Saturday, May 31, 2014

አረብሳት ከኢትዮጵያ የሞገድ አፈና እየተደረገብኝ ነው አለ

አረብሳት ከኢትዮጵያ የሞገድ አፈና እየተደረገብኝ ነው አለ
ተቀማጭነቱን በሳዑዲ አረቢያ ያደረገውና በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚያሰራጨው የአረብ ሳተላይት ኮሙኒኬሽን ተቋም (አረብሳት) ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እየተፈጸመበት ያለው ዓለማቀፍ የሳተላይት ሞገድ አፈና (Jamming) ምንጩ ከኢትዮጵያ መሆኑን እንዳረጋገጠ ገለጸ፡፡
ሳትኒውስ የተባለው የአገሪቱ የዜና ምንጭ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ አረብሳት በሚያስተላልፋቸው በርካታ የቴሌቪዝን ጣቢያዎቹ ላይ መታየት የጀመረውን የስርጭት መስተጓጎል መነሻ ለማወቅ ባደረገው በረቂቅ ቴክኖሎጂ የታገዘ ጥናት፣ ከኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚነሳና ሆን ተብሎ የሚፈጸም የሳተላይት ሞገድ አፈና (Jamming) እየተደረገበት መሆኑን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ ይህን መሰሉ ህገወጥ ድርጊት መፈፀሙ መሆኑ እጅግ እንዳሳዘነው ያስታወቀው አረብሳት፤ ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ የሚተላለፍ ምንም አይነት ስርጭት ሳይኖረው፣ የሳተላይት ሞገድ አፈና መደረጉ እንቆቅልሽ እንደሆነበት ገልጿል፡፡ 
የሳተላይት ሞገድ አፈናው፣ ምናልባትም ከሁለቱ አገራት የአንዱ ተቀናቃኝ የሆኑና ከአረብሳት ሳተላይቶች አቅራቢያ በሚገኙ ሳተላይቶች አማካይነት የሚሰራጩ የቴሌቪዝን ጣቢያዎችን ለማፈን የታለመ ሊሆን እንደሚችል ያለውን ግምትም ሰጥቷል፡፡
እየተፈጸመበት ያለውን ህገወጥ ተግባር ለመመከት በብሄራዊና በአለማቀፍ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጸው አረብሳት፣ ጉዳዩን ለዓለማቀፉ የቴሌኮምኒኬሽን ህብረት እና ለአረብ ሊግ ማሳወቁንም ጠቅሷል፡፡አረብሳት ጉዳዩን በቀጣይ ከመረመረ በኋላ፣ ከአለማቀፍ የህግ  ተቋማትና የአገሪቱ የህግ አካላት ጋር በመቀናጀት ወደ ህግ እንደሚያመራና እየተቃጣበት ባለው የሳተላይት ሞገድ አፈና ለደረሰበትም ሆነ ለሚደርስበት ጉዳት ካሳ እንደሚጠይቅ  ማቀዱን ተናግሯል፡፡ከሁለት አመታት በፊት ከኢትዮጵያ ተመሳሳይ የሳተላይት ሞገድ አፈና እንደተፈጸመበትም አስታውሷል።                          ምንጭ አዲስ አድማስ 

Tuesday, May 27, 2014

የመደብ ወይስ የብሄር ጭቆና?!

እንዲህ ተጠይቋል

“ባለፉ ስርዓታት የነበረ የማሕበረ ፖለቲካ መዋቅር የመደብ የትግል (ጭቆና) መሰረት ያደረገ ነበር ወይስ ብሄር?”
ባለፉ ስርዓታት ጭቆና ነበረ (አሁንም አለ)። በኢትዮጵያ ታሪክ በህዝብ የተመረጠ ህዝብን ለማገለግል የተነሳ መንግስት አልነበረም (የለም)። ስለዚህ ጭቆና አለ። ጭቆናው ምን መሰረት ያደረገ ነው? ብሄር ወይስ መደብ? በኔ እምነት ጭቆናው ከሁለቱም ዉጭ ነው። በኢትዮጵያ የመደብ ጭቆና አልነበረም (የለም)፤ የብሄር ጭቆናም አልነበረም (የለም)። የነበረው (አሁንም ያለው) ጭቆና የኤሊት (Elite) ጭቆና ነው።
እስካሁን ድረስ የመደብ ፖለቲካ የለንም። የመደብ ፖለቲካ ከሌለ የመደብ ጭቆናም የለም። የብሄር ጭቆናም አልነበረም፣ የለም፣ ሊኖርም አይችልም። የመደብ ጭቆና ግን ለወደፊቱ ሊኖር ይችላል።
ያለፉ የኢትዮጵያ ገዥዎች ስልጣን ለመያዝ እንዲሁም በስልጣን ለመቆየት ሲሉ በህዝቦች ላይ በደል አድርሰዋል። በደል ሲያደርሱ ብሄር ወይ መደብ መሰረት አድርገው አይደለም። መደብ ጭራሽኑም አልነበረም፣ የለም። ብሄር ነበር፤ ግን ጭቆናው ብሄር መሰረት ያደረገ ሳይሆን ስልጣን መሰረት ያደረገ ነበር፣ ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ Class Based Or Nation Based Struggle ሳይሆን Elite vs People Based Power Struggle ነው።
ገዥዎች ስልጣን መያዝና እስከ ህልፈታቸው በስልጣን መቆየት ይፈልጋሉ። ለስልጣናቸው ሲሉ ታድያ ይደግፈናል የሚሉትን የሕብረተሰብ ክፍል ይጠቅማሉ፤ ለስልጣን አደጋ ነው በሚሉት ህዝብ ወይ ግለሰብ ደግሞ ጉዳት ያደርሳሉ፤ ስልጣናቸውን ለማጠናከር። ግን በፖለቲካ አንድን የሕብረተሰብ ክፍል መጥቀም አይቻልም፣ ይከብዳልና። ስለዚህ በሕብረተሰቡ ስም የተወሰኑ ግለሰቦች እንዲጠቀሙ ይደረጋል። ግለሰቦቹ ሲጠቀሙ የመጡበትን ሕብረተሰብ እንደተጠቀመ ተድርጎ ይታሰባል: ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ሲባል። ህብረተሰቡ በስልጣን ላይ ያለ ስርዓት “የኛነት” ስሜት ያሳድራል። ለዚህም ፕሮፓጋንዳ ይሰራል። ምክንያቱም የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ ነው መጥቀም የሚቻለው። ለስልጣን የሚረዳው ግን አብዛኝው ህዝብ ነው። ተጠቃሚ ግለሰቦች ታማኝ የስርዓቱ አገልጋዮች ይሆናሉ። በነሱ ታማኝነት ስርዓቱ ዕድሜው ያራዝማል።
ለስልጣን አደጋ የሚሆን ግለሰብ ወይ ማሕበረሰብ ደግሞ የጥቃት ዒላማ ይሆናል። የስልጣን ዒላማ የሚሆነው በመደቡ አልነበረም (በመደቡ ዒላማ ሊደረግ ይችላል ግን መደብ አልነበረም)። በብሄሩም አልነበረም። በግዜው ካልተመቱ የስልጣን ስጋት ይሆናሉ የተባሉትን ግለሰቦች ወይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይጠቃሉ፤ ብሄራቸው ምን ይሁን ምን። ግን በኢትዮጵያ ታሪክ አንዳንድ ብሄሮች የከፋ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ለምን? በብሄራቸው ምክንያት? አይደለም። ለስርዓቱ ታማኝ አይደሉም፤ ስጋት ይሆናሉ ስለተባሉ ብቻ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ የመጎዳትም የመጠቀምም መስፈርት ብሄር ወይ መደብ አይደለም፤ የፖለቲካ ታማኝነት (Political Patrimonial-ism) ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ልምድ መሰረት የፖለቲካ ታማኝነት የሚገናኘው ከብሄር ጋር ነው። ሙሉ በሙሉ ባይባልም አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች የበለጠ ይተማመናሉ (ምክንያቱም ፖለቲካችን መርህ መሰረት ያደረገ ሳይሆን ስሜት መሰረት ያደረገ ነው። በስሜት መነዳት ደግሞ አለመሰልጠን ነው)። አማርኛ ተናጋሪ ስልጣን ከያዘ አማርኛ የሚናገረውን (ሌላ ቋንቋ ከሚናገር) የበለጠ ያምናል። ኦሮምኛ ተናጋሪ ኦሮሞን የበለጠ ያምናል። ትግርኛ ተናጋሪ ትግራዋይን የበለጠ ያምናል። በዚህ መሰረት አማራኛ ተናጋሪ ስልጣን ሲይዝ አማራዎችን ያስቀድማል (ለስልጣኑ ሲል)። ሌሎች ደግሞ ቅሬታ ያድርባቸዋል። ከዛ ለስርዓቱ ታማኝ አይሆኑም። ታማኝ ካልሆኑ በጠላትነት ይፈረጃሉ። በጠላትነት ሲፈረጁ ተጎጂ ይሆናሉ። እነዚህ የስርዓቱ ተጠቃሚ የሚደረጉ ታማኞች ግለሰቦች ናቸው። ብሄር ሙሉ ተጠቃሚ ማድረግ አይቻልምና። ተጎጂዎች ግን ብሄር ሙሉ ወይ የሀገር ህዝብ በሙሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ተጠቃሚዎች ታማኝ ግለሰቦች ናቸው። ተጎጂዎች ግን ብሄር ሊሆኑ ይችላሉ። አንድን ብሄር ሌላኛው ብሄር እየበደለ ነው ይባላል። በዳዮቹ ግን ኤሊቶች (elites) ናቸው። ይህን ነገር ጉዳዩ የብሄር ጭቆና ያስመስለዋል። የብሄር ጭቆና ሊኖር ግን አይችልም።
ስለዚህ ባለፉ ስርዓታት (አሁንም ጭምር) በህዝቦች የሚደርስ በደል አለ። ይህንን በደል ብሄሮች የሚፈጥሩት አይደለም። ያለው በደል በብሄሮች ላይ የተፈፀመ የelites በደል ነው። ኦሮሞዎች የተበደሉ ኦሮሞ ስለሆኑ አልነበረም። ለተመሰረተው ስርዓት ተቀብለው አሜን ብለን እንዲገዙ ለማድረግ የተቃጣ ጥቃት ነው የተፈፀመባቸው። ስለዚህ ጥቃቱ ስልጣን መሰረት ያደረገ ነው። ዒላማው የፖለቲካ ታማኝነትን መሰረት ያደረገ ነው።
አማርኛ ተናጋሪ ንጉሶች ታማኝ ባልሆነ ማንም ሰው እርምጃ ይወስዳሉ። ለዚህም ነው በሁሉም ህዝቦች (አማራን ጨምሮ) በደል የደረሰው። ትግርኛ ተናጋሪ ገዥዎች ታማኝ ባልሆነ ማንኛውም ሰው እርምጃ ይወስዳሉ፤ ለስልጣን ሲሉ። ምሳሌ ህወሓት የትግራይ ልጆች በሆኑ እነ ስየ አብርሃ፣ አውዓሎም ወልዱ፣ አስገደ ገብረስላሴና ሌሎች ታጋዮች ላይ መጥፎ እርምጃ የወሰደው እነኚህ ሰዎች ትግርኛ ተናጋሪ ስላልነበሩ አይደለም። ለስርዓቱ ታማኝ ስላልሆኑ እንጂ።
ስለዚህ በኢትዮጵያ ምድር የደረሰውን እንዲሁም እየደረሰ ያለው ጭቆና ብሄር ወይ መደብ መሰረት ያደረገ ሳይሆን የፖለቲካ ታማኝነት መሰረት ያደረገ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያውያን ጭቆና የብሄር ወይ የመደብ ሳይሆን የፖለቲካ ነው።
Aseged Tamene

Friday, May 23, 2014

የታንዛኒያ አልቢኖ ጎሳ አስገራሚ ኑሮና በህይወታቸው የተጋረጠው አስቃቂ ፈተና ….


(አድማስ ሬዲዮ አትላንታ እንዳቀናበረው)
በታንዛኒያ ከሚገኙት ጎሳዎች መካከል አልቢኖዎች ይጠቀሳሉ። አልቢኖዎች በተለይ የሚጠቀሱት የቆዳቸው ንጣት ከሌሎች ጠቆር ካሉ ታንዛኒያውያን ስለሚለያቸው ነው። ንጣታቸው የፊታቸው ቆዳ ብቻ ሳይሆን ጸጉራቸውም ጭምር ነው። ከህጻን እስከ አዋቂ ባጭሩ የአልቢኖ ጎሳ አባላት ሙሉ በሙሉ በለምጽ የተሸፈነ ዓይነት መልክ አላቸው። እናም ህይወታቸው በታንዛኒያ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። እስቲ ታንዛኒያ እንሂድና እንያቸው ……
አንዲት አልቢኖ ሴት ፣ ህጻን ልጇን ይዛ ሳር ላይ እያሯሯጠች ታጫውታለች። ጓደኞቿ አጠገቧ ሆነው ያያሉ። ካሜራ የሚያነሱ ሰዎች ከበዋቸዋል - እነሱም ለካሜራው ፈገግ ማለትን ለምደዋል። እንደ ልዩ ሰው ስለሚታዩ ሁሉም ፎቶ ያነሳቸዋል።

ፎቶው ግን ለነሱ አስቸጋሪ አልነበረም። የተቸገሩትና ዘራችን ሊጠፋ ነው እስከማለት ያደረሳቸው ግን አሳ አጥማጆች፣ ማዕድን አውጪዎችና የውሸት ፈዋሾች ያሉበት ድረስ እየመጡ በድብቅ ስለሚገድሏቸው እንጂ። የሚገድሏቸውም የአልቢኖ ጎሳ አባላትና ለየት ያለ ነጭ መልክ ስላላቸው ብቻ ነበር።
ብዙዎቹ ታንዛኒያውያን የመናፍስት ጎሳ አባላት ወይም የማይታዩት ጎሳዎች ሲሉ ይጠሯቸዋል። አንዳንድ ጊዜማ ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው ጎሳ አባላትም ግድያ ይፈጸምባቸዋል። ግድያው የሚፈጸመው የውስጥ አካላቸውን አውጥቶ ለመሸጥ ነው፣ ይህም የሚሆነው በታንዛኒያ የነዚህ የአልቢኖዎች የውስጥ አካል ገድ አለው፣ ሃብትና ዕውቀት ያስገኛል ተብሎ ስለሚታመን ነው።
የቸገረው የታንዛኒያ መንግስት ለነዚህ ለአልቢኖዎች ለብቻ መጠለያ በመስራት ልጆቻቸው እዚያ ገብተው ራሳቸውን በራሳችው እንዲመሩና እንዲያስተዳደሩ እስከማድረግ ደርሷል። ከዚያም አልፎ በታንዛኒያ መንግስት ፓርላማ ውስጥ አንድ የአልቢኖ ተወላጅ የፓርላማ አባል ሆኖም በ2008 ዓ.ም ተመርጦ ድምጻቸውን እንዲያሰማ ተደርጓል።
ችግሩ ግን በቀላሉ የሚለቅ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ራሱ የአልቢኖ ቤተሰብ አባወራ የራሱን ልጆች በመግደል የውስጥ አካላቸውን በሺዎች ለሚቆጠር ዶላር የሚሸጥበት ጊዜ ያጋጥማል።
አሳ አጥማጆች ፣ የአልቢኖዎች ጸጉር በማጥመጃ መረባቸው ላይ ከተቋጠር ብዙ ዓሳ እንይዛለን ብለው ስለሚያምኑ ለጸጉራቸው ሲሉ ይገድሏቸዋል። ማ ዕድን አውጪዎች ፣ የአልቢኖዎች አጥንት በርካታ አልማዝና እንቁ ያስገኝልናል ብለው ሰለሚያምኑ ይገድሏቸዋል። የውሸት ፈዋሾችና የሃሰት የመንደር ሃኪሞች የአልቢኖዎች ብልት፣ የሌላውን ለወሲብ አልታዘዝ ያለ ብልት ይፈውሳል ብለው ስለሚያምኑ ገድለውም ሆነ አስገድለው ብልቶቻቸውን ይወስዳሉ። እናም የአልቢኖ ጎሳዎች ይህን ሁሉ የመቋቀም ፈተና አለባቸው።
አልቢኖዎች 48 ሚሊዮን ከሚሆነው የታንዛኒያ ህዝብ መቶ ሺህ ያህል ቁጥር እንዳላቸው የአልቢኖዎቹ ተወካዮች ይናገራሉ። በየጫካው ተሰባጥረው የሚኖሩትንና ምንም መከላከያ የሌላቸው የነዚሁ አልቢኖዎች ዘር ከመጥፋቱ በፊት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከፈቱላቸው መጠለያ ጣቢያዎች ለወደፊት ትውልዳቸው መቀጠል ሊጠቅም እንደሚችል የብዙዎች ግምት ነው።

አንዳንድ ጊዜ ራሳቸው አልቢኖዎች ርስ በርስ ተፈራርተው ይኖራሉ፣ አንዳንድ ጊዜ የአልቢኖ ሴቶች ሲያረግዙ ቶሎ ያስወርዳሉ፣ ምክንያቱም የሚወልዷቸው ህጻናት የዚሁ ችግር ቀማሽ ይሆናሉ ብለው ስለሚሰጉ ነው።
በ2013 ዓ.ም በአንድ ጉዳዩን በሚያጠና ድርጅት አማካኝነት ይፋ የወጣ ታሪክ እንደሚያወሳው፣ ከወላጆቿ የተለየች የ17 ዓመት ወጣት አልቢኖ ከ እናቷ ጋር እንድትገናኝ ተደረገ። ታሪኳ እንደዚህ ነው፣ ..
ይህች ወጣት እንደተወለደች አባቷ የፈጣሪ ስጦታ አገኘሁ ብሎ ደስ አለው፣ ከጊዜ በኋላ ግን እሷን ገድሎ አካሏን ለመሸጥ እንደሚፈልግ እናቷ ደረሰችበት። 13 ዓመት እስኪሞላትም እናት እየጠበቀቻትና አባትን እያዘናጋች አቆየቻት፣ 13 ዓመት ሲሞላት ግን ጥቃት እንዲያደርሱባት የመለመላቸውን ሰዎች ይዞ መጣ፣ በዚህ ጊዜ እናትና የ እናቷ ወላጆች ህጻኗ ላይ ሊደርስ የታቀደውን አፍኖ መውሰድና መገደል ለመከላከል ትግል ገጠሙ፣ በዚህ ጊዜ እሷ ስታመልጥ አያቶቿ ግን ህይወታቸው አለፈ።
ወጣቷ እንደምትለው ለጊዜው ታምልጥ እንጂ፣ ያን ጊዜ በ አ እምሮዋ የተቀረጸው ነገር ዛሬም ድረስ ያስጨንቃታል። ስለ አልቢኖዎች ብዙ ነገር ይባላል። አንዳንድ ታንዛኒያውያን “አልቢኖዎች እንደዚህ ነጭ የሆኑት ጥንት የአልቢኖዎች ሁሉ እናት የሆነችው ሴት ከፈረንጅ ጋር በመተኛቷ ነው” ብለው ያምናሉ።
ሆነም ቀረ እነዚህ ለየት ያለ መልክ ያላቸው የአልቢኖ ዝርያዎች በአጉል ዕምነት በተዋጡ ሰዎች እየተገደሉና የሰውነት አካላቸው እየተቆረጠ ለገበያ እየቀረበ ነው። ምናልባት ከጊዜ በኋላ አልቢኖዎች ከምድረ ገጽ ይጠፉ ይሆን?                     

በአባይ ጉዳይ ኃያላኑ በግብጽ ላይ ጫና እየፈጠሩ ነው የጫናው መነሻ አነጋገሪ ሆኗል


ምዕራባውያን ሃያላን አገሮች ግብጽ በአባይ ዙሪያ የድርድር ጠረጴዛ ላይ እንድትቀመጥ ጫና እያደረጉ መሆኑ ተሰማ፡፡ ዜናውን የዘገበው አልአህራም ቃል በቃል ግብጽ ላይ ጫና ተፈጠረ ብሎ ባይጽፍም ከዜናው ለመረዳት እንደተቻለው ግብጽ ላይ ጫና እየተደረገባት ነው፡፡ ሃያላኑ ግብጽ ላይ እያሳደሩት ያለው ጫና መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

እንደ ጋዜጣው ዘገባ ያለፈው ቅዳሜ የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ከኢትዮጵያ ጋር በአባይ ጉዳይ ለመደራደር አገራቸው ፈቃደኛ መሆኗን ማሳወቃቸውን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ይህንን መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መ/ቤት የውሃ ሃብት ልዩ አስተባባሪ ከሆኑት አሮን ሳልዝበርግ እንዲሁም ከአውሮጳ ኅብረት ልዩ ልዑክ አልክሳንደር ሮንዶስ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

በተለይ የአሜሪካው ተወካይ ሳልዝበርግ ወደ ግብጽ ከመሄዳቸው በፊት አዲስ አበባ ላይ ቆይታ አድርገው ከኢህአዴግ ባለሥልጣናት ጋር ግድቡን በተመለከተ ውይይት ማድረጋቸው አብሮ ተዘግቧል፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ በምን ነጥቦች ላይ እንደተደራደረ የተገለጸ ነገር ባይኖርም የአሜሪካው ባለሥልጣን ወዲያው ወደ ግብጽ እንደበረሩ ግብጽ ድርድር መፈለጓ መገለጹ የበርካታዎችን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኗል፡፡

በተያያዘ ዜና ሪፖርተር እሁድ ባስነበበው ጋዜጣ ላይ እስራኤል በኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ሥራ የመሰማራት ዕቅድ እንዳላት ዘግቧል፡፡ እስካሁን ድረስ እስራኤል በኃይል ማመንጨት ሥራ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለት ሲጠቀስ የቆየ ቢሆንም ከዚሁ ጋር ተያይዞ በርካታ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም እንደ ሪፖርተር ዘገባ ከሆነ በኢትዮጵያ የፖታሽ ፕሮጀክት 30በመቶ ባለድርሻ የሆኑትን የሚስተር ኢዳን ኦፈር ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ የመሰማራት ዕቅድ እንዳላቸው ጠቅሷል፡፡

እንደ ዜናው ከሆነ እስራኤል የምትሰማራበት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ “የውኃ፣ የጂኦተርማል ወይም የንፋስ መሆኑን” በግልጽ እንዳላሳወቀች ነገር ግን ጥናቱ በኩባንያው ቴክኒክ ቡድን በኩል እንደሚካሄድ የኩባንያው ባለቤት መናገራቸውን ጨምሮ ዘግቧል፡፡ ሚስተር ኦፈር የሚመሩት ኢዝራኤሊ ኬሚካልስ የተባለው ኩባንያ በማዳበሪያና መሰል ምርቶች ላይ የተሠማራ ሲሆን የማዕድን ማውጣት ተግባሩን በእስራኤል፣ በአሜሪካ፣ በአውሮጳና ቻይን ያካሂዳል፡፡ ከኩባንያው አክሲዮን ሁለተኛው ከፍተኛ ባለድርሻ የካናዳው የፖታሽ ኮርፖሬሽን እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የእስራኤል በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተግባር የመሰማራቷ ዜና ምናልባትም ከአባይ ግድብ ጀርባ የሃያላኑ አገራት ድጋፍና ጥበቃ እንዲሁም ቀጥተኛ ወይም ተዘዋዋሪ የሆነ ጥቅም የማስከበር ፍላጎት እንዳለ የሚሰነዘረውን ሃሳብ ያጠነክረዋል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት የጫናው መነሻ ይህ የጡንቸኞቹ የጥቅም ጉዳይ እንደሆነ ያስረግጣል ይላሉ፡፡

በዚህና በተለያዩ ምክንያቶች በአባይ ግድብ ዙሪያ የሚነሱት መላምቶች ወይም መከራከሪያዎች ከሃያላኑ ጫና ጋር ተዳምረው መነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል፡፡ግብጽ ጫናውን አስመልክቶ በይፋ የገለጸችው ተቃውሞ ወይም ቅሬታ የለም፡፡ ይሁን እንጂ በግብጽ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ ላይ ያሉትና የምዕራባውያን ቀጥተኛ ድጋፍ ያላቸው ፊልድ ማርሻል አል-ሲሲ “የውሃ ነገር” ለግብጽ “የህይወትና የሞት ጉዳይ” መሆኑን መግለጻቸውንና ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን መፍትሔ መፈለጉ “የግድ” እንደሆነ ማስታወቃቸውን ጎልጉል ዘግቦ ነበር፡፡

በዜናው መሠረት አል-ሲሲ “የሌሎችን ፍላጎትና ጥቅም የምንረዳ መሆናችንን ማሳየት ይገባናል፤ (የዚያኑ ያህልም) የራሳችንን ጥቅም ለማስጠበቅ ጽኑ መሆን አለብን፤ (ምክንያቱም) ውሃ ማለት ለእኛ የህይወትና የሞት ጉዳይ ነው” ማለታቸውን ጎልጉል ጨምሮ በማስታወቅ እጩው ፕሬዚዳንት ከዚህ በፊት ያልታየ መለሳለስ በማሳየት “ለኢትዮጵያና ለሌሎች አፍሪካ ወንድሞቻችን ተገቢውን ጥረት አለማድረጋችንን ማመን አለብን፤ በዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ለመተባበርና መፍትሔ ለማግኘት ድርድርና የጋራ መግባባት ቁልፍ ናቸው” ማለታቸውን ጭምሮ ዘግቦ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡

የአባይ ጉዳይ ኢትዮጵያንና ግብጽን ለዘመናት በተለያዩ እሰጥ አገባ ውስጥ የከተታቸው ነው፡፡ በአባይ ከሚፈሰው 90በመቶ የሚሆነው ውሃ የሚመነጨው እንዲሁም በአባይ ተጠርጎ ከሚወሰደው ለም አፈር 96በመቶ የሚሆነው የሚሄደው ከኢትዮጵያ ደጋማ ክፍል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የአባይ ወንዝን አጠቃቀም በተመለከተ የሚያስተዳድሩት ሕጎች እኤአ በ1929 እና በ1959 በግብጽና በሱዳን እንዲሁም በግብጽና በብሪታኒያ በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረሙ ውሎች ሲሆን በውሉ መሠረት ግብጽና ሱዳን ከአባይ ወንዝ ኃብት በድምሩ 90በመቶ የሚሆነውን የመጠቀም መብት አላቸው (ይህም በየዓመቱ 55.5 ሜትር ኩብ የሚሆነው ለግብጽ 18.5 የሚሆነው ደግሞ ለሱዳን ማለት ነው)፡፡

ይህ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ውልና አሠራር እንዳለ ሆኖ የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ በታህሳስ ወር አቶ መለስ ይህንኑ የቅኝ ግዛት ዘመን ውል እንደገና በመቀበል ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ የተፈቀደላትን የድርሻ ኮታ ማግኘት ይገባታል በማለት ስምምነት መፈረማቸውን አልአህራም በወቅቱ ዘግቦ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ ኢነርጂ ቢዝነስ ሪቪውን በመጥቀስ ሪፖርተር ለንባብ ባበቃው ዜና ላይ “በምሥራቃዊ ሱዳን በኩል ከከሰላ ግዛት ተነስቶ ወደ ኤርትራ በሚዘረጋ የ45 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር” በኩል ሱዳን ከኢትዮጵያ የምትገዛውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለኤርትራ ለመሸጥ እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ዘግቧል፡፡ ሱዳን ከዚሁ የአባይ ግድብ በርካሽ የምትገዛውን የኤሌክትሪክ ኃይል ምን ያህሉን በምን ያህል ትርፍ ለኤርትራ ለመሸጥ እንዳሰበች እስካሁን አለመታወቁን ጋዜጣው ጭምሮ አስታውቋል፡፡

አቶ መለስ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ዓመታት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ያለቀረጥ ክፍያ በነጻ ያህል ከኢትዮጵያ የምትወስደውን ቡና በዓለም ገበያ ላይ በመሸጥ ከቡና አምራችና ሻጭ አገራት ውስጥ ተመዝግባ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ልምድ በመነሳት አሁንም ኤርትራ ከሱዳን የምትገዛውን ከአባይ ግድብ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል በአቅራቢያዋ ለሚገኘው አጎራባቿ የሰሜን ኢትዮጵያ ክልል መልሳ በትርፍ ትሸጥ ይሆናል የሚለው አስተያየት ስላቃዊ ቢሆንም አነጋጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡
******************
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

Tuesday, May 20, 2014

ራስ ምታት ያስቸግሮታል? እነዚህን ምግቦች ቢሞክሩስ?

በተለምዶ በእንግሊዝኛ ስያሜዉ ማይገሬን የሚባለዉ የእራስ ምታት አይነት በተለይም በአንደኛዉ የጭንቅላት ክፍል ላይ ከፍተኛ ህመም የሚፈጥር ሲሆን ፥ ዋና መነሻዉ በተለያየ ምክንያት የሚመጣ የነርቭ ስርዓት መዛባት ነዉ፡፡
ብዙዎቻችን በቅርብ በምናገኛቸዉ ምግቦች ይህንን የራስ ምታት አይነት ማስታገስ ይቻላል ይላል ኸልዝ ትዌንቲ ፎር ዶት ኮም ያወጣው መረጃ
1. የአበባ ጎመን፦ የነርቭ ስርዓትን ፣ ጡንቻንና ደም ግፊትን በማስተካከል የራስ ምታትን ይቀንሳል!
2. ወተት፣ ስኳር ድንች፦ በቫይታሚን ቢ2 ይዘታቸዉ የነርቭ እና ቀይ የደም ሴሎችን እድገትና በሽታ የመከላከል አቅምን ይጨምራሉ!
3. ገብስ ፦ በቫይታሚን ቢ6 ይዘቱ ሄሞግሎቢንን (የሰዉነት ኦክስጂን ተሸካሚ ንጥረ ነገር) በመገንባት የነርቭ ስርዓት እንዲገነባ እና በሽታ ለመከላከል ያግዛል!
4. የዶሮ ስጋ፦ በያዘዉ ቪታሚን ቢ3 የደም ዝዉዉርን በማፋጠን የደም ቧንቧን ክፍት ያደርጋል፣ በወር አበባ ጊዜ ለሚከሰት ራስ ምታት፣ ለድብርት እንዲሁም ለተያያዥ የህመም ስሜቶችም ፍቱን ነዉ!
5. እንቁላል፦ ሰዉነታችን በራሱ ማምረት የማይችለዉን ኦሜጋ 3 የተሰኘ አሲድ የያዘ ሲሆን ፥ ለአእምሮ ስራና እድገት እጅግ ተቃሚ ነዉ ፤ በተጨማሪም በድብርት እና ምክንያት አልባ ጭንቀት ለሚሰቃዩ ሰዎች ጠቃሚነቱ ተረጋግጧል።

ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚመደብ የሚገልጽ የሕግ ረቂቅ ለውይይት ቀረበ


ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚመደብ የሚገልጽ የሕግ ረቂቅ ለውይይት ቀረበ
    ‹የፓትርያርኩን ሥልጣን ይገድባል›› በሚል ተተችቷል
  • ‹‹አመራራቸውን በብቃት እንዲያከናውኑ የሚያግዝ ነው›› /የሕግ ረቂቁ/
  • ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሚያስተላልፉት በብሔራዊ ቋንቋ ብቻ ይኾናል
       የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ፓትርያርኩን የሚያግዝ እንደራሴ እንደሚመደብ በሚገልጽና የፓትርያርኩን ሓላፊነትና ተጠያቂነት በጉልሕ የሚያሳዩ አንቀጾችን ባካተተ የሕግ ረቂቅ ላይ እየተወያየ እንደኾነ ተገለጸ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በ1991 ዓ.ም. ያወጣችውን ሕግ ከሌሎች ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ጋር በማጣጣም፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድገትና ነባራዊ ኹኔታዎች ጋራ በማገናዘብ ያሻሽላል የተባለው የሕግ ረቂቁ ለውይይት የቀረበው፣ ባለፈው ረቡዕ ጀምሮ በመካሔድ ላይ በሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶሱ ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጎች ኹሉ የበላይ ነው የተባለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቁ÷ ርእሰ አበውና ለካህናቷና ለምእመናንዋ ኹሉ መንፈሳዊ አባት ለኾኑት ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚሾም በአንቀጽ 24 ላይ ማስፈሩ ተመልክቷል፡፡ እንደራሴው ‹‹ቅዱስ ፓትርያርኩ ከቤተ ክርስቲያን የተጣለበትን ሓላፊነትና መንፈሳዊ አመራር በሚጠበቀው ብቃትና ደረጃ ለማከናወን እንዲችል የሚያግዝ›› መኾኑ በሕግ ማሻሻያ ረቂቁ ተገልጧል፡ ፡
እንደራሴው የሚመደበው የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ብቻ በሚሳተፉበት ምርጫ ሲኾን፣ ለምርጫው ሦስት ዕጩዎች በፓትርያርኩና በቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ጥቆማ እንደሚለዩ ተጠቅሷል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖት፣ ቀኖናና ትውፊት የማስጠበቅ እንዲሁም ያለአድልዎ የማስተዳደር ሓላፊነት ላለበት ለፓትርያርኩ በእንደራሴነት የሚመረጠው ሊቀ ጳጳስ ማሟላት የሚገባው መመዘኛ በሕጉ መመልከቱ የተጠቆመ ሲኾን መመዘኛው ለእንደራሴው ከ50 - 60 ዓመት የዕድሜ ገደብ ሲያስቀመጥ፣ የአስተዳደር ችሎታና የመንፈሳዊ አመራር ልምድን፣ መንፈሳዊና ዘመናዊ ዕውቀት አጣምሮ መያዝን እንደሚጠይቅም ታውቋል፡፡ ‹‹ግለሰባዊ የሥልጣን ፈላጊነት ስሜት የሚገንበት፣ የፓትርያርኩን ሥልጣን የሚጋፋና መካሠስን የሚያበረታታ ነው›› በሚል አንቀጹን የተቃወሙ የቤተ ክህነት ሓላፊዎች፣ ምደባው አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘም እንደራሴው በፓትርያርኩ ጥቆማ ብቻ መመረጥ እንዳለበት የቃሉ ትርጉም እንደሚያስገደድ በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡
የአህጉረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች በአንጻሩ፣ የእንደራሴው ምደባ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ብልሹ አሠራር እንዲታረም የአደረጃጀትና የአሠራርለውጥ ጥናት በማድረግ ላይ ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አመራር መጠናከር የራሱ አስተዋፅኦ አለው በሚል እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡ እንደራሴው ፓትርያርኩን ከማገዝ ውጭ ‹‹ለቅዱስ ፓትርያርኩ ከተሰጡት ተግባራት ውስጥ የሚጋራው የተለየ ሓላፊነት አይኖረውም፤›› በሚል በረቂቁ የሰፈረውን አንቀጽ በመጥቀስ ምደባው ፓትርያርኩን የመጋፋት ሚና እንደሌለውም ገልጸዋል፡፡ ተጠያቂነትን በተመለከተም ፓትርያርኩን ብቻ ሳይኾን ኹሉንም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ለቅዱስ ሲኖዶስ ተጠሪ ከማድረግ፣ በአስተዳደር በደልና በአመራር ጉድለት የካህናቱንና የምእመናኑን አመኔታና ተቀባይነት ማጣትን ጨምሮ ከሀብትና ንብረት ባለቤትነት ጋራ የተያያዙ ዝርዝር የተጠያቂነት አንቀጾች በረቂቁ በመካተታቸው በፓትርያርኩ አልያም በወቅታዊ እይታ ላይ ብቻ የታጠረ ረቂቅ እንዳልኾነ ያስረዳሉ፡፡
ጉዳዩ በዋናነት የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ አመራር ከማጠናከር አንጻር ሊታይ ይገባል የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች፣ ምልዓተ ጉባኤው የሕግ ማሻሻያ ረቂቁን በጥልቀት በማዳበር የቅዱስ ሲኖዶሱ ሉዓላዊ ሥልጣን በማንም የማይገሠስበት መሣርያ አድርጎ እንደሚያጸድቀው እንጠብቃለን ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ በዓላት ላይ እንዳስፈላጊነቱ እየተገኘ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሚሰጠው እንዲሁም በብዙኃን መገናኛ መንፈሳዊ መልእክት የሚያስተላልፈው በአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ብቻ እንደሚኾን በሕግ ማሻሻያ ረቂቁ ላይ መስፈሩ ተጠቅሷል፡፡   ምንጭ አዲስ አድማስ 

በጅዳ የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ጣቢያ ዘጋቢ ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዙሪያ መረጃ እንዳያቀርብ ታገደ ።

በሳውዲ አረቢያ እና በመካከለኘው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በደል እና ስቃይ በማለዳ ወጎቹ ዘገባው የሚታወቀው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ በመረጃ ቅበላው ባልተደስቱ ወገኖች ለእስር መዳረጉ ይታወሳል። ነብዩ ሲራክ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ከኖረባት ሳውዲ አረቢያ «ጅዳ » ከተማ በስሙ በከፈተው ሶሻል ሚዲያ እና ከቅርብ ግዜ ወዲህ የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ወኪል በመሆን በአረቡ አለም የሚገኙ ወገኖች የሚያሰሙትን እሮሮ በማስተጋባት በህዝብ ዘንድ ክብር እና አድናቆትን ያተረፈ ጋዜጠኛ ነው ። ይህ ጋዜጠኛ እንደማንኛውም ሰው የስደት አለም ህይወቱን ለመግፋት በግል ተቀጥሮ ከሚሰራበት መ/ቤት የስራ ሰዓት ውጭ የእረፍት ግዜውን መስዋት በማድረግ ሰለቸኝ፡ደከመኝ ሳይል «ሳይማር ያስተማረውን ወገኑን» በሙያው ሲያገለግል የኖረ ጋዜጠኛ መሆኑ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይነገራል ። ነብዩ ሲራክ በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፀሙ ቅጥ ያጡ ግፍ እና በደሎች መቋጫ ይበጅላቸው ዘንድ በሚያቀርባቸው ተከታታይ ዘገባዎቹ በስልክ እና በጽሑፍ ይሰነዘሩበት ለነበሩ ስድብ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ቅንጣት ያህል ሳይሸበር ወህኒ እስከገባበት ዕለት የወገኑን ህይወት ለመታደግ ከማለዳ ወግ የመረጃ ቅበላው ባሻገር በስው ሃገር በወረበሎች የታገቱ እህቶቻችንን ነጻ ለማውጣት ከህግ አስከባሪዎች ጎን ቆሞ የአጋች እና ታጋች ድራማ በሠላም እንዲጠናቀቅ ያደረገ ከህዝብ የወጣ ለህዝብ የኖረ ኢትዮጵያዊ ነው ።

ከዚህ ባሻገር ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ለውጭ ሃገር ዜጎች ያወጣውን የ 6 ወር እና የ 3 ወር የግዜ ገደብ መጠናቀቅ ተከትሎ ሰነዶቻቸውን ለማስተካከል ጅዳ ቆንስላ ጽ/ቤት አይን ያልገልጹ ህጻናት ልጆቻቸውን ታቀፈው በጠራራ ጸሃይ ሲነፍሩ ለነበሩ እናቶች እና በስደት አለም ግራ ተጋብተው በተስፋ ቆንስላ ጽ/ቤት በር ላይ ድንጋይ ተንተርሰው ጸሃይ እና ነፋስ ሲፈራረቅባቸው ለነበሩ ዜጎች ቀዝቃዛ ውሃ በማደል ከሰው ምስጋናንን ከፈጣሪ ጽድቅን ያገኘ ሩሩሁ እና ለወገን አዛኝ መሆኑ ይታወቃል።
በሰው ሃገር ተስፋ ሰንቀው ግፍ በደሉ የስደት አለም ኖሮቸውን መቅኔ ላሳጣው ወገኖች ድምጽ በመሆን የሚታወቀው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በቆንስላው ጽ/ቤት በአግባቡ መስተናገድ እና ፈጣን የሆኑ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚገባው ባቀረበው የመፍትሄ ሃስብ በተበሳጩ አንዳንድ የጽ/ቤት ሹማምንቶች ቂም ተይዞበት ጉድጓድ ሲማስለት መሰንበቱ ይታወሳል። ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ እንደ ዜጋ በጅዳ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር ስር የሚገኙ ንብረቶችን ለማስተዳደር በት/ቤት የወላጆች ኮሚቴ እና በተለያዩ የኮሚኒቲው መዋቅሮች የሃላፊነት ቦታዎች እንዲያገለግል በማህበረሰቡ ተመርጦ የመረጠውን ህዝብ በቅንነት እና በታማኝነት ለማገልገል በነበረው ሂደት ውስጥ ህሊናው የማይቀበላቸውን አያሌ ሚስጥራዊ አሰራሮች በመቃወሙ ብቻ ከነበረበት የሃላፊነት ቦታ እንዲነሳ ከማድረጉም በላይ ላልተወሰነ ግዜ ቆንስላ ጽ/ቤት አካባቢ እንዳይደርስ ህገወጥ ውስኔ ተላልፎበት እንደነበር የሚያስታውሱ ወገኖች ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ ከወህኒ ነጻ ከወጣም በኃላም ስለወገኑ ስቃይ እና በደል እንዳይጽፍ እና እንዳይናገር የተጣለበት የህሊና ነጻነት ገደብ ከዚህ በላይ በተገለጹ መስረታዊ ጉዳዩች ህዝብ መረጃ የማግኘት መብቱን ለመቀልበስ በእጅ አዙር የተውሰደ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል ።
ከሁለት ወራት ወህኒ ቆይታ በሃላ በቀርብ ቀን ነጻ የወጣው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ በአሁኑ ሰአት በመልካም ጤንነት ላይ መሆኑን ቢታወቀም ጋዜጠኛው ከእንግዲህ በስደተኞች ዙሪያ ምንም አይነት መረጃዎችን በሶሻል ሚዲያ ሆነ በጀርመንድ ድምጽ እንዳይዘግብ ከባድ ማስጠንቀቂያ የተላለፈበት መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል ። የጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ የህሊና እስረኛ መሆንን ተከትሎ አንዳንድ ወገኖች በመካከለኛው ምስራቅ ግፍ እና በደል የሚፈጸምባቸውን በሚልዮን የሚቆጠሩ ድምጽ አልባ ኢትዮጵያውያን ህይወት የከፋ ሊያደርገው እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ ። 
Ethiopian Hagere ጅዳ በዋዲ

Wednesday, May 14, 2014

ዩኤስኤአይዲ በግብረ ሰዶማዊያን ላይ አያተኩሩም ያላቸውን ፕሮጀክቶች መደገፍ አቆመ

የአሜሪካ የዕርዳታና የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ኤድስ ሪሶርስ ሴንተር (ኤአርሲ) ተግባራዊ ያደርጋቸው ለነበሩ ፕሮጀክቶች ይለቅ የነበረውን ፈንድ በግብረ ሰዶማዊያን ላይ አይሠሩም በሚል በድንገት ማቋረጡን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በፈንዱ መቋረጥ ምክንያት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎችን ሕይወት የሚያስቃኘውና ቤተኛ የተሰኘውና ለቫይረሱ ተጋላጭ ከሆኑ የኅብረተሰብ ክፍል ወጣቶች ላይ የሚያተኩረው ዳጉ የሬዲዮ ፕሮግራሞች በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ የተቋረጡ ሲሆን፣ ሌሎችም የኤድስ ሪሶርስ ሴንተር ፕሮግራሞች እየታጠፉ መሆናቸውን ምንጮች አመልክተዋል፡፡
የኤአርሲ ፕሮጀክቶች እ.ኤ.አ. እስከ 2016/17 መዝለቅ ሲጠበቅባቸው የፈንዱ በድንገት መቆም እስከዛሬ የኤችአይቪ ሥርጭትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ፕሮግራሞችን ማቋረጡ ለረዥም ጊዜ የተገኘውን ውጤት ወደኋላ መመለስ እንደሚሆን ምንጮች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በለጋሾች በኩል የኤችአይቪን ሥርጭት ለመግታት የሚሠሩ ሥራዎችን በሚመለከት የትኩረት አቅጣጫ ለውጥ መኖሩን፣ እዚህ ደረጃ የደረሱ ፕሮጀክቶችን ከዚህ ወዲያ መንግሥት ተረክቦ ያስቀጥል የሚል አቋም መኖሩን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ፕሮጀክቶቹን መንግሥት የራሱ እንዲያደርግ ተገቢ የሽግግር ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ በዩኤስኤአይዲና በፌደራል የኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያና ጽሕፈት ቤት (ሀፕኮ) ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ቢሆንም በድንገት በዩኤስኤአይዲ ብዙዎቹ የኤድስ ሪሶርስ ሴንተር ፕሮጀክቶች ባለፈውና በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ማብቂያ ላይ እንዲቋረጡ ተደርጓል፡፡ ይህ ደግሞ የፕሮጀክቶች ሽግግር በዕቅድ የተመራ፣ ስትራቴጂካዊና የአገሪቱን ፍላጐት ያገናዘበ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያና የአሜሪካ መንግሥት የተፈራረሙት የአጋርነት ማዕቀፍ ላይ የተቀመጡ ስምምነቶችን የሚፃረር መሆኑን ምንጮቹ ያስረዳሉ፡፡
የኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት መንግሥት ፕሮጀክቶቹን ለመቀበል ዝግጁ አለመሆኑንና የፕሮጀክቶቹን ሽግግር በሚመለከትም ግልጽ የሆነ ዕቅድ ማስፈለጉን ለለጋሾቹ አሳውቆም ነበር፡፡
ዩኤስኤአይዲ ኤችአይቪን በሚመለከት ከሚሠሩ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት ትኩረት የሚሰጠው አጠቃላይ ሕዝብን ሳይሆን ተጋላጭ የሆኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ለሚያደርጉ መሆኑን፣ በዚህ ረገድ ተለይተው የተቀመጡት ሴተኛ አዳሪዎችና ግብረ ሰዶማዊያን መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የኤችአይቪ ድጋፍ (PEPFAR) ፕሮግራሞች የኤችአይቪን የሥርጭት አቅጣጫ ተከትለው ይሄዱ ዘንድ ግፊት እየተደረገ መሆኑን፣ የፔፕፋር የኢትዮጵያ ቢሮ ለሀፕኮ አሳውቆ ነበር፡፡ የፕሮግራሞችን መቋረጥ በሚመለከት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሽያ ሀስላክና የሀፕኮ ኃላፊዎች ረዥም ውይይት ቢያደርጉም ምንም ዓይነት ውጤት ላይ መድረስ አለመቻሉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹን ተግባራዊ ያደርግ የነበረው የኤድስ ሪሶርስ ሴንተር ኃላፊ አቶ ጋሻው መንግሥቱ ቢሯቸው በገንዘብ እጥረት ምክንያት ብዙ ፕሮጀክቶችን መዝጋቱንና በርካታ ሠራተኞችን መቀነሱን ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡ ታጥፈው እንዲቀጥሉ እየተደረጉ ያሉ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም ከአንድ ዓመት በላይ የሚዘልቁ አይደሉም፡፡
እ.ኤ.አ. በ2002 በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ሥራ የጀመረው ኤድስ ሪሶርስ ሴንተር በአገሪቱ የሚካሄዱትን የኤችአይቪ ፕሮግራሞች ለማገዝ ከ18 በላይ ፕሮጀክቶች የነበሩት ቢሆንም፣ አሁን ብዙዎቹ በመዘጋት ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 952 ወገን ኤድስ ቶክላይን ሰዎች መረጃና የምክር አገልግሎት የሚያገኙበት ነፃ የስልክ ጥሪ መስመሮች የነበሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አቅሙን ቀንሶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ፈንዱ በድንገት በመቋረጡ ምክንያት ሠራተኞቹም በግማሽ መቀነሳቸው ታውቋል፡፡
ፕሮጀክቶቹን በድንገት ለማቆም በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው የኤችአይቪ ሥርጭት አቅጣጫ በቀጣይ ለሚሠራው ሥራ መሪ መሆን አለበት የሚል መከራከሪያ በዩኤስኤአይዲ በኩል መቅረቡን የሀፕኮ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ፈይሣ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ የፕሮጀክቶቹን መቋረጥ በሚመለከት ሚኒስትሩ የተገኙበት ሰፊ ድርድር ስለመደረጉ ግን የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ቢገልጹም፣ ሪፖርተር ያገኛቸው መረጃዎች ድርድሩ በእርግጥም ስለመካሄዱ ያስረዳሉ፡፡ ጉዳዩን በሚመለከት ማብራሪያ የተጠየቁት የአሜሪካ ኤምባሲ የኢንፎርሜሽንና ሚዲያ ጉዳዮች ኦፊሰር ካትሪን ዲዮፕ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ጋር በተደረገ ውይይት ብዙዎቹን ኤችአይቪን የሚመለከቱ ፕሮጀክቶች ለመንግሥት ለማስረከብ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ቤተኛንና ሌሎች የኤድስ ሪሶርስ ሴንተርን የመሰሉ ውጤታማ ፕሮጀክቶችን መንግሥት ያስቀጥላቸዋል ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት የአሜሪካ መንግሥት በፔፕፋር በኩል በኢትዮጵያ ኤችአይቪን ለመዋጋት ሁለት ቢሊዮን ዶላር መለገሱ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቤተኛ የተሰኘው የሬዲዮ ፕሮግራም ቀደም ሲል ፕሮግራሙ ላይ ይሠሩ በነበሩ ጋዜጠኞች የግል ጥረት በሌላ ስፖንሰር ድጋፍ መቀጠል ችሏል፡፡ Reporter Amharic.

Monday, May 12, 2014

በሪያድ የአባይ ግድብ 3ኛ አመት ከብረ በዓል ላይ ኢትዮጵያውያን የሃገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በአሸባሪነት መፈረጃቸው ተቃውሞ አስነሳ ።


በቀርቡ በሪያ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ የተከበረውን የአባይ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግደብ 3ኛ አመት ክብረ በዓል አሰመልክቶ ኤምባሲው በጠራው ስብሰባ ላይ ሪያድ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች እንዳይገኙ በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያው አምባሳደር መሃመድ ሃሰን ባስተላለፉት ቀጨን ተዕዛዝ አዛውንቱ በአሸባሪነት ተፈርጀው በአሉን እንዳይታደሙ መታገዳቸው ሪያድ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፈተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። በተለይ ሰሞኑን ውስጥ ወስጡን ሲነገር የነበረው የአምባሳደሩ መሃመድ ሃሰን ነውረኝነት ተግባር አርብ May 9 2014 ምሸት በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒት አዳራሽ ውስጥ ለአንድ ኢትዮጵያዊ በተዘጋጀ የእርዳታ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ህዝቡ ተቃውሞውን ማሰማቱን ለማወቅ ተችሏል። በወቅቱ አንድ የሃይማኖት አባት ሪያድ ከተማ ውስጥ መኖር ከጀመሩ 35 አመታትን እንዳስቆጠሩ በማውሳት በሪያድ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ በተለያዩ ግዜያት ከሚፈራረቁ መንግስታት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ጋር በተለያዩ የሃገር ጉዳዮች ከኤንባሲው ጎን ቆመው ህዝብን በማስተባበር በሰላም እና በፍቀር እየሰሩ ማሳለፋቸውን ጠቅሰው ዛሬ በማን አለብኝነት የሚከተሉትን የተሳሳተ አቅጣጫ እንዲያርሙ የሚመክሯቸውን ሁሉ በጠላትነት በሚፈርጁ ስረአት አልበኛ የመግስት ሹማምንቶች ኤምባሲያችን እየተመራ በፀረሰላም እና በአሸባሪነት መፈረጃችን በህግ ደረጃ አነጋጋሪነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የስም ስያሜው የተለመደ እና ለታላላቅ ኢትዮጵያውያን እየተሰጠ የሚገኝ የኢትዮጵያውያን መለያ በመሆኑ ልንኮራበት እንጂ ልንሸማቀቅ እና ልናፍርበት አይገባም በለው እምባ እይተናነቃቸው ባሰሙት ንግግር በተሰብሳቢው የድጋፍ ጭብጨባ የአዳርሹ ድባብ ተለውጦ መዋሉን ለማወቅ ተችሏል። 


የዛሬውን የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ለጨቆኞች መለዕክታችንን በግልጽ የምናስተላለፍበት መልካም አጋጣሚ በመሆኑ ፈጣሪን ልናመስግነው የገባል በማለት የመናገር እደል አጊተው ተቃውሞቸውን ማሰማት የጀመሩ አንድ በዕድሜ የገፉ የሃገር ሽማግሌ በአምባሳደር እርምጃ የተሰማቸውን ቅሬታ ሲገልጹ ለህዳሴው ግድብ 20 ሺህ ሪያል ( 1 መቶ ሺህ በር ) የቦድ ግዢ መፈጸማቸውን ጠቅሰው ወዳጅ እና ጠላቶቻቸውን መለየት በተሳናቸው የመንግስት ተወካዮች ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ የተሰጣቸው ስም ተችሮኝ ሰንደቃላማችን የተሰቀለበት ግቢ እንዳልገባ መታገዴ መንግስት በተለያዩ ሃገራት የሚልካቸውን ሹማምንቶች የአምባሳደርነት ብቃት ትዝብት ውስጥ የከተተው ብቻ ሳይሆን የኮሚኒቲውን ንብረት ለግል ለመቆጣጠር አምባሳደሩ በማን አላበኝነት በግሉ የወሰደው እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬያቸውን ገልጸው ህዝብን በአሸባሪነት ፈርጆ በብሄር እና በሃይማኖት በማተራመስ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ጉዳይ ተሳታፊ እንዳይሆኑ በንጹሃን ላይ የሚለጠፍ ው የአሸባሪነት ውንጀላ በፍጹም ህጋዊ መስረት እና ምክንያት የሌለው መሆኑን በተጨባጭ አረጋግጫለሁ ብለዋል። 


አንዳንድ የልማት ማህበር ስራ አመራር አባላት በአምባሳደር መሃመድ ሃሰን የተቀንባበረውን ስረአት አልበኝነት ለማስፈፀም በህዳሴው ግድብ 3ኛ አመት ከበረ በአል ላይ የሚገኙ እና የማይገኙ ኢትዮጵያውያን ስም ዘርዘር በማውጣት ንጽሃን ኢትዮጵያውያንን በአሸባሪነት በማፈርጅ ተግባር ላይ ተስማርተው የልማት አጋር የሆነውን ህዝብ እየለዩ የጥሪ ወረቀት በማዘጋጀት ሲያከፋፍሉ እንደነበር ከውስጥ አውቂ ምንጮች ለመረዳት ተችሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ልማት ማህበር በኩል በአሉን እንዲታደሙ የጥሪ ደብዳቤ ደርሷቸው የነበሩ በሪያድ ነዋሪዎች ዘንድ የተጣላን በማስታረቅ የተራበን በማብላት የታረዘን በማልበስ በአጠቃ ላይ በሰው ሃገር የቤት ኪራይ ላጣ ገንዘብ በመለገስ እና መህበረሰቡን በማስተባበር እርዳታ እንዲዋጣ በማድረግ የሚታወቁ እንደነ ፊት አውራሪ አሊ ሙሃመድ ( አሊ ደሴ ) አይነቱን የህገር ሽማግሌ እና መስል ታላላቅ የሃይማኖት አባቶች የበአሉ ተሳታፊ እንዳይሆኑ መታገዳቸውን ተከትሎ የህዝብ አገልጋይ ነን እያልን ስለልማት እንዴት መናገር ያስችለናል በሚል አንዳንድ የአማራ ልማት ማህበር አመራር አባላቶች በአምባሳደሩ ላይ ቅሬታ ማሰማታቸውን ለማወቅ ተችሏል። የሰሞኑንን እርምጃ በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ መስራች እንደነበሩ የሚነገር ላቸውን የኮሚኒቲው አንጋፋ አባላት እና ደጋፊዎች ወደ ኮሚኒቲው ቀጥር ግቢ እንዳይደርሱ እየተደረገ ያለው ጥረት አንዱ አካል መሆኑን የሚናገሩ ምንጮች ሪያድ ከተማ ውስጥ ተደረገ በተባለው የአባይ ግድብ 3ኛ አመት በዓል ላይ እንዳይገኙ የታገዱ ኢትዮጵያውያን በአሸባሪነት በመፈረጃቸው በህዝብ ዘንድ የቀሰቀሰው ቁጣ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊያመራ እንደሚችል አክለው ገልጸዋል ፡። 
አምባሳደር መሃመድ ሃሰን በሪያድ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ከወገኖቻቸው ይልቅ ለጥቂት የዓረብ ሃብታሞች የሚያጎበድዱ በቅርቡ መፉሃው ውስጥ በተነሳው ሁከት የዜጎቻቸውን ክቡር ያስደፈሩ ለንዋይ ያደሩ አምባሳደር መሆናቸው ይታወቃል። አምባሳስደር መሃመድ ሃሰን የሃገሪቷን በሄራዊ ክበር ከሚፈታተኑ የተለያዩ ህገወጥ የሃዋላ ነጋዴ የአስሪ እና ሰራተኛ ኤጀንሲ ባለቤቶች ጋር የጥቀም ግንኙነት ፈጥረው በኢትዮጵያውያኑ ህይወት ዶላር ሲሰበስቡ የከረሙ በወገኖቻቸው ሬሳ ገንዘብ የሚበሉ ጨካኝ ሰው መሆናቸው በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሪያድ ነዋሪ ይነገራል። 
ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶች እና የገር ሽማግሌዎችን በአሸባሪነት በፈረጀው አወዛጋቢው የአባይ ግደብ 3ኛ አመት ክብረ በአል ዙሪያ አርብ ሚይ 09 ምሸት ኢትዮጵያኑ ያሰሙትን ተቃውሞ አስመልክቶ የዲያስፖራውን ሃላፊ አቶ ተመስገን ኡመር ማብራሪያ እንዲሰጡኝ በስልክ ለማነጋገር ያደረኩት ሙከራ ለግዜው አልተሳካም። 

ይህ ሥ ዕላዊ መግለጫ በዓሉን ለመታደም የመጡ ኢትዮጵያውያን ወደ ኮሚኒቲ ግቢ እንዳይገቡ ታግደው ጥቂቶች የህዳሴውን ግደብ 3ኛ አመት ክብረ በዓል ሲያደርጉ የሚያስይ ነው! 
Ethiopian Hagere ጅዳ በዋዲ

Friday, May 2, 2014

ሰበር ዜና ከታላቁ ጋዚጠኛ ነብዩ ሲራክ የማለዳ ወግ ... እነሆ የጨለመው ነጋ ! ... ነጻ ወጣሁ ! አመሰግናለሁ : )



እነሆ 60 ፈታኝ የመከራ ቀናቶች በትዕግስት ተገፍተው አለፉ ፣ ክፉውን ቀን ለማለፍ የትዕግስት ጽናት ብርታት ተስፋየ ምንጩ በመላ አለም የምትገኙ ወገን ወዳጆቸ ነበራችሁና ላደረጋችሁልኝ እና ላሳያችሁልኝ የሞራል ድጋፍ ልባዊ ምስጋና አቀርባለሁ ! አሰልችውን ቢሮክራሲ አልፈው ፣ በማይጨበጠው ቀጠሮ ሳይሰላቹ ሌት ተቀን እኔን ሀፐነው ታመው ጉዳዬን ለምስለኔ አቅርበው ድቅድቅ ጨለማው እነወዲገፈፍልኝ ያደረጉትን ለማመስገን ቃላት ያጥረኛል ! ለደህንነታቸው ስል በስም ለማንሳት የማይቻለኝ ወንድሞቸ ብርታት ፈጣሪ ታክሎበት ለዛሬው ንጋት ደርሻለሁ ! ተመስገን ! ነግቶም በአይኔ ሲንቀዋለሉ ከነበሩት ብላቴና ልጆቸና ከመላ ቤተስብ ዘመደ አዝማድ ጓደኛ አፍቃሪዎቸ ለመገናኘቴ ምክንያት እናነተ በአካል ከጎኔ የቆማችሁ ነበራችሁና በሁሉም ስም ምስጋና ወደር የለውም !
ከማዕከላዊው የብሪማን እስር ቤት ወዳጆቸ ...በብሪማን ያላፉ ኢትዮጵያውያን የህግ ታሳሪዎች መካከል በግፍ የታሰሩት አሰገራሚ ታሪኮችን ከእናንተው ጋር በአካል ተገኝቸ " እህ " ሰምቸ ተምሬባቸዋለሁ ። በእስር ቤቱ ታዛ እና ግድግዳዎች ላይ የጻፏቸው ማስታወሻና ጥቅሶችን ተመልክቸ ተጽናንቸባቸዋለሁ ። አንዷ ተደጋግማ የሰማኋት ጥቅስ ውስጥ እኔም በመከራው ሳልፍ ተስፋን ሰንቄ እዚህ ደርሻለሁ! " እኔ መውጣት የምፈራው መውጣት ከማልችለው ከመቃብር እንጅ ፣ መውጣት ከምችለው የብሪማን ወህኒ አይደለም! " ትላለች ! አዎ ያ ቤት መቃብር አይደለም ... በተስፋ ኑሩ ! አካላችሁ እንጅ አዕምሯችሁን ማሰር የሚቻለው የለምና ብሩህ ተስፋን ሰንቁ ! ፍትህ ርትዕ የጎደለባችሁን ድምጽ ዛሬም እንደ ትናንቱ ለምሰለኔዎቻችን አሰማለሁ ! አይዟችሁ !
ለእነ እንቶኔ መረጃ ቅበላየን ጠልታችሁ ላሳደዳችሁኝና ላልተሳካላችሁ ! " ወደ ገደል አፋፍ ገፋነው ! " በትምክህት የታበያችሁ ፣ ህልማችሁ ያልተሳካ እኩዮችም ቢሆን ያለመታከት በመስራታችሁ በመንገላታቴ አልተጎዳችሁኝምና ደስ አይበላችሁ ! እግሬና እጆቸ በካቴና ታስረው ወደማላውቀው የወህኒ ህይወት ስወረወር የማላውቀውን አውቄ ፣ ተምሬና ኑሮ በመከራ እንዴት እንደሚገፋ እማር ዘንድ ምክንያት ስለሆናችሁኝ አመሰግናችኋለሁ ! አዎ ዛሬ ነጻ ወጥቻለሁ !
ያሳለፍኳቸው 60 የወህኒ ቀናት ራሴን አዙሬ እንዳይ አድርጎኛል። በቀረጣይ ቀናት አረፍ በፍጥነት ከሚስገመገመው የመረጃ ቅብብሎሽ አውድ ገለል ማለት ባይቻለኝም ለአፍታ አረፍ ማለትን መርጫለሁ! በቀጣይ እረፍት ቀናቶቸ ወደ ብላቴና ልጆቸና ቤተሰቦቸ ፣ያለፉ እና በውዝፍ የቀሩትን የቀሩ የአረብ ሃገር ስደቱኛ ህይወት ከጋዜጠኝነት ህይዎት ተሞክሮው ጋር አዙሬ እመለከተው ዘንድ ግድ ይለኛል!
ከአፍታ እረፍት በኋላ እስክንገናኝ ፣ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ: )
ሰለም ለሁላችሁ !
ነቢዩ ሲራክ
ነቢዩ ሲራክ

Thursday, May 1, 2014

በአንዳንድ ዩንቨርስቲዎች በተፈጠረ ግርግር በህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ


አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 23 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በተፈጠረ ግርግር በህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
ጽህፈት ቤቱ ማምሻውን  እንደገለፀው  በአዲስ አበባና በዙሪያው የሚገኘውን የኦሮሚያ ልዩ ዞንን በልማት ለማስተሳሰር የተነደፈውን የተቀናጀ የልማት ማስተር ፕላን አስመልክቶ ከፕላኑ ፋይዳና አላማ ጋር የሚቃረን መሰረተ ቢስ አሉባልታ በአንዳንድ ወገኖች በስፋት ሲሰራጭ ቆይቷል፡፡
ይህን መነሻ በማድረግም በበርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ትክክለኛውን መረጃ የማወቅ ፍላጎት መኖሩን ከግምት በማስገባት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት በእቅዱ ልማታዊ ዓላማና በሚያስገኛቸው  ጥቅሞች  ዙሪያ ማብራሪያ ሲሰጡ መቆየታቸውንና አሁንም በመስጠትም ላይእንደሚገኙም ነው ያመለከተው፡፡
በምክክር መድረኮቹ የተጀመረው  ህዝባዊ ውይይት እየተካሄደ  ባለበት በአሁኑ ወቅት ትክክለኛው መረጃ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ላቀረቡ የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችንም በውይይቶቹ ውስጥ የማሳተፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል ፡፡
ይሁንና በሁሉም ክልሎች ከሚገኙ ባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው  ይህ  ህዝባዊ ምክክር  ከመዳረሱ በፊት አስቀድሞ  ጥርጣሬዎችን ለመንዛት ሆነ ተብለው በተሰራጩ አሳሳች አሉባልታዎችና ሃሜታዎች  የተደናገሩ የተወሰኑ ተማሪዎች በፈጠሩት ሁከት  በክልሉ በሚገኙ የተወሰኑ ዩንቨርስቲዎች  በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብሏል፡፡
በዚህ በሃይል በታጀበ  ግርግር ሳቢያ በመደ ወላቡ የሶስት ተማሪዎች ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል፡፡
በተለይም በአምቦ ዩኒቨርስቲ  የተቀሰቀሰው ሁከት  ወደ ከተማ በመዝለቁ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት በአምቦ ከተማ ቢዝነስና ኮንስትራክሽን ባንክ ላይ በተደረገው የዘረፋ  ሙከራና ሌሎችም ህገ ወጥ የነውጥ እነቅስቃሴዎች በአምቦና ቶኬኩታዮ ከተሞች የሰባት ሰዎች ህይወት እንዳለፈና  ባንኩን ጨምሮ በበርካታ የመንግስትና የሀዝብ ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተመልክቷል፡፡
በተያያዘም በሃረማያ ዩንቨርሲቲ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በሰላም የእግር ኳስ ጨዋታ በቴሌቪዥን በመከታተል ላይ በነበሩ ተማሪዎች ላይ  በተወረወረ ፈንጂ ወደ  70 ያህል ተማሪዎች የመቁሰል አደጋ  የደረሰባቸው ሲሆን፥  የአንድ ተማሪ  ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል፡፡
በፌዴራልና በክልል የፀጥታ ሃይሎች ትብብር ሁከቱ በተፈጠረባቸው ዩንቨርስቲዎች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት ተችሏል፡፡
እስካሁን በተደረገው ማጣራት ከበስተጀርባ በመሆን  ሁከቱን በማነሳሳትና በማቀነባበር  ተግባር ላይ የተሰማሩት ጥቂት ፀረ ሰላም ሃይሎች መሆናቸውን ለማወቅ መቻሉን ነው መግለጫው ያመለከተው ፡፡
ፅህፈት ቤቱ እንዳለው ከዚሁ ግርግር በስተጀርባ የቆሙትና ከዚህ ቀደም በነበሩ ግጭቶች እጃቸውን ሲያስገቡ የነበሩ የአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ያሉ ሃይሎች በሚቆጧጠሯቸው ሚዲያዎች እየታገዙ ይህንን የተማሪዎችን ጥያቄ ለጥፋት አላማቸው መጠቀሚያ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸው ታውቋል፡፡
እነዚሁ አካላት ህገ ወጥ እንቅስቃሴያቸውን ሰላማዊ ዜጎችን ሰለባ በማድረግ ጭምር ከማራመድ የሚቦዝኑ አልሆኑም ያለው መግለጫው  በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሚሹ ተማሪዎችን ተገቢ ጥያቄ በአግባቡ እንዳይስተናገድ የሚፈልጉት የነውጥ አቀንቃኞች  ከአንድ ጥግ ሆነው ብዙሃኑን ሰለባ በማድረግ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በመራወጥ ላይ ይገኛሉ  ብሏል፡፡
የአገሪቱ ዴሞክራሲያዊው  ስርዓት ማንኛውንም አይነት ጥያቄ ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በማጤን ብዙሃኑ ወጣት ተማሪዎች ከጉዳዩ በስተጀርባ በሚንቀሳቀሱ ጥቂት የጥፋት ሃይሎች በሚነዙት የተዛባ ዘመቻና አሉባልታ ሳይደናገሩ ትምህርታቸውን በሰላም እንዲከታተሉ መንግስት አሳስቧል፡፡
በዚህ አጋጣሚ  በተፈጠረው ሁከት  ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸውና ወገኖችና  ቤተሰቦቻቸው  መንግስት የተሰማውን ሃዘን እየገለፀ የጥፋቱ ዋነኛ አንቀሳቃሽ የነበሩትን ተከታትሎ ለፍርድ ለማቅረብ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል ፡፡