Friday, May 23, 2014

የታንዛኒያ አልቢኖ ጎሳ አስገራሚ ኑሮና በህይወታቸው የተጋረጠው አስቃቂ ፈተና ….


(አድማስ ሬዲዮ አትላንታ እንዳቀናበረው)
በታንዛኒያ ከሚገኙት ጎሳዎች መካከል አልቢኖዎች ይጠቀሳሉ። አልቢኖዎች በተለይ የሚጠቀሱት የቆዳቸው ንጣት ከሌሎች ጠቆር ካሉ ታንዛኒያውያን ስለሚለያቸው ነው። ንጣታቸው የፊታቸው ቆዳ ብቻ ሳይሆን ጸጉራቸውም ጭምር ነው። ከህጻን እስከ አዋቂ ባጭሩ የአልቢኖ ጎሳ አባላት ሙሉ በሙሉ በለምጽ የተሸፈነ ዓይነት መልክ አላቸው። እናም ህይወታቸው በታንዛኒያ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። እስቲ ታንዛኒያ እንሂድና እንያቸው ……
አንዲት አልቢኖ ሴት ፣ ህጻን ልጇን ይዛ ሳር ላይ እያሯሯጠች ታጫውታለች። ጓደኞቿ አጠገቧ ሆነው ያያሉ። ካሜራ የሚያነሱ ሰዎች ከበዋቸዋል - እነሱም ለካሜራው ፈገግ ማለትን ለምደዋል። እንደ ልዩ ሰው ስለሚታዩ ሁሉም ፎቶ ያነሳቸዋል።

ፎቶው ግን ለነሱ አስቸጋሪ አልነበረም። የተቸገሩትና ዘራችን ሊጠፋ ነው እስከማለት ያደረሳቸው ግን አሳ አጥማጆች፣ ማዕድን አውጪዎችና የውሸት ፈዋሾች ያሉበት ድረስ እየመጡ በድብቅ ስለሚገድሏቸው እንጂ። የሚገድሏቸውም የአልቢኖ ጎሳ አባላትና ለየት ያለ ነጭ መልክ ስላላቸው ብቻ ነበር።
ብዙዎቹ ታንዛኒያውያን የመናፍስት ጎሳ አባላት ወይም የማይታዩት ጎሳዎች ሲሉ ይጠሯቸዋል። አንዳንድ ጊዜማ ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው ጎሳ አባላትም ግድያ ይፈጸምባቸዋል። ግድያው የሚፈጸመው የውስጥ አካላቸውን አውጥቶ ለመሸጥ ነው፣ ይህም የሚሆነው በታንዛኒያ የነዚህ የአልቢኖዎች የውስጥ አካል ገድ አለው፣ ሃብትና ዕውቀት ያስገኛል ተብሎ ስለሚታመን ነው።
የቸገረው የታንዛኒያ መንግስት ለነዚህ ለአልቢኖዎች ለብቻ መጠለያ በመስራት ልጆቻቸው እዚያ ገብተው ራሳቸውን በራሳችው እንዲመሩና እንዲያስተዳደሩ እስከማድረግ ደርሷል። ከዚያም አልፎ በታንዛኒያ መንግስት ፓርላማ ውስጥ አንድ የአልቢኖ ተወላጅ የፓርላማ አባል ሆኖም በ2008 ዓ.ም ተመርጦ ድምጻቸውን እንዲያሰማ ተደርጓል።
ችግሩ ግን በቀላሉ የሚለቅ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ራሱ የአልቢኖ ቤተሰብ አባወራ የራሱን ልጆች በመግደል የውስጥ አካላቸውን በሺዎች ለሚቆጠር ዶላር የሚሸጥበት ጊዜ ያጋጥማል።
አሳ አጥማጆች ፣ የአልቢኖዎች ጸጉር በማጥመጃ መረባቸው ላይ ከተቋጠር ብዙ ዓሳ እንይዛለን ብለው ስለሚያምኑ ለጸጉራቸው ሲሉ ይገድሏቸዋል። ማ ዕድን አውጪዎች ፣ የአልቢኖዎች አጥንት በርካታ አልማዝና እንቁ ያስገኝልናል ብለው ሰለሚያምኑ ይገድሏቸዋል። የውሸት ፈዋሾችና የሃሰት የመንደር ሃኪሞች የአልቢኖዎች ብልት፣ የሌላውን ለወሲብ አልታዘዝ ያለ ብልት ይፈውሳል ብለው ስለሚያምኑ ገድለውም ሆነ አስገድለው ብልቶቻቸውን ይወስዳሉ። እናም የአልቢኖ ጎሳዎች ይህን ሁሉ የመቋቀም ፈተና አለባቸው።
አልቢኖዎች 48 ሚሊዮን ከሚሆነው የታንዛኒያ ህዝብ መቶ ሺህ ያህል ቁጥር እንዳላቸው የአልቢኖዎቹ ተወካዮች ይናገራሉ። በየጫካው ተሰባጥረው የሚኖሩትንና ምንም መከላከያ የሌላቸው የነዚሁ አልቢኖዎች ዘር ከመጥፋቱ በፊት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከፈቱላቸው መጠለያ ጣቢያዎች ለወደፊት ትውልዳቸው መቀጠል ሊጠቅም እንደሚችል የብዙዎች ግምት ነው።

አንዳንድ ጊዜ ራሳቸው አልቢኖዎች ርስ በርስ ተፈራርተው ይኖራሉ፣ አንዳንድ ጊዜ የአልቢኖ ሴቶች ሲያረግዙ ቶሎ ያስወርዳሉ፣ ምክንያቱም የሚወልዷቸው ህጻናት የዚሁ ችግር ቀማሽ ይሆናሉ ብለው ስለሚሰጉ ነው።
በ2013 ዓ.ም በአንድ ጉዳዩን በሚያጠና ድርጅት አማካኝነት ይፋ የወጣ ታሪክ እንደሚያወሳው፣ ከወላጆቿ የተለየች የ17 ዓመት ወጣት አልቢኖ ከ እናቷ ጋር እንድትገናኝ ተደረገ። ታሪኳ እንደዚህ ነው፣ ..
ይህች ወጣት እንደተወለደች አባቷ የፈጣሪ ስጦታ አገኘሁ ብሎ ደስ አለው፣ ከጊዜ በኋላ ግን እሷን ገድሎ አካሏን ለመሸጥ እንደሚፈልግ እናቷ ደረሰችበት። 13 ዓመት እስኪሞላትም እናት እየጠበቀቻትና አባትን እያዘናጋች አቆየቻት፣ 13 ዓመት ሲሞላት ግን ጥቃት እንዲያደርሱባት የመለመላቸውን ሰዎች ይዞ መጣ፣ በዚህ ጊዜ እናትና የ እናቷ ወላጆች ህጻኗ ላይ ሊደርስ የታቀደውን አፍኖ መውሰድና መገደል ለመከላከል ትግል ገጠሙ፣ በዚህ ጊዜ እሷ ስታመልጥ አያቶቿ ግን ህይወታቸው አለፈ።
ወጣቷ እንደምትለው ለጊዜው ታምልጥ እንጂ፣ ያን ጊዜ በ አ እምሮዋ የተቀረጸው ነገር ዛሬም ድረስ ያስጨንቃታል። ስለ አልቢኖዎች ብዙ ነገር ይባላል። አንዳንድ ታንዛኒያውያን “አልቢኖዎች እንደዚህ ነጭ የሆኑት ጥንት የአልቢኖዎች ሁሉ እናት የሆነችው ሴት ከፈረንጅ ጋር በመተኛቷ ነው” ብለው ያምናሉ።
ሆነም ቀረ እነዚህ ለየት ያለ መልክ ያላቸው የአልቢኖ ዝርያዎች በአጉል ዕምነት በተዋጡ ሰዎች እየተገደሉና የሰውነት አካላቸው እየተቆረጠ ለገበያ እየቀረበ ነው። ምናልባት ከጊዜ በኋላ አልቢኖዎች ከምድረ ገጽ ይጠፉ ይሆን?                     

No comments:

Post a Comment