Thursday, August 20, 2015

(ርዕዮት አለሙ) አክራሪና አሸባሪዉ ኢህአዴግ ወይስ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት?

ልጆች ሆነን “እከሌ (እከሊት) አክራሪ ነዉ (ናት) ” ሲባል ይሰጠን የነበረዉ ትርጉም እና አሁን አክራሪነት እየሰጠ ያለዉ ትርጉም ለየቅል ይመስለኛል፡፡ ያኔ አንድ ሰዉ በአክራሪነት ሲጠራ ከብዙሃኑ በተለይ ሁኔታ ሃይማኖቱን ወይም የሚያምንበትን አንዳች ነገር አጥብቆ መያዙን እና በሚያምንበት ነገር ላይ የማይደራደር መሆኑን ከማሳየት አልፎ የአሁኑን አይነት አሉታዊ ትርጉም አይሰጥም ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀዉ የአማርኛ መዝገበ ቃላትም ያኔ ቃሉን እረዳበት ከነበረዉ ትርጉም ብዙም የራቀ ፍቺ አያቀርብም፡፡ በ1993 ዓ.ም የካቲት ወር የተዘጋጀዉ ይኸዉ መዝገበ ቃላት አክራሪ ለሚለዉ ቃል የሚሰጠዉ ፍቺ “በሚከተለዉ እምነትና አስተሳሰብ ዉስጥ ፍፁምነት ሊኖር ይገባል ብሎ የሚያምንና የቆየዉን እምነትና አስተሳሰብ ከዘመናዊዉ ሁኔታ ጋር ማስተካከል እና ማጣጣም የማይፈልግ አጥባዊ (ሰዉ)” የሚል ነዉ፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የቃሉ ፍቺ እየተቀየረ መጥቶ አሁን ያለዉን እጅግ አሉታዊ የሆነ ገፅታ ይዟል፡፡
የህግ ባለሙያዉ ተማም አባቡልጉ የካቲት3 2007ዓ. ም በወጣዉ ኢትዮምህዳር ጋዜጣ ላይ “አክራሪ ሰዎች እነማን ናቸው?” በሚል ርዕስ ባስነበቡት ፅሁፋቸዉ “የራሱን ዘር፣ ሃይማኖትና ቡድን ጥቅም ሌሎችን በመጉዳት ጭምር ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀስ ወይም ከማስጠበቅ የማይመለስ” ሰዉ እንደሆነ አክራሪ የሚባለዉ ገልፀዋል፡፡
የዚህ ፅሑፍ አላማ አሁን እየተግባባንበት ካለዉ ፍቺ አንፃር ” የአክራሪነትና የአሸባሪነት ባህሪ የሚንፀባረቀዉ በቅርቡ በተፈረደባቸዉ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ ወይስ በከሳሹ መንግስት?” የሚላዉን ጉዳይ መፈተሽ ይሆናል፡፡
የኢህአዴግ የምናብ ቀበሮዎች
ኢህአዴግ እኔን ጨምሮ በርካታ ከሽብር ጋር ሊገናኝ የማይችል ማንነት ያለንን ዜጎች የአሸባሪነት ስም ሰጥቶናል፡፡ ይሄን በአሰብኩ ቁጥር ሁሌም ወደ አእምሮዬ የሚመጣዉ ብዙዎቻችሁ የምታዉቁት የዉሸታሙ እረኛ ታሪክ ነዉ፡፡ እንደምታስታዉሱት ሌሎችን በማታለል የሚዝናናዉ ዉሸታም እረኛ ቀበሮ መጥቶ በጎቹን እየበላበት እንደሆነ አድርጎ የድረሱልኝ ጥሪ በጩኸት በማቅረብ አላፊ መንገደኞችን ይሰበስባል፡፡ መንገደኞቹ ለእርዳታ ሲመጡ ታዲያ ቀበሮዉ በገሀዱ አለም ያለ ሳይሆን የእረኛዉ የምናብ ዉጤት መሆኑን ይረዱና እየተበሳጩ ወደየመንገዳቸዉ ይመለሳሉ፡፡ ኢህአዴግም “አክራሪ ደረሰብን ፤ አሸባሪ መጣብን” እያለ አደንቋሪ ጩኸቱን ለቁጥር በሚያዳግት መልኩ በተደጋጋሚ አሰምቷል፡፡ ጩኸቱን ሰምተዉ ስለሁኔታዉ ለማወቅ የሞከሩትን ሁሉ ግን የጠበቃቸዉ እንደዉሸታሙ እረኛ የምናብ ቀበሮ ሁሉ የዉሸት አክራሪና አሸባሪ ነዉ፡፡የምናብ ቀበሮ የሚበላዉ በግ እንደሌለ ሁሉ የምናብ አክራሪና አሸባሪም የሚያወድመዉ ንብረትም ሆነ የሚያጠፋዉ የሰዉ ህይወት የለም፡፡ እስክንድር ነጋና ሌሎች በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን አሸባሪ ሊያሰኝ የሚችል ምን አደረጉ? አንዷለም አራጌ እና ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ምን አጠፉ? ምንም!
የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትም እንደከዚህ ቀደሞቹ ሁሉ የኢህአዴግ የምናብ ቀበሮዎች ናቸዉ፡፡ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ይሁን ሌሎቹ የኮሚቴ አባላት አክራሪም ሆነ አሸባሪ ለመባል የሚያበቃ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ ይልቁንም መንግስት በሃይማኖታቸዉ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ እምነቱን ለመበረዝና ለመከለስ የሚያደርገዉን ጥረት እንዲያቆም እጅግ በሰለጠነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲጠይቁ የነበሩ በህዝበ ሙስሊሙ የተመረጡ የአላማ ሰዎች ናቸዉ፡፡ ለመረጣቸዉ ህዝብና ለሃይማኖታቸዉ ታማኝ ሆነዉ መገኘታቸዉ ግን ለኢህአዴግ ስላልተስማማዉ እንዲያስራቸዉ ብሎም ለመስማት የሚከብድ አሰቃቂ በደሎችን እንዲፈፅምባቸዉ ምክንያት ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በስህተት ያሳየዉ የአንደኛ ተከሳሽ የአቡበከር አህመድ እጆች በካቴና ታስረዉ ሲመረመር የሚያሳየዉ አሳዛኝ ምስል የተመለከተዉን ሁሉ ልብ የሚያደማ ነበር፡፡ በሁኔታዉ ልባቸዉ የተነካ ሙስሊም ወገኖቻችንን
አቡኪ ወንድሜ የእስልምና ብርሃን 
ሁኔታህን አይተን ሁላችን አነባን
ብለዉ እንዲያዜሙ ያስገደደ ነበር፡፡
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ኮሚቴዎቹ ከታሰሩበት አሰቃቂ ቦታም ሆነዉ ሰላማዊ የሆነዉ ጥያቄ መንግስት በሚወስዳቸዉ ያልተገቡ የአፈና ምላሾች ሳቢያ ሌላ መልክ እንዳይዝ በጎ መልዕክት ከማስተላለፍ ወደኋላ አላሉም፡፡ ኮሚቴዎቹ በዚህ መጠን ከህዝበ ሙስሊሙ አልፈዉ ለሀገር ሰላም ቢጨነቁም ዉሸታሙ እረኛ ግን የተለመዱ የሀሰት ዶክመንተሪዎችን በማቅረብ ስማቸዉን ለማጥፋት ሲታትር ነበር፡፡ ይብስ ብሎ ደግሞ በቅርቡ ከሰባት እስከ ሃያሁለት አመታት የሚደርስ ፍርድ ቀኝ እጁ በሆነዉ ፍርድቤት በኩል አስተላለፈባቸዉ፡፡ ይህ አስገራሚ ፍርድ በሚተላለፍበት ወቅት ግን ኮሚቴዎቹ በጀግንነት ቆመዉ እንባ የሚራጩ ዘመድ ወዳጆቻቸዉን ሲያፅናኑ እንደነበር ችሎቱን የተከታተሉ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ አስቀድመዉ በነበሩ ችሎቶች ላይ “እዚህ የቆምነዉ ፍትህ እናገኛለን በሚል እምነት አይደለም፡፡ ለታሪክ ምስክር ለመሆን እንጂ” በማለት እንደገለፁት ከካንጋሮ ፍርድቤት የሚጠብቁት ፍትህ ባለመኖሩ የተሰጣቸዉ ፍርድ እንደማያስደነግጣቸዉ ግልፅ ነዉ፡፡ የኮሚቴዎቹ አባባል ኔልሰን ማንዴላ ያልተገባ ስም ተሰጥቷቸዉ ለፍርድ በቀረቡበት ወቅት የተናገሩትንና የግል የህይወት ታሪካቸዉን ባሳተሙበት መፅሐፍ ዉስጥ የሚገኘዉን የሚከተለዉን ሃሳብ ያስታዉሰኛል፡፡
ይህ የፍትህ ስርዐት ጥፋተኛዉ ንፁሑን በህግ ፊት እንዲያቀርበዉ ጉልበት የሚሰጠዉ በመሆኑ ትልቅ ስጋት ዉስጥ ይከተኛል፡፡ የፍትህ ስርዐቱ ልክ ያልሆነዉ ልክ የሆነዉን እንዲከስና ማስቀጣት እንዲችል የሚያደርግ ነዉ……. በመሆኑም ፍትሃዊና ተገቢ ፍርድ አላገኘም፡፡
ያኔ ኔልሰን ማንዴላ አስቀድመዉ እንደተናገሩት የአፓርታይድ መሪዎቹ የሚያሽከረክሩት ፍርድቤት ያልተገባ ፍርድና የወንጀለኛነት ስም ሰጥቷቸዋል፡፡ ዛሬም ኮሚቴዎቹ ኢህአዴግ በሚያሽከረክረዉ ፍርድቤት አማካኝነት ከማንዴላ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ፍርድና ተመሳሳይ የሆነ ስያሜ አግኝተዋል፡፡ “አሸባሪነት” ዛሬም እንደትላንቱ ሁሉ አምባገነኖች የሚቃወሟቸዉን ንፁሃን የሚመቱበት ዱላ መሆኑን ቀጥሏል፡፡
አክራሪዉ ኢህአዴግ ነዉ!
የኢህአዴግ ባላስልጣናት አክራሪነት ከሱ ሌላ የሆነ ቡድን ወይም ማንነት እንዲኖር የማይፈቅድ እንደሆነና “ለልማታችን እና ለዲሞክራሲ ግንባታችን” ዋነኛ ጠር መሆኑን ሁሌም እንደነገሩን ነው፡፡ ከአባባሉ ተነስተን አክራሪ ስንፈልግ ዉለን ብናድር የምናገኘዉ ትልቁ አክራሪ ግን እራሱ ኢህአዴግ ሆኖ ይገኛል፡፡
ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሌላ ርዕዮተ አለም በሀገራችን እንዳይኖር አይደለም እንዴ የተለየ መስመር የሚከተሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚያፈርሰው? በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጦችና መፅሔቶች የመዘጋታቸዉና ጋዜጠኞቹ የመታሰርና የመሰዳደቸዉ ምክንያትስ እርሱ ከሚቆጣጠራቸዉ ዉጪ የሆኑ ሚዲያዎች እንዳይኖሩ ከመፈለግ የመጣ አይደለምን? የደሃ ሀገራችንን አንጡራ ሃብት እንደ ሃኪንግ ቲም ላሉ የጣልያን ተቋማትን የሚከሰክሰዉ ሁሉን ለመቆጣጠር ባለዉ ክፉ አባዜ ምክንያት መሆኑን መች አጣነዉ? የትምህርትም ሆነ የስራ እድል የኢህአዲግ አባል ካልተሆነ ለማግኘት የጠበበዉ ከኢህአዲግ አክራሪ ባህሪይ የመነጨ መሆኑ ግልፅ ነዉ፡፡ ሌሎች ብዙ የኢህአዲግ አክራሪነት መገለጫዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ ለማጠቃለል ያህል አንዱን ልጥቀስ
በሜታ ሮቢ ወረዳ አስተዳደር የወራቦ ቀበሌ አስተዳደር ነዋሪ የሆኑ አስራ አራት ግለሰቦች “በ2007ዓ.ም በተካሄደዉ ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሲደግፉ ነበር” በሚል አስገራሚ ምክንያት የተነሳ ማናኛዉንም የህግና የአስተዳደር አገልግሎቾችን ማግኘት እንዳይችሉ በቀበሌ አስተዳደሩ ለሚመለከተዉ ሁሉ ስማቸዉ ተዘርዝሮ ተፅፏል፡፡ ባለፈዉ ረቡዕ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንደሻዉ እንዚህን ግለሰቦች ጨምሮ በርካታ የፓርቲዉ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየደረሱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የችግሩን ምክንያት ሲያስረዱም “እነዚህ ታጋዮቻችን ህዝቡ መድረክን እንዲመርጥ ምን ሲሰሩ እንደነበር ስለሚያዉቅ አሁን እየወሰደ ያላዉ የበቀል እርምጃ ነዉ” ብላዋል፡፡ በዚህ መጠን ከእርሱ ሌላ እንዳይኖር የሚፈልገዉና ኖሮ ሲገኝ ደግሞ ተሸብሮ ህዝቡን የሚያሸብረዉ ኢህአዲግ የማይገባቸዉን ሰዎች አሸባሪ እና አክራሪ ሲል አፉን ያዝ እንኳን አያደርገዉም፡፡ ገዢዉ ፓርቲ ያልተገባ ስም የሰጣቸዉ ሙስሊም እህቶቻችን ቢቸግራቸዉ እንዲህ በማለት ሊያርሙት ሞክረዉ ነበር
የሂጃቡ ነገር ከላይ ከፈጣሪ
የኒቃቡስ ነገር ከላይ ከፈጣሪ
ልባል አይገባም አክራሪ አሸባሪ
የኮሚቴዎቹ እስርና ፍርድ ምን ሊያስከትል ያችላል?
ገዢዉ ፓርቲ ጥያቄዎችም ሆነ ተቃዉሞዎች ሲነሱበት ራሱን ከመመርመር ይልቅ በድፍረት ድምፃቸዉን ያሰሙ አካላትን ማሰርን ይመርጣል፡፡ በዚህም እፎይታን የሚያገኝ ይመስለዋል፡፡የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትም ላይ ያደረገዉ ይህንን ነዉ፡፡ ነገር ግን ይሄ አካሄዱ የተመኘዉን እፎይታ ሊያስገኝለት ይቅርና ለሀገር የሚተርፍ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ጉዳዩን በጥልቀት የተከታተሉ ወገኖች ይገልፃሉ፡፡
ከነዚህ ወገኖችአንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ሀይለመስቀል በሸዋምየለህ በቅርቡ ገበያ ላይ በዋለዉና “የሀይለማርያም እዳ እና የሙስሊሙ ትግል” በሚል ርዕስ ባዘጋጀዉ መፅሐፉ ዉስጥ በርካታ በጉዳዩ ላይ የተሰሩ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ እንደገለፀዉ ኢህአዲግ የሙስሊሙን ጥያቄ ለማፈን እየተጓዘበት ያለዉ መንገድ እጅግ አፍራሽ ዉጤት ይኖረዋል፡፡ ከአፍራሽ ዉጤቶቹ አንዱ ደግሞ “ኢህአዴግ እየተከላከልኩት ነዉ የሚለዉ ፅንፈኝነት መፈጠር” ሊሆን እንደሚችል መፅሐፉ ያስረዳል፡፡ ዶ/ር አባድር ኢብራሂም ADDIS STANDARD በተሰኘ ወርሃዊ መፅሔት የዚህ ወር እትም The unfair trial of Muslim Leaders ; why it undermines counter terrorism in Ethiopia በሚል ርዕስ ባቀረቡት ፅሁፋቸዉ ዉስጥም ተመሳሳይ ስጋት እናገኛለን፡፡ ዶ/ር አባድር ኮሚቴዎቹ ላይ የተሰጠዉን የጥፋተኝነት ዉሳኔ መነሻ በማድረግ ባዘጋጁት በዚህ ፅሁፋቸዉ የተላለፈዉ ውሳኔ የፍትህን መክሸፍ ከማሳየቱ በላይ እነዚህ የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች ወደፊት ከሚመጣ የሽብር አደጋ የመስዕዋት ጠቦት ሆነዉ ሊያድኑን አለመቻላቸዉ እንዳሳዘናቸዉ ገልፀዋል፡፡ ዶክተሩ ኮሚቴዎቹ ላይ የተላላፈዉ ውሳኔ እንደዉም የሽብር ስጋቱን እንደሚጨምር አምስት መከራከሪያዎችን በማቅረብ ይሞግታሉ፡፡ እኚሁ የህግ ምሁር ከመከራከሪያዎቹ በአንዱ እንዳብራሩትኮሚቴዎቹ በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ እጅግ ተሰሚነት ያላቸዉ መሪዎች እንደመሆናቸዉና በፀረ ሽብር ትግሉ አገላለፅ “ለዘብተኛ” የሚባሉ ስለሆኑ አክራሪነትን ለመከላከል ግንባር ቀደም አጋር ሊሆኑ የሚችሉ ነበሩ፡፡ ኢህአዲግ እነዚህን ትልቅ አጋር ሊሆኑ የሚችሉ መሪዎችን በመክሰስና በማሰር እዋጋቸዋለሁ የሚለዉን አክራሪ ድርጅቶች የቤት ስራ እንደሰራላቸዉ ዶክተሩ በፅሁፋቸዉ ይገልፃሉ፡፡ ምክንያቱን የሚያብራሩትም እንደነ አቡበከር አይነቶቹ ቅሬታዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍረታት የሚታትሩ ሙስሊም መሪዎች ባላቸዉ ተቀባይነት ፅንፈኛ ድርጅቶች ቅቡልነት እንዲያጡ በማድረግና የድርጅቶቹን ትምህርቶች ሊገዳደር በሚችል የሃይማኖቱ ትምህርት በመምታት እስልምናን ሽፋን አድርጎ የሚመጣን የሽበር አደጋ ለመከላከል የነበራቸዉን አቅም በመጥቀስ ነዉ፡፡ ዶክተሩ በሌላኛዉ መከራከሪያቸዉ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ለመወያየት ጥያቄያቸዉን ለማቅረብ በሞከሩ ሙስሊሞች ላይ መንግስት እየፈፀማቸዉ ባሉ በደሎች ሳቢያ አመፅአልባ ትግሉጥያቄ ዉስጥ መግባቱና ሰዎች ወደሌላ አማራጭ ለማየት መገደዳቸዉ እንደማይቀር ያስገነዝባሉ፡፡
ጋዜጠኛ ሀይለመስቀልም ሆነ ዶ/ር አባድር ይሄ ትልቅ ሀገራዊ ችግር የሚያመጣዉ ኪሳራ አሳስቧቸዉ መፍትሄ ፍለጋ ላይ ታች ቢሉም ኢህአዲግ ግን አሁንም ከመጥፎ ድርጊቱ አልታቀበም፡፡ በትላንትናዉ ዕለት እራሱ ኮሚቴዎቹን ለማስፈታት ተንቀሳቅሳችኋል ያላቸዉ ሃያ የዕምነቱ ተከታዮች ላይ ክስ እንደመሰረተ በማህበራዊ ድረገፆች እያነበብን ነዉ፡፡ እስርቤት በነበርኩበት ወቅትም የአዳማ ሙስሊምተማሪዎችን ጨምሮ በተመሳሳይ ክስ በርካታ ሙስሊሞች ይታሰሩ እንደነበር አዉቃለሁ፡፡
ገዢዉ ፓርቲ ስህተቱን በስህተት ለማረም የሚያደርገዉ እንዲህ አይነቱ አሳፋሪ እንቅስቃሴ መገታት ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ በሀሰት ቀበሮ እየተባሉ ፍዳቸዉን የሚያዩ ንፁሃን ወገኖቻችን ጉዳይ አሳስቦን በአንድነት መቆምና ገዢዉን ፓርቲ መታገል ካቃተን ነገ እዉነተኛ ቀበሮዎች ቢመጡ የምንመክትብት ጉልበት አይኖረንም፡፡ ለአሁኑ ግን ለእኔ የታየኝ አደገኛ ቀበሮ ኢህአዴግ ራሱ ነዉ፡፡

Monday, August 17, 2015

እስላማዊ መንግስት ለመመስረት በመንቀሳቀስ የተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 11 ፣ 2007 ( ኤፍ ቢ ሲ) እስላማዊ መንግስት ለመመስረት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች እንቅስቃሴ በማድረግ በሽብር ድርጅት ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው።
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ የወንጀል ችሎት የተከሰሱት፤ ከድር መሃመድ
፣ ነዚፍ ተማም፣ ካሊድ መሃመድ፣ ፉአድ አብዱልቃድር፣ ኢብራሂም ካሚል፣ አብዱ ጁባር፣ ሁሴን አህመድ፣ ሃሚድ ሙሃመድ፣ ቶፊቅ ሚስባህ፣ ዑስማን አብዱ፣ ሙሃመድ ኑሪ፣ አብዱልሃፊዝ ሺፋ፣ ዳርሰማ ሶሪ፣ ፍጹም ቸርነት፣ ሃሮን ሃይረዲን፣ ሸሃቡይን ኑረዲን፣ አያትል ኩበራ፣ ሃሺም አብደላ፣ ሙጂብ አሚኖ እና መሃመድ ከማል ናቸው።
የአቃቤ ህግ ክስ በአዲስ አበባ እና በጅማ ከተሞች የሚኖሩት ተከሳሾች በሃገሪቱ ያለውን የእምነት ነጻነት በመቃወም ከእነርሱ የአክራሪነት አስተሳሰብ ውጭ ምንም አይነት አስተሳሰብና አስተምህሮ መኖር የለበትም በማለት ተንቀሳቅሰዋል ሲል ያስረዳል።
ተደራጅተው መንግስትን በሃይል ከስልጣን በማውረድ በሸሪአ ህግ የሚመራ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት መንቀሳቀሳቸውን አቃቤ ህግ በክሱ አካቷል።
በቅርቡ በፅኑ እስራት ተቀጥተው በማረሚያ የሚገኙት እነ አቡበክር አህመድ ከዕስር እንዲፈቱ በሚል መነሻ ህዝበ ሙስሊሙን ለአመፅ በመቀስቀስ መንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር መንቀሳቀሳቸውም ተጠቅሷል።
ለዚህ ውጥናቸው ማሳኪያም በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ ወልቂጤ እና ወራቤ ከተሞች ህዝበ ሙስሊሙን ለአመጽ የሚቀሰቅሱ ጽሁፎችን በትነዋል የሚለውም በክሱ ሰፍሯል።
ፅሁፎቹ መጅሊሱ አይወክለንም፣ መንግስትን በሃይል ተደራጅተን እናወርዳለን፣ ትግላችን ይቀጥላል እና ሌሎች የአመፅ መልዕክቶችን ያዘሉ ወረቀቶች መሆናቸውንም ነው አቃቤ ህግ በክሱ ያስረዳው።
በተጠቀሱት ከተሞችም የሌሊቱን ክፍለ ጊዜ ተጠቅመው የአመጽ ወረቀቶች መበተናቸው በክሱ ተዘርዝሯል።
“ድምጻችን ይሰማ” የሚለውን የሽብር ቡድን ድረገጽ ተጠቅመው፤ በጂማ ዞን በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች እና በሌሎች ከተሞች የሽብር ቡድን በማቋቋም የሴቶች ክንፍ በመመስረት ጭምር ቅስቀሳ ያደረጉ አባላትን የመለመሉ መሆናቸውንም አቃቤ ህግ በክስ መዝገቡ ዘርዝሯል።
1ኛ ተከሳሽ ከድር ሙሃመድን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሌሎች ተከሳሾች ከ2004 መጨረሻ እስከ የካቲት 2007 በአዲስ አበባ ታላቁ አንዋር እና አወልያ መስጊዶች በነበረው አመጽ መሳተፋቸውም ተገልጿል።
ከድር ሙሃመድ ታህሳስ 2007 ጅማ ለሚገኘው የሽብር ቡድን የተለያዩ የአመፅ መልዕክቶችን የያዙ 10 ሺህ በራሪ ፅሁፎችንና 2 ሺህ ስቲከሮችን በካርቶን አድርጎ መላኩንና የተላኩትም በተለያዩ ቦታዎች መለጠፋቸው በክሱ ሰፍሯል።
በመዝገቡ የተጠቀሰው 2ኛ ተከሳሽ ነዚፍ ተማም የጅማ የሽብር ቡድን መሪ መሆኑ በአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ተጠቅሷል።
ተከሳሹ አዲስ አበባ ካለው የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር ቂሊንጦ በመምጣት፣ በዕስር ካለው አህመዲን ጀበል የጅማው አመፅ ተቀዛቅዟል አጠናክረህ ቀጥል የሚል መመሪያ ተቀብሎ፥ በ1ኛው ተከሳሽ በኩል ለአመፅ መቀስቀሻ የሚሆን በራሪ ወረቀት ማባዣ፣ ለፎቶ ኮፒ እና የወረቀት መግዣ ተልኮለት አመፁን መርቷል የሚለውም ተጠቅሶበታል።
አያትል ኩበራ የተባለችው ሴት በአዲስ አበባ የሽብር ቡድን ያቋቋመች፣ የሴቶች ክንፍ ሃላፊ የሆነች፣ በስልጤ ዞን የሽብር ቡድኑ አካል የሆኑ በርካታ ሴቶችን ያፈራች፣ በስልጢኛ ቋንቋ የሽብር ወረቀት የበተነች፣ በአዲስ አበባ ረብሻና ብጥብጥ እንዲነሳ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በየመስጊዶቹ በነበረው ብጥብጥ የተካፈለች ብሏል አቃቤ ህግ በክሱ።
ሌሎችም በተለያዩ ከተሞች አመጽ የሚቀሰቅሱ ወረቀቶችን በመበተናቸው በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ ተሳትፈዋል በማለት ነው የተከሰሱት።
ተከሳሾች ዛሬ ክሱ ተነቦላቸው በጠበቃቸው አማካኝነት የክስ መቃወሚያ እናቀርባለን በማለታቸው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ የወንጀል ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

በጥላሁን ካሳ


ሰበር ዜና ! አንድ ግለሰብ ወደ 15 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የእንግሊዝ ፓውድ ይዞ ለንደን አየር ማረፊያ ላይ በከስተም ( ጉምሩክ ) ፓሊሶች ተያዘ ።

አንድ ግለሰብ ወደ 15 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የእንግሊዝ ፓውድ ይዞ ለንደን አየር ማረፊያ ላይ በከስተም ( ጉምሩክ ) ፓሊሶች ተያዘ ። ግለሰቡ ከአዲስ አበባ የተነሳ ሲሆን በሻንጣው የያዘው ገንዘብ እንዲመለስለት እና እሱም የህውሀት አባልና የመንግስት ዲፕሎማ እንደሆነ ለመግለጽ ቢሞክርም የለንደን ግምሩክ ፓሊሶች ይህ ህግ ወጥ መሆኑን አስረድተውት በቁጥጥር ስር አውለውታል ።
ለግዜው የግለሰቡ ስም አልተገለፀም ።

ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ « ልጆቼን ለአደጋ እናቴን በመጨረሻ ዘመኗ ስንቅ አቀባይ ማደረግ አልሻም አለ ! »

የአረቡን ዓለም አስከፊ የስደት ገጽታ በማለዳ ወጉ የሚያስቃኘው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ የቱንም ያህል ኑሮው የስመረ ቢሆንም አንድም ቀን ነፍሱ በሃሴት ተሞልታ እንደማታውቅ በቀርብ የሚያውቁት ሁሉ ይናገራሉ ። በተለይ ከቁጥጠር ውጭ በወጣው ስደት ፤ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ስቃይና በደል መቋጫ እንዲያገኝ ድምጽ አልባ ለሆኑ ግፉሃን ድምጽ በመሆን ጋዜጠኛው እያሰማን ያለው የብዕር ጩኃት  የቱንም ያህል የህዝብን  ቀልብ ስቦ ደረት ቢያስደቃም ፤ ድጊቱ  በህወሃት/ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስረአት ባለስልጣናት ዘንድ ግን አልተወደደለትም።  ጅዳ ቆንስላ ጽ/ቤትና ሪያድ ኤንባሲ  ተሰግስገው በዜጎች ንግድ የከበሩ የስረአቱ ፖለቲካ ደላሎች ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ « የዲፕሎማቱን የስራ እንቅስቃሴ አሰናክሏል ፡ ህዝብን  በመንግስት ላይ አነሳስቷል » በሚል ተራ ውንጀላ ጣታቸውን ቀስረው  በሀወሃት መራሹ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ድህንነት  ጥርስ ውስጥ ገብቶ ጋዜጠኛው በአይነ ቁራኛ መጠበቅ  ከጀመረ  እነሆ  አመታትን አስቆጠሯል።



ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ  ፈጽሞል በተባለው ነገር ተላልፎ እንዲሰጥ ህወሃቶች   ለሳውዲ መንግስት እስካሁን በይፋ ያቀረቡት ጥያቄ ባይኖረም አንደበታቸው በእውሸት  የተገነባ የስረዓቱ ካድሬዎች  ጋዜጠኛው  የስይፍ ሰላባ እንዲሆን ለሳውዲ ሸሪዓ  ፍ/ቤት የሃሰት መረጃ ለማቅረብ  ያልበጠሱት ቅጠል ያልፈነቀሉት ድንጋይ  እንደሌለ  ይነገራል። ነብዩ ሲራክ በአንድ ወቅት በሳውዲ ፀጥታ ሃይሎች ታስሮ ከተፈታ ወዲህ  እስካሁን የጎላ ችግር ባይደርስብትም ለእረፍት ወደ ሃገር ሲያቀና  በቁጥጥር ስር ለማዋል  እቅድ እንዳለ ለጉዳዩ ቅረበት ያላቸው ምስጢራዊ ምንጮች አረጋግጠዋል። በማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ  በሚያጠነጥን  የማለዳ ወግ መረጃ ቅበላው እንደ ጥፋት ተቆጥሮ ክትትል የሚደረግበት ይህ ጋዜጠኛ በወዳጅ ዘመድ ናፍቆት እይተብስለስለ በዜጎች ስቃይና በደል ሰላም ያጣውን አይምሮ ለማሳረፍ ፤  የሚወዳትን ሃገሩንና የተወለደበትን ቀዬ ለመርገጥ አለመታድሉን መረዳት ተችሏል። እያደረገ  ባለው ነገር ሁሉ ደስተኛ መሆኑንና ቅንጣት ያህል ለፈሪዎች ዱላ እንደ ማይበረከክ በዚህ ዙሪያ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ የስጠው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ፤ «ይህ ስጋት በአንዳንድ ወዳጅ ዘመዶቹ እንደተነገረውና ለግዜው ወደ ሃገር ከመሄድ መቆጠቡን ገልጾ በዓረቡ አለም በሚገኙ ዜጎቻን ላይ የሚፈፀመው ቅጥ ያጣ በደል እስኪያበቃ ፤ በግሉ እያቀረበ ባለው መርጃ የሚመጣውን ሁሉ በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን  አልሸሸገም ።ጋዜጠኛው  በማስከተል  « ምንም እንኳን የማቀርበው መረጃ ከማህበራዊ ጉዳዮች ያለፈ ባይሆንም በድርጅት አባላትና በተወካዮቻቸው ላይ የምሰነዝረው የሰላ ሂስ ለሁሉም ስጋት መሆኑ ግልጽ ነው፣ ታዲያ ሃገርችን ውስጥ ትክክለኛ ፍትህ የሚሰጥ ቢሆን ብከሰስ እንኳ እንደ ማሸንፋቸው ጥርጥር የለኝም  ፣ ዳሩ ግና የ 4 ዓመት ህጻን የደፈረን ፍ/ቤትና የፍትህ ስርአት ተማምኖ ወደ ሀገር መግባት ልጆቼን ለአደጋ እናቴን በመጨረሻ ዘመኗ ስንቅ አቀባይ ማደረጉን ስለማልሻ ከመሄድ መታቀብ ግድ ሆኖብኛል! » በማለት ሃገር ለመግባት  እምነት እንድሌለው ገልጾል። በተያያዘ ዜና  ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ ሰሞኑን ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን ወንድሙን መርዶ አልቅሶ እርሙን ማውጣት በማይችልበት ስደት አለም ከዘመድ አዝማድ ርቆ በሃዘን ላይ ሃዘንን ማስተናገዱን ለማወቅ ተችሏል ። Ethiopian Hagere Jed Bewad

Saturday, August 8, 2015

ሰበር ዜና ሪያድ ከተማ በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ፀረ ወያኔ /ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ተቃውሞ ስትናጥ አደረች !

ሰሞኑን የህወሃት/ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ፍ/ቤት በሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ የወሰደውን ኢፍተሃዊ ውስኔ በመቃወም ሪያድ ከተማ ውስጥ ትላንት አርብ ኦገስት 7 2015 ምሸት ኢትዮጵያዊው ህዝበ ሙስሊም አንድነቱን ጠብቆ ተቃውሞውን አሰምቷል ። ቁጥሩ ከፍተኛ እንደሆነ ህዝብ የተገኘበት  ይህ ታላቅ ተቃውሞ የአካባቢውን ድባብ ለውጦት እንደ ነበር ለማወቅ ተችሏል። የተከሰተው ነገር በራሳችን እንደደረሰ ተሰምቶን በሶስት ቀን ውስጥ በተጠራ የተቃውሞ ጥሪ ይህን ያህል ህዝብ አንድነቱን ጥብቆ ለተቃውሞ በነቂስ መውጣቱ የትግሉ አንዱነት ጥንካሬ መገለጫ መሆኑን የገለጹት ሼክ ሲዒድ አህመድ ህዝበ ሙስሊሙ በመንግስት ከባድ ፈተና እንደ ተጋረጠበት አውስተው ይህ ፈተና አዲስ ሆኖብን ሳንደናገጥ ትግሉን በበሰለና በስለጠነ መንገድ በማጠናከር እስከ ድል መቀጠል እንደሚገባ በቁጣ የወጣውን ህዝብ ሙስሊም በማረጋጋት በአባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል ።
ሼክ ሰዒድ በማስከተል አቡበከር በአንድ ወቅት በመንግስት ፀጥታ ሃይሎች ወህኒቤት ግፍ እይተፈፀመበት  « ፍ/ቤቱም የኛ ፤ ፖሊሱም የኛ ፤ አቅቤ ህጉም የኛ ፤ መርማሪውም የኛ ስለሆነ የፈለከውን የመከላከያ ምስከር ብታመጣ ብትወጣ ብትወርድ ከፍርድ አታመልጥም እኛ ነን የምንፈርድብህ » ተብሎ በስረአቱ ካድሬዎች በምጸት ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በፊት ተነግሮት የነበረውን በተግባር ማየቱን ሼኩ ለተስብሳቢው በመጥቀስ በመሪዎቻችን ላይ የተፈፀመው ደባ ሊያስደንቀን እንደማይገባ ገልጸው የፍ/ቤቱን ኢፍታሀዊነት ለተሰብሳቢው በተጨባጭ  አስረድተዋል። በውቅቱ በቁጣ ገንፍሎ የወጣውን ህዝብ ለማስተናገድ ተይዞ የነበረው ቦታ በመጨናንቁ የነበረውን የሪያድ የአየር ሙቀት በመቋቋም ከ ምሽቱ 1 ስዓት ጀምሮ እስከ ሊሊቱ 9 ስዓት ድረስ በዘለቀው በዚህ  ፀረ ጭቆና ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ አንዳንድ የስብሰባው ተሳታፊዎች  ህዝበ ሙስሊሙን በገዛ ሃገሩ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣውን የህወሃት/ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስረዓት እንዲያጠፋላቸው እያለቀሱ  ለፈጣሪያቸው  ፀሎት  «  ዱአ » አድርሰዋል ።                                       የህወሃት/ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት ፍ/ቤት በህዝበ ሙስሊም ተወካዮች ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ሰረዓቱ በመላ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ላይ እየፈጸመ ያለው ሃይማኖታዊ ጭቆና ግፍና በድል አንዱ አካል መሆኑን የገለጹት እንዚህ የስብሰባው ተሳታፊዎች ከእንግዲህ ትዕግስታቸው መሞጠጡን ጠቅሰው  በዚህ አምባ ገነን ስረዓት ላይ የጀመሩትን ትግል እስከ መጨረሻ አጠናክረው ለመቀጠል በመወሰን የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።                                                                                                     በሳውዲ አረቢያ ድምጻችን ይሰማ ደጋፊዎች እያካሄዱ ባለው ሃይማኖታዊ ፀረ ጭቆና ትግል የህወሃትን/ኢ.ህ.አ.ዴ.ግን ስረዓት የቦንድ ሽያጭና መስል የስረአቱን እንቅስቃሴ በማሽመድመድ  የታወቁ  ግንባር ቀደምና ጠንካራ መሆናቸው  ይነገራል። «ማሳሰቢያ ሊንኩን ተጭነው ያድምጡ  ኢንጂነር መሃመድ አባስ ከሪያድ ሳውዲ አረቢያ