Saturday, September 28, 2013

በመስቀል በዓል ዕለት እንዲዘመር የደረሰው ዜማ፡

ቅዱስ ያሬድ፡
መስከረም ፲፯ ቀን በሚውለው፡
በመስቀል በዓል ዕለት እንዲዘመር የደረሰው ዜማ፡
ከድጓ መጽሓፉ የተገኘ።
_________________________

ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ የነበረ!
ዛሬም ያለ! እና ወደፊትም፡ ለዘለዓለም የሚኖር!

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ወደኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ፡ ክረምት ነበረና፡ በዚያ በሚገኘው፡ በሰሎሞን የሰላም ደጃፍ፡ መስቀልን ተመርኵዞ፡ ድንቅ ተአምራትን እያሳየ፡ ተመላለሰ። 
አዎን! ዛሬ፡ መስቀል ተከበረ! ለተቀበሉት አበራ! አዎን! ለእኛ፡ ካሣችን፥ ጽንዓታችን፥ የነፍሳችን መዳኛ ለኾነው መስቀል፥ አይሁድ ሲክዱት፡ እኛ ግን ለዳንበት፡ ለመስቀል የሚገባው ምስጋና፡ እነሆ ዛሬ ቀረበ! 
ከዚህ እውነት ጋር፡ "መስቀል፡ ለዓለሙ ኹሉ ብርሃን ነው!" ሲሉ፡ ነቢያት የተናገሩት ቃል ይተባበራል።
መስቀል ድል ነሥቷልና፡ ሞት ተቈጣ! የመስቀል ኃይል አበራ! 
አንተ መስቀል ሆይ! በስሙ የታነፀች፥ በደሙ የተቀደሰች፥ በመስቀሉ ስም የተጠበቀች፥ ያማረች፥ መልካምና ፍጽምት የኾነችውን መቅደስ የያዘችው፥ የሰው እጅ ያልሠራትና ለእግዚአብሔር፡ የምስጋናው ማኅደር የኾነችው፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን፡ የድል ምልክት ነህ! 
ዘወትር በቅዱሳን የሚመሰገነው፥ ለአሕዛብና ለዓለሙ ኹሉ፡ በላይ በሰማያት፥ በታችም፡ በምድር የነገሠው መስቀል፡ ዛሬ፡ በዓሉ የሚከበርበት ነው። 
ዳግመኛ፡ የሕይወት መንገድ መሪ የኾነው፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ለአይሁድ እንዲህ አላቸው፦ "በእኔ እመኑ! በአባቴም እመኑ! ዛሬስ፡ በመስቀሌ፡ ለእናንተ አበራለሁ።" 
ቅዱስ ዳዊት፡ በትንቢት መንፈስ ኾኖ፡ በእርሱ ላይ፡ የእግዚአብሔር አብ ቃል ስለተሰቀለበት፡ ስለዚህ፡ የእንጨት መስቀል፡ እንዲህ አለ፦ "በላያችን ላይ ቆመው፡ የሚያሠቃዩንን፡ በስምህ እናዋርድበታለን።" ደግሞም አለ፦ "በጋሻነቱ፡ ከተወረወረ ቀስት ያመልጡበትና ይድኑበት ዘንድ፡ ለሚፈሩህ ወዳጆችህ፡ ምልክትን ሰጠሃቸው።"
ስለዚህ፡ እኛም፡ ዛሬ፡ ደስ ብሎን፡ በዚህች፡ በጌታችን የበዓል ዕለት፡ ሓሤት እናደርጋለን።
እርሱ፡ ጌታችን፡ ለፍጡሩ ሰው፡ ሕይወትን ሊሰጥ፡ ወደዚህ ዓለም፡ በሥጋ መጣ፤ መጥቶም፡ ተሰቀለ፤ ተሰቅሎም አዳነው፤ ለሥጋዊውና ለመንፈሳዊ ዕረፍቱም፡ ሰንበትን ሠራለት።
ከኹሉ ይልቅ ታላቅና ኃያል የኾነው አምላክ፡ ቅዱሳት እጆቹ፡ በዚህ መስቀል ላይ ተቸነከሩ፤ ጎኑን፡ በጦር ተወግቶ፡ ለዓለሙ ኹሉ መድኃኒት የኾነው ደሙ፡ ከውኃ ጋር ተቀላቅሎ ፈሰሰ። 
ይህም የኾነው፡ "መስቀል አበራ!" እያልን፡ በደመራው ዙሪያ፡ እየዞርን ለምንዘምረው፡ ለእኛ፡ በመስቀሉ ሃይማኖት አምነን፡ እያመሰግንን ለምንኖረው ነው።
ይህ መስቀል፡ ካሣ ኾኖ ያዳነን ነው፤ ለአይሁድ መሰደጃቸው ሲኾን፡ ለእኛ ግን፡ ሕይወት ኾነን። 
አዎን! ዛሬ፡ መስቀል ተከበረ! ለተቀበሉት አበራ! አዎን! ለእኛ፡ ካሣችን፥ ጽንዓታችን፥ የነፍሳችን መዳኛ ለኾነው መስቀል፥ አይሁድ ሲክዱት፡ እኛ ግን ለዳንበት፡ ለመስቀል የሚገባው ምስጋና፡ እነሆ ዛሬ ቀረበ!
ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለብሽ አንቺ፡ የጎልጎታዋ ቀራንዮ ሆይ! የጌታችን እግሩ በቆመብሽ፥ ጎኑ በተወጋብሽ፡ በአንቺ ዘንድ፡ ዛሬ፡ በመስቀሉ በዓል ዕለት፡ ለእርሱ መስቀል፡ እኛ ኹላችን እንሰግዳለን። 
ዛሬ፡ በላይ፡ በሰማያት፥ በታችም በምድር፡ በዚህ መስቀሉ፡ ሰላምን ያደረገበት፡ የመስቀሉ በዓል ነው።

No comments:

Post a Comment