Friday, February 7, 2014

የሃይማኖት ተቋማትን በሚመለከተው አዋጅ ላይ የሚመክር ስብሰባ በአዋሳ ተጠራ


ጥር ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተዘጋጀው  የእምነት አኩልነትና ተቻችሎ የመኖር የሃይማኖት እሴትን ሊያጎለብት ይችላል የተባለ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሚመለከታቸውን ወገኖች ሃሳብ ለማሰባሰብ  ከነገ ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ምንጮቻችን ጠቆሙ።
በዚሁ ስብሰባ ላይ በዋንኛነት የሚሳተፉት በአገሪቱ አሉ የሚባሉት 945 ያህል የእምነት ተቋማት መሆናቸውም ታውቆአል፡፡ መንግስት የሙስሊም ማህበረሰብ የመብት ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ ለውይይት በተደጋጋሚ ሲያገኛቸው የነበሩትን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮምቴ አባላት በአክራሪነትና በሽብርተኝነት ወንጅሎ እስር ቤት ከከተተ ወዲህ “መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፣አንዱ በሌላው ስራ ጣልቃ አይገባም” የሚለውን ሕገመንግስታዊ ድንጋጌ በመዘንጋት በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ሙሉ በሙሉ ማስገባቱን ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡
መንግስት ረቂቅ ህጉ  በሃይማኖት ስም  ይደረጋሉ የሚላቸውን የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ይስችለኛል ብሎ ያምናል። የሃማኖት ተቁዋማቱ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ከመጋበዝ ባለፈ የረቂቅ አዋጁ ኮፒ አስቀድሞ እንዲደርሳቸው እንዳልተደረገ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት የሕግ ሰውነትን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ የተደነገገው በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አቋቁሞ፣  ሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ሕጉን ተከትሎ በሚወጣ ልዩ ደንብ እንደሚመዘገቡ መደንገጉ ይታወቃል፡፡ በደርግ ዘመንም ሃይማኖትን የተመለከተ ድንጋጌ ወጥቶ አያውቅም።
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ያወጣው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 27 ላይ ማንኛውም ሰው የማሰብ፣የህሊናና የሃይማኖት ነጻነት እንዳለው በግልጽ ደነግጋል፡፡ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም መቀበል ፣ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣የመከተል፣የመተግበር፣የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡ከዚህ በተጨማሪም የሃማኖት ተከታዮች ሃማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችላቸውን የሃማኖት ትምህርትና የአስተዳዳር ተቋማት ማቋቋም እንደሚችሉና ወላጆች ህጋዊ ሞግዚቶች በእምነታቸው መሰረት የሃይማኖታዊና የመልካም ስነምግባር ትምህርት በመስጠት ልጆቻቸው የማሳደግ መብት እንዳላቸው ደንግጓል።

የታፈነ ስቃይ ! የጋዜጠኛ ሰሎሞን ሙሉ ታፈሰ አስዛኝ ህይወት ከኢትዮጵያ « ለወገን ደራሽ ወገን ነው ! »



ጋዜጠኛ ሰሎሞን ሙሉ ታፈሰ የነፃው ፕሬስ ካፈራቸው ምርጥና ድንቅ ብእረኞች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይነሳል። የሰሎሞን ልዩ ተሰጥኦ በማንኛውም ጉዳይ ላይ የሚፅፍ መሆኑ ነው። በጭራሽ የማይፈራ ደፋር ጋዜጠኛና ደራሲ ነው። ለእውነት የቆመ፣ ብዙ መስዋእትነት ለአገሩና ለነፃው ፕሬስ የከፈለ ሰው ነው። ዛሬ..ዛሬ ሃብት ጥግ ከደረሱ በርካታ አርቲስቶች ጀርባ ሰሎሞን አለ። ለምሳሌ መጥቀስ ቢያስፈልግ አንዱ ሰራዊት ፍቅሬ ነው። 

ሰሎሞን ሕይወት ፊቷን አዙራበት ለአምስት አመት ገደማ ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን ጀርባ (ጎዳና) ይተኛ ነበር። ራበኝ፣ ጠማኝ፣ ታረዝኩ…ብሎ ማንንም አይጠይቅም። ሶስትና አራት ቀን ምግብ በአፉ ሳይዞር የሚያሳልፍበት ቀናት አሉ። ባለፈው አመት ሰሎሞን ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ በዚሁ ማህበራዊ ገፅ መጣጥፍ አቅርቤ ነበር። በለንደን የሚኖሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሰሎሞንን ሲረዱት ቆይተዋል። ሊመሰገኑ ይገባል። አሁን ግን ሰሎሞን በተደራራቢ ችግርና ስቃይ ውስጥ ወድቋል። የኪንታሮት በሽታ እያሰቃየው፣ በዛ ላይ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ተቸግሯል። ስቃይና ረሃብ በውስጡ ይዞ የመከራ ቀንና ሌት እየገፋ ነው። ለታፈነው ስቃይ የሚደርስ ወገን ይጥፋ?...ቢያንስ ህክምና የሚያገኝበት?...ጋዜጠኞችና ሌሎች ወገኖች ምን ትላላችሁ?... 
( የሰሎሞን ፎቶ, ባለፈው አመት የላከልኝ ደራሲ ፋሲል ተካልኝ ነው..) 

Thursday, February 6, 2014

ስልክ ጠላፊው ሰላይ “ጋዜጠኛ”


በማህሌት ነጋ (ሲያትል)

ከሁሉ የእኔን ቀልብ የሳበው የቀጂው ማንነት ነበር። ለማጣራት ያደረኩት ጥረት ብዙም ግዜ አልፈጀብኝም። አበበ ገላው በዚሁ “ሊክድ” በተባለው ቅጂ “እኔ ከሞትኩም እንደ ሃየሎም መጠጥ ቤት በከንቱ መሞት አልፈልግም። መሞት የምፈልገው ለአላማ ነው ይላል።” በዚህ ግዜ አንድ ሳቅ ይሰማል። የኢያጎ ሳቅ። ዳዊት ከበደ ስለመሆኑ ብዙም አልተጠራጠርኩም።

Dawit Kebede Awramba Times editor in restaurant
ሰሞኑን አንድ ሚስኪን ጋዜጠኛ ነኝ ባይ ከአንድ የከሰረ ፖለቲካኛ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርግ በቪዲዮ ለቆ ስለነበር ለሶስት ደቂቃ ያህል ተምልክቼ ጭንቅላቴን በሃዘን እየነቀነኩ ዘጋሁት። እኔን ጨምሮ በርካቶች ድረ ገጾችን የምናስሰው መረጃ ፍለጋ እንጂ የከሰሩ ግለሰቦችን ደረቅ ወግ ለማዳመጥ እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው። በአንድ ወቅት ያዙን ልቀቁን ይሉ የነበሩት ሁለት ግለሰቦች የዛሬን አያድርገውና ኢትዮጵያዊያን እንደ ማንዴላ የነጻነት ታጋዮች አድርገው ያከብሯቸው ስለነበር ድምጻቸው የጎላ በራስ መተማመናቸው ከውስጣቸው ሞልቶ በአፋቸው ይገነፍል ነበር። ዛሬ ግን ድምጽ አጥሯቸው ቀልብ እርቋቸው ሲንሾካሾኩ ያየ ሁሉ እንደ እኔ ከንፈር መጦ የሁለቱን ምስኪኖች ወግ በግዜ ዘግቶ ወደ ስራው እንደሚመለስ ብዙም አያጠራጥርም።
“ምስኪኖች እነማን ናቸው?” እንደማትሉኝ እርግጠኛ ነኝ:: የአውራምባው ዳዊት ከበደና የኢዴአፓው ልደቱ አያሌው ጉዳይ መቼም አንገት ያስደፋል። ሁለቱም ጠላታቸው ወያኔ እንዳልሆነ እነርሱ እንደሌሎች “ጽንፈኛ” እንዳልሆኑ ሌሎችን ከሰው እራሰቸውን ከፍ ለማድረግ ሲጥሩ ላስተዋለ ጠበል የሚወስዳቸው ያጡ በሽተኞች መሆናቸውን ድርጊታቸው ይመሰክራል። ዲያስፖራውና የግል ጋዜጦች በተለይ የጋራ ጠላቶቻቸው ይመስላሉ። እንደው ለመንደርደሪያ እንጂ የዚህ ጹሁፍ አላማ የሁለቱ ምስኪኖች ወግ ስላልሆነ ወደ ቁም ነገሩ ልመለስ::
ሾተላዩ ሰላይ ዳዊትን ለመጀምሪያ ግዜ በአካል ያገኘሁት ወደ ሲያትል የዛሬ ሶስት አመት በመጣ ግዜ ነበር። አስተባባሪዎች መርጠን፣ ገንዘብ አዋጥተን፣ ድግስ ደግሰን፣ ሽልማት አዘጋጅተን ነበር የጀግና አቀባበል ያደረግንለት። ወቅቱ የብርድ እና የበረዶ ግዜ ስለነበር እኔም እንደሌሎች ይህንን “ጀግና ጋዜጠኛ” ለመቀበል ብዙ መስዋእትነት ነበር የከፈልኩት። በተለይ የኢትዮሜድያው አብርሃ በላይና ሼክስፒር ፈይሳ እንግዳውን ተቀብለው ቤታቸው ከማሳደር አልፈው ለዝግጅቱ ስኬት ያበርከቱት አስተዋስኦ ቀላል አልነበረም። ሰላዩ ጋዜጠኛ ግን አብርሃ በላይን አራክሶ፣ ሼክስፒር ፈይሳን ደግሞ ስምህን አጠፋለሁ ብሎ በማስፈራራት ከንቱነቱን ብቻ ሳይሆን የኢያጎ ባህሪውን ፍንትው አድርጎ አጋልጧል።
ይሁንና ኢያጎን (ዳዊትን) በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ አትመኑት ማለታቸው አልቀረም። እውነት ለመናገር ዳዊት እነ ውብሸት ታዬ እና ርእዮት አለሙን በማሳሰሩ ድርጊት እጁ አለበት የሚል ሹክሹታ ከወደ አገር ቤት ሲናፈስ ማናችንም የዚህ ጎጠኛ “ጋዜጠኛ” ወዳጆች በቁም ነገር አልወሰድነውም። መቼም ሰው በምልካም ስራው ሲታወቅና ሲወደስ ምቀኛ እንደማይጠፋ ለማንም ግልጽ ነው። ስለዚህም ነበር ዳዊትን አትመኑት የሚለውን የአገርቤት መልእክት ማንም ትኩረት ያልሰጠው። አሁንም ስለዚያ ድርጊቱ ተጨባጭ መረጃ ስለሌለኝ ድርጊቱን ፈጽሟል አልፈጸም ለማለት ባልችልም ከጀርባ የመውጋት ጋህሪውን ለማስተዋል በመቻሌ አያደርግም ብዬ መከራከር አልችልም።
ዳዊት ተራ የሆኑ ጉዳዮችን ሁሉ የመቅዳት ባህሪ አለው። ሰው ሲጎርስ፣ ሲጠጣ፣ ሲናገር፣ ሲቀልድ (ከተቻለውም ሽንት ቤት ሲጸዳዳ) ቪዲዮና ፎቶ ማንሳት ድምጽ መቅዳት ይወዳል። በስውር የሚቀዳበት ሪኮርደርም ይዞ እንደሚዞር ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። ብዙ ሰው ግን የዳዊትን ድርጊት ከጋዜጠኝነት ስራው ጋር ስለሚያያይዘው ተንኮሉን አይጠረጥርም። ነገሩ ያልጠረጠረ ተመነጠረ መሆኑን ነው።
Dawit Kebede's brother besrat amareአሁን እንደምንሰማው ነዋሪነቱ በአሪዞና ፊኒክስ የሆነው የዳዊት ከበደ ታላቅ ወንድም ብስራት ከበደ የሚታወቀው በተመሳሳይ የመቅዳት ባህሪው ነው። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ብስራት ምንም ጭንብል ሳያጠልቅ አይኑን በጨው አጥቦ ስለሚንቀሳቀስ የህወሃት ታማኝ ካድሬና ሰላይ መሆኑ በስፋት ይነገራል። እርሱም
እንደ ወንድሙ የትርፍ ግዜ ስራው ስለሆነ እንኳን ፖለቲከኞችን እና ታጋዮችን በስካይፕም ይሁን በስልክ የሚያናግራቸው ሴቶች ምስልና ድምጽ ሳይቀር እንደሚቀዳ በጉራ ይናገራል፣ ለቅርብ ጓደኞቾም ያሳያል። እዚህ ላይ ግለሰቡን እምታውቁ ሴቶች ጠንቀቅ በሉ ማለት ሳያስፈልግ አይቀርም።
የኢያጎ ጩቤ ወደ ዲሲ ደዋውዬ እንዳጣራሁት ዳዊት ወያኔ አባረረኝ ብሎ ወደ አሜሪካ ፈርጥጦ ሲመጣ የኢሳት ሰዎችም የተቀበሉት በመልካም አይን ነበር። በተለይ ከሲሳይ አጌና፣ ከመሳይ መኮንን እንዲሁም አበበ ገላው ጋር መልካም ወዳጅነት ለማፍራት፣ አብሮ ለመጠጣትና ለመብላት ግዜ አልወሰደበትም። ለጋዜጠኝነት ስነምግባር እጨነቃለሁ የሚለው ይሄው ግለሰብ ወያኔ ጠለፍኩ ያለውን የዶ/ር ብርሃኑን የስካይፕ ውይይት በድህረ ገጹ ላይ በማውጣት የራሱ አጸያፊ ድርጊት መነጋገሪያ ሆኖ እንደ ነበር ይታውሳል። ዳዊት ከበደ በኢሳት፣ ግንቦት ሰባትን እና ዶ/ር ብርሃኑ ላይ በተከታታይ የሰራውን አሳፋሪ ግን ደግሞ የከሸፈ ፕሮፓጋንዳ ሁሉም ስለሚያውቀቅ መድገም አያስፈልግም። ከሁሉ የገረመኝ ሰሞኑን ዳዊት ኢያጓዊ የስለላ ስራውን ለማራቀቅ መሞከሩ ነው። ሞኝ እራሱን ያታልላል ነው ነገሩ።
ልክ እንደ ኢያጎ ዳዊትም ጩቤን በጀርባው ደብቆ ያመኑትን እና ያቀረቡት ሁሉ ላይ ከማሴር ቦዝኖ እንደማያውቅ ሙሉ በሙሉ ግልጽ ሆኗል። በቅርቡ ለመረዳት እንደቻልኩት በርግጥም የዛሬው ኢያጎ ዳዊት ከበደ መስዋእትነት ከፍሏል፣ መልካምነቱንም በስራው አስመስክሯል በማለት እንደ ትግል አጋር ያዩት ከነበሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አንዱ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ይገኝበታል። ለዚህም ምክንያት አንዱ ኢያጎ ከእስር ወጥቶ በሲፒጄ ሳይቀር ለፕሬስ ነጻነት ላበረከተው አስተዋጽኦ በታላላቅ የአለማችን ጋዜጠኞች ፊት በኒውዮርክ ቀርቦ ሽልማት ሁሉ መውሰዱ ነው። ይቺም ስኬት ለዳዊት ጥሩ ጭንብል ሆና ቆይታለች።
በወቅቱም ወያኔ ይገለኛል ያስረኛል እንጂ አገር ለቅቄ አልሰደድም ብሎ በየመድረኩ ሲደነፋ በእውነትም የጎልያድ ጠላት ቅዱስ ዳዊትን ነበር የመሰለን። ያሁሉ ተረት ሆኖ ወያኔ ሊያስረኝ ነው ብሎ አገር ጥሎ ሲፈረጥጥ አሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ክብርና ፍቅር አልነፈጉትም ነበር። የእኛው ኢያጎ ግን ያን ሁሉ ክብር ትቶ በእኩይ ተግባሩ የነጻንት ትግሉን የሚጎዳና የህወሃት አንባገነኖችን በሚጠቅም እኩይ ተግባራት ላይ ለመሰማራት ግዜ አልፈጀበትም።
በቅርቡ ወያኔዎች ክፉውን ጎልያድ መለስ ዜናዊን በአለም መሪዎች ፊት አዋርዶና አስደንግጦ የመጨረሻና ወሳኝ ስንብት ላደረገለት ጋዜጠኛና አክቲቪስት አበበ ገላውን ለማስጠላት እንዲሁም ኢትዮጵያዊውን ለመከፋፈል በህገወጥ መንገድ የተቀዳ የግል የስልክ ንግግር አዛብተው፣ ቆርጠውና ቀጥለው በኢንተርኔት ላይ ለቀቁ። ይሄም የተለቀቀው በዳዊት ድርገጽ ሳይሆን በቀንዲል የወያኔ የፈስቡክ አቀንቃኝ ዳንኤል በርሄ አማካኝነት በሆድ አደሩ ሹምባሽ ከበደ ካሳ አቀናባሪነት ነው። ደግነቱ የተባለው ሁሉ ምንም ሚስጥር የሌለው ስለነበር እንዳሰቡት ሳይሳካላቸው እነርሱንው መሳለቂያ አድርጓቸዋል።
ከሁሉ የእኔን ቀልብ የሳበው የቀጂው ማንነት ነበር። ለማጣራት ያደረኩት ጥረት ብዙም ግዜ አልፈጀብኝም። አበበ ገላው በዚሁ “ሊክድ” በተባለው ቅጂ “እኔ ከሞትኩም እንደ ሃየሎም መጠጥ ቤት በከንቱ መሞት አልፈልግም። መሞት የምፈልገው ለአላማ ነው ይላል።” በዚህ ግዜ አንድ ሳቅ ይሰማል። የኢያጎ ሳቅ። ዳዊት ከበደ ስለመሆኑ ብዙም አልተጠራጠርኩም። ሳቁ በጣም የተለየች ውስጧ ሸፍጥና ተንኮል ያዘለች ነች። ዳዊትን ለሚያውቁት ወዳጆቼ አስተያየት ሳልሰጥ ይቺን አምልጣ ስትቆረጥ የወጣች ወሳኝ መረጃ አድምጣችሁ የማን ሳቅ እንደሆነ ንገሩኝ ብዬ በኢሜይል አያይዤ ላኩላቸው። አራቱም መልሳቸው አንድ ነው፣ የኛው ኢያጎ ዳዊት ከበደ።
ዳዊት በጣም አሳዘነኝ። ብዙ ተስፋ የጣልንበት “ጋዜጠኛና የነጻነት ታጋይ” እንዴት ከክብር ወንበሩ ወርዶ ቆሻሻ ትቦ ውስጥ ይወድቃል? ለነገሩ ከልብ ያልሆነ ነገር ሁሉ እራሱን መግለጡ አይቀርምና ዳዊትም ከልቡ ኢያጎ እንጂ ሌላ አልነበረም። በጣም ተምታቶበታል። እኛ ግን የበለጠ ነቃን። እነዳዊት ከበደ ግን ግራ እንደተጋቡ እንደሰካራም በየትቦው ውስጥ እየወደቁ ይገኛሉ። ተመስገን ደሳለኝ ከጥቂት ወራት በፊት “የፖለቲካ ስር ቁማርተኞች” በሚል የጻፈው አንጀት አርስ ጹሁፍ ትዝ አለኝ። ተመስጌን የጠየቀው መሰረታዊ ጥያቄ በእኔም አእምሮ ውስጥ ያቃጭላል። ለመሆኑ ወደ አገር ቤት ከአሜሪካ ልክ እንደ አመጣጡ ፈርጥጦ ያስመለሰው ጉዳይ የፕሬስ ነጻነት መሻሻሉና “የጽንፈኞችን” ፖለቲካ በመጸየፉ ነው ወይንስ ደግሞ ኢሳትን የማፍረስ እና በጸረ-ወያኔ ትግሉ ግንባር ቀደም ሚና ይሚጫወቱ ኢትዮጵያዊያንን ለማምታታትና ለመሰለል ስላላመቸው? መልሱ ግልጽ ነው።
ወያኔዊ ኢያጎነት በቀላሉ እንደማይለቅ ከዳዊት መማር ይቻላል። ዲሲ አካባቢ በቅርብ የታዘቡት እንደነገሩኝ ዳዊት ሁለት ነገሮች አብዝቶ ይወዳል፣ መጠጥና ሴት ማባረር። ከአገር ቤት ፈርጥጦ ዲያስፖራ የተቀላቀለው ዳዊት ሲነቃበትና ይሄ የሱስ ጥማት ሲያስቸገረው ፈርጥጦ እነአቦይ ስብሃት እና ሽመልስ ከማል ጋር ብርጭቆ ማጋጨት መጀመሩን ሰማን። ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች አብረው ግር ይላሉ አሉ ፈረንጆች። አበው ሲተርቱ ግም ለግም አብረህ አዝግም እንዳሉት መሆኑ ነው። መልካም እድል፣ መልካም ቅምቀማ ብለናል ከወደ ሲያትል!!

በሦስት የመንግስት ተቋማት ላይ አንድነት ፓርቲ ክስ መሰረተ


ሕገ-መንግሥቱ የሚፈቅድልኝን ሰላማዊ ሰልፍ እንዳላካሂድ ከልክለውኛል፤ አባላቶቼን ያለአግባብ በማንገላታት አስረውብኛል፤ ቅስቀሳ እንዳላካሂድ አግደውኛልና ድምፅ ማጉያዎቼን ቀምተውኛል ሲል አንድነት ለዴሞክራሲ ለፍትህና ፓርቲ (አንድነት) በሶስት የመንግስት ተቋማት ላይ ክስ መሰረተ። ፓርቲው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ ፍትሃ ብሔር ችሎት ላይ ክስ የመሰረተባቸው ተቋማት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መሆናቸውን በክስ መዝገቡ ተገልጿል።
ፓርቲው የዘወትር ፖለቲካዊ ስራዎቹን እንዳላያካሂድ መስተጓጉል ተፈጥሮብኛል በማለቱ ክሱ መዘጋጀቱን ለሰንደቅ ያስረዱት የሕግ ባለሙያው አቶ ተማም አባቡልጉ፤ በክስ ዝርዝሩ ውስጥ ፓርቲው በመስቀል አደባባይ የጠራው ሰልፍ እንዳይካሄድ ከመደረጉም በተጨማሪ የቅስቀሳ እገዳ፣ የአባላት መታሰርና የቁሳቁስ መነጠቅ ሁሉ ስለማጋጠሙ በክሱ ውስጥ በዝርዝር ተካቷል ብለዋል።
በከተማዋ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ከፈቃድ ሰጪ አካላት ፈቃድ መገኘት አለበት ቢባል እንኳን ተቋማት የተከተሉት አካሄድ አግባብነት የሌለውና ከሕግም ውጪ በመሆኑ ይህን ለመጠየቅ ክስ መስርተናል ብለዋል። የመንግሥት አካላቱን የሰልፍ እገዳ ተከትሎ አንድነት ፓርቲ ዘጠኝ የሚደርሱ አማራጭ የሰልፍ ቦታዎች ቢያቀርብም አንዱንም ሳይቀበሉ በራሳቸው ምርጫ ጃንሜዳ ላይ ሰልፍ እንዲካሄድ መፍቀዳቸው በሕጉ ላይ ከሰፈረውና ማንኛውም ዓይነት ሰላማዊ ሰልፍ ከጦር ካምፕ በ50 ሜትር ርቀት ላይ መካሄድ አለበት ከሚለው መመሪያ ጋር የማይጣጣም ነው ብለዋል።
ይህም በመሆኑ አንድነት ፓርቲ የመንግስት ተቋማት በጣምራ በመሆን ሕዝብን ለመቀስቀስ የሚደረገውን ጥረት ስልታዊ በሆነ መንገድ አስተጓጉለውብኛል ይላል።
በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተመሰረተባቸውን ክስ አስመልክተው በችሎት በመገኘት የሚሰጡትን መልስ ለማድመጥ ለየካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ምንጭ ዜና ሰንደቅ

ጐፋ ገበያ ማዕከል ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ 19 መደብሮች ወደሙ


በገበያ ማዕከሉ የእሳት ቃጠሎ ሲደርስ ለዘጠነኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል


goffa
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ቄራ ጐፋ የገበያ ማዕከል ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ 19 መደብሮች ሙሉ በሙሉ ወደሙ፡፡
ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7፡15 ሰዓት ላይ የእሳት ቃጠሎው እንደተከሰተ የገለጹት፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ ናቸው፡፡ የእሳቱ መነሻ ምክንያትና በንብረት ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡
በቄራ ጐፋ የገበያ ማዕከል ውስጥ ቁጥራቸው 500 የሚደርሱ ነዋሪዎችና ነጋዴዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ንጋቱ፣ ከቤቶቹና ከሱቆቹ አሠራር አኳያ ሲታይ 19 መደብሮችና መኖሪያ ቤቶች ብቻ ተቃጥለው ሌሎቹ መትረፋቸው አስገራሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቤቶቹ ከተሠሩበት ግብዓትና መቀራረብ አኳያ መሆኑን አክለዋል፡፡
ከ53 ሺሕ ሊትር በላይ ውኃ በመርጨትና ሌሎች የማጥፊያ ዘዴዎችን በመጠቀም በ1፡30 ሰዓት ውስጥ እሳቱን ለመቆጣጠር መቻሉን ኦፊሰሩ ተናግረዋል፡፡ ቤቶቹ ቆርቆሮ በቆርቆሮ ሆነው ከመሠራታቸው በተጨማሪ፣ እጅግ በጣም የተጠጋጉና መደብሮቹም ውስጥ ለእሳት መቀጣጠል ምቹ የሆኑ ሸቀጣ ሸቀጦች በመኖራቸው ምክንያት ለማጥፋት አስቸጋሪ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
ባለሥልጣኑ የግምት ባለሙያ ባይኖረውም ከተረፈው ንብረትና በአካባቢው ካሉት የንግድ ባንክና ሌሎች ድርጅቶች መትረፍ አንፃር በእሳቱ የወደመው ንብረት ትንሽ መሆኑን አቶ ንጋቱ አክለዋል፡፡ 

ግብፅ ሱዳንን ከኢትዮጵያ ለመነጠል ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ጀመረች

-የግብፅ የልዑካን ቡድን በህዳሴው ግድብ ላይ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ሊነጋገር ነው
የግብፅ መንግሥት በታላቁ የህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ በተመለከተ ሱዳን ለኢትዮጵያ የሰጠችውን ድጋፍ ለማጨናገፍ፣ ሱዳንን ከኢትዮጵያ ለመነጠል ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ መጀመርዋን ዘገባዎች አመለከቱ፡፡
የተለያዩ የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ሰሞኑን እንደዘገቡት፣ የግብፅ መንግሥት የተለያዩ የመንግሥት አመራሮችና ፖለቲከኞች ከሱዳን መንግሥት አቻዎቻቸው ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጀምረዋል፡፡
ለአብነት ከተጠቀሱት መካከል የግብፅ አል ዋፍድ ፓርቲ ሊቀመንበር ሳይድ አል ባዳዊ በካይሮ ከሱዳን አምባሳደር ከማል ሐሰን ዓሊ ጋር በሁለቱ አገሮች ድንበር የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በዋነኝነት መክረዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች ድንበር የጦር መሣሪያ ዝውውር ለማስቆም የተነጋገሩት ሁለቱ ባለሥልጣናት፣ ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው የታላቁ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብና በሱዳን አቋም ላይ ተነጋግረዋል፡፡
ከውይይታቸው በኋላ አል ባዳዊ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላት አቋም ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ነው መባሉ በእውነት ላይ ያልተመሠረተ ተባራሪ ወሬ ነው ብለዋል፡፡ 
በግድቡ ላይ ሦስቱ አገሮች ጥልቅ ውይይት አካሂደው የሁሉንም ወገን ጥያቄዎች በሚመለስ ደረጃ መግባባት ይኖርባቸዋል የሚሉት አል ባዳዊ፣ ሱዳን የግብፅን የውኃ ፍላጐት በሚነካና ብሔራዊ ደኅንነቷን በሚጐዳ ጉዳይ ላይ አሉታዊ አቋም አትይዝም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ 
የሱዳን የመገናኛ ብዙኃን ባለፈው ሰኞ ዘገባዎቻቸው የሱዳን የመከላከያ ሚኒስትር በዚህ ሳምንት ወደ ካይሮ በማቅናት ከግብፅ አቻቸው ከፊልድ ማርሻል አብዱልፋታህ አል ሲሲ ጋር በሁለቱ አገሮች የጋራ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ወደ ግብፅ በዚህ ሳምንት እንደሚያመሩ የሱዳን ትሪቡን ዘገባ ያመለክታል፡፡ 
የግብፅ የመስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብዱል ሙታሊብ ባለፈው ሰኞ በሰጡት መግለጫ ደግሞ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ማቆም እንደሚገባት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ የኃይል ማመንጫ ግድብ መገንባት ከፈለገች መጠኑ አነስተኛ መሆን ይገባዋል፤›› ብለዋል፡፡ እንደሳቸው አባባል የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከታቀደው ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ወደ 30 በመቶ ዝቅ ማለት አለበት፡፡ በዚህ ስሌት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ወደ 1,800 ሜጋ ዋት መውረድ አለበት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ 45 አባላትን የያዘ የግብፅ የዲፕሎማሲ ቡድን ከጥር 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ቀናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ግብፅ በኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን ተቃውሞ ለአፍሪካ ኅብረት እንደሚያሳውቅና የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትንም እንደሚያነጋግር ለመረዳት ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያን የሚጐበኘው የልዑካን ቡድን በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማሲ ኢንስቲትዩት ኃላፊ አምባሳደር ዓሊ ኣል ሃዲዴ የሚመራ መሆኑን በኢትዮጵያ የግብፅ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል፡፡ የልዑካን ቡድኑ ከአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ኃላፊና ከኅብረቱ የመሠረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር ጋር እንደሚመክር የተያዘው ፕሮግራም ያስረዳል፡፡ 
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፣ ከዓባይ ተፋሰስ ዳይሬክቶሬትና ከሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ኃላፊዎች ጋር እንደሚነጋገር ታውቋል፡፡ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በመገናኘት በህዳሴው ግድብ ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በቅርቡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ፣ ሱዳን በህዳሴው ግድብ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር የወገነችው ለራሷ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በአጋጣሚ ለድርድር በካርቱም በቆዩባቸው ጊዜያት በተለያዩ መስጊዶች ውስጥ ሳይቀር የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሱዳንን እንዴት ሊጠቅም እንደሚችል ሲሰበክ በግርምት መታዘባቸውን በመግለጽ፣ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጐን ለራሷ ጥቅም ስትል መቆሟን መረዳት ይቻላል ብለዋል፡፡
የግብፅ ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ ጋር በሚደረገው ውይይትም ሆነ ድርድር ሱዳን የግብፅን ጥቅም የሚፃረር አቋም እንድትይዝ አለመፈለጋቸው ቢነገርም፣ ሱዳን እስካሁን የግድቡን ግንባታ እንደምትደግፍ ነው የሚታወቀው፡፡ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጎን ለመሰለፍ የቻለችው በሦስቱ አገሮች ተወክሎ ሲሠራ የነበረውና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን ያካተተው የኤክስፐርቶች ፓነል ሪፖርት ድምዳሜን አገናዝባ ነው፡፡ በሪፖርቱ ግድቡ በሱዳንም ሆነ በግብፅ ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት እንደማያደርስ ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ የግብፅ ባለሥልጣን የሱዳን አቋም ከኢትዮጵያ ጋር ወግኗል መባሉን ተባራሪ ወሬ ነው ቢሉም፣ የሱዳን ባለሥልጣናት በአደባባይ ድጋፋቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡  
ምንጭ ኢትዮጵያ ሪፖርተር   http://www.ethiopianreporter.com 

Wednesday, February 5, 2014

ሰውነት ቢሻው፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ እና አጨዋወት


ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው የተሰናበቱት ሰውነት ቢሻው
ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው የተሰናበቱት ሰውነት ቢሻው
በሶስተኛው የአፍሪካ ሀገሮች እግርኳስ ሻምፒዮና (ቻን) የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ ሶስት ውስጥ ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች በሁሉም ተሸንፎ፣ አራት ጎሎች ገብቶበት እና አንድም ጎል ሳያስቆጥር ያለምንም ነጥብ ከምድቡ የመጨረሻ ደረጃን ይዞ ከሻምፒዮናው መሰናበቱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሀገር ውስጥ ክለቦች በሚጫወቱ ተጨዋቾች ብቻ የተገነቡ ብሄራዊ ቡድኖች ወደተሳተፉበት የአፍሪካ ሀገሮች ሻምፒዮና (ቻን) ውድድር ላይ ለመካፈል ወደ አስተናጋጇ ሀገር ደቡብ አፍሪካ ሲሄድ ለዋንጫ ባለቤትነት የገመቱት በርካቶች ነበሩ። ምክንያታቸው ብሄራዊ ቡድኑ በብራዚል አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአለም ዋንጫ ለማለፍ በተካሄዱት የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ባሳየው ብቃት እና አብዛኞቹ የቡድኑ ተጨዋቾች በሀገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ በመሆናቸው ቡድኑ ከአለም ዋንጫ ማጣሪያው ብሄራዊ ቡድን ጋር ተመሳሳይነት ስለነበረው ነው።
ሻምፒዮናው ከተጀመረ በኋላ ግን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድቡ አብረውት ከተደለደሉት ሊቢያ፣ ኮንጎ ብራዛቪል እና ጋና ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ያሳየው የጨዋታ እንቅስቃሴ እና ያስመዘገባቸው ውጤቶች እንደተጠበቀው ለዋንጫ ባለቤትነት የሚያስጠብቁ ሳይሆኑ በጣም ደካማ እንቅስቃሴዎች ነበሩ።
አሰልጣኝ ሰውነት ቡድናቸው ለምን ጎል ማግባት እንደተቸገረ ሲጠየቁ ከሀገር ውጪ በሚገኙ ክለቦች የሚጫወቱት ሳልሀዲን ሰኢድ፣ ጌታነህ ከበደ እና ሽመልስ በቀለን የመሳሰሉ ቋሚ የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች የቻኑ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ አለመኖርን በተደጋጋሚ እንደምክንያት ቢያስቀምጡም በአጠቃላይ በሻምፒዮናው ላይ የተሳተፉት ብሄራዊ ቡድኖች ወሳኝ የሚባሉ ተጨዋቾቻቸውን (አንዳንዶቹ ሙሉ ለሙሉ) ሳይዙ ለሻምፒዮናው እንደመጡ ረስተውት ነው ወይ የሚያስብል ጥያቄን የሚያስነሳ ነበር።
በርግጥ የቻንን ውጤት እንደዋና መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ለሁለት አመት ያህል በዋና አሰልጣኘት ከያዙት ብሄራዊ ቡድን ሀላፊነታቸው አሰናብቷቸዋል።
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ እና ለአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ እንዲደርስ ቢያበቁትም ቡድኑ የሚከተለው የአጨዋወት ስታይል፣ የተጨዋቾች አመራረጣቸው፣ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በተያያዘ በጋዜጣዊ መግለጫዎች እና በቃለ-መጠይቆች ወቅት የሚሰጧቸው የተዘበራረቁ አስተያየቶች ከተለያየ አቅጣጫ ትችቶችን ያመጡባቸው ክስተቶች ነበሩ።
የኢትዮጵያ እግርኳስ እና አጨዋወት
በዚህ ጽሁፌ እንደአስተያየት ማስቀመጥ የምፈልገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሰውነት ቢሻውም ሆነ ከሳቸው በፊት በነበሩት አሰልጣኞች ዘመን እኔ እግርኳስን ማየት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ የታዘብኩት የአጨዋወት ዘይቤን መነሻ በማድረግ ነው።
ኢትዮጵያዊያን የእግርኳስ ተጨዋቾች አብዛኞቹ አጨዋወታቸው ኳስን በመያዝ እና በአጭር ኳስ ቅብብል ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ እንደሆነ በተለያየ ደረጃ ያሉ የሀገሪቷ ቡድኖች ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በተለያየ አጋጣሚ እና መንገድ ያየ የሚያውቀው ነው።
ይሄንን አጨዋወት መነሻ በማድረግ ለረጅም ጊዜ በባለሞያዎች እና በስፖርቱ አፍቃሪ በተደጋጋሚ ከሚሰጡት አስተያየቶች መካከል ዋናዎቹ “ለምን ይሄንን አጨዋወት አንቀይርም?” የሚለው እና “ለምን ያለንን ችሎታ በደንብ አወቀን ያንን ችሎታችንን የበለጠ አናዳብረውም?” የሚሉት ናቸው።
በአፍሪክ ዋንጫ ጎል ያገባው አዳነ
በአፍሪክ ዋንጫ ጎል ያገባው አዳነ
በተለይ በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አልፎ አልፎ ያሳያቸውን ፈጣን አጭር ቅብብል ጨዋታዎች የተመለከቱ የውጪ ሀገር ባለሞያዎች ለብሄራዊ ቡድኑ አድናቆታቸውን የገለጹ ሲሆን በአዲ አበባ ስታዲዬምም ሆነ በተለያዩ የክልል ከተሞች የኢትዮጵያ ቡድኖች የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች ለረጅም ጊዜ ሲከታተል የቆየው የስፖርት አፍቃሪ ግን (እኔን ጨምሮ) በዚህ አስተያየት አልተገረመም ነበር። ምክንያቱም እድሜ ልካችንን ስናየው የነበረው አጨዋወት ነበር እና ነው። የሀገሪቷ ቡድኖች በውጪ ቡድኖች ተሸንፈው ከውድድር ሲወጡ በአብዛኛው ከአፋችን ይወጣ የነበረው አስተያየት “ጥሩ እኮ ተጫውተን ነበር፤ ግን ውጤት እንቢ አለን” የሚለው ነው።
ብሄራዊ ቡድኑ ከዛምቢያ ጋር በአፍሪካ ዋንጫው ያደረገውን ጨዋታ አይተው አድናቆታቸውን የገለጹት የውጪ ዜጎች እና በሀገር ፍቅር ስሜት ብሄራዊ ቡድን ስለሆነ ብቻ እግርኳስን መከታተል የጀመሩት “አዲስ” ኢትዮጵያዊያን ተመልካቾች አድናቆታቸውን ያጎረፉለት ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያን እግርኳስ ለማየት ባለመታደላቸው ነው።
በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ እና በቅርቡ በተጠናቀቀው የቻን ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ኳሱን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ችሏል ከማለት ይልቅ አልፎ አልፎ ብልጭ ብለው በሚጠፉ አጋጣሚዎች ብቻ ኳሱን በበላይነት ከመቆጣጠሩ በተጨማሪ ያ ቁጥጥሩ የነበረው የራሱ ሜዳ ላይ ብቻ በመሆኑ እና ያንን የበላይነት ወደተጋጣሚ ሜዳ ይዞት ባለመሄዱ እና ተግባራዊ ለማድረግ አለመቻሉ ደካማነቱን የበለጠ አጉልቶታል።
እ.አ.አ በ1907 ዓ.ም የእንግሊዙ ኖርዝሀምተን ክለብ አሰልጣኝነት የተረከቡት ኸርበርት ቻፕማን በጊዜው “እግርኳስ ጨዋታን ለማሸነፍ ኳስን በቁጥጥር ስር ማድረግ ብቻ በቂ አይደለም፤ ኳሱን የት እንደተቆጣጠርከው እና የተቆጣጠርክበት ሁኔታዎች ወሳኝነት አላቸው” በማለት የተናገሩት ለምን የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ እና በሌሎች ሻምፒዮናዎች ኳሱን ቢቆጣጠሩም ያንን ቁጥጥራቸውን ወደውጤት መቀየር በተደጋጋሚ እንደተቸገሩ ፍንጭ የሚሰጥ ነው።
የቀድሞው የስዋንሲ ሲቲ ክለብ አሰልጣኝ እና በአለም እግርኳስ ውስጥ በተጨዋችነት በታላቅነታቸው ከሚደነቁት መካከል አንዱ የሆነው ዴንማርካዊው ማይክል ላውድሮፕ በተደጋጋሚ ሲል እንደሚሰማው ኳስን መቆጣጥር ብቻ ሳይሆን ዋናው መታየት ያለበት ኳሱን የት እና እንዴት ተቆጣጠርከው የሚለው ነገር ነው።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም ሆነ ክለቦች በተደጋጋሚ ከውጪ ከመጡ ቡድኖች ጋር በተለያዩ ሻምፒዮናዎች ላይ ሲሳተፉ ሜዳ ላይ አልፎ አልፎ ኳሱን በፈጣን የአጭር ቅብብል ለመቆጣጠር ቢችሉም ያ ቁጥጥራቸው ግን በአብዛኛው የተጠና ሀሳብ እና አካሄድ እንደሚጎለው ይሰሩ ከነበሩት ስህተቶች መረዳት ይቻላል።
ምንም እንኳን አንዳንዶች ኳስ የያዘው ሰው የሚሰራውን ስህተት በማየት ኳሱን ያበላሸውን ሰው በተደጋጋሚ ለመተቸት ሲሞክሩ ቢታይም መተቸት የነበረበት ግን ኳሱን ላለመቀበል የሚሸሸጉት እና ያንን አጨዋወት ተግባራዊ እንዲሆን ታክቲኩን ወይም የአጨዋወት ዘዴውን የመረጠው አሰልጣኝ ነው። እናም ለምን ያንን አደረክ ብሎ አሰልጣኙን መጠየቅ ምኑ ላይ ነው ስህተቱ?
በርግጥ እግርኳስ እንዲህ በቀላሉ “ይሄ መሆን አለበት፣ ይሄ መሆን የለበትም” በማለት የሚተነተን ስፖርት አይደለም። ለዚህም በ1980 ዎች መጨረሻ እና በ1990 ዎቹ መጀመሪያ የአለም እግርኳስን ተቆጣጥሮ የነበረው የጣሊያኑ ኤሲ ሚላን ክለብን የገነቡት ታላቁ አሰልጣኝ አሪጎ ሳኪ “እግርኳስ በጣም የተወሳሰበ ስፖርት ነው” ያሉት።
አሪጎ ሳኪ ይህ አባባላቸውን እንዲህ ይተነትኑታል -
“ስታጠቃ በተጨዋቾችህ መሀል ያሉት ርቀቶች ትክክለኛ መሆን አለባቸው። ጊዜ አጠባበቅህ እና አጠቃቀምህ ልክ ሊሆን ይገባል። የያዘህን ተጨዋች ማስለቀቂያ ትክክለኛ መንገድ ሊኖርህ ይገባል። እነዚህ ነገሮች ከሌሉህ የምትጫወተው እግርኳስ ፍሰት አይኖረውም። ብዙውን ጊዜ ቡድኖች ቡድን ከመሆን ይልቅ ዝም ብለው የተጨዋቾች ስብስብ ሆነው ይቀሩና በአንድነት መንቀሳቀስ ሲቸገሩ ታያለህ” ያሉት።
ሁሉም የእግርኳስ ቡድኖች ከሳሞአ ብሄራዊ ቡድን እስከ ስፔን ብሄራዊ ቡድን፤ በሰፈር ውስጥ ከሚጫወቱ ቡድኖች እስከ ግዙፎቹ ባርሴሎና፣ ባየርን ሙኒክ፣ ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ሪያል ማድሪድ ድረስ ተመሳሳይ አይነት ፍላጎት አላቸው። ጠንካራ ቡድን መሆን እና እንደ ቡድን መጫወት።
አሪጎ ሳኪ ይሄንን ቡድን የመሆን ፍላጎትን እና ቡድን መሆንን አስመልክተው ሲያስረዱ፦
“ምን አልባት ቡድን የመሆን እና በቡድን የመንቀሳቀስ ፍላጎት ሊኖር ይችላል። ፍላጎት ብቻውን ግን በቂ አይደለም። ስብስብን ወደ ቡድን የሚቀይረው ጨዋታ/አጨዋወት ነው። የምትከተለው የአጨዋወት ዘዴ ደግሞ በምታጠቃበትም ሆነ በምትከላከልበት ጊዜ ፍሰት ኖሮት ሊሰራ ይገባዋል። ይሄንን ለማብራራት ያህል ሁልጊዜም ቢሆን በመሀላቸው ሰፊ ርቀት ሳይኖር አብረው/ተጠጋግተው የሚንቀሳቀሱ ተጨዋቾች የተሰራ ቡድን ለሚፈጠሩበት ፈተናዎች በቀላሉ መልስ የማግኘት እድሉ ሰፊ ነው።
“አብረው ስል ተጠጋግተው (compact) ማለቴ ነው። ይሄን አይነት አጨዋወት የሚከተል ቡድን ኳሱን ቢነጠቅ እንኳን ቢበዛ 10 ሜትሮችን ብቻ ለነጠቃ ስለሚሮጥ 20 እና 30 ሜትሮች በመሮጥ የምታቃጥለውን ሀይል ያህል እንዳታቃጥል ያደርግሀል። ምክንያቱም እዛው አብረህ ኳሱን የነጠቀህ ቡድን ላይ ጫናን እንድትፈጥር እና መፈናፈኛ እንድታሳጣው ያደርግሀል። በምታጠቃበት ጊዜ ደግሞ የቡድን አባሎችህ አጠገብህ ስለሚገኙ ኳስን ለማቀበል ብዙ አማራጮች እንዲኖርህ ያደርጋሉ። ምክንያቱም ሁልጊዜም እንቅስቃሴ ላይ በመሆናችሁ። እነዚህ ናቸው እንግዲህ ተግባቢነት ባላቸው ተጨዋቾች በተገነባ ቡድን እና በተጨዋቾች ስብስብ የተገነባ ቡድን መካከል ያሉ ዋና ልዩነቶች።”
በአፍሪካ ዋንጫው ላይ እና በአለም ዋንጫ ማጣሪያው ወቅት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአብዛኛው ሳልሀዲን ሰኢድን ፊት ላይ አቁሞ ኳስን በረጅሙ እየጠለዘ ሲጫወት እና ኳሱም ተመልሶ ራሱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ላይ ጫናን ሲፈጥር ነበር በተደጋጋሚ የታየው። ታዲያ ያ ተመልሶ የመጣ ኳስ ድንገት ከተቆጥረ ጨዋታውን በቴሌቪዥን የሚያየው አብዛኛው ተመልካች በረኞችን ሲተች በተደጋጋሚ ይሰማ ነበር። ግን እስከመቼ ነው በረኛን እየሰደብን፣ በቀጥታ በአይን የሚታዩ ስህተቶችን ብቻ የሰሩ ተጨዋቾችን እየተቸን የምንኖረው።
በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በረኞችን መተቸት ምን አልባትም ባህል ሆኗል ብል እያጋነንኩ አይደለም። በርግጥ በረኞቻችን ሙሉ ለሙሉ መተቸት የለባቸውም እያልኩ አይደለም። በረኛው ሊያከሽፍው የሚችለው ኳስ ሲገባ እና ሌሎች እሱ መስራት የሌለባቸውን ስህተቶች ሲሰራ ከታየ መተቸት አለበት። እነዚህ ሁኔታዎች የሚከሰቱት ግን በጣም በጥቂት አጋጣሚዎች ነው።
ዋናው ትኩረት መደረግ ያለበት ኳሱ እንዴት በረኛችን ጋር ደረሰ፣ ለምንስ ከበረኛው ፊት የቆሙት ተከላካዮች፣ አማካዮች እና አጥቂዎች ኳሱን በረኛው ጋር ከመድረሱ በፊት ሊያቆሙት አልቻሉም? ለምንድነው ተጨዋቾች ኳሱ በቁጥጥራቸው ስር እያለ ይዘውት በመጫወት ቀዳዳዎችን ከመፈለግ ይልቅ ያንን ኳስ እየጠለዙ ተጋጣሚያቸው በአካል ብቃት ለሚበልጣቸው ተጨዋቾች ሁኔታዎችን ቀላል የሚያደርጉላቸው?
ተጨዋቾችን የመረጡት እና ሜዳ ውስጥም ገብተው የሆነ አጨዋወትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያደርጓቸው አሰልጣኞች ናቸው። ለምንድነው የተነደፈው አጨዋወት ዘዴ ሲበላሽ አሰልጣኞች የማይተቹት? ለምንድነው ግለሰብ ተጨዋቾች ለቡድን ውጤት ሁልጊዜ የትችት ማምለጫ ተደርገው የሚወሰዱት? እስከመቼ አብዛኞቹ አንጋፋ አሰልጣኞቻችን የሚታይ ስህተቶችን ከሰሩ ተጨዋቾች ጀርባ ተደብቀው እያጭበረበሩ ይኖራሉ?
ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች በተፈጥሮ የግል ኳስ ችሎታቸው ከማንም አያንሱም። ታዲያ ለምን ቡድን ሆነው ሲመጡ ወይም ሜዳ ላይ ሲገቡ ከተጋጣሚዎቻቸው አንሰው ይገኛሉ? መልሱ አንድ እና አንድ ነው – የሚከተሉት የአጨዋወት ዘዴ። ያንን የአጨዋወት ዘዴ የሚነድፈው ማነው? አሰልጣኙ። ያ አሰልጣኝ የነደፈው የአጨዋወት ዘዴ መነሻው ማንን ያደረገ ነው? ተጋጣሚ ቡድንን ወይስ ራሱን?
ተጋጣሚ ቡድንን መሰረት አድርገው ቡድናቸውን የሚሰሩ አሰልጣኞች ያላቸው ችግር ምንድነው? የራሳቸው ልጆች ያላቸውን ችሎታ ይተዉና ተጋጣሚ ቡድን እንዲጫወቱ እንደሚፈልገው ይጫወታሉ። ታዲያ ያ ሲስተም ሲበላሽ እና ውጤት ሲጠፋ አሰልጣኞች ስህተት የሰራውን ተጨዋች ይተቹና ራሳቸውን ከትችት ነጻ ለማውጣት ይሞክራሉ።
ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች በአብዛኛው ኳሱን ቢችሉትም የታክቲክ ችግር እንዳለባቸው ይነገራል። እነዚህ ታክቲካል ዲሲፕሊኖች ኳስን ለመቀበል ወደክፍት/ባዶ ቦታ መሮጥ፣ የሜዳውን ስፋት እና ርዝመት ግምት ውስጥ አስገብቶ የሚቆምባቸውን ቦታዎች ማወቅ፣ ከቡድን አባል ጋር መቀናጀት፣ ኳሱን ለመቀበል ክፍት ቦታዎች ላይ መገኘት፣ በራስ እና በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ኳስን በበላይነት መቆጣጠር፣ እንቅስቃሴዎችን ኳስ እግር ስር ከመግባቷ በፊት ቀድሞ ማንበብ፣ መቼ ኳስን ማቀበል እና በግል እያንከባለሉ መሄድ እንዳለባቸው ትክክለኛ እርምጃን መውሰድ፣ ኳስን ለጓደኛ ሲያቀብሉ እና ሲያንከባልሉ ከተጋጣሚ ቡድን ተጨዋች እይታ/ንባብ መሸፈን፣ የተጋጣሚ ቡድን ሊጠቀምበት የሚችለውን አደገኛ ቦታ እና ሰው መከላከል እና መሸፈን የሚሉት በዋናነት የሚጠቀሱ የታክቲክ ስርአቶች በኢትዮጵያ እግርኳስ ቡድኖች ላይ በተደጋጋሚ የሚታዩ ታሪካዊ ችግሮች ናቸው።
እናም እነዚህን ታሪካዊ ችግሮች በስልጠና የሚገኙ በመሆናቸው፣ እነዚህን አሻሽሎ ተጨዋቾቹ በተፈጥሮ ከታደሏቸው ችሎታዎች ጋር በማዋሀድ ለተሻለ ውጤት መስራት ነው እንጂ አንድ ሰው ትችት የሚመስል አስተያየት በሰነዘረ ቁጥር “ከ31 አመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፍነው” በማለት ድፍን ባለ ሁኔታ አስተያየቶችን መደምሰስ ለማንም አልጠቀመም። አይጠቅምም።
ከዚህ በኋላ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ተክቶ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሚሆንውም (ከውጪም መጣ ከሀገር ውስጥ) እየተደነቀ እና እየተተቸ ስራውን መስራቱን ይቀጥላል። እግርኳስን አስደሳች የሚያደርገው ነገር ጥበበኛ ተጨዋቾቹ እና ወበት ያለው ጨዋታን የሚጫወቱት ቡድኖች ብቻ ሳይሆኑ፣ እያንዳንዳችን እንደይታችን የራሳችን አስተያየቶች እንዲኖረን ማድረጉ ነው።