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያመለክታል፡፡በቤት ውስጥ ወንጀለኛው አባቷ  የሚያኖራት እንደ ሚስትና ቤት ሠራተኛ በመሆኑ፣ ‹‹እኔ ልጅህ አይደለሁም›› ብላ እስከ መጠየቅ  መድረሷን ዓቃቤ ሕግ በምስክርነት አቅርቧት ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቷን የውሳኔ መዝገቡ ይገልጻል፡፡
በሥነ ልቦናዋ ላይ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰባት ለፍርድ ቤቱ በሰጠችው የምስክርነት ቃል መግለጻው የውሳኔ መዝገቡ፣ አስገድዶ መድፈርና በዘመዳሞች መካከል ግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም በወንጀል ሥር ስለሚመደብ አፈጻጸሙ ከባድ ተብሎ እንዲወሰንለት ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ቅጣት ማክበጃ ሐሳብ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ፣ በከባድ ወንጀል ወስኖታል፡፡
በመሆኑም ወንጀለኛውን አባት በአስገድዶ መድፈር ወንጀል በ15 ዓመታት ከሦስት ወራት ፅኑ እስራት፣ በዘመዳሞች መካከል በተፈጸመ ግብረ ሥጋ ግንኙነት በሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወራት ፅኑ እስራት፣ በድምሩ በ18 ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡
ወንጀለኛው ከቤተዘመድ መብቶቹና ከሕዝባዊ መብቶቹ ለሦስት ዓመታት መሻሩንም  ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አስታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment