Thursday, August 20, 2015

እስራኤል ለስለላ የላከችው ዶልፊን በሃማስ ቁጥጥር ስር ውሏል

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 14 ፣ 2007 ( ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል ከመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ጋር ያላት ግንኙነት የሻከረ እና መተማመን የጎደለው ነው።
በተለይ ደግሞ ከፍልስጤማውያን ጋር ዘወትር አተካሮ በመፍጠር ለበርካታ አመታት በግጭት የታጀበ ግንኙነታቸውን ዛሬም ድረስ ይዘውት ቆይተዋል።
ታዲያ የእስራኤል መንግስትም "ግዛቴንና ህዝቦቼን" ከጥቃት ለመከላከል በሚል ዘወትር የፍልስጤማውያንን እንቅስቃሴ በተለያዩ መንገዶች ይከታተላል።
ከሰሞኑ በጋዛ ሰርጥ በፍስጤማውያን የባህር ሃይል ኮማንዶዎች የተገኘውና በቁጥጥር ስር የዋለው ዶልፊን ግን ግርምትን ፈጥሯል።
ዶልፊኑ በባህር ክልሉ የፎቶ ካሜራ ተገጥሞለት በአካባቢው የእስራኤልን ባላንጣዎች እንቅስቃሴ ሲቀርጽና ሲሰልል ነበር ነው የተባለው።
ዶልፊኑ ባልተለመደ እና ቦታን ለማመልከት በሚመስል ሁኔታ በቦታው ላይ ብቅ ጥልቅ በማለት ያደረገው እንቅስቃሴ የባህር ላይ ቃኝዎችን ትኩረት በመሳቡ በቁጥጥር ስር መዋሉም ነው የተዘገበው።
ሰላዩ ዶልፊን በስፍራው ያለውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በተገጠሙለት ካሜራዎች እና የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በመቅዳት ለእስራኤሉ የስለላ ተቋም ሞሳድ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ይሰራ ነበርም ተብሏል።
ዋነኛ ተልዕኮውም በአካባቢው የሚካሄደውን የባህር ሃይል ስልጠና እና ተያያዥ ጉዳዮችን ቀርጾ መላክ እና መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንደነበር ነው ከፍልስጤማውያኑ ጋዜጣ ል ቁድስ የተገኘ መረጃ የሚያሳየው።
የፍልስጤሙን ታጣቂ ቡድን ሃማስን ሰሞነኛ እንቅስቃሴ በመቅዳት እስራኤል በቡድኑ አንድ ክንፍ ላይ ልትወስድ ላሰበችው እርምጃ የሚያግዝ መረጃ ማቅረብን ታሳቢ አድርጎ የተካሄደ የስለላ ተግባር ነበር ተብሏል።
ሞሳድ በእንስሳት በሚደረጉ ስለላዎች በተደጋጋሚ ይጠረጠራል፤ ከዚህ ቀደም በግብጽ፣ በኢራን ፣ በቱርክ፣ በሱዳን እና በሌሎችም ሃገራት መሰል ስለላዎችን አካሂዷል በሚል ይታማል።
ድርጅቱ ለእስራኤል ደህንነት ስጋቶችን ለመቀነስ በሚል በእርግቦች፣ በሽኮኮ፣ በሻርኮች እና ሽመላ በሚባሉ የአዕዋፍ ዝርያዎች ሃገራት ላይ በተላያዩ ጊዜያት ስለላውን አካሂዷል።
ምንጭ፤ www.thedailybeast.com

ተተርጉሞ የተጫነው፤ በምናለ ብርሃኑ


No comments:

Post a Comment