Monday, January 6, 2014

‹‹የፍትሕ መጓተት ብቻ ሳይሆን የፍትሕ መጓደል አለ›› አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት

‹‹የፍትሕ መጓተት ብቻ ሳይሆን የፍትሕ መጓደል አለ››  አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ የኢሠማኮ ፕሬዚዳንትዋና ዜና
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ወቅታዊ የሠራተኞችን ችግር በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ውይይት እንደሚያደርግ ታኅሳስ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቆ ነበር፡፡
የኮንፌዴሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች በሠራተኞች ላይ እየደረሱ ናቸው ያሉዋቸውን በርካታ ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅዳሜ ዕለት እንደሚያቀርቡ አስታውቀው ነበር፡፡ በተለይ በበታች የመንግሥት አካላት ሊመለሱ ያልቻሉ ያሉዋቸውን ችግሮች በማደራጀት በጥያቄ መልክ ይዘው የሚቀርቡ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊዎቹ፣ በተለይ በመደራጀት ዙሪያ ያሉ ችግሮች አሳሳቢ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የሠራተኞች በነፃነት የመደራጀትና የመሥራት መብት  በሕገ መንግሥቱ በግልጽ መደንገጉን፣ ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸውና ካፀደቀቻቸው ኮንቬሽኖች መካከል ስምንት ስምምነቶች የሚገኙ መሆናቸውን በማስታወስ፣  እነዚህ ዓበይት ስምምነቶች የሠራተኞችን የመደራጀት መብትና ሌሎች ሰብዓዊ መብቶችን የሚያካተቱ ናቸው ብለዋል፡፡ የተፈረሙት ስምምነቶችና ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ የሕግ አካል ቢሆኑም፣ እነዚህን ድንጋጌዎች የሚያጓድሉ ተግባራት እየታዩ ነው ይላሉ፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባለፈው ቅዳሜ በሚያደርጉት ውይይትም በተለይ የመደራጀት መብት ጥሰትን የሚመለከተው ጉዳይ በዋናነት ይነሳል ተብሏል፡፡ በፍትሕ ዙሪያም ተመሳሳይ ችግር አለ የሚሉት የኢሠማኮ መሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚያደርጉት ውይይት አቅጣጫ ሊሰጥባቸው ይገባሉ ያሉዋቸውንም ሌሎች ጥያቄዎች እንደሚያቀርቡ ገልጸው ነበር፡፡ በተለይ የሠራተኞች የመደራጀት ችግር ሊያሳስብ የሚገባው አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ስትሸጋገር ሊኖሩ የሚችሉትን ሠራተኞች ታሳቢ በማድረግ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚደረገው ውይይት ዙሪያ ከተሰጠው መግለጫ በኋላ ዳዊት ታዬ ባለፈው ሐሙስ ከኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ወቅታዊ በምትሏቸው የሠራተኞች ችግሮች ዙሪያ ልትወያዩ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ውይይት ከዚህ በፊት የተለመደ ነው እንዴ? 
አቶ ካሳሁን፡- ከዚህ በፊትም ነበር፡፡  ክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ ወዲህ ግን የመጀመርያችን ነው፡፡ ከዚያ በፊት ከባድ ችግር ካልገጠመ ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጋር በየዓመቱ ውይይት ይደረግ ነበር፡፡ በዚህም ውይይት በሠራተኛው ዘንድ ያሉ አጠቃላይ ችግሮችን የያዙ ጥያቄዎችን እናቀርብና እሳቸው አቅጣጫ ይሰጡበታል፡፡ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ችግሩን እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ ልምዱ አለ፡፡
ሪፖርተር፡- በዚያን ወቅት ታደርጉ በነበረው ውይይት ላይ አቅርባችኋቸው የነበሩ ጥያቄዎች በምትፈልጉት መንገድ መፍትሔ አግኝተው ነበር? ለምሳሌ ቢጠቅሱልኝ?
አቶ ካሳሁን፡- አሉ፡፡ ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡
ረፖርተር፡- ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመወያያት በያዛችሁት ፕሮግራም እንወያይባቸዋለን የምትሉዋቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ዋነኛ ጥያቄያችሁ ሆኖ የሚቀርበውስ ምንድነው? 
አቶ ካሳሁን፡- ጥልቅ ጉዳዮችን በውይይቱ ላይ ትሰማላችሁ፡፡ ዝርዝር ጥያቄዎች አሉን፡፡ ለምሳሌ በመደራጀትና በመደራደር ዙሪያ ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ ሠራተኛው ለመደራጀት ይፈልጋል፡፡ ለመደራጀት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የማደራጁትን ሥራ የሚሠሩት ሠራተኞች ወዲያው ከሥራ ይባረራሉ፡፡ ከተደራጁም በኋላ ቢሆን የማኅበሩን መሪዎች ከሥራ የማባረርና የማኅበሩ ሕልውና እንዲከስም የማድረግ ነገር ይታያል፡፡ ብዙ ፈተናዎችን አልፈው እንደምንም ማኅበሩ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ በኋላም ቢሆን የኅብረት ስምምነት ያለማድረግ ችግሮች አሉ፡፡
እንዲህ ያሉና ሌሎች ችግሮችን በተመለከተ ከሠራተኞች ጋር በየጊዜው እያየንና  እየተነጋገርን ነው፡፡ ውይይቱን አሁን ለማድረግ የተፈለገበት ዋና ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ኮንፌዴሬሽኑና በሥራ ያሉ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኖች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በዚህ እንቅስቃሴያችን ወቅት መጀመርያ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ከአሠሪው ጋር በመደራደር ለመፍትሔ ጥረት ይደረጋል፡፡ ይህ ጥረት ካልተሳካ የመንግሥት አካላት እንዲገቡበት ይደረጋል፡፡ በዚህም ካልተቻለ ወደ ፍርድ ቤት እንሄዳለን፡፡ 
በዚህ አቅጣጫ ተጉዘንም ቢሆን አሁንም ብዙ ያልተፈቱ ችግሮች አሉን፡፡ እነዚህ ችግሮች ሁልጊዜ ለኢሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤት ይቀርቡለታል፡፡ በተለያዩ ወቅቶችም በእነዚህ ችግሮች ዙሪያ ብዙ ውይይት ተደርጓል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለዘለቄታው እንዲፈቱ የምንፈልግ በመሆኑና ችግሮቹ ሥር እየሰደዱ ከሄዱ ሊከሰት የሚችለውን ሁኔታ በማሰብ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተናል፡፡ እነዚህ ችግሮች ታች ባሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሊፈቱልን ባለመቻላቸው ደግሞ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሊታይልን እንደሚገባ በማመን፣ ጥያቄዎቹ ለመንግሥት እንዲቀርቡ የኢሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ በዚህ መሠረት ከታች ጀምሮ የሚመጣውን ጥያቄ በመያዝ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲቀርብ እያደረግን ነበር፡፡
በተለይ ሠራተኞች በመደራጀት ሰበብ የሥራ ዋስትናቸው እየተጣሰ ነው፡፡ ማኅበራት ከተደራጁ በኋላ በማኅበራት መሪዎች ላይ የሚወሰደው ሕገወጥ ዕርምጃ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጭምር ይስተዋላል፡፡
በማኅበር መደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ላይም ተደንግጓል፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ድንጋጌ ፈርማለች፡፡ በዚህ ድንጋጌ ቁጥር 87 እና 98 መሠረት ሠራተኞች በነፃ የመደራጀትና የመደራደር መብት ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሠራተኞች ይህንን መብታቸውን ለመጠቀም ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡
ከመደራጀታቸው ጋር ተያይዞ የሚታየው ችግር በአብዛኛው በግል ድርጅቶች ላይ የጐላ ቢሆንም፣ በአንዳንድ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የማኅበር መሪዎች ምንም ጥፋት ሳያጠፉ ከሥራ እንዲሰናበቱ ይደረጋል፡፡ ይህንን ሕገወጥ ድርጊት ለማስቆም ወደ ፍርድ ቤት ስንሄድ ደግሞ የሚያሳዝን ነገር ይገጥመናል፡፡  
ሪፖርተር፡- በፍርድ ቤት አካባቢ እየገጠመ ነው የምትሉት ችግር ምንድነው?
አቶ ካሳሁን፡- የማኅበር መሪዎች በሕገወጥ መንገድ የሥራ ውላቸው ሲቋረጥ ወደ ፍርድ ቤት በምንሄድበት ጊዜ ፍርድ ቤት የሥራው ውሉ የተቋረጠው በሕገወጥ መንገድ ነው ብሎ  ያረጋግጣል፡፡ ግን ሠራተኛው ወደ ሥራው ቢመለስ የኢንዱስትሪ ሰላም ያደፈርሳል ይላል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? እንዲህ ከተባለ እንዴት አድርገህ ነው የማኅበር መሪን የምታቆየው? ነገሩን በዚህ መንገድ ተቀብለህ ነገ የምትመርጠው የማኅበር መሪ ከሥራው መባረሩ ይቀጥላል፡፡ ወደ ሥራ ከተመለሰ የኢንዱስትሪ ሰላም ስለሚያደፈርስ በሚል የስድስት ወራት ደመወዝ ተከፍሎ ይሰናበት ይባላል፡፡ ይህ ማለት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ያለመሪ እንዲቀሩ ማድረግ ነው፡፡ ሠራተኞች በተዘዋዋሪ መደራጀት አይችሉም ማለት ነው፡፡ በሕገወጥ መንገድ የተባረረ ሠራተኛ የተባረረበት ምክንያት ሕገወጥ መሆኑ እየታመነ ነገር ግን ወደ ሥራ መመለሱ ችግር ያመጣል የሚለው አካሄድ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፡፡ 
በዚህ ዓይነቱ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሚገርመው ነገር የተባረረውን ሠራተኛ ወደ ሥራ መመለስ የኢንዱስትሪ ሰላም ማደፍረስ ነው ብሎ ፍርድ ቤት ሲወስን፣ ተከሳሹ ቀርቦ ይህ ሰው ቢመለስ የኢንዱስትሪ ሰላም ይደፈርስብኛል ብሎ ክርክር ባላቀረበበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ፈጽሞ ከሕጉ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ይህ ሆን ብሎ ማኅበራትን የማፍረስ ሥራ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ሰላም ስለሚደፈርስ አስናብቼሃለሁ ይላል ዳኛው፡፡ በቃ የስድስት ወራት ደመወዝና ካሳ ተከፍሎህ ትሄዳለህ… ትሄዳለህ…. ይባላል፡፡ ይህ ከሆነ የት ላይ ነው የምንቆመው ነው  ጥያቄው፡፡ የትስ ሄደን እንደራጅ? አገራችን ኢትዮጵያ ነች ሌላ አገር የለንም፡፡ ሕገ መንግሥቱ አለ፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ አለ፡፡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም አሉ፡፡ እነዚህ ካልተከበሩ ግን የት ሄደን ነው የምንደራጀው? 
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በምናደርገው ውይይት የሚነሳው ሌላው ጉዳይ በሙያ ደኅንነትና ጤንነት ላይ የሚታየው ችግር ነው፡፡ የፍትሕ ጉዳይን የሚመለከቱ ጥያቄዎችንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እናቀርባለን፡፡ የፍትሕ መጓተት የተሻሻለ ቢሆንም አሁንም ችግር አለ፡፡ የፍትሕ መጓተት ብቻ ሳይሆን የፍትሕ መጓደል አለ፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥያቄዎች ይቀርባሉ፡፡ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖች አፈጻጸማቸውን በተመለከተ ፍርድ ቤቶች እንዴት እየተረጐሙት እንደሆነ የምናነሳቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡
በድኅረ ፕራይቬታይዜሽን ዙሪያ ያሉ ችግሮች አሉ፡፡ ከዚህ ውይይት በኋላም ቀጣይ ግንኙነታችንንም በሚመለከት የሚነሳ ነገር አለ፡፡ በውይይቱ አቅጣጫ ይሰማል፤ ከዚያ እንመለሳለን፡፡ ከዚያ በኋላ ምን ሊሆን ይችላል ለሚለውና ወደፊት ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት በትክክል መቀመጥ አለበት፡፡ በተለይ በዝርዝር ያቀረብናቸው ጥያቄዎችና ችግሮች የሚፈቱበትን አቅጣጫ እንዲያስቀምጡልን እንፈልጋለን፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንደ ሠራተኛ በዓመት ሁለት ጊዜ ቋሚ መድረክ ሊኖረን ይገባል የሚል እምነት ስላለን ለዚህም ምላሽ እንጠብቃለን፡፡
ሪፖርተር፡- በመደራጀትና በተያያዥ ጉዳዮች በሠራተኞች ላይ አሉ ለምትሉዋቸው ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ ብላችሁ የምታቀርቧቸው ምንድናቸው? ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በተያያዘ እየደረሱ ነው የምትሉዋቸውን ችግሮች በዚህ የውይይት መድረክ ታቀርባላችሁ?
አቶ ካሳሁን፡- አዎን! የምናነሳቸው ችግሮች በውጭ ኩባንያዎችም በአገር ውስጥ ኩባንያዎችም ይፈጸማሉ የምንላቸውን ነው፡፡ ለምሳሌ በሆቴል ሥራ ላይ የተሰማሩት አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በፋብሪካ አካባቢ ደግሞ አብዛኛዎቹ የውጭ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ግን የመብት ጥሰቱ ያለው በውጭም በአገርም ውስጥ ኩባንያዎች ነው፡፡ ስለዚህ እኛ እንደ መፍትሔ የምናቀርበውና  በእኛ እምነት በሠራተኞቹ የመብት ጉዳዮች ባለሀብቶችም ጭምር የአገሪቱ ሕግ ምን እንደሚልና የሠራተኞች መብት ምን እንደሆነ መንግሥት ሊያስረዳቸው ይገባል፡፡ ወደ ኢንቨስትመንት በሚገቡበት ጊዜ ይህን አውቀውት መሆን አለበት፡፡ መንግሥት ይህንን ለኢንቨስተሮች ማስረዳት አለበት፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች ከገቡም በኋላ የሠራተኞች መብት፣ በተለይ መሠረታዊ የሚባሉት መብቶቻችን መጠበቅ አለባቸው፡፡ ይህንን በተመለከተ መንግሥት ግንዛቤ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ በመተሳሳይ ለሠራተኞችም እንዲሁ፡፡ ሠራተኞች ተደራጅተው ቢንቀሳቀሱ መብቶቻቸውንና ግዴታቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ነው፡፡ ጥቅም የሚገኘው ድርጅቱ ሲያተርፍና ምርቱ ከፍ ሲል ነው፡፡ ካልሆነ ምንም የማያገኙ መሆኑን ሠራተኞች  ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሠራተኛው የሚደራጀው መብትና ጥቅም ለማግኘት ብቻ አይደለም፡፡ የመብትና የጥቅም ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጅቱን ምርታማ ማድረግ እንዳለበት ለሠራተኛውና ለእኛ ግንዛቤ እዲሰጠን እንፈልጋለን፡፡ እያደረግንም ነው፡፡ በጋራ ግንዛቤ መሰጠት አለበት፡፡ መደራጀት ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ወሳኝ ጉዳይ የሚመራ አገር አቀፍ የሦስትዮሽ መድረክ እንዲቋቋም እንፈልጋለን፡፡ ይህ ጥሩ መፍትሔ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር:- የሦስትዮሽ መድረኩ ከዚህ በፊት ነበር፡፡ የእስካሁኑ ጉዞ ምን ይመስላል?
አቶ ካሳሁን:- በእርግጥ የሦስትዮሽ መድረክ አለን፡፡ አሁን ያለው መድረክ ግን ሥራውን በአግባቡ እየሠራ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በአሠሪና በሠራተኛ አዋጁ ይህ የሦስትዮሽ አማካሪ ቦርድ ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ምክር የሚሰጥ ነው፡፡ በቦርዱ ውስጥ ያሉት ከአሠሪ፣ ከመንግሥትና ከሠራተኛ የተወጣጡ 15 አባላት ሚኒስትሩን ነው የሚያማክሩት፡፡ ሚኒስትሩ ምክር ከፈለገ ደግሞ የሚቀበለው ካልፈለገ የሚተወው ነው፡፡
ሪፖርተር:- በዚህ ረገድ የሌሎች አገሮች ልምድ ምንድነው?
አቶ ካሳሁን:- ለምሳሌ ኢትዮጵያ የማኅበራዊ ምክክሮች ኮንቬንሽን 144 ፈርማለች፡፡ በዚህ ኮንቬንሽን መሠረት የሚደራጀው የሦስትዮሽ ምክር ቤት መድረክ ከአሠሪው፣ ከሠራተኛውና ከመንግሥት በእኩል የተመጣጠነ አካል ኖሮ በጋራ ጉዳይ የሚመክሩ ናቸው፡፡ በምክክሩም የአሠሪና የሠራተኛ ግንኙነትን በተመለከተ አቅጣጫ ያሳያል፡፡ በጋራ ምክክሩ የተነሳው ጉዳይ ለመንግሥት መቅረብ ካለበት በቀጥታ ለመንግሥት ይቀርባል፡፡ የሚቀርበውም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡ በየትኛውም አገር ያለው ልምድ ይኼ ነው፡፡ የእኛ አገር ሕግና አሠራር ብቻ ነው የተለየው፡፡ 
ሪፖርተር:- በሦስትዮሽ የውውይት መድረክ የኢትዮጵያን አሠራር የተለየ የሚያደርገው ምንድነው? እናንተ ሊሆን ይገባል የምትሉትስ?
አቶ ካሳሁን፡- እስካሁን ያለው የሦስትዮሽ መድረክ በምክክሩ መድረክ ላይ የሚነሱ ጉዳዮችን በተመለከተ ማለትም የአሠሪና የሠራተኛ ጉዳዮችን ለሚኒስትሩ ምክር ይሰጣል የሚል ነው፡፡ ይህ መሆን የሌለበት ነው፡፡ ለአንድ ሰው  ምክር ለመስጠት ከሆነ ባለሙያ ተቀጥሮ ይህንን ማድረግ ይችላል፡፡ በሌሎች አገሮች በአገር አቀፍ ደረጃ ይህ አካል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ይመራል፡፡ ወይም በአንዱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ይመራል፡፡ ግን ውሳኔው ቀጥታ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይቀርባል እንጂ፣ አንድ ባለሥልጣን ሲፈልግ የሚቀበለው ሳይፈልግ የሚተወው አይደለም፡፡
በእኛ እምነት ሊሆን የሚገባው ከሠራተኛው፣ ከአሠሪውና ከመንግሥት እኩልና የተመጣጠሩ ተወካዮች ያሉበት የሦስትዮሽ መድረክ ሊኖር ይገባል፡፡ ተስማሚነት ያለው፣ እኩል መወሰን የሚችልና ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ ውሳኔ እንዲሰጥበት ማድረግ መቻል አለበት፡፡ ውሳኔ ሲባል እንደ ፍርድ ቤት ውሳኔ አይደለም፡፡ በጋራ የተስማማንበት ጉዳይ ሊፈጸም የሚችልበት ሁኔታ ተመቻችቶ በመድረኩ ተወያይተን የምናሳልፈው ውሳኔ ቀጥታ ለመንግሥት የሚቀርብበት አሠራር ያስፈልጋል፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትን በተመለከተ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው መቅረብ ያለበት እንጂ፣ ሦስታችን ተማክረን ለሚኒስትሩ ምክር  መስጠት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ይህ ሊሆን አይገባም፡፡ መድረኩ አንድ ባለሥልጣን ለማነጋገር አይደለም የሚቋቋመው፡፡ በአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ሁኔታውን የሚገመግምና አቅጣጫ የሚያሳይና በስምምነት የሚፈቱ ጉዳዮችን እየፈታን መሄድ አለብን፡፡ ይህም እታች መውረድ አለበት፡፡ ምክንያቱም ኢንዱስትሪ እየበዛ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢንዱስትሪ ሰላም እየተረጋጋ ካልሄደ ደግሞ የሚታሰበው ዕድገት ሊመጣ አይችልም፡፡
ሪፖርተር፡- ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የምታደርጉት ውይይት ምን ውጤት ያስገኛል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ?
አቶ ካሳሁን፡- በመረጃ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ወዲያው ምላሽ የሚያገኙበት ነው፡፡ አቅጣጫ የሚሰጥባቸው ጉዳዮችም ይኖራሉ፡፡ በቀጣይ ደግሞ በውይይት መድረኩ የተነሱ ጉዳዮች እንዴት ተፈጻሚ እንደሚሆኑም ምላሽ ይገኝበታል ብለን እናስባለን፡፡  ለማንኛውም መልሱን በጋራ እናያለን፡፡

No comments:

Post a Comment