Monday, September 30, 2013

የተቃውሞ ፓርቲዎች ሠላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ

የተቃውሞ ፓርቲዎች ሠላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትኅ ፓርቲ ከ 33ቱ ፓርቲዎች ጋራ በመሆን ለዛሬ በመስቀል አደባባይ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በፖሊስ ክልከላ የአንድነት ጽ/ቤት በሚገኝበት ቀበና መካሄዱ ተገለፀ።

የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር ሰልፉን ተከታትሎ ባደረሰን መረጃ መሰረት እጅግ በርካታ ሠላማዊ ሰልፈኞች ሠልፉን ለማከናወን ወዳቀዱበት መስቀል አደባባይ እንዳይሄዱ ፖሊስ መንገዱን በመዝጋት ተከላክሎዋል። ከ ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር ጋ ያደረግነውን ቃለ መጠይቅ ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል።

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትኅ ፓርቲ ከ 33ቱ ፓርቲዎች ጋራ በመሆን ለዛሬ በመስቀል አደባባይ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በፖሊስ ክልከላ የአንድነት ጽ/ቤት በሚገኝበት ቀበና መካሄዱ ተገለፀ። የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር ሰልፉን ተከታትሎ ባደረሰን መረጃ መሰረት እጅግ በርካታ ሠላማዊ ሰልፈኞች ሠልፉን ለማከናወን ወዳቀዱበት መስቀል አደባባይ እንዳይሄዱ ፖሊስ መንገዱን በመዝጋት ተከላክሎዋል። አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በሰልፉ ወደ 80,000 የሚጠጉ ሰዎች መሳተፋቸውን የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንደሚገምቱ ጠቅሷል። የዜና አውታሩ አያይዞም የመንግሥት ቃል አቀባይ ሬድዋን ሁሴን በሰልፉ የተገኙት በጥቂት መቶ የሚቆጠሩ እንደሆኑ መግለፃቸውንም ገልጿል።

ሰልፈኞቹ የጸረ-ሽብር ሕጉ ይሰረዝ፣ የታሰሩ የኅሊና እስረኞች ይፈቱ፣ የኢሕአዴግ መገለጫው ሙስና ነው፣ የሕዝቡ የመሬት ባለቤትነት ይረጋገጥ፣ መብትን መጠየቅ አሸባሪነት አይደለም፣ ፍትኅ እንፈልጋለን፣ ዲሞክራሲ እንሻለን የሚሉና ሌሎች በርካታ መፈክሮችንም በከፍተኛ ድምፅ ማሰማታቸው ታውቋል።

በሰልፉ ላይ ከቃሊቲ እስር ቤት የተላከው የአንዱዓለም አራጌን ጨምሮ ዝዋይ ከሚገኙ እስረኞች የተላከ መዕልክት በንባብ ቀርቧል። ሠልፉ በአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ንግግር በፓርቲው ጽ/ቤት መጠናቀቁ ታውቋል። (ፎቶና ዜና: DW)

Saturday, September 28, 2013

በመስቀል በዓል ዕለት እንዲዘመር የደረሰው ዜማ፡

ቅዱስ ያሬድ፡
መስከረም ፲፯ ቀን በሚውለው፡
በመስቀል በዓል ዕለት እንዲዘመር የደረሰው ዜማ፡
ከድጓ መጽሓፉ የተገኘ።
_________________________

ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ የነበረ!
ዛሬም ያለ! እና ወደፊትም፡ ለዘለዓለም የሚኖር!

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ወደኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ፡ ክረምት ነበረና፡ በዚያ በሚገኘው፡ በሰሎሞን የሰላም ደጃፍ፡ መስቀልን ተመርኵዞ፡ ድንቅ ተአምራትን እያሳየ፡ ተመላለሰ። 
አዎን! ዛሬ፡ መስቀል ተከበረ! ለተቀበሉት አበራ! አዎን! ለእኛ፡ ካሣችን፥ ጽንዓታችን፥ የነፍሳችን መዳኛ ለኾነው መስቀል፥ አይሁድ ሲክዱት፡ እኛ ግን ለዳንበት፡ ለመስቀል የሚገባው ምስጋና፡ እነሆ ዛሬ ቀረበ! 
ከዚህ እውነት ጋር፡ "መስቀል፡ ለዓለሙ ኹሉ ብርሃን ነው!" ሲሉ፡ ነቢያት የተናገሩት ቃል ይተባበራል።
መስቀል ድል ነሥቷልና፡ ሞት ተቈጣ! የመስቀል ኃይል አበራ! 
አንተ መስቀል ሆይ! በስሙ የታነፀች፥ በደሙ የተቀደሰች፥ በመስቀሉ ስም የተጠበቀች፥ ያማረች፥ መልካምና ፍጽምት የኾነችውን መቅደስ የያዘችው፥ የሰው እጅ ያልሠራትና ለእግዚአብሔር፡ የምስጋናው ማኅደር የኾነችው፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን፡ የድል ምልክት ነህ! 
ዘወትር በቅዱሳን የሚመሰገነው፥ ለአሕዛብና ለዓለሙ ኹሉ፡ በላይ በሰማያት፥ በታችም፡ በምድር የነገሠው መስቀል፡ ዛሬ፡ በዓሉ የሚከበርበት ነው። 
ዳግመኛ፡ የሕይወት መንገድ መሪ የኾነው፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ለአይሁድ እንዲህ አላቸው፦ "በእኔ እመኑ! በአባቴም እመኑ! ዛሬስ፡ በመስቀሌ፡ ለእናንተ አበራለሁ።" 
ቅዱስ ዳዊት፡ በትንቢት መንፈስ ኾኖ፡ በእርሱ ላይ፡ የእግዚአብሔር አብ ቃል ስለተሰቀለበት፡ ስለዚህ፡ የእንጨት መስቀል፡ እንዲህ አለ፦ "በላያችን ላይ ቆመው፡ የሚያሠቃዩንን፡ በስምህ እናዋርድበታለን።" ደግሞም አለ፦ "በጋሻነቱ፡ ከተወረወረ ቀስት ያመልጡበትና ይድኑበት ዘንድ፡ ለሚፈሩህ ወዳጆችህ፡ ምልክትን ሰጠሃቸው።"
ስለዚህ፡ እኛም፡ ዛሬ፡ ደስ ብሎን፡ በዚህች፡ በጌታችን የበዓል ዕለት፡ ሓሤት እናደርጋለን።
እርሱ፡ ጌታችን፡ ለፍጡሩ ሰው፡ ሕይወትን ሊሰጥ፡ ወደዚህ ዓለም፡ በሥጋ መጣ፤ መጥቶም፡ ተሰቀለ፤ ተሰቅሎም አዳነው፤ ለሥጋዊውና ለመንፈሳዊ ዕረፍቱም፡ ሰንበትን ሠራለት።
ከኹሉ ይልቅ ታላቅና ኃያል የኾነው አምላክ፡ ቅዱሳት እጆቹ፡ በዚህ መስቀል ላይ ተቸነከሩ፤ ጎኑን፡ በጦር ተወግቶ፡ ለዓለሙ ኹሉ መድኃኒት የኾነው ደሙ፡ ከውኃ ጋር ተቀላቅሎ ፈሰሰ። 
ይህም የኾነው፡ "መስቀል አበራ!" እያልን፡ በደመራው ዙሪያ፡ እየዞርን ለምንዘምረው፡ ለእኛ፡ በመስቀሉ ሃይማኖት አምነን፡ እያመሰግንን ለምንኖረው ነው።
ይህ መስቀል፡ ካሣ ኾኖ ያዳነን ነው፤ ለአይሁድ መሰደጃቸው ሲኾን፡ ለእኛ ግን፡ ሕይወት ኾነን። 
አዎን! ዛሬ፡ መስቀል ተከበረ! ለተቀበሉት አበራ! አዎን! ለእኛ፡ ካሣችን፥ ጽንዓታችን፥ የነፍሳችን መዳኛ ለኾነው መስቀል፥ አይሁድ ሲክዱት፡ እኛ ግን ለዳንበት፡ ለመስቀል የሚገባው ምስጋና፡ እነሆ ዛሬ ቀረበ!
ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለብሽ አንቺ፡ የጎልጎታዋ ቀራንዮ ሆይ! የጌታችን እግሩ በቆመብሽ፥ ጎኑ በተወጋብሽ፡ በአንቺ ዘንድ፡ ዛሬ፡ በመስቀሉ በዓል ዕለት፡ ለእርሱ መስቀል፡ እኛ ኹላችን እንሰግዳለን። 
ዛሬ፡ በላይ፡ በሰማያት፥ በታችም በምድር፡ በዚህ መስቀሉ፡ ሰላምን ያደረገበት፡ የመስቀሉ በዓል ነው።

የማለዳ ወግ ... በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያውያን ክራሞት « በታላቁ የጀርመን ድምጻ ጋዜጠኛ ሲዳሰስ »






የማለዳ ወግ ... በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያውያን ክራሞት*ከተፈናቃዮች አበሳ እሰከ አሳሳቢው የስደት ፍሬ ልጆቻችን ትምህርት አሰጣጥ ህጸጽ ! 

አዲሱ አመት ባባተ ማግስት በሳውዲ አረቢያ የከተምን የብዙዎችን ቀልብ የሳበው መረጃ ትኩረት በኮንትራት ስራተኞች መፈናቀል ዙሪያ በጅዳና ሪያድ የሚገኙ ተፈናቃዮች አሳዝኝ ይዞታ ጉዳይ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በጅዳም በሪያድም ግፉአን የሚታደጋቸው ጠፍቶ ኑሯቸው ከፍቷል ፣ ይህንን የከፋ የዜጎች በደል አንስቶ መናገርና መረጃ መስጠት ደግሞ ነውር ሆኗል ፣ በሃላፊዎቻችን ዘንድ በተፈናቃዮች ዙሪያ መረጃ ማቅረብ እንደ ወንጀለኛ ስለሚያስቆጥር ብዙሃኑ ነዋሪ ቀርቦ ተፈናቃዮችን እንዳይረዳና በመፍትሔው ዙሪያ እንዳይመክር ስልታዊ ጫናው በርትቶበታል። ነዋሪው እንዳይቅርብ ፣ እንዲፈራና አንዲሸሽ እየተደረገም ነው። ያን ሰሞን እኔን ጨምሮ በዜጎች መብት ጥበቃና ግልጋሎት አሰጣጥ ላይ የሰላ ሂስ የምናቀርብ ዜጎች በቆንስሉ ስብሰባ እንዳንሳተፍ ተደርጎ ነበር ። ዛሬም ያው እገዳ ቀጥሎ የመንግስታችን ሃላፊዎች ለመብት ጥበቃው እንዲተጉ በአደባባይ የሚናገሩ ወንድሞች በተለያዩ ስብሰባዎች እንዳይገቡ የጅዳው ቆንስል አቶ ዘነበ ከበደ አዘው እየተተገበረ ይገኛል። ያው የጅዳው ቆንስል እገዳ ቀጥሎ ትናንት አርብ ምሽት በጅዳ ቆንስል በተደረገው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትት የአቶ መለስ ዜናዊ " ፋውንዴሽን "።መዋጮ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ጅዳ ቆንስል የስብሰባ አዳራሽ ጎራ ያሉ ተፈናቃዮችን በመደገፍ የሚታወቁ ወጣቶች በስብሰባው እንዳይሳተፉ መደረጋቸውን ሰምቻለሁ ! ያሳዝናል ...
ይህ ግራ እያጋባን ባለበት በዚህ ሰአት ደግሞ ሌላ ሊሰሙት የሚያም መረጃ ከወደ ሪያድ ተሰራጭቷል ። የኢንባሲው ድጋፍ የተነገፋቸው ተፈናቃይ የኮንትራት ሰራተኞች በውስጥ ደወዌ ተጠቅተው በህክምና እጦት እየሞቱ ነው። ኑሯቸውን በሪያድ ያደረጉትም ቢሆን ክራሞታቸው ድስ አይልም። ኢትዮጵያውያን የሪያድ ነዋሪዎች እና የሪያድ ኢንባሲ በትምህርት ቤቱ ዙሪያ ፍጥጫ ገጥመው መሰንበታቸው እውነት ነው ። ብርቱዎች የሪያድ ወላጅ ኮሚቴ አባላት " በልጆቻችን ለመጣ ወደ ኋላ አንልም !" በማለት ከኢንባሲው ጋር እየዶለቱ የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያደናቅፉ ያሏቸውን በጽናት ተቃውመዋል። ኮሚቴዎች ከማስፈራሪያ ጀምሮ የህዝብ አዳራሽ እስከ መከልክል ቢደርሱም የሪያድ ኢንባሲን ፍትሃዊ ያልሆነ የሚሉትን አሰራር በመቃወም በአስገራሚ ጽናት የመሞገታቸውን ጭብጥ ያለው መረጃ ከፊስ ቡክ ወዳጀ ከ Ethiopia Hagere ለመረዳት ችያለሁ ። ለጊዜውም ቢሆን በሪያድ ስላለው ለሪያዶች ትቸ ለጊዜው ትኩረቴን በጅዳው የኢትዮጵያውያን አለም አቀፍ ትምህርት ቤት እና በትምህርት አሰጣጡ ዙሪያ እየሆነ ስላላው ህጸጽ እና ትኩረት ሳቢ ጉዳይ ላቅና ...
የጅዳ የኢትዮጵያውያን አለም አቀፍ ትምህርት ቤት አዲሱን የ2006 አመት ትምህርት ካስጀመረ ወር ቢደፍንም ልጆቻችን በቂ ትምህርት እየቀሰሙ አይደለም ! ዛሬም እንዳምናና ካች አምናው የትምህርት ጥራት ሊያዘባራን መንገዱ ተጀመሯል። ከአመት አመት የትምህርት ጥራቱ እያደረ መዝቀጥ ሲነሳ ነዋሪው ስብሰባ ይጠራና በቀጣይ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ይመክራል...
*የመምህራን እጥረት 
* የተሟሉ የትምህርት ቁሳቁሶች በተፈለገው ደረጃ አለመሟላት
(የመጽሃፍት ፣ የኮምፒውተር እና የላብራቶሪ እቃዎች አለመሟላት ይጠቀሳል)
* የመምህራን በስራ ገበታቸውን አክብረው አለመገኘት ፣ 
* የመምህራን ትምህርት ቤቱን እየለቀቁ መሄድ 
* በትምህርት አሰጣጡ የመምህራኑ ብቃት ማነስ ቢያንስ ላለፉት ስምንት አመታት በዋናነት በሚጠሩት ስብሰባዎች የሚጠቀስ እየተነሳ የሚጣል ዋንኛ ችግር ነው ። 

የጅዳ ወላጆች ነዋሪ በተጠቀሱት ችግሮች ዙሪያ ያለውን መሰረታዊ ቅያሞት አቤቱታውን ሲያቀርብ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር እና አስተዳደር አንድም ጊዜ በወላጅ የሚቀርበው ክስና አቤቱታ ሃሰት ነው ብለው አያውቁም ! ዳሩ ገና አሁንም ቢያንስ ላለፉት ስምንት አመታት ሃላፊዎች ለሚያምኑት ለማይክዱት ስህተት መፍትሄ ሲያመጡ አልተስተዋለም ! ከአመት አመት በሚጠራ ስብሰባ ላይ የትምህርት ቤቱ ሃላፊዎች የማይካደው ስህተት የማይታረምበት እንቆቅልሽ ማቆሚያ መቸ እንደሆነ ለማናችንም ግልጽ አይደለም። በላባችን ያመጣነውን ገንዘብ ከፍለን የምናስተምር ተገልጋይ ወላጆች አቤቱታ የከረመ መሰረታዊ የትምህርት ቤታችን ችግር መፍትሄ ፈላጊ አላገኘምና ዛሬም የምንነጋገረው ያነኑ የሚታወቅ ችግር ነው ።
ትምህርት ቤቱ በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ኮሚኒቲ እያደር መጫጫት ለመፍትሄ ፍለጋው መኮላሸት ብቻ ሳይሆን ትምህርት ቤቱ በተፈለገው ፍጥነት ጥሩ ዜጎች ማፍራቱን እንዳይገፋበት ጋሬጣ ሆኖታል። የጅዳ አለም አቀፍ ትምህርት ቤት ከሁለት ሽህ በላይ ተማሪዎችን ያስተናግዳል። ይህ ትምህርት ቤት የብዙዎች ተስፋ ሆኖ የተስፋ ብርሃንን ወጋገን ያደረገልን አንጋፋ ትምህርት ቤት ለመሆን የበቃበት መንገድም ቀላል አይደለም። እንዲህ ብርቱ ፈተናዎችን እያለፈ ዛሬ ላይ ቢደርስም ማደግ ባለበት ፍጥነትና ደረጃ አድጓል ለማለት አይቻልም። ትምህርት ቤቱን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የጅዳና አካባቢዋ ኮሚኒቲ መስሪያ ቤት በተለያዩ ተጽዕኖዎች ስር ወድቋልና አለ አይባልም። ኮሚኒቲው አለ እየተባለ እዚህ ቢደርስም ትምህርት ቤቱ በማህበሩ ተጽዕኖ ስር መውደቁን ተከትሎ እያደር የትምህርት ቤቱ ችግሮች መቋጫ እንዳይገኝላቸው ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል። 
የጅዳ ኮሚኒቲ በትምህርት ቤቱ ከአመት እስከ አመት የሚነሱትን አንኳር አንኳር ችግሮች መፍታቱ ይቅርና በውስጥ አስተዳደር ክፍተት ለሚናጠው ትምህርት ቤት መፍትሄ መስጥት ያለቻለ የስም ብቻ ባለቤት አድርጎታል። ከሁሉ አስቀድሞ በመንግስት ለሚደራጁት የልማት ማህበራት ቅድሚያ እየተሰጠ ኮሚኒቲው ሽባ እንዲሆን መደረጉን መካድ አይቻለም ። ዛሬ ዛሬ ከመንግስት ደጋፊነት ቅርበት ካላቸው ወገኖች የሚሰጠን ገደምዳሜ መረጃ " የትምህርት ቤቱ ባለቤት ኮሚኒቲውን ለማጠናከር ሌላ አደረጃጀት ያስፈልገዋል !"በሚል የዱባይ ኮሚኒቲ ተሞክሮ ትግበራ ውስጥ ውስጡንም ቢሆንም ጥናት ላይ መሆኑን ያመለክታል። "ኮሚኒቲው አስተዳዳሪ ከሃገር ቤት ሊመጣለትም ነው !" መባሉን እየሰማን ነው! ያም ሆነ ይህ ማህበረሰቡ በኮሚኒቲው ያጣውን እምነት መመለስ እሰኪቻል የትምህርት ቤቱን ችግር ለመፍታት ከኮሚኒቲው መስሪያ ቤት በኩል የሚጠበቀው መፍትሄ ተስፋ የሚጣልበት አለመሆኑን ብዙዎች ይሰማሙበታል።

በዚህም ሆነ በዚያ የታዳጊዎች ልጆቻችን ጉዳይ ያገባኛል የሚል ጠፍቷል። ኮሚኒቲው ካለ አይቆጠርም እንኳን ቢባል በትምህርት አሰጣጡ ሂደት ችግር መኖሩን መርምሮ መፍትሔ ማፈላለግ ያለበት የወላጅ ኮሚቴ የት እንደገባ አናውቅም ! ይህን የምለው የትምህርት ቤቱ ጉዳይ የነዋሪው ሰፊ መወያያ እየሆነ መጥቶ እያለ ብዙሃን የመረጣቸው የወላጅ ኮሚቴዎች እንዲወገዱ ተደርገው በመንግስት ድጋፍ የወላጅና መምህራን ህብረት ኮሚቴ ካች አምና የተተኩት ተመራጮች "የዝሆን ጀሮ ይስጠኝ " በሚል መንፈስ ዝም ፣ ጭጭ ማለታቸውን መታዘቤ ነው ። ትምህርት ቤቱ ከቅጥር ፣ ምዝገባና አሁን ወደ ትምህርት አሰጣጡ ቅሬታዎች ሲቀርቡበት የወላጅ እና መምህራን ህብረት ኮሚቴው የት ነው ያለው? በተለይ የትምህርት ጥራቱን ሊያጎድሉ በሚችል ሁኔታ አብዛኛው ተማሪዎች የተሟላ ትምህርት ሳይሰጣቸውና ባዶ ክፍል እየዋሉ ለመመለሳቸው ኮሚቴ እኛን ሆኖ መናገር እና መሞገት አልቻለም ። ለምን ? ችግሮችን ለመቅረፍ ሃላፊነት ያለበት የወላጅ እና መምህራን ህብረት ኮሚቴ ሃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ በስሙ ብቻ አለ መባሉ ፋይዳ የለውም! 

የትምህርት ግብይቱ በያዝነው አዲስ አመት ልክ የዛሬ ወር ሲጀመር ክፍያ ተጨምሯል ተባለ፣ ወላጅ አይኑን ሳያሽ ጭማሪ ክፍያውን ተቀበለ ፣ ይህ በሆነ ማግስት አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ የሚልካቸው ልጆቹ ግን በቂ ትምህርት እያገኙ አይደለም ! መምህራን የሉም እና ሌላም ሌላ ምክንያቶች ዛሬም ሊቀርቡ ይችሉ ይሆናል ። ይህንምም ምክንያት ከመቀበል ሌላ አማራጭ የለምና ምክንያቱ ተቀነባብሮ እስኪነገረን " ሳይደርቅ በእርጥቡ! " እንደሚባለው ያሉት መምህራን በሃላፊነት እና በአግባቡ ትምህርት እየሰጡ ለመሆኑ ትምህርት ቤቱ ቁጥጥር ያደርግ ዘንድ እንማጸናለን! በቁጥጥር ማነስ ፣ በእንዝህላልነት እና የመሳሰሉት ሃላፊነትን ካለመረዳት የሚስተዋሉ ችግሮች እየጎዱን ነውና ጊዜ ሳንሰጥ መፍትሄ ሊፈልግላቸው ይገባል ! በአሳር በመከራ በአረብ ሃገር ስደት የምናሳድጋቸው የስደት ፍሬ ልጆቻችን አብዛኛው የትምህርት ሰአት እየባከኑ ነውና እባካችሁ ተማለዱን ! 

ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ


Friday, September 27, 2013

በዲፕሎማቱ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ሳይሸበር ህጻናት ከማሃይምነት ለመታደግ የት/ቤቱ ወላጅ ኮሚቲው በአቋሙ ፀና


በዲፕሎማቱ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ሳይሸበር የትምህርት እድል የተነፈጋቸውን ህጻናት ከማሃይምነት ለመታደግ በአቋሙ እንደሚጸና በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ት/ቤት የወላጆች ኮሚቴ ገለፀ።

ትላንት ሃሙስ ሴፕቴምበር 26 2013 ኮሚቲው ለወላጆቹ ባስተላለፈው አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ ማስተላለፉን ተከትሎ ብዛት ያላቸው ወላጆች መገኘታቸውን የሚገልጹት ምንጮች ዲፕሎማቱ የመንግስትን ስልጣን ተጠቅመው በወላጅ ኮሚቴው ላይ ተጸኖ ለማሳረፍ የኮሚቴውን አባላት እምባሲ ድረስ በስልክ አስጠርተው የፈጸሙት ተራ ማሰፈራሪያ እና ዛቻ ህጋዊ መስረት የሌለው እና መንግስት የቆመለትን ልማታዊ አስተሳሰብ በቅጡ ያላገናዘበ መሆኑን በመግለጽ፡ ዲፕሎማቱ የት/ቤቱን የመማር ማስተማር ስረአት ለማደናቀፍ እየፈጸሙ ያለውን ጣልቃ ገብነት ፀረ ህዝብ እና ጸረ ልማት ድርጊት እስከ መጨረሻው እንደሚታገሉ የወላጆቹ ኮሚቴ ደግመው አረጋግጠዋል ። 

ወላጆቹ በኢትዮጵያ ኮሚኒት አዳራሽ ስብሰባ ማድረግ እንድሚችሉ በዲያስፖራው ሃላፊ አቶ ተመስገን ኡመር ቀደም ተብሎ በተገባላቸው ቃል መስረት ሴፕቴምበር 22 2013 ምሽት አጠቃላይ የወላጆች ስብሰባ ተጠርቶ እንደነበር በማስታወስ በተጠቀሰው ቀን ብዛት ያላቸው ወላጆች ወደ መሰብሰቢያ አዳራሹ ሲጎርፉ በኤምባሲው ተዕዛዝ በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በር መዘጋቱ ዲፕሎማቱ ለህዝብ ያላቸውን ንቀት እና የለየ ጠብጫሪ ተግባራቸውን በግልጽ ያሳዩበት አጋጣሚ በመሆኑ የኛ ቅሬታ እና ተቃውሞ በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ፡ መሽገው ዲያስፖራወን እና መንግስትን ለማራራቅ በኮሚኒቲው አካባቢ ሰላም እያሳጡን ካሉት ዲፕሎማቶች ጋር ነው ብለዋል። ይህ በዚህ እንዳለ በየአቅጣጫው የፈነዳባቸውን ተቃውሞ ማዳፈን የተሳናቸው በሪያድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ወላጆችን በብሄር ከፋፍሎ ለማጋጨት የሚያስችላቸውን እቀድ ማውጣታቸውን የሚናገሩ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ዲፕሎማቱ ለዚህ እቅዳቸው መሳካት ያልታወቀ ህገወጥ ቡድን በስውር ሪያድ ከተማ ላይ ማሰማራታቸውን የኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም ተጠሪ የሆኑት ዲፕሎማት አቶ ዘላለም የወላጅ ኮሚቲውን ለማስፈራራት ሲናገሩ ከነብረው ገለጻ መረዳት መቻሉን አረጋግጠዋል። 
ይህ በዚህ እንዳለ መንግስት ቀደም ብሎ በብሄር ያደራጃቸውን የልማት ማህበራት ዲፕሎማቱ በተጓዳኝነት ለድብቅ አጀንዳዎቻቸው ማስፈጸሚያ ግበአት ለማድረግ የማህበራቱን ስራ አመራር አባላት ትላንት ሃሙስ ሴፕቴምበር 26 ቀን 2013 ምሽት በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒት አዳራሽ፡ ጠርተው በሚስጥር እንዳነጋገሯቸው የሚጠቅሱት የአይን እማኞች አባላቱ በአካቢያቸው የሚገኙትን የልማት ማህበራት አባላት እና ደጋፊዎች የፊታችን አርብ ኦክቶበር 4 2013 ኤንባሲው በጠራው የወላጆች አጠቃላይ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ እና የወላጅ ኮሚቴው ከተወሰኑ ነፍጠኛ እና ጽንፈኛ የአማራ የኦሮሞ እና የስልጤ ብሄረሰቦች የተውጣጡ ግለሰቦች መሆናቸውን በማስረዳት ቅስቀሳ ማድረግ እንደሚገባቸው መመሪያ ቢሰጡም በአብዛኛው አመራር አባላት ዘንድ ተቀባይነትን ማጣቱን ገልጸዋል። 

አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ት/ቤት ከ20 አመት በፊት ሻይ እን ዳቦ ሸጠው ያቋቋሙት ህጋዊ ንብረታቸው መሆኑንን በመረጃ እስደግፈው የሚናገሩት ወላጆች በየትኛውም አቅጣጫ ዲፕሎማቱ እየፈጸሙ ባለው ከፋፋይ ሴራ ሳንጠለፍ በቡድን እና በግል ለሚሰነዝሩብን ማስፈራሪያ እና ዛቻ ሳንበረግግ ህጋዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ዲፕሎማቱን ለህግ እናቀርባቸዋለን ብለዋል። 

በተለይ ላለፉት 5 አመታት ምንም አይነት ኦዲት ተደርጎበት የማያውቀው ት/ቤት ካዝና ላይ ብቅርቡ በተደረገው ማጣራት እስከ ከ1.5 ሚልዮን ሪያል ወይም በአሁኑ የሃገራችን ምንዛሪ «ከ5ሚሊዮን 8መቶ ሺህ ብር» በላይ ጉድለት ማሳየቱን የሚናገሩ እነዚህ ምንጮች ዲፕሎማቱ ከተማሪዎቹ ወላጆች ጋር እንካሰላምታ ውስጥ፡እንዲገቡ ያሰገደዳቸው አንዱ ምክንያት ይህ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ። ዲፕሎማቱ በት/ቤቱ የውስጥ ጉዳይ ከ3 አመት በፊት እጃቸውን በቀጥታ በማስገባት ከወላጆች እና ከኮሚኒቲው ፍላጎት ውጭ፡ በእጅ አዙር ኮሚኒቲው ት/ቤት ካዝና ውስጥ እጃቸውን ሲዶሉ እንደ ነብር የሚታወቅ ሲሆን ከቀር ግዜ ውዲህ በዲፕሎማቱ እና በአጠቃላይ የሪያድ መህበረሰብ መሃከል በተፈጠረው አለመግባባት ግዜያችንን ሳንጨርስ መንግስት ወደ ሃገር ካስጠራን ገበናችን አደባባይ እርቃኑንን ይቀራል በሚል ስጋት የተጠቀሰውን ት/ቤት እስከ ናካቴው ለማዘጋት አሊያም ለኢንቨተር ለመሸጥ እቅድ እንደነበ ራቸው ለመረዳት ተችሎል። 

የወላጆ ኮሚቴው ቀደም ስል ካቀረባቸው 4 ጥያቄዎች የት/ቤቱን ንብረት ከዘራፊዎች ለመከላከል ት/ቤቱን ወደ ቀድሞ ስሙ «በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ት/ቤት» እንዲለወጥ ማስቻል ግንባር ቀደም የትግላቸው መነሻ እንደሆነ በመግለጽ ዲፕሎማቱ ወላጆች ላቀረቦቸውን ህጋዊ ጥያቄ ተገዢ ሆነው በአግባቡ መመልስ ተስኖቸው ሰላማዊ ወላጆችን በጅምላ በሸባሪነት በመፈርጅ የዲያስፖራውን ጥያቄ የትኩርተ አቅጣጫ ለማስለወጥ፡እያደረጉ ያለው ጥረት አምኖ የወከላቸውን መንግስት እና በሪያድ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ክቡር የሚነካ ወራዳ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ መሰረት መንግስት ውጭ ሃገራት የተሰማሩ ዲፕሎማቶች በህግ አግባብ መጠየቅ የሚቻልበት እድል ካለ የፌደራሉ ስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ድንበር ተሻግሮ በሪያድ የኢትዮጵያ አለመ አቀፍ ት/ቤት ካዝና ላይ የተፈጸመውን አስነዋሪ ተግባር በመመርመር በሪያድ የኢትዮጵያውያ ኤንባሲ ህንጻ ውስጥ፡የመሸጉትን ስረአት አለበኛ ዲፕሎማቶች እና ከት/ቤቱ ካዝና ጋር ግንኙነት ባላቸው ተባባሪ ወገኖች ላይ መረጃ በማጠናቀር አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ ማስወሰድ ፡እንደሚጠበቅበት አበክረው አሳስበዋል። 

እንደሚታወቀው በሪያድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መ/ቤት የሴቶች እና የህጻናት ጉዳይ ተጠሪ ክብርት ወ/ሮ ደስታ ወ/የሃንስ በተገኙበት ስብሰባ በሪያድ ኢትዮጵያዊው ዲያስፖራ በዲፕሎማቱ ላይ ያሰማውን ተቃውሞ እና ቅሬታ ተከትሎ በሪያድ የኢትዮጵያው አምባሳደር መሃመድ ሃሰን በስቸኳይ ወደ ኢትዮጵያ መጠራታቸው ይታወሳል።

Ethiopian Hagere ከሳውዲ አረቢያ «፡ጅዳ በዋዲ»

Thursday, September 26, 2013

ፕሬዝዳንት ነጋሶ መሪ ሆኑ – ከአበበ ገላው (ጋዜጠኛ)



ጋዜጠኛና አክቲቪስት አበበ ገላው ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ትናንት ለዘ-ሐበሻ ከሰጡት አጭር ቃለ ምልልስ በኋላ በፌስ ቡክ ገጹ ያሰፈራት አጭር ግን ብዙ የምትናገር መልዕክት፦
መሪ ማለት ሌሎችን አጋፍጦ ዘወር የሚል ሳይሆን ከፊት ቀድሞ የመጣውን ሁሉ የሚጋፈጥ ማለት ነው። በትናትናው እለት የአንድነት አባላት በሰላማዊ መንገድ ስራቸውን በመስራታቸው ሲታሰሩ አብሬ እታሰራለሁ በማለት መደ ቤት ሳይሆን ወደ እስር ቤት ገብተዋል። በዚህም የታሰሩትን አስፈትተው መሪ መሆናቸውን አስመስክረዋል። ከዚህ በሁዋላ መታሰር የሚገባን እኛ እንጂ አባላቶቻችን አይደሉም ማለታቸው ቁርጠኝነታቸውን ያሳያል። ነጋሶ ወያኔን በቃኝ ብለው ህዝቡን በመቀላቀል ክብራቸውን አስመልሰዋል።
በሌላ በኩል አንድነቶችና ሰማያዊዎች ከምርጫ ፱፯ በሁዋላ የነጻነት ጥሪ እንዲያስተጋባ ማድረጋቸው ታላቅ እመርታ ነው። ፍርሃት ሲሸነፍ የአንባገነኖች የምጽአት ቀን ይቃረባል። ሁለቱ ፓርቲዎች እየተደጋገፉ መታገል ይጠበቅባቸዋል። የአንድነቶች ቅስቀሳ ምርጥ ነው።

በሪያድ አለም አቀፈ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ት/ቤት የወላጆች ኮሚቴ ዛሬ አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ መለዕክት አስተላለፈ !


በሪያድ አለም አቀፈ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ት/ቤት የወላጆች ኮሚቴ ዛሬ አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ መለዕክት አስተላለፈ !

በሪያድ አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ት/ቤት ተማሪዎች የወላጅ ኮሚቴ እና በሪያድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች መሃከል የተፈጠረው እሰጣገባ ከ ሴፕቴምበር 22 2013 በሃላ አደገኛ ሁኔታ ላይ መድረሱን ተከትሎ ኮሚቲው አስቸኳይ ጠቅላላ የወላጆች ስብሰባ ለመጥራት መገደዱን ገልጾል። በተለይ ሴፕቴምበር 24 2013 ዲፕሎማቱ 11 አባልት ያለውን አንጋፍ የወላጅ ኮሚቴ አስጠርተው ለማስፈራራት ያደረጉት ሙከራ ህጋዊ መስረት የሌለው እና አንድ ሉአላዊ መንግስትን እወክላለሁ ኪሚል አካል የሚጠበቅ ባለመሆኑ ዲፕሎማቱ መንግስታችን ከሚያራምደው ልማታዊ አስተሳሰብ እና አቋም አፈንግጠው በመሄድ እያካሄዱብን ላለው ማስፈራሪያ እና ዛቻ ሳንበገር የልጆቻችን መማሪያ የሆነውን ት/ቤት ከዘራፊዎች ለማስጣል ትግላችንን ህጋዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል። በዚህም መስረት ዛሬ ቀን ሃሙስ ሴፕቴምበር 26 2013 በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 02 30 ጀምሮ ልዩ ስሙ በተለምዶ አዚዚያ እየተባለ በሚጠራ አካባቢ በሚገኝ የመዝናኛ አዳራሽ፡ውስጥ ስብሰባው እንደሚካሄድ ተገልጾል ።
በመጨረሻ ዘግይቶ የደረሰ ዜና 

ይህን ተከትሎ ዲፕሎማቱ በወላጆች የተነሳባቸውን ተቃውሞ ለምታት ህዝቡን በብሄር መከፋፈል ያመቻቸው ዘንድ ዲፕሎማቱ በስራቸው የሚገኙትን የልማት ማህበራት ስራ አመራር አባላት እና አንዳንድ የሃገር ሽማግሌዎች ዛሬ ማታ በኢትዮጵያ ኮምኒቲ አዳራሽ ስብሰባ መጥራታቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል። 

ሙሉ ዘገባውን ዛሬ ከስብሰባው በሃላ ይጠብቁ 


Ethiopian Hagere ሳውዲ አረቢያ «ጅዳ በዋዲ

Wednesday, September 25, 2013

“ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ሆኖ የገደለው ሰው የለም’ – ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ምላሽ ሰጠ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በፓርላማ ማህበረ ቅዱሳንን “አክራሪ” ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ የአቶ ኃይለማርያም መንግስት በተለይ የጸረ ጽንፈኝነትን እና አክራሪነትን ለማጥፋት እታገላለሁ እያለ ባለበት ወቅት ማህበረ ቅዱሳንን ደግሞ አክራሪ ሲል መግለጹ ከፍተኛ ቁጣን መቀስቀሱ ይታወሳል። በአዲስ አበባ እየታተመች የምትወጣው እንቁ መጽሔት ሰሞኑን ዲ/ን ዳንኤል ክብረትን አነጋግራ ወጥታለች – በዚህ ጉዳይ። ዘ-ሐበሻ ይህን ቃለ ምልልስ እንደወረደ ለአንባቢ ግንዛቤ ሊሰጥ ይችላል በሚል መንፈስ አስተናገዳዋለች።
ዕንቁ፡- ጽንፈኝነት ምንድን ነው? አክራሪነትስ?

ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፡- አንድን ነገር ወደ ጥግ ወይም ወደ መጨረሻው ጠርዝ ላይ መውሰድ ጽንፈኝነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ፣ አክራሪነት ይሁን ጽንፈኝነት በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብዙም ልዩነት ያላቸው ጉዳዮች አይደሉም ፡፡ ልዩነታቸው በአፈጻጸም ላይ ነው ፡፡ ጽንፈኞቹ ‹‹ይሄ እና ይሄ ብቻ!›› የማለት ጠባይ አላቸው፡፡ አክሪዎቹ ደግሞ ‹‹ይሄ እና ያ….. ካልሆነ እንዲህ እናደርጋለን›› ወደሚልና ወደ ተግባሩ ርምጃ የሚያዘሙት ናቸው፡፡ ጽንፈኝነት በየትኛውም ጠባይ ሊኖር ይችላል፡፡ በማንኛውም ጉዳይ በቅርብ ስትመጣ ለዘብተኝነት ፣ ወደ መሀል ሲሆን ወግ አጥባቂነት ፣ ወደ ዳር ሲኬድ ጽንፈኝነት ይኖራል፡፡ በባሕልም ቢኾን ለዘብተኛ ሰው አለ ፤ ማንኛውም ባህል ምንም የማይመስለው፡፡ ባህሉን የሚያጠብቅም አለ ፤ ‹‹ባሕሌን እወደዋለኹ፤ አከብረዋለኹ፤ ለምን ትነካብኛለህ? ለምንስ ትበርዘዋለህ? እንዲሁ ሳይበረዝና ሳይከለስ እንዲሁ እንዲኖርልኝ እፈልጋለኹ. . .›› ብሎ የሚያስብ ሰው አለ፡፡ ወደ ዳር ያለው ደግሞ ‹‹ከዚህ ውጭ ያለውን ፈጽሞ ማየትም ኾነ መስማት አልፈልግም!. . .›› ባይ ነው፡፡ የሌላውን ህልውና የሚክድ ነው፡፡ ይህ ለእኔ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ከባዱ ነገር አክራሪነት ነው፡፡ ወደ አክራሪነት ስትመጣ ‹‹ይሄኛውን ካልተቀበለ…›› ከሚል ይነሣና ርምጃ እስከ መውሰድ ጥግ ድረስ የሚሄድ ይሆናል፡፡
ዕንቁ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ አክራሪነት አለ?
ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ፡- በአገራችን ‹‹አክራሪነት የለም›› ብለን መደምደም አንችልም፡፡ በተወሰነ ደረጃ አለ፡፡ የሚለያየው በምን ያህል ደረጃና የት ነው ያለው? የሚለው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የመኖሩን ምልክት ሰዎች ከእምነታቸው የተነሣ ሲገደሉ፣ የእምነት ቦታዎች ሲቃጠሉ ፣ የእምነት አባቶች መቃብራትና የተለያዩ ነገሮች እንዲፈርሱ ሲደረጉ አይተናል፡፡ ጽንፈኝነትን ብቻ ሳይሆን ወደ ኃይል ርምጃው የመሄዱን ነገር አይተናል፡፡የዛሬ ሰባት ዓመት ከተመለከትነው የጅማው ድርጊት ብንነሣ እንኳ አክራሪነት መኖሩን እንረዳለን፡፡ እነዚያ የጅማ ክርስቲያኖች የተገደሉት ምንም መጥፎ ነገር አድርገው አልነበረም፡፡ ‹‹ብዙዎች ሆነው ነውጥ ፈጥረው ነው›› እንዳይባል በቁጥራቸው ትንሽ ናቸው፡፡ የነበሩትም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በገባበት ከኻያ ዓመት በፊት በነበሩት ሰሞናት በአሰቦት ገዳም እነ ጃራ አል ኢስላሚያ የፈጸሙትም በምሳሌነት ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ እነዚያ መነኮሳት ተራራ ላይ በነበረ አንድ ገዳም ይኖሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ሌላ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ የተገደሉት መነኩሴ ወይም ክርስቲያን በመኾናቸው ብቻ ነው፡፡ ይህ ሲታይ የአክራሪነት ጠባዕያት በአገራችን የለም ለማለት ያስቸግራል፡፡
ዕንቁ፡- ከመቼ ወዲህ ነው ይህ ዝንባሌ በኢትዮጵያ መስተዋል የጀመረው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ይህ የመገዳደል ሁኔታ ማለትም አንድ ሰው ክርስቲያን በመኾኑ የመግደል፣ ሙስሊም በመኾኑ የመግደል ወይም የሙስሊምን መስጊድ፣ የክርስቲያኑን ቤተ መቅደስ በማቃጠል የሚገለጸው ድርጊት በቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ከ1980ዎቹ በኋላ መታየት የጀመረ ነው ፤ የተመዘገቡት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፣ ከ1980 ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡ ይህም ከአካባቢያዊ ሁኔታዎችና በመላው ዓለም ከተስተዋለው የተከተለና ችግርን የመፍቻ አንድ አማራጭ አድርጎ ከመመልከት የመነጨ ነው፡፡
ዕንቁ፡- በአገር ውስጥ እንዲህ ዐይነት ነገሮች እንዳይከሠቱ ያልተሠሩ ሥራዎች አሉ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አንድ ከመንግሥት ፣ ሁለት ከሃይማኖት ተቋማት ፣ ሦስት ከሌሎች አካላት በኩል ያልተሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ‹‹ሃይማኖት እና መንግሥት የተለያዩ ናቸው›› ብሏል ፡፡ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ፖሊስ እንኳ የለም፡፡ ይሄ ባለመኖሩ መንግሥት ሃይማኖቶችን እንዴት ነው የሚያያቸው? ለሚለው መልስ ለማግኘት አስቸጋሪ ይኾናል፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል ያለው ለሌላው ያደላል፣ በሌላ በኩል ያለውም ለሌላው ያደላል እያለ እንዲያማርር ኹኔታው በር ከፍቷል፡፡ አሠራሮች ላይ የሚፈጠሩ ነገሮች አሉ፤ በምዝገባውና በሌላውም፡፡ አንዳንዶቹ የተጨቋኝነት፣ ሌሎቹ የጨቋኝነት፣ ደግሞ አንዳንዶቹ የተገላጋይነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ናቸው፡፡የሃይማኖት አስተሳሰቦች የሚመሩትን ብዙኃኑን ሕዝብ እንዴት ነው? በምን መልኩ ነው? እምነቱን ከአገሪቱ ዕድገት፣ ከአገሪቱ የፖሊቲካ አስተሳሰብ ጋራ በማይጣላበት ሁኔታ ጋር ማስኬድ የሚቻለው….. በሚለው ላይ በደንብ የተጠና ፖሊስ በአገሪቱ አልነበረም፡፡ የተሠራ ሥራ አልነበረም፡፡ አሁንም አለ ለማለት ይከብደኛል፡፡ ዛሬ በሃይማኖት ጉዳዮች አንድ የሃይማኖት ‹‹ዳይሬክቶሬት›› ነው ያለው፡፡ ግን አገሪቱ ውስጥ ትልልቅ ቦታ የሌላቸው፣ ታላላቅ ጉዳዮችን የማይወስኑ…. በትልቅ ፖሊሲ፣ በትልቅ ሚኒስቴር ደረጃ ይታያሉ፡፡ ይህ ለቦታው የተሰጠውን ግምት ያንጸባርቃል፡፡ ብዙውን ውኃ በትንሽ ኮዳ ለመያዝ የመሞከር አሠራር ነው የሚስተዋለው፡፡ ስለዚህ በእምነቱ ጉዳይ ከኮዳው አቅም በላይ ሲኾን የሚፈጠሩ ዐይነት ችግሮች እየተመለከትን ነው፡፡
ዕንቁ፡- አክራሪነትን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አኳያ እንዴት ታየዋለኽ?
ዲ/ን ዳንኤል ፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አክራሪነት ቦታ የለውም፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት፣ ከቀኖናው ስንነሣ ይህች ቤተ ክርስቲያን ለሌሎች ዕውቅና የመንፈግ ችግር አልነበረባትም፡፡ ዕውቅና ስትሰጥ ነው የኖረችው፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ አገሪቱ ሲመጡ፣ በወቅቱ የነበሩት ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናን ባይቀበሉት ኖሮ ንጉሡ ብቻውን ምንም ሊያደርግ ባልቻለ ነበር፡፡ የዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ የነገሥታቱ ሥልጣን፣ ከእምነት አባቶች ተቀባይነት ማግኘት የሚመነጭ በመኾኑ ነው፡፡ ያ ሳይኾን ሲቀር በአገሪቱ የተፈጠሩትን ችግሮች ቀረብ ካሉት ጊዜያት በእነ ዐፄ ቴዎድሮስ፣ በእነ ዐፄ ሱስንዮስ ከኾኑት ድርጊቶች ማየት እንችላለን፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ግጭቶች ይፈጠሩ የነበሩት፣ ሌሎች ለእርሷ ዕውቅና መስጠት ሲያቅታቸው ነው፡፡
ለምሳሌ ባለፉት ሁለት ሺሕ ዘመናት ስትቀድስ፣ ስታስተምር የኖረችበትና በ6ኛው መ/ክ/ዘ በእጅ የተጻፈው ወንጌል የተገኘው በዐድዋ እንዳባ ገሪማ ገዳም ነው፡፡ ከእርሱ የቀደመ እስከ አሁን ሊገኝ አልቻለም፡፡ እንደዚህ ያለ የክርስትና ታሪክ የተገኘባትንና አስቀድማ ወንጌል ስታስተምር የነበረችን ቤተ ክርስቲያን ‹‹ወንጌል ስታስተምሪ አልነበረም›› የሚልና ለሥራዋ፣ ለአገልግሎቷ ዕውቅና የመንፈግ ችግር አለ፡፡ ይህን ኃይል በመጠቀም፣ ድንበሯን በመሻገር፣ እርሷው ቤት ድረስ ገብተው ካህናቷ ካሉበት፣ ቅኔ ማሕሌቷና መቅደሷ ውስጥ የመዝለቅ ፍላጎት ያላቸው ሲመጡ ችግር ነው የሚኾነው፡፡
በ17ኛው መ/ክ/ዘ በዐፄ ሱስንዮስ ጊዜ በካቶሊኮችና በኦርቶዶክሶች መሐል የተከሠተው ግጭት መንሥኤው አስቀድሜ የገለጸኹት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሮማ አልሄደችም፡፡ ሮም ናት እዚህ የመጣችው፡፡ እዚህ መምጣቷ ብቻ አልነበረም ችግሩ፣ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ከበሮው፣ ታቦቱም፣ የካህናቱ አልባሳትም ይውጣ! የዘመን አቆጣጠሩም እንደ ጎርጎሮሳውያን ይሁን! በዓላቱም ይቀየሩ! የዓመቱ መጀመሪያ መስከረም መኾኑ ቀርቶ ታኅሣስ ይሁን!›› በሚል በቀጥታ በቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ውስጥ ገቡ፡፡ ይህን የመሰለው ግፊትና ዕውቅና የመንፈግ ኹኔታ ሲመጣ ወደ ጦርነት ደረጃ ታለፈ፡፡
በስተኋላ የዐፄ ሱስንዮስ ዘመን አልፎ የዐፄ ፋሲል ዘመን ሲመጣና ችግሩ ቆሞ ኢትዮጵያውያን አባቶች፣ እነዚህ ሰዎች ምን ይደረጉ ሲባሉ ‹‹ጉባኤ ይጠራና እንከራከር›› ነው ያሉት፡፡ ጉዳዩን ከጉልበት ወደ ዕውቀት አቅጣጫ ነው የወሰዱት፡፡ ‹‹የሐሳብ ክርክር እናድርግ፤ በጉባኤው የረታ ይሂድ›› አሉ እንጂ ሌላ ነገር አላሉም፡፡ ይህም የሊቃውንቱን ጠባይ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ አክራሪነትን ሊያበቅል የሚችል መሬት አይገኝም፡፡
ዕንቁ፡- በቅርቡ የመንግሥት ወኪሎችና ሌሎች የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት አገር ዓቀፍ የሆነ ጉባኤ፣ አባ ዮናስ የተባሉ ሰው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተለይ በማኅበረ ቅዱሳን በኩል ‹‹የአክራሪነት ችግር አለ›› የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በርግጠኝነት በቤተ ክርስቲያኒቱ የአክራሪነት ችግር ስለመኖሩ ለማሳወቅ የደፈሩ የፖሊቲካ ሰዎችም ነበሩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የአንተ አስተያየት ምንድን ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- በቅድሚያ አሁን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሦስት ከፍለን ማየት አለብን፡፡ አንደኛ የሌሎች መሣርያ በመኾን መሣርያ ያደረጓቸውን ወገኖች ጉዳይ የሚያስፈጽሙ አሉ፡፡ እነዚህ ሰይጣን ወደ ገነት መግባት በቻለበት ሁኔታና መንገድ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ እንደሚታወቀው ሰይጣን ራሱ ወደ ገነት አልገባም፡፡ ወኪል ነበረው፡፡ ወኪሉም እባብ ነበር፡፡ በእባብ ውስጥ አድሮ ነው ወደ ገነት የዘለቀው፡፡ ምክንያቱም የሰይጣን ባሕርይም ጠባይዕም ስለማይፈቅደለት ራሱ ወደ ገነት አይገባምና ነው፡፡ በአባቶቻችን መጽሐፍ እንደሚነገረው፣ እባብ ተንኮለኛ፣ ውብና ትክለ መልካም ነበረች፡፡ ስለዚህ ሰይጣን ክፉ ሐሳቡንና ሤራውን በተዋበውና በማራኪው የእባብ ውበትና ተክለ ሰውነት ሸፍኖ ወደ ገነት ገባ፡፡ ሔዋንም ልትሳሳት የቻለችው የምትነጋገረው ከእባብ ጋራ ስለመሰላት ነው፡፡ ከእባብ ጀርባ ያለውንና የእባብን ሐሳብ የቀየረውን ነገር መመልከት አልቻለችም፡፡ልክ እንደዚሁ ሁሉ ገነት በኾነችው ቤተ ክርስቲያን የሌላውን ሐሳብ ይዘው የመጡ ወገኖች ገብተዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በምንኩስና፣ በቅስና፣ በዲቁና፣ በመምህርነት፣ በዘማዊነት አለባበስ ውስጥ ሁሉ የሚገኙ ናቸው፡፡ ግን ሐሳባቸው የእነርሱ አይደለም፡፡
ሁለተኛ፡- ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዘመናት ስትቃወመው የነበረችውን የለዘብተኛ ማለት የሊበራል ክርስትና አስተሳሰብ ተጭነው በመምጣት ያን የሚያራምዱ ሰዎችም አሉ፡፡ ከእኒህ ጋራ ሊታዩ የሚችሉ ግን ደግሞ ለምንም ነገር ግድ የሌላቸው ሰዎችም አሉ፡፡ በአርባና በሰማኒያ ቀናቸው ከመጠመቃቸው በቀር ለምንም ሆነ ለምን ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ግድ የሌላቸው መኖራቸው አይካድም፡፡
ሦስተኞቹ ደግሞ ፣ ‹‹የለም፣ ይህች ቤተ ክርስቲያን የራሷ የኾነ በጣም ብዙ ጠንካራ ነገሮች አሏት፡፡ በዶግማ፣ በቀኖና፣ በትውፊት፣ በቅርስ፣ በባህል ሀብታም ነች፡፡ በዓለም ላይ የጠፉ ቅርሶችን ጠብቃና ተከባክባ የቆየች ናት፡፡ የዓለም የባህል ሙዝየም ናት. . .›› ብለው የሚያምኑ፣ የሚሟገቱላትም ናቸው፡፡
ለምሳሌ፡- ሰንበቴ ይህች ቤተ ክርስቲያን ይዛው የቆየችው የዓለም ባህል ነው፡፡ የዓለም ክርስትና ሲጀመር ሰንበቴ ነበር፡፡ ሲጠፋ ግን ጠፋ፡፡ እርሷ ዘንድ ግን አለ፡፡ ጽዋ በሌላም ቦታ ነበር፤ ግን ጠፋ፡፡ ዛሬ የአውሮፓን ካታኮምብ (ጥንታዊ ከርሰ መቃብሮች) ቁፋሮ ሲካሄድ የሚገኙ ሥዕሎች ሰንበቴ ተሰብስበው ሲበሉ፣ ጽዋ ሲጠጡ የሚታዩባቸው ናቸው፡፡ እነርሱ አሁን የድሮ ክርስቲያኖች እንዲህ ነው የሚበሉት፣ የሚጠጡት ይሉኻል እንጂ ዛሬ ህልውናው የለም፡፡ እኛ ጋራ ግን ከነሕይወቱ ተጠብቆ ታገኘዋለህ፡፡ ሌላ ምሳሌ እንውሰድ፤ መስቀል እኛ ጋራ አልነበረም የተጀመረው፡፡ ሌሎች ጋራ የነበረ ነው፡፡ ግን እኛ ጋራ ነው ሕያው ኾኖ የሚገኘው፡፡ በሌሎች ቦታዎች ታስቦ ነው የሚውለው፡፡ ጥምቀትም ታስቦ ነው የሚውለው፡፡ የግብጽን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስታይ፣ እስከ ስምንትና ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ጥምቀትም መስቀልም በአደባባይ ይከበር ነበር፡፡ ዛሬ ግን አልኾነም፡፡ ይኸው እኛ ጋራ ግን በህልውናው አለ፡፡ ስለዚህ ነው ይህች ቤተ ክርስቲያን የራሷ ብቻ ሳትኾን የዓለም ባለ አደራ ናት የምንለው፡፡ ከዓለም ከኦሪት ታቦታቱን፣ ከሐዲስ መስቀሉን ጠብቃ በአደራ አስቀምጣ የቆየች አደራ የማትበላ ናት፡፡
‹‹ይህች ቤተ ክርስቲያን አደራዋን እንደጠበቀች፣ ሃይማኖትን እንደ አባቶቻችን፣ አሠራሩን እንደ ዘመናችን አድርጋ መሄድ አለባት›› የሚሉ ወገኖችም ያሏት በመሆኑ ፣ በእነዚህ ወገኖችና የሌላውን ሐሳብ ተጭነው በሚመጡ ሰዎች መሐል ትግል አለ፡፡ ክርክር አለ፡፡ ሰውዬውን በአካል ባላውቃቸውም ሲናገሩ ባላዳምጥም አሉ የተባለውን ሰምቻለሁ ፡፡ ምናልባት ስማቸው የተነሣው አባት የተባለውን ሐሳብ ይዘው መጥተው ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለኹ፡፡
የሆነው ሆኖ፣ የሌላውን ሐሳብ ይዘው የሚመጡ ሰዎች ትልቁ ችግራቸው ምንድን ነው? ዘመኑን ከመዋጀት ይልቅ (መጽሐፉ ‹‹ዘመኑን ዋጁ›› ይላልና) ዘመኑን የመጠቀም ስልት መከተላቸው ነው፡፡ የኮሚዩኒስት ሐሳብ ሲራመድ ካዩ፣ ራሳቸውን ኮሚዩኒስት ሌላውን ካፒታሊስት ያደርጋሉ፡፡ የካፒታሊስት ሐሳብ በዘመኑ ሲራመድ ሲያዩ ደግሞ ራሳቸውን ካፒታሊስት ሌላውን ኮሚዩኒስትነት ፈርጀው ማስመታት ይፈልጋሉ፡፡ ይህን መሰል ተግባርም በየዘመኑ ይፈጽማሉ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተ ወደ ሃያ ዓመት በላይ ኾኖታል፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ይሰጡት የነበረውን ስሞች ብንመለከት የሚያስገርምና የሚያስደንቅ ነው፡፡ መአሕድ በአገሪቱ ትልቅ መነጋገርያ በኾነበት ጊዜ ‹‹መአሕድ ነው›› ተባለ፡፡ አገሪቱ ቅንጅት፣ ቅንጅት በምትሸትበት ጊዜ ደግሞ ‹‹ቅንጅት›› ተባለ፡፡
ዕንቁ፡- ለምንድን ነው እንደዚህ የሚባለው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ምክንያቱ አስቀድሜ ባቀረብኹት ምሳሌ መሠረት በዘመኑ የመጠቀም ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጠባይና ባሕርይ የሚመጣ ነው፡፡ አንተ በሐሳብ ስትሸነፍ ማስመታት መቻል አለብኽ፡፡ በእኛ አገር የተለመደ ሦስት ዐይነት አሠራር አለ፡፡ አንድን ነገር መጀመሪያ ታውቀዋለህ ፡፡ ቀጥለህ ስም ትሰጠዋለኽ፡፡ ሠልሰህ ትመታዋለህ፡፡ ስም ካላወጣህለት አይመታልህም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለምን ነበር ‹‹መአሕድ›› ይባል የነበረው? የሚያደርገው እንቅስቃሴ በመታወቁ ነው፡፡ እንደዚህ የሚወነጅሉትም ሰዎች እኮ ያውቁታል፡፡ ግን ለመምታት የሚያስችላቸውን ስም ማውጣት አለባቸው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ግን እስከ አሁን ድረስ አክራሪ ሆኖ ያመጣው ነውጥ፣ ያስነሳው ነገር፣ የደበደበው፣ የገደለው ሰው፣ ያቃጠለው ቤተ እምነት የለም፡፡
ዕንቁ፡- ሰው ሕይወቱን፣ እምነቱን፣ ትምህርቱን፣ የዕውቀትና የኑሮ ምርጫውን በተመለከተ የራሱ ሐሳብና ከሐሳቡም የሚመነጭ ውሳኔ አለው፡፡ የሌላውን መብት እስካልተፃረረ ድረስ በራሱ ለራሱ የመመራት መብት ባለቤት ነው፡፡ ‹‹ለምንድን ነው እኛ ወዳደራጀነው ተቋም፣ ማእከል የማትመጣው›› የሚሉ ‹‹አልመጣም›› ሲል በአክራሪነት ወይም በሌላ የሚፈርጁ ሰዎችና ቡድኖች ደግሞ አሉ፡፡ ይህን ኹኔታ በጠራና የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠር ደረጃ ለኅብረተሰቡ ማስተማር የሚቻልበት መንገድ አለ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አስቀድሜ ለማንሣት እንደፈልግኹት፣ ለዘብተኛው አካል መሥዋዕትነት ለመክፈል ወይም ደግሞ አንዳች ሱታፌ ለማድረግ ፍላጎት የለውም፡፡ ያኛው ደግሞ የሌላው ወኪል ነው፡፡ ምክንያቱም ይህች ቤተ ክርስቲያን እኮ በሦስት ደረጃ ማለትም ወይ ለማፍረስ! ወይ ለመጠምዘዝ (ከምትሄድበት አቅጣጫ ወደ ሌላ መሥመር ለመውሰድ) ይህ ካልኾነ ደግሞ ለማደንበሽ ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡ ማደንበሽ ማለት ምንም እንቅስቃሴ እንዳታደርግ፣ ዝም ብላ እንድትኖር ማድረግ ማለት ነው፡፡ ለአንድ ሰው ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ ተሰጥቶት ግን በአእምሮው ምንም ዕውቀት እንዳይኖረው የማድረግ አይነት ነው፡፡ እንደዚህ አይነቱ ሰው አንድ ሰፈር ውስጥ ቁጭ ብሎ የፈለገውን ፊልም፣ የፈለገውን ሙዚቃ እያየና እያደመጠ፣ በዚህ ብቻ እየተደሰተና እየጨፈረ እንዲኖር ቢደረግ ይህ ኑሮ አይደለም፡፡ ያ ሰው ምንም የሚያስበው፣ የሚሠራው፣ የሚፈጥረው ነገር የለውም፡፡ በቃ ሰፈሩ ብቻ መኖርያው ነው፡፡ የምግብ፣ የልብስ ችግር የለበትም፡፡ እንግዲህ ይሄ ነው መደንበሽ የሚባለው፡፡
በእኒህ በሦስቱ የማጥፊያ ስልቶች ይህች ቤተ ክርስቲያን ተሞክራለች፡፡ ግን የእግዚአብሔር ኃይል፣ የቅዱሳን ጸሎት በውስጧ ስላለ የተመኙላትን ልትኾን አልቻለችም፡፡ በርግጥ የተወሰኑ ሰዎችን መማረክ ይቻል ይኾናል፤ ግን ይህች ቤተ ክርስቲያን ከማናችንም ኃይል በላይ ናት፡፡ ያልታወቀና ማንም የማይደርስበት ኃይል ያላት ነች፡፡ ባትሆን ትጠፋ ነበር፡፡ ግራኝ አንድ ዐሥረኛ ምእመኗ እስኪቀር ጭፍጨፋ አካሂዶባታል፡፡ ብዙዎቹን መቅደሶቿን አቃጥሎባታል፤ ግን አልጠፋችም! ፋሽስት ኢጣልያ ብዙ ነገር አድርጓል፡፡ የፋሽስት ኢጣልያ ወራሪ ጦር እንደገባ ወደ አራዳ ቅ/ጊዮርጊስ በመሄድ የቤተ ክርስቲያኑን ቅጽር በወታደሮች ነው ያስከበበው፡፡ ቀጥሎም የቅ/ጊዮርጊስ ታቦት ‹‹ወታደራዊ ፍርድ ቤት›› በሚለው ችሎት እንዲቀርብ በማድረግና ‹‹ሞት ሊፈረድበት ይገባል!›› የሚል ውሳኔ በማስወሰን ዙሪያውን ተኩስ እንዲከፈትበት አድርጓል፡፡ የተኩሱ አሻራ አሁንም ድረስ በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ውስጥ አለ፡፡ ግን ይህ ለምን ተደረገ?….. የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ ታቦቱ አገር በመጠበቁ ካልኾነ ምን ወንጀል ነበረበት? ከአራዳ ጊዮርጊስ አልፈው ደብረ ሊባኖስ በመሄድ መነኮሳቱን የገደሉት ለምንድን ነው? ቅርሷንስ ጭነው የሄዱት? ያኔ ብዙ መነኮሳት ተገድለዋል፡፡ ከሞቱት መሐል እነ አቡነ ጴጥሮስ የዚህች ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ራስ ናቸው፡፡ ግን የሚጠብቃት ኃይል ስላለ ምንም ሊያደርጓት አልተቻላቸውም፡፡
ዕንቁ፡- ይህ ‹‹አክራሪ›› የሚባለው ስያሜ የመነጨው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማፍረስ፣ ለመጠምዘዝ ወይም ለማደንበሽ ከሚፈለገው መንፈስ ነው ማለት ይቻላል?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ታድያስ! እርሱ እኮ ነው ‹‹ይህችን ቤተ ክርስቲያን እንጠብቅ›› የሚሉትን የሚፃረረው፡፡
ዕንቁ፡- ‹‹መንፈሱ መኖር አለበት›› በሚሉና ‹‹መንፈሱ መኖር የለበትም›› በሚሉ መካከል ነው ትግሉ ያለው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ነው!. . .ትግሉ እርሱ ነው፡፡ ‹‹ይህች ቤተ ክርስቲያን ተጠብቃ፣ ሥርዐቷን ይዛ ወደሚቀጥለው ትውልድና ዘመን መሻገር አለባት›› የሚሉትን አካላት ነው አሁን ‹‹አክራሪ›› ማለትና ዝም ማሰኘት የሚፈለገው፡፡ እነዚህን ሰዎች ዝም ማሰኘት ግን አይቻልም፡፡ ሃይማኖት የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
ዕንቁ፡- ዝም ማሰኘት ካልተቻለ ግቡ ምን ሊኾን ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እርሱን በሂደት የምናየው ነው፡፡ የዚህችን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ማንም በዕቅድ፣ በስትራተጂ፣ በምን ሊተምነው አይችልም፡፡ ታሪኳ የእግዚአብሔር ሥራ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹እገሌ ነው እርሷን የሚመራት›› ሊባል አይችልም፡፡ አስተዳደራዊ አመራር ይኖራታል እንጂ መንፈሳዊ አመራሯን ከፈጣሪ የምታገኝ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ስለዚህ እኛ የተባሉት ሰው…. ይህን ዓላማ ይዘው መጥተው ተናግረውት ካልኾነ በቀር ማኅበረ ቅዱሳንን አክራሪ ለማሰኘት የሚያበቃ ምንም፣ አንድም መከራከሪያ ሊያመጡ አይችሉም፡፡ ለነገሩ እርሳቸውም ቢሆኑ ማስጠንቀቂያ ሰጡ እንጂ ይሄ፣ ይሄ፣ ይሄ ብለው በዝርዝር ያመጡት ምንም ነገር የለም፡፡ ከሳቸውም በፊት የነበሩት ሌሎች ሰዎች እንደ እርሳቸው ብለዋል፡፡ ማናቸውም ግን ማስረጃ ብለው የሚያቀርቡት ነገር የላቸውም፡፡
በበኩሌ አራት፣ አምስት ነገሮች ሲነገሩ እሰማለኹ፡፡ ‹‹አንዲት አገር አንዲት ጥምቀት››፤ ‹‹አንድ አገር አንድ ሃይማኖት›› ብለዋል የሚል፡፡ ይህን ከብዙኀን መገናኛ እሰማዋለኹ እንጂ ከየትኛውም የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ላይ ተጠቅሶ አይቼ አላውቅም፡፡እንዴ ‹‹አንድ አገር አንድ ሃይማኖት›› የሚለው እኮ ከራሷ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ጋራ የሚጋጭ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 1 ቁጥር 8 ላይ የሚለው ‹‹በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ እስከ ዓለም ዳርቻ አስተምሩ›› ነው፡፡ አንድ አገር ውስጥ ተቀመጡ አላለም፡፡ የሚባለውን የማንቀበለው ከእኛ አስተምህሮ ጋራ ስለሚጋጭ ነው፡፡ ቢቻል ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማልያ፣ ታንዛንያ፣ ጋና፣ ጃማይካ ሄደን አስተምረን ክርስቲያን ማድረግ ነው የሚጠበቅብን፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ የኾኑ አሜሪካውያን፣ ጃማይካውያን፣ እንግሊዛውያን፣ ጀርመናውያን አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ እንዴት ወደ አንድ አገር መጥቅለል ይቻላል? ሊሆን አይችልም፡፡ ፈጽሞ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ጋራ የማይሄድ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በዜግነት ኢትዮጵያውያን ያልኾኑ የእምነት አባቶች ያሏት ነች፡፡ የመጀመሪያው ጳጳስ አቡነ ሰላማ ግሪካዊ ነው፡፡ ዘጠኙ ቅዱሳን የሶርያ፣ የግሪክ፣ የሮም ሰዎች ናቸው፡፡ ወደዚህ ቀረብ ስንል አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ግብጻዊ ናቸው፡፡ የደብረ ሊባኖሱ 11ኛው ዕጨጌ አቡነ ዕንባቆም የመናዊ ነው፡፡ እንዴት ተደርጎ በአንድ አገርና በአንድ ሕዝብ መወሰንና ማስተማር የሚቻለው፡፡ በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እኮ ዕድሉ የለም፡፡
ዕንቁ፡- ጽንፈኝነትን ይኹን አክራሪነትን የሚያበረታታ ታሪካዊ መሠረት በአገራችን ታሪክ አለ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ከዚህ ጥያቄ አንጻር ሦስት ነገሮችን ማየት ያለብን ይመስለኛል፡፡ አንደኛ፡- የእምነቶቹ ግንኙነት በመተዋወቅና በመግባባት እንዲኾን የተሠራ ሥራ የለም፡፡ ይሄ ባለመሠራቱ አንዳንድ ወገኖች ሁልጊዜ የተጨቋኝነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ግን እነዚህን በቀላሉ ማጥፋት የሚቻልበት መንገድ፣ እርስ በርስ የሥነ ምግባር መመሪያ እንዲኖራቸው የማድረጉ ዕድል አለ፡፡
ለምሳሌ አንዱ ስለሌላው ሲናገር መሆን ስለሚኖርበት ኹኔታ ተቀራርቦ በመወያየት አንድ የሚያግባባ ነጥብ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ በመሠረቱ ስለሌላው እምነት ማስተማር ተፈጥሯዊ ነው፡፡ አንተ ‹‹እኔ ትክክል ነኝ›› ስትል ሌላው ‹‹ስሕተት ነው›› ማለት በፍጹም ችግር ያለበት ጉዳይ አይደለም፡፡ አንድ ሙስሊም ‹‹እስልምና ትክክለኛ የመዳን ሃይማኖት ነው›› እስካለ ድረስ ‹‹ክርስትና ስሕተት ነው›› ብሎ ስሕተት ናቸው ብሎ ስለሚያምንባቸው ነገሮች ቢያስተምር ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ለምን ይህን አደረግኽ ልንለው አንችልም፡፡ አለበለዚያ ‹‹ክርስትናም እስልምናም ትክክል ነው›› ማለት መቻል አለበት፡፡ አንድ ክርስቲያንም ስለ እስልምና ‹‹ቁርዓን እዚህ ጋራ ተሳስቷል፤ ነቢዩ መሐመድ እዚህ ላይ ተሳስተዋል፤ አካሄዳቸው ስሕተት ነው›› ቢል ለእኔ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ግን እርሱ አይደለም ችግሩ፡፡ ይህን ስታስተምር ምን ዓይነት ሥነ ምግባራዊ መርሕ መከተል አለብህ፤ አንዱ ወደ አንዱ እንዲመጣ ሳይሆን አንዱ በሌላው ላይ የጥላቻ ስሜት እንዳያድርበት ማድረግ የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማትን የሚያይበት አሠራር መስተካከል አለበት ባይ ነኝ፡፡ በአንድ ሚኒስቴር ሥር የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው ያለው፡፡ ፖሊሲ የለውም፡፡ አሁን ተቋቋመ የተባለው ጉባኤ በራሱ ሲታይ ሕዝቡ በሚገባ የተረዳው አይነት አይደለም፡፡ የምንመሠርታቸው ተቋማት ለምን እንደ ሐበሻ መድኃኒት ድብቅ እንደሚኾኑ ይገርመኛል፡፡ ሲኾን እንደዚህ ዐይነቱ ተቋም መቋቋም የሚገባው በላይኛው አካል አልነበረም፡፡ ከታች ከአጥቢያ ጀምሮ አብያተ ክርስቲያንና መስጊዶች ባሉበት አካባቢ የሚገኙ ምእመናን ተሰብስበው ‹‹እንዴት ነው ሁሌ ከምንቧቀስ፣ ከምንጋጭ በጋራ በሚያገናኝን ጉዳይ ላይ የማንነጋገረው? የሚያስማማን ኹኔታ የማንፈጥረው?›› የሚለውን ጥያቄ በማንሣት መወያየት ይኖርባቸዋል፡፡ የምንለያይበት ነገር ቢኖርም የጋራችን በኾነው ጉዳይ መነጋገር፣ የተለያየንበትን በየራሳችን አስቀምጠን ጊዜ የሚፈጅ ቢኾንም የፈጀውን ያህል ጊዜ ፈጅቶ ይሄን፣ ይሄን፣ ይሄን እያልን ወደላይ መድረስ አለብን፡፡
ምንም ነገር ቢሆን ሊሰምር የሚችለው በእኛ በኢትዮጵያውያን ጠባይ ከታች ወደላይ ሲሆን ነው፡፡ እምነት ከታች ወደላይ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ያለጳጳስ ኖረው ያውቃሉ፡፡ ያለምእመናኑ ግን ጳጳሳቱ ኖረው አያውቁም፡፡ ስለዚህ ወሳኞቹ ምእመናን ናቸው፡፡ ያለ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ብዙ ሙስሊሞች ኖረዋል፡፡ የእስልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤት የተቋቋመው በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ብዙ ሙስሊሞች ነበሩ፡፡ ሙስሊሞች ባልነበሩበት ዘመን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ኖሮ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ወሳኞቹ ሙስሊሞቹ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የእምነቱ ነገር ከታች ወደላይ እንጂ ከላይ ወደታች ኾኖ አይኾንም፡፡ በቃ አይኾንም! የኢትዮጵያ እምነት ጠባዩ እርሱ አይደለም፡፡ ይህን ጠባይ እኛ እንሻገረው ብንል ብሎኑ ጭራሽ አይገጥምም፡፡ የሚመጣው ስድስት ቁጥር ብሎን ነው፤ ማስገባት የሚፈለገው ግን አራት ቁጥር ብሎን ነው፡፡ ና ግባ፤ ቢባል እሺ አይልም፡፡ ስለዚህ ምን ይደረጋል. . . ልኬቱ መመጠን አለበት፡፡ ቀዳዳውን ላስፋው ሲሉ ግን ግጭቱ ይፈጠራል፡፡
ዕንቁ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹የሃይማኖት መቻቻል›› አለ ትላለህ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እኔ ከመቻቻል ያለፈ መገንዘብ ነበረ እላለኹ፡፡ ‹‹መቻቻል›› የሚለውን አልቀበለውም፡፡ ለምን? አሁን ባልና ሚስትን ብዙ ጊዜ ስናስታርቅ ‹‹እኔኮ ችዬው ነው የኖርኩት›› ብለው ሲሉ ተስማምቶኝ ነው ማለታቸው አይደለም፡፡ ምን ይደረግ ብዬ፤ ልጅ ለማሳደግ ብዬ፤ ችዬው፣ ተሸክሜው እያሉ ነው የተበደሉት ሚስቶች፡፡ አንደኛው ተሸካሚ ኾኖ እህህ…ብሎ የመቻል ነው፡፡ ጭነት የበዛበት ነው፡፡ የማይፈለግ ነገር ያለበት ነው፡፡ ቻለው ተብለህ የምትኖረው ኑሮ ማለት ነው፡፡ መገንዘብ ማለት ግን አንዱ የሌላውን ችግር፣ ብርታት ተገንዝቦ በዚያ ውስጥ መኖር ማለት ነው፡፡
ዕንቁ፡- ይኼ የምትለው መገናዘብስ አለ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ሕዝብ ዘንድ አለ፡፡ አሁን አለና የለምን በቃላት ደረጃ ስናገረው ተግባራዊ መመዘኛው በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል የእስልምና እምነት፣ ምን ያህልስ የክርስትና እምነት ተከታዮች አሉ ብለን ስንጠይቅ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሁለት እምነት ተከታዮች ቁጥር ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብላጫው ነው፡፡ በአብዛኛው ማኅበረሰብ ዘንድ ይኸው መገናዘብ አለ፡፡ በርግጥ በጥቂቶች ዘንድ ላይኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድን ሙስሊም ‹‹እንኳን ለመውሊድ በዓል አደረሰኽ›› ስትለው ተገንዝበህዋል ማለት ነው፡፡ በዚያ በዓል ላይ ተስማምተህ ላይኾን ይችላል፡፡ እንደውም ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያ ብዙኀን መገናኛዎች ለሙስሊሞች ‹‹እንኳን ለዒድ አል አረፋ በዓል አደረሳችኹ››፤ ለክርስቲያኖች ‹‹እንኳን ለጥምቀት በዓል አደረሳችኹ›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ግን ለምንድን ነው እንዲህ የሚሉት? እኔ በኢትዮጵያዊነቴ የሙስሊም ወገኔን በዓል ገዝቼዋለኹ፡፡ ሙስሊሙም የእኔን በዓል ገዝቶታል፡፡ እርሱም በእኔ እምነት እድናለኹ፤ እኔም በእርሱ እምነት እድናለኹ፤ አላልንም እንጂ በባህላችን አንዳችን የሌላችንን በዓል ገንዘብ አድርገነዋል፡፡
ስለዚህ በብዙኀን መገናኛ በኩል መባል የሚኖርበት ‹‹ለኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ለዒድ አል አረፋ፤ እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በዓል አደረሳችኁ›› ነው፡፡ ለምን ሚዲያው ይለየናል? እኛ ያልተያየነውን ለምን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚለያየን እላለኹ፡፡ ብዙውን ጊዜ እኔ ጓደኛዬን ‹‹እንኳን አደረሰን›› ነው የምለው፡፡ ለምሳሌ እርሱ የመውሊድን በዓል ሲያከብር የሚያገኘው ሃይማኖታዊ በረከት እንዳለ አስቦ ነው፤ ልክ እኔ ጥምቀት በማከብርበት ጊዜ እንደማደርገው፤ ግን እርሱን እንኳን አደረሰኽ ስለው እርሱ በዓሉን ሰላማዊ ኾኖ፣ ነጻ ኾኖ፣ ደስ ብሎት የሚያከበርበትን ከባቢያዊ ኹኔታ መፍጠር ግዴታዬ ነው፡፡
ዕንቁ፡- ‹‹እንኳን አደረሰህ›› እና ‹‹እንኳን አደረሰን!›› በሚለው መሀል ልዩነት አለ እያልኽ ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ስንኾን አዎ፣ ልዩነት አለው፡፡ ለምን? እኔም አስተዋፅኦ አድርጌአለሁ፡፡ ሙስሊሙ ሃይማኖታዊ በዓሉን ደስ ብሎት፣ ነጻ ኾኖ እንዲያከብር፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ እኔም የጥምቀት በዓሌን ደስ ብሎኝ በሰላማዊ ሁኔታ ለማክበሬ የሙስሊሙ አስተዋፅኦ አለበት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ‹‹እንኳን ለመውሊድ፣ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሰን፤ አደረሳችሁ›› ማለት ወይም መባባል ነው ያለብን፡፡ የሁላችንም አስተዋፅኦ ያለበት ነገር እኮ ነው፡፡እስኪ ፈጣሪ ያሳይህ. . .ለጥምቀት፣ ለፋሲካ. . .ቀን በግ ይዞ የሚመጣውን ሰው ሙስሊም ይሁን ክርስቲያን በምን ታውቀዋለኽ? ለይተህ የምታውቅበት ልዩ ዘዴ አለህ እንዴ? እርሱ ይዞ ባይመጣ አንተ ከየት ነበር የምታገኘው? ይህ ሰው እኮ ለፋሲካ ይህን ነገር ማድረስ አለብኝ ብሎ ከሠራ ትልቅ ተግባር ነው ያከናወነው፡፡ እና የእነዚህ ወገኖቻችን አስተዋፅኦ በእኛ በዓል አከባበር ላይ አለበት፡፡ ለምን ታድያ የሥራውን ቀን ዝግ እናደርጋለን? የማይገባኝ ነገር እርሱ ነው፡፡ ጥምቀት ዕለት ሙስሊም ወገናችን ለምን ሥራ እንዲገባ አይደረግም? የመውሊድ ዕለትስ እኛ ሥራ እንዳንገባ የሚደረገው ለምንድን ነው? መገናዘቡ የለም ከተባለ፣ አንዱ ለሌላኛው ያበረከተው አስተዋፅኦ የለም አልነበረም የሚባል ከኾነ ሥራው ሲዘጋ በከፊል ነው መዘጋት የሚኖርበት፡፡ የመውሊድ በዓል ሲሆን ሙስሊም የሆናችሁ ወደ ሥራ አትምጡ፤ የስቅለት ዕለት ሲሆን ደግሞ ክርስቲያን የሆናችሁ ወደ ሥራ አትግቡ፤ ሌሎቻችሁ ግን ወደ ሥራ መግባት አለባችሁ መባል ነበረበት፤ በዓሉ የእነርሱና የእኛ ብቻ ከሆነ፤ ግን የሁላችንም ነው፡፡ በሕግ ደረጃ ብሔራዊ በዓል ነው ተብሎ ከተደነገገ በኋላ በሚዲያ በኩል ልዩነቱ ለምን ይመጣል? ይሄ ነው በተግባር መልስ ማግኘት ያለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን ከሥር ሆነን ያዳበርነው ከወደላይ ትልቅ ችግር ይፈጠርበታል፡፡ አስቀድሜ እንደተናገርኹት በኢትዮጵያ ውስጥ እምነት ከታች ወደላይ ነው፡፡ ታች ያለው ያለ በላዩ መኖር ይችላል፡፡ በስተላይ ያለው ግን ያለ በታቹ መኖር አይችልም፡፡
ቤተ ክህነት መኖሯን ሳያውቁ የሚኖሩ ብዙ ምእመናን አሉ፡፡ ጋምቤላ፣ ጎጃም፣ አሶሳ ጠረፍ ሄደህ፣ ጎንደር ገጠር ወርደህ ፤ .ፓትርያርኩ ማን ናቸው? ብለኽ ጠይቅ፤ የት ያውቃል! የእስልምና ጉዳዮች ሰብሳቢ ማን ቸው? ብትለው እስኪ የት ያውቅልሃል! እግዚአብሔርን ፣ የአጥቢያውን ታቦት፣ ቃዲውን ነው የሚያውቀው፡፡ ወይም ደግሞ በሰፈሩ ያለውን ዑሏማ ‹‹አሏህ ወ አክበር›› የሚያሰኘውን ሰው ነው የሚያውቀው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋራ፣ ከአላህ ጋራ የሚያገናኘው ያ በቅርቡ ያሉት የሃይማኖቱ ተጠሪ ናቸው፡፡ እርሱ ካለለት በቂ ነው፡፡ ከዚያ በላይ ያለው ትርፍ ነው፡፡ እኔ ታች ያሉት ከተግባቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ችግር የለም ባይ ነኝ፤ የሃይማኖት መሠረቶች እነርሱ ናቸውና፡፡ ሌላው ዓለም ስንሄድ ከላይ ወደታች ነው፡፡ ለዚህም ነው ለኢትዮጵያውያን በሃይማኖታቸው ጸንተው መኖር እምነቱ ከታች መኾኑ ዋነኛው መሠረት ነው፡፡
ዕንቁ፡- እምነቱ ከላይ ወደታች ቢኾን ምን ችግር ይገጥመዋል?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ግብጽ ስንት ጊዜ ጳጳስ ስታስቀር ምን ይውጠን ነበር? በዚህ ሁሉ ጭቅጭቅ፣ በዚህ ሁሉ ክርክር በንጉሡም በደርግ ዘመንም እንይ፤ አሁንም እንመልከት፡፡ ስለ እምነት ተቋማት የተለያየ አመለካከት ነው የነበረው፤ ያለውም፡፡ በየዘመኑ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ከመንግሥት ጋራ ናቸው አይደሉም የሚለው ክርክር አለ፡፡ ይህ ክርክር ግን ታች ያለውን ሰው አይነካውም፡፡ ጥፍጣፊው አይደርስበትም፡፡ ለምን? ብለን ስንል ጉዳዩ ከላይ ነው፡፡ እርሱ ከታች አንድ የንስሐ አባት፣ አንድ ቁርዓን የሚያስቀራው ካለ በቂው ነው፡፡ ታቦቱ አጠገቡ ካለ እዚያው ሄዶ ያስቀድሳል፤ ክርስትና ያሥነሳል፤ ሲሞት እዚያው ይቀበራል፡፡ እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ የምለው መገናዘብ፣ መግባባት ይህን ነው፡፡
ዕንቁ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ህልውና ለመጠበቅ፣ እሴቶቿን በነበረበት ለማቆየት የሚደረገውን መንፈሳዊ ትግል ወይም ይህን የመሰለውን ተነሣሽነትና መንፈሳዊ አስተምህሮ እንደ አክራሪነት ተግባር የሚመለከቱትን ለመከላከል ምን መደረግ ይኖርበታል?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አንደኛ መገንዘብ አለባቸው! በደንብ ስለማውቀው ክርስትና ልናገር፡፡ ክርስትና የሚጠይቅህ አንተ አምነህ ፣ ተጠምቀህ ብቻ እንድትኖር አይደለም፡፡ ይሁዳ በመልእክቱ ቁጥር ሦስት ላይ ‹‹ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እመክራችኋለኹ›› ነው ያለው፡፡ እንድትጋሉ እንጂ አምናችሁ፣ ተጠምቃችኹ እንድትቀመጡ አላለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክት ላይ ‹‹ሩጫዬን ፈጽሜአለኹ፤ ሃይማኖቴን ጠብቄአለኹ፤ መልካሙን ገድል ተጋድዬአለኹ›› ብሏል፡፡ ስለዚህ ሃይማኖት መጠበቅ አንድ ነገር ነው፡፡ ብዙ ሰው እንደሚለው ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ መልካሙን ገድል መጋደል ደግሞ ይኖርብናል፡፡ ያ መልካሙ ገድልም ደግሞ ከሦስት አካላት ጋራ የሚደረግ ነው፡፡ አንደኛ፡- ከራስ ጠባይዕ ጋራ፣ ሁለተኛ፡- ከሰይጣን ጋራ፣ ሦስተኛ፡- ከተለያዩ አካላት ማለትም ሃይማኖትኽን፣ ቤተ ክርስቲያንህን ወይም እምነትህን ለማፍረስ ከተነሡ ወገኖች ጋራ፣ ከመናፍቃን፣ ከከሐድያን፣ ከአላውያንና ከሌሎች አካላት ጋራ የምታደርገው ተጋድሎ ነው፡፡
ለምሳሌ፡- መናፍቃን ከውስጥ የሚወጡ ናቸው፡፡ አላውያን የምንላቸው ኃይልና ሥልጣን ተጠቅመው የሚመጡ ሲኾኑ ፤ ከሐድያን ደግሞ ወጥተው የሚሄዱ ናቸው፡፡ መልካሙ ገድል የሚባለውም ከእኒህ ጋራ የሚደረግ ተጋድሎ ነው፡፡ ይሄ ከሌለ ተጋድሎ አለ ሊባል አይችልም፡፡ ስለሆነም በክርስትና የመጋደል ግዴታ አለ፡፡ ስለዚህ የክርስትና ተጋድሎ በሚሰጠው ግዴታ ውስጥ አንድ ክርስቲያን አንዱን የተጋድሎ ዐይነት መምረጥ ይኖርበታል፡፡ ‹‹ቀኝኽን ለሚመታኽ ግራኽን ስጥ›› የሚል ክርስትናን የምንከተል በመኾናችን እስከ አሁን አባቶቻችን ሞተዋል እንጂ አልገደሉም፡፡
ሃይማኖትን የመጠበቅና የመጋደል ግዴታ በክርስትና አለ፡፡ በዚህ መሠረት የሚጋደሉትን አክራሪ የሚሉ ሰዎች ካሉ ያልተገነዘቡት ነገር አለ፡፡ አክራሪነት ይሄ ከኾነ በክርስትና አክራሪነት የሚጀምረው በቅዱስ ጴጥሮስ ዘመን ከነበሩት ሐዋርያት ነው ማለት ነው፡፡ እነዚያ ሁሉ አክራሪዎች ከኾኑ የምናወራው ስለ ክርስትና ነው ማለት ነው? ስለዚህ ስም በሌላው ላይ ከመለጠፋቸው በፊት ማወቅ፣ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡በተለይ ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ የሚሰነዘሩ ሐሳቦች ምንጫቸው መታየት አለበት፡፡ ለምንድን ነው ያ ሰው እንደዚያ ያለ ሐሳብ ያቀረበው፤ በምን ፍላጎት ላይ ተመርቶ ነው የሚለው መጤን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በፊት መንግሥት ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የሚል ትልቅ አጀንዳ አንሥቶ በነበረ ጊዜ የሆኑ አካላት ተነሥተው ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ኪራይ ሰብሳቢ ነው›› ብለዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉ አካላት ነገ ሌላ ስም ቢመጣ የመጣውን ስም ከማለት አይመለሱም፡፡
ዕንቁ፡- ማኅበረ ቅዱሳን እንደዚህ ዐይነቱን ነገር ለመከላከል ምን ማድረግ አለበት?
ዲ/ን ዳንኤል፡- የተለየ ነገር ማድረግ አለበት ብዬ አላምንም፡፡ እያደረገ ያለውን መቀጠል ነው፤ ምክንያቱም ለሚነሣው ሁሉ መልስ በመስጠት ራስን ከሠራተኛነት ወደ ተዋጊነት መለወጥ አያስፈልግም፤ እውነት ነውና የሚያሸንፈው፡፡ በአገራችን ይትበሃል ‹‹ቂጣም ከኾነ ይጠፋል፤ ሽልም ከኾነ ይገፋል›› እንደሚባለው በተያዘው ሐቅ መቀጠል ነው፡፡ አንድ ሰው እርግዝና መኾኑን ባወቀው ጉዳይ ‹‹አይ ይሄ ቦርጭ ነው›› ላሉት ሰዎች ሁሉን ለማስረዳት በመድከም ጨጓራውን መላጥ የለበትም፡፡ ሲወለድ ይታወቃል፤ ያኔ ይደርሳል፡፡
በበኩሌ አንድ የተባለ ነገር ብቻ አውቃለኹ፡፡ በዓለም ላይ ተከሥቶ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን አላደረገውም›› የተባለውን ነገር፡፡የመስከረም 11 የአሸባሪዎች ተግባር ማኅበረ ቅዱሳን አደረገው አልተባለም፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉት ነገሮች ግን ተመልክተውታል፡፡ እናም ክፉ ነገር ሲመጣ መለጠፍ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ ግን የሚመለከታቸው አካላት ጊዜ ሰጥቶ፣ መዛግብቱን ይዞ ማስረዳት ይኖርበታል፡፡ እንደውም ማኅበሩ አንድ የሚጎድለው ነገር ቢኖር ማስረዳት ነው፡፡ መልስ መስጠት እንጂ ቀድሞ የማስረዳት ነገር ውስጥ ብርቱ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቀድሞ ጉዳዮቹን የማስረዳት፣ የመንገር ሓላፊነት አለበት፡፡ የሚያስረዳውም ሰዎች እንዲገባቸው ብቻ አይደለም፡፡ መረዳት፣ አለመረዳት ግን የእነዚያ አካላት ድርሻ ነው፡፡
ዕንቁ፡- በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ወንጃይ ጣቶች የሚቀሰሩት ለምንድን ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ቤተ ክርስቲያን ከሃይማኖታዊ ዕሴቷ በተጨማሪ ለብዙ ዘመናት ሁለት ለአገሪቱ የሚጠቅሙ ዕሴቶችን ይዛ የኖረች ነች፡፡
አንደኛ፡- የኢትዮጵያዊነት ዕሴት ማለትም አገርን የመውደድ፣ አገርን ከአጥቂዎች የመከላከል፣ የአገር ፍቅር ስሜት በደም ሥር እንዲዘዋወር የሚያደርግ፣ ለአገር የመሞት እሴትን የያዘች ነች፡፡ ይሄ በግልጽ ይታያል፡፡ በተለያየ ዘመን የመጡ የአገሪቱ ጠላቶች መጀመሪያ ማፍረስ የሚፈልጉት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም አገሪቱ በጠላቶቿ ስትወረር ከግንባር ቀድማ የምትደርሰው ይህች ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ለምን? ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይኾን አገራዊ አደራንም የተረከበች ቤተ ክርስቲያን በመኾኗ፡፡
ሁለተኛ፡- የአገር፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የእምነት፣ የቅርስ ባለአደራ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያቃጠለውና ብዙ ምእመን የፈጀው የግራኝ መሐመድ ካባ የሚገኘው በመርጡለ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያንን ካባ ያስቀመጠችው እርሱን በመሳምና በመሳለም በረከት ይገኛል ብላ እንዳልኾነ ይታወቃል፤ ግን የአገር ታሪክ ነው፡፡ የብዙ ነገሥታት፣ የአያሌ መኳንንት፣ የሚወዷትና የሚጠሏት ሰዎች ቅርስ ያለው በቤተ ክርስቲያኗ ነው፡፡ ባለአደራ ስለኾነች፣ እርሷን የሚመለከቱም የማይመለከቱም መጻሕፍት ይገኙባታል፡፡ በጭራሽ ከእርሷ ጋራ የማይሄዱ የእነአርስቶትል፣ የእነሶቅራጥስ የእነፕሌቶ መጽሐፎች ሁሉ አሉ፡፡ ይህችን አገር የማድከም ፍላጎት ያለው፣ በዓለም ላይ አንገቷን ቀና አድርጋና ከፍ ብላ እንድትሄድ የማይፈልግ ማንኛውም ኃይል መጀመሪያ መምታት ያለበት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ነው፤ ምክንያቱም አገሪቱን አገር የሚያሰኟት ሁለት ትልልቅ ዕሴቶች ውስጧ ያሉ በመኾኑ፡፡
በብዙ ዓለም አገሮች ዞሬአለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሚደሰቱ አላየሁም፡፡ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ በእኛው አገር ውስጥ አንድ የውጭ ማኅበረሰብ ት/ቤት አለ፡፡ ይህ ት/ቤት ከውጭ በሚመጣ የትምህርት ቁሳቁስ እየተረዳ የትምህርት ሥርዐቱን የሚያስኬድ ነው፡፡ በታሪክ ማስተማርያ መጽሐፉ ላይ(አንድ ተማሪ አምጥቶ እንዳሳየኝ) ስለ አፍሪካ በሚገልጸው ክፍል ‹‹ኢትዮጵያና ላይቤሪያ ቅኝ አልተገዙም›› ይልና ምክንያቱን ሲያብራራ ‹‹ላይቤሪያ በአሜሪካ የበላይ ጠባቂነት ሥር ስለነበረች ሲኾን ኢትዮጵያ ደግሞ መሬቷ አስቸጋሪ ስለኾነ ነው›› ይላል፡፡ አየኽ! ያን ሁሉ ከዐድዋ የተጀመረ የፀረ ቅኝ አገዛዝ መሥዋዕትነት ድምጥማጡን አጥፍተውታል፡፡
ይህን የሚለው የትልቋ አገር የአሜሪካ የታሪክ ማስተማርያ መጽሐፍ ነው፡፡ እነርሱ ሳያውቁት ቀርተው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኾን ብለው ኢትዮጵያን የማንኳሰስ ዘመቻ ግን በብዙ ቦታ ይታያል፡፡ የቀደመውን ተወው፤ ሰሞኑን የኾነውንና የአንድ ሳምንት ዕድሜ ብቻ ያስቆጠረውን ጉዳይ በምሳሌ ላምጣልኽ፡፡ ኃይሌና ቀነኒሳ ከሞ ፋራኅ ጋራ ያደረጉትን ልዩ ውድድር አስታውሱ፡፡ ቢቢሲ ይህን ውድድር ምን ብሎ ዘገበ…‹‹ሞ ፋራኅ ተሸነፈ›› አለ፡፡ እንዲህ ያለው ቀነኒሳ አሸነፈ ላለማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የሚገርመው ራሱ ቢቢሲ ‹‹የኬንያው አትሌት ቀነኒሳ አሸነፈ›› አለ፡፡ ይህ ትልቅና ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ያለው የዜና ማሰራጫ ተቋም እንዴት ነው ቀነኒሳን ኬንያዊ የሚያደርገው? ‹‹ኢትዮጵያዊ›› የሚለው መጠሪያ፣ መለያ እንዴት ሊጠፋው ቻለ? ከዚህ ጀምሮ ስታይ ይህችን አገር ኾን ብሎ የማዳከም ነገር እንዳለ በብዙ መንገዶች እንዳለ ትገነዘባለኽ፡፡
እኔ ከፍተኛ ድጋፍ የምሰጠው ‹‹ይህችን አገር በምንም በምንም ብለን በኢኮኖሚውም ይኹን በሌላው ራሷን የቻለች አገር ማድረግ አለብን›› የሚለውን የዚህን መንግሥት አቋም ነው፡፡ ከሕዳሴው ግድብ ጀምሮ ያለውን ነገር ሁሉ የማንንም ድጋፍ ሳንጠይቅ መሥራት አለብን የሚለው ይስማማኛል፡፡ ለምን? ማንም በጎአችንን አይፈልግም፡፡ የትም ስለኢትዮጵያ ተብሎ የሚሰጠውን ትምህርት እንመልከት፤ በሁለት የአውሮፓ አገሮች የታሪክ ማስተማርያ መጻሕፍት አይቻለኹ፡፡ ስለአፍሪካ የሚገልጸው ንኡስ ክፍል ‹‹ግብጽ›› ይልና ‹‹መርዌ›› ይመጣል፡፡ በጭራሽ ስለ አክሱም ማውራት አይፈልግም፡፡ ለምን? ምን አደረገች? የኾነ ነው፡፡ የሐቅ ጥያቄ ነው፡፡ የምርጫ ጥያቄ አይደለም፡፡
ዕንቁ፡- እንደ ጀርመን የግዕዝን ቋንቋ በትምህርት ሥርዐታቸው ውስጥ ያስገቡትስ አገሮች?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እርሱ በጣም ጥቂት በኾኑ በጎ አድራጊዎች የኾነ ነው፡፡ እንደዚያም ቢኾን ያ የተደረገበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ለእኛ ተብሎ የተደረገ አይደለም፡፡ ከዚህ የሚሄድና የሄደ ስንት ጥበብ አለ፤ ነበር፡፡ ግእዙ የሄደውና የሚሄደው ጥበብን የመፍቻ ቁልፍ ስለኾነ ነው፡፡ እንደ ‹‹ባየር›› ያሉ የመድኃኒት ፋብሪካዎች ከየት ተነሥተው የመድኃኒት ማምረቱን ሥራ አሐዱ እንዳሉት፣ ምንን ወስደው አስተርጉመው እንደጀመሩት ይታወቃል፡፡ ያ ለራስ ጥቅም ሲባል የተደረገ ነው፡፡ የዚህችን አገር የዕድገትና የብልጽና ከፍታ የሚያመጣ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያመጣ ነገር ሲሞከር ግን፣ አገራችን ስትመታ ነው የሚታየው፡፡ ኢትዮጵያ በኢጣልያ ስትወረር ማን አብሯት ነበር? በወቅቱ የነበረው እውነት ጠፍቷቸው ነው? አይደለም፡፡ እና ይህችን ቤተ ክርስቲያን ከዚህች አገር ጋራ የማየት ጉዳይ ስላለ ምንጊዜም ቢኾን ሰበብ ፈጥረው መምታት ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ በውጭዎቹ ብቻ የሚፈጸም አይደለም፤ ወኪሎችም አሏቸው፡፡ ትግሉ ከሁለቱ ጋራ ነው የሚኾነው፡፡ ዓላማቸው መበተን ሳይኾን ይህችን ቤተ ክርስቲያን ማጥፋት ነው፡፡ ይህን ካልቻሉ ማደንበሽ!
ዕንቁ፡- በኢትዮጵያ ያለው የፖሊቲካ ነው የሃይማኖት አክራሪነት?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እኔ የሁለቱም አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ የእምነት አለ፡፡ የፖሊቲካ እንኳ ባንል የአስተሳሰብ አክራሪነት ይኖራል፡፡ በእኛ አገር የተለመደው የፓርቲ ፖሊቲካ ነው፡፡ አንዱም ትልቅ ችግር እርሱ ነው፡፡ ይህ ስላለ ‹‹እገሌ እንደዚህ ነው›› ሲባል ‹‹እገሌ መአሕድ ነው››፣ ‹‹እገሌ እንደዚህ ብሏል›› ሲባል ‹‹ኢሕአዴግ ነው፤ ቅንጅት ነው›› ይባላል፡፡ ለስላሳ ወይም ቢራ ይመስል የኾነ ሣጥን ውስጥ ካልገባኽ ብቻኽን አስተሳሰብኽን ሊመዝነው ወይም ሊያደምጠው አይፈልግም፡፡
በነገራችን ላይ እንዲህ ዐይነቱ ጠባይዕ ከባህላችንም የመጣ ነው፡፡ በገበያው ላይ ያታያል፡፡ የኾነ ነገር ለመግዛት ስትጠይቅ ‹‹በደርዘን ካልኾነ፣ ከነሣጥኑ ካልወሰድኽ፤ የጠርሙስ ማስያዣ ካላመጣኽ ወይም ይህን ያህል ክፈል›› ይልኻል፡፡ ነጥሎ ማየት አይወደድም፡፡ ጠቅልሎ የማየት በሽታ አለብን፡፡ ስለዚህ ከመኖር የመጣ የአክራሪነት አመለካከት አለ፡፡ አክራሪ ሰዎችም አሉ፡፡ ከጠቅላላው ማኅበረሰብ አንጻር ሲታዩ ግን ኢምንት ናቸው፡፡ ኾኖም አንዳንዴ የማኅበረሰቡን ሐሳብ የማግኘት ዕድል ያላቸው ሲኾኑ፣ ይህንንም ዕድል የምናመቻችላቸው እኛው ነን፡፡ ሰዎቹ አቅም ኖሯቸው አይደለም፡፡ በማንኛውም ሰዓት በአቅራቢያው ጉንፋን አማጭ ቫይረስ ሊኖር ይችላል…ያ ሰው ሲደክም፣ በጉዞ ወይም በከባድ የሥራ ጫና ሊኾን ይችላል በዚያን ጊዜ እርሱ በሽታ ኾኖ ይመጣል፡፡ የሰውዬው መድከም ነው ለበሽታው መከሠት አስተዋፅኦ ያደረገው፡፡ ሰውዬው ጠንካራ ከኾነ ግን በአካባቢው የፈለገው ነገር ቢኖር ምንም ሊያደርገው አይችልም፡፡ የአክራሪነትን ጉዳይ የማየው እንደዚህ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ አመኔታ ያለው የዕምነት ተቋም የለም፤ ጠንካራ እምነቶች ግን አሉ፡፡ ጠንካራ የእምነት ተቋምና አስተዳደራዊ ኹኔታዎች የሉም፤ አንዱ ትልቁ ችግር ይህ ነው፡፡ ተአማኒነት ያለው ተቋም አለመኖር፡፡ ቤተ ክህነቱንም የእስልምና ጉዳዮችንም ፕሮቴስታንቱንም በምሳሌነት ብንወስድ ምእመናኑ በፍርሃት በጥርጣሬ የሚያዩት እንጂ የሚወዱት የሃይማኖት ተቋም የለም፡፡ ከምእመናኑ ጋራ በጣም ተቀራርቦ የሚሠራ የሃይማኖት ተቋም አይታይም፤ ምክንያቱም በዚህች አገር ላይ ብዙዎቹ ምእመናን ናቸው፡፡ ጳጳሳቱ ኀምሳ ያህል ናቸው፡፡ ካህናቱ ተሰፍረው ወይም ተቆጥረው የሚደረስባቸው ናቸው፡፡ ሕዝቡ ግን ብዙ ነው፡፡ ከላይ እስከ ታች በሚገባ፣ በታማኝነት፣ ከሙስና፣ ከዘረኝነት፣ ከፖሊቲካ አቋም የጸዳና ግልጽና ተጠያቂነት ያለው ጠንካራ የሃይማኖት ተቋም ቢኖር ኖሮ አሁን አሉ የምንላቸውን የአክራሪነት ዝንባሌዎች በጣም እንቀንሳቸው ነበር፡፡ ይህ ባለመኖሩ ከሃይማኖት ተቋሙ የሚነሣውን የአስተዳደር ችግር በሙሉ ሰውን የመገፋት፣ የመጨቆንና አደጋ ውስጥ የመግባት ስሜት እንዲያድርበት አድርጎታል፡፡ ይህ ለእነማን ዕድል ይሰጣል? የአክራሪነት ስሜት ላላቸው አካሎች ነው፡፡ ስለዚህ ትልቁ ነገር፣ የእምነት ተቋማት ተጠያቂነት፣ ግልጽነት ባለበት ኹኔታ በየራሳቸው ሃይማኖት ሥርዐት መሠረት የሚኾንና በሌላ የማይቀየር፣ የእምነቱን ታሪክ መነሻ ያደረገ፣ ግን ለማንኛውም ሰው ግልጽ የኾነ ራሳቸውን በራሳቸው ማረምና ማስተካከል የሚያስችላቸውን አሠራር መዘርጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ዛሬ ስለእምነት ተቋማት ጉዳይ ተነሥቶ ጨዋታ ሲጀመር ምእመናኑ ፤ ስለሙስና፣ ስለገንዘብ፣ እገሌ በዘመድ ተሾመ፣ እገሌ ገንዘብ ተቀበለ፣ እገሌ የእነ እገሌ ወገን ነው የሚለውን ነው አብዝተው የሚናገሩት፡፡ እና ነገሩ ይጽዳ፤ ይወገድ ከተባለ ከዚህ ነው መጀመር የሚኖርበት፡፡

Tuesday, September 24, 2013

ከለውጡ በኋላስ? (ጋዜጠኛ ተመሰገን ደሳለኝ )

ኢህአዴግ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ (በውስጥም በውጪም ተግዳሮቶች) መገፋቱን በሚያመላክቱ የፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ የሚያጠነጥን አንድ ፅሁፍ (‹የአብዮቱ የምፅዓት ቀን ምልክቶች›› በሚል ርዕስ) አቅርቤ እንደነበር ይታወሳል፤ ይዘቱም በመጪዎቹ ወራት ወይም ዓመት ስርዓቱምርጫአሊያምህዝባዊእምቢተኝነት ከሚያመጣውማዕበል› (እንደበረከት ስምዖን አገላለፅናዳን በሚገታ ሩጫ›) የማምለጥ ዕድሉ የጠበበ መሆኑን የሚያመላክት ነው፤ ይሁንና አንድ አብዮት ታላቅ (ውጤታማ) ሊባል የሚችለው አምባገነን ስርዓትን በመቀየሩ ብቻ ስላልሆነ (ሥር-ነቀል ለውጥ የሚፈጥር አብዮት ዋጋ የሚኖረው የዲሞክራሲ ተቋማትን መሰረት መጣል ሲችል ነውና) በቀጣይ መፃኢ ዕድሉ ላይ መነጋገሩ አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በዚህ ፅሁፍህ ተጠየቅምከስርዓቱ ለውጥ በኋላ፣ ማን ነው አማራጩ?› የሚለው ጥያቄ ትኩረት ይደረግበት ዘንድ አመላክታለሁ፡፡

 
ምክንያቱም በጠለፉ መንገድ ከቀሩ አብዮቶች ታሪክ ተምረን፣መጥነን ካልደቆስንየሚከፈለውን ዋጋ በብላሽ የሚያስቀር አሳዛኝ ሁናቴ ሊፈጠር ይችላልና (ቭላድሚር ኤሊች ሌኒን ‹‹አብዮት፣ ለአብዮት ብቻ ሲባል መካሄድ የለበትም›› እንዲል፣ ከኢህአዴግ መገላገሉ መልካም ቢሆንም፣ የአገላጋዩን ማቀፊያ ከወዲሁ መምረጡ ወይም የምንጠይቀውን ማወቁ ብልህነት ነው)

አማራጩ ተወልዷልን?

ከኢህአዴግ በኋላ የሚተካው አማራጭ ተዘጋጅቷል? …ይህንን ቀዳዳ አስቀድሞ መድፈኑን አስቸኳይ ያደረገው፣ ለውጡ የሚመጣበት መንገድከህዝባዊ እምቢተኝነትይሆናል የሚለው ቅደመ-ግምት ነው፡፡ ከታዓማኒና በዕኩል አሳታፊ ምርጫ የሚነሳ ሽግግር (‹ሕዝብ የሚፈልገውን ያውቃልና ውሳኔው መከበር አለበትከሚለው የዲሞክራሲ ፅንሰ-ሃሳብ በመነሳት) አሳሳቢነቱ ከአደባባይ ተቃውሞ የሚመነጨውን ያህል አይደለም፤ ስለዚህም ከስጋት ነፃ መሆን የሚቻለው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መሰረታቸውን ሀገር ቤት አድርገው በህግ የተመዘገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች የቤት ስራቸውን ሰርተው ዝግጁ ሆነው ሲጠብቁ ብቻ ነው፡፡ ይህ ግን የድርጅቶቹን ቁጥር ከሰማኒያ በላይ ከማሻቀብ ያለፈ አስተዋፅኦ የሌላቸውን አሰስ-ገሰስፓርቲዎች በሙሉ እንደሚመለከት ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡

 
ነፍስ ይማርና ‹‹ልዕልና ጋዜጣ›› እልፍ አእላፍ ችግሮቹን ማረም ከቻለ መድረክ ተስፋ ሊጣልበት ይችላል ብዬ እንደማስብ መፃፌን አስታውሳለሁ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የመድረክ አሰላለፍ ሊቀየር በማጋደሉ (ከአንድነት አብሮ መቀጠሉ ማጠራጠሩ) እና ሰማያዊ ፓርቲ አዎንታዊ እንቅስቃሴ ከማድረጉ አኳያ ተፎካካሪ ሊሆን የሚችልበት ዕድል በመፍጠሩ፣ በአጀንዳው ላይ ማካትቱን ተገቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ይሁንና ሌሎች ፓርቲዎችን እዚህ ያላነሳሁበት፣ ከላይ ከጠቀስኩት በተጨማሪ ሶስት ምክንያቶች አሉኝ፤ ቅቡልነትን ማጣት፣ እንቅስቃሴ አልባ መሆን እና በገዥው ፓርቲ ስፖንሰርነት መተንፈስ የሚሉ፡፡

መድረክ

የስድስት ፓርቲዎች ስብስብ ነው፤ በምርጫ ሁለት ሺህ ሁለት (ምንም እንኳ ከአንድ የምክር ቤት ወንበር በላይ ባይሳካለትም) ከሁሉም

 
ተቀናቃኞች በላይ ጐልቶ መውጣት ችሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የአምስተኛውን ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫም ተስፋ አድርጎ ለመጠበቁ
ማሳያዎቹ፡- አንድም ስብስቡ ዛሬም ህላዊ መሆኑ፣ ሁለትም ለበርካታ አባላቱና ደጋፊዎቹ ወደግንባር ተሻጋገሩግፊት ምላሽ መስጠት
መቻሉ ነው፡፡

 
በምስረታው ዋዜማና 
ማግስት ብዙ የተነገረለት መድረክ እርስ በእርሱ (በአንድ ጠርዝ-የአንድነት አመራሮች፤ በሌላኛው-ኦፌኮ እና
ኢሶዴፓ) የፈጠረው ውዝግብ በዙሪያው ለተሰለፉ አባላትና ደጋፊዎች ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ ለግንባሩ ቅርብ የሆነ ወዳጄ የችግሩን
መጦዝ የገለፀው ‹‹ሁለቱ ጎራዎች በስብሰባ ወቅትበውሃ ቀጠነለፀብ ሲገባበዙ የሚያይ እና ለስድብ የሚጠቀሙባቸውን ቃላት የሚሰማ በአንድ ግንባር የተሰለፉ ናቸው ብሎ ከሚያምንግመል በመርፌ ቀዳዳ መሽሎኩንቢቀበል ይቀለዋል›› በሚል ምፀት ነው፡፡ አደጋውን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ኩነቶቹ ከመለዘብ ይልቅ መባባሳቸው ይመስለኛል፡፡

በመሬት ያለው እውነታ ይህ ቢሆንም፣ ፓርቲው 2005 . ወርሃ መጋቢት ወደግንባርመሻገሩን ከማብሰሩም በላይ፣
‹‹
የኢትዮጵያን ወቅታዊና መሰረታዊ ችግሮች የመፍቻ አጋጣሚዎች›› በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው ባለአራት ገፅማኔፌስቶ የሀገሪቱን

 
ችግር በሙሉ በአራት ክፍል ቀንብቦ ካስቀመጠ በኋላ፣ ጉዳዩን ፈረንጅኛውየሲኒ ማዕበልእንደሚለው አድርጎ በማለፍ ደግፉኝ

ጥሪውን እንዲህ ሲል አስተላልፏል፡-‹‹ይህንን ፀረ-ህዝብና ፀረ-ሀገር የሆነውን ኢህአዴጋዊ ስርዓት በሰላማዊ አግባብ በምታደርገው ብርቱ ትግልህ መለወጥ እንደምትችል ካለፈው የትግል ተሞክሮህ ሆነ የአለም ህዝቦች ለነፃነት፣ ለዕኩልነትና ለፍትህ ብሎም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን ከሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎችና ከሚያስመዘግቧቸውም ድሎች ትገነዘባለህ፡፡ ስለሆነም መድረክ ይህንን ክቡር ትግልህን በመምራት ባለቤትነት እንድትበቃ በፅናትህ ከጎንህ ሆኖ ለመታገለ መወሰኑን ተገንዝበህ ከምንጊዜም በላይ ሁለንተናዊ ድጋፍህን እንድትሰጥ ጥሪያችንን በከፍተኛ አክብሮትና በአንተም ላይ ባለን ሙሉ እምነት እናስተላልፋለን፡፡››በግሌ መድረክ ራሱ በሁለት ምክንያቶች እምነት ሊጣልበት የሚችል አልመስለኝም፡፡

የመጀመሪያው ከአንድነት ጋር የገባበት ድምፅ የለሽ ውዝግብ ከዕለት ወደ እለት እያደገ መሄዱ ነው፤ አዲሱ የዶክተር መረራ ጉዲና መጽሐፍም ቅራኔውን ቢያሳፋው አይገርምም፤ / ስለ2002 ምርጫ ባወሳበት ምዕራፍ ‹‹1997 የቅንጅት ወራሽ ነው ብለን የተማመንበት አንድነት እውነተኛ ወራሽ ለመሆን በጣም ብዙ እንደሚቀረው ተረዳው›› ያለበት ግምገማ እና ‹‹ያልገባኝና የሚከነክነኝ አንድነት ኦሮሚያ ላይ በብዛት ያወዳደራቸው ኦህዴድ ያሰማራቸው ወሮበሎች ነበሩ›› ፍረጃውትችት በቅንነት ለመቀበል ልምድ ከሌለው የሀገሪቱ ፖለቲካ አንጻር አቧራ ማስነሳቱ አይቀሬ ለመሆኑ መገመቱ አይከብድም፡፡ ይህ እንግዲህ አንድነትን የአማራ (የከተማ ልሂቃን) ተወካይ የሚያደረገውን ወቀሳ ሳይጨመር ነው (እዚህ የሚነሳው አስቂኙ ጉዳይ ወቀሳውን የሚሰነዝሩት አባል ፓርቲዎች አንድነት የብሔር ድርጅት ቢሆን ይበልጥ ተጠቃሚ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለአብዛኛው ችግሮቻቸው በቀላሉ መፍትሄ የመስጠቱ ጉዳይ ሲታሰብ ነው) ሁለተኛው መድረኩ ከለውጡ በኋላ ሀገር ለመምራት የሚያስችል የጠራ የፖለቲካ አመለካከት አለመከተሉ ነው፤ በውስጡ ያሉ ፓርቲዎች ቢያንስ ሁለት የተለያዩ ፕሮግራም የሚያራምዱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የአንድነትን እና የኦፌኮን ፕሮግራም ብንወስድ

የችግሩን ግዝፈት ያሳየናል፤ አንድነት መልካ ምድር ላይ ስለተመሰረተ ፌደራሊዝም አስተዳደር ጠቀሜታ ሲያብራራ፤ የኦፌኮ ባለስድስት ገፅ

 
ፕሮግራም ደግሞ በማንነት ላይ ስለተመሰረተ ፌደራሊዝም ይሰብካል፡፡ በግልባጩ ውድሀት ይፈፅሙ እንዳይባል ደግሞ የእነ / መረራ

ከተዋህድን ኦሮሞ ተውጦ ይጠፋልስጋት ጋሬጣ ነው፡፡ አንዳንድ የአመራር አባላቱ ‹‹ዓላማችን ቅድሚያ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን
መገንባት ነው›› የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ ቢደመጡም፣ ከዚህ በኩል ከሚነሳው ተግዳሮት በቀላሉ የሚመለጥ አይመስለኝም
(
በነገራችን ላይ መድረኩ በወቅታዊው ቁመናግንባርለመመስረት የሚያስችለውን መስፈርት ሟሟላቱ ራሱ አጠራጣሪ ነው)

አንድነት

የአንድነት ተግዳሮት ወደ መድረክ ከመግባት ተያይዞ የመጣ ነው (ከጠዋቱ ሰማያዊ ፓርቲን የመሰረቱት ወጣቶች ከድርጅቱ
ለመውጣት አንዱ ምክንያታቸው ይህ እንደሆነ ይታወሳል) ትብብሩንያልተባረከ ጋብቻየሚያስብለው ደግሞ የዛሬ አራት ዓመትወደ

 
መድረክ ካልገባን ትግሉን እናደናቅፋለንሲሉ የነበሩ አንዳንድ የአንድነት አመራሮች የውዝግቡ ተሳፊ መሆናቸውን ስንመለከት ነው፤

 
መተነኳኮሱ 2002 ምርጫ ማግስት የተጀመረ ቢሆንም፣ ባለፈው ዓመት ወደ መጦዝ ተሸጋግሯል፡፡ በተለይም አንድነት ‹‹የሚሊዮኖች

 
ድምፅ ንቅናቄ›› በሚል መርህ ያካሄደው የሶስት ወር ዘመቻ መድረክን አለማካተቱ የሚያስተላልፈው መልዕክት ግልፅ ነው፡፡ ‹‹ፀረ-

ሽብር›› አዋጁ ላይ (ኢህአዴግንና ኢዴፓን ጨምሮ) በተደረገው ክርክርም አንድነት እና መድረክ በተለያዩ ሰዎች ተወክለው መቅረባቸው

 
ግንኙነቱን እንደ ቀድሞ ለማየት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

ይህም ሆኖ አንድነት በራሱ የተሻለ ፓርቲ ሆኖ ሊወጣ የሚችልበት ዕድል አለው፡፡ ምሁራዊ ስብስቡም ሆነ የኢኮኖሚ አቅሙ
(
የዲያስፖራ ድጋፉ) አንፃራዊ ጥንካሬ እንዲያገኝ ረድቶታል፤ ርዕዮተ-ዓለሙንም ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች በጠበቀ መልኩ ማዘጋጀቱ
ለቅቡልነቱ አስተዋፅኦ ሊያደርግለት ይችላል፤ ከመኢአድ ጋር የጀመረውን ውህደት (‹የአማራ ተወካይየሚለውን ፍረጃ ቢያጠናክረውም)

ከዳር ካደረሰ ደግሞ ከአቻዎቹ ያለው ልዩነት በእጅጉ መስፋቱ አይቀሬ ነው (መኢአድ የፈራረሰው ከአናት ነውና ግዙፍ መዋቅሩእረኛ አልባበመሆኑ፣ አንድነት በውህደት ስም ቢሰበስበው በከፍተኛ ደረጃ ይጠቅመዋል)

የወል-መንገድ

 
በቀጣይ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ለመገኘት መድረክና አንድነት መቻቻላቸው ወሳኝ ነው፡፡ ይሁንና ኩነቱን በታዛቢነት መመልከት
የመረጡት የአረና ሰዎቸ በግንባሩ ቢሮ ሰላም ለማውረድ የአስታራቂነት ሚና ቢጫወቱ ጠቃሚነቱ ለእነርሱም ነው፡፡ አንድነቶችም፣
በመድረክ ስም እዚህ ድረስ ለመጓዝ የከፈሉት ዋጋ ብላሽ ከሆነ ማንንም አያተርፍም፡፡ በአናቱም ወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አስገዳጅ

 
መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ ምክንያቱም አንድነት የሰበሰባቸው ልሂቃኖችም ሆኑ በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ያነበረው መዋቅር (ጥንካሬው
ላይ ያለኝ ጥርጣሬ እንደተጠበቀ ሆኖ) ቅድሚያ ለብሔር ፖለቲካ ከሚሰጡ አካባቢዎች መድረክ ባርኔጣበሚገኝ ድጋፍ (ድምፅ)
ካልታገዘ በቀር አየር ላይ ተንጠልጥሎ ከመቅረት አይታደገውም፡፡


 
የመድረክ ተግዳሮትም ተመሳሳይ ነው፤ በፖለቲካው ላይ ውጤት የሚያዛባ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚቻላቸውንና አንድነት የራሱ
ያደረጋቸውን ከተሜዎችቡራኬሳይቀበል ወደ ውድድር መግባቱውሃ በወንፊት…› አይነት ሊሆንበት ይችላል፡፡ የመድረክንና
የአንድነትን የወል ቀዳዳ መዘርዘሩን እዚሁ ገትቼ፣ የተሻለ ጥንካሬና የመግባባት መንፈስ ለማስረፅ በቅድሚያ የችግሮቻቸውን መንስኤ
ለይተው ማወቅ አለባቸው ብዬ ስለማስብ፣ በግሌያለመግባባቱ መነሻከምላቸው ዋና ጉዳዮች ሶስቱን በአዲስ መስመር እጠቅሳለሁ፡፡

- የፕሮግራም መጋጨት ያመጣው ጣጣ አንዱ ነው፤ ይኸውም የፀቡ የቡድን አባቶች ሕብረ ብሔርእና ክልልፖለቲካ አቀንቃኝነት፣ ሁሉም አባል ፓርቲዎች መድረኩን ሲፈጥሩ የየራሳቸውን ፕሮግራም እንደያዙ መሆኑ፣ ጥቂት የማይባሉ ልዩነታቸውን ሳይፈቱበይደርማስቀመጣቸውእንደ ማሳያ ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ሁኔታም የእርስ በእርስ መተማማን እንዳይኖራቸው ያደረገ ይመስለኛል(ከዚህ አኳያም ለመፍትሄው ቅድሚያ ከልሰጡ በመድረክ በኩልመጪው ጊዜ ብሩህ ይሆናልብሎ መጠበቅየዋህሊያስብል ይችላል) የጫናው ተፅእኖ ደግሞ በሁለቱም በኩል (በአንድነትና በብሄር ድርጅቶቹ) ከሚከተሉት የፖለቲካ አመለካከት አንፃር ወደ ስልጣን የመምጣቱ አጋጣሚ ቢፈጠር፣ የታገሉለትን ስርዓት ማንበሩ ፍፁም አዳጋች መሆኑን በማስታወስ ነው፤ አንድነቶች ፓርቲያቸው ከመድረክ እንዲወጣ ይጎተጉታሉ፤ ብሔር ተኮሮቹ ደግሞአንድነት የነፍጠኛውን ስርዓት የሚመለስ በመሆኑ፣ ወይ ወደ ብሄር ድርጅት ራሱን ይቀየር፣ አሊያም ፕሮግራሙን ይከልስየሚለው ሙግታቸው በአሳማኝ ሁኔታ መፍትሄ አለማግኘቱ ራሱን የቻለ ሌላ ትግል ከሚፈልግ አጀንዳ አላትሟቸዋል፡፡

-አንድነት በሚያራምደው የሊብራል ዲሞክራሲ እና አብዛኛው የመድረክ አባል ድርጅቶች በሚከተሉት የሶሻል ዲሞክራሲ መካከል ያለውን ልዩነት የማሰታረቅ ስራ አለመሰራቱ ነው፡፡ ‹‹የአንድነት ፓርቲ ስትራቴጂና የአምስት ዓመት ዕቅድ›› በሚል ርዕስ 246 ገፅ ይዞ በታተመው መፅሀፍ ላይ ‹‹አንድነት የሚመሰረትበት ርዕዮተ-ዓለም ሊበራሊዝም ሆኖ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች የሶሻል ዲሞክራሲን ጠቃሚ ገፅታዎች ይወስዳል›› የሚለው አንቀፅ ቢጤን ለመልካም ግንኙነት መደላድል መሆን ይችላል (በነገራችን ላይእንዲህ የችግር ቋት ተሸክመው ስለምን በጋራ ለመስራት ተስማሙ?› የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርምና ግምቴን ላስቀምጥ፤ የብሔር ድርጅቶቹን እስትንፋስ የሚቆጣጠሩት / በየነ ጴጥሮስ እና / መረራ ጉዲና ምርጫ 97 ከሁለት አቅጣጫ ገምግመው ከደረሱበት ድምዳሜ የሚያያዝ ይመስለኛል፤ ይኸውምአንድነት፣ የቅንጅት ወራሽ ነውየሚለው የተሳሳተው ትንተና አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛው በዛው ምርጫ ተቀማጭነታቸው አውሮፓና አሜሪካ ከሆኑ አስራ ሁለት ፓርቲዎች ጋር መስርተውት የነበረው ‹‹ህብረት›› ፓርላማ በመግባታቸው፣ ከውግዘት ጋር እንዲባረሩ በማድረጉ ያሳደረባቸው መገለል ሊሆን ይችላል፤ በአንድነት በኩል ደግሞየመድረኩ መሀንዲስተደርገው የተወሰዱት / ነጋሶና አቶ ስዬ አብርሃ አንድነትን ለመቀላቀል ወደ መድረክ መግባትን እንደ መደራደሪያ በማቅረባቸው ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ዛሬም ያልተሸነፈው ተባበሩ ወይም ተሰባበሩግልብ ግፊት ነው ብዬ አስባለሁ፤ የዚህ ድምር ውጤትም ከነርዕዮተ-ዓለም እና የፕሮግራም ልዩነት ወደ መድረኩ አምጥቷቸው አይን የሚገባ ሥራ እንዳይሰሩ አግዷቸዋል)

-የመድረክ አባል ድርጅቶች መተዳደሪያ ደንብን አለማክበርየፖለቲካ ብልጠትበማድረጋቸው፣ ለራሳቸው ተጨማሪ የመናተረኪያአጀንዳ ፈጥረዋል፡፡ ይህ አይነቱ ስርዓት አልበኝነት በጋራም በተናጥልም ተፈፅሟል፡፡ አንድነትን ጨምሮ የመድረኩ ስራ አስፈፃሚ ደጋግሞከመርሁ ሲያፈነግጥ ታይቷል፤ ለምሳሌ በደንቡ ላይ መሻሻል ያለበትን አንቀፅ የሚወስነውም ሆነ ከፍተኛው ስልጣን የጠቅላላ ጉባዔውመሆኑ በግልፅ ተቀምጦ ሳለ፣ ጉባዔው ከተሰበሰበባቸው በአንዱ ዕለትየመድረኩ ሊቀ-መንበረ በዙር ከሚሆን፣ በብቃት ይሁን፤እንዲሁምአዲስ ፓርቲ በአባልነት የምንቀበልበት መንገድ መሻሻል አለበትየሚሉ አቋሞች ላይ ቢደርስም፣ ስራ አስፈፃሚው ቃል በቃልይህንን አሰራር ጉባኤው ሊቀይረው አይችልምሲል ውድቅ ያደረገበትን አጋጣሚ መጥቀስ ይቻላል፡፡

 
በተናጥል አንድነት፣ ኦፌኮ እና ኢሶዴፓ በአንቀፅ 21 ‹የአባል ድርጅቶች ግዴታበሚል ርዕስ ስር የተቀመጡትን፡- ‹ከአፍራሽና
ተቃራኒ ከሆኑ እንቅስቃሴዎች መቆጠብበአባላት መካከል አለመተማመን ከሚፈጥሩ ማናቸውም ተግባር መቆጠብየግንባሩን አቋም

 
የሚፃረር አቋም ያለማራመድእና መሰል ደንቦችን ደጋግመው በአደባባይ ሲጥሱ ታይተዋል፤ ይህ አይነቱ ስርዓተ-አልበኝነት መፍትሄ

 
ሳያገኝ የተሻለና ጠንካራ ሆኖ መውጣቱ አዳጋች ይመስለኛል፡፡

ሰማያዊ

 
ሰማያዊ ፓርቲ አዲስ በመሆኑ ለወቀሳ መቸኮሉ አግባብ እንዳልሆነ ቢሰማኝም፣ ፓርቲው እያሳየ ካለው ፈጣን እንቅስቃሴ አኳያ፣
በፍጥነቶቹ መካከል የሚፈጥራቸውን ድክመቶቹን ቢያሻሽል ጠቀሜታው ለሀገር ስለሆነ የግል አስታየየት መስጠቱን አስፈላጊ ሆኖ
አግኝቸዋለሁ፡፡የሰማያዊ ዋናው ድክመት ግንፍሌ ፓርቲነት አልፎ የመሄድ ፍላጎት ያለው አለመምሰሉ ነው (/ቤቱ አራት ኪሎ /ግንፍሌ/ አካባቢ ይገኛል)፡፡

 
ከአዲስ አበባ ውጪ ለመንቀሳቀስ ሲሞክር አይታይም፤ በሌሎቸ የሀገሪቱ ከተሞች የተከፈተ ተጨማሪ ቢሮ ካለ፣ ከምስረታው
በኋላ የአባላቱ ቁጥር ምን ያህል እንደደረሰ፣ እና መሰል መረጃዎችን ለማግኘት ወደ ፓርቲው /ቤት ሄዶ የነበረው የመፅሄቱ ሪፖርተር

እንዴት እንደምትጠቀሙበት ስለማናውቅ አንናገርምበሚል ክልከላ በመመለሱ ስለወቅታዊው ቁመና እዚህ መጥቀስ አልተቻለም

(
ከዚህ ውጪ ሊቀ-መንበሩ ይልቃል ጌትነት ሰንደቅጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ ‹‹ባለፉት 40 ዓመታት ከመጣው የፓርቲዎች ጥንካሬ ይልቅ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ሰማያዊ ፓርቲ ብቻውን አምጥጦታል›› ያለው ሀረግ ስህተት ቢሆንም፣ አንድም በሂደት የሚታረም፣ሁለትም የአፍ ወለምታ፣ ሶስትም ከልምድ ማነስ የሚያጋጥም በመሆኑፀጉር መንጨቱፓርቲው ፍርሃትን ለመስበር ከሚያደርገው እንቅስቃሴ አኳያ ገንቢ አይደለምና አልፈዋለሁ፡፡)

እምነት ጨምሩልን

 ‹
ለውጥ! ለውጥ!› የሚል ድምፅ በመላ ሀገሪቱ የበረከተው ቡርዣወይምአድሀሪአብዮትን በመናፈቅ አይደለም፤ እንዲህ አይነት

 
አብዮት፣ ከሰው ለውጥ በቀር ሕዝባዊ ጠቀሜታ የለውማና፡፡ የደርግም ሆነ የኢህአዴግአብዮትየዚህ አምሳያ በመሆኑ ነው፣ ዛሬም

 
ዘመን ተጋሪዎቼፋኖ ተሰማራ!› ከማለት ነፃ ያልወጡት፡፡ሶስተኛው አብዮትየማይሸነፍ እና የማይንበረከክ እንዲሆንልን ከምንመኘው
በላይ ወደመፈንቅለ-መንግስትነት እንዳይቀየር መጠንቀቁንም ግዴታ ያደረገው ጠንካራ ፓርቲና የነቃ ማህበረሰብ ያለመኖሩ ስጋት ነው፡

 
ይህ ደግሞ ከወዲሁ ከአማራጩ ኃይል ጎን መቆም ይቻል ዘንድእምነት ጨምሩልን!› (ሀገር የመረከብ አቅማቸውን አሳዩን?) እንድንል አስገድዷል (‹ጀግናውኢህአዴግ ወደ ማይቀረው ሽንፈት መንገዱን ከጀመረ ጥቂት ክረምቶች በማለፋቸው፣ ከለውጡ በኋላ የሚመጣው ኃይል ሁለንታው የተቃና መሆኑን ማስመስከር አለበት)መድረክ፣ አንድነት እና ሰማያዊ ወደራሳቸው ይመለከቱ ዘንድ ከሞላ ጎደል የወልክፍተቶችወይምድክመቶችየምላቸውን ሶስት ጉዳዮች ከዚህ ቀጥሎ እጠቅሳለሁ፡፡

ሃሳብ-አልባ

 
ፓርቲዎቹ በምስረታቸው ዘመን ቅድሚያ የሚሰጡት ለምርጫ ቦርድ የእውቅና ሰርተፍኬት እናተቃዋሚ ድርጅትተብለው
ለመጠራት በመሆኑ አንድም የሀገሪቱን አንኳር ችግሮች አጥንተው መፍትሄ በመያዝ አልተዘጋጁም፤ ሁለትም ከነባር ድርጅቶች ድክመትና

 
ጥንካሬ ተምረው አልመጡም፤ በዚህም የሚፈልጉትን ሳያወቁ እና የተለየ አማራጭ ሳይይዙ ወደ ፖለቲካው ገብተዋል ወደሚል ጠርዝ

 
እየገፋን ነው፤ ጠንካራና የተፍታታ የፖለቲካ ፕሮግራም የላቸውም፤ በንፅፅር ‹‹አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ›› የተሻለ ፕሮግራም
ለመቅረፅ ከመሞከሩ ውጪ፣ የመንግስቱ ስልጣንገጭ-ቢልአማራጭ ሊሆኑ ይችላሉየሚባሉት ፓርቲዎችእያሾፉ ነውበሚል

 
ችላ ካልተባሉ በቀርፕሮግራሜብለው ያቀረቡትን ለተመለከተ ምን ያህል ሃሳብ አልባ እንደሆኑ ለመረዳት አይቸገርም፡፡
የሆነው ሆኖ ይህንን ፅሁፍ ሳዘጋጅ የነበረኝ አመለካከት ስለመድረክና አንድነት የፖለቲካ ፕሮግራም ደካማነት ከዚህ ቀደም ስለጠቀስኩ፣

 
ዛሬ ሰማያዊ ፓርቲን ብቻ አንስተን ብንነጋገር ይሻላል የሚል ነበር፤ ይሁንና የድርጅቱን ፕሮግራም ካነበብኩ በኋላ ግን ምንም ማውራት

 
እንደማይቻል ተረዳው (ያውም ያየሁት ወረቀትፕሮግራምተብሎ ሊጠራ ከቻለ ማለት ነው)፡፡ ፓርቲው ለስልጣን የመብቃት ዕድል

 
ካገኘ፣ ለዘመናት ሲንከባለልና ሲደራረብ የመጣውን ዘርፈ ብዙ የሀገሪቷን ችግር የሚፈታው ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ ፕሮግራም›› በማለት ርዕስ
ባዘጋጀው ባለአስራ አምስት ገፅ ወረቀት ነው፡፡ መቼም በዚህ ፕሮግራምከሌሎች የተሻልኩ ነኝ-ምረጡኝየማለቱ ድፍረት ግራ አጋቢ

 
ይመስለኛል፤ ምናልባትየፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ / መረራ ጉዲና ካዘጋጀው አራት ገፅ ፕሮግራም፣ የእኛ የበለጠ ነውየሚል
መከራከሪያ ካልቀረበ፡፡

 
ስለርዕዮተ-ዓለሙም ቢሆንለዘብተኛ ሌብራሊዝምከማለት ያለፈ ያብራራልን ጉዳይ የለም (በዚህ በኩል ኢዴፓ ከሁሉም በተሻለ የተብራራና የጠበቀ ፕሮግራም አለው፤ ግና! ለአንድ ፓርቲ ከምንም በላይ አስፈላጊ የሆነውንታአማኒነትአፍርሷልና ፕሮግራሙ ጠቀመ አልጠቀመ ፋይዳ አለው ማለት አይቻልም) በተቀረ ያለ ርዕዮተ-ዓለም ፓርቲ መስርቶ፣ሀገሬን፣ ሀገሬን…› ማለቱን


 
ከቀረርቶ ለይቶ መረዳት ይቸግራል፡፡ መድረክ፣ አንድነት እና ሰማያዊ አሁንም ጊዜውም ዕድሉም አላቸውና ስልጣን ቢይዙ በዋና ዋና ሀገራዊ አጀንዳዎች፣ በፖሊሲዎች፣ በማህበራዊ ፍትህ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ያላችውን የመፍትሄ ሃሳብ እና የተሻለ አማራጭ በትክክል ተንትነው ማዘጋጀቱን ቢያስቀድሙ መልካም ይመስለኛል፡፡

ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ 1997 . ‹‹የምርጫ ማኒፌስቶ›› ብሎ ያዘጋጀው ሰነድ እንኳ 130 ገፅ በላይ የፈጀ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ እናም ፓርቲዎቹፕሮግራሜየሚሉትንም ሆነ፣ ከተራራ የገዘፈ ችግሮቻችንን በደቃቃ ግምገማ ለማብራራት መዳከሩን አርቀው በመስቀል ወደ ቁም-ነገሩ ቢያዘንብሉ ጠቀሜታው ለራሳቸው ነው፤የትም ፍጪው…› መረሳት አለበት፤ ለፖለቲካ ፓርቲ ሃሳብ ከምንም በላይ ወሳኝ ነው፡፡ ዳሩስ! በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የተዘጋጀ ፓርቲ፣ የሚሸጥ ርዕዮተ-ዓለም ካላዘጋጀ በቀር ወታደራዊ ድርጅት አይደለምናበኃይል ተጠቅሜ ፍላጎቴን አሳካለሁሊል አይችልም፡፡ እውነት እውነት እላችኋለውም በዚህ በኩል ቀድሞ የነቃ፣ እርሱ አትራፊ ነው፤ ረቢው እንዳለውምላለው ይጨመርለታልና፡፡

ምሁር አልባ

የተፎካካሪ ድርጅቶች ሌላኛው ክፍተት ምሁራንን /ሙያተኞችን/ አለማቀፍ እንደሆነ ተደጋግሞ ቢነገርም፣ ዛሬም በዚህ በኩል የተሰራ

 
ሥራ የለም፡፡ ይህንን ቀዳዳ ለመድፈን አመራሩና አባለቱ ከጽ/ቤት በመውጣት መቀስቀስ፣ ማሳመን፣ ማግባባትአለባቸው ብዬ
አስባለሁ፤ መቼም በሁሉም ዘርፍእኔ ብቻ ነኝ የማውቀውግብዝነትን የወረሱት ነፍሱን ይማረውና ከአቶ መለስ ይመስለኛል፤ ይህ
አይነቱ አመለካከት ግን ወንዝ አያሻግርም፡፡ በርግጥፖለቲካና ኮረንቲ…› በሚባልበት አገር፣ በደፍረት፣ ድርጅት እስከመመስረት መድረስ

 
ትልቅ ታሪክ ቢሆንም፣ ጠንካራ መሆን ካልተቻለ ዞሮ ዞሮ ያው ክሽፈት ነው፡፡ አደባባዩም እንደቀድሞድንጋይ ዳቦ ነውብለው
ለሚከራከሩ አፈ-ጮማ ፖለቲከኞች ቦታ የሌለው መሆኑ ግልፅ ይመስለኛል፡፡ በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ ምሁራኖችን ወደ ፓርቲያችሁ
ለመሳብ መደላደሉን አመቻቹ፤ ፍርሃት መሰበር እንዳለበት አሳምኗቸው፤ አንኳኩ፤ ከልከፈቱም ደጋግሙት፡፡

የሴራ ፖለቲካ

ሌላው ድርጅቶቹ የሚጠነክሩት፡- ከሴራ፣ ከስርቻ ስር ፖለቲካ፣ ከጠልፎ መጣል ጨዋታ፣ ከአፍቅሮተ-ስልጣን አና ከመሳሰሉት ነፃ
ሲሆኑ ነው፡፡ በአናቱም የጥናትና ምርምር ዘርፍ መሰል እያቋቋሙ እውቀትና መረጃን ወደላይም ወደታችም በማሰራጨት አመራሩንና

 
አባላትን ማብቃት፣ እንዲሁም ግልፅነትን በመተግበር፣ ጀርባ ፖለቲካ ማዳካም ይቻላል፡፡ ይህ ሲሆን ነው ኩነቶችን ከመበለጥና
ያለመበለጥ፤ ከመሸነፍና ያለመሸነፍ አኳያ ብቻ የማየቱ አባዜ የሚለወጠው፡፡ ከእዚህ ሁሉ ስንክሳር በላይ ደግሞ በምሬቷ ብዛት
በአማራጩ ኃይል ላይ ተስፋ የጣለች ሀገር መኖሯም ከእያንዳንዷ እንቅስቃሴ መታወስ ይኖርበታል፡፡

በመጨረሻም-የአልባራዲ መንገድ

ሀገሪቱ ካለችበት ወሳኝና ታሪካው ወቅት አኳያ ቢያንስ በመንግስት ጥቁር መዝገብ ስማቸው ያልሰፈረ፣ እውቀትና አቅም ያላቸው፣
በየትኛውም ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው መንገድ ወደ ሀገራቸው ገብተው ትግሉን ማገዝ የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁናቴ
የሚያስገድደው ነው፡፡ በተለይም በእንዲህ አይነት ጉዳዮች ከትምህርትም ሆነ ከመስክ ልምድ ያካበቱ ወንድምና እህቶች የግብፃዊውን
መሀመድ አልባራዲ መንገድ ቢከተሉ፣ አንድም ሁኔታዎች ከቁጥጥር እንዳይወጡ ማገዝ ይችላሉ፤ ሁለትም አብዮቱን ከሽንፈትና ቅልበሳ
ይታደጋሉ፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ