Saturday, April 19, 2014

አይ አዜብ! (ዘመናይ ዘ አራት ኪሎ)


አዜብ ሲባል ማን በአዕምሮህ ሊመጣ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ በውስጥህ ያሰብከው ‹የባለራዕዩን መሪ› ባለቤት አዜብ መስፍንን ከሆነ ለጊዜው ግምትህ አልሰራም፡፡ አሁን አዜብ የምልህ ሌላ ሴት ናቸው፡፡ አዜብ አስናቀን ነው፡፡ (አስናቀ ስልህም እንዳትደነግጥ…የሰው ለሰው ድራማው አስናቀ አይደለም፡፡) ለማነኛውም አዜብ አስናቀ የግልገል ጊቤ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩትን ሴት ነው እየጠቀስኩልህ ያለሁት፡፡
azeb aእና አዜብን እንዴት አነሳኋቸው ካልክ ጉዳዩ ወዲህ ነው፡፡ ሴትዮዋ ከግቤ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅነታቸው ተነስተው ወደ ሌላ ‹ከፍ› ወዳለ ሹመት መጥተዋል፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚነት አድገዋል፡ ፡ ሹመታቸው በቀድሞው ስራ አስፈጻሚ አቶ ምህረት ደበበ ቦታ መሆኑ ነው፡፡ እኒህ ሴት ታዲያ ‹አይ› የሚያስብል ነገር ገጥሟቸዋል፤ ወይም እንዲያ እንድንል አድርገውናል፡፡
ሴትዮዋ ይህን ሹመት ካገኙ ወዲህ የት እንዳሉ ጠፍተዋል፤ ማለቴ ከበፊቱ የበለጠ ስልጣን ይዘው ከበፊቱ ያነሰ ነው ወደ ህዝብ በሚዲያ እየወጡ ያሉት፡፡ ታዲያ በእኒህ አዜብ በተባሉ መሐንዲስ ሴት ምክንያት አንዳንድ ‹ጉድ-ዳዮች› እየተሰሙ ነው እልሃለሁ፡፡ ይህ ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት ጉዱ ብዙ ነው መቼም! ድርጅቱ የአራት ውላጆች ጥርቅምም አይደል! እና አልኩህ የእኒህ ሴትዮ አባልነት ወይም ወገንተኝነት ከወዴት እንደሆነ ግራ ያጋባል፡፡
አብረን እንጠይቅ እስኪ…እውነት ሴትዮዋ ለማን ይወግናሉ? ለህወሓት ነው? ለኦህዴድ ነው? ለደኢህዴን ነው? ወይስ ኢህአዴግ የሚባለው ራሱን ችሎ ያለ መስሏቸው ተታለው ነው?! በነገርህ ላይ ብአዴን ብዬ ያለጠየኩት በምክንያት ነው፡፡ ምክንያቱ ምን መሰለህ…ሴትዮዋ ብአዴንን እንደማይወግኑ የታወቀ ጥርጣሬ ነው፤ (የታወቀ ጥርጣሬ ምን ማለት ነው አልክ?)
እውነትም ሴትዮዋ ተታልለዋል! እኔን ካልወገንሽ የሚል አተያይ ይገጥመኛል ብለው የሚገመቱ አልመሰሉም ነበር ማለት ነው! ለዚህ ነው ‹መደበቅ› ያበዙት፡፡ ታዲያ አልኩህ ብአዴን ሆዬ ቦታው ለእኔ ይገባኝ ነበር ብሎ ዘራፍ ለማለት ቃጣው አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት አለመግባባቱ አይሏልም እየተባለ ነው፡፡ ምክንያት ህወሓት ማንም ዘራፍ እንዲል አለመፈለጉ ነው! በዚህ ምክንያት እኮ ነው አሉ የመብራት መቆራረጡ የባሰበት፡፡ እንዴ ማን ማንን ይምራ!? ፍትጊያቸውን እንጂ ህዝቡን ማን ልብ ብሎት!
አይ አዜብ! ባላሰቡት መልኩ ፍትጊያውን ተቀላቅለው ቁጭ አሉት፡፡ (ከፍትጊያው ከሌሉበት እንኳ በፍትጊያው ምክንያት ስራቸውን እንዳይሰሩ ተደርገዋል!) አንተዬ እነዚህ ኢህአዴጎች ሊበላሉ እኮ ነው፡፡ (ለነገሩ ህዝብን ብቻ እያኘኩ ከሚኖሩ እርስ በእርሳቸውም ቢናከሱ ይሻላቸዋል፡፡ ድሮስ ጅብና ጅብ መቼ ተስማምቶ በልቶ ያወቃልና!)፡፡ የህዝብ አምላክ መልካሙን ቢያመጣ ያምጣ ብሎ ዝም ያለው ህዝብም አንድ ቀን መነሳቱ አይቀርም፡፡ ያኔ ምን ይውጣቸዋል? ካሁኑ እርስ በእርስ ቢበላሉ ከአደባባዩ ገመና ይሻላቸዋል! ለማነኛውም መሐል ሜዳ ላይ የሚዋልሉት አዜብ ጥግ ቢይዙ ሳይሻላቸው አይቀርም፡፡ ምስኪን አዜብ!
source: goolgul.com

Tuesday, April 15, 2014

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች በፈፀሙት ጥቃት የ9 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ በነበረ ተሸከርካሪ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የዘጠኝ ሰዎች ህይወት አለፈ።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ ማንነታቸው ያልተወቀ ሰዎች በተሽከርካሪው ላይ ጥቃቱን ያደረሱት ማክሰኞ ከንጋቱ 12 ሰዓት ተኩል ላይ ነው ።
ጥቃቱ የተፈጸመው ከአሶሳ ከተማ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሸርቆሌ ወረዳ ልዩ ስሙ ጠይባ በተባለው ሥፍራ ነው ።
በወንጀል ድርጊቱ ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ በሌሎች ስድስት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ወንጀሉን ፈጽመው የተሰወሩት ግለሰቦችን አድኖ ሕግ ፊት ለማቅረብ የፀጥታ ኃይሎች ክትትል በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።
በወንጀሉ ተጠያቂ የሆኑት ግለሰቦች ማንነት ለማጣራትም የወንጀል ምርመራ ሥራ መጀመሩና የምርመራ ውጤቱን የሚመለከቱ መረጃዎችም በወቅቱ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።
ምንጭ http://www.fanabc.com/ 

Monday, April 14, 2014

ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ ‹‹የተነጠቁ መብቶችን እናስመልስ!››

=======================================================
አዲስ አበባ፡- ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹የተነጠቁ መብቶችን እናስመልስ!›› በሚል መሪ ቃል ሚያዚያ 19/2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከአሁን ቀደም የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ምላሽ እንዲሰጣቸው ቢጠይቅም ጥያቄዎቹ ምላሽ ያልተሰጣቸው ከመሆኑም ባሻገር ጭራሹን እየተባባሱ በመምጣታቸውና ህዝብም እየተማረረ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፉን መጥራት እንዳስፈለገ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25 2005 ዓ.ም ያደረገውን ጨምሮ በአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፎችንና ህዝባዊ ስብሰባዎችን ባደረገበት ወቅት የኑሮ ውድነት፣ የእምነት ጣልቃ ገብነት፣ ሉዓላዊነት፣ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀልና ሌሎችም መሰረታዊ ጥያቄዎችን አንስቶ የነበረ ቢሆንም ጥያቄዎቹ ምላሽ ሊያገኙ እንዳልቻሉ የህዝብ ግንኙነቱ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በእስልምና እና ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት፣ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉ፣ የኑሮ ውድነት፣ ሙስና አሁንም ድረስ ተባብሰው መቀጠላቸው ሰላማዊ ሰልፉን በመጥራት ህዝቡ እነዚህን የተነጠቁ መብቶች እንዲያስመለስ ማስተባበርና ማታገል የግድ በማለቱ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ለገዥው ፓርቲ ስልጣን እንጅ ለህዝብ አገልግሎት የማይጨነቁት ተቋማት ስራቸውን በሚገባ ባለመስራትቸው ህዝብ ለከፈለው ክፍያ የሚገባውን አገልግሎት እያገኘ አለመሆኑም ሌላኛው ሰላማዊ የሰልፉ ምክንያት መሆኑን ተገልጹዋል፡፡ በተለይ የውሃ፣ የመብራት፣ የቴሌኮሚኒኬሽንና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ህዝብን እያማረሩ መቀጠላቸው መፍትሄ ስለሚያስፈልገው የሰላማዊ ሰልፉን አስፈላጊነት እንዲሚያጎላው ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ምንም እንኳ ‹‹የህዝብ መብት መነጠቅና የአግልግሎቶች እጦት ሰላማዊ ሰልፉን ወቅታዊ ቢያደርገውም የሰማያዊ ፓርቲ በአመት ውስጥ ከያዛቸው ፕሮግራሞች መካከል አንዱ ህዝብ የተቀማቸውን መብቶች ማስመለስ መሆኑንና ይህም በተደጋጋሚ በተለያዩ ሚዲያዎች መገለጹን›› አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ ገልጸዋል፡፡

ሰላማዊ ሰልፉ እሁድ ሚያዚያ 19 ከቀኑ 4 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት ካሳንቺስ ከሚገኘው የፓርቲው ጽህፈት ቤት እስከ ጃን ሜዳ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን ጃን ሜዳ የተመረጠበት ምክንያትም መብቱን የተነጠቀውና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በሚገባ ማግኘት ያልቻለው ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ጥያቄዎቹን እንዲያነሳ ሰፊ ቦታ በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በየ ክፍለ ከተማው የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሰላማዊ ሰልፉን ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው ‹‹በሀይል የተቀሙትን መብቶችን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ሚዲያውና እያንዳንዱ ዜጋ ተሳትፎ በማድረግ አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Source: - ነገረ ኢትዮጵያ

Saturday, April 12, 2014

ጉንፋን መስል ገዳይ «የኮሮና Corona ቫይረስ» ስጋት በሳውዲ አረቢያ ::



የሳውዲ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር ጅዳ ከተማ ውስጥ 11 ስዎች በጉንፋን መስል አደገኛ ተላላፊ «የኮሮና Corona ቫይረስ» መለከፋቸውን ገለፀ።

የሳውዲ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር ተወካይ ዶ/ር ዚያድ ትላንት ሃሙስ Apr 10 2014 ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በስጡት መግለጫ ጅዳ ከተማ ውስጥ 11 የቫይረሱ ተጥቂዎች መገኘታቸውን ጠቅሰው ባለፈው አመት ሪያድ ከተማ ላይ ከተመዘገበው የበሽተኞች አሃዝ የበለጠ በመሆኑ ቫይረሱ በመላ ሀገሪቱ በስፋት ሳይስራጭ እንዳልቀረ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ዶ/ር ዚያድ በማከል ቫይረሱ ማስነጠስ ፤ የሰውነት መገጣጠሚያዎች ላይ ቁርጥማት ፤ የጡንቻ መዛል እና አልፎ አልፎ ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ትኩሳት እንደሚያሳይ ስለበሽታው አስከፊነት በማብራራት እንደዚህ አይነት የህመም ምልክቶች የታዩበት ማንኛውም ሰው አቅራቢያው ወደ ሚገኝ ጤና ጣቢያ ቀርቦ በአፋጣኝ ምርመራ እና ህክምና ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።


በዋንኛነት የመተንፈሻ አካልን እንደሚያጠቃ የሚነገርለት ይህ ክትባት ያልተገኘለት አደገኛ ጉንፋን መስል ገዳይ በሽታ «ኮሮና Corona » እስካሁን በአለማችን ላይ የተከስተው በሳውዲ አረቢያ እና ፈረንሳይ ብቻ መሆኑን የሚገልጹ የዘርፉ ባለሙያዎች ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው « በማስነጠስ እና በማሳል » በትናፋሽ አማካኝነት በቀላሉ የሚተላለፍ በመሆኑ በበሽታው የተለከፍው ታማሚ የሃኪም ምከር እና የቅርብ ከትትል ካላገኝ ቫይረሱ እስከ ሞት ሊያደርስው እንደሚችል ይናገራሉ።



ሳውዲ ውስጥ ተከሰተ በተባለው በዚህ አዲስ ጎንፋን መስል «የኮሮና Corona »ቫይረስ የተጠቃ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ቢታወቀም ስለበሽታው በሚገባቸው ቋንቋ መረጃ ሊደርሳቸው የማይችሉ በቤት ሰራተኝነት የተሰማሩ እህቶቻችን እና ሌሎች ወገኖች ከበሽታው እራሳችውን መታደግ ይቻላቸው ዘንድ ከወዲሁ ጥንቃቄ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

Ethiopian Hagere ጅዳ በዋ

Friday, April 11, 2014

ሰበር ዜና ባህር ዳር ከተማ የሰዎችን ህይወት የነጠቀ ግጭት ተነሳ ተኩሱ አሁንም እንደቀጠለ ነው::


በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 13 ሜትሮሎጂ ጀርባ በተለምዶ ዝንጀሮ ወንዝ በሚባለው አካባቢ የከተማው አስተዳደር የመኖሪያ ቤቶችን በግሬደር ማፍረሱን ተከትሎ በአካባቢው ነዋሪዎችና በታጣቂዎች መካከል  በተነሳ ግጭት ሁለት ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ የፍኖተ ነጻነት ምንጮች ከሶስት በላት ሰዎች መሞታቸውን የአይን ምስክሮችን ጠቅሰው ዘግበዋል፡፡  ከስፍራው የደረሰን መረጃ እንደሚያመላክተው ግጭቱ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን ተኩሱ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡  ዘግይቶ ከባህርዳር የደረሰን ዜና እንደሚያስረዳው ከሆነ በአካባቢው መንግስት ክላሽን ኮቭ ቦንብ እና ክላሽ የታጠቁ የፌደራል ሰራዊት  እና መትረየስ የተጠመደባቸው ጆፕ ተሽከርካሪዎች  ወደ አካቢው በማቅናት  ላይ ናቸው ።   See more at: http://www.fnotenetsanet.com/

Thursday, April 10, 2014

አቡጊዳ – የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የእሪታ ቀን ሰልፉን ከሶስት ሳምንታት በኋላ ለማድረግ ወሰነ !



መጋቢት 28 ቀን ይደረጋል ተብሎ የተጠበቀዉ የአንድነት የእሪታ ቀን ሰልፉ ፣ «ሰልፍ እንዲደረግ በታሰበበት ቀን፣ ሌሎች ዝግጅቶች ስላሉ በቂ ጥበቃ ልናሰማራ አንችልም» በሚል እውቅና ባለመስጠቱ ለሚያዚያ 5 ቀን መተላለፉ ይታወቃል።

የሚያዚያ አምስቱን ሰልፍ በተመለከተ ምላሽ የሰጠው የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ በሚያዚያ 5 ቀን ፣ ሩጫ ስለሚኖር ሰልፉ ለቅዳሜ ሚያዚይ 4 ቀን እንዲደረግ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለአንድነት ፓርቲ የላከ ሲሆን፣ የሚያዚያ አራቱን ቀን ፣ ቅዳሜ በመሆኑና ግማሽ ቀን ሥራ የሚኖራቸው በርካታ ዜጎችን ስለሚኖሩ፣ አስተዳደሩ በጠየቀው ቀን ሰልፉን ለማድረግ ፍቃደኛ እንዳልሆነም የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።

የአንድነት ከፍተኛ አመራሮች በጉዳዩ ላይ መክረዉበት ፣ የሚቀጥሉት ሁለት እሁዶች የባህል ቀናት እንደመሆናቸው፣ ከሶስት ሳምንታት በኋላ ሰልፉን ለማድረግ ማሰባቸውን ያነጋገርናቸው ከፍተኛ የአንድነት አመራር አባል ገልጸዉልናል።
ያንን በተመለከተ አስፈላጊዉን የማሳወቅ ደብዳቤ ለአስተዳደሩ የሚያስገቡ ሲሆን፣ በዚህ ሂደት፣ የተለያዩ ሩጫዎችን ለማስተናገድ ሲባል፣ መንገዶች ሲዘጉ፣ የትራፊክ መጨናነቅና የልማት ሥራ መደናቀፍ ሲፈጠር፣ ያላሳሰበው፣ የአዲስ አበባ አስተዳደሩ፣ ሕዝቡ ሕግ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ ድምጹን ለማሰማት ሲዘጋጅ ይጨናነቃል፣ «የልማቱ ሥራ ይደናቀፋል፣ የትራፊክ መጨናነቅ ይኖራል» እያለ እውቅና አለመስጠቱ አሳዛኝ እንደሆነ የሚናገሩት የአመራር አባሉ ፣ «የኛን ሞራል ሞራል ለማዳከም የሚያደርጉት አሳዛኝ እንቅስቃሴ፣ ዉጤት እንዳመጣላቸው፣ ይልቅስ የበለጠ በቁርጠኝነት እንድንነሳ የሚያደርግ መሆኑን አውቀው፣ ከሶስት ሳምንት በኋላ አስፈላጊዉን ትብብር ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አለኝ» ሲሉ 
በፓርቲያቸው ዘንድ ያለውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
የአንድነት ፓርቲ መጋቢት 28 ቀን በደሴ ከተማ እጅግ ታልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉ ይታወቃል። ፓርቲዉ ከደሴና ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአዋሳ፣ ድረዳዋ፣ አዳማ በመሳሰሉት ወደ 14 በሚጠጉ ከተሞች ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ እየተዘጋጀ እንደሆነም በስፋት ተዘግቧል።

Tuesday, April 8, 2014

ወ/ሮ አስቴር ማሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ተሾሙ።


Aster Mamo - Dep. PM Ethiopiaወ/ሮ አስቴር ማሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማእረግ የመልካም አስተዳደር ሪፎርም ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር በመሆን ተሾሙ።
የወይዘሮ አስቴር ማሞን ሹመት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም  ደሳለኝ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አስፀድቀዋል።
ምክር ቤቱም  ሹመቱን በሙሉ  ድምፅ  ያፀደቀ  ሲሆን፥  ወይዘሮ አስቴር  ማሞም በምክር ቤቱ  ፊት ቃለ መሃላ  ፈፅመዋል።
ወይዘሮ አስቴር የመጀመሪያ  ድግሪያቸውን በቋንቋና ስነ ፅሁፍ የሰሩ  ሲሆን፥  ሁለተኛ  ድግሪያቸውን በኦርጋናይዜሽናል ሌደርሺፕ አግኝተዋል።
ከ1991 ዓመተ ምህረት እስከ 1993 ድረስ የዞን ካቢኒ አባል፣ ከ1994 እስከ 1997  የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ፣ ከ1998 እስከ 2002  የኢፌዴሪ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር፣ ከ2003 እስከ 2004 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና  ተጠሪ ሚኒስትር  በመሆን አገልግለዋል።
እስከ  ተሾሙበት  ቀን ድረስም የኦሮሚያ  ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማእረግ  የፕሬዚዳንቱ የህዝብ ግኑኝነት አማካሪ በመሆን  ሰርተዋል።
ወይዘሮ አስቴር  ማሞ  በአሁኑ ወቅት  የኦሮሞ  ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ኦህዴድ/ ምክትል  ሊቀመንበር ናቸው።
*******
ምንጭ፡- ፋና – መጋቢት 30/200