Sunday, January 19, 2014

ግራና ቀኝ ጠፋን! (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)


Left of Right
በአለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ወያኔ-ኢሕአዴግ የሚወቀስበት ሥራ በጣም ቢያመዝንም የሚመሰገንበት ሥራ የጽሑፍ ቁጥጥርን ማስቀረቱ ብቻ ነው፤ ሁልጊዜም አንድ ጥሩ ነገር የሚያስከትለው አብዛኛውን ጊዜ የማይጠበቅ ነገር ሊኖር ይችላል፤ ለምሳሌ አጠቃላይ ነጻነት ሲመጣ ወንጀለኛነት ይጨምራል፤ እንዲሁም የጽሑፍ ቁጥጥር ሲነሣ ጸሐፊዎች ይበዛሉ፤ ትምህርት በተስፋፈበትና ማንም እንደፈለገ ለመጻፍና ለማሳተም ችሎታውም ዕድሉም በማይገኝበት፣ ሳያበጥርና ሳይሰልቅ አሰር-ገሰሩን ጽፎ በአደባባይ የሚወጣውን ጥምብ-እርኩሱን አውጥተው ሁለተኛ እንዳይለምደው የሚያደርጉ የታወቁና የሰላ አእምሮና ብዕር ያላቸው አርታእያንና ሐያስያን (ገምጋሚዎች) ባሉበት ብዕሩን የሚያባልግ ጸሐፊ አይወጣም፤ ይህ ሁሉ ባልተሟላበት እንደኛ ባለ አገር ውስጥ ብዕርን ማባለግ እንደመብት ወይም እንደነጻነት እየታየ ነው፡፡
በአደባባይ የሚጽፉ ሰዎች ሁለት ነገሮችን ለይተው መገንዘብና ለሌሎችም ሲየያስተላልፉ ለይተው ማስተላለፍ አለባቸው፤ አንዱ የሆነና የተረጋገጠ ሁነት ነው፤ይህንን ሳይበርዙና ሳይከልሱ እንዳለና እንደተገኘ ማስተላለፍ ግዴታ ነው፤ ሁለተኛው የራስ አስተያየት ነው፤ የጠራውንና የነጣውን አውነት ከጎደፈ የግል አስተያየት ጋር አጋብቶ ማቅረብ ወይ አለማወቅ ነው፤ አውቀው ከሆነም ለማታለል ከመሞከር የሚቆጠር ነው፤ በአለንበት ዘመን አብዛኛውን ጊዜ የምናየው ፊደሎቹን ማወቅ እንደሙሉ እውቀት ይቆጠራል፤ ወይም በሌላ አነጋገር ፊደልን ማወቅ የመጻፍ ችሎታን ይሆናል፤ ይህ ትልቅ ስሕተት ነው፤ ፊደሎችን ማወቅ ትልቅና መሠረታዊ የእውቀት ጎዳና ላይ መግባት ነው፤ ጎዳናው ግን በጣም ረጅም ነው፤ በእውቀት ጎዳና ላይ መግባት የእውቀት ባለቤት ከመሆን ጋር እንዳይደባለቅ በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ በአገራችን ፊደልን ማወቅ ሌላም አደጋ አለው፤ ፊደልን ማወቅ ከሥልጣን ጋር ሲጋባ የሚያስከትለውን ውድቀት ከአንዴም ሁለቴ አይተናል፤ እያየንም ነው፤ ስለዚህም ፊደል ኃላፊነትን ያመጣል፤ አለዚያ በአለፉት ሠላሳ ዓመታት ያየነው ውድቀት እየተከበረ ይቀጥላል፡፡
መጻፍ እንደመናገር ሊቆጠር ይቻላል፤ሆኖም በመጻፍና በመናገር መሀከል ትልቅ ልዩነት አለ፤ በንግግር ላይ ከሰዎች በሚቀርበው ጥያቄም ሆነ ተቃውሞ እንዲህ ማለቴ ነው ብሎ የተናገሩትን እዚያው ለማረምና ለማስተካከል ይቻላል፤ በተጻፈ ነገር ላይ እንዲህ ዓይነቱ ወዲያው የመታረም ዕድል የለም፤ ስለዚህም ለመጻፍ በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ማለት ነው፤ ከላይ እንደተገለጸው ፊደልና ሥልጣን ሲጋቡ ሰንደቅ ዓላማው ጨርቅ ነው ከማለትም ሊያልፍ ይችላል፤ ለምሳሌ የደርግን የትርፍ ቤቶች አዋጅ ብንመለከተው ‹‹ትርፍ ቤት›› ሲል ትርፍን እንተወውና ‹‹ቤት›› ለሚለው ትክክለኛ ትርጉም አልሰጠም፤ ስለዚህም በጭራሮ የተያያዘ ምንም ‹‹ቤት›› የሚያሰኘው (መኝታ ቤት፣ ወጥ ቤት፣ መታጠቢያ ቤት፣ … የሌለው) በሃምሳ ሳንቲም የሚከራይ ነገር ‹‹ቤት›› ተብሎ በሺህ ብር ከሚከራይ ቤት ጋር ተወረሰ! ያፈረ የለም እንጂ አሳፋሪ ነው!
እንዲህ ዓይነቱ ችግር ከየት የሚመጣ ነው? አንድ አጠቃላይ የአስተሳሰብ ችግር አለ፤ ለየት ያለውን ከጅምላው፣ ግዙፉን ከረቂቁ፣ አንዱን ከብዙው ያለጥንቃቄ ማደባለቅ በአማርኛ በጣም የተለመደ እየሆነ ነው፤ የአስተሳሰብ ችግር ነው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ (አበሻና ሆድ የሚለው ጽሑፍ ባሕር ተሻግሮ የአበሻን ነገር-ዓለም ትቶ የተጠበሰ ውሻ (ሆት ዶግ) የሚበላውንም አስቀየመውና ሌሎች ስለአበሻ የጻፍኋቸውን ተውኩት እንጂ አበሻና መናገር የሚለው በተለይ ለባሕር ማዶው ዘሎ-ጥልቅ ተስማሚው ነበር፤) በማናቸውም ነገር ላይ ለመቀባጠር በጣም ኃይለኛ ምኞት አለው፤ አንዱ ያስተሳሰብ ችግር ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፤ ሳያስቡና ሳይጨነቁ አፍ እንዳመጣ ከመናገር ልማድ ጋር የተያያዘ ነው፤ አሁን ደግሞ የጎሠኛነት ሥርዓት ካመጣብን ጣጣ ዋኖቹ የአስተሳሰብ ችግሮች እነዚህ ናቸው፤  የቡድን መብትን መሠረታዊ አድርጎ የግለሰብን መብት ጨፍልቆ የተነሣው የወያኔ የጎሣ ሥርዓት ከሃያ ዓመታት በኋላ በስንት ጥረት የደረሰበት አሁንም የተዛባ ድምዳሜ የቡድን መብትንና የግለሰብ መብትን ጎን ለጎን አቁሞ እኩል ናቸው ማለትን ነው፤ ለውጡ የተጣራ ባይሆንም ሃያ ዓመታት መፍጀቱ የወያኔን የመማር ፍጥነት የሚያመለክት ነው፤ የሥልጣን ጉልበትና የሥልጣን ምኞት ተጽእኖ እንደአንድነት ያለውንም የፖሊቲካ ፓርቲ ፐሮግራሙን እንዲለውጥና የግለሰቦችንና የቡድን መብቶች በአንድ ደረጃ ላይ እንዲያስቀምጥ ተደርጎአል፤ ከቡድን ውስጥ ግለሰቦች ሁሉ ሙልጭ ብለው ሲወጡ ስለቡድን መብት የሚያወራ ምን እንደሚባል እንጃ! ከቀኝ ወደግራ የዞረ? ወይስ ከግራ ወደቀኝ? ወይስ … ቀኝ ፖሊቲካ ባዶ ከረጢት ይዞ ይቀራል።
በተደጋጋሚ እንዳየሁት ለግለሰብ መብቶች የቆመ ቀኝ-ዘመም፣ ለቡድን መብቶች የቆመ ግራ-ዘመም የሚባል ይመስላል ይህ ስሕተት ነው።
ቀደም ሲል የታወቀው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ እኔን ቀኝ-ዘመም እያለ ጽፎ ሳይ ይህ ሰው በአውነት አንድ መዝገበ ቃላት ማየት አቅቶት ነው? ወይስ እኔን በተለየ ዓይን ለማየት ከመፈለግ የተነሣ ነው? ወይስ የሲአይኤውን መልክተኛ ፖል ሄንዜን ሰምቶ ነው? የሱ ጎሣ አባል መሆንንና አለመሆንን እኔ የምመርጠውና የምወስነው አይደለም፤ ታምራት በኢትዮጵያዊነት ወይም በዜግነት ዓይን ሊመለከተኝ አለመቻሉም የእኔ ጥፋት አይደለም፤ ሁሉም ቢቀር በሰውነት ደረጃ ሊያየኝ ይችል ነበር፤ ይህንንም አልቻለም፤ እንግዲህ ወይ እኔ ሰው አልሆንኩለትም፤ ወይ እሱ ወደሰውነት ደረጃ አልደረሰም፤ በታምራት ነገራ ቀኝ-ግራ መጋባት እንደኔው ጥርጣሬ ውስጥ ገብቶ የነበረው ክፍሉ ሁሴን ወደጥናት ተመልሶ የታምራትን ስሕተት አረጋገጠ፤ እኔም እንዲሁ አደረግሁና የታምራት ነገራን ግራ መጋባት አረጋገጥሁ፤ ታምራት ነገራ የጎሣ ቀኝ ገብቶት ግራ ፖሊቲካ ቀኝ ሆኖበታል! ቀኝ-ግራ ፖሊቲካ በጎሣ አባልነት የሚገኝ ወይም የሚታጣ ይመስለዋል፤ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ሀብትና ሌላ ማናቸውንም ነገር ከቁም-ነገር ሳይቆጥሩ ለማንም ሰው በሰውነቱ ብቻ ማግኘት የሚገባውን መብት እንዲያገኝ ቆሞ መከራከር ለታምራት እንግዳ ነገር ይመስለኛል፤ ገና እሱ ሳይወለድ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር በተደረገ ስብሰባ ላይ ለምን የኢትዮጵያ ራድዮ በኦሮምኛ አይናገርም? በማለት ጌታቸው ኃይሌ ጋር ሆነን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰዎችን ሞግተን  ነበር፤ ይህ ለታምራት የቀኝ ፖሊቲካ ነው፤ የሱ ጎሣ-ዘመም ፖሊቲካ ግራ መሆኑ ነው! ጎሠኛነት ምን ጊዜም የትም ቦታ እንደግራ ፖሊቲካ ተፈርጆ አያውቅም።
አሁን ደግሞ ሰሎሞን አብርሃም ይህንኑ የታምራት ነገራን ስሕተት ለመድገም የዳዳው ስለመሰለኝ በዝምታ ለማለፍ አልፈለግሁም፤ ሰሎሞን (liberalism) የሚለውን የአንግሊዝኛ ቃል በባሕርዩ የሌለበትን ትርጉም ሊሰጠው ይዳዳዋል፤ ሰሎሞን አብርሃም ሊጽፍበት የተነሣው ጉዳይ በእኔ ግምት በጣም ወቅታዊና አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን የግል ስሜትን ከሁነት ጋር፣ ያልተጣራ የተውሶ ሀሳብን (‹‹ፊዩዳሊዝም፣ ሊበራሊዝም››…) ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በማያያዝ አስተሳሰቡን ያጎደፈው ይመስለኛል፤ ያነሣው ጉዳይ በተለይም እንደሱ ላለ ፖሊቲከኛ ከስሜተኛነትና ከወገንተኛነት የጸዳ ቢያደርገው (‹‹ወግ አጥባቂ፣ቀኝ አክራሪ›› ..)፣ወይም ደግሞ ያልተጣራ (‹‹የሊበራል ዴሞክራሲን ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ይመስላሉ፤›› እያለ በጎን ከሚጎሽም የጸዳውን እውነት ፊት ለፊት እያቀረበ ድካማቸውን ቢተነትን የሚጠቅም ይሆን ነበር።
ግራና ቀኝ ፖሊቲካ የሚባለውን ከጎሣ ፖሊቲካ ጋር ለማገናኘት የሚፈልጉ ሰዎች ወጣቶችን ወደአስከፊ ስሕተት እንዳይመሩ መጠንቀቅ ያለባቸው ይመስለኛል፤ የጎሣ ሥርዓትን የሚቃወሙትን ወገኖች በሌላ መንገድ ለመቋቋም ቢሞክሩ የተሻለ ነው፤ በጎሣ ክፍፍል ማመን ሌላው ቀርቶ በሰውነት ደረጃ ለመሰለፍም ያስቸግራል፤ ለማናቸውም የጎሣ ፖሊቲካን ከግራ ፖሊቲካ ማዛመዱ እሳትና ውሀ ነው።

በህይወት የሚገኙ አካለ ሰንኩላን እህቶቻችን እና ባለቤት አልባው የዜጎቻችን አስከሬን ብሶት በሳውዲ አረቢያ ሆስፒታሎች ።


ላለፉት ተከታታይ ፫ ሳምንታት በርካት ኢትዮጵያውያን ከ ሳውዲ አረብያ ጂዛን፡ወደ አዲስ አበባ በቀጥታ በረራ እየተሸኙ ሲሆን በመኪና አደጋ እና መሰል ተዛማጅ አደጋዎች ቆመው መራመድ የማይችሉ ወገኖቻችን በሳውዲ አየርላይንስ እንደማይጫኑ በመግለጹ ለከፍተኛ የሞራል ዝቅጠት መዳረጋቸውን ምንጮች ይገልጻሉ።በተለይ በጂዛን ከተማ በአቡሰዳድ ኣድ ደርብ ሆስፒታል ለ፫ አመታት ያልጋ ቁራኛ እንደሆነች የሚነገርላት ወጣት ከዲጃ መሓመድ ሑሴንን አብነት የሚጠቅሱት እነዚህ ምንጮች ።



ዛሬ በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኝ ኢትዮጵያውያን ለሃገራቸው በመብቃት ሰቃይ እና በደል ሲፈራረቅባት የኖረውን ህይወታቸውን ከሞት መታደግ ሲችሉ በተመሳሳይ ሞት ቀድሞት በለስ የቀናው የወገን ሬሳ በሳጥን ታሽጓ ለህገሩ አፈር ሲበቃ እንደነ ከድጃ ያሉ ዜጎች በሳውዲ አረቢያ ሆስፒታሎች የሚደርስላቸው አጠተው ሞታቸውን ሲጠብቁ ማየት ምንኝኛ እንጀት እንደሚበላ ይናገራሉ ። በአካላቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷባቸው የአልጋ ቁራኛ ከሆኑ ወገኖቻችን መሃከል አንዶ የሆነችው ወጣት ከድጃ መሃመድ ከኢትዮጵያ ከቆንስላ ፅ\ቤት ተወካዮች የተሰጣት ምላሽ ተስፋ አስቋራጭ፡መሆኑን የሚገልጹ ወገኖች የወጣቷ ህይወት ቆንስላው በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንጂ በሳውዲ አየር መንገድ ማሳፈር እንደማትችል ከማስረዳት ባሻገር እስካሁን የረባ ነገር ማድረግ እንዳልቻለ ገልጸዋል ።

ለዚህም በጂዛን የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሊቀመንበር አቶ ግደይ ግራማ ማምሻውን ከጂዛን ፡ ጀዳ ፡አዲስ አበባ ትራንዚት ቲኬት ቆርጣ ወጣቷ መሄድ እንዳለባት እንደተናገሩ የሚገልጹት ምንጮች ። ወጣቷ በደረሰባት የመ ኪና አደጋ ቀሪ ሰውነትዋን ማዘዝ እንደማትችል እና « ከሽንጥዋ በታች » በድን ከመሆኖ ባሻገር ያለ «ዳያፐርና ካታተር » የ ሽንት ማስወገጃ ቱቦ ስለማትንቀሳቀስ እርዳታ እና የቀርብ ክትትል እንደሚያሻት እያወቁ አንጻራዊ እርዳት ከማድረግ ይልቅ ከጂዛን ጅዳ የምሄዱን ሃላፊነት በዝች ባልታደለች ወጣት ላይ መጣላቸው ሰባዊ ነት የጎደለው መሆኑንን ይናገራሉ ።

Ethiopian Hagere's photo.ለደረሰባት የመኪና አደጋ የኢንሹራንስ መብቷን የሚያስከብርላት እጥታ ከወግቧ በታች በድን ሆና ሃገር ለመግባት መገደዷን የሚናገሩ የአካባቢው ምንጮች ለዚች አካለ ሰንኩል ወጣት ፧የጉዞ ሰነድዋን የሚያዘጋጅላት ፧ከጂዛን እስከ ጀዳ የስምንት መቶ ኪሎ መትር ርቀት ከዛም ጅዳ ስትደርስ ተቀብሎ የሚያስተናግዳት ወገን እንደሌላት የሚናገሩ እንዚህ ወገኖች በዚህ ዙሪያ ወገናዊ ትብበር እንዲያደርጉ ጉዳዩ ለሚመላከታቸው አካላት በጅዳ ጄነራል ዘነበ ከበደ ለሚመራው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት አመልከተው መፍትሄ እንዳለገኙ የሚገልጹ እነዚህ ምንጮች በተመሳሳይ መልኩ ወደ ሃገር መግባት እየፈለጉ መግባት ያልቻሉ በየቤቱ እና በየሆስፒታሉ የሚገኙ አካለሰንኩል ዜጎቻችን ያለረዳት ወገን አልባ ሆነው ለከፋ ስቃይ እና በደል እየተዳረጉ መሆኑገልጸዋል።

ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ድረስ ወጣቷ ያለጠያቂ እና ደጋፊ ሆስፒታል ውስጥ፡መሆኗን ለማረጋጋጥ፡ተችሎል ። በተመሳሳይ ሁኔታ በከባድ የመኪና አደጋ ማየት እንጂ መስማትም ሆነ መናገር አሊያም መንቀሳቀስ የማይችለው ኢትዮጵያዊ ወጣት በዛው ሆስፒታል ውስጥ እንደሚኖር እንዚሁ ምንጮች ገልጸዋል። በሳውዲ አረቢያ የተለያዩ ሆስፒታሎች ከሚገኙ አካለ ሰንኩል ወገኖቻችን ባሻገር ሪያድ ጅዳ ጂዛን መዲና ወዘተ በሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ አድራሻቸው የማይታወቅ በተለያዩ አደጋዎች ህይወታቸው ያለፈ በሺህ የሚቆጠር የኢትዮጵያውያን ሬሳ እንደሚገኝ ይታወቃል።

Ethiopian Hagere ጅዳ በዋዲ
L 

Friday, January 17, 2014

አቶ ጌቱ ገለቴና ሌሎች ተጠርጣሪዎች በጋዜጣ እንዲጠሩ ታዘዘ


‹‹የቀረበብኝ ክስ ብዙ በመሆኑ መቃወሚያ ለማቅረብ ረዘም ያለ ቀጠሮ ይሰጠኝ›› አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ 
-  አቶ ጌቱ ገለቴና ሌሎች ተጠርጣሪዎች በጋዜጣ እንዲጠሩ ታዘዘ
በተጠረጠሩበት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል፤ በፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶባቸው ላለፉት ስምንት ወራት በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ፣ ‹‹ክሴ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሁን ብዬ የጠየቅኩት እኔ አይደለሁም፤›› አሉ፡፡
አቶ መላኩ ተቃውሞአቸውን ያቀረቡት ጥር 6 ቀን 2006 ዓ.ም. የተጠረጠሩበትን ክስ እየመረመረው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡ እሳቸው ሳይጠይቁና ምንም ሳይናገሩ በርካታ የመገናኛ ብዙኃን እሳቸው እንደጠየቁና እንደተከለከሉ አድርገው መዘገባቸውን በመቃወም፣ እንዲስተካከል ወይም ታርሞ እንዲዘገብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ ጥያቄውን ያቀረበው ፍርድ ቤቱ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ከፍረጃ ጋር በማያያዝ ዘገባ እንዳያስተላልፉ ከማስጠንቀቂያ ጋር የሰጠውን ትዕዛዝ ካስታወሰ በኋላ፣ ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን በትክክል ባይዘግቡም ሁሉም ደግሞ ተሳስተዋል ማለት እንደማይቻል ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከዚህ በላይ የሚለው ነገር እንደሌለ በማሳወቅ ተከሳሾቹ ጠበቆቻቸውን አማክረው የስም ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞብናል የሚሉ ከሆነ፣ የሚመለከተውን አካል መጠየቅ እንደሚችሉ አስረድቷል፡፡
ሌላው ፍርድ ቤቱ በዕለቱ መዝገቡን ቀጥሮ የነበረው የአቶ መላኩን ክስ የማየት ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት የትኛው እንደሆነ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚሽን በደረሰው የምርመራ ውጤት ላይ ውሳኔ ሰጥቶ እንዲያሳውቀው የሰጠውን ትዕዛዝ ለመጠባበቅ እንደነበር ለችሎቱ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ፌዴሬሽን ምክር ቤት ታህሣሥ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ባደረገው ውይይት፣ የአቶ መላኩን ክስ የማየት ሥልጣን ያለው ከፍተኛው ፍርድ ቤት መሆኑን በማሳወቁ፣ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ ላይ የተመሠረተው ክስ በመደበኛነት እንደሚቀጥል አሳውቋል፡፡
የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የክስ መግለጫ እንደሚያስፈልገው በመጠቆም፣ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ማቅረብ የሚችሉ መሆኑም በችሎት ተነግሯቸዋል፡፡ ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ ቅሬታ እንዳላቸውና መቃወሚያ እንደሚያቀርቡ ተናግረው፣ ከክሱ ስፋት አንፃር ረዘም ያለ ጊዜ እንዲሰጣቸው ሲያመለክቱ፣ የአዲስ ኢንተርናሽናል ካርዲያክ ሆስፒታል ባለድርሻ የሆኑት ተጠርጣሪ ተከሳሽ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ተቃውሞአቸውን ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡
‹‹ጠበቆች እየጠየቁ ያሉት ረጃጅም ጊዜ በመሆኑ እኛ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብታችንን ያጣብብብናል፡፡ የምንፈልገው አጭር ቀጠሮ እንዲሆንልን ነው፤›› በማለት አመልክተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪ ድጋፋቸውን ሰጥተዋቸዋል፡፡
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ ግን የእነ ዶ/ር ፍቅሩን ተቃውሞ በመቃወም፣ ‹‹እኔ ብዙና ሰፊ ክስ አለብኝ፡፡ ጠበቆቼ በደንብ ተረድተውና አብራርተው የክስ መቃወሚያ እንዲያቀርቡ ረዘም ያለ ቀጠሮ ይሰጠን፤›› በማለት ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪ ተከሳሾቹን ማመልከቻ ከሰማ በኋላ ብይን ሰጥቷል፡፡ በሰጠው ብይንም፣ በተጠረጠሩበት የተለያየ የሙስና ድርጊት ወንጀል ክስ ቢመሠረትባቸውም በችሎት ሊቀርቡ ያልቻሉት አቶ ጌቱ ገለቴን ጨምሮ ሌሎችም ግለሰቦች በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ እንዲሁም በችሎት ተገኝተው ክሳቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙትና የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግን ክስ በሚመለከት መቃወሚያ እንዳላቸው ያመለከቱ ተጠርጣሪዎች ለጥር 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ተቃውሞአቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

Thursday, January 16, 2014

ድርድሩ አልተሳካም፡ ተኩስ ተከፍቷል ህዝብ እየተደበደበ ነው

ፖሊሶች አራት የኗሪዎቹ ተወካዮች በሃይል ሲወስዱ የአፅቢ ህዝብም አስራ አራት ፖሊሶችና አንድ ምልሻ አግተው ነበር። ህዝቡ ፖሊሶቹ እንዲለቅ አስተዳደሩ ደግሞ አራቱ ተወካዮች እንዲለቅ ድርድር ተጀምሮ ነበር። በድርድሩ መሃል የወረዳው አስተዳደር አዲስ ሃይል በመጥራት (ከሌላ ወረዳና ከክልል አስተዳደር የፀጥታ ሃይሎች በመላክ) ህዝብ በተሰበሰበብት መተኮስ ጀመሩ (ከምሽቱ 2:30-2:56)። ምልሻዎቹና ወታደሮቹ የታገቱትን ፖሊሶች ለማስለቀቅ እስከ ሁለት መቶ (በኗሪዎቹ ግምት መሰረት) የሚደርስ ጥይት በመተኮስ የታገቱት ፖሊሶችን ማስለቀቅ ችለዋል። እስከ ሁለት ሺ የሚጠጋ ህዝብ ተሰብስቦ እየጨኸ ይገኛል። አሁን (ከምሽቱ ሦስት ሰዓት) ብዙ ምልሻዎች የጫኑ ብዙ መኪኖች ወደ አከባቢው እየገቡ ነው። በሌላ አቅጣጫ (በስተ ሰሜን በኩል) ደግሞ ሌሎች ብዙ መኪኖች እየገቡ ነው (ምልሻ ወይ ፖሊስ ወይ ወታደሮች መሆናቸው ግን በትክክል አይታወቁም)። ህዝብ በዱላ መደብደብ ጀምረዋል። ህዝቡ እየጮኸና ፈጣሪው እየለመነ ነው። የህዝቡ ጩኸትና ለቅሶ በስልክ መስማት ችያለሁ። እያናግሩኝ ያሉ ሰዎችም መረጋጋት ተስኗቸዋል። አሁን ከምሽቱ 3:05 ሁነዋል።
Abraha Desta

በዲሲ መፀዳጃ ቤት የወለደች ሃበሻ” እየሩሳሌም አራአያ


(በፎቶው ዳይሬክተሩ አቶ ዳዊት..)

Sunday, January 12, 2014

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ እና የኢትዮጵያ ምህዳር ጋዜጣ አዘጋጆች ለውሣኔ ተቀጠሩ

በህገመንግስቱ ላይ ህዝብን ለአመጽ በማነሳሳት፣ የህዝብን ሃሳብ በማናወጥ እና “ጨፍጫፊ” በማለት የመንግስትን መልካም ስሙን በማጥፋት የተከሰሰው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ በመከላከያ ማስረጃነት ያቀረበው የቢቢሲ ዶክመንተሪ ፊልም፣ የቢቢሲ ስለመሆኑ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ሲል ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለውሣኔ ቀጥሯል፡፡
ተከሳሹ ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ቢቢሲ ያዘጋጀው ነው በሚል በመከላከያ ማስረጃነት የቀረበው የድምጽ ምስል ዶክመንተሪ ፊልም በእርግጥም የቢቢሲ ስለመሆኑ ጥያቄ በማስነሳቱ ከጣቢያው ሃላፊዎች ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ቀደም ባለው ቀጠሮ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠው፡፡ ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት የተከሳሽ ጠበቃ ለፍ/ቤት እንዳስረዱት፤ ማረጋገጫውን ለማግኘት ከቢቢሲ ሃላፊዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ጠቁመው ለዚህኛው ቀጠሮ ሊደርስላቸው ባለመቻሉ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሠጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን ቀደም ሲል በአቃቤ ህግ የቀረበበትን ማስረጃ ይከላከሉልኛል ያላቸውን የሰው ምስክሮች ለፍ/ቤቱ ከማሰማቱም በተጨማሪ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ መከራከሩ ይታወሳል፡፡
ለፍ/ቤቱ ካቀረባቸው የመከላከያ የሰነድ ማስረጃዎች መካከልም 4 ገጽ ያለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ (ኢሠመጉ) ሪፖርት፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “ኢትዮጵያን አመጽ አያሰጋትም” ሲሉ የሠጡት ቃለ ምልልስ፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት እንዲሁም ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ቢቢሲ በፎከስ ኦን አፍሪካ ያሠራጨውና ፍ/ቤቱ ማረጋገጫ የጠየቀበት ዘገባ ይገኙበታል፡፡ ተከሣሹ ባቀረባቸው የመከላከያ ማስረጃዎች ላይ አስተያየቱን የሰጠውን አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ የቀረቡት ማስረጃዎች ከክሱ ፍሬ ሃሳብ ጋር ግንኙት የላቸውም ብሎ የተከራከረ ቢሆንም ፍ/ቤቱ ሣይቀበለው ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ በቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ላይ ያለውን አጠቃላይ አስተያየት በቀጣዩ ቀጠሮ ለማቅረብ ፍ/ቤቱን ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ፍ/ቤቱም የተከሳሽን የቢቢሲ ዘገባ ማረጋገጫ ለመቀበልና የአቃቤ ህግን አጠቃላይ የማስረጃ አስተያየት ሠምቶ ውሣኔ ለመስጠት ለየካቲት 5 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
በሌላ በኩል ሐዋሣ በሚገኘው የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት፤ የሃዋሣ ዩኒቨርሲቲ የ300ሺህ ብር የፍትሃ ብሔር ክስ ያቀረበባቸው የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ አሳታሚና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ደግነው እንዲሁም ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ ባለፈው ረቡዕ ፍ/ቤት ቀርበው የቃል ክርክር ካደረጉ በኋላ፣ የፍ/ቤቱን ውሣኔ ለመስማት ለጥር 20 ቀን 2006 ተቀጥረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፍ/ቤቱን ሂደት ለመከታተልና ስለዘገባው ማብራሪያ ለመስጠት ወደ ሃዋሣ በሄደበት ወቅት የትራፊክ አደጋ የደረሰበት ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ስለ አደጋው ፖሊስ አዲስ አበባ ድረስ መጥቶ ቃሉን የተቀበለ ሲሆን፤ እስካሁን ግን ክስ እንዳልተመሠረተ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
አዲስ አድማስ

Saturday, January 11, 2014

አቶ ሽፈራው ጃርሶ ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ እስካሁን በህክምና ላይ ይገኛሉ ተባለ

በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው ጃርሶ ከ2 ሳምንት በፊት ባጋጠማቸው ከባድ የመኪና አደጋ የተነሳ እስካሁን በህክምና ላይ እንደሚገኙ የውስጥ አዋቂ ምንጮች ገለጹ።

shiferaw jarso

ከ2 ሳምንታት በፊት በደቡብ ኦሞ አካባቢ እየተገነባ የሚገኝን የስኳር ፕሮጀክትን ለመጎብኘት ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት ወደ ዛው አምርተው እንደነበር የገለጹት ምንጮች በአቶ ሽፈራው ጃርሶ መኪና ላይ በደረሰ አደጋ ባለስልጣኑ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል።

አቶ ሽፈራው ላይ አደጋው የደረሰው በወላይታ አካባቢ እንደሆነ ያስታወቁት ምንጮቹ እንደ አደጋው አሰቃቂነት ሕይወታቸው መትረፉ በራሱ ትልቅ እድል ነው። በአካባቢው ሄሊኮፕተር ተልኮ ወዲያውኑ ወደ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል እንደመጡና ህክምናቸውን በዛው እየተከታተሉ እንደሚገኙ ምንጮቹ ጠቅሰው ባለስልጣኑ እስካለፉት 2 ቀናት ድረስ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ህክምና ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ካለፉት 2 ቀናት ወዲህ ያለውን የአቶ ሽፈራው ጃርሶን ሁኔታ ዘ-ሐበሻ ለማጣራት ሞክራ አልተሳካላትም።
ዘ-ሐበሻ ድረገጽ ላይ የሚከተለው ግጥም የዋልድባ የመታረስ ዜና የተዘገበ ሰሞን ወጥቶ ነበር። ግጥሙን ከትውስታ እዚህ አምጥተነዋል።

ስኳር ገዳም ገባ ምንጭ 

(ዘ-ሐበሻ)