Monday, December 30, 2013

በአዲስ አበባ የቅርብ ጊዜ የጅምላ መቃብር ተገኘ ::የጅምላ መቃብሩ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል!

December 30, 2013

ሁኔ አቢሲኒያዊ
ነገሩ የተከሰተው አርብ እና ቅዳሜ እለት ነው ከስድት ኪሎ ወደ ፈረንሳይ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው የጃንሜዳ ጦር ካምፕ(በቀድሞ ስሙ ሦስተኛ ሻለቃ) ግቢ ውስጥ በትንሹ ወደ 6 የሚጠጉ አስከሬኖች በብርድልብስ እንደተጠቀለሉ ተገኝተዋል! አስከሬኖቹ ሊገኙ የቻሉት ለመንገድ ስራ የጦር ካምፑ ግቢ አጥር ወደ ውስጥ ፈርሶ መቆፈር ነበረበት፡፡ በዚህ ሂደት ላይ ነው እንግዲህ በስካቫተር ሲቆፈር በመጀመሪያ ሁለት አስከሬኖች በብርድልብስ እንደተጠቀለሉ ተንከባለሉ፡፡ በዚህ የተደናገጡት ሰራተኞች ለጊዜው ስራቸን ያቋረጡ ሲሆን በበነጋው ቅዳሜ እለት ረፋዱ ላይ በሌላ አቅጣጫ ቁፋሮ ሲያደርጉ በዛም በኩል እዲሁ በብርድ ልብስ የተጠቀለሉ አራት አስከሬኖች በተመሳሳይ ሁኔታ ከአፈሩ ዉስጥ ተገኙ፡፡A mass grave in Addis Ababa, Ethiopia
በዚህ መሃል ከጦር ካምፑ አካባቢ የተወሰኑ መኮንኖችና ከፍተኛ ማዕረግ(ጄነራሎች)በትከሻቸው ላይ ያለባቸው ሰዎች ወደ ቦታው በመምጣት ስራው እንዲቆም ትእዛዝ ያስተላለፉ ሲሆን በአካባቢው የነበረውንም ሰው ከቦታው አባረው በትነዋል፡፡ በስፋራው ተገኝተው ሁኔታውን ሲከታተሉ እና በስራው ላይም ተሳታፊ የነበሩ ለሰማያዊ ፓርቲ ቅርብ የነበሩ ሰዎች ፎቶ ለማንሳት ጥረት ቢያደርጉም በወታደሮቹ ተመናጭቀዉ ክልከላ ደርሶባቸዋል፡፡ እንደምንጮቻችን እና የምስል ማስረጃዎች ከሆነ አስከሬኖቹ የተጠቀለሉበት ብርድልብስ አንዳችም ሳይቀደድና ሳይበሰብስ ከነአዲስነቱ መገኘቱ ጅምላ ግድያው በቅርቡ የተፈፀመ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ጥርጣሬን አሳድሯል! በጉዳዩ ላይ ማጣራት ለማድረግ ሙከራ ያደረጉት የሰማያዊ ፓርቲ አባሎችንም ፊት እንደተነሳቸውና ለማናገርም ፈቃደኛ የሆነ ሰው አለማግኘታቸዉንም እንዳዉም ቦታውን ባስቸኳይ እንዲለቁ ከሀይለ ቃል ጋር መታዘዛቸውንም ጨምረውተናግረዋል፡፡
ከወታደሮቹ መሀከል የሆነ አንድ ስምና ሀላፊነቱ ለጊዜው ያልታወቀ ምናልባትም የግቢው አዛዥ ሊሆን የሚችል ሰው ይህ ግቢ ሶስት ስርዓቶችን ያገለገለ በመሆኑ የማናቸው እንደሆነ ለማወቅ ባይቻልም ሰዎች በመሆናቸው ክቡር ናቸውና አፈር አልብሷቸው ብሎ ትእዛዝ ሲሰጥ የሰሙ የአይን ምስክሮች ለምንጫችን ስለሁኔታው አስረድተዋል! በሁኔታው በአካባቢው የነበሩ ሰዎች በእጅጉ ያዘኑና የተደናገጡ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላትና መንግስት ይህን ጉዳይ አጣርተው ለህዝብ ይፋ እንዲሆን አስተያየት ሲሰጡም ተደምጠዋል! በአሁኑ ሰዓት በስፍራው ምንም አይነት የስራ እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ አካባቢውም በቆርቆሮ ተከልሏል፡፡
ተጨማሪ ብርድልብሱ ደብረ ብርሃን ሲሆን ዲዛይኑ በኢህአዲግ ዘመን በቅርብ የተጀመረው ነው!
ምንጭ ሁኔ አቢሲኒያዊ ከፒተርቦሮው ዩ.ኬ  ( በ ታምራት ይፈጎ )

ከሳውዑዲ አረቢያ በግፍ ተገፍተው ለተመለሱ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ምን እየተደረገ ነው? (በይበልጣል ጋሹ)

በይበልጣል ጋሹ

የተለያዩ የዜና ምንጮች እንደገለጹት ከሳውዑዲ አረቢያ በግፍ ተገፍተው የተመለሱ ኢትዮጵያን ቁጥር ከመቶ ሺ በላይ ደርሰዋል። አሁን በዋናነት ማንሳት የፈለኩት ስለ ቁጥር መጠናቸው ትክክለኛነት፣ ያሳለፉትን ስቃይና መካራ፣ ማን በአስቸኳይ ደረሰላቸው ወይም በምን መልኩ ትውልድ ሀገራቸው ተመለሱ የሚለውን የትናት ገሀዳዊ እውነታ መተረክ ሳይሆን ለእነዚህ ወገኖቻችን ምን እየተደረገላቸው ነው የሚለውን ጥያቄ አዘል ሃሳቤን ለማካፈል ነው።

ለእነዚህ ለተጎዱ ወገኖቻችን በህብረትና በግል የውስጥ ሃዘናችንን በእንባ፣ በልቅሶ፣ በጩኸት የዓለም ጀሮ በቃኝ እስኪል ድረስ ገልጸናል፤ ተናግረናል፤ ጽፈናልም። መቼም ቢሆን ሀዘኑና ድርጊቱ ከልባችን አይጠፋም። ይህ በራሱ አንዱ የአንድነታችን መገለጫ ነው። ይህን አንድነታችንንና ሃዘናችንን ወደ ተግባር ቀይረን ማሳየት ብንችል የበለጠ ለእኛ ለህሌናችን ውስጣዊ እርካታ፤ ለተጎዱ ወገኖቻችን ደግሞ መጠገኛ/መቋቋሚያ ይሆናቸዋል።
በእርግጥ ድርጊቱ ከተፈጸበት ጊዜ ጀምሮ በተለያየ መልኩ ከግለሰብ እስከ ተለያዩ ማህበራት ድረስ እርዳታ ለመስጠት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ይህ ጥረት ግን ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ሁላችንም ልዩ ትኩረት ልንሰጥበት የሚገባ ተግባር ነው። እንዴትና በምን መልኩ ለወገኖቻችን ልንደርስላቸው እንደ ሚገባ በግልጽና ታማኒነት ባለው መልኩ እንቅስቃሴያችንን ማስኬድ ይኖርብናል። ለዚህ ተግባር ግልጽነትና አንድነት ተግባራዊ የሆነ ሥራ ለመስራት በእጅጉ ያስፈልጉናል።
  ሀ. አንድነት፦ ለዚህ በጎ ተግባር ድጋፍ ለማድረግ ሰው መሆን ብቻ በራሱ በቂ ነው። ችግሩን በትክክል ለተገነዘበ ሰው ሌላ የተለየ ቅስቀሳ አያስፈልገውም። በተለይ ደግሞ  በውጭው ዓለም ያለ ሰው በአንድም በሌላም የችግሩ አካል በመሆኑ ለዚህ ተግባር ግንባር ቀደም ድጋፍ ሰጭ እንደሚሆን እርግጠኛ ሁኖ መናገር ይቻላል። አስተባባሪ አካላት ግን መንግስት፣ ተቃዋሚ፣ ጾታ፣ ብሄር፣ ሃይማኖት፣ ድርጅት፣ ማህበር ፣ የውጭ የውስጥ ብሎ ልዩነት ሳይፈጥሩ በአንድነት ማስተባበር ከቻሉ በቀላሉ ተጎጅዎችን ማቋቋም የሚቻልበትን መስመር መዘርጋት ይቻላል።  ይህ ችግር ሃገራዊ እንጂ የአንዱን ቡድን ብቻ የሚመለከት አይደለም። ቢሆንም እንኳ ከጠባብነት የአስተሳሰብ ጎራ ተላቀን ለዚህ በጎ ተግባር አንድነት መፍጠር ይኖርብናል። ይህን ችግር ምክንያት አድርጎ ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ የተለየ ጥቅም ለማግኘት መሞከር ደግሞ ከሰባዊ ነት ወደ እንስሳዊነት ባህሪ የመቀየርን ያክል አሳፋሪ ይሆናል።  ስለዚህ ሁላችንም በተለይ አስተባባሪ አካላት በመካከላችን የቱንም ያህል ልዩነት ቢኖርም ለዚህ አንገብጋቢ ተግባር ከማነኛውም ሰው ጋር በቅንጅት ድጋፍ ለማድረግ መወሰን እና መስራት ይኖርብናል።
  ለ. ግልጽነት፦ በዚህ በአለንበት ዘመን የቱንም ሥራ ለመስራት ግልጽነት ያስፈልጋል። ግልጽነት የጎደላቸው ተግባሮች ሁሉ ውጤታቸው እዚህ ግባ የባይባል ነው። ለዚህ በጎ ተግባር ገንዘብ ከመሰብሰብ ጀምሮ እንዴትና በምን መልኩ ለተቸገሩ ወገኖቻችን ሊደርሳቸውና ምን አይነት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደታሰበ በግልጽ ለእኛንዳንዱ ህብረተሰብ መንገር ያስፈልጋል። ግልጽ መሆናችን 3 ጥቅሞች አሉት። አንድ ድጋፍ የሚሰጡ ሁሉ ከፍራቻ፣ ከጥርጣሬ እና ከሌላ እይታ አልፈው የተቻላቸውን ያክል ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ያደርጋል። ሁለት ለአስተባባሪዎችም ሆነ ገንዘብ ለሚሰበስቡት ሁሉ ታማኝነት ያገኛሉ። ነጻ ሁነው ማንኛውንም ሰው ለዚህ ድጋፍ ተባባሪ እንዲሆን መጠየቅ ይችላሉ። ሦስት ድጋፍ የሚደረግላቸው ወገኖች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ምክንያቱም በግልጽነት የምንሰበስበው የገንዘብ መጠን የተሻለ እና የታሰበውን ፕሮጀክት መሸፈን የሚችል በቂ ገንዘብ መሰብሰብ ስለሚቻል ነው። ግልጽነትን ካለምክንያት አላነሳሁትም ለዚህ ድጋፍ ተብሎ አገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የተለያዩ ተቋማትና ግለዘቦች ገንዘብ ለመሰብሰብ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። እየሰበሰቡ ያሉም አሉ። ነገር ግን ገንዘብ ከመሰብሰብ ውጭ እንዴት፣ በምን መልኩ እና ግንኙነቱ ከማን ጋር የሚሉ መሰረታዊ ጥያቂዎችን በግልጽ ለማወቅ አልተቻለም። ስለዚህ ለእነዚህ እና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ግልጽነታችን በጣም አስፈላጊ ስለሚሆን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በግልጽነት ማካሄድ የሚቻልበትን መስመር ዘርግቶ መንቀሳቀስ ከምንም በላይ ትኩረት ልንሰጥበት የሚገባ ተግባር ነው።
ከላይ ያነሳኋቸውን መሰረታዊ ነገሮች አንድነትን እና ግልጽነትን ሰንቀን ድጋፋችን ዘላቂነት ያለው ይሆን ዘንድ ኃላፊነቱን ደረጃ በደረጃ መውሰድ ይኖርብናል።
  1. 1.      መንግሥት፦  ምንም እንኳ አስተዳደራዊም ሆነ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች በአገሪቱ ውስጥ ቢሰፍኑም ለዚህ ችግር ግንባር ቀደም መፍትሄ ሊሰጥ የሚገባው አካል መንግሥት ነው። ይህን ማድረግ አልነበረበትም? የችግሩ መንስኤ መንግሥት ራሱ ነው? እና ሌሎችንም ጥያቄዎች በትችት መልክ ሁልጊዜ ማንሳቱ ለውጥ ሊያመጣልን አልቻለም። በእርግጥ በተለያየ መልኩ አቅጣጫ የሚያሳዩ ኢትዮጵያውያን ሙህራን በርካታ ናቸው። ምናልባት አብዛኞቹ ከትችት ስለሚጀምሩ ሃሳባቸውን ላለመቀበል ምክንያት ሊሆን ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን ጠቃሚ ሃሳቦችን መውሰድ ብልህነት ነው።
መንግሥት ቢያንስ በግፍ ወደ ሃገራቸው ለተመለሱ ወገኖች ዘላቂነት ባለው መልኩ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል። በአጭሩ ሦስት ተግባራትን መከተል ቢቻል ዘላቂነት ያለው ድጋፍ ማድረግ ይቻላል።
  • ወደ አገር የተመለሱትን ስም ዝርዝርና በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉበትን አድራሻ መያዝና ስለ እያንዳንዱ በቂ መረጃ መሰብሰብ(የት/ት ደረጃ፣ የሥራ መስክ፣ የቤተሰብ ሁኔታ፣ ፍላጎት)። ከምንም አድሎአዊነት ነጻ ሁኖ በትክክል እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ማወቅና መለየት።
  •  በሰበሰብነው መረጃ መሰረት ሁሉን ሊያካትት የሚችልና ዘላቂ ፕሮጀክት መቅረጽ። ለምሳሌ፦ ለውጭ ባለ ሃብቶች የምንሰጠውን መሬት ማለትም የእንስሳት ልማት፣ የአበባ ልማት፣ እና የተለያዩ የንግድ ሥራወችን  ዘመናዊ በሆነ መልኩ ሊሰሩ የሚችሉበትን እድል ማመቻቸት። እንዲሁም መማር ለሚፈልጉ ነጻ የትምህርት እድል መስጠት።
  •   ፕሮጀክቱ ዘላቂነት እንዲኖረው እና ትርፋማ ሁኖ በትክክል ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል የባለሙያ ድጋፍና ክትትል እንዲያገኝ ማድረግ። 

  1. 2.   ማህበራትና ተቋማት፦ ሊታይና ሊቆጠር የሚችል ፕሮጀክት ቀርጾ ገንዘብ መሰብሰብ። ፕሮጀክቱ የት፣ ለእነማንና በምን መልኩ ሊተገበር እንደሚችል ይፋ ማድረግና ገንዘብ ሊገኝ ከሚችልባቸው የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶች፤ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ መሰብሰብ። ለዚህ ተግባር ይመለከታቸዋል ከምንላቸው ድርጅቶች ጋር በቅንጅት መስራት ድጋፋችንን ዘላቂነት እንዲኖረው ያደርግልናል።
በተለይ በውጭው ዓለም ገንዘብ ከመሰብሰብ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ በተለያየ መልኩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ይህን እንቅስቃሴ ተግባራዊ ለማድረግ አገር ውስጥ ከአሉ ድርጅቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ማድረግ እና በውጭ በተለያዩ  ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ዘላቂነት ባለው መንገድ የሰባዊ መብት ጥሰትን ማስቆም የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ትልቅ ተግባርና ሃላፊነት ነው።

  1. 3.   ባለሙያዎች፦ ለዚህ በጎ ተግባር ዘላቂነት ያለው ፕሮጀክት ከመቅረጽ ጀምሮ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ በራስ ተነሳሽነት ለሚመለከታቸው አካላት ሃሳባችንን ማካፈል። ሁሉም የሙያ ዘርፍ በተለያየ መልኩ ስለሚያስፈልግ እኔ አላስፈልግም ሳንል ለወገኖቻችን ድጋፍ መስጠት ከቻለን በቀላሉ ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት የሚቻልበትን አማራጮች ማስቀመጥ ይቻላል።

በአጠቃላይ በግፍ ወደ ሃገራቸው ለተመለሱትም ሆነ በዓለም ላይ ኢ_ሰባዊ ድርጊት የሚፈጸምባቸውን ኢትዮጵያውያንን ለመታደግ የእያንዳንዳችን ድርሻ ወሳኝ መሆኑን ተረድተን ዜጋዊ ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል። የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ኢ_ሰባዊ ድርጊቶችን ማስቆም የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆን ይኖርበታል የሚል ጽዕኑ እምነት አለኝ። ኮሚቴ ማቋቋም ብቻ ትርጉም የለውም። እንዲህ ሰሩ ለመባል ሳይሆን ተግባራዊ ስራ ሰርተን አገራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ

የሚያሣዝነው በዚህ በጐሣ በተከፋፈለ ከለላና አስተዳደር ምክንያት የተፈጠሩት ጥላቻዎች ማርከሻ መድሃኒት ማጣታቸው ነው፡፡


“የራበው ሥራ ፈልጐ ማግኘት የማይችልና ልጆቹን ለማስተማር አቅም ያጣ ሰው ከባርነት ነፃ ነው ማለት አይቻልም፡፡” የሚለው የአሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ. ጆንሰን ንግግር እውነትነት አሁን አሁን በጆሮዬ መደወሉ ራሴን እያስገረመኝ መጥቷል፡፡ የዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት ገደማ ደራሲና ጋዜጠኛ አለማየሁ ገላጋይ፤ ስለኑሮ ውድነት ሲጽፍ ብዙዎቻችን እያነበብን ፈገግ ከማለት በቀር ብዙ ልባችን አልተነካም ነበር፡፡ ምናልባትም በጣም አልፎ አልፎ ከምናነባቸው መጣጥፎች ይልቅ መንግስት ስለ ልማት የሚነፋው ጥሩንባ አደናቁሮን ይሆናል፡፡ አሁን አሁን የመንግሥት መዝገበ ቃላት “ልማት” የሚለው ትርጓሜ ግራ እያጋባን መጥቶ ጭራሽ ወደ ብስጭት የተመነዘረብን ብዙ ነን ብዬ አስባለሁ፡፡ መንግስት ልማት የሚለው ከእኛ አፍ “ቫት” እያለ የሚነጥቃትን ገንዘብ ሰብስቦ ለሌቦች ካጠገበ በኋላ፣ በፍርፋሪዋ የሚሠራትን መንገድና ጤና ጣቢያ ወይም ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ “ኮንደሚኒየም”
እየተባሉ የተሠሩት ቤቶች አካባቢ ያለውን ግድየለሽነት ተመልከቱ፡፡ የውሃ መፍሰሻ ቦዮቹ ገና ተሠርተው ሳያልቁ ይፈርሣሉ። ሕንፃው ውስጥ ያሉትን የግብር ይውጣ ሥራዎች ተውአቸው፡፡ ለመሆኑ ልማትና ዕድገት ምንድነው? ወረቀት ላይ የሃሰት ሪፖርቶችን ከምሮ መቀለድ ነው። ቀልድና ውሸትስ እስከ የት ያዘልቀናል? ከወር ወደ ወር ሰዎች በልተው የማደር አቅማቸውን እያጡ፣ ልጆቻቸውን ማስተማር ተራራ መቧጠጥ እየሆነባቸው ሲመጣ — እንዴት ስለ ዕድገት ይወራል? ጋዜጠኛ መሳይ ካድሬዎች ስለልማትና እድገት ብዙ ቢለፈልፉም ከሕዝቡ የበለጠ ጓዳውን የሚያውቅ ማንም ሊኖር አይችልም፡፡ አለ ቢባልም ከተራ ቀልድነት አያልፍም፡፡ እርግጥ ነው፤ ባለፉት ሃያ ዓመታት ጥቂት ሰዎች በኑሯቸው አድገው ይሆናል፤ ለስላሳ መጠጣት የማይችሉ ዛሬ ቤታቸው ውስኪ ደርድረው የሚመርጡበት ዕድል ደርሷቸው ይሆናል፡፡
ያ ግን ዕድገት አይደለም፡፡ የማሕበረሰብ ሳይንስ ምሁራን የዕድገትና ልማትን ዓላማዎች እንዲህ ያስቀምጡታል – የሕዝቡን የገቢ መጠን በፍጥነት ማሳደግ ለዜጐች የሥራ ዕድልን መፍጠር መሠረታዊ የሆኑ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጐቶችን ማርካት፤ ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን ሥራንና የቁጠባ ባህልን በሕብረተሰቡ ማስረጽ መልካም አስተዳደርና አሣታፊ የሆነ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ተጨማሪ ነጥቦች የአንዲት ሀገርንና ሕዝብን ዕድገት መንገድ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በሀገራችን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ከዚህ በተቃራኒ የቆመ ይመስላል፡፡ ምናልባት የማይካድ ለውጥ አምጥቷል ብለን የምንወስደው ሕብረተሰቡ በሥራ ላይ ያለውን አመለካከት በመጠኑ መቀየር መቻሉ ነው፡፡ ቁጠባውንም በውድም ሆነ በግድ በየሰበቡ ለማስለመድ የሚደረገው ጥረት የሚናቅ አይደለም፡፡ የፖለቲካው አሣታፊነት ጉዳይ የሕፃን ልጅ ዕቃ ዕቃን የመሰለ ቀልድ ስለሆነ ጉዳዩ ለሰለቸው አንባቢ ይህን አንስቶ እንዲህና እንዲያ ማለት እንደ ደንቆሮ መቁጠር ሊመስልብኝ ይችላል፡፡ ጠቃሚ ባህሎችን ማሳደግ በሚለውም መሥመር እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ (በመንግስት መሠረት) ሥነ ጽሑፉንና ባህሉን ማሳደጉን እኔ በግሌ እደግፈዋለሁ፡፡ ልክ ነው ብዬም አምናለሁ፡፡ አንዱ በባህሉ እየኮራ፣ ሌላው እያፈረ የሚደበቅባት ሀገር አሁንም እኩልነት የጐደላት ስለሆነች ያንን ሕልም ማለም ጠባብነት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የሚያሣዝነው ግን በዚህ በጐሣ በተከፋፈለ ከለላና አስተዳደር ምክንያት የተፈጠሩት ጥላቻዎች ማርከሻ መድሃኒት ማጣታቸው ነው፡፡ መሪዎቻችን በወጣትነት መንፈስ በስሜታዊነት ያደረጉትን ነገር ምራቅ ሲውጡ እንኳን ለማስተካከል ያለመቅናታቸው የሚገርም ነው፡፡ ለዚህ ሃሳብ ዋቢ የሚሆነኝን አንድ ሃሳብ ወደኋላ መለስ ብዬ ሕዳር 18 ቀን፣ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በዶክተር እሸቱ ጮሌ አዳራሽ፣ ለዶ/ር ፋሲል ናሆም (ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ) ያቀረበውን ጥያቄ ልጥቀስ፡፡
ተማሪው የተወለደበትን ክልል ጠቅሶ፣ በክልሉ ዋና ከተማ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች ሀገራቸው እስከማይመስላቸው ድረስ በደል እየተፈፀመባቸው እንደሆነ ገልፆ፣ መንግስት ለ “minority” ምን መፍትሔ አለው ሲል ጠይቆ ነበር፡፡ በሌላ አንፃር ደግሞ ያ ተማሪ እኖርበታለሁ ወይም ተወልጄበት ግን የዜግነት መብት አላገኘሁም የሚልበት ክልል ተወላጅ የሆነ ሌላ ተማሪ ተነስቶ፣ ችግሩ የሚታየው የቀደመው ተማሪ በጠየቀበት ክልል ብቻ ሣይሆን በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች መሆኑን ጠቅሶ፣ ሥራ ለመቀጠርም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ዘር መቁጠር ግድ ስለሆነ፣ ችግሩን መፍታት ያለብን ሁላችንም ነን ብሎ ደመደመ፡፡ እኔ ግን በሁለተኛው ተማሪ ሃሳብ አልስማማም፤ ችግሩን ለመፍታት እኛ ድርሻ ቢኖረንም የአንበሳው ድርሻ ግን የመንግስት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ለዚህ ነቀርሣ መፍትሔ መፈለግ አለበት፤ ሰው በገዛ ሀገሩ ባዕድ እየሆነና እየተገፋ መኖሩ የሚያመጣው ልማት ፈፅሞ ግልጽ አይደለም፡፡ ለመሆኑ መንግስት ማለትስ የሰዎች ስብስብ አይደለም እንዴ? እንዴት ይህንን ነገር ማሰብ ያቅተዋል? ባለሥልጣን ሲኮን ተከትሎ የሚመጣው አጃቢ ወታደር፣ ያበጠ ወንበር— የነገን ጉዳይ ያዘናጋልና መሪዎቻችንም ሊያስቡበት የሚገባ ይመስለኛል። አብዛኛው ሕዝባችን ከእጅ ወደ አፍ እንኳን ኑሮ እያቃተው ከመጣ፤ የመኖር ዕድሉ እየጠበበ ከሄደ ሊፈጠር የሚችለው ነገር ምንድነው ብሎም ማሰብ ደግ ይመስለኛል፡፡ የኢሕአዴግ አማካሪዎች ምናልባት እውነት የማይናገሩ አሸርጋጆች እንዳይሆኑ እሠጋለሁ። ሕዝቡ እየተራበ “ጠግቧል”፣ እየተማረረ “ደስተኛ ነው” እያሉ ከሆነ ፍፃሜው አያምርም። በርግጥ እኛ ሥልጣን የሌለን አስበን ምንም አናመጣም፣ ሥልጣን ያላቸው ናቸው ለችግሩ መቋጫ መፍትሄ ሊያበጁለት የሚገባቸው፡፡
አዲሱም ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ ሁልጊዜ የታላቁ መሪያችንን መዝሙር ከመዘመር ይልቅ አዲስ መዝሙርና ራዕይ ለመፍጠር መሞከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቶማስ ጀፈርሰን፤ ሁሉም ሰው የየራሱ ዘመን አለው፣ በሕይወት የሌለ ሰው በሕያው ሰው ዘመን ሊወስን አይችልም እንደሚል፣ አሁን ያለውን ኑሮና ሕይወት የማያዩት የቀድሞው መሪያችን ራዕይ ሊያዘልቀን ይችላል ብሎ ማመን ያስቸግራል፡፡ ርግጥ ነው ያስጀመሩትን ግድብ ማጠናቀቅ፣ የባቡሩን ሥራ መፈፀም፣ ወዘተ ጥሩ ነው። ግን በጤፍ ዋጋ፣ በስኳርና በትራንስፖርት ጉዳይ ያለውን ጣጣ ዛሬ ቢያዩ፣ እሳቸውም ደንግጠው ጭንቅላታቸውን ይይዙ ነበር፡፡ በዓመት ውስጥ ለአንድ የሆቴል ተመጋቢ ቢያንስ ሦስቴና አራቴ ዋጋ ይጨምርበታል፡፡ ታዲያ ሆዱ ባልጠገበ ሲቪል ሠራተኛ ተሠርቶ፣ ሀገርን ማሳደግ ይቻላል እንዴ? ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ሕልም ያልሙ እንጂ — አዲስ ራዕይ ያምጡ! የስነ አመራር ምሁሩ ጆን ሲ ማክስዌል እንደፃፉት፤ በየዓመቱ ዶሮዎቹን የክረምት ጐርፍ የሚወስድበት ዶሮ አርቢ፣ ሁልጊዜ በዶሮ ላይ የሙጢኝ ማለት የለበትም፤ ይልቅስ ጐርፉ ላይ ዋኝቶ አልፎ ሀብት የሚሆን ዳክዬ የማርባት ጥበብና ዘዴ ሊኖረው ይገባል። መቼም መንግስታችን ሁልጊዜ በሕይወት በሌሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ መንጠልጠል ያለበት አይመስለኝም፤ እሳቸው በጊዜያቸው የሚሰሩትን ሰርተው አልፈዋል፡፡ አሁን ተራው የሥልጣን ወንበሩ የተሰየሙት ሰውዬ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ. ጆንሰን እንዳሉት፤ ድሀና ሀብታም በጠብደል ግድግዳ ሲለይ ጥሩ አይደለም። ይልቅስ ግድግዳው የመስተዋት ነውና በኋላ የሚያመጣው መዘዝ መጥፎ ነው፡፡ ከፊሉ በሌብነት እየበለፀገ፣ ሌላው በጨዋነት እየተራበ – ለዘላለም – አይኖርምና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ዶክተር መረራ ጉዲና እንደሚሉት፤ የራበው ሕዝብ – መሪውን ለመብላት እንዳይነሣ – ካሁኑ ማሰብ የግድ ይላል፡፡ ጆንሰን – “There are two courses open to us. We can master the problem, or we can leave it to master us” ብለዋል – የኛም ምርጫ ይኸው ነው። አዲዮስ!
ምንጭ ፡አዲስ አድማስ
posted by Aseged Tamene

Sunday, December 29, 2013

በሰሜን ሸዋ ዞን ሞተዋል ተብለው ፍታት ሲደረግላቸው የነበሩት አዛውንት ከሞት ነቁ


አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 18 ፣ 2006 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሲያ ደብር ዋዩ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት የ65 አመቱ አዛውንት አቶ ሃይሉ በልሁ ከቀናት ህመም በኋላ ታህሳስ 16 ቀን 2006 ዓ.ም ህይወታቸው አልፏል ። የቅርብ ወዳጅ ዘመድ እስኪሰበሰብ ድረስም ቀብራቸው እንዲዘገይ ይደረጋል።
በአካባቢው ባህል መሰረትም ከ18 ሰዓታት ቆይታ በኋላ በባህሉ መሰረት የቤተክርስቲያን ካህናት ተገኝተው ፍታት ያደርጉላቸዋል፥ ይሁን እንጅ በዚህ ጊዜ ያልተለመደ እና እንግዳ ነገር ይከሰታል። ይኸውም ካህናቱ የሟች አስክሬን ባለበት ሳጥን ውስጥ የሰው ድምጽ እንደሰሙ በመናገር ሳጥኑ ይከፈት ዘንድ ያዛሉ።
ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይም ሞተዋል የተባሉት አዛውንት ያሉበት ሳጥን እንዲከፈት ሲደረግ፥ አቶ ሃይሉ በህይዎት ነበሩ ። ህይዎታቸው አልፏል ተብለው ለቀብር የተዘጋጁት አቶ ሃይሉ ግንዛቱን ፍቱልኝ በማለትም የሚጠጡት ውሃ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።
ለለቅሶ የተሰበሰበው ቤተ ዘመድም በውሃ ፈንታ አጥሚት በማዘጋጀት ከሰጧቸው በኋላ አቶ ሃይሉ ደህና መሆን ችለዋል። አዛውንቱን ለመቅበር የተሰበሰበው ዘመድ አዝማድም በደስታ ተለያይቷል።
መረጃውን የሲያ ደብር ዋዩ ወረዳ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አድርሶናል።

ቴዲ አፍሮ ለአድናቂዎቹ ስለተሳሳተው የመጽሔት ቃለምልልስ ምላሽ ሰጠ


በሃገር ቤት የሚታተመው እንቁ መጽሔት የቴዲ አፍሮን ቃለምልልስ በተሳሳተ ርዕስ ማውጣቱን ተከትሎ በርካታ ውዝግቦች ተከስተው ቆይተዋል። መጽሔቱ እርማት የሰጠ ቢሆንም አንዳንድ ወገኖች ግን የተሳሳተውን የመጽሔት የሽፋን ገጽ በማየት መነጋገሪያ አድርገውት ቆይተዋል። ቴዲ በዚህ ጉዳይ ላይ ለአድናቂዎቹ በፌስቡክ ገጹ በአማርኛ እና በ እንግሊዘኛ ቋንቋ ምላሽ ሰጥቷል። እንደሚከተለው ይነበባል።
ለሙዚቃ አፍቃሪዎቼ በሙሉ
ከጥቂት ሳምንት በፊት የዳግማዊ ሚኒሊክን መቶኛ አመት የሞት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ በእንቁ መጵሔት ተጋብዤ ቃለ ምልልስ አድርጌአለሁኝ። ይሀዉ ዉይይታችን በ “አመጣጡን ያየ አካሄዱን ያዉቃል “ እርዕስት ስር ለህዝብ እንደቀረበ አዉቃለሁ። ከዚህ ዉጪ እኔ በማላዉቀዉ ሁኔታ መፅሔቱ በሰራዉ ስህተት ፎቶዬን በሌላ አነጋገር አጅቦ ያወጣዉ ከኔ እምነትም ሆን ጉዞ ጋር የሚራመድ ጉዳይ አይደለም። ይህንኑ ለማረጋገጥ “አመጣጡን ያየ አካሄዱን ያዉቃል” በሚል ርዕስ ስር በወጣዉ መፅሔት መልክቶቼን በማየት ማረጋገጥ ይቻላል። ያም ሆኖ መፅሔቱ በሰራዉ ስህተት እርምት አድርጎ ይቅርታም ጠይቆናል። ጉዞዬ የፍቅር የአንድነት እና የይቅር ባይነት ነዉና ይህንንም ጉዳይ በዚሁ ስሜት ውስጥ እናስተናግደዋለን።
ፍቅር ያሽንፋል!
ቴዎድሮስ ካሳሁን
To lovers of my music;
A few weeks ago I gave an interview to Enqu magazine in relation to the memorial marking the 100th year since the death of Menelik II.
I know that this interview was presented to the public under the title “Ametatun yaye akahedun yawkal.” However, under circumstances unbeknownst to me and due to the error of the magazine, my photo was printed along side a different quote which is not in line with my belief or journey.
As proof of this, one can refer to my message contained in the article titled “Ametatun yaye akahedun yawkal,” in the magazine article. The magazine has issued a correction and apologized to us for its error.
As my journey is one of love, unity and closeness/togetherness, we will handle this issue with the same emotion/ principle/sentiment.
Love will triumph”
Tewodros Kassahun.
 Source Zehabesha

Saturday, December 28, 2013

ንግድ ምክር ቤቶቹ ወዴት?

ንግድ ምክር ቤቶቹ ወዴት?
የንግድ ምክር ቤቶች ምሥረታ ታሪክ የሚጀምረው ከአዲስ አበባ ነው፡፡ 1947 .አካባቢ በአዲስ አበባ የነበሩ የውጭና የአገር ውስጥ ነጋዴዎች የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ማኅበር በሚል ስያሜ የጀመሩት እንቅስቀሴ የንግድ ምክር ቤቶች ምሥረታ ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ 
በወቅቱ በንግድ ሥራ በተለይ በዘመናዊ በሚባል የንግድ አሠራር ይንቀሳቀሱ የነበሩት የውጭ ኩባንያዎች ስለነበሩ ከማኅበርተኞችም ብልጫ ይይዙ የነበሩት  እኚሁ የውጭ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ የማኅበሩ የመጀመርያ ፕሬዚዳንትም በመሆን የተሰየሙት የውጭ ዜግነት ያላቸው ግለሰብ እንደነበሩ ይነገራል፡፡
ከዚህ በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንግድ ምክር ቤት አስፈላጊነቱን በማመን ለማኅበሩ እውቅና በመስጠት የራሱ የሆነ ሕንፃ እንዲኖረው አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች አመሠራረትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ 
ምክር ቤቶቹ በተለያዩ አደረጃጀት 69 ዓመታት ዘልቀዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድ ታክሎበት ዛሬ ሜክሲኮ አደባባይ የሚገኘውን ባለ ሰባት ፎቅ ሕንፃ ለመገንባት ተችሏል፡፡
በወቅቱ 1.8 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሕንፃ ከተገነባ በኋላ የአዲስ አበባም ሆነ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች የራሴ የሚሉት ተጨማሪ ሕንፃ መገንባት ሳይችሉ 70 ዓመታት ሊደፍኑ ነው፡፡ 
65 ዓመታት በፊት የተገነባው ሕንፃ በደርግ ተወርሶ ድጋሜ ለንግድ ማኅበረሰብ የተመለሰው 1999 .ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሕንፃው የባለቤትነት ጉዳይ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች ሲያወዛግብ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የመንግሥት እገዛ ቢኖረውም ጥቂት አባላትን ይዞ 65 ዓመታት በፊት የነበረው የንግድ ኅብረተሰብ ሕንፃ ለመገንባት ችሏል፡፡ አሁን ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ አባላትን የያዘው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትም ሆነ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ሌሎች ንግድ ምክር ቤቶች በተናጥልም ሆነ በጋራ የራሴ የሚሉት ሕንፃ ለመገንባት ሐሳብ ማፍለቅ ከጀመሩ ገና አንድ ዓመት እንኳን አልሞላውም፡፡ 
በንጉሡ ዘመን የንግድ ምክር ቤት አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እንደ ቀድሞው የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ክቡር ገና ገለጻ፣ በአፄው ዘመን የነበሩ የንግድ ምክር ቤት መሪዎች የተመረጡት በራሳቸው የሥራ ደረጃና በሥራቸው ያገኙት ውጤት ተመዝኖ ነበር፡፡ ምርጫ የሚባልም ነገር አልነበረም፡፡ የሚተዋወቁ ይጠራሩና የተሻለው እንዲመራ ይደረጋል፡፡
በደርግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ ቀደም ብሎ የነበረው አሠራር ተቀይሮ እያንዳንዱ ነጋዴ የምክር ቤቶቹ አባል የሚሆነው በግዳጅ ሆነ፡፡ የንግድ ፈቃድ የሚያወጣ ነጋዴ ፈቃዱን በእጁ ያስገባ ዕለት የንግድ ምክር ቤቱ አባል ይሆናል፡፡ ለአባልነት የተጣለበትን ዓመታዊ መዋጮ ይከፍላል፡፡
አባልነቱ በፍላጐት ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ የአባላቱ ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም፣ የንግድ ምክር ቤቶቹ እንቅስቃሴ ከአንድ መንግሥታዊ ተቋም ብዙም ባልተለየ የሚጓዝና፤ አባላቶችንም ለመደገፍ የሚደረግ ሥራ አልነበረም፡፡ ‹‹ምርጫ ስለመኖሩም እጠራጠራለሁ›› የሚሉት አቶ ክቡር፣ ፍላጐት በመቅረቱ የግል ዘርፍ አለ ብዬ ለመናገር ስለማልችል በደርግ ዘመን የንግድ ምክር ቤት በስም የነበረ ብቻ ነው ይላሉ፡፡
አገሪቱ ትከተል የነበረው የሶሻሊስት ሥርዓት በመሆኑ፣ የንግድ ምክር ቤቶች ዓላማና ግብ ከሥርዓቱ ጋር የተሳሰረ ነበር፡፡ ትክክለኛውን የንግድ ምክር ቤቶች ክንዋኔዎች ያልተገበሩበት ወቅት እንደነበር ተደርጐ ይወሰዳል፡፡
ከደርግ ውድቀት በኋላ ግን የነፃ ኢኮኖሚና ገበያ ሥርዓት በመታወጁ የንግድ ምክር ቤቶች በተወሰነ ደረጃ ዓይናቸው ተገልጧል፡፡ በቀድሞ ሥርዓት አባልነት በግዴታ ይሆን የሚለው ድንጋጌ ተሽሮ አባልነት በፈቃደኝነት ላይ መመሥረት አለበት ወደሚለው አሠራር ተገባ፡፡ የአገሪቱ የንግድ ምክር ቤቶች እንቅስቃሴ ሲወሳ ቀድሞም ሆነ አሁን በግንባር ቀደምትነት የሚቀጠሰው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ስለነበር ከደርግ ውድቀት በኋላም የተሻለ የሚባል ነበር፡፡ በተለይ 1988 .አካባቢ ጀምሮ አዳዲስ ነገሮች መታየት ጀመሩ፡፡
ንግድ ምክር ቤቱን የሚመሩ አዳዲስ አመራሮች ብቅ አሉ፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ ታሪክ ዘመናዊ የሆነ የንግድ ምክር ቤቶች እንቅስቀሴ የታየው ወይም ከዓመታት በኋላ ንግድ ምክር ቤቶች እንደ አንድ ወሳኝ ተቋም መታየት የቻሉት 1988 .አካባቢ ነው፡፡ 
ምክር ቤቱን ወደ ላቀ ደረጃ እናሸጋግራለን ብለው በፈቃደኝነት ጭምር ወደ አመራር ከመጡት ግለሰቦች መካከል አቶ ክቡር ገናና አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ይጠቀሳሉ፡፡ በቦርድ አባልነት ለማገልገልም እንዲሁ ከጊዜው ጋር ሊራመዱ የሚችሉ የንግድ ኅብረተሰቡ አባላት በቦርድ ውስጥ ተካትተዋል፡፡
በወቅቱ ለንግድ ምክር ቤቱ እንግዳ ሆኖ የነበረው አዳዲሶቹ የምክር ቤቱ አባላት ወደ አመራር ለመውጣት የፈጠሩት አዲስ የምርጫ አካሄድ ነበር፡፡ ምክር ቤቱን እናገለግላለን በማለት የቀረቡት እነዚህ ግለሰቦች፣ ከዚህ ቀደም ከተለመደው አሠራር ውጭ በፕሬዚዳንትነት ለመመረጥ እንዲህ አደርጋለሁ፣ እንዲህ እሠራለሁ ብለው በመቀስቀስ ወደ ምርጫ ገቡ፡፡ ነጋዴዎች ይገኙበታል ወዳሉት መርካቶ ድረስ በመዝለቅ መቀስቀሳቸው ብዥታ እስከመፍጠር ደርሶ ነበር፡፡
በዚህ ስልት ተወዳድረው አቶ ክቡር አሸንፈው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡ በምክር ቤቱ የዓመታት የሥራ ሒደት አዳዲስ የሚባሉ አሠራሮች ተዘረጉ፡፡ የጽሕፈት ቤቱም አደረጃጀት ተለወጠ፡፡ ‹‹ይቻላል›› የሚለው የምክር ቤቱ መለያም በዚህ ወቅት ነበር ብቅ ያለው፡፡
‹‹ይቻላል›› የሚለው መሪ ቃል እስከዛሬ ድረስ የምክር ቤቱ መለያም ሆኖ ከንግድ ምክር ቤቱ አርማ ጐን ሳይለይ ዘልቋል፡፡ ይህ ቃል በወቅቱ የነበረው ቢሮክራሲ መስፋፋት ጋር የተያዘ የነበረውን ችግር ለመቅረፍ የራሱን እገዛ አድርጓል ተብሎ ይታመናል፡፡
አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም የሚወስደውን ጊዜና አይቻልም የሚባሉ ጉዳዮች የሚቻሉ መሆናቸውን ለማሳየት ዕድል ሰጥቷል፡፡ በይቻላል መንፈስ የተጀመሩ ብዙ ጥረቶች ውጤት ማምጣታቸው፣ የመደማመጥ ባህል እንዲኖርና ግንዛቤ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ በተለይ የቻምበር ፎረምና የምሳ ላይ ውይይቶች በዚሁ ጊዜ ተጀምሮ በተከታታይ ዓመታት ተጠናክሮ መቀጠል ችሏል፡፡ ዛሬም ድረስ የቻምበር ፎረም ይሠራበታል፡፡
ይህ የውይይት ፕሮግራም ቀደም ብሎ ያልተሞከረ መሆኑም የንግድ ምክር ቤቱ መነቃቃት የታየበት ወቅት ነው ሊባል ይችላል፡፡ ይህ የውይይት ፕሮግራም ነጋዴዎች በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ግንዛቤ እንዲይዙ በባለሙያ የሚቀርብ ጽሑፍ ጭምር የሚያካትት በመሆኑ፣ በየወቅቱ ለውይይት የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የመንግሥት አካላት እንዲያውቁት ስለሚደረግ ለፖሊሲ አውጭዎች ግብአት እንዲሆን ረድቷል የሚሉም አሉ፡፡ ይህም የንግድ ምክር ቤቶች አካሄድ ጠንካራ እየሆነ መምጣቱን ከማሳየቱ በላይ አባላት ወደ ንግድ ምክር ቤቱ እንዲቀርቡ አዲስ ዕድል ፈጥሯልም የሚል እምነት አሳድሯል፡፡
በተለይ በአገሪቱ ውስጥ የሚታወቁ ትላልቅ የሚባሉ ኩባንያዎች የንግድ ምክር ቤቱ አባል መሆን የቻሉበት ወቅም ተደርጐ ይወሰዳል፡፡ የኩባንያዎች ባለቤቶችም በቀጥታ የመሳተፍ ባህላቸው ጐልቶ መታየት የጀመረበት በመሆኑ በንግድ ምክር ቤቱ ታሪክ በተለይ የሚታይ ጊዜ ነው፡፡
ከአቶ ክቡር ገና በኋላም የተተኩት አቶ ብርሃነ መዋና ቦርዳቸው ቀደም ብሎ የተጀመረውን አሠራር አስቀጥለዋል ቢባልም፣ አካሄዳቸው የንግዱ ኅብረተሰብ አጀንዳ ውጭ እየተንቀሳቀሱ ነው መባሉ በንግድ ምክር ቤቱ ላይ የተለየ ድባብ እንዲፈጥር አድርጓል፡፡ ሆኖም በተለይ ለንግዱ ኅብረተሰብ ችግሮችን እንዲቃለሉ ከመንግሥት አካላት ጋር ውይይት እንዲካሄድ ግፊት በማድረግ በወቅቱ እንደችግር  የሚነሱ ጉዳዮች ላይ ብዙ ሲሟገቱ ነበር፡፡ በመንግሥትና በንግድ ምክር ቤቱ መካከል የተጀመረው ውይይት ላይ የሚነሱ ጉዳዮች ግን በመልካም የታተዩ አይመስሉም ነበር፡፡ 
በአቶ ክቡር ገናና በአቶ ብርሃነ መዋ አመራር ወቅት ምክር ቤቱን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ከአቶ ብርሃነ መዋ ከኃላፊነት ከለቀቁ በኋላ ፕሬዚዳንት ሆነው የቀድሞ አሠራር ቀጥሏል፡፡ አዳዲስ አሠራሮችም ተተግብረዋል፡፡ የአባላት ቁጥርም እያደገ መጥቷል፡፡ ይህ አካሄድ ምክር ቤቱ እየተለወጠ መምጣቱን ያሳያል፡፡ በአንፃሩ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንቅስቃሴ የጐላ አልነበረም፡፡
ንግድ ምክር ቤቶች 1995 .በኋላ
 ከደርግ ውድቀት በኋላ መነቃቃት ታይቶባቸዋል የተባሉ ንግድ ምክር ቤቶች ያልተጠበቀ ውጥረት ውስጥ ገቡ፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት፣ የንግድ ምክር ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም የሚወጣው አዋጅ አዲስ የቤት ሥራ ሆነባቸው፡፡  አደረጃጀታቸውን በአዲስ እንዲቀይሩ ያስገደደውን አዋጅ ተከትሎ እንደገና ለመደራጀት የወሰደው ጊዜ ንግድ ምክር ቤቶች በዚሁ አዋጅ መሠረት ለመደራጀት በሥራ ተጠመዱ፡፡ ሊሠሩ ይገባ የነበረውንም ሥራቸውን አቀዘቀዘው፡፡
የንግድ ምክር ቤቶች ከስያሜያቸው ጀምሮ እንዲለወጥ ተደረገ፡፡ ከንግዱ ጋር ዘርፎች እንዲቀላቀሉም ሆነ፡፡ ይህ አደረጃጃት መንግሥት ከሚፈልገው ፖሊሲ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ ቢሆንም፣ አዋጁ በአደረጃጀት ላይ ግን ክፍተት በመፍጠሩ ብዥታዎች ተከተሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ በአገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ የተዋቀሩት የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አንደኛው ችግር ከአዲሱ አዋጅ ጋር የተሳሰረ ስለመሆኑ ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡ አዲሱ አዋጅ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በአገር አቀፍ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በምክትል ፕሬዚዳንትነት ያገለገሉትና የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም እንደሚሉት፣ ‹‹ይህም አዋጁ የንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀትን በተመለከተ አተገባበሩ በተለይ በሰዎች የተለያየ አተረጓጐም እየሰጡት ብዥታ ይፈጥራል፡፡››
የንግድ ምክር ቤቶች ወቅታዊ ችግሮች አንዱም ይኸው አዲሱ አደረጃጀት የፈጠረው ነው የሚሉ አሉ፡፡ በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔዎች ላይ ይገኙ የነበሩ የታላቅ ኩባንያዎች መመናመን አንዱ ምክንያት ተደርጐም ይወሰዳል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ የንግድ ምክር ቤቶች አባላት እንደተጠበቀው ንቁ ተሳትፎ አለመኖር ደግሞ የንግድ ምክር ቤቶች ውስጣዊ ችግሮች በተለይ የእርስ በርስ ሽኩቻ ነው፡፡ ወደ አመራር ለመምጣት ውስጥ ለውጥ በሚደረግ ሽኩቻ ነጋዴዎች የንግድ ምክር ቤቶችን በጥንቃቄ እንዲመለከቱ አድርጓል፡፡ ቀድሞ የነበረ ድባብም እንዲደበዝዝ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን የሚናገሩም አሉ፡፡
የንግድ ምክር ቤቶች የእርስ በርስ ግንኙነት ያለመጠናከር፣ ኃላፊነቱን በአግባቡ አለመወጣትና በአመራር ደረጃ ያሉ ሰዎች ለራስ ስም መጨነቅ ሌሎች መገለጫዎች እንደሆኑም ይገለጻል፡፡ በየጊዜው የፈጠረው ችግርም በቀጠታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከቡድናዊ አሠራር ጋር ይያዛል፤ ይህም ንግድ ምክር ቤቶቹንም ጐድቷል፡፡ 
ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት አቶ ኤልያስ ነገቴ እንደሚሉት ደግሞ የመጀመርያ ሥራቸው አሉ የሚባሉ ችግሮችን ለመፍታት መጣር ነው፡፡ አንዱ ምክር ቤቱን ዓይን ውስጥ የከተቱ የፎረም አባላት ጉዳይን የሚመለከት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ከኮረም መሙላት አለሙሙላት ጋር በተያያዙ የሚነሱ ችግሮችም ሆነ ሌሎችንም ችግሮች በቅድሚያ ካልተፈታ ለሥራ ስለሚያስቸግር፣ ይህንን የማስተካከል ሥራ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ይናገራሉ፡፡
በየጊዜው ተፈጠሩ ለሚባሉ አለመግባባቶች ንግድ ምክር ቤቶች ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራ እንደመሥራት በቡድንተኝነት የሚሠራው ሥራ የንግድ ምክር ቤቶቹ አካሄድ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ እያደረገ ነው፡፡ ወደ አመራር ለመምጣት የሚታየው ፉክክር ደግሞ ቅጥር ሠራተኞች ሳይቀሩ እጃቸውን ስለሚያስገቡበት ለንግድ ምክር ቤቶቹ ችግሮች መባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡
የአባላት ወደ ንግድ ምክር ቤት ያለመምጣት ጉዳይም እንደ ችግር የሚታይ በመሆኑ፣ አባላት ወደ ንግዱ ምክር ቤት እንዳይመጡ የሆኑት ለምንድን ነውየሚለውን ጥያቄን በመያዝ ጥናት በማካሄድ መፍትሔ መስጠትም ቀዳሚ ሥራቸው እንደሚሆን የአቶ ኤልያስ ገለጻ ያስረዳል፡፡
ሌሎች የምክር ቤት አባላት ደግሞ ንግድ ምክር ቤቶች ለንግዱ ኅብረተሰብ የሚሰጡት አገልግሎት አርኪ ባለመሆኑ ምን ብሎ ወደ ምክር ቤት ይመጣል የሚል ትችት ይሰነዝራሉ፡፡ በተለይም በየጊዜው ተፈጠሩ የሚባለው ግጭት ለአባላት መሸሽ ምክንያት ነው በማለት ይገልጻሉ፡፡
እንደ አቶ ክቡር ገና ያሉት ደግሞ አሁን ባለው አካሄድ መሠረት የንግድ ምክር ቤቶች መኖር ምንም ጥቅም እንደሌለው ይናገራሉ፡፡ ሥራቸውን እየሠሩ ነው ማለት እንደማይቻልም ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ አሁን የሚሰጡዋቸው አገልግሎቶች በግል ነጋዴ የሚሠሩ ስለሆነ የንግድ ኅብረተሰቡን ችግሮች በትክክል ያወቁ ንግድ ምክር ቤቶች አለመሆናቸውን ያክላሉ፡፡
አቶ ኤልያስ ደግሞ አባላትን ለማገልገል እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በተለይ በቅርብ ‹‹የኮል ሴንተር›› አገልግሎት ተግባራዊ ስለሚደረግ ነጋዴዎች ያለባቸውን ችግር በቀጥታ የሚገልጹበት ዕድል ስለሚኖራቸው ችግሮችን በቀላሉ ለመፍታት ይቻላል የሚል እምነት አላቸው፡፡
የንግድ ምክር ቤቶች እንቅስቃሴ ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነው እንደማይባልና ብዙ ችግሮች እንዳሉ የሚገልጹ አሉ፡፡ አቶ ኤልያስ ደግሞ ወቅታዊው ንግድ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በተሻለ የሚንቀሳቀስና የተንቀሳቀሰም መሆኑን በመግለጽ፣ የቀድሞ ይሻላል የሚለውን አይቀበሉም፡፡ 
እንደ አቶ ሙሉወርቅ ገለጻ ደግሞ የግለሰቦች ጣልቃ ግበነት መስተካከል መቻል አለበት፡፡ አቶ ሙሉወርቅ ጨምረው እንደገለጹት፣ የንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀትና የአዋጁ አተገባበር በተለይ ሰዎች የተለያየ ግንዛቤ እየሰጠ በንግድ ምክር ቤቶች መካከል ችግሮችን እየፈጠረ በመሆኑ ይህ መስተካከል አለበት ይላሉ፡፡ 
ሌላው በንግድ ምክር በቶች ውስጥ የሚመረጡ ሰዎች የአመራረጡ ሒደት ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮቸ እየተስተዋሉበት በመሆኑ፣ የሕግ ማዕቀፎችን ማጠናር ሲገባ ይህ እየተሠራ ባለመሆኑ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ብዙ መሠራት አለበት፡፡ 
በአዋጁ በተለይ አደራጁ አካል ሚናው ምንድነውለሚለው የተለየ ነገር የለም፡፡ ይህም ትልቅ ችግር ነው፡፡ የግለሰቦችም አመለካከት ሲገባ ደግሞ ክፈተቱን ያሰፉታል፡፡ ይህ አደረጃጀት ችግር መፈታት አለበት የሚሉት አቶ ሙሉወርቅ፣ ሁሉም ንግድ ምክር ቤቶች በራሳቸው ሥልጣንና ኃላፊነት አላቸው፡፡ በጋራም አንድ ኅብረት መሥርተዋል፡፡ ይህንን የጋራና የተናጠል ኃላፊነታቸው ምን ድረስ ነውየሚለው ጉዳይም ተለይቶ መቀመጥ አለበት፡፡ 
‹‹ይህም ግለሰቦች በፈለጉት ወቅት የፈለጉትን ትርጉም እየሰጡ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ችግሮች የሚፈጠሩት በምርጫ ወቅት ነው፡፡ ስለሠሩት ሥራ ሳይታወቅ ምርጫ ወቅት ላይ ግርግር ይፈጥራሉ፡፡ ለነጋዴው ምን እንደሠሩ እንኳ አይታወቅም፡፡ አንዳንዴ እንደሚሰማው አንዳንዶች ቀጣሪያቸውን እስከማስቀጠር ደርሰዋል መባሉ አቅጣጫ እየተሳተ መሆን ያሳያልም፤›› ይላሉ፡፡  
‹‹ስለዴሞክራሲና ስለመልካም አስተዳደር የሚጠይቅ አካል በራሱ ውስጥ መልካም አስተዳደር የማይታይበት ከሆነ ትልቅ ችግር ነው፡፡ በዚህ መልክ በምን ሞራል ከመንግሥት ጋር ሊደራደሩ ይችላሉ?›› በማለት የነገሩን አሳዛኝነት ይጠቅሳሉ፡፡ ስለዚህ ንግድ ምክር ቤቱን ከግል መገልገያነት ከማየት ይልቅ ለንግድ ኅብረተሰብ ቢሠሩ ይመረጣል ይላሉ፡፡  
ከዚህ በኋላ ያሉ አመራሮችም ይህንን የንግድ ምክር ቤት ስም ሲያስነሱ የነበሩ ጉዳዮችን መቀየር እንዳለባቸውም ተጠቁሟል፡፡ ንግድ ምክር ቤት ይፍረስ እስከማለት የደረሱ አካላት ለምን እንዲህ እንዳሉ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ኅብረተሰቡን ያላገለገለ ሆኖ አግኝተውት ሊሆን እንደሚችል በማመን ለዚህ መሥራት ያስፈልጋል ባዮች ናቸው፡፡ በተለይ አላሠራ እያለ ነው ያለውን አዋጅ እንዲስተካከል ማድረግ የብዙዎች እምነት ነው፡፡