Friday, January 31, 2014

አስገራሚ ዜና – ሽመልስ ከማል ተሳደቡ፣ አስፈራሩ






አስገራሚ ዜና – ሽመልስ ከማል ተሳደቡ፣ አስፈራሩ “በአብዛኛዎቹ የህትመት ሚዲያዎች ላይ የሚታየው ማስታወቂያ እንጥል እቆርጣለሁ፣ ግግ እቧጥጣለሁ የሚል የአንድ ደብተራ ማስታወቂያ ነው” አቶ ሽመልስ ከማል መንግስት የህትመት ውጤቶች አከፋፋዮች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ፍንጭ ሰጠ በዘሪሁን ሙሉጌታ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በሀገሪቱ ውስጥ ፈርጀ ብዙ ኀሳቦች ለህብረተሰቡ እንዳይደርስ እያደረጉ ነው ባሉዋቸው የጋዜጣና መፅሔት አከፋፋዮች ላይ መንግስት በፍጥነት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቁ። 
ሚኒስትር ዴኤታው ይሄህን የተናገሩት “የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስትና የመገናኛ ብዙኃን ግንኙነት” በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጆርናሊዝምና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት በኢንተርኮንቲነታል ሆቴል ሰሞኑን ባዘጋጀው የአንድ ቀን ሲምፖዚየም መዝጊያ ላይ ነው። የፕሬስ ነፃነት አፈና ሲነሳ በአከፋፋዮች አማካኝነት የሚደረግ አፈና አንዱ መሆኑን በመጥቀስ ጥቂት መፅሔቶችንና ጋዜጦችን በባለቤትነት የያዙ ግለሰቦች የማከፋፈል ስራውን በሞኖፖል ይዘው የአመለካከት ፈርጀ ብዙነት እንዳይኖር በማድረግ፣ በርካታ ህትመቶችን በለጋነታቸው ለሞት እንዲበቁ በማድረግ የአፈና ስራ ውስጥ የገቡ ወገኖች አሰራራቸው በፍጥነት መስተካከል አለበት ብለዋል። “ሚዲያን የመደጎምና የማስተካከሉ ስራ መንግስት በአግባቡ በተጠና ሁኔታ መግባት እንዳለበት ያምናል” ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው በሚዲያ የኀሳብ ገበያ ውስጥ ምቹ ሁኔታዎችን በማዘጋጀት ለኢንዱስትሪው ቀና እድገት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአከፋፋዮች በኩል በርካታ ችግሮች ተለይተው እየተጠኑ መሆኑንም ጠቁመዋል። የህትመት ሚዲያው ብቻ ሳይሆን የሕዝብ የመገናኛ ብዙኀን አውታሮች ከችግሮች ነፃ አለመውጣታቸውንም የጠቀሱት አቶ ሽመልስ መንግስት ፈጣን መረጃ የሚሰጥ የሚዲያ ስርዓት እንዲፈጠር እንደሚፈልግ ገልጸዋል። 
መንግስት መረጃዎችን በገፍ የሚያቀርብ፣ ጥራት ባለውና ወቅታዊ በሆነ መንገድ የሚሰራ የሚዲያ ስርዓት እንዲገነባ ይፈልጋልም ብለዋል። ብሔራዊ የሚዲያ ፖሊሲው በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የህብረተሰቡን የፖለቲካ ብዙሃነት፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ፈርጀብዙነት ከመቀበል የሚነሳ መሆኑ አስታውሰው፤ ነገር ግን ሚዲያው በማንኛውም የባለቤትነት ውስጥ ቢሆንም ብሔራዊ መግባባትን ለማስረፅ መተኪያ የሌለው ቀዳሚ ሚና እንዲጫወት ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል። ሚዲያው በብሔራ ዊ መግባባት ላይ እንዲሰራ መንግስት ቢፈልግም ከማንኛውም ርዕዮተዓለም ተፅዕኖ ነፃ እንዲሆን ይፈልጋል ብለዋል። አሁን ያለው የሚዲያ ችግር በንግድ ሚዲያ መርህ ወይም በገበያ መርህ መንቀሳቀስ አለመቻል መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሽመልስ አብዛኛዎቹ ሚዲያዎቻቸው ገበያቸውን ከማስታወቂያ የሚሸፍኑ አይደሉም ብለዋል። “በአብዛኛዎቹ የህትመት ሚዲያዎች ላይ የሚታየው ማስታወቂያ “እንጥል እቆርጣለሁ፣ ግግ እቧጥጣለሁ” የሚል የአንድ ደብተራ ማስታወቂያ ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ ማስታወቂያ የላቸውም። ኮሜርሺያል አይደሉም፤ ኮሜሪሻያል ካልሆኑ ይደጎማሉ። በድጎማ የሚተዳደሩ ከሆነ ታማኝ አንባቢ ነው ያላቸው። ከተወሰኑ ርዕዮተአለማዊ አጥሮች አልፈው መጓዝ አይፈልጉም። ስለሆነም የህትመት ሚዲያ እድገት ላይ አንድ ትልቅ ጋሬጣ የሆነው ከነፃ ሚዲያ ህግጋት ውጪ ተንጋዶ የበቀለ የሚዲያ አካሄድ ነው” ያሉት አቶ ሽመልስ ይህንን ለማስተካከል መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች ሊተባበሩ ይገባል ብለዋል። የሰንደቅ ዜናዎች (ጥር 21/2006)
ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ

Wednesday, January 29, 2014

በ6 የሱዳን ወጣቶች የተደፈረችው ኢትዮጵያዊት በእስር ላይ እንደምትገኝ ታወቀ





ቀድሪያ እንድሪስ የተባለች ኢትዮጵያዊት ወጣት በ6 የሱዳን ወጣቶች እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ ስትደፈር የሚያሳይ ቪዲዮ ኢሳት የደረሰው ሲሆን ፣ ካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ የዲያስፖራ ክፍል ሃላፊ የሆኑት አቶ አረጋ ልጂቷ መደፈሩዋን አምነው ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ግን ከፍተኛ ባለስልጣኖች መፍቀድ አለባቸው በሚል ዝርዝር ጥያቄዎችን ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ጥቅምት ወር አካባቢ ቤት ለመከራየት በአካባቢው የነበሩትን ወጣቶች የጠየቀችው ኢትዮጵያዊት፣ ወጣቶችም ” እኛ የሚከራይ ቤት እናሳይሻለን” ብለው በመውሰድ በአሰቃቂ ሁኔታ እየደፈሩ በእርቃኑ ላይ የተለያዩ አስጸያፊ ስራዎችን እየሰሩ በቪዲዮ እየቀረጹ ተጫውተውባታል።
ለራሱ ምስል የተጠነቀቀው የሱዳን መንግስት ቀድሪያንና ሞርጋን ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ አስሮአት እንደሚገኝ ኢሳት ከኢምባሲው የውስጥ ምንጮች መረጃ የደረሰው ሲሆን፣ የኢምባሲው የዲያስፖራ ሃላፊ ግን ልጅቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች ብሎአል። የሱዳን ፍርድ ቤት ድርጊቱ ሲፈጸም በወቅቱ ለምን ሪፖርት አላደረግሽም በሚል ወጣቷንም ተጠያቂ ለማድረግና የአገሪቱን መንግስት ከተጠያቂነት ለማውጣት እንቅስቃሴ መጀመሩን የውስጥ ምንጮች የገለጹ ሲሆን፣ ወጣቷ በበኩሏ ” መረጃውን የምታወጪው ከሆነ እንገድልሻለን ስለተባለች በፍርሃት በወቅቱ ሪፖርት ለማድረግ እንዳልቻለች ገልጻለች።” በአሁኑ ጊዜ ወጣቷ ከማንኛውም ሰው ጋር እንዳትገናኝ በመደረጓ ኢሳት ለማነጋገር ሳይችል ቀርቷል። ወጣቷን በእስር ቤት ለማነጋገር የሚፈልጉ ሰዎች ልዩ ወረቀት ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ማምጣት የሚኖርባቸው ሲሆን፣ አንዳንድ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ወጣቷን ለመጠየቅ ፈልጎ በወረቀት ክልከላ ምክንያት ሳይችል ቀርቷል።
በወንጀል ከሚፈለጉት ወረበሎች መካከል የተወሰኑት የታሰሩ ቢሆንም ሌሎች ደፋሪዎች ግን እስካሁን አለመታሰራቸው ታውቋል። በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳዩን እየተከታተልኩት ነው ቢልም እስካሁን በእስር ላይ የምትገኘዋን ወጣት ለማስፈታት አልቻለም።
ወጣቷ በአሁኑ ጊዜ ነፍሰጡር ስትሆን፣ የእርግዝናዋ ምክንያት ከመደፈሩዋ ጋር የተያያዘ ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም.

ምንጭ ኢሳት ዜና 

ኢሳት ዜና :-
ኢሳት ዜና :-

Tuesday, January 28, 2014

በእውነት ወያኔ የተረከበው የፈራረሰ አየርሃይል ነበርን? አየር ሃይልስ እንዴት ተያዘ?

ፋንታ በላይ

MiG-23 Flogger Tactical Fighter Jet
የስነ ስሁፍ ሰው አይደለሁም:: ይህንን ስሁፍ እንድጽፍ ያስገደደኝ ግን በኢትዮጳያ ቴሌቪዝን አየር ሃይልን በተመለከተ የተላለፈው ዜና ነው:: በዚሁ ዜና ላይ ያሁኑ አየር ሃይል ኢንዶክትሪኔሽን ሃላፊ ኮሎኔል አስፋው ማመጫ በ 1983 ሰለነበረው አየር ሃይል ሲያስረዱ ” በ1983 የተረከብነው የደከመ የፈራረሰና የወደቀ አየር ሃይል ነበር” [i] በማለት እጅግ አስቂኝና ከውነት የራቀ መግለጫ ሰተዋል:: አዲሱ ትውልድ ስለቀደመው አየር ሃይል እውነት ጥቂትም ቢሆን ያውቅ ዘንድና አየር ሃይሉ ምን ይመስል እንደነበር እንዴትስ እጅ እንደሰጠ በጥቂቱ ልጽፍ ወደድኩ::
በመጀመርያ ወያኔ አየር ሃይሉን ሲረከብ ምን እንደሚመስል እንመልከት
MiG-23 Flogger Tactical Fighter
1. የውጊያ የስለላና የትራንስፖርት አውሮፕላኖች
ወያኔ ግንቦት 1983 አየር ሃይሉን ሲቆጣጠር አየር ሃይሉ በበርካታ ዘመናዊ አውሮፕላኖች የታጠቀ ነበር:: በውጊያ አውሮፕላኖች ዘርፍ ሚግ 23 : ሚግ 23 ፍሎገር እና ሚግ 21 የተባሉ ሱፐር ሶኒክ የአየር ለአየርና ያየር ለምድር ተዋጊ ጀቶችን ( ሚግ 23 ማክ 3 ነው:: ይህም ማለት ከድምጽ ፍጥነት ሶስት ግዜ ይፈጥን ነበር) የታጠቀ ነበር:: ሚ 24 (ነጮቹ flying tank ይሉታል) እና ሚ 35 የተባሉ ከጠላት ጋር እየተናነቁ መዋጋት የሚችሉ ሄሌኮፕትሮችም የአየር ሃይሉ ንብረቶች ነበሩ:: ሚ 35 ከጠላት የሚተኮስበትን ጸረ አየር ሊከላከልና አቅጣጫ ሊያስቀይር የሚችል እስከ 12 ጸረ ታንክ ሚሳኤሎችን መታጠቅ ይችላል:: በግዜው ( 1970 ዎቹ መጨረሻ) ሚግ 23 ፍሎገርና ሚ 25 ሄሌኮፕተሮችን የታጠቀች የመጀመርያዋ ሰብ ሰሃራ ሀገር ኢትዮጵያ ነበረች::
በትራንስፖርቱም በኩል ወያኔ አየር ሃይሉን ሲረከብ አየር ሃይሉ አንቶኖቭ(Antonov 12,22,260) : ሲ- 130 እና ቲ ዩ( TU) የተባሉ ዘመናዊ የትራንስፖርት አውሮፕላኖች ነበሩት:: አንቶኖቭ ከትራንስፖርት ጠቀሜታው ሌላ በርካታ ቦንቦችን ጭኖ ውጊያ ላይ መሳተፍም የሚችል ሶቪየት ሰራሽ አውሮፕላን ሲሆን ሲ 140 ም ተመሳሳይ አገልግሎትን የሚሰጥ አሜሪካ ሰራሽ አውሮፕላን ነው:: ቲ ዩ የተሰኘው አውሮፕላን ደግሞ የአገሪቱ ርእሰ ብሔር ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ልዩ የትራንስፖርት ጀት ነው:: ወያኔ የደብረዘይቱን የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና ቤዝ ሲቆጣጠር በነዚህ ሁሉ የውጊያና የትራንስፖርት አውሮፕላኖች የተደራጀን አየር ሃይል ነበር የተረከበው::
በቁጥር መልኩ ሲተነተን አየር ሃይሉ በጠቅላላው 112 ሚግ 21 ተዋጊ ጀቶች: 37 ሚግ 23 የአየር ለአየርና የአየር ለምድር ተዋጊ ጀቶች: 15 ሚግ 17 : 20 አንቶኖቭ 12: 18 አንቶኖቭ 26 : 5 አንቶኖቭ 22: አስራ ሱኮይ ሰባት ጀቶች: አርባ ሶስት ሚ 8 እና ሰላሳ ሚ 24 ተዋጊ ሄለኮፕተሮች ነበሩት:: ከነዚህ ውስጥ ወያኔ ደብረዘይትን ሲቆጣጠር በርካቶቹን ተረክቧል::
2. አየር መቃወሚያና የስለላ ራዳሮች
ከአየር ሃይሉ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የኢትዮጵያን ያየር ክልል ለመጠበቅ የተቋቋመው ሌላው ክፍል ደግሞ አየር መከላከያ ነበር:: ወያኔ በ 1983 የደብረዘይትን ኤር ቤዝ ሲቆጣጠር አየር መከላከያ እጅግ ዘመናዊ በሆነ ራዳርና ሚሳኤሎች የተደራጀ ነበር:: በተለይ ቮልጋ ፐትቼራና ስትሬላ ( Volga, Petchera, stinger, SAM) የተባሉ በርካታ የአየር መቃወሚያ ሚሳ ኤሎችን የታጠቀ ነበር::ግንቦት 1983 ወያኔ አየር ሃይሉን ሲይዝ ሙሉና የተደራጀ አየየር መከላከያን ነበር የተረከበው:: የሚደንቀው እሰከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ የአየር መቃወሚያ ባለሙያዎች አገሪቷ ላይ ያለ የውጭ ሀገር ጀቶች እንዳይገቡ የሙያ ግዴታቸውን ሲወጡ ነበር:: ወያኔ ሲገባም ሙያቸው ያገሪቱንያየር ድንበርን ማስጠበቅ እንደሆነና ወያኔም ስለአየር መቃወሚያ ሚሳኤሎቹ ግንዛቤ እስኪያገኝ ድረስ ክፍሉን እንዳይበትናቸውና በመሃል የጠላት ሀገር ጀቶች ገበተው ኢትዮጵያን እንዳይጎዷት ለወያኔው የጦር አዛዥ ግንቢት 1983 ወያኔ አየር መከላከያን እንደያዘ ወዲያ እዛው ግቢ ውስጥ ጥያቄ አቅርበውለት ነበር::
3. የጥገገናና የድጋፍ ሰጭ ክፍሎች
ለነዚህ አውሮፕላኖችና ሚሳኤሎች ጥገናና አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ደጋፍ ሰጭ ክፍሎችም ነበሩት:: ተዋጊ ጀቶች : ሄሌኮፕተሮችና ትራንስፖርት አውሮፕላኖች የሚጠገኑበት በርካታ ሃንጋሮች ወያኔ ሲገባ አብሮ የተረከባቸው የአየር ሃይሉ አካላት ናቸው:: እነዚህ የጥገና ሃንጋሮች ወያኔ ገብቶ እስኪረከባቸው ድረስ ሙሉ ነበሩ:: አንዲትም ብሎን እንኳን አልተነካችም ነበር:: ከዚህም ባሻገር የአውሮፕላን ስፔር ፓርቶችን ሞዲፊክ የሚሰሩ አሰደናቂ ማሽን ሾፖችም እና ውድ ወርክ ሾፖችም የአየር ሀይሉ ስውር አካላት ነበሩ:: እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ በተለይ ማሽን ሾፕ በርካታ የአውሮፕላን መለዋወጫዎችን በሞዲፊክ ይሰራ ነበር:: ወያኔ በ1983 ሲገባ የተረከበው እነዚህን ሙሉ ሀንጋሮች ጭምር ነበር::
4. የሰው ሃይል ማሰልጠኛ ኮሌጆች
እነዚህን ስራ የሚሰሩ ባለሙያዎንና ተዋጊዎችን የሚሰለጥኑበት የሁለት ድንቅ ኮሌጆችም ባላቤት ነበር – ወያኔ የተረከበው የኢትዮጵያ አየር ሃይል:: የመጀመርያው የበራሪዎች ማሰልጠኛ ኮሌጅ ሲሆን ሁለተኛው በተለምዶ ግራውን ስኩል በመባል የሚታወቀው የግራውን ቴክኒሻን ማሰልጠኛ ኮሌጅ( ground technician college) ነው:: እነዚህ ሁለት ኮሌጆች በጊዜአቸው በአፍሪካ አሉ ከሚባሉ ማሰልጠኛዎች የሚጠቀሱ ነበሩ:: ራሺያና ሌሎች ሀገራት ሰልጥነው የሚመጡ ተማሪዎች እንኳን ስራ ከመጀመራቸው በፊት እነዚህ ኮሌጆች ውስጥ ገበተው መፈተን ነበረባቸው::አየር ሃይሉ በነዚህ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የታነጹ የባለሙያዎችና የተዋጊዎች መናሃርያ ነበር::ወያኔ ሲገባ የተረከበው እነዚህን ኮሌጆች ጭምር ነበር::
5. ማህበራዊ ተቋማትን በተመለከተ
የሰራዊቱን አካላት ለመደገፍ ይረዳ ዘንድ በርካታ ተቋማት በአየር ሃይሉ ውስጥ ነበሩ:: የሰራዊቱ አባላት ከራሳቸው ደሞዝ እየተቆረጠ ስራው የተጀመረ እጅግ ዘመናዊ ሆስፒታል ነበር:: የሰራዊቱን አባላትም ከስውር የገበያ ጥቃት ( የተመረዘ ምግብ ) ለመሰወርና ለመከላከል ኮሚሴሪ በመባል የሚታወቅ የህብረት ስራ ንግድ ማዕከል ነበር:: ይህ ድርጅት የተለያዩ የፍጆታ እቃዎችን ለአየር ሃይሉ አባላት በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ሃላፊነት ተሰጥቶት የሚንቀሳቀስ ራስ አገዝ ( economic cooperative) ሲሆን ሁለት የመዝናኛ ክበቦችም ( ኦፊሰርስ ክለብ እና ኤ ን ሲ ኦ ክበብ) ነበሩት:: በግዜው በከተማው ብቸኛ ፊልም ቤትም የነበረው አየር ሃይሉ ብቻ ነበር:: ያየር ሃይሉ እና አየር ወልድ አባላትም ሲያርፉ ሬሳቸው በከብር የሚያርፍበት እጅግ ያማረና በወታደራዊ ዘቦች የሚጠበቅ የመቃብር ቦታ በደብረ ዘይት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስትያን ተከልሎ ነበር:: ይም መቃብር የጦሩ የክብር መቃብር ስለነበር ከአየር ሃይልና ከአየር ወለድ ውጭ ማንም አይቀበርበትም ነበር:: ወታረዶችም ተመድበውለት ይጠበቅ ነበር:: እጅግ በጣምም ያማረና ማራኪ ቦታ ነበር::
6. የሰው ሃይል
የሰው ሃይልም ደረጃ አየር ሃይሉ ከ 6 እሰከ ሰባት ሺህ የሚደርሱ ባለሙያዎች ነበሩት:: እነዚህ ባለሙያዎች በአሜሪካ : ሩስያ: ሰሜን ኮርያ : ቼኮስላቫኪያ: እስራ ኤል ወዘተ የሰለጠኑ ብቃት ያልቸው ብሔራዊና አለማቀፋዊ ምሁራን ነበሩ:: ይህም ሰራዊት ወታደራዊ መኮንንኖችንና ሲቪል ባለሙያዎችን ያካተተ ነበር:: በርካቶቹ አባላት የአቪዬሽን መሃንዲሶች: የጥገና ባለሙያዎች : የአየር ላይ intellegence አማካሪዎች ነበሩ::
ወያኔ ሀሜን ሲቆጣጠር ( ሀሜ ሀረር ሜዳ ማለት ሲሆን ደብረዘይት የሚገኘው ያየር ሃይሉ ዋና ጣብያ ሀሜ ይባል ነበር:: ) የተረከበው እነዚህን ሁሉ ነው:: በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጊያና የትራስፖርት አውሮፕላኖች: በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳ ኤሎች: ሁለት ትልለቅ ስቴዲየሞች: የአየር ሃይል ቁጠባ ባንክ: ያያር ሃይል ሆስፒታል: ሁለት ዝነኛ ያይር ሃይል ማሰልጠኛ ኮሌጆች : ራዳሮችና ከ ስድስት እሰከ ሳባት ሺህ የሚቆጠሩ ያያር ሃይል ባላሙያዎችን ነበር::
ያሁኑ አየር ሃይል ኢንፎክትሪኔሽን ሃላፊ ኮሎኔል አስፋው ማመጫ ” የተረከብነው አየር ሃይል የተዳከመ የፈራረሰ እና የወደቀ አየር ሃይል ነበር” የሚለው መግለጫ በፍጹም ህሰትና ከውነት የራቀ ነው:: ኮሌኔሉ ወይ አየር ሃይሉን አያውቀውም ነበር ወይ ደግሞ አድር ባይነት ያጠቃው ይመስላል:: እውነትን እውነት ማለት ግን ጅግንነት ነበር:: የሚደንቀው ግን አያር ሃይሉን ያወደመውና የበታተነው ራሱ ወያኔ መሆኑ ነው:: ይሄንንም ያይን እማኝነቴን ከዚህ በታች እገልጸዋለሁ:: በመጀመርያ አየር ሃይል እንዴት ተያዘ?
ኣየር ሃይል እንዴት በሰላም እጁን ሰጠ?
እግረኛው የጦሩ ክፍል እየሸሸ በመጣባቸው ቦታዎች የወያኔን ጉዞ ለመግታት ከፍተኛ ውጊያ ሲያደርግ የነበረው አየር ሃይሉ ነበር:: ይሄን ወያኔ አሳምሮ ያውቀዋል:: በተለይ ሄሌኮፕተሮችና ተዋጊ ጀቶች እጅግ በርካታ ግዜ በመመላለስ ከእግረኛ በከፋ ሁኔታ ተዋግተዋል:: በተለይም ወያኔ ነጻ አወጣሁ በሚላቸውና የኢትዮጵያ ሰራዊት በሌለባቸው ቦታዎች ላይ ብቸኛው ተዋጊ አየር ሃይሉ ነበር::
እንደ አየር ሃይልም እንደ እግረኛም ታች ድረስ በመውረድ ፓይለቶቻችን ሰፊ መስዋትነት ከፍለዋል:: በስተመጨረሻም ወያኔ የደብረ ዘይትን አየር ሃይል ሊይዝ ውጊያ ሲያደርግ ከፍተኛ እልቂት እንደሚደርስ ተፈርቶ ነበር:: ጨፌ ዶንሳ ( ከደብረ ዘይት ወጣ ብሎ የሚገኝ ቦታ ነው) ላይ እጅግ አስከፊና ደም እንደውሃ ያፋሰሰ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ የወያኔ ጦር ወደ ኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና ቤዝ ወደ ደብረ ዘይት ሲገባ አየር ሃይሉ በሁለት ሃሳብ ተከፍሎ ነበር::
የመጀመርያው ” የአየር ሃይልን ግቢ እንዲሁ አናሲዝም እስከመጨረሻው እንዋጋለን:” የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “ደብረ ዘይት ላይና አየር ሃይል ግቢ ውስጥ ባለን መሳርያ ውጊያ ከጀመርን የሚወደመው ሀገሪቷ ለበርካታ ዘመናት የገነባችው አየር ሀይልና በውስጡ ያሉት የአቪዬሽን ባለሙያዎች : መሳርያዎች ይበልጡኑ ደግሞ የደብረ ዘይት ሕዝብ ስለሆነ አየር ሃይሉ ግቢ ውስጥ ባንዋጋ ይሻላል” የሚል ነበር:: በስተመጨረሻም ከተማው ውስጥ እንዳይገቡ ከፍተኛ ውጊያ እንዲደረግና ከተማው ውስጥ ከገቡ ግን በተለይም የአየር ሃይል ግቢ ውስጥ ውጊያ መግጠሙ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ስምምነት ላይ ተደረሰ:: በተለይ አየር ሀይሉ ግቢ ውስጥም የሚከፈተው የጅ በእጅ ውጊያ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ስምምነት ላይ ተደረሰ::
ይህም ምክንያቱ አንደኛ አየር ሀይሉ ውስጥ ተከዝነውና ተከማችተው ያሉት መሳርያዎች ይልቁንም ናፓልና ክላስተር ቦምቦች ቢመቱ ከተማዋ በሙሉ ልትጠፋ ትችላለች የሚል ሲሆን: ሁለተኛው ደግሞ አየር ሀይሉ ግቢ ውስጥ ያሉት በርካታ አገሪቱ በዲፕሎማሲና በከፍተኛ ወጭ ለሃምሳና ስልሳ አመት የገነባቸው ያቪዬሽን ቴክኖሎጂ ይወድማሉ የሚል እሳቤ ስለነበር ነበር:: ይሄንንም ተቋም ሀገሪቱ መልሶ ለመገንባት ሌላ ስልሳ አመት ይፈጅባታል:: በዚህ መሃልም የጠላት አየር ሀይል እንደፈለገው በኢትዮጵያ አየር ክልል ውስጥ ሊፈነጭ ይችላል የሚል ነበር:: ከተማዋን ከውድመት ለመታደግና አየር ሃይሉን ከጥፋት ለመታደግ አየር ሃይል ግቢ ውስጥ ወጊያ እንዳይካሄድ ስምምነት ላይ ተደረሰ:: ደብረ ዘይት ዙርያ በተለይ ጨፌ ዶንሳ : የረር ላይ ከፍተኛ ትንንቅ ተካሄደ:: በውስጥ አዋቂና ባንዳ ይመራ የነበው ወያኔ ግን ሳይታሰብ ሾልኮ ደብረዘይትን ተቆጣጣረ:: አየር ሀይልም እንደቀልድ በሰላም ተያዘ::
አስደናቂውና ወደር የለሹ በቀል _ ወያኔና አየር ሃይሉ
ወያኔ አገረቱን ከተቆጣጠረ በኋላ አየር አየር ሃይሉን ላገሪቷ ጥቅም ይጠቀምበታል የሚል እሳቤ ነበር:: ቢያንስ ፓይለቶቹንና ወታደራዊ መኮንንኖቹን ባይቀበል እንኳን ሲቪል እና የሙያ ሰዎች የሆኑትን አረጊቷ በከፍተኛ ወጭ ያሰለጠነቻቸውን የበረራ መሃንዲሶችና ሌሎች ባለሙያዎችን ይበትናል ተብሎ አልታሰበም ነበር:: ምክንያቱም እነዚህ አካላት አውሮፕላኖችንን ከመጠገን : ስፔር ፓርቶችን ከማምረትና ስለ አቪዬሽን ከማስተማር ውጭ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ውስጥ ምንም ተሳትፎ ያልነበራቸው ንጹህ ሲቪል ባለሙያዎች ነበሩ::
ወያኔ አየር ሀይሉን ያለምንም ውጊያ ከያዘ በኋላ የመጀመርያ ስራው ማፍረስ እና ማፈራረስ ሆነ:: አየር ሃይሉ እንደሀገር ንብረት ሳይሆን በሚገርም ሁኔታ እንደጠላት ጠላት ንብረት ታይቶ ተበዘበዘ:: እጅግ በከባድ ወጭ ተገዝተው የተተከሉ ማሽኖች በሙሉ ከአየር ሃይሉ እየተፈቱ ተጫኑ :: በትልልቅ መኪኖችም እየተጫኑ በሌሊት ይጓዙ ጀመር:: በተለያየ ሀገር ተምረዉ ( ከምስራቁም ከምራቡም ዓለም) ከፍተኛ ያቪዬሽን እውቀት የነበራቸው የበረራ እና የአውሮፕላን ጥገና መምህራን እየታደኑ ጦላይና ብላቴ ታሰሩ:: ቀላል ቁጥር የሌላቸው ባለሙያዎች በጦላይና ብላቴ በረሃ በወባና ኮሌራ አለቁ::ይህም የተደረገው ሆን ተብሎ ነበር:: ጥቂት የማይባሉትንም ፓይለቶች ወያኔ እያደነ አረመኔያዊ በሆነ ሁኔታ ገደላቸው:: በተለይም ባይኔ ያየሁት የኮለኔል ጥላሁን ግድያ የማይረሳ ነበር:: በአየር ሃይሉ ውስጥ የሚገኘውንም የአየር ሃይል ቁጠባ ባንክ በዝርፊያ የተካነው ወያኔና ጀሌዎቹ ዘረፉት:: ያሁሉ ያየር ሃይል አባልና ቤተሰቡ ያለደሞዝና ጡረታ ንብረቱ ተዘርፎ ተበተነ:: ተራው የወያኔ ወታደርም የበርካታ አውሮፕላኖችን መስታውታቸውን በመሰበር እና ውስጣቸው ያሉትን የተለያዩ ሲስተሞችን በስለትና በብረት በጣጠሱት::በድንጋይ አውሮፕላን ማረክን እያሉም ዘፈኑ:: የአየር ሀይሉ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሚገኙ ልዩ ልዩ የስለላ ሚስጥሮችን : መዛግብትንና የጦሩ መረጃዎችን እንደቀልድ በተኗቸው:: ያየር ሀይሉን ማሰልጠኛ ትምርት ቤቶችና ቤተ መጻህፍት ዘበዙት:: ማንም ተራ ወታደር ቤተ መጻሕፍት ገብቶ መጽሃፍ መዝረጥ እያደረገ ማንደድና እሳት መሞቅ ይችል ነበር:: መጻሕፍቶቹ የሚያወጡት ዋጋ ; የያዙት ቁም ነገር ለነሱ ትርጉም አልነበረውም:: ምናልባትም ጀቶቹ በራሳቸው ድንገት የሚነሱ እየመሰላቸው ይመስላል : በከፍተኛ ወጭ የተገነባውን የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ በታንክ ሄዱበት :: ኮሚሴሪው : ክበባቱ: ሆስፒታሉ በሙሉ የጨፍጫፊው አየር እየተባለ ብትንትኑን አወጡት:: አየር ሃልን አፈረስነው እያሉ ደስታቸው ወሰን አጣ:: የሚደንቀው ግን አየር ሃይሉ ግቢ ውስጥ ከወያኔ ጋር አብረው ገብተው በርካታ እቃዎችን እየመረጡ ሲያስጭኑ የነበሩት ሱዳኖችና ወደ ሱዳን መሆኑ ነው::
ነገር ግን የቀድሞው ያየር ሃይል ሰራዊቱ አባላት ወያኔ የቀድሞውን ሰራዊት ባያምን እንኳን የራሱን የሚያምናቸውን ሰው እንኳን አሰልጥኖ የኢትዮጵያን ያየር ክልል ያስጠብቅ ዘንድ በርካታ ተማጽኖዎች ያደረጉለት ነበር:: ያይር ሃይሉን እንዳልሆነ ሆኖ መመዝበር የሰሙት እስር ላይ ያሉ መኮንንኖችም በየግምገማው ወቅታ( ግምገማ እያሉ በየግዜው ይሰበስቡን ነበር) ያሰሙ የነበረው ለቅሶ ለነሱ ሳይሆን ላየር ሃይሉ ነበር:: እነሱን ባያምን እንኳን የኔ የሚላቸውን ሰዎች አሰልጥኖ አገሪቱ አየር ሃይል አልባ እንዳትሆን እንዲያደርጋት ከፍተኛ ተማጽኖ ነበር::
ወያኔ ወደ ልቡ ሲመለስ “የራሴን አየር ሃይል ማሰልጠን አለብኝ ” በማለት አየር ሃይሉን ከማፍረስ እንቅስቃሴው ተገቶ ስለ ስልጠና ማሰብ ጀመረ:: የተወሰኑ የቀድሞ አየር ሃይል አባላትን በመመለስም ስራዎች እንዲጀመሩ ሆነ:: ነገር ግን ወያኔ ለፓይለትነትና ለተዋጊነት እንዲሰለጥኑለት የሚፈልጋቸው ወታደሮች ትንሽ እንኳን ዘመናዊ ትምህርት ያልቀመሱ ለአስራ አምስትና ከዛ በላይ አመት ግዜያቸውን በበረሃ ላይ ያሳለፉ ትምርት ለመቀበል እድሜያቸው የገፋ ስለሆነ ሌላ ችግር ነበር:: ከሁሉም በላይ አሰልጣኞቻቸውንና አስተማሪዎቻቸውን የማይሰሙ እብረተኞች ሰለነበሩ በርካታ አውሮፕላኖች እየተከሰከሱ አለቁ:: በዘጠናዎቹ ብቻ ከ 13 የማያንሱ አውሮፕላኖች ወድቀዋል:: ይሄ ባየር ሃይሉ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ነበር :: በተለይ ሞጆ ገበያ ላይ የተከሰከሰው አወሮፕላን አይረሳም::
የሻቢያ ወረራ
ወያኔና ሻቢያ የጫጉላ የፍቅር ግዜያቸው ሲያልቅ ጦርነት ከፈቱ:: ወያኔም ሻቢያ ወረረችኝ አለ:: በሚያሳዝን ሁኔታ ተራ ፓይለት በተራ አውሮፕላን ትግራይን ያውም የህጻናት ትምርት ቤትን ባሰቃቂ ሁኔታ ደበደበ:: ከጣልያን በኋላ ያየር ክልሏ ተደፍሮ የማታውቀው ኢትዮጵያ ያየር ክልሏ ተደፍሮ በጀት ተደበደበች:: ወያኔ ግራ ገባው:: ሰባት አመት ሙሉ ያለ ደሞዝና ጡረታ በትኖ በረሃብ ሲቆላው ለከረመው ለኢትዮጵያ አየር ሃይል አባላት ጥሪ አቀረበ:: ለባንዲራውና ላገሩ ቃል የገባው ሰራዊት ግን ቂም ይዞ ጥሪውን እምቢ አላለም:: ሁሉንም ይቅር ብሎ በሚገርም ሁኔታ አየር ሀይሉን ድጋሚ አነሳው::
ሲጠቃለል ወያኔ የተረከበው አየር ሃይል የፈረሰ : የወደቀና የደከመ አየር ሃይል አልነበረም::የተረከበው ሙሉና ብቁ የሆነ አየር ሃይልን ነበር:: አየር ሃይሉን እንደጠላት ንብረት ያፈርሰውና ያረሪቱን አቪዬሽን ወደ ኋላ የጎተተው ራሱ ወያኔ ነው:: የአየር ሃይል አባላትን እንደ ሰው ሳይሆን እንደማርያም ጠላት ተጫውቶበታል:: የአየር ሃይል አባላት ገንዘብ ያጠራቅሙበት የነበረውን የቁጠባ ባንክ ዘርፎ የአያር ሃሉን አባላት ንብረትዘርፎ ያየር ሃይሉን አባላት ቤተሰብ በሙሉ ከድህነት በታች በማድረግ ከባድ ወንጀል የፈጸመው ወያኔ ነው:: ስንቱን ምሁር የበተነው ወያኔ ነው:: አየር ሃሉን እንደጠላት ንብረት ሙጥጥ አድርጎ የዘረፈውም ወያኔ እንጂ ሰራዊቱ አንዲት ብሎን እንኳን ሳትጎል ሙሉ አየር ሃይል ነበር ያስረከበው::
እንዲህ አይነት ከባድና አሰቃቂ ውንጀል ፈጽሞም ወረራ ሲመጣና ዳግም ጥሪን ሲያቀርብ የቀድሞው ጦር አባላት እምቢ አላሉም:: ምንም አይነት ቅሬታ ሳይሰማቸው ወደ አየር ሃሉ በመመለስ ወያኔ እንክትክቱን ያወጣውን አየር ሃይል ዳግም አቆሙት:: የሚገርመው ወያኔ ግን 7 up እያለ ያላግጥባቸው ነበር:: ( ከሰባት አመት በኋላ ወደ ስራ ስለተመለሱ):: በመሃልም ያለምክንያት በፈለገው ወቅት እየተነሳ ስንቱን ፓይለቶች ይጨርስ ነበር:: እነ ሻለቃ ዳንኤል ነፍስ ይናገር::
እናም እነ ኮሎኔል አስፋው
ባጭሩ ታሪክን መበረዝና መመራዝ ለማንም አይጠቅምም:: ወያኔ የተረከበው ሙሉና ብቁ የሆነ አየር ሃልን ነው:: አየር ሃይልን እንደጠላት ንብረት የዘረፈውና ያወደመው ራሱ ወያኔ ሲሆን እንደገናም ወያኔ ያወደመውን አየር ሃይል መልሶ ያቋቋመው ያው የጥንቱ አየር ሃይል አባላት መሆናቸው አይዘንጋ:: እውነት እውነት ናት::
በዚህ አጋጣሚ የምፃፍ ችሎታው ያላችሁ ይሰራዊቱ አባላት ለሚመጣው ትውልድ ያለውን እውነት ጽፋችሁ ብታስቀምጡት መልካም ስለሆነ ጥሪዬን አቀርባለሁ

በቂ ጥበቃ ያልተደረገለት ሰርግ በሰው ደም ተጨማልቆ ተጠናቀቀ


በዳዊት ሰለሞን


በአዲስ አበባ ሐምሌ 19 መናፈሻ ትናንት 18/05/2006 እሁድ 10፡00 ገደማ በሰርግ ታዳሚዎችና በአካባቢው በሚገኙ ወጣቶች መካከል በተነሳ ግጥት ብዙዎች ክፉኛ ተጎድተው ወደ የካቲትና ምኒልክ ሆስፒታሎች መወሰዳቸውን በሰርጉ የታደሙ ሰዎች ለፍኖተ ነጻነት ተናግረዋል፡፡
ፈረንሳዊ ዜግነት ያለው ሙሽራ ኢትዩጵያዊቷን በሚያገባበት ሰርግ ላይ ለመታደም ከ300 የሚልቁ ሰዎች በአዳራሹ በመገኘት የሙሽሮቹን ደስታ ሲካፈሉ ቆይተዋል፡፡የጥሪ ካርድ በመመልከት ወደ አዳራሹ እድምተኛውን ሲያስገቡ የነበሩ አስተናባሪዎች ያለ ጥሪ ወረቀት ወደ አዳራሹ ለመግባት ከፈለጉ ወጣቶች ጋር ሲጨቃጨቁ መቆየታቸውን የሚናገሩት የሐምሳ አለቃ ሹምዬ ያለው ሾልኮ ወደ አዳራሹ መግባት የቻለ ወጣት ከአንዲት እድምተኛ የእጅ ስልክ ሰርቆ ሊወጣ ሲል በመያዙ ጭቅጭቁ ወደ ለየለት ድብድብ ማምራቱን ይናገራሉ፡፡

‹‹ድንጋይ፣ ብረትና ዱላ ማንነት ሳይለዩ በሰው አካል ላይ ማረፍ በመጀመራቸው እጃቸው የተሰበረ፣ የተፈነከቱና የተረጋገጡ ሰዎች ብዛት ቁጥር አልነበረውም፡፡ከውጪ የነበሩ ወጣቶች ጓደኛቸው ሰርቆ ተይዟል መባሉን እንደውሸት በመቁጠር ድንጋይ መወራወር በመጀመራቸው መልስ ለመስጠት የሰርጉ ታዳሚዎች ያገኙትን ይዘው ድንጋይ ወርዋሪዎቹን መፋለም ይጀምራሉ፡፡በዚህ መሐል ከሁለቱም ወገን ለጉዳት በመዳረጋቸው ሆስፒታል መመላለስ የሰርጉ አዘጋጆች አጣ ፈንታ በመሆን ሰርጉ ተጠናቅቋል ››ብለዋል፡፡
ሰርጉን ለማጀብ የተገኙ ሁለት መኪኖችም በድንጋይ የፊትና የኋላ መስታወቶቻቸው ረግፎባቸዋል፡፡ሰርጉ እንዲከናወንበት አዳራሹን ያከራየው የሐምሌ 19 መናፈሻ አስተዳደር በቂ ጥበቃ ባለማዘጋጀቱና በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶችም ለራሳቸው ደህንነት በመስጋት መሰወራቸው ለሰው አካልና ለንብረት መጎዳት ከፍተኛ አስተዋእጾ ማበርከቱን ሐምሳ አለቃ ተናግረዋል፡፡

Monday, January 27, 2014

“የአዲስ አበባ ተማሪዎች ለከፍተኛ የስነ ምግባር ጉድለት ተጋልጠዋል”

prostitute-in-Addis-Ababa
  • ተማሪዎች ያለዕድሜያቸው ጫት፣ ሲጋራና ልቅ ወሲብ ይጀምራሉ
  • ሴት የቢሮ ሠራተኛ ሴቶች በወሲብ ንግድ ኑሮአቸውን ይደጉማሉ
  • ኢትዮጵያ ልጆችዋን እየከሰረች ነው
  • ትግራይ ጫት መቃም ክልክል ነው
  • “በስነምግባር የታነፁ ዜጐችን በማፍራት ረገድ አገሪቱ ፈታኝ ሁኔታ ላይ ናት”
በአዲስ አበባ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች፤ ለከፍተኛ የስነ ምግባር ጉድለቶች እንደተጋለጡ ጥናቶች አመለከቱ፡፡ ሰሞኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር “ስነምግባር ለእድገት ሁሉ መሠረት ነው” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በቀረቡት ጥናቶች በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፤ በየትምህርት ቤቶቹ አካባቢ ባሉ ህገወጥ የአልኮል፣ የአደንዛዥ እጽ መጠቀሚያ እና የወሲብ ፊልሞች ማሣያ ቤቶች መበራከት የተነሣ ለችግሩ ተጋላጭነታቸው በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ተጠቁሟል፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎች ወሲብ መፈፀም የሚጀምሩት በዚሁ የትምህርት ደረጃ ላይ እያሉ ነው ተብሏል፡፡ ከጥናት አቅራቢዎቹ አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ጽዮን አክሊሉ በጥናታቸው እንዳመለከቱት፤ ተማሪዎች ሲጋራ፣ የአልኮል መጠጥ፣ ጫት እና ልቅ ወሲብ የሚጀምሩት በአብዛኛው ሁለተኛ ደረጃ ከገቡ በኋላ ሲሆን 41.5 በመቶ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ሲጋራ ማጨስ እንደሚጀምሩ ጠቅሰው፤ 67.1 በመቶ ያህሉ ደግሞ በዚህ የትምህርት ደረጃ ወሲብ መፈፀም ይጀምራሉ ብለዋል፡፡
18.1 በመቶ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችም ያለ እድሜያቸው በሲጋራ ሱስ የሚጠመዱ ሲሆን 20.6 በመቶዎቹም በዚህ የእድሜ እርከን ውስጥ ወሲብ መፈፀም እንደሚጀምሩ ተጠቁሟል፡፡ የአልኮል መጠጥ እና የጫት ተጠቃሚነትን መጠን በተመለከተ ከሌሎች የትምህርት ደረጃዎች ይልቅ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በከፍተኛ ደረጃ የድርጊቱ ጀማሪዎችና አዘውታሪዎች እንደሆኑ ጥናቱ ይገልፃል፡፡ በጥናቱ ከተካተቱ ተማሪዎች መካከል 51.4 በመቶዎቹ የአልኮል ተጠቃሚነትን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ የጀመሩ ሲሆን፤ 27.2 በመቶዎቹ ደግሞ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ጀምረዋል፡፡ 44.6 በመቶ የሚሆኑት ጫት የጀመሩት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ሲሆን፤ 15.1 በመቶዎቹ ደግሞ የ1ኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ መጀመራቸው ታውቋል፡፡
በተለይ የአንደኛ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በከፍተኛ መጠን ያለእድሜያቸው ለአጓጉል ድርጊቶች መጋለጣቸው፣ በስነምግባር የታነፁ ዜጐችን በማፍራት ረገድ አገሪቱ ፈታኝ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አመላካች ነው ብለዋል – ጥናት አቅራቢዋ፡፡ እጽና አልኮል መጠቀም፣ ልቅ ወሲብ ከመፈፀም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ያመላከቱት አጥኚዋ፤ በተለይ ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት የከተማ ልጆች ሲሆኑ ወላጆቻቸው የተማሩ የሚባሉና ከፍ ያለ የገንዘብ አቅም ያላቸው እንደሆኑ ጠቅሰዋል። ከገጠር አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎች በአንፃሩ የገንዘብ አቅማቸው አነስተኛ በመሆኑ፣ አልኮልና እፆችን እንዲሁም የወሲብ ተግባራትን እንደልባቸው ለመፈፀም እንደሚቸገሩ ተጠቁሟል፡፡
በእነዚህ የትምህርት ደረጃዎች ያሉና የአቻ ግፊት ሳይበግራቸው ከእነዚህ ሁሉ ሱሶች ነፃ ሆነው የተገኙት ለስነ ምግባራቸው መታነጽ ምክንያቱ፣ በወላጅ ምክር ያደጉና የሃይማኖት ጥንካሬ ያላቸው መሆኑን ያመለከቱት ጥናት አቅራቢዋ፤ የሃይማኖት ተቋማት በዚህ ረገድ ጠንካራ ስራ ለመስራት ቢሞክሩ የበለጠ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ በእኚሁ ጥናት አቅራቢ የቀረበው ሌላው ርዕሰ ጉዳይ በጐልማሶች ላይ ያተኮረ ሲሆን በሀገራችን ከ150ሺህ በላይ ሴተኛ አዳሪዎች እንዳሉ ቢገመትም በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ሴት የቢሮ ሠራተኞች እና ተማሪዎች በወሲብ ንግድ ተሰማርተው በአቋራጭ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ ኑሮአቸውን እየደጐሙ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ለዚህ ልማድ መስፋፋት ደግሞ ባለሃብቶችና በእድሜ የገፉ ሰዎች አማጋጭ እየሆኑ መምት፣ የመዲናዋ የቱሪስቶችና ዓለማቀፍ ክንውኖች ማዕከልነቷ ማደጉና የጥበብ ውጤቶች ስለ ወሲብ የተዛባ አመለካከት ይዘው ብቅ ማለታቸው በምክንያትነት ተቀምጧል፡፡ ማሣጅ ቤቶችና ራቁት የዳንስ ቤቶች ወሲብ ንግድ መስፋፋቱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
ለእነዚህ ሁሉ የስነምግባር ጉድለቶችና ማህበረሰባዊ እሴቶች ውድቀት የህግ ክፍተት መኖሩ ትልቅ ሚና እንዳለው ባይካድም፣ በመንግስት ሚዲያዎች ሳይቀር የሚተላለፉ የማስታወቂያ መልዕክቶች፣ የቃላት አመራረጥና የፕሮግራም አቅራቢዎቹ አለባበስ፣ የመረጃዎች ፍሬ ሃሳብ እና ስነ ምግባር የጐደላቸው ጽሑፎች በስፋት መስተናገድ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ተብሏል፡፡ ሌላው ጥናት አቅራቢ አባ በአማን ግሩም የተባሉ የሃይማኖት አባት በበኩላቸው፤ ከቤተሰብ እስከ አገር አቀፍ ደረጃ የመከባበር እሴት መጥፋት፣ ማታለልና ሙስና መስፋፋት ለትውልዱ በስነምግባር አለመታነጽ እንደምክንያት ካቀረቧቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ይሄን ለመቀየር ከሃይማኖት መሪዎችም ሆነ ከመንግስት የስራ ሃላፊዎች የአርአያነት ተግባር እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አባ በአማን፤ እነዚህ አካላት የትውልዱን ስነምግባር በማነጽ ረገድ ያላቸው ሚና እንዲጐላ ቢደረግ መልካም ነው ብለዋል፡፡
ምቀኝነት፣ ውሸት፣ ሃሜት፣ ስርቆት፣ ሙስና፣ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የአደንዛዥ እፅ ዝውውርና ተጠቃሚነት እንዲሁም ሽብርና ጦርነት በዓለም ላይ መበራከታቸው ለስነምግባር እሴቶች መጓደል ምክንያት መሆኑን የዘረዘሩት ሌላው ጥናት አቅራቢ ሐጂ አብዱልሃማድ አቡበከር፤ መንግስት እና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ማህበረሰቡ በጋራ ኢትዮጵያውያን ወጣት ተማሪዎች ከእነዚህ የስነምግባር ጉድለቶች የሚርቁበትን አቅጣጫ ማሳየት እንደሚገባቸው አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የከተማው የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዲሳሞ ኦቶሬ በበኩላቸው፤ ተማሪዎችን ከአልኮል፣ አደገኛ እጽ፣ ጫት እና ከወሲብ ሱስ ተጋላጭነት የራቁ ለማድረግ ቢሮአቸው የተለያዩ የድርጊት መርሃ ግብሮችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆንም፣ ለእነዚህ መጤ ልማዶች መስፋፋት ምክንያት የሆኑ የንግድ ቤቶች ከትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚርቁበትን የወሰን መጠን የሚያስቀምጥና ህጋዊ ክልከላ የሚያደርግ ህግ እየተረቀቀ እንደሆነ በቢሮው ሃላፊዎች ተገልጿል፡፡ (አዲስ አድማስ)

በዐረቡ ምድር የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልትታነጽ ነው ! ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ለማሳነጽ ለተጀመረው እንቅስቃሴ ፈረቀዳጅ መሆኑ ተገለፀ !


በዐረቡ ምድር የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልትታነጽ ነው !

በሳውዲ አረቢያ ጅዳ እና ሪያድ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የእምነቱ ተከታዮች የመቃበር  እና የጸሎት ስፍራ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ለማቅረብ የድጋፍ ፊርማ እያሰባሰቡ መሆናቸውን ቀደም ተብሎ መጠቀሱ አይዘነጋም ! ይህ በዝህ እንዳለ ሰሞኑንን ከወደ ኳታር የተሰማው ዜና እንዚህ ኢትዮጵያውያኖች ለጀመሩት የተቀርደሰ ተግባር ተስፋ ሰጪ መሆኑንን የሚገልጹ ምንጮች ይህ  ይኳታሩ ቤተ ክርስቲያን የመን ውስጥ ከተገነባው  ቀጥሎ ሁለተኛው ሊሆን እደሚችል ይገልጻሉ ! ሙሉ ዜናው እደሚከተለው  ቀርቦል! (

Ethiopian Hagere ጀዳ በዋዲ )

በመካከለኛው ምሥራቅ ከእሥራኤል ቀጥሎ ሁለተኛዋ፣ በዐረቡ ምድር ደግሞ የመጀመሪያዋ የምትሆነው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በኳታር ምድር ልትታነጽ ነው፡፡
በኳታር ምድር የዛሬ አሥር ዓመት ለጸሎትና ለትምህርት መሰባሰብ በጀመሩ ወንድሞችና እኅቶች የተጀመረችው የኳታር ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ወደ አካባቢው ለሥራ የሚጓዙ ምእመናንን በማሰባሰብና በማገናኘት፣ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋትና ክርስቲያናዊ ማኅበራዊ ኑሮን በማጠናከር የምትታወቅ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያንዋ አገልግሎቷን የምትፈጽመው በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሆን በዓረቡ ዓለም እንደተለመደውም ዘወትር ዓርብ ከሰዓት በኋላ የቅዳሴና የትምህርት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የኳታር ቅድስት ሥላሴ ምእመናን የሥራ ጫናውን ሁሉ ተቋቁመው ተግተው በማገልገል ብቻ ሳይሆን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው በማስጠበቅም የሚታወቁ ናቸው፡፡
በአብዛኞቹ የዓረበ ሀገሮች እንዳሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በኳታር ለነበረችው ቤተ ክርስቲያንም ዋና ፈተና የነበረው የራስዋ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አለመኖር ነው፡፡ ይህም አገልግሎቷን በሳምንት ወደ ተወሰኑ ቀናትና ሰዓታት ከማሳነሡም በላይ፣ ምእመናን የሚፈልጓቸውን ሁሉን አገልግሎቶች ለመስጠት እንዳትችል አድርጓት ነበር፡፡ ለቤተ ክርስቲያንዋ የራስዋ ሕንጻ መሥሪያ ቦታ በመፈለግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ የነበረው የሰበካ ጉባኤ ባሳለፍነው ሳምንት በዐረቡ ዓለም የመጀመሪያ የምትሆነውን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የሚያስችል መሬት ተረክቧል፡፡
እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየመን፣ በዓረብ ኤምሬትስ፣ በባሕሬን፣ በኩዌት፣ በሊባኖስና በግብጽ የራስዋ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሯትም በራስዋ ገንዘብ የተሠራና ንብረትነቷ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሆነ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ግን አልነበራትም፡፡ የኳታር ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ከተሠራ ከእሥራኤል ቀጥሎ በመካከለኛው ምሥራቅ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ‹ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን› ይሆናል፡፡
በኳታር ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ መሠራት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ በአንድ በኩል የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑን አገልግሎት ከሳምንት እስከ ሳምንት የማያቋርጥ እንዲሆን ሲያደርገው በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢው ላሉት ሌሎች አጥቢያዎችም አርአያነት ይኖረዋል፡፡ ከኳታር በፊት እንቅስቃሴ የጀመሩት እንደ አቡዳቢ መድኃኔዓለም ያሉትን አጥቢያዎች የጀመሩትን በርትተው እንዲፈጽሙ ያነሣሣቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያነት ታሪክ በዐረቢያ ፔኒዙኤላ የነበረው ቤተ ክርስቲያን ከ1400 ዓመታት በፊት በየመን ናግራን ታንጾ የነበረው የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ እርሱ ከጠፋ ከ1600 ዓመታት በኋላ በዓረቢያ ፔኑዚኤላ ሁለተኛው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት ሥላሴ ስም እንደገና በኳታር መታነጹ የታሪኩ ተገጣጣሚነት የሚያስደንቅ ነው፡፡
ይህ ቤተ ክርስቲያን በአንድ በኩል ታሪካዊ፣ በሌላ በኩል የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ወደ አንድ ምዕራፍ የሚያሸጋግር፣ ሲሠልስም ለሌሎች አርአያነት ያለው በመሆኑ ሥራ በኳታር ለሚገኙ ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ግብጻውያን እንደዚህ ባሉ አካባቢዎች የሚታነጹ የተለየ ታሪክና ጠቀሜታ ያላቸውን አብያተ ክርስቲያናት በመተጋገዝ እንደሚገነቧቸው ሁሉ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም እያንዳንዷን የሕንጻዋን ብሎኬት ተካፍለው በመገንባት በታሪክ ምዕራፍ ላይ አሻራቸውን ማስቀመጥና በረከት ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በሀገር ቤት፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በአውስትራልያ የሚገኙ ምእመናን በአካባቢያቸው ቤተ ክርስቲያን ባይኖር ነድተውም ሆነ ተሳፍረው ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ ቤተ ክርስቲያን መገልገል ይችላ፤ በዐረቡ ዓለም ግን በአንድ አካባቢ አንድ አጥቢያ ብቻ ስለሚገኝ ወጣ ብሎ በሌላ አጥቢያ መገልገል አይቻልም፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ኳታር ባሉ ሀገሮች ያለው ቤተ ክርስቲያን አንድ ነው፡፡ ይህን ቤተ ክርስቲያን ማነጽና አገልግሎቱን ማጠናከር፣ በዐረቡ ዓለም የሚገኙ ወገኖቻችን በመንፈሳ ሕይወታቸው በርትተው፣ ከመንፈስ ጭንቀት ተላቅቀው፣ የሚደርስባቸውን ፈተናም አሸንፈው ለሀገራቸውና ለወገኖቻቸው የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው፡፡ በመሆኑም በመላው ዓለም የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚታነጸው የራሳቸው አጥቢያ መሆኑን አስታውሰው ልባቸው ኳታር ሊሆን ይገባል፡፡
የገባው ክርስቲያን እግዚአብሔር ሲሠራ አብሮ ይሠራል፡፡

Sunday, January 26, 2014

የባለሥልጣናት ሃብት ተመዝግቦ አያልቅም እንዴ?



• የሃብታቸው መጠን ይፋ የሚደረገው ከስልጣን ሲወርዱ ይሆን? (ያመለጡን አሉ!) 
• በሃብት ምዝገባው ላይ የትዳር አጋርም ሊካተት ይገባል (መነጣጠቅ ተጀምሯላ!) 
• “Grand corruption” አለ የሚባለው ገንዘብ ሚኒስቴር ሲዘረፍ ነው እንዴ? 
• የእነቴሌ “የእንኳን አደረሳችሁ” መልዕክት “ፅድቁ ቀርቶብኝ–” ያሰኛል! 

ኢትዮ- ቴሌኮም በየበዓሉ የሚልከው የ “እንኳን አደረሳችሁ” መልካም ምኞት አሁን አሁን “ሙስና” እየመሰለኝ 
መጥቷል፡፡(ግራንድ ኮራፕሽን ሳይሆን ሚጢጢዬ ሙስና!) ለነገሩ ቢመስለኝም እኮ አይፈረድብኝም፡፡ ለምን መሰላችሁ? 
ዓመቱን ሙሉ በብዙ የአገልግሎት አሰጣጦች ችግር ሲያማርረን ከርሞ — በዓል ሲደርስ እንደ ደህና አገልጋይ “እንኳን 
አደረሳችሁ” የሚለን ሊደልለን ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? (“ደለለኝ — ደለለኝ” ነው ያለችው ድምፃዊቷ) 
ነፍሷን ይማረውና! እውነቴን እኮ ነው… ኔትዎርክ ሳይኖር፣ ኢንተርኔት ተቋርጦ፣ የቢሮና የቤት ስልክ ጠፍቶ… እንዴት ነው 
“እንኳን አደረሳችሁ” የሚለን? (ያውም ለእኛ አሻፈረኝ በሚለን ኔትዎርክ!) እኔ የምለው —- እኛና ቴሌ የምንተዋወቀው 
በስልክ አገልግሎት አይደለም እንዴ? (ከዚያ ውጭ የት ስንተዋወቅ ነው!) ከሁሉም የሚገርመኝ ደሞ ”ከመጪው ዘመን ጋር 
አገናኛችኋለሁ” የሚለው ፉከራው ነው፡፡ (“ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” አሉ!) እንኳንስ ከመጪው ዘመን… ከዛሬ ጋር 
እንኳን መች ተገናኘን! (ማን ነበር “አቅምን አውቆ ማደር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው” ያለው?!) አሁንማ ከምንፈልገው ሰው 
ጋር መገናኘት አይደለም— ሂሳብ ለመሙላትም ኔትዎርክ ማግኘት መከራ ሆኗል (ቴሌኮም በነፃም እንኳን ገንዘብ 
አልቀበልም እያለን እኮ ነው!) እስካሁን የውሃና የመብራት መ/ቤቶች ለገና በዓል “እንኳን አደረሳችሁ” ማለት 
አለማለታቸውን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ምናልባት ሳልሰማቸው ብለውን ከሆነ ግን የእነሱንም ከ“ሙስና” ለይቼ 
አላየውም፡፡ ለምን ብትሉ… ገንዘብ የምንከፍልበትን ዋናውን አገልግሎት በቅጡ ሳናገኝ በየበዓሉ “እንኳን አደረሳችሁ” ማለት 
ለእኔ ተራ መደለያ ነው፡፡ 

(የመረረው ደንበኛ አታውቁም!?) ለነገሩ እዚህ አገር እኮ ቀድመው የሚናደዱት አገልግሎት ሰጪዎቹ እንጂ ደንበኞች 
አይደሉም፡፡ እኛ ደህና አገልግሎት የሚሰጠን አጣን ብለን ከመናደዳችን በፊት እነሱ ቀድመውን ይናደዱብናል (“ራሱ በድሎ 
ራሱ አለቀሰ” አለች አስቱ!) እናላችሁ—የበዓላት ጊዜው ድለላ ቀርቶብን አንዴም ክፍያው ተቋርጦ የማያውቀውን የውሃና 
የመብራት አገልግሎት ሳይቆራረጥ፤ሳይጠፋ እናገኝ ዘንድ ለብዙ መቶኛ ጊዜ እንማጠናለን፡፡ (“Where is my beef?” አለ 
ፈረንጅ!) ምን እንደሚገርመኝ ታውቃላችሁ? ሦስቱም የመንግስት ተቋማት ለአገልግሎታቸው መቋረጥ የሚሰጡት ሰበብ 
ሁሌም ተመሳሳይ ነው – እንደሰነፍ ተማሪ እየተኮራረጁ፡፡ (አዲስ ሰበብ መፍጠር ሮኬት ሳይንስ ሆነ እንዴ?) እናላችሁ —- 
ውሃም መብራትም ኔትዎርክም የሚጠፉትና የሚቆራረጡት በ“ልማቱ” የተነሳ ነው፡፡ መብራት ለምን ይቋረጣል? ግድቦች 
እየተሰሩ ስለሆነ! ኔትዎርክ ለምን ይጠፋል? ኔትዎርክ እየተስፋፋ በመሆኑ! ውሃ ለምን ትጠፋለች? አዲስ የውሃ መስመር 
እየተዘረጋ ነዋ! ሰላማዊ ሰልፍ ለምን ታገደ? ልማቱን ለማፋጠን! እኔ የምለው ግን —- ነባሩ አገልግሎት ሳይቋረጥ፣ እኛም 
ሳንማረር — ልማቱን ማስፋፋት እንዴት አቀበት ይሆንብናል? ሳስበው ግን አቀበት ሆኖብን አይመስለኝም፡፡ በልማት ሰበብ 
የስንፍናን ካባ ደርበን ለሽ ስላልን ነው፡፡ 

(ልማትና እንቅልፍ መቼም ተስማምተው አያውቁም!) አሁን የምፈራው ግን ምን መሰላችሁ? ለምን ሙስና ያለቅጥ ዓይን 
አወጣ ብለን ስንጠይቅ —“የፀረ- ሙስና ዘመቻው ስለተጧጧፈ” የሚል ምላሽ እንዳንሰማ ነው፡፡ (ነገሩ ሁሉ እኮ ምፀት 
ሆኗል!) እኔ የምላችሁ ግን… ለምንድነው ግን ጦቢያን እንዲህ የጠላናት? ብንጠላትማ ነው… በየመንግስት መ/ቤቱ ቱባ ቱባ 
ሹማምንቶች የአገር ሀብት ዘርፈው የተያዙት! ብንጠላትማ ነው— ከአገርና ከህዝብ ላይ እየዘረፍን የ15 ሚ.ብር ዶዘሮች 
ስንገዛ ቅንጣት ታህል የማይቆረቁረን! ብንጠላትማ ነው… ከመንግስትና ከባለሀብት ላይ እየነጠቅን በሚስትና በዘመዶቻችን 

ስም በየባንኩ ብዙ ሚሊዮን ብሮችና ዶላሮች የምናከማቸው! ብንጠላትማ ነው… በሙስና ገንዘብ መንትፈን በየቦታው 
ግራውንድ ፕላስ 2 ምናምን የምንገነባው! የጠላነው ግን ጦቢያን ብቻ እንዳይመስላችሁ… ራሳችንንም ነው!! 
ቤተሰቦቻችንንም ነው!! ልጆቻችንንም ጭምር ነው!! በሙስና ተይዘን የመገናኛ ብዙሃን ዜና መክፈቻ ስንሆን ቀድመው 
የሚያፍሩብን እኮ ቤተሰቦቻችን ናቸው፡፡ ልጆቻችን ናቸው፡፡ ወዳጆቻችን ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ የሾመን 
መንግሥት ነው። የመለመለን ፓርቲ ነው፡፡ 

የማታ ማታም የጠላናት ጦቢያ—- በተራዋ አንቅራ ትተፋናለች፡፡ “እኒህ ከእኔ ማህፀን አልወጡም!” ብላ ትክደናለች (“ሰው 
የዘራውን ያጭዳል” አለ ታላቁ መፅሐፍ!) አሁን አሁንማ ወዳጆቼ… በመዲናዋ ዙሪያ እንደ እንጉዳይ የፈሉትን አማላይ 
ህንፃዎች ስመለከት ልቤ ድንግጥ ማለት ጀምሯል (“ከሙስና ነፃ” የሚል ታፔላ ይለጠፍባቸው!) ምን ህንፃዎቹ ብቻ… 
በኢቴቪ ብቅ እያሉ ስለ ኪራይ ሰብሰባቢዎች ፀረ – ልማት እንቅስቃሴ የሚደሰኩሩንን የመንግስት ሹማምንቶችም 
መጠራጠር ከጀመርኩ እኮ ቆየሁ! (ከቫይረሱ ነፃ የሆነውና ያልሆነው አይለይማ!) እንዴ…አንዳንዶቹ እኮ “አገሩን የሚወድ 
ሰው ሙስና አይፈጽምም” ብለው በነገሩን ማግስት ነው “ቫይረሱ” እንዳለባቸው በኢቴቪ የዜና እወጃ የምንሰማው! (ዕድሜ 
ለፀረ – ሙስና ኮሚሽን!) እኔ የምለው ግን —- የፀረ ሙስና ኮሚሽን በአገራችን Grand corruption የለም የሚል ነገር 
የተናገረው በግምት ነው እንዴ? በጥናት ላይ ተመስርቶ እንዳልሆነማ ራሱ እያሳየን እኮ ነው፡፡ (Grand corruption ቀላል 
አለ እንዴ!) የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቁንጮ ቁንጮ ሃላፊዎች ሲፈጽሙ የከረሙትን ሙስና ምን ልንለው ነው? 
(መቼም “ግራንድ ኮራፕሽን” ነው ለማለት የገንዘብ ሚኒስቴር ሙሉ በሙሉ መዘረፍ ያለበት አይመስለኝም!) እኔ የምለው 
ግን—-የመንግስት ባለስልጣናት ሃብት ተመዝግቦ አያልቅም እንዴ? ለነገሩ የአንዳንዶቹን የሃብት መጠን ለመመዝገብ እኮ 
አመትም የሚበቃው አይመስልም፡፡ 

ቦቴው፣ ዶዘሩ፣ ቪላው፣ በየባንኩ ያለው ገንዘብ፣ የጦር መሳሪያው፣ (የጦር መሳሪያም እንደ ሃብት ይቆጠራል እንዴ?) እኔማ 
አንዱ ወዳጄ “የባለስልጣናት ሃብት ተመዝግቦ አልቋል” ሲለኝ — እንግዲያውስ ከስልጣን ሲወርዱ ይሆናል ይፋ 
የሚደረግልን ብዬ ጠረጠርኩ፡፡ (አንዳንዶቹ እኮ ሃብታቸው ሳይታወቅ እያመለጡን ነው!) በነገራችሁ ላይ የባለስልጣናቱን 
የሃብት ምዝገባ ጉዳይ ያነሳሁት ክፉ አስቤ አይደለም፡፡ ባለስልጣን ባየሁ ቁጥር “የሙስና ቫይረስ ይኖርበት ይሆን?” እያልኩ 
በመጠርጠር ሃጢያት እንዳልገባ ሰግቼ ነው፡፡ ከደሙ ንፁህ የሆኑ ባለስልጣናትስ ለምን ያለምግባራቸው ይጠርጠሩ? 
እናላችሁ —- የባለሥልጣናቱ የሃብት መጠን ቶሎ ተጠናቆ ይፋ ቢደረግ በጥርጣሬ ዓይን ከመተያየትና መረጃ ላይ 
ካልተመሰረተ ሃሜትና አሉባልታ እንድናለን፡፡ ሃሜት እኮ ሃጢያት ነው! መረጃ እንደ መንፈግ ግን አይሆንም!! የሃብት 
ምዝገባው ገና ካልተጠናቀቀ—- ይህችን ማዳበሪያ ሃሳብ ተቀበሉኝ (መዝጋቢውን አካል ማለቴ ነው!) ምን መሰላችሁ… 
በሃብት ምዝገባው ላይ የትዳር አጋርም መካተት አለበት የሚል ሃሳብ ስላለኝ ነው (መነጣጠቅ ተጀምሯላ!) በመጨረሻ አንድ 
የቤት ሥራ ጣል አድርጌ ልሰናበት፡፡ ይሄ የሥነ ዜጋ (ሲቪክ ኤጁኬሽን) ትምህርታችን እንደገና ይቀረፅ ይሆን እንዴ? 
(ሙስናው ቅጥ አጣ ብዬ እኮ ነው!) 

By Aseged Tamene 

ከሞያሌ ወደ ሻሸመኔ ሲጓዝ የነበረ ሀገር አቋራጭ አውቶብስ ተገልብጦ 16 ሰዎች ሞቱ


አዲስ አበባ ፣ ጥር 18 ፣ 2006 ትናንት አመሻሽ ላይ ከሞያሌ ወደ ሻሸመኔ ሲጓዝ በነበረ ሀገር አቋራጭ አውቶብስ ላይ በደረሰ የመገልበጥ አደጋ የ16 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ32 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደረሰ።

ከሟቾቹ ውስጥ ዘጠኙ ወንዶች ሲሆኑ ሰባቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው።
ከተሳፋሪዎቹ ውስጥ የ2 አመት ህጻን ያለ ምንም ጉዳት ተርፏል።
አደጋው የደረሰው በጌዲዮ ዞን በይርጋ ጨፌ ወረዳ ቆንጋ ቀበሌ ሲሆን ፥ ከፍተኛ ቁልቁለት ባለበት መንገድ ላይ በፍጥነት ማሽከርከር የአደጋው መንስኤ ነው የይርጋ ጨፌ ወረዳ የትራፊኮች አስተባባሪ ምክትል ሳጅን እድገት አምባዬ እንዳሉት።
ከዚህ በፊትም በዚህ ቦታ ላይ የተለያዩ የትራፊክ አደጋዎች ይደርሱ እንደነበርም አስተባባሪው ገልጸዋል።
ተጎጂዎቹ በዲላ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝና የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተናግረዋል።

Friday, January 24, 2014

አብርሃ ደስታ አዲግራት ላይ በሕወሓት ካድሬዎች ተደበደበ


የአረና ለትግራይ ፓርቲ በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሕዝብን የማነቃቃስ ስብሰባዎችን በመጥራትና በማወያየት ላይ የሚገኝ ሲሆን በሚያደረጋቸው ሰላማዊ እንስቃሴዎች በሕወሓት ካድሬዎች ፈተና እየገጠመው ይገኛል። ዛሬ ከወደ አዲግራት የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው በፌስቡክ፣ በትዊትር እና በተለያዩ ድረገጾች ላይ “አብርሃ ደስታ ከመቀሌ” እያለ የሚዘግበው መምህር ድብደባ ተፈጽሞበታል።
Abrha Destaአረና ፓርቲ ነገ እሁድ ጁላይ 26 ቀን 2014 በአዲግራት ከተማ የጠራውን ሕዝባዊ ስብሰባ ለሕዝብ ለማስተዋወቅ በከተማዋ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በሕወሓት ካድሬዎች በተደራጁ በተባሉ ወጣቶች “ሕዝብ መቀስቅሳችሁን አቁሙ” በሚል ጥቃት የተፈጸመባቸው አሰገደ ገብረ ሥላሴ፣ አምዶም ገብረስላሴና አብርሃ ደስታ ላይ ሲሆን በአብርሃ የደረሰው ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት ባያደርስም አቶ አሰገደ እና አንዶም ወደ ሃኪም ቤት ተወስደው ህክምና እንደተደረገላቸው ለዘ-ሐበሻ የደረሱት መረጃዎች አመልክተዋል።
በተያያዘ ዜና በተጨማሪ የአዲግራቱን ስብሰባ ለማስተጓጎል ሕወሓት ወታደሮችን በማሰማራት የአረና ሰዎችን በማሳሰር ላይ እንደሚገኝ የደረሰን ዜና አመልክቶ ለማሰር የቀረበው ምክንያትም “ሕዝብ በስብሰባ እንዲሳተፍ ቀስቅሳችኋል” በሚል ነው።
ከዚህ ቀደም የአረና አባላት በተንቤይን ሕዝባዊ ስብሰባ ጠርተው የነበረ ስሂን እዚያም እስር እና እንግልት እንደደረሰባቸው ዘ-ሐበሻ በወቅቱ መዘገቧ አይዘነጋም።
(ከዚህ ቀደም የአረናን ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳይሳተፉ የተከለከሉ የሽሬ ነዋሪዎች - ፎቶ ከአብርሃ ደስታ) - ፎቶ ፋይል
(ከዚህ ቀደም የአረናን ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳይሳተፉ የተከለከሉ የሽሬ ነዋሪዎች – ፎቶ ከአብርሃ ደስታ) – ፎቶ ፋይል

ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው ግንባታ ማንኛውንም ዓይነት ሕግ የጣሰ አይደለም በማለት መንግሥት የግብፅን አቤቱታ ውድቅ አድርጓል፡፡


አል ሞኒተር የተባለ የግብፅ ሚዲያ የተለያዩ የአገሪቱ ባለሥልጣናትን በመጥቀስ፣ ግብፅ በኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን ተቃውሞ ዓለም አቀፍ ማድረግ እንደምትፈልግ ዘግቧል፡፡ 
ግብፅ የህዳሴውን ግድብ በመቃወም ለተመድ አቤት እላለሁ ማለቷን ኢትዮጵያ አጣጣለች‹‹የህዳሴው ግድብ አሁን ባለው የግንባታ ደረጃ ተገንብቶ ዕውን የሚሆን ከሆነ በግብፅ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩን ወደሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት መውሰድ እንደሚገባ፣ ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው፤›› ያሉት የአገሪቱ የመስኖና ውኃ ሀብት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ካህሊድ ዋሲፍ ናቸው፡፡ 
‹‹ግብፅ የህዳሴው ግድብ ግንባታን ፈፅሞ አትፈቅድም፡፡ ይህንን ለማሳካትም ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የውጭ ዕርዳታ ለግድቡ እንዳታገኝ ግፊት እናደርጋለን፤›› ሲሉ በይፋ ተናግረዋል፡፡ 
ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የኢትዮጵያን ግድብ በማውገዝ ከግብፅ ጐን እንዲቆም አስፈላጊው ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ በዓለም አቀፍ ሕግ የተከበረና የተረጋገጠ መብት አላት፡፡ ነገር ግን ይህ የግብፅ መብት በኢትዮጵያ እየተጣሰ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ ሕጋዊ መብት አላት የሚሉት ቃል አቀባዩ፣ ማናቸውም የተፋሰሱ አገሮች ተፋሰሱን በመጠቀም ወደ ልማት መግባት ሲፈልጉ በቅድሚያ ግብፅን የማማከርና ይሁንታ የማግኘት ግዴታ አለባቸው ሲሉ የአገራቸውን አቋም አስታውቀዋል፡፡ 
ኢትዮጵያ ይህንን ግዴታ በመጣስ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ መጀመሯ በራሱ ሕግን የጣሰ መሆኑን፣ ነገር ግን የግብፅ መንግሥት ጉዳዩን በወዳጅነት በመያዝ ሲወያይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ምንም ዓይነት ጉዳት በግብፅ ላይ እንደማያደርስ ኢትዮጵያ ለማረጋገጥ እንቢተኛ በመሆኗ ግብፅ ከውይይቱ ራሷን እንዳገለለች አስረድተዋል፡፡ 
የግብፅ የቀድሞ የመስኖና የውኃ ሀብት ሚኒስትር ሙሐሙድ ናስር አል ዲን አላም በበኩላቸው፣ ግብፅ ከዚህ በኋላ በህዳሴው ግድብ ላይ ሌላ አማራጭ የላትም ብለዋል፡፡ የቀረውና በፍጥነት ተግባራዊ መሆን የሚገባው አማራጭ ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ፣ በዋናነትም ይፋዊ ቅሬታና ተቃውሞ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማቅረብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 
‹‹ማንኛውም የዓባይ ተፋሰስ ተጋሪ አጋር በወንዙ ላይ ፕሮጀክት ከመጀመሩ በፊት የግብፅን ይሁንታ ማግኘት አለባት የሚለው ስምምነት ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያለው ነው፤›› በማለት የሚከራከሩት የቀድሞው ሚኒስትር ኢትዮጵያ ይህንን ስምምነት በመጣስ ለጀመረችው ግንባታ በተባበሩት መንግሥትት ድርጀት ልትጠየቅ ይገባታል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል አሁን ያለውን አለመግባባት በተመለከተም ዓለም አቀፍ እውነት አፈላላጊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ማጥናት ይኖርበታል በማለት ተከራክረዋል፡፡ 
የግብፅ ባለሥልጣናት እያንፀባረቁት ስላለው አዲስ አቋም የተጠየቁት የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅ አህመድ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ውል አይመለከታትም፣ ምክንያቱም አልፈረመችም፤›› ሲሉ የግብፅ ባለሥልጣናት መግለጫን አጣጥለዋል፡፡ የቅኝ ግዛት ውሉ የተፈረመው በግብፅና በእንግሊዝ መካከል መሆኑን ያስታወሱት አቶ ፈቅ፣ እንግሊዝ ቅኝ የገዛቻቸውን ኬንያ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ በመወከል ስምምነቱን ፈርማለች፡፡ ይህ ግን ኢትዮጵያን ፈፅሞ አይመለከትም ብለዋል፡፡ 
የግብፅ የቀድሞው የመስኖና የውኃ ሀብት ሚኒስትር በተደጋጋሚ ይህንን መሳይ ነገር ያነሳሉ በማለት ያስታወሱት አቶ ፈቅ፣ ‹‹ሰውዬው ከሳይንስ ውጭ ነው የሚናገሩት፣ ከእሳቸው የሚጠበቅ አይደለም፤›› ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡ 
‹‹ኢትዮጵያ የጀመረችው የህዳሴው ግድብ ግንባታ የትኛውንም ዓለም አቀፍ ሕግ የጣሰ አይደለም፡፡ ወደፈለጉበት ቢሄዱ የሚመጣ ነገር የለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ ጉዳዩን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መምራት ሊያተርፍ የሚችለው በሁለቱ አገሮች ያለውን የትብብር መንፈስ ማጥፋት ነው ሲሉ የግብፅ ባለሥልጣናትን የሰሞኑን ዘመቻ አውግዘዋል፡፡ 

ለኢሳት መረጃ አቀብሏል የተባለው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ::!


ለኢሳት መረጃ አቀብሏል የተባለው 
ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

በአሸናፊ ደምሴ

ከአሜሪካን፣ ከኔዘርላንድና ከእንግሊዝ በመላው ዓለም ለሚሰራጨው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ (ኢሳት) በኢትዮጵያ ተቋማት፣ ድርጅቶችና ዜጎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል መረጃን አቀብሏል ሲል የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተበት በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የጋምቤላ ኤርፖርቶች የጥበቃ ዋና መምሪያ ሠራተኛ የሆነው አቶ ሚኪያስ ንጋቱ በፈፀመው የስለላ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በ4 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ከትናንት በስቲያ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎበታል።
እንደዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር ከሆነ ተከሳሹ፣ ቀኑና ወሩ በውል ባልታወቀ ነገር ግን ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ በጋምቤላ ክልል በሚገኘው የኤርፖርቶች ድርጅት የጥበቃ ዋና መምሪያ ሠራተኛ ሆኖ በሚሰራበት ወቅት ስርጭቱን ከአሜሪካ፣ ከኔዘርላንድ እና ከእንግሊዝ በማድረግ የአሸባሪው የግንቦት 7 ልሳን እንደሆነ ለሚነገርለት ኢሳት በተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ውስጥ ከሚሰራው ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም ጋር ግንኙነት በመፍጠር መረጃዎችን ሲያስተላለፍ ቆይቷል ይላል። 

        ለዚህም ውለታው 4460 ብር በመቀበል፤ ለስራ ተመድቦ በሚያገለግልበት የጋምቤላ ክልል ውስጥ በተለያየ ዘርፍ ኢንቨስተሮች ሆነው ግድያ ስለተፈፀመባቸው የውጪ ዜጎችና 19 በሚደርሱ የክልሉ የግብርና ኮሌጅ ተማሪዎች ላይ ተፈፅሟል ስለተባለው ግድያ በተመለከተ በፎቶ የታገዘ መረጃን ከማቀበሉም ባሻገር፤ በክልሉ መንግስት ስር የተካሄደውን ሹምሽር በተመለከተም በምስልና በፅሁፍ አስደግፎ በኢ-ሜይል እና በስልክ መረጃዎችን በማስተላለፉ በፈፀመው የስለላ ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ በዝርዝር ያትታል። 
በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ጉዳዩ በመታየት ላይ የነበረው ተከሳሹ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበበትን ከኢ-ሜይል ሳጥኑ የተሰበሰቡ 10ገፅ የፅሁፍ ማስረጃዎችና ከስልኩ የተወሰዱ ሶስት ፎቶግራፎችን አስመልክቶ በአግባቡ መከላከል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ያለው ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል መረጃን ለአሸባሪ ቡድን አባላት ከማስተላለፉም በተጨማሪ የሙያውን ስነምግባር በሚፃረር መልኩ በፅሁፍና በፎቶ የታገዘ መረጃዎችን ሲያስተላልፍ በመያዙ እንደቅጣት ማክበጃ ይወሰድልኝ የሚል ሀሳብ አቅርቧል።

          የተከሳሹ ተከላካይ ጠበቃ በበኩላቸው ግለሰቡ ከዚህ በፊት የፈፀመው ምንም አይነት ወንጀል አለመኖሩንና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን፤ እንዲሁም በአካባቢው የወጣት ማዕከላት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበረውና የመልካም ባህሪይ ባለቤትነቱን በመጥቀስ ቅጣቱ እንዲቀልለት ጠይቀዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ፍርድ ቤቱም፤ ተከሳሽን ጥፋተኛ ነው ባለው መሰረተ በ4 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ከትናንት በስቲያ ጥር 12 ቀን 2006 ዓ.ም የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፏል።

Thursday, January 23, 2014

ልጁን አስገድዶ ለሦስት ዓመታት የደፈረው አባት በፅኑ እስራት ተቀጣ


 
-ነዋሪነቱ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 10/11 ውስጥ ነዋሪ የሆነው ሙሉጌታ ውብሸት የተባለው ግለሰብ ልጁን አስገድዶ በመድፈርና ለሦስት ዓመታት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲፈጽምባት መቆየቱ፣ በሰውና በሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ በ18 ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት፡፡
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሰባተኛ ወንጀል ችሎት  ባስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ እንደገለጸው፣ ግለሰቡ የራሱን ልጅ ከሦስት ዓመታት በፊት አስገድዶ ክብረ ንፅህናዋን ገስሷል፡፡ በወቅቱ ልጅቷ የ12 ዓመት ታዳጊ ነበረች፡፡‹‹አንች እያለሽ ሌላ ሚስት አያስፈልገኝም በማለት የራሱን ልጅ እንደ ሚስት ቆጥሮ ለሦስት ዓመታት ወንጀሉን  ፈጽሞባታል፡፡ ሕፃኗ ከሦስት ዓመታት በኋላ ለወንድሟ እኔ ምን እስከምሆን ነው የምትጠብቀኝ? አባቴ ቀለበት አድርጎ እስከሚያገባኝ ነው? በማለት በጻፈችው ደብዳቤ  የወንጀለኛው አባቷ ጉድ መጋለጡን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያመለክታል፡፡በቤት ውስጥ ወንጀለኛው አባቷ  የሚያኖራት እንደ ሚስትና ቤት ሠራተኛ በመሆኑ፣ ‹‹እኔ ልጅህ አይደለሁም›› ብላ እስከ መጠየቅ  መድረሷን ዓቃቤ ሕግ በምስክርነት አቅርቧት ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቷን የውሳኔ መዝገቡ ይገልጻል፡፡
በሥነ ልቦናዋ ላይ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰባት ለፍርድ ቤቱ በሰጠችው የምስክርነት ቃል መግለጻው የውሳኔ መዝገቡ፣ አስገድዶ መድፈርና በዘመዳሞች መካከል ግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም በወንጀል ሥር ስለሚመደብ አፈጻጸሙ ከባድ ተብሎ እንዲወሰንለት ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ቅጣት ማክበጃ ሐሳብ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ፣ በከባድ ወንጀል ወስኖታል፡፡
በመሆኑም ወንጀለኛውን አባት በአስገድዶ መድፈር ወንጀል በ15 ዓመታት ከሦስት ወራት ፅኑ እስራት፣ በዘመዳሞች መካከል በተፈጸመ ግብረ ሥጋ ግንኙነት በሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወራት ፅኑ እስራት፣ በድምሩ በ18 ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡
ወንጀለኛው ከቤተዘመድ መብቶቹና ከሕዝባዊ መብቶቹ ለሦስት ዓመታት መሻሩንም  ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ሄዶ ሰርግ ለማድረግ እየተዘጋጀ ያለውን ኢትዮጵያዊ የገደለው አሜሪካዊ ተያዘ


tulu

(ዘ-ሐበሻ) በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ሄዶ ሰርግ ለማድረግ እቅድ ነበረው ኢትዮጵያዊው ዮሴፍ ቱሉ እንደ ቴክሳሱ ፋክስ 4 ቴሌቭዥን ዘገባ። የ30 ዓመቱ ዮሴፍ በጋዝ ስቴሽን ሥራ ተግቶ የሚሰራው ሃገር ቤት ሄዶ የሚመሰርተውን ትዳር በማሰብ፤ በወግ ማዕረግ መዳርን ነበር። በተለምዶ 7/11 በሚባለው ጋዝ ስቴሽን ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ዮሴፍ ረዥም ህልም ያለው ዜጋ ነበር።
guy killed ethiopian men

እንደ ወዳጆቹ ገለጻ ከሆነ ዮሴፍ መልካም፤ ተግባቢና ረዥም ህልም የነበረው ሰው ነበር። ሆኖም ግን በሚሰራበት ጋዝ ስቴችሽን በጥይት ተመትቶ ተገድሎ ሕይወቱ አለፈ። ሃገር ቤት ሄዶ ወዳጅ ዘመዱን ሊያኮራበት የተዘጋጀው ትዳርም ህልም ሆኖ ቀረ። ይህ ነገር ብዙ ወዳጆቹን እና ዘመዶቹን የበለጠ ሃዘኑን እንዳባሰባቸው የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ጠቁመዋል።
guy with gun

የ30 ዓመቱን ኢትዮጵያዊ እዚሁ ሰሜን አሜሪዓ.ምካ የቴክሳስ ግዛት ውስጥ እንደገደለ በፖሊስ ተጠርጥሮ የተያዘው ከልተን ጃን የተባለው ወጣት የ18 ዓመቱ ሲሆን፤ በጋዝ ስቴችኑ ውስጥ የተገጠመው ካሜካ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያውን ካሸር ትናንት ማክሰኞ ጃንዋሪ 21 ቀን 2014 ሊገድል ሲገባ በቁመቱ ልክ የሆነ መሳሪያ ታጥቆ ነው። ወጣቱ ተጠርጣሪ ገዳይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቢውልም፤ ጠመንጃውን ይዞ የፈለገውን ገንዘብ ቢወስድም በቅርቡ ወደ ሃገሩ ገብቶ ሰርግ ለማድረግ ገንዘብ እያጠራቀመ የሚገኘውን ዮሴፍ ቱሉን ከመግደል አልተመለሰም።
የጋዝ ስቴሽኑ ባለቤቶች የኢትዮጵያዊውን አስከሬን ወደ ሃገር ቤት የሚመለስ ከሆነ ወጭውን ለመቻል ፈቃደኛ ሲሆኑ ገዳዩ የ1 ሚሊዮን ቦንድ ተጠይቋል።
ዘ-ሐበሻ ፎቶዎቹን ያገኘችው ከፋክስ 4 ቲቪ መሆኑን ትገልጻለች።

Wednesday, January 22, 2014

አንቶኖቭ 28 አውሮፕላን በለገዳዲ አካባቢ ተከሰከሰ


ንብረትነቱ የዩክሬን የሆነ አንቶኖቭ 28 የመንገደኞች አውሮፕላን ከኡጋንዳ ኢንቴቤ ተነስቶ ወደ ሰንዓ የመን በመብረር ላይ እንዳለ ባለፈው ሰኞ አዲስ አበባ አቅራቢያ ለገዳዲ አካባቢ መከስከሱን ሪፖርተር ጋዜጣ ከአዲስ አበባ ዘገበ። ጋዜጣው ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አገኘሁት ባለው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች ሰኞ ማለዳ ከባለሥልጣኑ ጋር ባደረጉት የሬዲዮ ግንኙነት ከኢንቴቤ ተነስተው በኢትዮጵያ በኩል ወደ የመን ለመብረር ፈቃድ ጠይቀው ነበር፡፡ ባለሥልጣኑም የበረራ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል፡፡
ሪፖርተር በዘገባው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኤር ናቪጌሽን ክፍል ለአብራሪዎቹ የሚበሩበትን ከፍታ እንደሰጣቸውና አውሮፕላኑ የኢትዮጵያን አየር ክልል አቋርጦ በማለፍ ላይ ሳለ አዲስ አበባ አካባቢ ሲደርስ የሞተር ብልሽት ሲያጋጥመው ይህንኑ ለአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ መቆጣጠሪያ ማማ አሳውቆ ‹‹ኢመርጀንሲ ላንዲንግ›› እንደሚያደርግ (በድንገተኝነት እንደሚያርፍ) ሪፖርት አድርጐ፣ ከጠዋቱ 3፡35 ሰዓት ላይ ለማረፍ ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በማምራት ላይ ሳለ ለገዳዲ አካባቢ መከስከሱን ዘግቧል።
“አደጋው እንደደረሰ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ፈልጐ ማዳን ቡድን ወደ ሥፍራው ተንቀሳቅሶ የአውሮፕላኑ አብራሪዎችን ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ሕክምና እንዲያገኙ ማድረጉን” የዘገበው ሪፖርተር በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፋሪዎች እንዳልነበሩና፣ በአደጋው አብራሪዎቹ የተጐዱ ቢሆንም፣ ሕይወቱ ያለፈ ሰው እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል ሲል ጋዜጣው ዘግቧል።
ሪፖርተር ዘገባውን ሲያጠናቅቅም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአውሮፕላን አደጋ መከላከልና ምርመራ ክፍል ባለሙያዎች የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ ምርመራ ጀምረዋል፡፡ ባለሙያዎቹ አውሮፕላኑ ወደ ወደቀበት ሥፍራ በማምራት መረጃ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ፤ ሩሲያ ሰራሽ የሆኑ አንቶኖቭ አውሮፕላኖች ከተመረቱ ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ በመሆኑ በየጊዜው እክል እየገጠማቸው በተለያዩ አገሮች በመከስከስ ይታወቃሉ፤ እነዚህ ዕድሜ ጠገብ አውሮፕላኖች ዋጋቸው ርካሽ በመሆኑ በአፍሪካ አገሮች በብዛት ይገኛሉ፤ ያረጁ በመሆኑና ተገቢ የሆነ ጥገና ስለማይደረግላቸው በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በተደጋጋሚ አደጋ እንደሚያደርሱ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ያስረዳሉ ይላል።
zehbesha

Monday, January 20, 2014

በደምና በአጥንት መስዋዕትነት ተከብሮ የቆየ የሃገራችንን ዳር ድንበር ለባዕድ አሳልፈን አንሰጥም!


ብርሃኔ አሰበ አለሁድረስ
ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የታደለች ፣መልካም የአየር ፀባይ ያላት፣ህዝቦቿ የራሳችን አኩሪባህልና ወግያለን፣የራሳችን መልካም መልክዓ ምድራዊና አሰፋፈር ያለን በጋራ ተሳስረን አብረን የኖርንባትና የምንኖርባት በየትኛውም ዘመን ሉአላዊነቷ ያልተደፈረ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች ሀገር ናት። በተለያየ ወቅት የተፈጥሮ ሃብቷን ለመቀራመትና ሉአላዊነቷን ለመዳፈር የሞከሩ ሃገራት ሁሉ፣በውድ ልጆቿ የተባበረ ክንድ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተው ኢትዮጵያን ዳግም እንዳይመኟት የተባረሩበትና የኢትዮጵያን አይበገሬነት በአፍሪካም ሆነ በአለም መድረክ ያስመሰከረች፣ አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን ጠብቃ በማቆየት በአለም ታሪካዊ ስፍራ ያላት፣ በቀደምት ውድ ልጆቿ የደም መስዋዕትነት ሀገራችን ሉአላዊነቷ ሳይደፈር ለብዙ ሺ አመታት ቆይታለች።
Ethiopian government to hand over land to Sudan
በአሁኑ ስዓት ኢህአዴግ/ህወሃት ለግልና ለግዚያዊ የፖለቲካ ጥቅም ሲል የኢትዮጵያን አንድነት በማደብዘዝ እንሆ በእኛ ዘመን ለዘመናትተደፍሮ የማያውቀውን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመጋፋት የኢትዮጵያ የሉአላዊነት ባለቤት የሆኑት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሳይወያዩበትና ሳያፀድቁት በጓሮ በር የኢትዮጵያን መሬት ለባዕድ ሃገር/ሱዳን ቆርሶ ለመስጠት ሽርጉዱን ተያይዞታል። ከአመታት በፊት በምዕራቡ የሃገራችን ክፍል /ድንበር በኩል/ በመሸራረፍ ለም የሰሊጥ ምርት የሚሰጥ መሬት ለሱዳን ሲሰጥ ዝም በማለታችን  እንሆ ዛሬ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጋፋ ፣ የኢትዮጵያን ቅርጽ የሚያጠፋ ረጅም ርዝመት ያለው ለም መሬት ለሱዳን ለመስጠት ዝግጅቱ መጠናቀቁን ሰማን።
ዛሬ ላይ ሆነን ይህንን መሰሪ ተግባር አንድነታችንን አጠናክረን መግታት ካልቻልን ነገ ደግሞ በሌላኛው የኢትዮጵያ ጫፍ በኩል የኢትዮጵያ መሬትተቆርሶ ለሌሎች አጎራባች ሀገራት ላይሰጥ ምን ዋስትና አለን?
አያቶቻችንና አባቶቻችን ደማቸውን ገብረው ፣አጥንታቸውን ከስክሰው ያስረከቡንን የሀገር ሉአላዊነት ሳይሸራረፍ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የእኛ የአሁኑ ትውልድ የታሪክ  ግዴታ ነው። ይህን የታሪክ ግዴታችንን ሳንወጣ/ችል በማለት/ በመሰሪው የህወሃት/ ኢህአዴግ አመራር የሃገራችን ሉአላዊነት እየተሸራረፈ ለባዕድ ሀገራት ሲሰጥ በምን አገባኝ ስሜትዝም ብለን ብንመለከት በ– ዚ–ያ ዘመን ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀ የውጭ ጠላትጋር የሀገሬን ሉአላዊነት አላስደፍርም በማለት በዱላ፣ በጦርና ጋሻ፣ ዘመናዊ ባልሆነ  የጦር መሳሪያ ፣በባዶ እግራቸው በመዝመት ደማቸውን አፍስሰው ፣ አጥንታቸውን ከስክሰው የኢትዮጵያን ሉአላዊነትሳያስደፍሩ ያስረከቡን የአባቶቻችን አጥንት እሾህ ሆኖ ይወጋናል።
“የኢትዮጵያ ድንበሮች በኢትዮጵያውያን ደም የራሱ፣ በኢትዮጵያውያን አጥንት የተገነቡ ሲሆኑ ድንበሮቻችንን ለማስከበር ከሁልቆ መሣፍርት፣ ተራ ዜጐች አንስቶ እስከ አንድ ታላቅ ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ አንገታቸው ሰጥተዋል፡፡ በዶጋሊ፣ በጉራዓ፣ በጉንዲት፣ በመተማ፣ በአድዋ፣ በወልወል በቅርብ ጊዜያት ደግሞ በሶማሊያና በኤርትራ የፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም የሌላውን ግዛት በመቋመጥ ሳይሆን ድንበሬን አላስነካም በሚል ነበር፡፡ እንደዛሬው መኪና ወይንም ባቡር ባልኖረበት የቀደምት ኢትዮጵያውያን ከመሃል አገር ተነስተው በእግር ለወራት በረሃውን አቋርጠው፣ ተራራውን ወጥተው፣ ንዳዱን ተቋቁመው፣ ወባውን ደፍረው ከሙስታሂል እስከ ጋምቤላ፣ ከራስ ካሣር እስከ ሞያሌ ዘልቀው ድንበሩን ሰፍረው ኢትዮጵያን ለዚህ ትውልድ አስረክበው ሄዱ፡፡ ይህ ተረካቢ ትውልድ የተረከበውን መሬት ሳይቀነስ ለቀጣዩ ትውልድ ያስተላልፋል ይሆን—-” ከያዕቆብ ኃይለማሪያም/20 July 2008/።
ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን አደራ ጠብቆ የሀገሩን ሉአላዊነት ሳይሸራረፍ በማስከበር ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ ያለበት መሆኑን ለአፍታ መዘንጋት የለበትም ። ህወሃት/ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ህዝብ እውቅና ውጭ በሚስጥር የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመጋፋት ዳር ድንበራችንን ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገውን የውል ስምምነት የፖለቲካ ልዩነት፣ ብሄር፣ ሃይማኖት፣አመለካከት ሳይለያየን  የፖለቲካፓርቲዎች ፣ ድርጅቶች፣ ሲቪክስማህበራትና ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በጋራ ተንቀሳቅሰን አሁኑኑ ማስቆም ካልቻልን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከማስደፈርም አልፎ እስከ ወዳኛው ትውልድ ድረስ ብጥብጥና ትርምስን የሚያወርስ ስውር ደባ ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉአላዊነት በመጋፋት ለም መሬታችንን ለሱዳን አሳልፎ የሚሰጠውን ስምምነት አገር ወዳድ የሆንን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በጋራ በመንቀሳቀስበደምና በአጥንት መስዋዕትነት ተከብሮ የቆየ የሃገራችንን ዳር ድንበር ለባዕድ አሳልፈን አንሰጥም!  በሚል መርህ ተግባብተን ይህንን እኩይ ተግባር ለማስቆም ግዜ ሳንወስድ በያለንበት ፈጥነን መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል።
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለባዕድ ሀገር አሳልፎ የመስጠት ታሪክ አልወረስንም!