Friday, April 25, 2014

ሁለት : ባርያ ነጻ የሚወጣው መቼ ነው? እሱ ሲፈቅድ ነው? ወይስ ጌታው ሲፈቀድለት? ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም



አንድ በሀርቫርድ የኒቨርሲቲ ያጋጠመኝን ነገር መግቢያ ላድርገውና ልቀጥል፤ በአንድ ሴሚናር (የጥናት ውይይት) ላይ አንድ ጥቁር አሜሪካን ፕሮፌሰር ወደአሜሪካ በባርነት በመጡት አፍሪካውያን ላይ የተፈጸመውን ግፍ በመዘርዘር አስረድቶ አሁን ለእነሱ ልጆችና የልጅ ልጆች ካሣ መከፈል አለበት የሚል ክርክር አነሣ፤ ካሣውን የመክፈል ግዴታ የሚጣለው ማን ላይ ነው? ካሣውንስ የመቀበል መብት የሚሰጠው ለማን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ሳናነሣ ብዙ ሌሎች ጥያቄዎች ይኖራሉ፤ — እነዚያ ከአፍሪካ በባርነት ተይዘውና ተሸጠው የመጡት ሰዎች ዛሬ የሉም፤ እነሱ በባርነት ሞተዋል፤ ዛሬ በሕይወት የሚገኙት ጥቁር አሜሪካውያን ነጻነታቸውን አግኝተው ባለሙሉ መብት ዜጎች ሆነዋል፤ በአንጻሩ ደግሞ ለባሪያዎች ነጻነት የተጋደሉ ነጮች አሉ የእነዚህ ልጆች ከባሪያዎቹ ወይንስ ከጌቶቹ ወገን ይመደባሉ? ዛሬ ለልጆቻቸው ካሣ ይከፈል ማለት ልጆቹ የራሳቸውን ነጻነት ችላ ብለው ከአባቶቻቸው ባርነት ጋር እንዲቆራኙ ማድረግ አይሆንም ወይ? የባርነት ምልክቶችን ሁሉ ደምስሰው ነጻ ሰዎች ለመሆን የመጀመሪያው ግዴታ ራስን ችሎ በሁለት እግሮች መቆም ነው፤ ካሣ ክፈሉን ማለት አንደኛ ዋጋ ለማይሰጠው ነጻነት ዋጋን በማውጣት ማርከስ ነው፤ ከሰውነት ወደቤት እንስሳነት መውረድ ነው፤ ሁለተኛ በጌታና በባርያ መሀከል ያለው ግንኙነት መልኩን ለውጦ እንዲቀጥል መድረግ ነው፤ የውይይቱ ባለቤት እኔ ያቀረብሁትን ሀተታ እንዳላሰበበት ቢናገርም የእኔ ጥያቄ የተወደደ አልመሰለኝም፤ ካሣ ተቀባዮች ባርነታቸውን ካሣ ከፋዮች የባሪያዎች ባለቤትነታቸውን ጠብቀው እንደተቆራኙ መቀጠላቸው ባርነትን አያጠፋም፤ ለእኔ ጤናማ አልመሰለኝም።
ባሪያና ኃላፊነት አይተዋወቁም፤ ባሪያ ለገዛ ራሱ ኑሮም ቢሆን ኃላፊነት የለውም፤ ለምግቡም ሆነ ለልብሱ፣ ለመጠለያውም ሆነ ለቀብሩ ኃላፊነት የለበትም፤ ለሁሉም ነገር ኃላፊነቱ የጌታው ነው፤ ከባርነት መውጣት ማለት፣ ከባርነት መላቀቅ ማለት ነው፤ ለገዛ ራስ ሕይወት፣ ለገዛ ራስ ኑሮ ሙሉ ኃላፊነትን መሸከም ነው፤ ስለዚህም ከባርነት ወደነጻነት መሻገር ከግድዴለሽነት ወደኃላፊነት መሻገር ነው፤ ስለዚህም ከግዴለሽነት ወደኃላፊነት ሳይሻገሩ ከባርነት ወደነጻነት መሻገር አይቻልም! ኤልሪድጅ ክሊቨር የሚባል ጥቁር አሜሪካዊ በእስር ቤት ሆኖ የጻፈው (Soul on Ice) የሚል መጽሐፍ በዚህ ጉዳይ ላይ አፍአዊ ምልክቶችን ዘልቆ የሚገባ የነጻነትንና የባርነትን ባሕርያት ያሳያል፤ በአንድ በኩል በሴት ባርያና በወንድ ጌታ መሀከል ያለውን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በወንድ ባርያና በሴት እመቤት በኩል ያለውን ግንኙነት በግላጭ ያወጣዋል፤ ባርነትን የባሕርዩ ያደረገ መገለጫው ለምንም ነገር ኃላፊነት የማይሰማው መሆኑ ነው፤ ለምንም ነገር ሳያስብ፣ በትእዛዝ ብቻ መመራት የተመቸው ባርያ ነው።
ደግ ጌታ በራሱ ተነሣሺነትና በራሱ ፈቃድ ባሪያውን ነጻ ቢያወጣው ባሪያው ሙሉ በሙሉ ነጻ የሚሆን አይመስለኝም፤ በሕግ ነጻ ይሆናል፤ በውስጡ ግን ገና ከባርነት አልተላቀቀም፤ ከጌታው ጥገኛነት ለመውጣት ባለመዘጋጀቱ በኑሮውም ቢሆን ከጌታው አልተላቀቀም፤ ሳይለቀለቅ ከነእድፉ እንደተሰጣ ልብስ ነው፤ ተፈቅዶለት ከባርነት የወጣ ገና ነጻነትን አላገኘም፤ ከባርነት ለመላቀቅ በፍላጎቱና በፈቃዱ ወስኖ ነጻነቱን ከጌታው በግድ ፈልቅቆ ማውጣት አለበት፤ ለምን? የነጻነቱንና የሰውነቱን ቁርኝት ተገንዝቦ፣ የዜግነት እኩልነቱን ተረድቶ፣ በሰውነትም በዜግነትም ጌታህ-ነኝ ከሚለው የማያንስ መሆኑን አምኖ በቆራጥነት ሲነሣ ነው፤ የሰውነቱንና የዜግነቱን ልክ፣ የነጻነትን ትርጉምና ጣዕም አውቆ በትግል ነጻነቱን ሲያገኝ ያለጥርጥር ከባርነት ወጣ ማለት ይቻላል፤ አለዚያ ነጻነቱን በስጦታ፣ በጌታው መልካም ፈቃድ የሚያገኘው የነጻነት ሙሉ ባሕርይ አይኖረውም።
የአፍሪካን አገሮች ብንመለከት የመረረ የነጻነት ትግል የተካሄደባቸው ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ አልጂርያ፣ ዚምባብዌ ናቸው፤ እንደሚታወቀው እነዚህ አራቱም አገሮች ለአውሮፓውያን ሰፈራ የታጩ ነበሩ፤ ምናልባት በእነዚህ ዘገሮች ለነጻነት የተደረገውን ትግል መራራ ያድረገው ዋናው ምክንያት አፍሪካውያኑ አገር-አልባ ሆነው እንዳይቀሩ የነበረው ስጋት ሊሆን ይችላል፤ በአንጻሩ ሱዳን የነጻነት ትግል አልነበረም፤ የኢትዮጵያ ጎረቤት ስለሆነ ቶሎ ነጻነትን በመስጠትና ወዳጅ በመፍጠር፤ በሶማልያም በኩል እንዲሁ ቶሎ ነጻነትን በማሸከም ምዕራባውያን ወደፊት ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት እየቀረጹ ነበር ለማለት ይቻላል፤ ግብጾች ከስንት ሺህ ዓመታት በኋላ ነው አሁን በዘመናችን ወንዶችና ሴቶች በአደባባይ ወጥተው እምቢ! በማለት ሙባረክን ያስወረዱት! ለነጻነት የመታገሉ ልምድ ስለሌላቸው፣ በዚያም ላይ ባህልና ሃይማኖት ተጨምሮበት ሙባረክን አስወርደው ነጻነትን አላገኙም፤ እንደዚሁም የኢትዮጵያ ሕዝብም አጼ ኃይለ ሥላሴን አስወርዶ ነጻነቱን አላገኘም::
እያንዳንዱ ሰው የተፈጠረው ከነፍላጎቱና ፍላጎቱን ለማሟላት ካለው አዛዥነት ጋር ነው፤ ባርያ ፍላጎቶቹን ለማሟላት አዛዥነቱ የለውም፤ አዛዡ የራሱ ፈቃድ ነው፤ የራሱ ፈቃድ የሌለው ሰው ወና ሰው ነው፤ ዋናውን የሰውነት ባሕርዩን ያጣ ባዶ ዕቃ ነው፤ ከባዶ ዕቃ ውስጥ የሚወጣ ነገር የለም፤ ለዚህ ነው ለነጻነቱ መታገልና በራሱ ጥረት ድልን ለመጎናጸፍ የማይችለው።

የዜጎቻቸውን ክብር እና የሃገራቸውን በጎ ገጽታ በማጉደፍ ስራ ላይ የተጠመዱ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ዲፕሎማቶች ።

በሳውዲ አረቢያ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንገስት ዲፕሎማቶች ሪያድ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ስም በከፈቱት የፌስ ቡክ ገጽ ሰሞኑንን አንዲት ኢትዮጵያዊት አሰሪዎን በሰቃቂ ሁኔታ በመጥረቢያ ፈልጣ ገደለች በሚል ጥቂት የሳውዲ መገናኛ ብዙሃኖች ሲያሰሙ የከረሙትን የተለመደ የቁራ ጩሀት በማስተጋባት የህዝብ እና የሃገራቸውን በጎ ገጽታ በማጠልሸት ስራ ላይ ተጠምደው መክረማቸውን ምንጮች ከሪያድ ገለጹ፡፤ ይህ ኢትዮጵያውያኑን በአውሬነት የመፈረጅ ዘመቻ የተለመደ እና ቀደም ብሎ ሪያድ ከተማ ውስጥ በተለምዶ መንፉሃ እየተባለ የሚጠራ አካባቢ በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የጅምላ ግድያ እና ድብደባ ከመፈጸሙ በፊት ሳውዲ አረቢያ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የግል ሚዲያዎች በሃሰት ኢትዮጵያውያኑን ሲወነጅሉ እንደ ነበር የሚናገሩ የአይን እማኞች ሰሞኑን ሳውዲ ውስጥ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚታተው አረብ ኒውስ http://www.arabnews.com/news/554481 የተባለ ጋዜጣ ሳውዲ አረቢያ ጣይፈ ከተማ አንዲት ኢትዮጵያዊት የ50 አመት የልጆች እናት የሆነች አዛውንት በመጥረቢያ ፈልጣ ገደለች የሚል ዜና መዘገቡን ተከትሎ በሪያድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እና አንዳንድ ሃላፊነት የማይሰማቸው ምስለኔዎች ነገሩን በማጋነን በተለያዩ ሶሻል ሚዲያ ገጾቻቸው ላይhttps://www.facebook.com/ethiopian.embassy.5 በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ከጋዜጣው በላይ እንደ ገደል ማሚቱ በማስተጋባት እያሰሙን ያለው መረን የለቀቀ ዘግናኝ ወሬ ከሃገራዊ ከህደት ተለይቶ እንደማይታይ ይናገራሉ፡፤

እራሱን አረብ ኒውስ እያለለ የሚጠራው ይህ ጋዜጣ ሳውዲ አረቢያ ጣይፍ ከተማ በስተደቡብ 130 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ መንደር ውስጥ በአንድ ኢትዮጵያዊት ተፈጸመ ብሎ የተዘገበውን አስቃቂ ወንጀል ለኢትዮጵያውያን ክበር ተቆርቋሪ የሆኑ ወገኖች ቦታው ድረስ ሄደው ጉዳዩን ለማጣራት ባደረጉት ሙከራ በተጠቀሰው አካባቢ የሚኖሩ ወገኖች እየተነገረ ያለውን ነገር እንደማንኛውም ሰው በወሬ ደረጃ ከመስማት ውጭ መንደራቸው ውስጥ እንደዚህ አይነት ወንጀል መፈጸሙን ምንም እንደማያውቁ እንዳረጋገጡላቸው ጠቅሰው የጋዜጣው ዘገባ ከተለመደው በሬ ወለደ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደማያልፍ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል። 
በተለይ ይህንን ወሬ የሚያራግቡ አንዳንድ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ የማይታይባቸው የዲፕሎማቱ ግብረ አበረ አበሮች የ50 አመቷ እማወራ በጸሎት ላይ ሳለች የተገደለቸው የክርስትና እምነት ተከታይ በሆነች ኢትዮጵያዊት መሆኗን በግል የማህበራዊ ገጾቻቸው የሌሎችን ቀልብ ለመሳብ የሚዘግቡትን አካላት የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያን እነዚህ ግለሰቦች በመሃከላችን አለመተማመንን ለመፍጠር እየፈጸሙ ያለው ድብቅ አጀንዳ ሰሞኑን የአረብ ሚዲያዎች በወገኖቻችን ላይ እያሰራጩ ካለው ጥላቻ የማይለይ እና የብዙሃኑን ህይወት በአዲስ መልክ አደጋ ላይ ለመጣል ከሚቆፈር ጉድጓድ ተለይቶ የማይታይ በመሆኑ  ዲፕሎማቱ እና ጀሌዎቻቸው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ከወዲሁ ሃይ ሊባሉ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል።

ጅዳ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው በዲፕሎማቱ ተፈፀመ በተባለው ነገር አዝነው በአረብ ኒውስ ስለተዘገብው ዜና ዲፕሎማቱ የቱንም ያህል መርጃ ባይኖራቸው እንኳን ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ደህነት ሲባል ኤምባሲው በስፋት የተወራውን ወንጀል አጣርቶ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ በማፈላለግ የህዝብን ደህነት እና የሃገሪቱን በጎ ገጻታ ማስጠበቅ ይገባቸው እንደነበር ገልጸው በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት እንዲሉ ዲፕሎማቱ ኢትዮጵያውያንን ጭራቅ አድርገው ለመሳል ከሚዳክሩ የአረብ ጋዜጣች ያገኙትን መረጃ ተቀብለው ህዝብን ያስተምራል በሚል አስፋሪ ተሞክሮ በኤንባሲው ስም በከፈቱት ድህረ ገጽ እያስተጋቡ ያለው ጩሀት ወደፊት በታሪክም በህግም እንደ ሚያስጠይቃቸው ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በመዲናይቱ ሪያድ አንዲት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ የ 9 አመት የአሰሪዎን ልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለች አስመስለው አንዳንድ የአረብ ጋዜጦች የኢትዮጵያውያንን ክበር እና የሃገራችንን በጎ ገጽታ በሚነካ መልኩ ለመዘገብ ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳክ የሚገልጹ ወገኖች የሳውዲ ፖሊስ ነፍሰ ገዳይ ብሎ በቁጥጥር ስር ባዋላት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ ላይ ባደረገው ምርመራ የህጻኗ አሞሞት ከቤት ሰራተኘዋ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌው መሆኑን በማረጋገጥ ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሰራተኛ በነጻ ማሰናበቷ ይታወሳል።
በሪያድ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ኤምባሲ ስም በከፈቱት ሶሻል ሚዲያ በማርኛ ለጠፉ ስለተባለው ኢትዮጵያውያንን የሚወነጅል አስቃቂ ዜና ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረኩት ሙከራ ለግዜው አልተሳካም ። 
Ethiopian Hagere ጅዳ በዋዲ

Saturday, April 19, 2014

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ‘ሮሮና ስጋት “ምላሽ ካልተሰጠን የትምህርት ማቆምና ሰላማዊ ሰልፍ እናደርጋለን!”

addis ababa university

የትምህርት ሚኒስትር በ2006 ዓ.ም በአገሪቱ በተፈጠረው የመምህራን እጥረት ምክንያት በተለ ያዩ የትምህርት ዘርፎች የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ኢትዮጵያውያንን ለአንድ አመት ሙሉ ወጫቸውን ችሎ የማስተማር ስነ ዘዴ (ፔዳጎጅ) በማስተማር ወደ መምህርነት እንዲገቡ ማስታ ወቂያ ያወጣል፡፡ በወጣው ማስታወቂያ መሰረ ትም ለማጣሪያነት የቀረበውን ፈተና በመፈተን መልምሎ ለስልጠና እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሰረት በ10 ዩኒቨርሲቲዎች (መቀሌ፣ ባህር ዳር፣ ወሎ፣ ወለጋ፣ ጅማ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ዲላ፣ ሀሮማያ፣ ሀዋሳና አዲስ አበባ) እንዲሰለጥኑ ይደረጋል፡፡
ይህ ስልጠና እየተካሄደ ባለበት ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡት ሙሉ ወጫቸ ውን መንግስት እንደሚችል ተነግሯቸው ነበር የመጡት፡፡ በዩኒቨርሲቲው መጀመሪያ የተደለ ደሉት 330 ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን ተማሪዎቹ ቃል በተገባላቸው መሰረት መቀጠል አለመቻላቸውን ነው በቅሬታ የሚናገሩት፡፡ ወደ ዝግጅት ክፍላችን በአካል መጥተው ስለሁኔታው ያስረዱት ተማሪዎች ሁኔታውን እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ማስታወቂያውን አይተን ስራችን ለቀን ነው የመጣነው፡፡ ሆኖም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ሚኒስትር ቃል በገባው መሰረት ከህዳር 23 ጀምሮ የምግብም ሆነ የቤት አገልግሎት ሊሰጠን አልቻለም፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመኝታ አገልግሎት የለም በመባሉ ደብረዘይት በሚገኘው የዩኒቨርሲቲው ቅርንጫፍ የእንሰሳት ህክምና እና የግብርና ኮሌጅ ለሁለት ሳምንት እንድንቆይ ተደረገ፡፡ ሆኖም ደብረ ዘይት በሚገኘው ኮሌጅ ጥቁር ሰሌዳን ጨምሮ ለመማር ማስተማር የሚያገለግሉ አቅርቦቶች ልናገኝ አልቻልንም፡፡››
ከዚህም ባሻገር በዚህ ወቅት ተማሪዎቹ የመብት ጥያቄ እንዲያነሱ ያደረጋቸው ሌላ ምክንያትም ተፈጠረ፡፡ ‹‹ትምህርቱ በተባለው መልኩ ሊሰጠን አልቻለም፡፡ አንድ መምህር ወደ ደብረዘይት ሄዶ የሳምንቱን የትምህርት ፕሮግራም ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት እንዲሁም ከ7 ሰዓት ተኩል እስከ 11 ሰዓት ተኩል አስተምሮ ይሄዳል፡፡ ይህን ተከትሎም አንዳንድ የመብት ጥያቄዎችን ማንሳት ጀመርን፡፡›› ይላል አስተባባሪውና የጅኦግራፊ ተማሪው ጋሻነህ ላቀ፡፡
ተማሪዎቹ ሌላ ስራ ስለሌላቸውና ከቤተሰብ ውጭ ስለሚኖሩ አንዳንድ መሰረታዊ አቅርቦቶች እንዲሰጧቸው ለትምህርት ሚኒስትር ያሳውቃሉ፡ ፡ አያይዘውም የትምህርት እድል እንዲያገኙና በደሞዝ ጉዳይም ድምጽ አሰባስበው ያስገባሉ፡፡ ትምህርት ሚኒስትርም ‹‹እናንተ የወጭ መጋራት ስላልሞላችሁ የጠየቃችሁት አቅርቦት አይሰጣችሁም፡፡›› ይላቸዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ በሁለት ሳምንት ውስጥ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ የተባሉት ተማሪዎች ለሁለት ወር ከሁለት ሳምንት በላይ (ከህዳር 24- የካቲት 8) በደብረዘይት እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ ከደብረ ዘይት ሲመለሱ ይዘጋጃል ተብሎ የነበረው አልጋም ሆነ ሌላ አቅርቦት አልተዘጋጀም፡፡ ይልቁንም ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ ከሚገኝ ባዶ ክፍል ውስጥ መሬት ላይ አራት አራት ፍራሽ እያነጠፉ እንዲተኙ ይደረጋሉ፡፡ ትምህርቱን ጥለው እንዳይሄዱ እስካሁን ያሳለፉትን ችግር ትተው መሄድ አልፈለጉም፡፡ ከዚህ ይልቅ ትምህርት ሚኒ ስትርንና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ችግሩን እንዲፈታ በተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ይህ ጥያቄያቸው ንም እስከ ፓርላማና ሌሎች ተቋማት ድረስ አድ ርሰዋል፡፡ ሆኖም ተገቢውን ምላሽ ሊያገኙ እንዳ ልቻሉ ይገልጻሉ፡፡
በዚህ ምክንያት የተማሪዎች ችግር እንዲፈታ ጥረት የሚያደርጉ አስተባባሪዎች ጉዳዩን ወደ ሚዲያ ለማውጣት ይቆርጣሉ፡፡ የሸገር ሬድዮ ጋዜጠኞችም ጉዳዩን ተማሪዎቹ ያሉበት አካባቢ ድረስ ሄደው ይዘግቡታል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ከሌሎች በተለይም አስተባባሪዎቹ በሌሎች ዩኒቨ ርሲቲዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ከሚማሩት ጋርም ግንኙነት ይመሰርታሉ፡፡ እነዚህ ተማሪዎች የሚ ያደርጉትን የመብት ጥያቄና እንቅስቃሴ አብረዋ ቸው የሚማሩ ካድሬዎች (እነሱ ሰርጎ ገቦች ይሏ ቸዋል) ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መሆኑን ለሶስተኛ አካል (ለመንግስት) መረጃ ይሰጣሉ፡፡ ከተቃዋሚ ዎች ጋርም ግንኙነት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ መረጃ ለመንግስት አካላት መድረሱንም መረጃው ከደረሳቸው መካከል ውስጥ አዋቂዎች መልሰው ለአስተባባሪዎቹ ይነግሯቸዋል፡፡ አስተባባሪዎቹ የሚያነሷቸው የመብት ጥያቄዎችም ወደ አመጽ ሊቀይሩት እንደሆነ በመግለጽ መታሰር እንዳለባ ቸው መወሰኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ተከትሎም እስ ራትና አፈና ሊደርስባቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
አስተባባሪዎቹ ‹‹ፖለቲካዊ ጥያቄ መጠየቅ መብ ታችን መሆኑን አላጣነውም፤ ነገር ግን የአሁኑ ጥያ ቄያችን የመብት እንጂ ፖለቲካዊ ጥያቄ አይደለም›› ይላሉ፤ አክለውም ሊታሰሩ እንደሚችሉ የውስጥ ምንጫቸው በእርግጠኝነት እንደነገራቸው ይገል ጻሉ፡፡
ወጭ መጋራት በስምምነታቸው ላይ ያልነበረ ቢሆንም አሁን ግን እንደገና መጥቷል፡፡ መምህር ከሆናችሁ በአገልግሎት ዘመን፣ ሌላ ስራ ከሰራ ችሁ በገንዘብ ትከፍላላችሁ ተብለዋል፡፡ ይህ ግን ስምምነቱ ላይ አልነበረም እንደተማሪዎቹ ገለጻ፡፡ ‹‹እንዲያው ይህን ስምምነት እንሙላ ከተባለ እንኳን የሚሰጡን አገልግሎቶች ሊሟሉልን ይገባ ነበር፡፡ አሁንም ያቀረብነው አገልግሎቶች እንዲሟ ሉልን የሚል ነው፡፡ ያቀረብናቸው ቅድመ ሁኔታ ዎች ከተሟሉ ወጭ መጋራቱን ልንፈርም እንችላ ለን፡፡ እነሱ ግን በሚገባ ጥያቄያችን ሊመልሱልን አልቻሉም፡፡ እንዲያውም ምግብና ሌሎች አቅርቦቶች እንደማይሰጠን፣ ትዕዛዙ ከትምህርት ሚኒስትር የመጣ በመሆኑ ካልፈረሙ ዩኒቨርሲቲውን ለቀን ልንሄድ እንደሚገባ ሁሉ አስፈራርተውናል፡፡›› የሚለው ደግሞ የስፖርት ሳይንስ ተማሪና እንቅስቃሴውን ሲመራ የቆየው ሚሊዮን ታደሰ ነው፡፡
በተመሳሳይ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙት ተማሪዎች መብታቸውን ስለጠየቁ ሁለት ቀን ምግብ ከልክለው ጾም እንዳዋሉዋቸው ይገልጻሉ፡፡ በፖሊስ እያስደበደቡም ከግቢ አስወጥተዋቸዋል፡ ፡ ‹‹ባልተዘጋጀንበት ሁኔታ ትምህርቱን ጥለን አንሄ ድም!› ብለው መኖሪያቸው ቁጭ ቢሉም በፖሊስ ተከበው በመደብደባቸው በግድ የወጭ መጋራቱን ለመሙላት ተገደዋል፡፡ ከጅማ ውጭ በሌሎች ዩኒ ቨርሲቲዎች የሚገኙት ተማሪዎች የወጭ መጋራት አልሞሉም፡፡ በሶስቱ ዪኒቨርሲቲዎች (መቀሌ፣ ባህር ዳርና ወላይታ ሶዶ) የወጭ መጋራት አልተጠ የቀም፡፡ እነሱም ግን መጠየቃቸው የማይቀር ነው፡፡ ጅማ በግድ ሞልተዋል፡፡ ሌሎቹ ጋር በግዳጅ እንዲሞላ ጫና እየተደረገ በመሆኑ ያልተጠየቁትንም እንዲሞሉ ያስገድዷቸዋል፡፡››
ለተማሪዎቹ የተሰጠው ምላሽ በዚህ አያበቃም፡ ፡ ‹‹መብት ብላችሁ መጠየቅ የለባችሁም፡፡ አርፋችሁ ተማሩ›› ተብለናል፡፡ የወጭ መጋራቱን እንድንሞላ ለማስገደድ ከትምህርት ሚኒስትር ሳይቀር ሰዎች እንደተላከባቸውን ይገልጻሉ፡፡
አስተባባሪዎቹ ተማሪዎችን በማስተባበር የምንመደበው መሰረታዊ ወጭዎችን አሟልተን የማንኖርበት መምህር ነት፤ መንግስት እያዋረደው፣ ህዝብም እየናቀው ባለ ሙያ ውስጥ ልንገባ ተጨማሪ እዳ አንገባም ይላሉ፡፡ ተማሪዎቹ እንደሚሉት መንግስት አስተባባሪዎቹን በማሰር ጉዳዩን አድበስብሶ ለማለፍ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ‹‹በእኛ በኩል ምላሽ ካልተሰጠን ትምህርት ማቆምና ሰላማዊ ሰልፍ የማ ድረግ እርምጃዎችን እንወስዳለን፡፡ ምግብ ሊከለክሉን አይችሉም፤ ይህ በእኛ እና በአባቶቻችን ስም ተለምኖ የመጣ ነው›› በማለት መብታቸውን አሳልፈው እንደማይ ሰጡም ይናገራሉ፡፡ የዝግጅት ክፍላችን ድረስ መጥተው ስለጉዳዩ መረጃ የሰጡት የእንቅስቃሴው መሪዎች የሚከ ፈለውን መስዕዋትነት ከፍለው መብታቸውን እንደሚያስ ከብሩ ገልጸውልናል፡፡ (ምንጭ: ነገረ ኢትዮጵያ)
goolgul

አይ አዜብ! (ዘመናይ ዘ አራት ኪሎ)


አዜብ ሲባል ማን በአዕምሮህ ሊመጣ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ በውስጥህ ያሰብከው ‹የባለራዕዩን መሪ› ባለቤት አዜብ መስፍንን ከሆነ ለጊዜው ግምትህ አልሰራም፡፡ አሁን አዜብ የምልህ ሌላ ሴት ናቸው፡፡ አዜብ አስናቀን ነው፡፡ (አስናቀ ስልህም እንዳትደነግጥ…የሰው ለሰው ድራማው አስናቀ አይደለም፡፡) ለማነኛውም አዜብ አስናቀ የግልገል ጊቤ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩትን ሴት ነው እየጠቀስኩልህ ያለሁት፡፡
azeb aእና አዜብን እንዴት አነሳኋቸው ካልክ ጉዳዩ ወዲህ ነው፡፡ ሴትዮዋ ከግቤ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅነታቸው ተነስተው ወደ ሌላ ‹ከፍ› ወዳለ ሹመት መጥተዋል፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚነት አድገዋል፡ ፡ ሹመታቸው በቀድሞው ስራ አስፈጻሚ አቶ ምህረት ደበበ ቦታ መሆኑ ነው፡፡ እኒህ ሴት ታዲያ ‹አይ› የሚያስብል ነገር ገጥሟቸዋል፤ ወይም እንዲያ እንድንል አድርገውናል፡፡
ሴትዮዋ ይህን ሹመት ካገኙ ወዲህ የት እንዳሉ ጠፍተዋል፤ ማለቴ ከበፊቱ የበለጠ ስልጣን ይዘው ከበፊቱ ያነሰ ነው ወደ ህዝብ በሚዲያ እየወጡ ያሉት፡፡ ታዲያ በእኒህ አዜብ በተባሉ መሐንዲስ ሴት ምክንያት አንዳንድ ‹ጉድ-ዳዮች› እየተሰሙ ነው እልሃለሁ፡፡ ይህ ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት ጉዱ ብዙ ነው መቼም! ድርጅቱ የአራት ውላጆች ጥርቅምም አይደል! እና አልኩህ የእኒህ ሴትዮ አባልነት ወይም ወገንተኝነት ከወዴት እንደሆነ ግራ ያጋባል፡፡
አብረን እንጠይቅ እስኪ…እውነት ሴትዮዋ ለማን ይወግናሉ? ለህወሓት ነው? ለኦህዴድ ነው? ለደኢህዴን ነው? ወይስ ኢህአዴግ የሚባለው ራሱን ችሎ ያለ መስሏቸው ተታለው ነው?! በነገርህ ላይ ብአዴን ብዬ ያለጠየኩት በምክንያት ነው፡፡ ምክንያቱ ምን መሰለህ…ሴትዮዋ ብአዴንን እንደማይወግኑ የታወቀ ጥርጣሬ ነው፤ (የታወቀ ጥርጣሬ ምን ማለት ነው አልክ?)
እውነትም ሴትዮዋ ተታልለዋል! እኔን ካልወገንሽ የሚል አተያይ ይገጥመኛል ብለው የሚገመቱ አልመሰሉም ነበር ማለት ነው! ለዚህ ነው ‹መደበቅ› ያበዙት፡፡ ታዲያ አልኩህ ብአዴን ሆዬ ቦታው ለእኔ ይገባኝ ነበር ብሎ ዘራፍ ለማለት ቃጣው አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት አለመግባባቱ አይሏልም እየተባለ ነው፡፡ ምክንያት ህወሓት ማንም ዘራፍ እንዲል አለመፈለጉ ነው! በዚህ ምክንያት እኮ ነው አሉ የመብራት መቆራረጡ የባሰበት፡፡ እንዴ ማን ማንን ይምራ!? ፍትጊያቸውን እንጂ ህዝቡን ማን ልብ ብሎት!
አይ አዜብ! ባላሰቡት መልኩ ፍትጊያውን ተቀላቅለው ቁጭ አሉት፡፡ (ከፍትጊያው ከሌሉበት እንኳ በፍትጊያው ምክንያት ስራቸውን እንዳይሰሩ ተደርገዋል!) አንተዬ እነዚህ ኢህአዴጎች ሊበላሉ እኮ ነው፡፡ (ለነገሩ ህዝብን ብቻ እያኘኩ ከሚኖሩ እርስ በእርሳቸውም ቢናከሱ ይሻላቸዋል፡፡ ድሮስ ጅብና ጅብ መቼ ተስማምቶ በልቶ ያወቃልና!)፡፡ የህዝብ አምላክ መልካሙን ቢያመጣ ያምጣ ብሎ ዝም ያለው ህዝብም አንድ ቀን መነሳቱ አይቀርም፡፡ ያኔ ምን ይውጣቸዋል? ካሁኑ እርስ በእርስ ቢበላሉ ከአደባባዩ ገመና ይሻላቸዋል! ለማነኛውም መሐል ሜዳ ላይ የሚዋልሉት አዜብ ጥግ ቢይዙ ሳይሻላቸው አይቀርም፡፡ ምስኪን አዜብ!
source: goolgul.com

Tuesday, April 15, 2014

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች በፈፀሙት ጥቃት የ9 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ በነበረ ተሸከርካሪ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የዘጠኝ ሰዎች ህይወት አለፈ።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ ማንነታቸው ያልተወቀ ሰዎች በተሽከርካሪው ላይ ጥቃቱን ያደረሱት ማክሰኞ ከንጋቱ 12 ሰዓት ተኩል ላይ ነው ።
ጥቃቱ የተፈጸመው ከአሶሳ ከተማ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሸርቆሌ ወረዳ ልዩ ስሙ ጠይባ በተባለው ሥፍራ ነው ።
በወንጀል ድርጊቱ ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ በሌሎች ስድስት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ወንጀሉን ፈጽመው የተሰወሩት ግለሰቦችን አድኖ ሕግ ፊት ለማቅረብ የፀጥታ ኃይሎች ክትትል በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።
በወንጀሉ ተጠያቂ የሆኑት ግለሰቦች ማንነት ለማጣራትም የወንጀል ምርመራ ሥራ መጀመሩና የምርመራ ውጤቱን የሚመለከቱ መረጃዎችም በወቅቱ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል
ምንጭ http://www.fanabc.com/ 

Monday, April 14, 2014

ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ ‹‹የተነጠቁ መብቶችን እናስመልስ!››

=======================================================
አዲስ አበባ፡- ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹የተነጠቁ መብቶችን እናስመልስ!›› በሚል መሪ ቃል ሚያዚያ 19/2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከአሁን ቀደም የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ምላሽ እንዲሰጣቸው ቢጠይቅም ጥያቄዎቹ ምላሽ ያልተሰጣቸው ከመሆኑም ባሻገር ጭራሹን እየተባባሱ በመምጣታቸውና ህዝብም እየተማረረ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፉን መጥራት እንዳስፈለገ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25 2005 ዓ.ም ያደረገውን ጨምሮ በአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፎችንና ህዝባዊ ስብሰባዎችን ባደረገበት ወቅት የኑሮ ውድነት፣ የእምነት ጣልቃ ገብነት፣ ሉዓላዊነት፣ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀልና ሌሎችም መሰረታዊ ጥያቄዎችን አንስቶ የነበረ ቢሆንም ጥያቄዎቹ ምላሽ ሊያገኙ እንዳልቻሉ የህዝብ ግንኙነቱ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በእስልምና እና ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት፣ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉ፣ የኑሮ ውድነት፣ ሙስና አሁንም ድረስ ተባብሰው መቀጠላቸው ሰላማዊ ሰልፉን በመጥራት ህዝቡ እነዚህን የተነጠቁ መብቶች እንዲያስመለስ ማስተባበርና ማታገል የግድ በማለቱ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ለገዥው ፓርቲ ስልጣን እንጅ ለህዝብ አገልግሎት የማይጨነቁት ተቋማት ስራቸውን በሚገባ ባለመስራትቸው ህዝብ ለከፈለው ክፍያ የሚገባውን አገልግሎት እያገኘ አለመሆኑም ሌላኛው ሰላማዊ የሰልፉ ምክንያት መሆኑን ተገልጹዋል፡፡ በተለይ የውሃ፣ የመብራት፣ የቴሌኮሚኒኬሽንና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ህዝብን እያማረሩ መቀጠላቸው መፍትሄ ስለሚያስፈልገው የሰላማዊ ሰልፉን አስፈላጊነት እንዲሚያጎላው ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ምንም እንኳ ‹‹የህዝብ መብት መነጠቅና የአግልግሎቶች እጦት ሰላማዊ ሰልፉን ወቅታዊ ቢያደርገውም የሰማያዊ ፓርቲ በአመት ውስጥ ከያዛቸው ፕሮግራሞች መካከል አንዱ ህዝብ የተቀማቸውን መብቶች ማስመለስ መሆኑንና ይህም በተደጋጋሚ በተለያዩ ሚዲያዎች መገለጹን›› አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ ገልጸዋል፡፡

ሰላማዊ ሰልፉ እሁድ ሚያዚያ 19 ከቀኑ 4 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት ካሳንቺስ ከሚገኘው የፓርቲው ጽህፈት ቤት እስከ ጃን ሜዳ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን ጃን ሜዳ የተመረጠበት ምክንያትም መብቱን የተነጠቀውና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በሚገባ ማግኘት ያልቻለው ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ጥያቄዎቹን እንዲያነሳ ሰፊ ቦታ በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በየ ክፍለ ከተማው የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሰላማዊ ሰልፉን ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው ‹‹በሀይል የተቀሙትን መብቶችን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ሚዲያውና እያንዳንዱ ዜጋ ተሳትፎ በማድረግ አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Source: - ነገረ ኢትዮጵያ

Saturday, April 12, 2014

ጉንፋን መስል ገዳይ «የኮሮና Corona ቫይረስ» ስጋት በሳውዲ አረቢያ ::



የሳውዲ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር ጅዳ ከተማ ውስጥ 11 ስዎች በጉንፋን መስል አደገኛ ተላላፊ «የኮሮና Corona ቫይረስ» መለከፋቸውን ገለፀ።

የሳውዲ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር ተወካይ / ዚያድ ትላንት ሃሙስ Apr 10 2014 ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በስጡት መግለጫ ጅዳ ከተማ ውስጥ 11 የቫይረሱ ተጥቂዎች መገኘታቸውን ጠቅሰው ባለፈው አመት ሪያድ ከተማ ላይ ከተመዘገበው የበሽተኞች አሃዝ የበለጠ በመሆኑ ቫይረሱ በመላ ሀገሪቱ በስፋት ሳይስራጭ እንዳልቀረ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

/ ዚያድ በማከል ቫይረሱ ማስነጠስ የሰውነት መገጣጠሚያዎች ላይ ቁርጥማት የጡንቻ መዛል እና አልፎ አልፎ ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ትኩሳት እንደሚያሳይ ስለበሽታው አስከፊነት በማብራራት እንደዚህ አይነት የህመም ምልክቶች የታዩበት ማንኛውም ሰው አቅራቢያው ወደ ሚገኝ ጤና ጣቢያ ቀርቦ በአፋጣኝ ምርመራ እና ህክምና ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።


በዋንኛነት የመተንፈሻ አካልን እንደሚያጠቃ የሚነገርለት ይህ ክትባት ያልተገኘለት አደገኛ ጉንፋን መስል ገዳይ በሽታ «ኮሮና Corona » እስካሁን በአለማችን ላይ የተከስተው በሳውዲ አረቢያ እና ፈረንሳይ ብቻ መሆኑን የሚገልጹ የዘርፉ ባለሙያዎች ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው « በማስነጠስ እና በማሳል » በትናፋሽ አማካኝነት በቀላሉ የሚተላለፍ በመሆኑ በበሽታው የተለከፍው ታማሚ የሃኪም ምከር እና የቅርብ ከትትል ካላገኝ ቫይረሱ እስከ ሞት ሊያደርስው እንደሚችል ይናገራሉ።



ሳውዲ ውስጥ ተከሰተ በተባለው በዚህ አዲስ ጎንፋን መስል «የኮሮና Corona »ቫይረስ የተጠቃ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ቢታወቀም ስለበሽታው በሚገባቸው ቋንቋ መረጃ ሊደርሳቸው የማይችሉ በቤት ሰራተኝነት የተሰማሩ እህቶቻችን እና ሌሎች ወገኖች ከበሽታው እራሳችውን መታደግ ይቻላቸው ዘንድ ከወዲሁ ጥንቃቄ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

Ethiopian Hagere ጅዳ በዋ