Thursday, February 27, 2014

"ዓድዋ - ይከበር፣ ይዘከር - ለዘላለም !" ( የማለዳ ወግ ... ጉዞ ወደ ዓድዋ ! ነቢዩ ሲራክ )


የማለዳ ወግ ... ጉዞ ወደ ዓድዋ ! 
"ዓድዋ - ይከበር፣ ይዘከር - ለዘላለም !"

የአድዋ ድል የአድዋ ድል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የማንነታችን መሰረትና የህልውናችንም መገለጫ ብቻ ነው አልልም ። ዓድዋ ለመላው የጥቁር ህዝብ የነፃነት ተምሳሌትና የአርነት ምንጭ ስለመሆኑ የታሪክ መዛግብትም ሆኑ ባእዳን የታሪክ ልሂቃን ሳይቀር የሚመሰክሩት ሃቅ ነው ። በዓድዋ የጥቁር ዘር አትንኩኝ ባይበት ሲረጋገጥ የጥቁር ዘር ለነጻነቱ ቀናኢ መሆኑን ለአለም የታየበት መሆኑም የሚታበል አይደለም ! 

የዚህ ታላቅ ድል ባለቤቶች ደግሞ ኢትዮጵያውያን መሆናችን አልፋና ኦሜጋ ሲያኮራን ይኖራል። የዓድዋን ታሪካዊ የድል በአል በመላ አለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን አመት በመጣ ባሰለሰ ቁጥር በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል። በአሉ ሃበሾች በነጭ እብሪተኞች ላይ የተቀዳጀነው የዓድዋ ነውና ቀጣዩ ትውልድ ታሪኩን አክብሮና ጠብቆ እንዲኖር ያደገዋልና የበአሉ መከበር ታሪክን ከማወራረስ አንጻር ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው ። የዘንድሮው 118ኛ የዓድዋ ድል በአል ለማክበር በአገርና በቀረው አለም በምንገኝ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ድህረ ገጾች ሰፋ ያለ የመታሰቢያ ማዘከሪያ ዝግጅትን በማድረግ ላይ መሆናችን እውነት ነው ። 

በአረቡ አለም በተለይም ከግማሽ ሚሊዮን የማያንስ ኢትዮጵያውያን በምንገኝበት በሳውዲ አረቢያ በአሉን አድምቀን እንድናስበው ስለማይደረግ እድሜ ለቴክኖሎጅ በአሉን በማህበራዊ ገጾቻችን ለማክበር ተፍ ተፍ በማለት ላይ እንገኛለን። በሪያድ ኢንባሲና በጅዳ ቆንስል ሃላፊዎቻችን የዓድዋን ታላቅ ሃገር አቀፍ በአል በአዳራሾቻቸው ተሰባስበን እንድናከብረው ቢያደርጉን ምንኛ በኮራን ነበር ! ዳሩ ግና የኢንባሲና የቆንስል ሃላፊዎቻችን እንዲህ አስበው አናውቃቸውም እንደ ልማዳችን እናዝናለን ። ቢያንስ የገዥው ፖለቲካ ድርጅቶች እና በጎጥ ለተመሰረቱት የልማት ማህብራት የሚሰጡትን ያህል ለቱባው ኢትዮጵያዊነት ክብር ሰጥተው ዓድዋን ሻማ አብርተን የጀግኖቻችን ታሪክ ላንድ አፍታ እያነሳሳን እንድናዘክር ፣ እንድንማማርና እንድናመሰግን አያደርጉም ። እውነቱ ይህ ሆነና የስደት ፍሬ የሆኑ በአረብ ሃገር ተወልደው የሚያድጉ ልጆቻችን የዓድዋንና የመሳሰሉ ሃገር አቀፍ በአላት ይልቅ ስላደጉበት አገር በአላት የተሻለ እውቀት እንዲኖራቸው እየገፋናቸው በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ። የበአሉን አከባበር ካነሳሁ አይቀር ቀልቤን ወደሳበው እና መነሻየ ወደ ሆነው በስድስት ትንታግ ጎልማሶች እየተደረገ ስላለው የዓድዋ ታሪካዊ የእግር ጉዞ ላምራ ...

በፍላጎት የተሰባሰቡ ስማቸው ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ስድስት ጎልማሶች
1ኛ / ጋዜጠኛና የፊልም ባላሙያው ብርሃኔ ንጉሴ 
2ኛ/ ጋዜጠኛ ኤርሚያስ ዓለሙ ከኢትዮጲካሊንክ 
3ኛ/ መሐመድ ካሣ (ኬር ኤቨንትስ ኤንድ ኮሙኒኬሽን - የባህልና የኪነ ጥበብ ፕሮሞተር) 
4ኛ/ ሙሉጌታ መገርሣ (ደብሊው) (የፊልም ባለሙያ) 
5ኛ/ አለምዘውድ ካሳሁን (የካሜራ ባለሙያ) 
6ኛ/ ያሬድ ሹመቴ (የፊልም ባለሙያ) 

በአንድ ውለው በአንድ አስበው ለታሪካዊው 118 የዓድዋ ድል መታሰቢያ ልዩ ዝግጅት አቅደው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴው አመሩ። ጥር 10 ቀን 2006 ዓ.ም ከሌሊቱ 11፡30 በግምት ወደ 40 ቀን የሚወስደውን ረጅሙን ወደ ዓድዋ የሚያደርጉትን የ1,006 ኪሎ ሜትር ርቀት ጉዞ ከአዲስ አበባ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አደባባይ በአንድ እርምጃ ጀምረው ወደ ማጠናቀቁ ተቃርበዋል። 

ታላቁን የአድዋ ድል ለማዘከር "ዓድዋ - ይከበር፣ ይዘከር - ለዘላለም" የሚል መፈክር ይህን ጉዞ ለማድረግ ያነሳሳቸው ዋና አላማ 118ኛ የዓድዋን ድል ቀን በዓድዋ ለማዘከር እንደሆነም ሰምተናል። ትንታግ ጎልማሳ ወንድሞቻችን በትጋት የጀመሩትን ጉዞ ሊያጠናቅቁ የቀራቸው ጥቂት ቀናት ብቻ ነው። 

ከአጤ ምኒልክ አደባባይ የተጀመረውን ጉዞውን ልዩ የሚያደርገው ቀደምት አባቶቻችን የዓድዋ ድል ከ118 አመት ለማስገኘት እየተሰባሰቡ የዘመቱባቸውን ከተሞች ተከትሎ መሆኑ ታሪካዊውን የሃገር ወዳድ ወንድሞች ጉዞ ልዩ አድርጎታል። የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርገው በማውለብለብ ጉዟቸውነወ በመከወን ላይ የሚገኙት ተጓዦች በየደረሱባቸው ታሪካዊ ከተሞች ሞቅና ደመቅ ያለ አቀባበል እየተደረገላቸው መሆኑን ያን ሰሞን ተጓዦች መረጃውን አድርሰውናል።

እኒህ የብርታት ተምሳሌት የሚሆኑን ትንታግ ወንድም ተጓዦች ቃል አቀባይ ወንድም ተጓዦች ኮንቦልቻ እንደደረሱ በሰጠው ማብራሪያ እንዲህ በማለት ያስረዳል "... ማለዳ በአድዋ ድልድይ ተሻገሩ፡፡ ለገጣፎ - ለገዳዲ - ሰንዳፋ - በኪ - አለልቱ - ፍቼ - ሐሙስ ገበያ - ሸኖ - ሰምቦ - ጥያኪ - ጫጫ - ጠባሴ - ጅሁር መገንጠያ - ደብረ ብርሃን - አንኮበር መገንጠያ - ቀይት - ጉዳ በረት - ጣርማ በር - ደብረ ሲና - ጭራ ሜዳ - አስፋቸው - ሸዋ ሮቢት - አጣዬ - ከሚሴ - ሃርቡ - ፎንተኒና - አልፈው ኮምቦልቻ ደርሰዋል፡፡ በመንገድ ላይ አጤ ምኒልክ እና ሠራዊቱ (የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች) ለአገርና ለሕዝብ ዘብ የቆሙ ወታደሮች የደረሰባቸውን መከራ ይዘክራሉ፡፡ የአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች ድል ነው፡፡ በዚህ ድል አፍሪካዊያን ይኮራሉ፡፡ የዚህ ድል ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ በዚህ የታሪክ ሰንሰለት ተምሳሌቱን ዳግም ለዓለም ለማወጅ ታሪካዊ ጉዞ እያደረጉ ናቸው፡፡ ተጓዦቹ - ሰንቃጣ ወይንም (ስንቅ አጣን) ሲደርሱ የታሪካዊ ጉዞ ፈተና ይቀምሳሉ፡፡ (ይራባሉ - ይጠማሉ፡፡) የስድስቱ ተጓዦች ለመራብ - ለመጠማት መዘጋጀታቸው ልዪ የሚያደርገው ስንቅ እያላቸው መሆኑ ነው፡፡ ስድስቱ የእግር ተጓዦች የካቲት 23 ቀን 2006ዓ.ም አድዋ ይደርሳሉ፡፡ 118ኛ የዓድዋ ድልን በአድዋ ተራራ ያከብራሉ፡፡ በርካታ ታሪካዊ መዘክሮችን አዘጋጅተዋል፡፡ ለምሳሌ ሶሎዳ ተራራ ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ በክብር ለማቆም አቅደዋል፡፡ የአድዋ ክብረ በዓል ላይ የበዓሉን ማብሰሪያም መድፍ ይተኮሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ተጓዦቹ - ‹‹በየደረስንበት የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ አቀባበልና ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡ !›› ብሏል ! ጉዞው አሁንም ቀጥሏል ... እኒህ ወንድሞች ትጋትና ቁርጠኝነትን በትጋት እና በተግባት ለማሳየት ፣ የአባቶቻችን ታሪካዊ ተጋድሎ በክብር ለማስታወስ "ዓድዋ - ይከበር፣ ይዘከር - ለዘላለም !" ሲሉ የእግር ጉዞ አኩርቶኛል! በእርግጥም እኒህ ወንድሞቻችን ለአባቶች ተጋድሎ ተድበስብሶ እንዳይቀር እና አንጸባራቂውን ድል ለቀጣዩ ትውልድ በክብር ለማውረስ ስራ በመስራታቸው ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል! ይህን መሰል ፋና ወጊ ታሪክ ለመስራት መታደል በእርግጥም መታደል ነው !

አዎ እኔም በአድዋ ድል እኮራለሁና "ዓድዋ - ይከበር፣ ይዘከር - ለዘላለም !" እላለሁ ! 
የዓድዋን ድል በክብር እዘክራለሁ ! እናዘክራለን !

ክብር ለኢትዮጵያ ክብር ለደሙ ለቆሰሉና በክብር ለሞቱ ሰማዕነታት ፣ ለጀግኖቻችን !

ከሰብር ለእምየ ምኒሊክ እና ለእቴጌ ጣይቱ !

ክብር ለኢትዮጵያ !

ሰላም

ነቢዩ ሲራክ

No comments:

Post a Comment