Monday, August 17, 2015

እስላማዊ መንግስት ለመመስረት በመንቀሳቀስ የተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 11 ፣ 2007 ( ኤፍ ቢ ሲ) እስላማዊ መንግስት ለመመስረት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች እንቅስቃሴ በማድረግ በሽብር ድርጅት ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው።
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ የወንጀል ችሎት የተከሰሱት፤ ከድር መሃመድ
፣ ነዚፍ ተማም፣ ካሊድ መሃመድ፣ ፉአድ አብዱልቃድር፣ ኢብራሂም ካሚል፣ አብዱ ጁባር፣ ሁሴን አህመድ፣ ሃሚድ ሙሃመድ፣ ቶፊቅ ሚስባህ፣ ዑስማን አብዱ፣ ሙሃመድ ኑሪ፣ አብዱልሃፊዝ ሺፋ፣ ዳርሰማ ሶሪ፣ ፍጹም ቸርነት፣ ሃሮን ሃይረዲን፣ ሸሃቡይን ኑረዲን፣ አያትል ኩበራ፣ ሃሺም አብደላ፣ ሙጂብ አሚኖ እና መሃመድ ከማል ናቸው።
የአቃቤ ህግ ክስ በአዲስ አበባ እና በጅማ ከተሞች የሚኖሩት ተከሳሾች በሃገሪቱ ያለውን የእምነት ነጻነት በመቃወም ከእነርሱ የአክራሪነት አስተሳሰብ ውጭ ምንም አይነት አስተሳሰብና አስተምህሮ መኖር የለበትም በማለት ተንቀሳቅሰዋል ሲል ያስረዳል።
ተደራጅተው መንግስትን በሃይል ከስልጣን በማውረድ በሸሪአ ህግ የሚመራ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት መንቀሳቀሳቸውን አቃቤ ህግ በክሱ አካቷል።
በቅርቡ በፅኑ እስራት ተቀጥተው በማረሚያ የሚገኙት እነ አቡበክር አህመድ ከዕስር እንዲፈቱ በሚል መነሻ ህዝበ ሙስሊሙን ለአመፅ በመቀስቀስ መንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር መንቀሳቀሳቸውም ተጠቅሷል።
ለዚህ ውጥናቸው ማሳኪያም በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ ወልቂጤ እና ወራቤ ከተሞች ህዝበ ሙስሊሙን ለአመጽ የሚቀሰቅሱ ጽሁፎችን በትነዋል የሚለውም በክሱ ሰፍሯል።
ፅሁፎቹ መጅሊሱ አይወክለንም፣ መንግስትን በሃይል ተደራጅተን እናወርዳለን፣ ትግላችን ይቀጥላል እና ሌሎች የአመፅ መልዕክቶችን ያዘሉ ወረቀቶች መሆናቸውንም ነው አቃቤ ህግ በክሱ ያስረዳው።
በተጠቀሱት ከተሞችም የሌሊቱን ክፍለ ጊዜ ተጠቅመው የአመጽ ወረቀቶች መበተናቸው በክሱ ተዘርዝሯል።
“ድምጻችን ይሰማ” የሚለውን የሽብር ቡድን ድረገጽ ተጠቅመው፤ በጂማ ዞን በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች እና በሌሎች ከተሞች የሽብር ቡድን በማቋቋም የሴቶች ክንፍ በመመስረት ጭምር ቅስቀሳ ያደረጉ አባላትን የመለመሉ መሆናቸውንም አቃቤ ህግ በክስ መዝገቡ ዘርዝሯል።
1ኛ ተከሳሽ ከድር ሙሃመድን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሌሎች ተከሳሾች ከ2004 መጨረሻ እስከ የካቲት 2007 በአዲስ አበባ ታላቁ አንዋር እና አወልያ መስጊዶች በነበረው አመጽ መሳተፋቸውም ተገልጿል።
ከድር ሙሃመድ ታህሳስ 2007 ጅማ ለሚገኘው የሽብር ቡድን የተለያዩ የአመፅ መልዕክቶችን የያዙ 10 ሺህ በራሪ ፅሁፎችንና 2 ሺህ ስቲከሮችን በካርቶን አድርጎ መላኩንና የተላኩትም በተለያዩ ቦታዎች መለጠፋቸው በክሱ ሰፍሯል።
በመዝገቡ የተጠቀሰው 2ኛ ተከሳሽ ነዚፍ ተማም የጅማ የሽብር ቡድን መሪ መሆኑ በአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ተጠቅሷል።
ተከሳሹ አዲስ አበባ ካለው የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር ቂሊንጦ በመምጣት፣ በዕስር ካለው አህመዲን ጀበል የጅማው አመፅ ተቀዛቅዟል አጠናክረህ ቀጥል የሚል መመሪያ ተቀብሎ፥ በ1ኛው ተከሳሽ በኩል ለአመፅ መቀስቀሻ የሚሆን በራሪ ወረቀት ማባዣ፣ ለፎቶ ኮፒ እና የወረቀት መግዣ ተልኮለት አመፁን መርቷል የሚለውም ተጠቅሶበታል።
አያትል ኩበራ የተባለችው ሴት በአዲስ አበባ የሽብር ቡድን ያቋቋመች፣ የሴቶች ክንፍ ሃላፊ የሆነች፣ በስልጤ ዞን የሽብር ቡድኑ አካል የሆኑ በርካታ ሴቶችን ያፈራች፣ በስልጢኛ ቋንቋ የሽብር ወረቀት የበተነች፣ በአዲስ አበባ ረብሻና ብጥብጥ እንዲነሳ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በየመስጊዶቹ በነበረው ብጥብጥ የተካፈለች ብሏል አቃቤ ህግ በክሱ።
ሌሎችም በተለያዩ ከተሞች አመጽ የሚቀሰቅሱ ወረቀቶችን በመበተናቸው በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ ተሳትፈዋል በማለት ነው የተከሰሱት።
ተከሳሾች ዛሬ ክሱ ተነቦላቸው በጠበቃቸው አማካኝነት የክስ መቃወሚያ እናቀርባለን በማለታቸው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ የወንጀል ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

በጥላሁን ካሳ


No comments:

Post a Comment